Thursday, December 4, 2014

በአማርኛ የተተረጎሙ ታላላቅ መጻሕፍት



 ጸሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ
-----
የውጪ ደራሲያን የጻፏቸውን መጻሕፍት ወደ አማርኛ መተርጎሙን ማን እንደጀመረው በትክክል አላውቅም፡፡ ሆኖም የዶ/ር ሳሙኤል ጆንሰን ድርሰት የሆነው “ራሴላስ” በአማርኛ የተተረጎመ የመጀመሪያው የውጪ መጽሐፍ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል፡፡ ከዚያም ክቡር ዶ/ር ከበደ ሚካኤል የትርጉም ስራዎችን በስፋት ተያይዘውት ነበር፡፡ ለምሳሌ ከበደ ሚካኤል የሼክስፒርን ሮሚዮና ጁሌት በ1940ዎቹ ተርጉመውት ነበር፡፡ ሎሬት ጸጋዬ ገብረመድህንም በርካታ የሼክስፒር ስራዎችን በ1960ዎቹ ተርጉመዋል፡፡
  
  የአማርኛ የትርጉም ስራዎች እንደ አሸን የፈሉት ግን “ኩራዝ አሳታሚ ድርጅት” በ1970ዎቹ ከተቋቋመ በኋላ ነው፡፡ በዚያ ዘመን በተለይም ዘመን አይሽሬ የሚባሉ ታላላቅ የስነ-ጽሑፍ ስራዎች በብዛት ወደ አማርኛ ተመልሰዋል፡፡ ኢ-ልቦለድ ከሆኑትም መካከል የካርል ማርክስን “ዳስ ካፒታል”ን ጨምሮ በርከት ያሉ መጻሕፍት ተተርጉመዋል፡፡

በ1980ዎቹ መጀመሪያ ላይ ደግሞ የትርጉም ስራው የዳኒኤላ ስቴልን፣ የሲድኒ ሸልደንንና የአርቪንግ ዋላስን ስራዎች ወደ አማርኛ በመመለሱ ላይ ነበር ያተኮረው፡፡ እስከ 1990ዎቹ መጀመሪያ ድረስ በብዛት ሲተረጎሙ የነበሩት ደግሞ የጃኪ ኮሊንስ ድርሰቶች ናቸው፡፡ አሁን ግን የትርጉም ስራው ቀዝቅዟል፡፡

   ለመሆኑ እስከ ዛሬ ድረስ በአማርኛ የተተረጎሙ ታላላቅ የስነ-ጽሑፍ በረከቶች የትኞቹ ናቸው? ይህንን ጥያቄ መመለስ ይከብዳል፡፡ ቢሆንም የቻልኩትን ያህል ለመዘርዘር እሞክራለሁ፡፡ ታዲያ በዚህ ዝርዝር ውስጥ የተካተቱት በመላው ዓለም ዝነኛ ለመሆን የበቁ ስራዎች ብቻ ናቸው፡፡ ለምሳሌ የነ ዳንኤላ ስቴል፣ ሲድኒ ሸልደንና ጃኪ ኮሊንስ ስራዎች በሀገራችን በብዛት ቢተረጎሙም በዓለም ዙሪያ ያላቸው ተነባቢነት እምብዛም ነው፡፡

    መጻሕፍቱን የምጠራቸው በአማርኛው ርዕሳቸው ነው፡፡ የዋናውን ደራሲ ስም እና የተርጓሚውንም ስም እጠቅሳለሁ፡፡ በአንዳንድ የተርጓሚዎችን ማንነት ለማወቅ ስቸገር ግን ዝም ብዬ አልፌአቸዋለሁ፡፡
(ማስታወሻ፡ ይህ ዝርዝር የሃይማኖት መጻሕፍትን አይመለከትም)፡፡

