Monday, July 19, 2021

ዐረፋ” እና “ዒድ አል-አድሐ”፡ መሠረታዊ መነሻ እና ማኅበረሰባዊ ሚና

ፀሐፊ አፈንዲ ሙተቂ

-------

ከአምስቱ የዲነል ኢስላም ማዕዘናት መካከል አንዱ “ሐጅ” ይባላል፡፡ የሐጅ ስርዓት ወደ ዐረቢያ በመጓዝ መካን ጨምሮ ሒጃዝ በሚባለው የዐረቢያ ክፍለ ሀገር ውስጥ ባሉት ሌሎች የተቀደሱ ስፍራዎች ላይ በአካል እየተገኙ የተለያዩ የዒባዳ እና የዱዓ ተግባራትን መከወንን ይጠይቃል፡፡ በዚህ የሐጅ ጉዞ ከሚፈጸሙት መንፈሳዊ ስርዓቶች መካከል አንዱ በዙልሒጃ ወር ዘጠነኛው ቀን “ጀበል ዐረፋት” በሚባለው አምባ ላይ የሚከወነው “ዉቁፍ ቢ ዐረፋት” (በዐረፋ ላይ ቆሞ ጸሎት ማድረግ) ነው፡፡ ይህ የዉቁፍ አምልኮ ቀዳሚው መሰረቱ ከነቢዩ አደም (ዐሰ) እና ከባለቤታቸው ሐዋ ታሪክ ጋር የሚገናኝ ነው፡፡ አደም እና ሐዋ ከጀንነት ከወጡ በኋላ በተለያዩ አካባቢዎች እየተፈላለጉ ቆይተው መጨረሻ ላይ የተገናኙት በዐረፋት ተራራ ላይ ነው፡፡ በዚያ ስፍራ ሲገናኙም “ዐረፍቱ…. ዐረፍቱኪ” ተባበሉ፡፡ “ዐረፍቱከ” በዐረብኛ “አወቅኩህ” (ለወንድ ጾታ) ማለት ነው፡፡ “ዐረፍቱኪ” በተመሳሳይ ቋንቋ “አወቅኩሽ” (ለሴት ጾታ) እንደማለት ነው፡፡  

 

ወደ ዐረፋ የተጓዘ መላው ሙስሊም በዕለቱ በጀበል ዐረፋት ተገኝቶ በዚያ የሚደረገውን “ኹጥባ” መስማት አለበት፡፡ በመሆኑም ከመላው ዓለም የተሰባሰቡ ሐጃጆች ብሄር፣ ጾታ፣ ቀለም፣ አህጉር፣ ሀገር፣ ክፍለ ሀገር፣ መደብ፣ ስልጣን፣ የስራ መደብ፣ ወዘቱ ሳይገድባቸው በአንድ ቦታ ቆመው የአዳም ልጆች መሆናቸውን ያስመሰክራሉ፡፡ ሁላቸውም የአደምና እና ሀዋ,,ሐዋ ልጆች መሆናቸውን ያስታውቃሉ፡፡

 

ታዲያ በዚሁ የዙልሒጃ ወር ዘጠነኛ ቀን ሁለት ትልቅ ድርጊቶች ተከናውነዋል፡፡ ከነዚህም መካከል አንዱ ነቢዩ ሙሐመድ (ሰዐወ) በታሪክ ገጾች “The Masterpiece Sermon of Prophet Mohammed” እየተባለ የሚጠራውን ታላቅ ዲስኩራቸውን ያሰሙበት እለት መሆኑ ነው፡፡ ነቢዩ ንግግራቸውን የጀመሩት ሰዎች ሆይ! ከዚህ በኋላ በናንተ መካከል ላልገኝ እችላለሁ፤ ስለዚህ ልብ ብላችሁ አድምጡኝ በሚል ዐረፍተ ነገር ነው፡፡ በርግጥም ነቢዩ ከዚህ የመሰናበቻ ንግግራቸው በኋላ በህይወት ብዙም አልቆዩም፡፡ ቢሆንም ከነቢዩ ንግግሮች መካከል በደንብ የተመዘገበው ይህ ንግግራቸው ነው፡፡ በሐዲስ ምሁራን ዘንድ የቃላትና የሐረጋት ልዩነት ሳይደረግበትና በእውነተኛነቱ ላይ ጥርጣሬ ሳይጣልበት (ሰሒሕ እና ደዒፍ ሳይባል) ተቀባይነትን ያገኘው ይህ የሐጀቱል ወዳዕ ንግግራቸው ነው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ንግግሩ በመቶ ሺህ ህዝብ የተሰማ መሆኑ ነው፡፡

