Thursday, January 9, 2020

እውነታውን የረሳው መንግስት እና ውሉን የሳተው ተሐድሶ


ጸሐፊ: አፈንዲ ሙተቂ
-----
የዶክተር አቢይ መንግስት የኢትዮጵያ ህዝቦች በከፈሉት ከባድ መስዋእነት ወደ ስልጣን ከመጣ አመት ከመንፈቅ ሆኖታል:: ይህ መንግስት በመጋቢት 2010 መጨረሻ ላይ ስልጣን ሲይዝ በርካቶች "የኢትዮጵያ ህዝቦች ለብዙ ዘመናት ሲጠይቋቸው የነበሩት ብሄራዊ የማንነት ጥያቄዎች ምላሽ የሚያገኙበትን መሠረት ይጥላል፣ የተዳከመውን የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ያነቃቃል፣ በተለያዩ ብሄሮችና ማኅበረሰቦች መካከል ብሄራዊ መግባባትን ፈጥሮ የሀገሪቷን አንድነት ከአደጋ ይታደጋል፣ በታሪካችን የመጀመሪያውን ዲሞክራሲያዊ ምርጫ የምናካሄድበት ጊዜ ደርሷል" በማለት ተስፋ ጥለውበት ነበር። ነገር ግን የሀገሪቷን ሰላምና ደህንነት ማስጠበቅ እንኳ የማይችልና የተጀመሩትን ፕሮጀክቶች ማስፈፀም የተሳነው ደካማ መንግስት ሆኖ ተገኝቷል።

የአሁኑ መሪ ወደ ስልጣን ከመጣ ከሃያ አንድ ወር በኋላ እንኳ ራሱን ከማስተዋወቅና የራሱን ስብእና ለመገንባት ከሚሰራቸው የህዝብ ግንኙነት ስራዎች መውጣት አልቻለም። ዛሬም “መደመር” የዘመኑ በሽታችን ፍቱን መድኃኒት ነው እየተባለ ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ “ብልጽግና” የማይደፈር የማይገሰስ የዘመናት ሀብት ነው እየተባለልን ነው፡፡
---
የዚህ መንግስት ቀዳሚው ችግር እንዴት ወደ ስልጣን እንደመጣ መዘንጋቱ (ወይንም ሆን ብሎ መርሳቱ) ነው። የአሁኑ የለውጥ ሂደት የመጣው በህዝብ ትግልና መስዋእትነት ነው። ትግሉ የተጀመረው ትናንት ሳይሆን ከሃምሳ ዓመታት በፊት ነው። በዚህ ሂደትም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ውድ ህይወታቸውን ሰውተዋል።

የዶክተር አቢይ መንግስት ግን ትግሉ የዛሬ ሁለት ዓመት የተጀመረ ይመስለዋል። በትግሉ የተሳተፉትም ጠቅላይ ሚኒስትሩና ጓዶቹ ብቻ እንደሆኑ አድርጎ ደምድሟል። ለዚህም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩና ጓዶቹ በተደጋጋሚ ጊዜያት "የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎችና የዲያስፖራ አክቲቪስቶች ምህረት አድርገንላቸው ወደ ሀገር እንዲገቡ ከፈቀድንላቸው በኋላ እየበጠበጡን ነው" በማለት የሚናገሩት። እኝህ ሰው ክቡር አቶ ለማ መገርሳ የኦህዴድ ሊቀመንበርነታቸውን ባይተውላቸው ኖሮ ለኢህአዴግ ሊቀመንበርነት ምርጫ የማይቀርቡ መሆናቸውን እንኳ ረስተውታል (ለማ መገርሳ ያኔ ወንበራቸውን ለቀውላቸው በአሁኑ ወቅት ከጨዋታ ውጪ ሆነዋል)

እርግጥ ጠቅላዩና ጓዶቹ የነበሩበት "ቲም ለማ" በወያኔ የመጨረሻ ዓመታት በኢህአዴግ ውስጥ ያካሄዱት ትግል ለድሉ አስተዋጽኦ ነበረው። ለዚህም እጅግ በጣም እናመሰግናቸዋለን። ነገር ግን በፓርቲው ውስጥ የፈነዳው ትግል ከፓርቲው ውጪ ሲካሄድ በነበረው ትግል ባይደገፍ ኖሮ ቲም ለማ የትም አይደርስም ነበር። ለምሳሌ የወያኔ ገዲም ጄኔራሎች አብዲ ኢሌን ቆስቁሰው በሚሊዮን የሚቆጠር ኦሮሞ ባፈናቀሉበት ወቅት ሴራውን በጥልቀት አስረድቶ ህዝቡ ከቲም ለማ ጋር እንዲቆም የቀሰቀሰው ጀዋር መሐመድ አልነበረምን? ቄሮ ቲም ለማን ደግፎ ህይወቱን ሲሰዋ አልነበረንም? ሌሎች የሀገራችን ማኅረሰቦች፣ አክቲቪስቶችና ፖለቲከኞች አብዲ ኢሌ በኦሮሞዎች ላይ ጦርነት ባወጀበት ወቅት ከኦሮሞ ወገናቸው ጋር ወግነው አልታገሉምን? አዎን! ቲም ለማ ያንን ሁሉ ድጋፍ ባያገኝ ኖሮ የፌዴራሉን ስልጣን የያዘውን ወያኔን እየተገዳደረ በትግሉ መቀጠል እንደማይችል እርግጠኛ ሆነን እንናገራለን።

የዶክተር ዐቢይ መንግስት ሁለተኛ ችግር የኢትዮጵያ ህዝቦች የሚፈልጓቸውን ነገሮች እና የታገሉላቸውን ጥያቄዎች በትክክል አለማወቁ (መዘንጋቱ) ነው። ከመሠረታዊው ነገር እንጀምርና ህዝቡ ከባድ የሆነ የኑሮ ውድነት እየጠለዘው ነው። የመሠረታዊ ሸቀጦች፣ የምግብና የአልባሳት ዋጋ በየዕለቱ እየናረ ነው። በመሆኑም ይህ መንግስት በትኩረት ሊሰራባቸው ከሚገባቸው ችግሮች አንዱ ገበያውን ማረጋጋት ሊሆን በተገባ ነበር። እርሱ ግን የሚታዩ ችግሮችን ትቶ "የከፍታ ቀን፣ መደመር፣ የመነቃቃት ቀን" እያለ የማይጨበጡ ሃሳቦችን በህዝቡ ውስጥ ለማስረጽ ሲደክም ይውላል።
በሌላ በኩል ህዝቡ በወያኔ ላይ ዱላውን ሰንዝሮ የታገለው ከዚህ ቀደም ባደረጋቸው ትግሎች የተጎናፀፋቸውን ድሎች ለማጣት እንዳልሆነ የአሁኑ መንግስት ዘንግቷል። ህዝቡ ወያኔን የታገለው ከተፈጥሮአዊ መብቶቹ መካከል ወያኔ እየሸራረፈ ያስቀራቸውን ለመጎናጸፍ እንጂ በወያኔ ዘመን የተመለሱለትን ጥያቄዎች አፈር ድሜ ለማስበላት አልነበረም።
ለምሳሌ ያህል በቅርቡ ሀገሪቱን ሊያናጋ ደርሶ የነበረውን የቋንቋ ጥያቄ እንውሰድ። ቋንቋን ማወቅ በጣም ጠቃሚ ነው። የእውቀት አማራጮችን የሚያሰፋ ፀጋ ነው። ነገር ግን ከአንድ ህዝብ የተወለዱ ልጆች የሚማሩበትን ቋንቋ መምረጥ የሚችለው ህዝቡ ራሱ ነው። ይህ ዓለም አቀፋዊ መርህ ከመሆኑም ባሻገር ሀገሪቱ በአሁኑ ወቅት በምትመራበት ህገ መንግስት ላይ ሰፍሯል።
የአቢይ መንግስት ግን ለዚህ ዓለም አቀፋዊ መርህ ቦታ ሳይሰጥ በእውርና ደንባራ አማካሪዎቹ እየተመራ የትምህርት ቋንቋን ሊወስንልን ተነሳ። ስድስት ወር ሙሉ "ተው" እየተባለ ቢነገረው አልሰማ አለ። ስለዚህ ህዝቡ የራሱን መብት ለማስከበር ተንቀሳቀሰ (የትምህርት ቋንቋን ለመሰወን የተሰጠው ምክንያት አስቂኝ ከመሆንም አልፎ ዘረኝነት የሚንፀባረቅበትም ነበር። "ኢትዮጵያዊነትን ለማጠናከር ሲባል ህፃናት ከአንደኛ ክፍል ጀምሮ አማርኛን እንደ ተጨማሪ ቋንቋ እንዲማሩ ተወስኗል" ነበር የተባለው። ህፃናቱ በኦሮምኛ ሲማሩ ጠባብነትን ይወርሳሉ ለማለት ነው? ይገርማል!!)
ይህ በጭራሽ የህዝቡ ጥያቄ አይደለም። አልነበረምም። ቋንቋን በተመለከተ ብዙ ኦሮሞዎች ሲያነሱት የነበረው ጥያቄ "አፋን ኦሮሞ የፌዴራል መንግስቱ የስራ ቋንቋ ይሁን" የሚል ነበር። ይህንን ጥያቄ መመለስ ካልተቻለ ሌላ ነገር ሳይነካኩ ጥያቄውን ለመጪው መንግስት ማስተላለፍ ይገባ ነበር።
---
አሁን ከዋናውና እጅግ ወሳኝ ከሆነው ነጥብ ላይ ደርሰናል።
አዎን! የዚህ መንግስት ዋነኛው ችግር ከላይ የተጠቀሱትም አይደለም። የአቢይ መንግስት አቢይ ችግር በህዝብ የተመረጠ መንግስት በምርጫ እስኪተካው ድረስ ሀገሪቷን ወደ ዲሞክራሲያዊ ምዕራፍ ለማሸጋገር ሲባል ከሃይለ ማሪያም ካቢኔ ስልጣን የተረከበ የባለ አደራ መንግስት መሆኑን መዘንጋቱ ነው። ይህ መንግስት የተመረጠው በኢህአዴግ ምክር ቤት ምርጫ እንጂ ኢትዮጵያዊያን በሙሉ በተሳተፉበት ህዝባዊ ምርጫ አይደለም። በመሆኑም የአሁኑ መንግስት ፖሊሲና ህገ መንግስት እንዲቀይር ከየትኛውም አካል mandate አልተሰጠውም።
የዚህ በምርጫ ያልመጣው መንግስት አጣዳፊ ስራዎች መሆን የነበሩባቸው
1 ለዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ የሚያስፈልጉ ተቋማትን መገንባት
2 የሀገሪቷን የዲሞክራሲ ጉዞ ሰንገው የያዙ ህጎችና መሻርና ማሻሻል
3 ፓርቲና መንግስትን ሙሉ በሙሉ መለያየት (ይህ ጉዳይ እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል። እስከ አሁኗ ሰዓት ድረስ በድርጅት /ቤት የተመደቡ ሰዎች እንደ መንግስት ሰራተኛ ደመወዝ እየተከፈላቸው ነው። ፓርቲው በመንግስት መኪናዎች ነው የሚጠቀመው። የህወሓት፣ የኦዴፓ፣ የአዴፓ እና የደኢህዴን ቢሮዎች የሚገኙት በወረዳ አስተዳደር ጽቤቶች ውስጥ ነው። እንዲህ ዓይነቱ አሰራር ከማዕከል እስከ ወረዳ ድረስ ስሩን ሰዷል። ይህ ዐይን ያወጣ ወንጀል ነው)
4 በመንግስት ጫና የተመሠረቱ ህዝባዊ ማህበሮችን (ለምሳሌ ኦልማ፣ አልማ፣ ትልማ፣ የወጣቶች ማህበር፣ የሴቶች ማህበር ወዘተ) ከመንግስት ተፅእኖ ነፃ ማድረግ
5 የዳኝነትና የፍትሕ ስርዓቱን ከመንግስት ተፅእኖ ሙሉ በሙሉ ነፃ ማድረግ
6 የምርጫ ህጉንና የምርጫ ስርዓቱን ማሻሻል (የምርጫ ቦርዱን አባላት ከፓርቲ ንክኪ ነፃ በሆኑ ሰዎች መሙላት)
7 የጸጥታ አካላት ህጋዊነትን በተላበሰ ሁኔታ ህዝቡን እንዲያገለግሉ ማድረግ
8 ያለፉት ስርዓቶች በረጩት መርዝ ሳቢያ በተቋሰሉ ህዝቦች መካከል ትክክለኛ ሂደትን በተከተለ ሁኔታ እርቀ ሰላምን መፍጠር
9 ህዝብን ሲገድሉ፣ ሲዘርፉ፣ ሲገርፉና ሲያፈናቅሉ የኖሩ ባለስልጣናትንና የፀጥታ አካላትን ለፍርድ ማቅረብ
10 ተፎካካሪ ፓርቲዎች በሁሉም ስፍራ፣ ክልል፣ ወረዳና ዞን በነፃነት የሚንቀሳቀሱበትን ሁኔታ ማመቻቸት (የተዘጉ ቢሮዎቻቸውን መክፈት፣ የታሰሩ አባላቶቻቸውን መፍታት)
11 በህዝባዊ ትግሉ ሳቢያ ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ወገኖቻችንን ማቋቋም (በአሁኑ ወቅት በባሌና በሀረርጌ ለረሃብና ለችግር እየተጋለጡ ነው)
12 ህገ ወጥ ታጣቂዎች በክልሎችና ድንበር አቅራቢያ በሚኖሩ ህዝቦች ላይ የሚፈፅሙትን ጥቃት ማስቆም
13 ህገ ወጥ የጦር መሳሪያና የገንዘብ ዝውውርን ማስቆም
14 ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ ለሚሄደው የኑሮ ውድነት አፋጣኝ መፍትሔ ማፈላለግ
15 ወዘተ
----
ባለፈው አንድ ዓመት ከአስር ወር ጊዜ እንዳየነው ከሆነ የዶክተር አቢይ መንግስት እነዚህን ትልልቅ ተግባራት መስራቱን ዘንግቷል። ከእነርሱ ይልቅ ለጊዜያዊ ታይታና ጭብጨባ ብቻ የሚመቹ ስራዎችን ማጧጧፉን ቀጥሎበታል። ውጤቱ ግን የትም የሚያስኬድ አልሆነም። የመነቃቃትና የኩራት ቀንን ማክበር ከፌዝና ከሽሙጥ በቀር ሌላ ትርፍ የሚያስገኝ አልሆነም (ሁሉም ኢትዮጵያዊ የተደሰበት ተግባር ቢኖር የዛፍ ተከላ ዘመቻው ብቻ ነው)

ከዚህ በተቃራኒው መንግስት ለታይና ለጭብጨባ ሲል የሚፈጽማቸው ተግባራት ቀደም ሲል የተገኙ ታላላቅ ለውጦችንና ድሎችን እየቀለበሳቸው ነው። ለምሳሌ ከሁለቱ ታላላቅ ብሄሮቻችን (ኦሮሞና አማራ) በወጡ ታጋዮችና ወጣቶች መካከል ተፈጥሮ የነበረው የትግል አንድነት በዚህ ወቅት ድምጥማጡ ጠፍቷል። በነሐሴ 2010 መጀመሪያ ላይ OMN በሚሊኒየም አዳራሽ ባዘጋጀው ዝግጅት ላይ የተገኙት ተወዳጁ አቶ ንጉሡ ጥላሁን ንግግር ሲያደርጉ ህዝቡ "ይደገም! ይደገም! ይደገም" እያለ ነበር ንግግራቸውን የተከታተለው። አሁን ግን ሁሉ ተረት ሆኖ ቀርቷል።

ወገኖቼ! እስቲ ሁለትና ሶስት ጊዜ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችን እያፈረሱ ማዋቀር ምን ይባላል? የአዲስ አበባ የወንዞች ተፋሰስ ግንባታ የሚባል አቅምን ያላገናዘበ ፕሮጀክት መወጠንስ ፋይዳው ምንድነው? ለዚህ ፕሮጀክት ገንዘብ ለማሰባሰብ ተብሎ የሚሊዮን ብር የእራት ስነ ስርዓት የሚባል ከሚዲያ ፍጆታ የማያልፍ fantasy ዝግጅት ማዘጋጀትስ ትርጉሙ ምንድነው? "ኦነግን ትጥቅ ማስፈታት ቀዳሚ ስራዬ ነው" እያሉ ሽማግሌዎች ያስቀመጡትን ስትራቴጂ ሳይቀበሉ በጎኑ የጉልበተኝነት ዘዴ በማወጅ በጉዳዩ ላይ ከአንድ ዓመት በላይ መፍጀትስ? የማስተር ፕላኑ ጣጣ ሳይፈታ የኮዬ ፈጬ ኮንዶሚኒየምን ለማከፋፈል መሞከርስ? የድንበርና የማንነት ኮሚሽን የተባለ አጨቃጫቂ መስሪያ ቤት አቋቁሞ ለንትርክ ህዝቡን መጋበዝስ? ህዝቡ ጥያቄ ሳያቀርብ “በሁሉም ትምህርት ቤቶች አማርኛ ከአንደኛ ክፍል ጀምሮ እንደ መደበኛ ትምህርት ይሰጣል” የሚል ፍኖተ ካርታ በስራ ላይ መነሳትስ? ተቃዋሚ ፓርቲዎች ራሳቸውን ችለው በህዝቡ ውስጥ በመንቀሳቀስ መዋቅራቸውን እንዲያደራጁ እንደመደገፍ በየጊዜው ከፓርቲዎች ጋር ኮንፈረንስ መቀመጥስ? አንዳንድ ፓርቲዎችንና መሪዎቻቸውን (በተለይ ኢዜማን) ከልክ በላይ እያቀረቡና እያሞገሱ በህዝቡና በሌሎች ፓርቲዎች ዘንድ ከባድ ጥርጣሬ መፍጠርስ? ህዝቡ የዛሬ አራት ዓመት ወያኔን ወጥሮ በሚታገልበት ወቅት እንዲህ ዓይነት ጥያቄዎች ተጠይቀው ነበር?
----
ይህ መንግስት በዲፕሎማሲው ዘርፍ ጥሩ ስራ ሰርቷል። በሌላው ዘርፍ ግን በጣም የተዳከመ ነው። ከነጭራሹ ኢትዮጵያ ሰላሟን አጥታ የግጭት አውድማ ሆናለች፡፡ ለዚህ ዋነኛው ምክንያቱ ደግሞ አንድ የባለ አደራ መንግስት መስራት ያለባቸውን ዋነኛ ስራዎች መዘንጋቱ ነው። ስለዚህ ወደ መነሻው ተመልሶ በተቀሩት ወራት ውጤታማ ስራ እንዲሰራ በአክብሮት እንጠይቃለን።

ህዝቡና አክቲቪስቱ እየተፈጠረ ላለው ችግር እንደ ምክንያት ሲጠቀሱ እናያለን። ለህዝባቸው የታገሉት ወጣቶች ጣት እየተጠቆመባቸው "መንጋውና ጎረምሳው ስራ አላሰራ አለ" እየተባሉ ይወቀሳሉ። እርግጥ በወጣቶቻችን ዘንድ አለመስከን እና ችኮላ ይታያል። ነገር ግን ዋናው የችግሩ ምንጭ ወጣቱን ከጎኑ አሰልፎ ለውጡን ማሻገር ያቃተው መንግስት ነው እንጂ ሌላ አካል አይደለም። ይህ ለህዝቡና ለሀገሩ ለውጥ ለማምጣት ሲል የሞተው ወጣት ዛሬም ስራ አጥ ነው። መንግስት ተብዬው ደግሞ ለወጣቱ ስራ መፍጠርን ትቶ በየእለቱና በየሳምንቱ "የምንትስ ቀን አከብራለሁ" እያለ በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ይረጫል። “የመደመር መጽሐፍ ለኢትዮጵያ ፍቱን መድኃኒት ነው” በማለት በእርሱ ላይ ብዙ ብር አውጥቶ ህዝቡን ያሸብራል፡፡ የሚያደንቁትንና እርሱ የሚወዳቸውን አይነት ግጥም የሚያነቡለትን አሸርጋጆች በሸራተንና በቤተ መንግስት እየጋበዘ ራሱን ያሽሞነሙናል። ዘይገርም!!
-----
ሀገሪቱን የምትመሩ ሰዎች ሆይ!

ለምርጫው አራት ወር ብቻ ይቀራል፡፡ እናንተም በህጋዊ መንገድ ሀገሪቱን መምራት የምትችሉት ለአራት ወራት ብቻ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ህዝቡ ለመረጠው መንግሥት ስልጣን ማስረከብ ይኖርባችኋል፡፡ የራሳችሁን ግለ-ስብእና ስትገነቡ እና በአዳዲስ ሃሳቦች ስትደነጋገሩ ጊዜው እያለቀ ነው፡፡ አሁንም ወደ ህሊናችሁ ተመልሳችሁ ሀገሪቱን ከጥፋት እንድትታደጓት ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡
-----
አፈንዲ ሙተቂ
መስከረም 1/2012