Tuesday, December 9, 2014

ኮ/ል መንግሥቱ ኃይለማሪያም እና የሀይሌ ፊዳ ሞት




አፈንዲ ሙተቂ
------

ዶ/ር ሃይሌ ፊዳ በፎቶግራፉ ላይ የምትመለከቱት ነው፡፡ ፎቶውን የሰጡን አንጋፋው ደራሲ አበራ ለማ ናቸው፡፡ ጋሼ አበራን እያመሰገንን በሃይሌ ፊዳ አሟሟት ዙሪያ የተጠናቀረውን ይህንን ጽሑፍ ጀባ ብለናችኋል፡፡

                                                                          *****
ኮ/ል መንግሥቱ ሀይለማሪያም “ሀይሌ ፊዳ የተገደለው በገበሬዎች ነው” ባይ ናቸው፡፡ ከጋዜጠኛና ደራሲ ገነት አየለ ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ የሀይሌ ፊዳን ሞት እንዲህ በማለት አስረድተዋል፡፡

ገነት፡ ሀይሌ ፊዳስ? በነሐሴ 1970 ተይዞ ከአንድ ዓመት በኋላ ነገር ከበረደ፤ ሁሉ ነገር ከተረጋጋ በኋላ ነው የተገደለው፡፡ በዚያን ጊዜ የኃይሌ ፊዳ በህይወት መኖር መንግሥትን ያሰጋ ነበር?

መንግሥቱ፡ መቼ ነው የሞተው ሀይሌ ፊዳ?

ገነት፡ በሀምሌ 1971 ነው::

መንግሥቱ፡ ማነው የገደለው?

ገነት፡ እኔ ምን አውቃለሁ? አስከሬኑ ከቀድሞው የራስ አስራተ ካሣ ግቢ ነው ተቆፍሮ የወጣው፡፡ እዚያ ነው የተገኘው፡፡

መንግሥቱ፡ ሀይሌ?

ገነት፡ አዎን! ሀይሌ ፊዳ፡

መንግሥቱ፡ እዚያ ምን ሲሰራ?

ገነት፡ እዚያ ነው አስከሬኑ የተገኘው፡፡

መንግሥቱ፡ እኔ አላውቅም፡፡

ገነት፡ መሞቱንም አያውቁም? እርሱንም እዚህ ከመጡ በኋላ ነው የሰሙት?

መንግሥቱ፡ መኢሶኖች እኮ ጥለውን ሄደዋል፡፡ የሶማሊያ ጥቃት አይሎ ሲመጣ የሻዕቢያዎች ጎራ ስለጠነከረ ከዚህ ከደከመ መንግሥት ጋር ምን እንሰራለን ብለው አይደል እንዴ ጥለው የነጎዱት? በነሱ ሃሳብ እኛ በመዳከማችን ወደፊት ከኛ ጋር በመቀጠል የስልጣን ጥማታቸውን የሚያረኩበት መንገድ ስለማይኖር ልዩ ልዩ ምክንያት ሲያቀርቡ ቆይተው በመጨረሻ ፈርጥጠዋል፡፡ በዚህን ጊዜ እነ መስፍን ካሱ ወደ ሲዳሞ፡ እነ ሀይሌ ፊዳ ወደ ወለጋ ሲሄዱ አግኝቶ ገበሬ ነው የከሰከሳቸው፡፡

ገነት፡ እዚያ ነው የተገደሉት?

መንግሥቱ፡ በሙሉ!