 

ይህ ቀን የሚታወስበት ሁለተኛው ታላቅ ክስተት  “ዲነል ኢስላም”  በሃይማኖትነቱ መሟላቱን የሚያበስረው የቁርኣን አያህ (አንቀጽ)  የወረደበት ዕለት መሆኑ ነው፡፡ አዎን!! ሙስሊሞች የሚመሩባቸውን የኑሮና የዒባዳ ደንቦችን የሚያወሱ የቁርኣን አንቀጾች በሙሉ ለነቢዩ ተገልጠው መጠናቀቃቸው በዚህ ተገልል፡፡ኢቅራእ በሚለው መለኮታዊ የቁርኣን ቃል የጀመረው እስልምናን የማብሰር፣ የማስተማርና የማብራራት ሂደት በዚህ ዕለት በወረደውና በሱረቱል ማኢዳ ውስጥ በሚገኘው ሶስተኛው አንቀጽ ላይ በተጻፈው ሁኔታ ተጠናቅቋል፡፡ ይህ አያህ እንዲህ እንዲህ ይላል፡፡

 

ዛሬ ለናንተ ሃይማኖታችሁን ሞላሁላችሁ፤ ጸጋዬንም በናንተ ላይ ፈጸምኩ፤ እስልምናንም በሃይማኖትነት ወደድኩላችሁ

(ሱረቱል ማኢዳ፤ 3)

 

እዚህ ላይ አንድ ነገር ማውሳት አለብኝ፡፡ በተለምዶ ከላይ የተገለጸው አያህ መጨረሻ የወረደው የቁርኣን አንቀጽ ነው እየተባለ የሚነገረው አባባል ስሕተት መሆኑን ለመጠቆም እፈልጋለሁ፡፡ መጨረሻ ላይ የወረደው የቁርኣን አንቀጽ የሱረቱል በቀራህ 181ኛ አያህ ነው፡፡

 

 

ዐረፋ ታላቅ የዒባዳ ቀን እንጂ የበዓል ዕለት አይደለም፡፡ ወደ ሐጂ ያልተጓዙ ሙስሊሞች የዐረፋን ዕለት በጾም እንዲያሳልፉ ይመከራሉ፡፡ ይህንንም በማስመልከት ነቢዩ ሙሐመድ (ሰዐወ) እንዲህ ብለዋል፡፡

 

በዐረፋ ቀን ለጾመ ሰው አላህ ያለፈውን ዓመትና የቀጣዩን ዓመት ሐጢአቱን ይቅር ይለዋል

 

በኛ ሀገር በተለምዶ ዐረፋ የሚባለው የኢድ አል አድሓን በዓል የምናከብርበት አስረኛው እለት ነው፡፡ በሸሪዓው እይታ ዐረፋ የሚባለው ግን የዙልሒጃ ወር ዘጠነኛው ቀን ነው፡፡