==== ዘመን አይሽሬ የልብወለድ መጻሕፍት (Classical Fictions)===

1.      “ነገም ሌላ ቀን ነው”፣ ደራሲ ማርጋሬት ሚሼል፣ ተርጓሚ ነቢይ መኮንን
2.     “መከረኞች”፣ ደራሲ ቪክቶር ሁጎ፣ ተርጓሚ ሳህለ ሥላሤ ብርሃነማሪያም (በህይወቴ ያነበብኩት ምርጥ የአማርኛ ትርጉም ስራ ይህኛው ነው)፡፡
3.     “የሁለት ከተሞች ወግ”፣ ደራሲ ቻርለስ ዲከንስ፣ ተርጓሚ ሳህለ ሥላሤ ብርሃነማሪያም
4.     “የአገር ልጅ”፣ ደራሲ ሪቻርድ ራይት፣ ተርጓሚ ሳህለሥላሤ ብርሃነማሪያም
5.     “ዶን ኪኾቴ”፣ ደራሲ ሚጉኤል ሰርቫንቴስ፣ ተርጓሚ ዳምጤ አሰማኽኝ (ሌላ ሰው ይህንኑ መጽሐፍ “ዶን ኪሾት” በሚል ርዕስ ተርጉሞት ነበር፤ ይሁን እንጂ ያኛው ትርጉም ብዙም አይጥምም)
6.     “ሳቤላ”፣ ደራሲ ሄንሪ ውድ፣ ተርጓሚ ሀይለ ሥላሤ መሓሪ
7.     “እናት”፣ ደራሲ ማክሲም ጎርኪ
8.     “ዩኒቨርሲቲዎቼ”፣ ደራሲ ማክሲም ጎርኪ
9.     “አጎቴ ቫኒያ”፣ አንቶን ቼኾቭ
10.    “ሼርሎክ ሆምዝ”፣ ደራሲ ሰር አርተር ኮናን ዶይል፣ ተርጓሚ ዳኛቸው ተፈራ
11.     “ውቢት”፣ ደራሲ አልቤርቶ ሞራቪያ፣ ትርጉም ሺፈራው ጂሶ
12.    የካፒቴኑ ሴት ልጅ፡ ደራሲ አሌክሳንደር ፑሽኪን
13.    “ካፖርቱ”፣ ደራሲ ኒኮላይ ጎጎል
14.    እንደ ሰው በምድር እንደ አሳ በባህር፡ ደራሲ ኒኮላይ ጎጎል
15.    “ወንጀልና ቅጣት”፣ ደራሲ ፊዮዶር ዶስቶየቪስኪ፣ ተርጓሚ ካሳ ገብረህይወት እና ፋንቱ ሳህሌ
16.    “እንዲህ ሆነላችሁ”፣ ደራሲ ሩድያርድ ኪፕሊንግ፣ ተርጓሚ አረፈዐይኔ ሐጎስ
17.    “አሳረኛው”፣ ደራሲ ነጂብ ማህፉዝ፣ ተርጓሚ አማረ ማሞ
18.    ሌባውና ውሾቹ፣ ደራሲ ነጂብ ማሕፉዝ፤
19.    “እፎይታ”፣ ደራሲ አሌክሳንደር ዱማስ ፔሬ፣
20.   “ጃኩሊን”፣ ደራሲ አጋታ ክሪስቲ
21.    “የደም ጎጆ”፣ ደራሲ አጋታ ክሪስቲ፣ ተርጓሚ ሌ/ኮሎኔል ጌታቸው መኮንን ሐሰን
22.   “አና ካሬኒና”፣ ደራሲ ሊዮ ቶልስቶይ፣
23.    “ሽማግሌውና ባህሩ”፣ ደራሲ አርነስት ሄሚንግዌይ፣
24.    “እሪ በይ አገሬ”፣ ደራሲ አላን ፒተን፣ ተርጓሚ አማረ ማሞ
25.    “የስዕሉ ሚስጢር”፣ ደራሲ ኦስካር ዋይልድ፣ ተርጓሚ ፋሲል ተካልኝ አደሬ
26.   “ጠልፎ በኪሴ”፣ ደራሲ ተውፊቅ አልሃኪም፣ ተርጓሚ መንግሥቱ ለማ
27.   “የእንስሳት እድር”፣ ደራሲ ጆርጅ ኦርዌል፣ ተርጓሚ ለማ ፈይሳ

===ዓለም አቀፍ የተረት መጻሕፍት===

1.       “ተረበኛው ነስሩዲን”፣ ደራሲ ኢድሪስ ሻህ፣ ተርጓሚ አማረ ማሞ
2.     “አንድ ሺህ አንድ ሌሊት”፣ ወደ እንግሊዝኛ ተርጓሚ ሪቻርድ በርተን፣ ወደ አማርኛ ተርጓሚ ተፈሪ ገዳሙ
3.     “ጥንቸሉ ጴጥሮስ፣ ደራሲ ቤትሪክስ ፖተር፣
4.     “የኤዞፕ ተረቶች”፣ ደራሲ ኤዞፕ፣ ተርጓሚ አማረ ማሞ
5.     “የግሪም ተረቶች”፣ ደራሲ የግሪም ወንድማማቾች፣ ተርጓሚ ዓለም እሸቱ