(ገነት አየለ አንበሴ፡ የሌተና ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማሪያም ትዝታዎች፡ 1984፣ ገጽ 207-208)
                                                                          *****
ሊቀመንበር መንግሥቱ “የሀይሌ ፊዳን መሞት ሰው ነው የነገረኝ” ነው የሚሉት፡፡ ነገር ግን ሀይሌ በነሐሴ 1969 ከተያዘ በኋላ በደርግ ምርመራ ክፍል ሲሰቃይ ቆይቶ እንደተገደለ ይታወቃል፡፡ ለዚህ ማስረጃ የሆነውንና ሀይሌ ከመሞቱ በፊት የሰጠውን ባለ 36 ገጽ የምርመራ ቃል በልዩ ልዩ መንገዶች ታትሞ አንብበነዋል፡፡ ከሀይሌ ጋር በአንድ ክፍል ታስረው የነበሩ ጓዶችም ሀይሌ በዚያ ወር እንደተገደለ ተናግረዋል፡፡ የደርግ የቅርብ ሰው የነበሩት አቶ ገስጥ ተጫኔ (ዘነበ ፈለቀ) “ነበር” በሚል ርዕስ በጻፉት ባለሁለት ቅጽ መጽሐፍ የምርመራ ቃሉን ከማተማቸውም በላይ ሀይሌ ከሱሉልታ ኬላ ተይዞ ወደ ደርግ ጽ/ቤት በመጣበት ወቅት በብሄራዊ ቤተመንግሥት እንዳዩት መስክረዋል፡፡
    

  በዚህም መሰረት “ሊቀመንበር መንግሥቱ ሀይሌን በእርግጥ ገድለውታል ወይ?” የሚለው ጥያቄ ለአሁኑ ዘመን አይሰራም፡፡ “መንግሥቱ ሀይሌን ለምን ገደሉት?” የሚለው ግን አሁንም ያከራክራል፡፡ ገነት አየለ እንደገለጸችው ሀይሌ በተገደለበት ወቅት ነገሮች ሁሉ በጣም በርደዋል፡፡ የሶማሊያ ወራሪዎች ከምስራቅ ኢትዮጵያ ከተባረሩ አንድ ዓመት አልፎአቸዋል፡፡  ሻዕቢያና ጀብሃ በሁለተኛው አብዮታዊ ሰራዊት ክፉኛ ተደቁሰው ወደ ሱዳንና ወደ ሳሕል በረሃ ገብተዋል፡፡ ከነዚህ ሁለት ክስተቶች ቀደም ብሎም ሀገር ያተራመሰውና ሺዎችን የቀሰፈው የቀይ ሽብር ዘመቻ ደርግ በሚፈልገው መልኩ ተጠናቋል፡፡ አብዮታዊው መንግሥት ከዚያ በፊት ያላየው ሰላምና እርጋታ በሀገሪቱና በሁሉም የስራ መስኮች ሰፍኗል፡፡ ታዲያ በዚህ ሰላማዊ ወቅት ሀይሌ ፊዳን ማስገደሉ ለምን አስፈለገ?
  
  
በርካታ ተመልካቾች የየራሳቸውን ግምት አስቀምጠዋል፡፡ አንዳንዶች ነገሩን ከቂም በቀል ጋር ያያይዙታል፡፡ “መንግሥቱ አንድ ቀን የገላመጠውን እንኳ የማይምር ቂመኛ ነው” -ይላሉ እነዚህ ወገኖች፡፡ የተወሰኑት ደግሞ መንግሥቱ በችሎታና በእውቀት ከርሱ የሚበልጥ ሰው ከታየው ወደፊት ስልጣኔን ይነጥቀኛል በሚል እንደሚያስገድለው ያወሳሉ፡፡ እነዚህኛዎቹ ክርክራቸውን ሲቀጥሉ “መንግሥቱ ሀይለማሪያም ሀይሌ ከእስር ቢለቀቅ ወይም ቢያመልጥ የራሱን ቡድን አደራጅቶ ወይ አንዱን ጄኔራል ተጠግቶ ከስልጣኔ ሊያሽቀነጥረኝ ይችላል” የሚል ፍራቻ ነበረው” ባይ ናቸው፡፡
     

   ከሁለቱ ወገኖች የሚለይ አስተያየት የሚሰጡ ጸሐፊያንና የታሪክ ሰዎችም አሉ፡፡ እነዚህኛዎቹ እንደሚሉት ኮሎኔል መንግሥቱ ሃይለማሪያም በሀይሌ ጉዳይ ላይ የሞት ውሳኔ ያሳለፉት እርሳቸውን ያስደነገጠ አንድ አደገኛ ክስተት ስለተፈጠረ ነው፡፡ እስቲ ታሪኩን አብረን እንየው፡፡
                                                                          *****

     ሊ/ር መንግሥቱ ለጉብኝት ወደ ኩባ ይጋበዛል፡፡ ከጓድ ፊደል ካስትሮ ጋር ጉብኝትና ስብሰባውን ማካሄድ ይጀምራል፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ግን ለስራ ጉዳይ ወደ ውጪ ሀገር በመሄዱ ህይወቱ ለጥቂት የተረፈችው የመኢሶኑ ዶ/ር ነገደ ጎበዜ አዲስ አበባ መግባቱ ይነገረዋል፡፡ “እንዴት መጣ?” ብሎ ቢጠይቅ “የደቡብ የመንን ፓስፖርት ይዞ፤ ከደቡብ የመን ልዑካን ጋር ተቀላቅሎ” ሆነ መልሱ! (ደቡብ የመን አሁን ከሰሜን ጋር ተዋህዳለች)፡፡ “ዶ/ር ነገደ ተይዟል ወይ?” ብሎ ሲጠይቅ አለመያዙ ተነገረው፡፡ ያለበትን ቦታ ጠይቆ የተሰጠውን መልስ ሲሰማ ደግሞ ሊ/ር መንግሥቱ በድንጋጤ ፈዝዞ ቀረ!
                                                                          *****
 በርግጥ ዶ/ር ነገደ አዲስ አበባ ገብቷል፡፡ ነገር ግን መጥፎ አጋጣሚ ሆኖ ድሮ ከሚያውቀው የኤርፖርት ደህንነት ሃላፊ ጋር አይን ለአይን ተገጣጠመ፡፡ ደህንነቱ ነገሩን ወዲያኑ ለደርጎች አስታወቀ፡፡ ደርጎችም ነገደ ጎበዜን ለመያዝ ተንቀሳቀሱ፡፡ ሆኖም ዶ/ሩ ኩባ ኤምባሲ ገብቶ ተደበቀ፡፡ ሁኔታው ለጓድ ፊደል ካስትሮ ሲነገራቸው ካስትሮ አማላጅ ሆኑና በነገሩ ውስጥ ገቡ፡፡ በርሳቸው ተማጽኖም ዶ/ር ነገደ ከኤምባሲው ወጥቶ ወደ አውሮጳ ተመለሰ፡፡
  

   ይህ ድርጊት የተከሰተው የሶማሊያ ወረራ ካበቃ ከጥቂት ወራት በኋላ ነበር፡፡ ደርጎች ነገሩን እንደ ኩዴታ ነው የወሰዱት፡፡ ለዚህም ነው በውስጣቸው ከፍተኛ መሸበር የተፈጠረው፡፡ እርግጥ ሀገራቱ ኩዴታ እናድርግ ቢሉ የማስፈጸም አቅሙ ነበራቸው፡፡ በወቅቱ የ"ሶማሊያን ወረራ ለመቀልበስ በተደረገው ዘመቻ አብዮታዊ አጋር ሆኖ የመጣው የኩባ ሀያ ሺ ሜካናይዝድ ጦርና የየመን ሁለት ሺህ መድፈኛ ጦር ኢትዮጵያ ውስጥ ስለነበሩ እነርሱን ይዘው አንድ ነገር ማድረግ ይችሉ ነበር ተብሎ ይገመታል፡፡ የዘመኑ ሀያል ሶሻሊስት ሀገር የሆነችውን ሶቪየት ህብረትንም ለእርዳታ ቢጠሯት “በጄ” ከማለት የምትመለስ አይሆንም-ከመንግሥቱ ይልቅ ኩባና ደቡብ የመን ይበልጡባታልና፡፡ ሆኖም የዶ/ር ነገደን መምጣት ብቻ በማየት “ኩዴታ” ተጠንስሷል ለማለት ይከብዳል፡፡


     ሊ/ር መንግሥቱ በዚህ መረጃ ላይ በመመርኮዝ “ኩዴታ” እንደታቀደባቸው አሰመሩበት፡፡ ሀገራቱ ፈጸሙብኝ ላሉት በደል ደግሞ ቀጥተኛ ምላሽ ከበዳቸው -ምክንያቱም የክፉ ቀን ወዳጆች ናቸውና፡፡ በሌላ በኩል ግን ሊቀመንበሩ ቁጭታቸውን መዋጥ አቃታቸው፡፡    ለምን ቢባል እንኳንስ እንዲህ ዓይነቱን ምልክት አግኝተው ይቅርና በጥርጣሬ ብቻ ብዙዎችን ቀስፈዋልና፡፡ የቀይ ሽብሩ ትርዒት ሳይደመር የተፈጁትን ሰዎች ቤት ይቁጠረው፡፡ ሌ/ኮ/ አጥናፉ አባተን “ለሀገራችን ሶሻሊዝም አይጠቅማትም፤ እንደ ዩጎዝላቪያ የቅይጥ ኢኮኖሚ መርህ መከተል አለብን” በማለታቸው ብቻ አስገድለዋቸዋል፡፡ “ለኤርትራ ጥያቄ ሰላማዊ መፍትሔ ያስፈልጋል” ያሉ በርካታ ጓዶቻቸውን አስረሽነዋል፡፡ አቡነ ቴዎፍሎስ፣ ቄስ ጉዲና ቱምሳ እና ሼኽ ሰይድ ቡደላ (የአብሬት ሼኽ) የመሳሰሉ የሀይማኖት አባቶች ያለ አንዳች ምክንያት ተገድለዋል፡፡ ከዚህ አንጻርም ለዶ/ር ነገደ ጎበዜ ድፍረት የሚሰጡት ቅጣት ከፍተኛ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ግን ዶ/ር ነገደ አልተያዘም፡፡ ስለዚህ ቁጭቱ በምን ይውጣላቸው?


    እንግዲህ በአንዳንዶች እምነት ዶ/ር ሀይሌ ፊዳ የተገደለው በዚህ እርግጠኛነቱ ባልታወቀ የዶ/ር ነገደ ጎበዜ “ኩዴታ” ጦስ ነው፡፡ ኩባና የመንን መበቀል ሲያቅታቸው ቁጭታቸውን በግቢአቸው ባጎሩት እስረኛ ላይ ተወጡት፡፡ ሀይሌን በአንድ ቀዝቃዛ ምሽት አሰናበቱት፡፡
                                                                          *****

     በቅርብ ጊዜ የተገኙ መረጃዎች ግን ከላይ የቀረበውን ታሪክ ዋጋ ቢስ አድርገውታል፡፡ እነዚህ መረጃዎች እንደሚሉት ዶ/ር ነገደ ጎበዜ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው የመጡት በሊቀመንበር መንግሥቱ እውቅና ነው፡፡ ለምሳሌ ዶ/ር መረራ ጉዲና በቅርቡ ባሳተሙት መጽሓፋቸው “ነገደ ጎበዜ በመንግሥቱና በኩባዊያን እውቅና መምጣቱን ነግሮኛል” በማለት ጽፈዋል፡፡ ከአሜሪካ የስለላ ምንጮች የተገኘው መረጃም ይህንኑ ያረጋግጣል፡፡ ስለዚህ ደርጎች “መፈንቅለ መንግሥት ሊካሄድ ነበር” እያሉ ወከባ ይፈጥሩ የነበረው ህዝቡንና የተቃዋሚውን ክፍል ለማደናገርና የበለጠ ጸጥ ለማድረግ ነው ማለት ነው፡፡ የሀይሌ ፊዳ ግድያም ከመፈንቅለ መንግሥቱ ጋር አንዳች ግንኙነት አልነበረውም፡፡