--

የዒድ አል-አድሓ ታሪካዊ ዳራ ደግሞ ነቢዩ ኢብራሂም (ዐሰ) ልጃቸውን ለአላህ ለመሰዋት ያደረጉት ቁርጠኝነት የተመላበት ውሳኔ እና ለመስዋዕትነት የቀረበው ልጅ ያሳየው የተለየ ጽናት ነው፡፡ ነቢዩ ኢብራሂም (ዐሰ) የበኩር ልጃቸው የሆነውን ዒስማኢልን (ዐሰ) ያገኙት በእርጅና ዘመናቸው ነው፡፡ ታላቅ ሚስታቸው ሳራ ለፍሬ ባለመብቃቷ አላህ ያለ ዘር አታስቀረኝ፤ እኔን የሚተካ ሷሊህ የሆነ ልጅ ስጠኝ በማለት ዱዓ አደረጉ፡፡ በዚሁ መሰረት በሳራ ፈቃደኝነት ሐጀራ የምትባለውን የቤት ሰራተኛቸውን አገቡ፡፡ ሐጀራም ዒስማኢል የተባለ (ዐሰ) ልጃቸውን ወለደችላቸው፡፡ ይህ ልጅ በአላህ ፈቃድ በመካ ከተማ እንዲያድግ የተወሰነ ስለነበረ ኢብራሂም (ዐሰ) ሐጀራን እና ዒስማኢልን ወደ ዐረቢያ ከተማ ወሰዷቸው፡፡

 

ዒስማኢል (ዐሰ) ካደገ በኋላ ደግሞ አላህ ልጅህን እንድትሰዋ ታዘሃል የሚል ትዕይንት በህልማቸው አሳያቸው፡፡ የነቢያት ህልም ደግሞ ከራዕይ የሚቆጠር ነው፡፡ ስለዚህ ኢብራሂም በህልማቸው ያዩትን በዝምታ አላለፉትም፡፡ በወቅቱ የሆነውን ቅዱስ ቁርኣን እንዲህ ይተርካል፡፡

 

ከርሱ ጋር ለስራ በደረሰ ጊዜም ልጄ ሆይ! እኔ በህልሜ የማርድህ ሆኜ አይቻለሁ፤ (እስቲ አንተም ነገሩን) ተመልከት፡፡ ምን ይታይሃል አለው፡፡ (ልጁም) አባቴ ሆይ! የታዘዝከውን ፈጽም፤ አላህ ቢሻ ከታጋሾቹ ሆኜ ታገኘኛለህ አለ

(ሱረቱ -ሷፍፋት፤ 102)

 

አባትና ልጅ በዚህ መንገድ ከአላህ የተላለፈውን ትዕዛዝ ሊፈጽሙ ተነሱ፤ ነቢዩ ኢብራሂም (ዐሰ) ልጃቸውን እንዲሰው የታዘዙት ከዐረፋት መሬት ብዙም ባልራቀ ቦታ ላይ ስለነበረ ወደዚያው ጉዞ ጀመሩ፡፡ በመንገዳቸው ግን ኢብሊስ በሰው ተመስሎ በጣም ተፈታተናቸው፤ ሶስት ጊዜ ያህል እየወጣ ከስንት ዓመት በኋላ ያገኘኸውን አንድዬ ልጅህን ስትሰዋ ምንም አይጸጽትም? እንዴት ጅል ትሆናለህ እያለ ሞገታቸው፡፡ ከአላህ ትዕዛዝ ፍንክች የማይሉት ኢብራሂም ግን ድንጋይ ከመሬት በማንሳት አዑዙቢላሂ ሚነ-ሸይጣኒ ረጂም እያሉ ኢብሊስን ወገሩት፡፡

 

ኢብራሂም ዒስማኢልን ሊያርዱት አጋደሙት፡፡ ልጁም ምንም ሳያንገራግር ከመሬቱ ላይ ተኛ፡፡ ኢብራሂም ልጁን ሊያርዱት ሲሞክሩ ግን ቢላዋው አላርድ አላቸው፡፡ ኢብራሂም እንደገና ቢላዋውን ገዘገዙት፡፡ ነገር ግን ፈጽሞ ዶለዶመ፡፡ ልጁ የሆነው ነገር አልገባውም፡፡ አባቱ ቶሎ ስላላረደው ተገረመና አባዬ! ምናልባት የአባትነት ፍቅር ይዞህ ይሆናል በቶሎ ያላረድከኝ፤ እስቲ ዐይኔን በጨርቅ ሸፍነውና እርዱን ሞክር የሚል አስተያየት ሰጠ፡፡

በዚህን ጊዜ ግን ከወደ ሰማይ ጥሪ መጣ፡፡ የአላህ መልአክ ኢብራሂም ታላቅነትህን አስመስክረሃልና እርዱን አቆየው በማለት አወጀ፡፡ በምትኩም መልአኩ ከገነት ያመጣውን በግ እንዲያርድና ልጁን ወደቤቱ እንዲወስደው ነገረው፡፡ በዚህም መሰረት በጉ ታረደ፡፡ ኢብራሂምና ዒስማኢልም ወደ መካ ከተማ ተመለሱ፡፡ ሁለቱ ሰዎች ለፈጣሪ መታዘዝን በግልጽ ያሳዩባት ያቺ ዕለት የዒድ አል-አድሓ በዓል ሆና እንድትከበርም ተወሰነ፡፡ ዒስማኢል ለመስዋእትነት የቀረበበት ድርጊት ደግሞ በዚሁ ዕለት የሚታረደው ኡድሒያ መነሻ ሆነ፡፡

----

ዒድ አል-አድሐ የመስዋዕትነትና የመዳን በዓል ነው፡፡ የሐጅ ጸሎት የሚፈጽም ሰው በዚህ ዕለት ኡድሒያ የማረድ ግዴታ አለበት፡፡ እኛም ወደ ሐጅ ያልሄድነው ደግሞ ከተቻለ በዚሁ ዕለት በየቤታችን እንስሳት እያረድን ኡድሒያ እንድናቀርብ ታዘናል፡፡

 

ታዲያ ኡድሒያው ኡድሒያ ተብሎ የሚመዘገብልን እርዱም ሆነ አጠቃቀሙ ነቢዩ (ሰዐወ) ያስተማሩትን መንገድ የተከተለ ከሆነ ብቻ ነው፡፡ ለምሳሌ አንዳንድ ሰዎች ፍየሉን ያርዱና ለበዓል የሚሆናቸውን ያህል ካስቀሩለት በኋላ ሌላውን ወደ ፍሪጅ ውስጥ ይከቱታል፡፡ ይህ ግን ራስን መጋበዝ ነው እንጂ ኡድሒያ ተብሎ አይመዘገብም፡፡

 

ነቢዩ (ሰዐወ) እንዳስተማሩት ለኡድሒያ ከታረደው ስጋ አንድ ሶስተኛው በቀጥታ ለድሆች መከፋፈል አለበት፡፡ አንድ ሶስተኛው ለዘመድና ለወዳጅ ነው የሚሰጠው፡፡ የተቀረው አንድ ሶስተኛ ብቻ ነው ለቤተሰቡ አገልግሎት የሚውለው፡፡ ስለዚህ በዚህ እለት የሚፈጸመው መስዋእት ኡድሒያ ሆኖ እንዲመዘገብልን ካሻን ትክክለኛውን መንገድ መከተል አለብን፡፡ በተለይ ከታረደው ስጋ የድሆች ድርሻ የሆነውን ሡሉሥ ከሁሉም አስቀድመን ለባለቤቶቹ እናስረክብ ዘንድ የአደራ መልዕክታችንን እናስተላልፋለን፡፡

-----

ዒድ ሙባረክ

አፈንዲ ሙተቂ

----

መጀመሪያ መስከረም 12/2008 ተጻፈ፡፡

እንደገና ተሻሽሎ ሀምሌ 12/2013 ተጻፈ፡፡

ሀረር-ምስራቅ ኢትዮጵያ