Thursday, August 14, 2014

እስልምና፣ “ጂሃድ” እና ሰሞነኛው የኢራቅ ሚሊሻ


ፀሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ
--------
ኢራቅ በሳዳም ሁሴን አገዛዝ ስር በነበረችበት ዘመን ከሞላ ጎደል ሰላምና መረጋጋት ነበራት፡፡ ሀገራዊ አንድነቷም የተጠበቀ ነው፡፡ አሜሪካ አንድም ማስረጃ ባልነበረው ወሬ ተነሳስታ በ2003 (እ.ኤ.አ) ሀገሪቷን ከወረረቻት በኋላ ግን አንድነቷም ሆነ ሰላሟ ተናግቷል፡፡ በኤፍራጥስና ጤግሮስ ወንዞች ላይ የከተመችው ውቢቷ ባግዳድም በየዕለቱ የቦንብና የፈንጂ ፍንዳታ ማስተናገድ ምሷ ሆኗል፡፡ 
    ከዚህ ባሻገር ሀገሪቷ ክቡር የሆነውን የእስልምና አስተምህሮ እንዳሻቸው እየተረጎሙ ስውር አጀንዳዎቻቸውን ለማስፈጸም የሚተጉ ጽንፈኛ ግለሰቦችና ቡድኖች መፈልፈያ ሆናለች፡፡ አቡ ሙስዓብ አል-ዘርቃዊን የመሳሰሉ ጽንፈኞች ኢራቅን የእቶን እሳት መቀጣጠያ ሲያደርጓት እንደከረሙ ተመልክተናል፡፡ በዘንድሮው ዓመት ደግሞ ድሮ ከምንሰማቸው እጅግ የከፋ ጽንፈኛ ቡድን በዚያው ምድር ላይ እጆቹን ሲዘረጋ ለመታዘብ በቅተናል፡፡
  ራሱን “የኢራቅና የሻም ኢስላማዊ መንግሥት” እያለ የሚጠራው (ከቅርብ ጊዜ ወዲህ “ኢስላማዊ መንግሥት” በሚለው አጭር ስያሜ ብቻ የሚጠራው) ቡድን ከየት ተገኘ?.. እንዴት ተመሰረተ?… መስራቾቹስ እነማን ናቸው?… ከጀርባ የሚገፉትስ እነ ማን ናቸው?…. የመጨረሻ ዓላማው ምንድነው?…. እነዚህን ጥያቄዎች ለመመለስ የነጠረ መረጃ ሊኖረን ይገባል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ግን ብዙዎቹን ጥያቄዎች ለመመለስ አይቻልም፡፡ ስለዚህ ጥያቄዎቹን ጊዜ ይመልሳቸው ማለቱ ይሻላል፡፡ ቡድኑ ለሚተግብራቸው የጽንፈኝነት አድራጎት እስልምናን እንደ ማስረጃ እየጠቀሰ ማነብነቡ ግን በጣም ያሳምመናል፡፡
   በዘመናችን የሚታዩትና በእስልምና ስም የሚነግዱ ጽንፈኞች በሙሉ “ጂሃድ እያደረግን ነው” እያሉ ነው የሚፎክሩት፡፡ ለብዙ ክፍለ ዘመናት በሙስሊሞች መሀል በሰላም ሲኖሩ የነበሩ ማህበረሰቦች ሀይማኖታቸውን እንዲቀይሩ ማስገደድም ጀምረዋል፡፡ “ጂሃዳቸው” ግብ መትቶ ሀገር ከተቆጣጠሩ በኋላ የሚመሰርቱት “ኋላቀር” መንግሥት ምን ዓይነት እንደሆነም ምልክቱን እያየን ነው፡፡ በርግጥ በእስልምና እይታ እንዲህ ዐይነቱ ጽንፈኝነት “ጂሃድ” ማድረግ ነው ተብሎ ሊጠራ ይችላልን?… እስልምናስ “ኋላቀርነትን” የሚናፍቅ እምነት ነውን?… በነዚህ ነጥቦች ዙሪያ አንዳንድ ነገሮችን ለመናገር አስቤ ነው ይህንን መጣጥፍ የጻፍኩት፡፡

==“ጂሃድ” እና ጽንፈኞች=

  ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) በህይወት ዘመናቸው ከብዙ ባላንጣዎቻቸው ጋር ተጋድለዋል፤ ተዋግተዋል፡፡ ይሁንና እሳቸውም ሆኑ ተከታዮቻቸው ከባላንጣዎቻቸው ጋር የተጋደሉት ሰዎች እስልምናን በጉልበት እንዲቀበሉ ለመጫን በሚል አይደለም፤ እነዚያ ባላንጣዎቻቸው ሊያጠፏቸው ስለተነሱባቸው ነው ራሳቸውን ለመከላከል የተዋጉት፡፡ ጠላቶቻቸው ከመካ ከተማ ጀምሮ ሊያጠፏቸው ሲዶልቱ፣ ሴራ ሲሸርቡና ቅጥረኞችን ሲልኩባቸው ነበር፡፡ ይባስ ብሎም “ሀይማኖታችንን አርክሶ አዲስ እምነት የጀመረው ሙሐመድ ተላልፎ ካልተሰጠን በስተቀር ከማንም ጋር ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ግንኙት እንዲያደርግ አይፈቀድለትም” ተብሎ ለሁለት ዓመታት ያህል ነብዩ በተገኙበት የበኒ ሐሺም ቤተሰብ ላይ ማዕቀብ ተጥሏል፡፡ የነቢዩ ቤተሰብም “ሙሐመድን አሳልፈን አንሰጥም” በማለት እቀባው እስኪነሳለት ድረስ ከመካ ከተማ ተሰዶ ለመኖር ተገዷል፡፡ በርሳቸው ተከታዮች ላይ የደረሰው ሰቆቃና ችግር ደግሞ በቀላሉ አይነገርም፡፡ በተለይ ደካሞችና ተከላካይ ያልነበራቸው እንደ አማር ቢን ያሲር እና ወላጆቹ፣ ኢትዮጵያዊው “ቢላል”፣ ወዘተ… የመሳሰሉት የሰቆቃና የስቃይ መሞከሪያ ሆነው ነበር ለማለት ይቻላል፡፡ ይህ ስቃይ ሲባባስ ነው ነብዩ ግማሾቹን ተከታዮቻቸውን በስውር ወደ ኢትዮጵያ የሰደዱት፡፡ በመጨረሻም ነቢዩና ተከታዮቻቸው በሙሉ ከመካ ወደ መዲና ለመሰደድ የበቁት ከቁሬይሽ መኳንንቶች ከሚመጣባቸው ጥቃትና በደል ለመሸሽ ሲሉ ነው፡፡
  የነቢዩ ጠላቶች ግን እዚያም አላረፉላቸውም፡፡ “ሙሐመድ ሀይል ገንብቶ እኛን ከማጥፋቱ በፊት እዚያ ሄደን ልናጥፋው ይገባናል” በማለት የክተት አዋጅ አውጀው እስከ መዲና ድረስ ሄዱላቸው፡፡ በዚህን ጊዜ ነው አላህ በቅዱስ ቁርኣን “ለነዚያ በእምነታቸው ምክንያት አላግባብ ለተፈተኑት ሙስሊሞች መዋጋት ተፈቀደላቸው” በማለት ጠላቶቻቸውን በጦርነት እንዲዋጉዋቸው መንገዱን ያሳያቸው፡፡ “ጂሃድ” (ተጋድሎ) የተሰኘው ጽንሰ-ሐሳብም ያኔ ነው የተፈጠረው፡፡
  “ጂሃድ” ቃሉ ራሱ እንደሚያመለክተው “ትግል” ወይንም “ተጋድሎ” ማለት ነው፡፡ ሐቀኛ ሰው ሐቁን ላለማስደፈር የሚያደርገው ትግል ነው በዚህ ስም የሚጠራው፡፡ አንድን ውጥን ከግብ ለማድረስ የሚደረግ ርብርብም “ጂሃድ” ሊባል ይችላል፡፡ ሀጢአተኛ ሰው ነፍሱን ከሐጢአት ለማጽዳት የሚያደርገው ትግልም ጂሀድ ነው፡፡ ነገር ግን አንዳንዶች አላግባብ “ቅዱስ ጦርነት” እያሉ ይፈቱታል፡፡ ፍቺውን ሲያሰፉትም “እስልምናን ለማስፋፋትና በሸሪዓ የሚተዳደር መንግሥት ለመመስረት የሚደረግ ጦርነት ነው” ይላሉ፡፡ ስህተት ነው፡፡ በጣም ስህተት! ጦርነት በባህሪው አውዳሚ ነው፡፡ የትኛውም ጦርነት “ቅዱስ” ሊባል አይችልም፡፡ የትኛውም ሀይማኖት ጦርነትን “ቅዱስ ነው” ብሎ አይባርክም፡፡ ነቢዩ ሙሐመድም ጦርነትን፣ ሁከትና ብጥብጥን አውግዘዋቸዋል፡፡
  ይሁንና አንተ የማታውቀው ጠላትህ አንተን አጥፍቶ ሀገርህን ሊወርስብህ ሲመጣብ ቆመህ አትጠብቀውም፤ የራስህን ሀይማኖት ትተህ የርሱን እምነት እንድትከተል ሲወጋህም በዝምታ አትመለከተውም፡፡ ያኔ በምትችለው መንገድ ሁሉ ትዋጋዋለህ፤ ቢቻል በዲፕሎማሲያዊ መንገድ እንዲመለስ ታደርገዋለህ፤ እምቢዮው ካለ ግን በሚገባው የጦርነት ቋንቋ ታናግረዋለህ፡፡ “ጂሃድ” የሚባለውም እንዲህ ዐይነቱ ፍትሐዊ ትግል ነው፡፡
    ለሀገርህ፣ ለህዝብህና ለሀይማኖትህ የምታደርገው ተጋድሎ በሰላማዊ መንገድ ካልተቋጨ ብቻ ነው የጦርነትን አማራጭ የምትከተለው፡፡ ታዲያ ጦርነቱን የምታከናውነው እንዲሁ በዘፈቀደ አይደለም፡፡ ለ“ጂሃድ” ስትሰለፍ በማንኛውም መልኩ ገደቡን አታልፍም፤ አንተን በቀጥታ ከሚወጉት ውጪ ሌሎችን አታጠቃም፤ በጦርነቱ ውስጥ የሌለውን ሰላማዊ ህዝብ አትነካም፡፡ በተለይም በጦርነት እሳት ቀዳሚ ተጠቂ በሆኑት ህጻናት፤ ሴቶችና አረጋዊያን ላይ በጭራሽ እጅህን አታነሳም፤ በማሳ ላይ ያለ አዝመራ፣ በበረት ውስጥ ያሉ ከብቶች፣ ህዝብ የሚጠቀምበት የጉድጓድ ውሃ፣ መስጊድ፣ ቤተክርስቲያን፣ ምኩራብ (የአይሁድ ቤተ-ጸሎት) ወዘተ… አታጠቃም፡፡ እነዚህን እያጠፋህ “ጂሃድ እያካሄድኩ ነው” ብትል በእስልምና ሚዛን አንድም ተቀባይነት አታገኝም፡፡
*****
ለ“ጂሀድ” የወጣ ጦር ከውጊያ ሜዳው ከደረሰ በኋላ እንኳ ውዝግቡ በሰላም እንዲያልቅ የሚቻለውን ጥረት ያደርጋል፡፡ የሰላሙ ጥረት መፍትሔ ካላገኘ ብቻ ነው ወደ ውጊያ የሚገባው፡፡ ለምሳሌ ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) በህይወት ዘመናቸው 27 ዘመቻዎችን አድርገዋል፡፡ ከነዚህ ዘመቻዎች መካከል ውጊያ የተደረገው በስምንቱ ብቻ ነው፡፡ አስራ ዘጠኙ ዘመቻዎች ያለ አንዳች ጦርነት ነው የተጠናቀቁት፡፡
  ከዚህ ሌላም ሁኔታዎች አስገደድውት በጦርነት ውስጥ የገባ “ሙጃሂድ” (ታጋይ) ጦርነቱ እንዳይራዘም እና አውዳሚ ባልሆነ መልኩ እንዲጠናቀቅ የተለያዩ ዘዴዎችን መጠቀም ይኖርበታል፡፡ ለምሳሌ ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) በመዲና ዙሪያ ምሽግ በመቆፈር በአምስት እጥፍ የሚበልጣቸው የአህዛብ ሰራዊት በፍርሐት ተርበድብዶ እንዲመለስ አድርገውታል፡፡ እንዲሁም ደግሞ በስምንተኛው ዓመተ-ሂጅራ የመካ ከተማን በአነስተኛ ውጊያ (13 ሰው ብቻ የሞተበት) ለመቆጣጠር የቻሉት ሰራዊታቸውን በአራት አቅጣጫዎች በማሰማራት ከተማዋን ለመክበብ በመቻላቸው ነው፡፡ በዚህም በመካ ከተማ ላይ አንድም ውድመት እንዳይሰከት ለማድረግ ችለዋል፡፡
     በጂሃድ ውስጥ ሌላው ውግዝ ተግባር ደግሞ ጦርነትን በጠቅላላ ድምሰሳ (total destrcuction) ስልት ለማሸነፍ መሞከር ነው፡፡ የጠላትን ሀይል በሚቻለው ዘዴ ሁሉ ለማንበርከክ እስከ መጨረሻው ድረስ መታገል ይቻላል፡፡ ይህ ዘዴ ግን ከተዋጊው ውጪ በጦርነቱ ውስጥ ባልተሳተፈው ሲቪል ህዝብ ላይ አደጋ የሚያደርስ መሆን የለበትም፡፡ አንድን ከተማ መቆጣጠር ሲያቅትህ በጅምላ ጥቃት ከተማዋን ማውደም በጭራሽ ከ“ጂሃድ” አይቆጠርም፡፡
  ለምሳሌ ነቢዩ ሙሐመድና ተከታዮቻቸው “ሐዋዚን” ከሚባለው የዐረብ ጎሳ ተዋጊዎች ጋር ውጊያ ገጥመው አሸንፈውታል፡፡ በጦርነቱ የተሸነፉት የሀዋዚን ተዋጊዎች “ጧኢፍ” በምትባለው ከተማ መሸጉ፡፡ ነቢዩ ጣኢፍን ለበርካታ ቀናት ከበቡ፤ የሀዋዚን ተዋጊዎችም እጃቸውን እንዲሰጡ ጠየቁ፡፡ ባላንጣዎቻቸው ግን አምቢኝ አሉ (ጣኢፍ በዘመኑ ሉአላዊነት ያላት የከተማ መንግሥት ነበረች)፡፡ ይባስ ብሎም በከተማዋ ግንቦች ጫፍ ላይ ሆነው በነቢዩና በተከታዮቻቸው ላይ ልዩ ልዩ የባለጌ ስድቦችን ያወርዱ ጀመር፡፡ ይሁንና ነቢዩ በምላሹ ተናድደው የጧኢፍ ከተማዋን አላወደሟትም፡፡ የሀዋዚን ተዋጊዎችን እንቅስቃሴ በዐይነ ቁራኛ የሚጠብቅ ጦር በከተማ አቅራቢያ መድበው ለራሳቸው በክብር ወደ መዲና ተመለሱ፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ደግሞ እዚያ የመደቡትን ጦር አስነሱ፡፡ ከዓመት በኋላ በጦርነት ያልተቻሉት የሀዋዚን ተዋጊዎች በራሳቸው ፈቃድ እጅ ሰጡ፡፡ ሁሉም በፍላጎታቸው እስልምናን ተቀበሉ፡፡
   ይህ የነቢዩ አድራጎት ያስገርማል፡፡ “ጧኢፍ” ነቢዩ በመልዕክተኛነት ከተላኩ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ስደትን የሞከሩባት ከተማ ናት፡፡ ነቢዩና ጥቂት ተከታዮቻቸው ወደ ከተማዋ ደርሰው ነዋሪቿ እስልምናን እንዲቀበሉ ጠየቋቸው፤ በከተማዋ ለመኖር እንዲፈቀድላቸውም ለመኑ፡፡ የጧኢፍ ነዋሪዎች ግን ነቢዩን የድንጋይ ውርጅብኝ አከናነቧቸው፤ ጧኢፍ ውስጥ የነበሩ ህጻናትና ታዳጊዎች ተሰባስበው ያንን አሰቃቂ ትርኢት በጩኸትና በዘፈን አዳመቁት፡፡ የትኛውም ከተማ ነቢዩን በእንደዚያ ዓይነቱ ወራዳ ምግባር አላስተናገደም (በመካ ከተማ ካዩት ስቃይና ሰቆቃ በስተቀር)፡፡ ከአስር ዓመታት በኋላ ያቺ ከተማ በነቢዩና በተከታዮቻቸው ተከበበች፡፡ በከተማዋ የመሸጉት የሀዋዚን ተዋጊዎች አስነዋሪ ስድቦችን እየተሳደቡ ተፈታተኗቸው፡፡ ይሁንና ነቢዩ የጥንቱን የድንጋይ ወገራ ትዝታቸውን ከሀዋዚን ጦረኞች ስድብ ጋር በመደመር ከተማዋን አላጠፏትም፡፡ በራሷ ጊዜ ከእጃቸው እንደምትገባ በመተማመን ወደ መናገሻ ከተማቸው ተመለሱ፡፡ በዚያ ዘመን የነበረ ሌላ መሪ እንዲህ ሲያደርግ አልታየም፡፡ አንድ ከተማ እጅ አልሰጥም ካለች ከተማዋን ማውደም ነው እንጂ ጦሩን ይዞ ወደ ኋላ መመለስ በዚያ ዘመን አይታወቅም፡፡ ሰውዬው ግን ነቢይ ነውና  ለ“ጠቅላላ ድምሰሳ” (total destrcuction) አልቸኮለም፡፡  የኢራቅ ጽንፈኛ ሚሊሻስ?…. አሜሪካስ?…. እስራኤልስ?.. አል-ሸባብስ?… ሂትለርስ?… ሁሉም በጠቅላላ ድምሰሳ (total destrcuction) ስልት ያምናሉ፡፡
*****
“ጀሃድ” በትንኮሳ የሚፈጸምም አይደለም፡፡ ሌሎች ሳይደርሱብህ የሰው ሀገርና ድንበር ወርረህ “ለእስልምና ነው የምዋጋው” ማለት የለም፡፡ በቅዱስ ቁርኣን በተጻፈውም ሆነ ነቢዩ በአንደበታቸው ባስተማሩት መልዕክት ውስጥ “እንዲሁ ከመሬት ተነስህ ሌሎችን ተዋጋ” የሚል ነገር አናነብም፡፡ እያንዳንዱ እርምጃህ የመነሻ ምክንያት ሊኖረው ግድ ይላል፡፡ ነቢዩ ያካሄዷቸው ዘመቻዎች በሙሉ በቂ ምክንያቶች ነበሯቸው፡፡ ጠላቶቻቸው ከተነኮሷቸው በኋላ ነው ነቢዩ ለጂሃድ የወጡት (ሰ.ዐ.ወ)፡፡ በኋለኞቹ ሁለት ዓመታት ውስጥ የተደረጉት ዘመቻዎች ደግሞ ነቢዩ ዐረቢያ ማዕከላዊ መንግሥት መሪነታቸው የሀገሩን ጸጥታና ዳር ድንበር ለማስከበር ያካሄዷቸው ናቸው እንጂ ውጊያ በመሻት የተደረጉ አልነበሩም፡፡
      ከነቢዩ ህልፈት በኋላ የነቢዩ ተከታዮች ከፋርስና ከሮማዊያን ጋር ያኳሄዷቸው ጦርነቶች ብዙ መነሻዎች ነበሯቸው፡፡ ከጀርባቸው የነበረው ዋነኛ ምክንያት ግን አንድና አንድ ብቻ ነው፡፡ ይህም ሮማዊያንና ፋርሶች ከዐረቢያ የተነሳውን አዲስ ሀይል በቅኝ ግዛቶቻቸው ላይ የተጋረጠ አደጋ አድርገው መውሰዳቸው ነው፡፡ በዚህም የተነሳ ሁለቱም ሀይሎች የነቢዩን መንግሥት በስውርና በግልጽ ውጊያ ሊያጠፉት ሞክረዋል፡፡ ይሁንና አዲሱ ሀይል የሚበገርላቸው አልሆነም፡፡ ሮማዊያንንና ፋርሶችን በከፍተኛ ወኔ እየተዋጋቸው ከያዟቸው የእስያ፣ የመካከለኛው ምስራቅና የሰሜን አፍሪቃ (ስፔንን ጨምሮ) ቅኝ ግዛቶች በሙሉ አባሮአቸል፡፡ ከነዚህ ቄሳራዊ ቅኝ ገዥዎች የነጠቃቸውን ግዛቶች በአዲስ የኸሊፋ መንግሥት ስር አጠቃሎአቸዋል፡፡ የሮም መንግሥት በደንበኛው መሬቱ (hinterland) ላይ ከተገደበ በኋላ ከሙስሊሞች ጋር በጉርብትና የመኖር ፖለሲን ስለተከተለ ከርሱ ጋር የሚደረገው ጦርነት ቆሟል፡፡ የፋርሶች መንግሥት ግን በጄ አላለም፡፡ በሙስሊሞች ላይ ትንኮሳ መፈጸሙንና ከተሞችን ማውደሙን ስለቀጠለ ውድቀቱን በራሱ እጅ አፋጥኗል፡፡
*****
የጅሃድ እስላማዊ ግንዛቤ ይህ ነው፡፡ በትክክል ጂሃድ ማድረግ ማለት እንዲህ ነው፡፡ አላህ ታጋዮችን ሊረዳቸው ቃል የገባው ይህንን መርህ ተከትለው የታገሉ እንደሆነ ነው፡፡ ነቢዩንና ተከታዮቻቸውን “አንድ ከልቡ የሚታገል ሙጃሂድ ለአስር ጠላቱ ይበቃል” በማለት ያወደሳቸው በዚህ መመሪያ መሰረት ይታገሉ ስለነበር ነው፡፡ ጥቂቶች ሆነው በብዙ እጥፍ የሚበልጧቸውን የሮምና የፋርስ የጦር ሀይሎችን ለማሸነፍ የበቁት ሐቁን ይዘው በወኔና በቆራጥነት ስለተዋጓቸው ነው፡፡
  የዘመናችን ጽንፈኛ ሀይላት ከዚህ መርህ ጋር በጭራሽ የሚተዋወቁ አይደሉም፡፡ ለጂሃድ የጨፈገገ ትርጓሜ እየሰጡት በአሉታዊ መልኩ እንዲታይ አድርገውታል፡፡ ቅዱስ ቁርአንንና የነቢዩን ሐዲሶች እንዳሻቸው እየተረጎሙ የድብቅ ፍላጎታቸው ማስፈጸሚያ ያደርጉአቸዋል፡፡ በሴፕቴምበር 11/2001 እንደታየው አውሮፕላኖችን እየጠለፉ በሺህ የሚቆጠሩ ንጹሐንን ይፈጃሉ፡፡ በህዝብ ማጓጓዣ ባቡሮችና አውቶቡሶች ላይ ቦንብ ያጠምዳሉ፡፡ የመኖሪያ ህንጻዎችን በፈንጂ ያጋያሉ፡፡ እንደ ሶማሊያው አል-ሸባብ የአንድ አባት ልጆችን ያጋድላሉ፡፡ እንደ ቦኮ-ሀራም በምንም ውስጥ የሌሉ ሴቶችን እየጠለፉ መደራደሪያ ያደርጉአቸዋል፡፡ አልፎ ተርፎም የነርሱን ድርጊት የማይደግፈውን “ሙስሊም አይደለህም” እያሉ ይረሽኑታል፡፡ ይህ ነው እንግዲህ ጽንፈኝነት ማለት!
  ነቢዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ዓይነት ጽንፈኛ ቡድኖች ወደፊት እንደሚነሱ ተንብየዋል፡፡ የጽንፈኝነቱ የመጀመሪያው ምልክትም በኸሊፋ ዑመር (ረ.ዐ) ዘመን ታይቷል፡፡ ከዚያም የዑስማን መንግሥት በነዚህ ጽንፈኞች ታውኳል፤ ኸሊፋ ዑስማንም በነርሱ እጅ ተገድለዋል፡፡ በኸሊፋ ዓሊ ዘመን ደግሞ ጽንፈኞቹ ለይቶላቸው ከኸሊፋቸው ጋር በግልጽ ተዋግተዋል፤ ከኸሊፋው ጋር የቆሙትንም “ከእስልምና የወጡ ካፊሮች” በማለት ፈርጀዋቸዋል፡፡ በመጨረሻም የዓሊ ህይወት በነርሱ እጅ ጠፍቷል፡፡
   በዚህ ዘመን የተነሱት ጽንፈኞችም የነዚያዎቹ ተከታዮች ናቸው፡፡ ነገር ግን ክርር ያለው አካሄዳቸው ለየትኛውም ሰው ስለማይመች ተቀባይነት አያገኙም፡፡ በተጨማሪም ከክር የቀጠነው ጽንፈኝነታቸው አንድነታቸውን ጠብቀው እንዲሄዱ አያስችላቸውም፡፡ በታሪክ እንደታየው እንዲህ ዓይነት ቡድኖች በጥቂት ዓመታት ውስጥ በብዙ ቡድኖች ተፈረካክሰው እርስ በረስ መባላት ይጀምራሉ፡፡ በዓሊ ዘመን የተነሱት የ“ኸዋሪጃ” ጽንፈኞች ተፈረካክሰው እንደጠፉት ሁሉ በሌሎች ዘመናት የተነሱ ጽንፈኞችም ራሳቸውን በራሳቸው ያጠፋሉ፡፡ የአሁኖቹም መንገዳቸው ይኸው ነው፡፡

===ጽንፈኞችና ሽብር===

ቀደም ብዬ እንደገለጽኩት ለጂሃድ የወጣ ሰው የሚዋጋው መሳሪያ ታጥቆ ለውጊያ ከተሰለፈ ሀይል ጋር ነው፡፡ በውጊያው ውስጥ ባልተሰለፉ ሲቪል ዜጎች ላይ ጥቃት ማድረስ በፍጹም አይፈቀድለትም፡፡ የዘመናችን ጽንፈኞች ግን ከዚህ መርህ ጋር የሚተዋወቁ አልሆኑም፡፡ ዓላማቸውን ለማሳካት የሚጠቀሙበት ዋነኛ ዘዴ ሽብር ፈጠራ ነው፡፡ ጽንፈኞቹ በሚያደርሱት ጥቃት የሚሸበሩትም ሆኑ የሚሞቱት በአብዛኛው ሲቪሎች ናቸው፡፡ ንጹሐንን እየቀጠፉ ነው “ለእስልምና ነው የምንታገለው” የሚሉት፡፡
እስልምና ግን እንዲህ የዘቀጠ ርዕዮት አይደለም፡፡ ኢስላም የሰው ልጅ ከየትኛውም ፍጥረት በላይ የተከበረ መሆኑን ነው የሚያስተምረው፡፡ ቅዱስ ቁርኣን “አንዲት ነፍስን ያለ ሐቅ ያጠፋ ሰው በምድር ላይ የሚኖሩ ሰዎችን በሙሉ እንደገደለ ይቆጠራል” ይላል፡፡ ጽንፈኞች በምን ማስረጃ ነው ይህንን ቁርኣናዊ ህግ የሚሞግቱት?… “ለአሜሪካ መንግሥት ታክስ የሚከፍል ሁሉ የእስልምና ጠላት ነው” የሚል ሎጂክ በጭራሽ ኢስላማዊ መሰረት የለውም፡፡ ኢስላም በግልጽ በተደነገገ ህግ ነው የሚተገበረው፡፡ እንደ ኒኮሎ ማኪያቬሊ “ወደ እውነት ለመድረስ በብዙ ውሸቶች ውስጥ መዘፈቅ” ወይንም “ዜጎችን እየጨረሱ ወደ ውጤት መድረስ” የሚል መመሪያ በእስልምና ውስጥ የለም፡፡ ሽብር ምን ጊዜም ቢሆን ሽብር ነው፡፡

==ጽንፈኞችና ብዝሐነት==

የጽንፈኛውን የኢራቅ ሚሊሻ መነሳትን ተከትሎ የዓለም ሚዲያዎችን የተቆጣጠረው ሌላኛው ርዕስ “ሙስሊም ያልሆኑ ወገኖች በግዴታ እስልምናን እንዲቀበሉ ተደርገዋል” የሚል ነው፡፡ ጽንፈኞች ለዚህኛው አድራጎታቸውም “እስልምና እንደዚያ እንድናደርግ አዟል” ይሉናል፡፡ ለመሆኑ ቅዱስ ቁርኣን “ሌሎችን በግዴታ እንዲሰልሙ አድርጉ” ይላል? በፍጹም! ቅዱስ ቁርኣን እንዲህ ነው የሚለው፡፡

لَاۤ اِکۡرَاہَ فِی الدِّیۡنِ ۟ۙ قَدۡ تَّبَیَّنَ الرُّشۡدُ مِنَ الۡغَیِّ

“በሀይማኖት ማስገደድ የለም፤ ቀጥተኛው ጎዳና ቀጥተኛ ካልሆነው በርግጥ ተብራርቷል”
(አል-በቀራህ-266)

ነብዩ እና ተከታዮቻቸው በዘመናቸው የነበሩ የበርካታ እምነት ተከታዮች እምነታቸውን እንዲቀይሩ ያላስገደዱት በዚሁ ቁርአናዊ መመሪያ ስለሚመሩ ነው፡፡ ክርስቲያኖች፣ አይሁዶች፣ ዞራስትሪያኖች (መጁስ)፣ ሳቢኢን (የጥንታዊ የሜሶጶጣሚያ እምነት ተከታዮች)፣ ቂብጢዎች (የጥንታዊ የግብጽ እምነት ተከታዮች)፣ የዚዲዎችና ሌሎችም ከሙስሊሞች ጋር በሰላም ይኖሩ ነበር፡፡ አሁን እንደምንሰማው ቤተክርስቲያንና ምኵራብ ማፍረስም ሆነ ቄስና ካህን መግደል በዚያ ዘመን በጭራሽ አልነበረም፡፡ ጽንፈኞች የሚነዙት ወሬ ከየትኛውም እስላማዊ መመሪያ ጋር አይጣጣምም፡፡
   በዚያ ዘመን ነቢዩና ተከታዮቻቸው በግልጽ የተዋጉት ከአይሁዶች ጋር ነው፡፡ ይህም በሀይማኖታቸው ምክንያት አይደለም፡፡ አይሁዶቹ የመዲና ከተማን ደንብ አክብረው ለመኖር የገቡትን ቃል-ኪዳን አፍርሰው ከነቢዩ ጠላቶች ጋር በመወገን ስለተዋጓቸው ነው፡፡ በዚህም  የተነሳ አይሁዶቹ ለጥፋታቸው ተመጣጣኝ ቅጣት ከፍለው በከተማዋ እንዲኖሩ፤ አሊያም ከተማዋን ለቀው እንዲሄዱ ምርጫ ተሰጣቸው፡፡ ጥቂቶች ቅጣቱን ለመክፈል ተስማማሙ፡፡ አብዛኞቹ ግን ከተማዋን ለቀው ወደ ተቡክ (አሁን ሳዑዲና ዮርዳኖስ ድንበር) ተሰደዱ፡፡
  ነብዩ በሀይማኖት የተነሳ ከክርስቲያኖች ጋር የተጋጩበት የታሪክ አጋጣሚ የለም፡፡ በዑመር (ረ.ዐ) ዘመን ደግሞ አስገራሚ ድርጊት ተፈጽሟል፡፡ በወቅቱ ሙስሊሞቹ ከሮማዊያን ጋር በፍልስጥኤም ምድር እየተዋጉ ነበር፡፡ ሙስሊሞቹ አሸንፈው ከተማዋን በያዙበት ቀን ዑመር ሳይጠበቁ ወደ ከተማዋ መጡ፡፡ እኚህ መሪ የትልቅ ግዛት ገዥ ሆነው በመናኛ አለባበስ፣ ያለ አንዳች አጃቢ ወደ ከተማዋ በመግባታቸው ብዙዎች ተደነቁ፡፡ ከሁሉም በላይ በድርጊቱ የተደነቁት ግን የእየሩሳሌም ፓትሪያርክ ነበሩ፡፡ ፓትሪያርኩ “ የሙስሊሞቹ መሪ ይህ መናኛ ልብስ የለበሰ እና አጃቢ የሌለው ሰውዬ ከሆነ በርግጥም ይህ ሰው ቅዱስ ነው” በማለት ደመደሙ፡፡ በመሆኑም ዑመር ከቤተ ክርስቲያናቸው ገብተው በሙስሊሞቹ ስርዓት “ሰላት” እንዲሰግዱ ጋበዟቸው፡፡ ዑመርም ግብዣውን ተቀበሉ፡፡ ነገር ግን ከቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ ሳይገቡ በቅጥረ-ግቢው ውስጥ “ሁለት ረከዓ” ሰላት ሰገዱ፡፡ (ዑመር ይህንን ያደረጉት ሙስሊሞች ወደፊት “ዑመር የሰገደበት ቤተክርስቲያን ለኛ የተገባ ነው” የሚል ውዝግብ ሊፈጥሩ ይችላሉ በሚል ምክንያት ነው እንጂ ወደ ውስጥ መግባቱን ጠልተውት አይደለም” )፡፡
*****
ሙስሊሞች፣ ክርስቲያኖች፣ አይሁዶችና ሌሎችም የሃይማኖት ቡድኖች ከዚያ ዘመን ጀምሮ ለብዙ ዘመናት በጉርብትና አብረው ኖረዋል፡፡ የኦቶማን ቱርኮች ኢምፓየር እስከፈረሰበት ድረስ በሙስሊሞች የበላይነት በተመራው ኢስላማዊ ኸሊፌት ውስጥ ክርስቲያኖችም ሆኑ አይሁዶች ሀይማኖታቸውን በግዳጅ እንዲቀይሩ የተደረገበት ዘመን የለም፡፡
  አዳዲሶቹ ጽንፈኞች ግን ከነብዩ ዘመን አስቀድሞ በመካከለኛው ምስራቅ የሚኖሩ የልዩ ልዩ እምነት ተከታዮች ሀይማኖታቸውን እንዲቀይሩ ያስገድዱአቸዋል፡፡ እንዲህ ዓይነት ትምህርት ከእስልምና ጋር ሆድና ጀርባ ነው፡፡ እስልምና እንደዚህ ዓይነት ርዕዮት ያለው ቢሆን ኖሮ በዛሬዋ ኢራቅ ምድር ከአስር የሚበልጡ ጥንታዊ የሀይማኖት ቡድኖች ባልተገኙም ነበር (ከነዚህ ቡድኖች መካከል አንዳንዶቹ ከጥንቱ የሀሙራቢ ዘመን የተረፉ ናቸው)፡፡

==ጽንፈኞች እና ዘመናዊነት==

እነዚህ ጽንፈኞች እስልምና ኋላቀር እምነት ተደርጎ እንዲታይ የሚፈልጉ አሻጥረኞችም ይመስላሉ፡፡ በየትኛውም ሀገር ሲነሱ በቅድሚያ የሚፈጽሟቸው ሁለት ነገሮች አሉ፡፡ አንደኛው በጥንት ዘመናት የተሰሩ ታሪካዊ መዘክሮችንና ቅርሶችን ማውደም ነው፡፡ ሁለተኛው ዘመን ያፈራቸውን የቴክኖሎጂ ትሩፋቶች እርም ማድረግ ነው፡፡ ለዚህም የሚጠቅሱት ምክንያት “በእስልምና ያልተፈቀዱ ናቸው” የሚል ነው፡፡ ይሁንና የእስልምና አስተምህሮ ከነዚህ ጽንፈኞች አባባል ጋር በጭራሽ አይገጣጠምም፡፡ እስቲ በምሳሌዎች ላስረዳ፡፡
  “ጣሊባን” የተባለው ጽንፈኛ ቡድን እ.ኤ.አ በግንቦት ወር 2001 በአፍጋኒስታን ምስራቃዊ ክፍል የነበሩ ሁለት የቡድሃ ሀውልቶችን በታንክ ደምስሷል፡፡ ለእርምጃው የሰጠው ምክንያት “ሀውልት በእስልምና የተከለከለ ነው” የሚል ነው፡፡ በርግጥ በሰው ልጅ አምሳል ሀውልት ማቆም በእስልምና አይፈቀድም፡፡ ይሁንና እስልምና “አዲስ ሀውልት ለራሳችሁ አትገንቡ” ነው የሚለው እንጂ “በጥንት ዘመን የተገነቡ  ሀውልