Wednesday, June 26, 2013

አንድ ሰው አየሁኝ


አፈንዲ ሙተቂ (ስነ ግጥም)
ጥንት እንደሰማሁት
በመድረሳ እንደተማርኩት
ነቢዩ እንደሰበኩት
በኮሌጅ እንዳጠናሁት
ፈላስፎች እንደጻፉት።
ጀግና ሰው ማለት
ጠላቱን ደምስሶ
ከመሬት ደባላቂ
የወደዱትን አቅርቦ
የጠሉትን አስጨናቂ
የናቁትን አድቃቂ
ማለት እኮ አልነበረም
ጦር አዝማች በዓለም።
ጀግናማ ማለት
እንደ ኮንፉሺየስ
ነጻነትን አስተማሪ
እንደ ሶቅራጥስ
እውነትን መስካሪ
እንደ ሀሩን አል-ረሺድ
እውቀትን አጥማቂ
እንደ ህንዱ ጋንዲ
ፍቅርን አድማቂ
እንደ ቶልስቶይ
ህላዌን ተንታኝ
እንደ ፐርሺያው ሩሚ
ጥላቻን አምካኝ።
እንደዚያ ነው ጀግና
የሚኖር በዝና
በማይጠፋ ጉብዝና
በማያረጅ ስብዕና።
ታዲያ በዚህ ዘመን
በዓለም ስሙ የገነነው
በሚዲያ የሚዘምረው
በቴቪ የሚንጎማለለው
በፕሬስ የሚመላለሰው
ሁሉም ቢሆንብኝ አረመኔ
አውደልዳይ ወመኔ
አሽቃባጭ ቦዞኔ።
እተክዝ ጀመርኩኝ
የጥንቶቹን እየዘከርኩኝ
በድርሰት ያወቅኳቸውን
ግን በአካል ያላየኋቸውን
እነርሱን እያሰብኩኝ
ለራሴ እንዲህ አልኩኝ
“ጀግና ሳላይ ነው የምሞተው?
ወደ አፈር የምመለሰው
ይሄስ ክፉ እድል ነው
እንዲያውም እርግማን ነው”
ሆኖም በትካዜዬ መሀል
አንድ ሰው ውልብ ብሎብኝ
“የዘመንህ ጀግና እኔ ነኝ
እኔ ነኝ ተመልከተኝ”
በማለት ደስኩሮብኝ
ፈገግታውን አልብሶኝ
ሓሳቤን አቃለለልኝ
ድብቱን አባረረልኝ
እኔም አልኩ ተመስገን
ተመስገን ያ አላህ ተመስገን
ተመስገን ጌታዬ ተመስገን።
ይህንን ጀግና የሰጠኸን
እንካችሁ ብለህ የሸለምከን
በትግሉ ጽናትን ያስተማርከን
በእስሩ ቻይነትን ያሳየኸን
በመሐሪነቱ ፍቅርን ያስዘመርከን
በአባትነቱ ብስለትን ያስጨበጥከን።
ተመስገን ያረቢ ተመስገን
ተመስገን አምላኬ ተመስገን
ማዲባን የሰጠኸን
መምህሩን ያነሳህልን።”
ከሐሳቤ ስመለስ
ልቤን ሞልቶት ኩራት
መፈንሴ በርቶ በብስራት
ሰውነቴ ጠንክሮ በጽናት
ራሴን ድኖ አገኘሁት።
(ለኔልሰን ማንዴላ ክብር የተገጠመ)

------ግጥም፡ አፈንዲ ሙተቂ፣
ሰኔ 19/2005 ዓ.ል.
ሀረር/ ምስራቅ ኢትዮጵያ

Tuesday, June 25, 2013

የምስራች!


 የሼኽ ሑሴን ጂብሪልን ሙሉ ግጥሞች እንድሰጣችሁ በጠየቃችሁኝ መሰረት በዶ/ር ጌቴ ገላዬ የተዘጋጀው ባለ 36 ገጽ ጥናታዊ ጽሁፍ በዘልዓለም ክብረት ብሎግ ላይ ተጭኖ አግኝቼዋለሁ። ስለዚህ ከታች ያለውን ሊንክ ተከትላችሁ ዳውንሎድ ማድረግ ትችላላችሁ።
-----------
ማስታወሻ፡-
1. የሼኽ ሑሴን ጂብሪል ግጥሞችን በዚህ ፔጅ ላይ ሳቀርብ የነበረው ስለኢትዮጵያ ቀደምት ዑለማ ስጽፍ ያዩኝ አንዳንድ የፔጁ ተከታታዮች "ስለወሎው ሼኽ ሑሴን ጂብሪልም ንገረን" የሚል ጥያቄ ስላቀረቡልኝ ነው፤ እንጂ ግጥሞቹ የወደፊቱን ጠቋሚ ትክክለኛ ትንቢቶች ናቸው በማለት አይደለም (ይህንን የሚያውቀው አላህ ብቻ ነውና)። ስለዚህ ግጥሞቹ ከማንኛችንም እምነት ጋር መያያዝ የለባቸውም።

2. እስከ አሁን post ያደረግኳቸው ግጥሞች ለራሴ ምርጫ የተስማሙት ብቻ  ናቸው። ከእኔም ሆነ ከብዙዎች እምነት ጋር የማይሄዱ ግጥሞችም በድርሳኑ ውስጥ አሉ። ስለዚህ እንዲህ ዓይነት ተቃርኖ ያሉባቸውን ግጥሞች እየዘለላችኋቸው ደስ የሚሉትን ብቻ እንድታዩአቸው ማስገንዘቢያ ቢጤ ጣል ላደርግላችሁ እፈልጋለሁ።

3. ሼኽ ሑሴን ጂብሪል ስለሚባሉት ሰው ማንነትም ሙሉ በሙሉ የሚታወቅ ነገር የለም። ስለዚህ የሼኹ የህይወት ታሪክ ተብሎ የተነገረው ጸሐፊው/ጸሓፊያኑ በአፈታሪክ ሲነገር የሰሙት ብቻ መሆኑን እንድታውቁት ይፈለጋል።

ለሁሉም ጽሁፉን ዳውንሎድ አድርጋችሁ ውሰዱት።
------አፈንዲ ሙተቂ
ሰኔ 20/2005
ሀረር- ምስራቅ ኢትዮጵያ
ሊንኩ ይኸውና http://zelalemkibret.files.wordpress.com/2011/03/gelaye4.pdf


N.B. ግጥሞቹ የታተሙበትን መጽሐፍ ብሔራዊ ቲያትር አካባቢ ወዳለው ደስታ መጻሕፍት መደብር ሄዳችሁ ጠይቁ። እኔም ከዚያ ነው የገዛሁት (ሽፋኑ ሰማያዊ ነው)።