  
     በአንጻሩ ደግሞ ሀይሌ ፊዳ የተገደለበት ሀምሌ 1971 በውል ሊመረመር የሚገባው የታሪክ ወቅት ሆኖ ሳለ ምሁራን በጥልቀት ሳያስሱት መቅረታቸው ይገርማል፡፡ ይህ ወር መንግሥቱ ከቀይ ሽብርና ነጭ ሽብር የተረፉ በርካታ ተቃዋሚዎቹን፣ አማካሪዎቹንና ታዋቂ ግለሰቦችን በድብቅ የገደለበት ጊዜ ነበር፡፡ እነ አቡነ ቴዎፍሎስን ጨምሮ የኢህአፓው ብርሀነ መስቀል ረዳ፣ የመኢሶኖቹ ከበደ መንገሻ፣ ንግሥት አዳነ፣ ደስታ ታደሰ፣ መስፍን ካሱ ወዘተ… በዚሁ ጊዜ ነበር የተገደሉት፡፡ “የማዕከል” ጥያቄ ደርጎችን ያናቆረው በዚህ ጊዜ ነበር፡፡ ኢማሌድህ የሚባለውን የማርክሲስቶች ህብረት ከመሰረቱት አምስት ድርጅቶች (አብዮታዊ ሰደድ፣ መኢሶን፣ ወዝሊግ፣ ኢጭአት እና ማሌሪድ) መካከል መንግሥቱ ከሚመሩት “ሰደድ” ጋር በመድረኩ ላይ የቀረው የማሌሪድ መሪ ተስፋዬ መኮንን የታሰረውና የማሌሪድ ግብአተ ሞትም የተፈጸመውም በዚህ ወር ነበር፡፡ ስለዚህ ያ ታሪካዊ ወቅት የምሁራን እይታ ሊያርፍበት ይገባል፡፡
------
አፈንዲ ሙተቂ
ጥቅምት 21/2006

1 comment:

  1. Dear Fikuru, Please can you pass this message to the writer from Zeg Fanta.

    thank you,ttsega.

    On Friday, December 19, 2014 6:32 PM, Zeg Fanta wrote:


    Selam Take,

    If you have any contact at all, the philosophy of Wallelign on Gossawoch had completely a different purpose and the reorganization of regions as he clearly put was for the formation of the socialist state, not the kind of form of government run by the junta or bandits many times worse than the monarchy and worse by many accounts than Derg. The writer is write that many individuals and organizations are trying to fit his ideas to suit their political goals. He shares the blame in his interpretations of his philosophical writing and their purposes. We can not see them in light of events that have taken place since his death. Some have happened he never imagined, some have happened perhaps as he imagined them. For instance, it is fair to say that he might have imagined the collapse of the monarch, and it did in ways expected by some, unexpected by many others. I do not believe Wallelign imagined the governments that followed. He would have turned pro HIM if he had known Derg and if he had heard the song of Toshome, let alone see in his wide awake eyes the regime in Ethiopia. We can stipulate that much.

    Take, if you ever have contact with the writer, please tell him to read my article and listen to the interview I gave on SBS.

    I had decided not to say any more feeling that I have done enough for now on the issues of Wallelign.
    The human nature is pushing me to the tips of things. What the heck! Here it goes once again and as always, on Wallelign.Funny, just yesterday, it was on Tecola on the other side of the spectrum so to speak about the politics-soups of Ethiopia!

    Peace
    Zeg Fanta
    zegfantam@aol.com

    ReplyDelete