Thursday, July 16, 2015

በዒድ ዋዜማ ምሽት


ጸሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ
----
ነገ የዒድ አል-ፈጥር በዓልን ልናከብር ነው፡፡ ድሮ ልጆች ሳለን በዚህ የዋዜማ ምሽት በየቤቱ ላይ እየዞርን የምንዘምረው ህብረ ዜማ ነበረን፡፡ ይህ ዝማሬ አሁንም ድረስ አለ፡፡ ይሁንና የአሁኖቹ ልጆች በኛ ጊዜ ያልነበሩ ግጥሞችንም ጨመርመር እንዳደረጉ ተነግሮኛል፡፡ ለምሳሌ ህጻናቱ ጠቀም ያለ ጉርሻ ከተሰጣቸው “ያ ቢጢ ቢጢ… ጀንነተ ሊጢ” (“አንተ የቤቱ ባለቤት ጀንነት ግባ” ለማለት ነው) የሚል ምርቃት ያወርዳሉ ሲባል ሰምቻለሁ፡፡ ምንም ነገር ሳይሰጣቸው የሚያሰናብታቸውንም ሰው “ያ ቢጢ ቢጢ… አዛባ ሊጢ” (“የቤቱ ባለቤት ሆይ ጀሀነም ግባ” ለማለት ነው) እያሉ ይረግሙታል የሚል መረጃ ተሰጥቶኛል (“ቢጢ” የሚለው ቃል ለግጥሙ ማሳመሪያ ሲባል የገባ ነው፤ ጠበቅ ተደርጎ ሲነበብ “እንጎቻ” እንደማለት ነው፤ ላላ ተደርጎ ሲነበብ ግን ምንም ትርጉም የለውም፤ ህጻናቱ “ላላ” በማድረግ ነው በግጥሙ ውስጥ ያስገቡት)፡፡

  በኛ ዘመን እንዲህ የሚል ግጥም አልነበረም፡፡ ከዚህ ወልካፋ ግጥም በስተቀር ዜማው እንዳለ የያኔው ነው፡፡ ያ ህብረ ዝማሬ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲሸጋገር ነው ለኛ የደረሰው፡፡ ለዜማው ለየት ያለ መጠሪያ አላበጀንለትም፡፡ በጥቅሉ የምንጠራው “ሙሐመዶ” በሚል ስያሜ ነው፡፡

“ሙሐመዶ” የዝማሬው የመጀመሪያ ቃል ነው፡፡ ይህንን ዝማሬ የምንዘምረው በአንድ ልጅ መሪነት ነው፡፡ ልጁ የግጥሙን ስንኞች እያከታተለ ሲያወርድልን ሌሎች ጓደኞቹ “ሙሐመድ ሰይዲና ሙሐመድ” እያልን እንቀበለዋለን፡፡ የህብረ-ዜማው ሙሉ ግጥም የሚከተለው ነው (ግጥሙ በኦሮምኛ ነው የተገጠመው፤ በቅንፍ ውስጥ በአማርኛ ተርጉሜዋለሁ)፡፡

ሙሐመዶ (ሙሐመድ ሆይ)
ሙሐመድ ጄንኔ (ሙሐመድ እያልን)
ነቢ ፋርሲኔ (ነቢዩን እናወድሳለን)
ያ ነቢ ባህሩ (አንተ እንደ ባህር የሆንከው ነቢዩ)
ዛሂድ ኢኒ ሂንአሩ (አላግባብ የማትናደድ ነህ)
ፋጢማ ነቢ ኢልኬን ቲሚራ (የነቢ ልጅ የሆነችው ፋጢማ ጥርሷ እንደ ቴምር ነው)
ዲና ነቢዳ ኢልኬን ዲጊራ (የነቢዩ ጠላት ጥርሱ እንደ “ድግር” ነው)
ሶመንኒ ገሌ  (ረመዳን ሄዷል)
ሲዲስቶ መሌ (ከስድስቶ/ሸዋል በስተቀር)
ያ ሀደ ዲራ (የቤቱ ባለቤት ሆይ)
ገድ ደርቢ ሊራ (እስቲ ሊራ ወርወር አድርጊልን)
ሊራ አፉሪ (አራት ሊራ ሰጥተሽን)
ሉብቡን ኑፉሪ (ከልባችን አስደስቺን)፡፡
ሙሐመድ ሰለላሁ ዐላ
ሙሐመድ ሰለላሁ ዐላ ሙሐመድ፡፡
-----
“ሙሐመዶ” በበርካታ ከተሞች የታወቀ ህብረ-ዜማ ነው፡፡ በልጅነቱ እርሱን ሳይዘምር ያደገ ልጅ የለም፡፡ የክርስቲያን ልጆች እንኳ ከኛ ጋር ተቀላቅለው “ሙሐመዶ”ን ይዘምሩ ነበር፡፡ ይሁንና በርሱ ብቻ መቆየቱ ስለማይበቃን ሌሎች ዜማዎችንም እንጨምር ነበር፡፡ እነዚህ ተጭማሪ ህብረ ዝማሬዎች ግን አንድ ወጥ አይደሉም፡፡ በአንድ ከተማ ውስጥ ባሉ ሁለት ቀበሌዎች ውስጥ የሚኖሩ ልጆች እንኳ የተለያዩ ዜማዎችን ሊዘምሩ ይችላሉ፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን “ጀማሉል ዓለም” የተሰኘው ህብረ-ዝማሬ ከመሐመዶ ቀጥሎ በሌሎችም አካባቢዎች በደንብ የሚታወቅ ይመስለኛል፡፡ “ሙሐመዶ”ን የማይዘምሩት የሶማሊ ልጆች እንኳ “ጀማሉል ዓለም”ን ሲዘምሩት በአንድ የነሺዳ ሲዲ ውስጥ አይቼአቸው ነበር፡፡ የ“ጀማሉል ዓለም” አዝማች የሚከተለው ነው፡፡

ጀማሉል ዓለም (ሸሊላ)
ጀማሉል ዓለም (ሸሊላ)
ባህረ ሙስጠፋ (ሸሊላ)
ያ ባህረ ጁህዲ ጁንዲላ

“ጀማሉል ዓለም” ማለት “አንተ የዓለም ውብ የሆንከው” እንደማለት ነው፡፡ እንዲህ የተባሉት ነቢዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ናቸው፡፡ ታዲያ ከአዝማቹ ቀጥሎ የሚዜሙት አንዳንድ ግጥሞች ከአዝማቹ ጋር የማይሄዱ (“አንታራም” ግጥሞች) መሆናቸውን ሳስብ ድንቅ ይለኛል፡፡ ለምሳሌ በዝማሬው ውስጥ እንዲህ የሚል ግጥም ነበር፡፡

“ጋረራ ያና ቦሮፋ ካፍና
ጆልሌ ኑቲ ካቲ ዱኬ ኢቲ ካፍና
ዱኬ ማል ካስና ጋረራ ባፍና”

የአማርኛው ትርጉም የሚከተለው ነው፡፡

“ጋራ ላይ እንሄዳለን ድኩላ እናባርራለን
የሚተናኮሉንን ልጆች እናርበደብዳቸዋለን
የምን ማርበድበድ ብቻ! ጋራው ላይ እንነዳቸዋለን”

በተለምዶ እንዲህ ዓይነት ግጥሞች የሚገጠሙት የሁለት ሰፈር ልጆች በሚጣሉበት ጊዜ ነው፡፡ የተጣሉ ልጆች በዱላ እየተመካከቱ የሚበሻሸቁበት ግጥም መሆኑን ካደግን በኋላ ነው የተረዳነው፡፡ እኛ ግን ምኑም ሳይገባን የዒድ ማድመቂያ አደረግነው፡፡ አይ ልጅነት ደጉ!!

የገንደ ሀድራ ልጆች ደግሞ አሉ! አንዱን ዝማሬ ለነርሱ ብቻ በሞኖፖል የተሰጠ አድርገው የሚያስቡ፡፡ ያንን ዝማሬ የኛ ሰፈር ልጆች ካዜሙት የቃል ማስጠንቀቂያና ማስፈራሪያ ይለቁብናል፡፡ ዝማሬውን ከደገምነው ግን በዱላ ጭምር ያዋክቡን ነበር፡፡ የዝማሬው አዝማች የሚከተለው ነበር፡፡

“አወይ ነቢ ሰላም ዐላ (አንተ ነቢ ሰላም ላንተ ይሁን)
ኑር ሐቢቢ ሶላት ዐላ (አንተ ነቢ ሶላት ላንተ ይሁን)

ከዚህ አዝማች ጋር ብዙ ግጥሞችን ይደረድራሉ፡፡ በመሃሉም እንዲህ የሚል ባለሁለት መስመር ግጥም አለ፡፡

“አክካ አዱ ጎላ ባቱ (ከጎሬዋ እንደምትወጣ ጮራ)
ከን ዱራ ዱብኒ አዳቱ” (ፊቱም ኋላውም የሚያበራ)

የሀድራ ልጆች በጣም ብዙ ነበሩ፡፡ ብዛታቸውን ተመክተው ነው “አወይ ነቢ ሰላምን አትዘምሩት” እያሉ የሚጫኑን፡፡ እኛም በምሽቱ መጀመሪያ ላይ ትዕዛዛቸውን እናከብርና “ሙሐመዶ”ን ወይንም “ጀማሉል ዓለም”ን ብቻ እንዘምራለን፡፡ በሶስት ሰዓት ገደማ ግን የሀድራ ልጆች ለሚያደርጉብን ጭቆና ብድሩን እንከፍላለን በማለት ከላይ የጻፍኩትን ግጥም እንዲህ እያበላሸን እንዘምራለን፡፡

አክከ አዱ ጎላ ባቱ (ከጎሬዋ እንደምትወጣ ጮራ)
ሚጪዮ ፉልሊ አዳቱ  (የልጅቷ ፊት ሲያበራ)

እንዲህ እያልን የምንዘምረው የሀድራ ልጆች እንዲሰሙን ድምጻችንን ከፍ በማድረግ ነው፡፡ ሀድራዎች በንዴት ዱላቸውን እየወዘወዙ በሩጫ ሲመጡብን በጨለማው ውስጥ እንበታተንና ወደቤታችን እንመርሻለን!! አይ ልጅነት ደጉ!!

እኛ ነቢዩን አልነካንም!! ሐድራዎች ዝማሬው የኛ ብቻ ነው እያሉ ስለሚጫኑን እነርሱን ለመበቀል የነበረን አማራጭ መንገድ ይኸው ብቻ ነው፡፡ ቢሆንም ለነቢዩ የተገጠመን ግጥም ማጣመም ልክ አልነበረም፡፡ በመሆኑም ሐራምና ሐላሉን በደንብ ስንረዳ “አስተግፊሩላህ” ብለናል!! አሁንም አስተግፊሩላህ!! ወደፊትም አስተግፊሩላህ!!
----
እንኳን ለዒድ አል-ፈጥር በዓል አደረሰን!!
ዒድ ሙባረክ!!