====ዘመን አይሽሬ የግጥም ስብስቦች====

1.      “ነቢዩ”፣ ገጣሚ ካህሊል ጂብራን
2.     የአሌክሳንደር ፑሽኪን ግጥሞች፣ ተርጓሚ አያልነህ ሙላቱ
3.     የዑመር ኸያም ሩባያቶች፣ ወደ እንግሊዝኛ ትርጉም በኤድዋርድ ፊዝጂራልድ፣ ወደ አማርኛ ተርጓሚ ተስፋዬ ገሠሠ
4.     ኢሊያድ እና ኦዲሴይ፣ ገጣሚ ሆሜር፣ ተርጓሚ ታደለ ገድሌ

==== ወቅታዊ የሽያጭ ሪከርድ ያስመዘገቡ መጻሕፍት (Best Sellers)====
1.      “የጡት አባት”፣ ደራሲ ማሪዮ ፑዞ
2.     “የሚስጢሩ ቁልፍ”፣ ደራሲ ኬን ፎሌት፣ ተርጓሚ ኤፍሬም እንዳለ
3.     “የዳቪንቺ ኮድ”፣ ደራሲ ዳን ብራውን፣
4.     “ሃሪ ፖተር እና የፈላስፋው ጠጠር”፣ ደራሲ ጄ.ኬ. ሬውሊንግስ፣
5.      “ሳዳም ሑሴን እና የባህረ ሰላጤው ቀውስ”፣ ደራሲ ባሪ ሩቢን፣
6.     “ሞገድ”፣ ደራሲ አርቪንግ ዋላስ፣
7.     “የኦዴሳ ፋይል”፣ ደራሲ ፍሬድሪክ ፎርስይዝ፣ ተርጓሚ ማሞ ውድነህ
8.     “ዘጠና ደቂቃ በኢንቴቤ”፣ ተርጓሚ ማሞ ውድነህ
9.     አስራ አንዱ ውልዶች፣ ደራሲ ጄፍሪ አርቸር፤

=== ዓለም አቀፍ ተጽእኖን የፈጠሩ የፖለቲካና የፍልስፍና መጻሕፍት===

1.      “ካፒታል”፣ ደራሲ ካርል ማርክስ፣ (በቡድን ነው የተተረጎመው፡፡ የጓድ መንግሥቱ ኃይለማሪያም አስተርጓሚ የነበሩት አቶ ግርማ በሻህ እና ደራሲ ስብሐት ገብረ እግዚአብሄር በተርጓሚዎቹ ውስጥ ይገኛሉ)፡፡
2.     “የኮሚኒስት ፓርቲ ማኒፌስቶ”፣ ደራሲ ካርል ማርክስና ፍሬድሪክ ኤንግልስ፣ ተርጓሚ “ኩራዝ አሳታሚ ድርጅት”
3.     “የሌኒን ምርጥ ስራዎች”፣ ደራሲ ቪላድሚር ሌኒን፣ ተርጓሚ “ኩራዝ”

=== ታዋቂ ግለ-ታሪኮችና የታሪክ ማስታወሻዎች===

4.     “ትንሿ መሬት”፣ ደራሲ ሊዮኒድ ብሬዥኔቭ፣ ተርጓሚ “ፕሮግሬስ የመጻሕፍት ማዘጋጃ ድርጅት”
5.     “የኦሽዊትዝ ሚስጥር”
6.     የአና ማስታወሻ፤ ደራሲ “አና ፍራንክ”፣ ተርጓሚ “አዶኒስ”
7.     “ፓፒዮ”፣ ደራሲ ሄንሪ ቻሬሬ
8.     “በረመዳን ዋዜማ”፣ ደራሲ ሙሐመድ ሀይከል፣ ተርጓሚ ማሞ ውድነህ
9.     “የጽናት አብነት”፣ ሄለን ከለር

=== ሌሎች ኢ-ልብወለድ መጻሕፍት===
1.      “ጠብታ ማር”፣ ደራሲ ዴል ካርኒጌ፣ ተርጓሚ ባሴ ሀብቴና ደምሴ ጽጌ



1 comment: