Wednesday, September 7, 2022

በዋስል ተራራ ላይ የተፈጠረው ክስተት


አፈንዲ ሙተቂ

-----

     

   ሁለቱ ኃይሎች ቀደም ሲል በተጠቀሰው የረቢዑል አወል ወር፣ ስድስተኛ ቀን፣ 938 ዓመተ ሂጅራ (October 27/1531) በታዋቂው “ዋስል ተራራ” ላይ በሰይፍና በጎራዴ መፋጨታቸውን ቀጠሉ፡፡ ታዲያ በአዳሎች ወገን የተሰለፈ አንዱ ተዋጊ በውጊያ ላይ እያለ በሆነ ነገር ጥርጣሬ ይዞት ልቡ ከላይ ታች ትባዝን ጀመር፡፡ የዚያ ሰው ስም “ፈቂህ ሼኽ አል-በርኸድሌ” ነው፡፡ ከአዳል ጎበዝ ፈረሰኞች አንዱ ነው፡፡ ፈቂህ በርኸድሌ ክብ ሰርተው ከቆሙት ጥቂት የአፄው ወታደሮች መካከል አንደኛው አፄ ልብነ ድንግል ራሱ እንደሆነ ገመተ፡፡ ወደዚያ ሄዶም ሰውዬውን በሰይፉ አስፈራርቶት ከኮርቻው ላይ ፈነገለው፡፡ ከዚያም “የሐበሻው ንጉሥ አንተ ነህ አይደለም እንዴ?” በማለት ጠየቀው፡፡ ሰውዬውም “አትግደለኝ፤ የሐበሻው ንጉሥ ያ ነው” በማለት ወደ ሌላ አቅጣጫ አመለከተው፡፡ ፈቂህ በርኸድሌ ግን “እንዴ? ልትዋሸኝ ትሞክራለህ እንዴ? ንጉሡ አንተ ነህ” እያለ ንግግሩን ጠንከር በማድረግ ሰይፉን እያወዛወዘ ጠየቀው፡፡ ከዚያ በኋላ የሆነውን ነገር ጸሐፊው ዐረብ ፈቂህ ደራሲ እንዲህ በማለት ይተርከዋል፡፡

 

 “ከሐበሾቹ መካከል የተወሰኑት ጌታቸው በተጠቀሰው ሰው (ፈቂህ በርኸድሌ) መማረኩን ሲያዩ ሰውዬውን አጠቁት፡፡ ከፊሎቹም ፈረሱን ያዙ፡፡ ከፊሎቹም እየመቱት ማረኩት”

  (ፉቱሕ አል-ሐበሽ፣ ቅጽ 2፣ ገጽ 72)

 

     በፈቂህ ሼኽ አል-በርኸድሌ የተማረከው ሰው በርግጥም አፄ ልብነ ድንግል ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ፈቂህ ሼኽ በርኸድሌ አፄውን ይዞ ለኢማም አሕመድ ከማስረከቡ በፊት የአፄው ልዩ ጠባቂዎች ጌታቸውን ከእጁ አስጥለውት ፈቂህ አልበርኸድሌን ራሱን ምርኮኛ አድርገውታል፡፡ ታዲያ ይህ ሁሉ የተከሰተው የአዳሉ መሪ ኢማም አሕመድ ኢብራሂም አል-ጛዚ ከነበረበት አካባቢ ጥቂት እርምጃዎች ብቻ በሚርቅ ስፍራ ላይ ነው፡፡

 

     ኢማም አሕመድ የእርሱ የቅርብ ሰው የሆነው ፈቂህ ሼኽ አል-በርኸድሌ በምርኮ መወሰዱን ሲያይ እየተንደረደረ መጥቶ ከማራኪዎቹ ጋር የጨበጣ ውጊያ ገጠመ፡፡ በልዩ ችሎታውና ጉልበቱ ሁሉንም ከራባብቶ በማባረር ፈቂህ በርኸድሌን ከጠላቶቹ እጅ አስለቀቀው፡፡ ከአጭር ቆይታ በኋላ ደግሞ በታላቁ የ“ፉቱሑል ሐበሻ ዘመቻ” ሂደት እጅግ አስገራሚ የነበረው ክስተት በዚሁ ስፍራ ላይ ተፈጠረ፡፡ እኛ “ዐረብ ፈቂህ” የምንለውና የተጸውኦ ስሙ ሺሃቡዲን አሕመድ ቢን አብዱልቃዲር የሆነው ደራሲም እንዲህ በማለት ክስተቱን በታሪክ መዝገብ ላይ ጻፈው፡፡

 

 “ኢማሙ በግራ እጃቸው ሰይፍ መያዛቸውን የሐበሻው ንጉሥ ተመለከተ፡፡ በፈረሳቸው ምልክትና ግራኝ በመሆናቸውም አወቃቸው”

  (ፉቱሕ አል-ሐበሽ፣ ቅጽ 2፣ ገጽ 72)

 

     አፄ ልብነ ድንግል ከዚያ በፊት ደመኛ ጠላቱን በአካል ባያየውም ሰውዬው ግራኝ መሆኑን ያውቅ ነበር ማለት ነው፡፡ በተጨማሪም የፈረሱን ምልክት ከታማኝ ምንጮቹ ሰምቷል፡፡ ይሁን እንጂ እርሱና ወታደሮቹ የአዳሉ ኢማም አሕመድ ኢብራሂም በዐውደ ውጊያው ውስጥ መኖሩን ሳያውቁ ነበር ፍልሚያ የገጠሙት፡፡ እርሱ ባልጠበቀው ሁኔታ ጠላቱ በግራ እጁ ሰይፉን እያወዛወዘ ሲመጣበት ደግሞ ስለኢማሙ የሰማውን መረጃ ነፍሱን ለማትረፍ ተጠቀመበት፡፡ ለወታደሮቹም “ሰይጣኑ ራሱ መጣላችሁ” በማለት ጮክ ብሎ ነገራቸው፡፡ ወታደሮቹም ይህንን ሲሰሙ ተተራመሱ፡፡ የውጊያ አቅማቸው ጠፋ፡፡ በመሆኑም አፄውን አጅበው “ድግምት አድርገህብናል! ድግምት አድርገህብናል!” እያሉ ከሜዳው ተበታትነው ጠፉ፡፡

*****

     አፄ ልብነ ድንግል በዚህ የዋሲል ውጊያ የኢማሙ ምርኮኛ ሊሆን ተቃርቦ የነበረ ቢሆንም በወታደሮቹ ጥንካሬ ተርፏል፡፡ ኢማሙ ወደርሱ ሲጠጋ ደግሞ ቀደም ብሎ በሰማቸው ምልክቶቹ ማንነቱን ለመለየት በመቻሉ ከሜዳው እግሬ አውጭኝ ብሎ በመሸሽ ሕይወቱን ለማትረፍ ችሏል፡፡

 

    ኢማም አሕመድ ኢብራሂም የአፄውን ማንነት ለመለየት ስለመቻሉ ግን የ“ፉቱሑል ሐበሻ” ጸሐፊ በግልጽ ያሳወቀን ነገር የለም፡፡ አፄውን ሊማርከው ተቃርቦ የነበረው ፈቂህ በርኸድሌም ቢሆን በዚያች ቀውጢ ወቅት የአፄውን ማንነት በትክክል ስለመለየቱ ከፉቱሑል ሐበሻ ትረካ ለማወቅ አይቻልም፡፡ አፄው ከዋስል ውጊያ በሽሽት ካመለጠ በኋላ ግን ፈቂህ በርኸድሌ ሊማርከው የነበረው ሰው እርሱ እንደሆነ ሁሉም አውቀዋል፡፡

 

     በነገራችን ላይ ኢማም አሕመድ ኢብራሂም “ግራኝ” ወይንም “ግራ-እጁ” እንደነበረ የሚገልጸው ብቸኛው የዐረብ ፈቂህ ዘገባ ከላይ የተጠቀሰው ነው፡፡ በዚህ መሠረት ኢማሙ በትውፊት “አሕመድ ግራኝ” (አሕመድ ግራ-እጁ) እና “አሕመድ ጉሬ” (በሶማሊኛ “ግራኙ አሕመድ” እንደማለት ነው) እየተባለ የሚጠራው በግራ እጅ ይጠቀም ስለነበረ ነው ማለት ነው፡፡ 

-------

(አፈንዲ ሙተቂ፡ “አዳል”፡ ሁለተኛ መጽሐፍ፡ 2015፡ ገጽ 124-127)

-------

·        ይህ አጭር ጽሑፍ “ፕሮቫ” ብቻ ነው፡፡ ሌላ ጽሑፍ ከመጽሐፉ እየተወሰደ አይለጥፍም፡፡ ሙሉው መጽሐፍ በቅርቡ ይታተማል፡፡

 

·        መጽሐፉ በድምሩ 534 ገጾች አሉት (ማሳተሚያው በጣም ከተወደደ በሁለት ቦታ ይከፈላል፡፡ ወይ ደግሞ ከአባሪዎቹ መካከል ለአሁን የማያስፈልጉት ተቀንሰው በአንድ ክፍል ይታተማል)፡፡

 

 

·        ዋጋው 410 ብር ነው፡፡ መጽሐፉን የምትፈልጉ ሰዎች ተዘጋጅታችሁ ጠብቁ፡፡

 

·        መጸሐፉ በደራሲው በኩል አንድ ጊዜ ብቻ ነው የሚታተመው፡፡ ከዚያ በኋላ ለአሳታሚ ድርጅቶች ይተላለፋል (ታሪኩን ማጥናት፣ መጻፍ፣ ማስተዋወቅ፣ መጽሐፉን ማሳተም፣ ማከፋፈልና በችርቻሮ መሸጥ በአንድ ሰው ሊከናወኑ አይችሉም፡፡ ስለዚህ የመጀመሪያውን ከፈጸምን በኋላ አሳትሞ የመሸጡ ስራ ወደ አሳታሚዎች ይተላለፋል)፡፡ ፊርማ የሚያርፈው በመጀመሪያው እትም ላይ ነው፡፡

 

 

·        የጸሐፊውና የአሳታሚዎች መብት በህግ የተጠበቀ ነው፡፡ መጽሐፉን በህገ-ወጥ መንገድ ማባዛትም፣ በPDF መቀየርም ሆነ በሁሉም ዓይነት የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያዎች መተረክ (Youtubeን ጨምሮ) ፍጹም የተከለከለ ነው፡፡

 

·        ይህንን ጽሑፍ የለጠፍኩት “አዳል - ቁጥር-2 ለምን አልወጣም?” እያሉ ለሚጠይቁ ሰዎች “መጽሐፉ እየመጣ ነው፤ በትዕግሥት ጠብቁ” ለማለት ያህል ነው፡፡

 

No comments:

Post a Comment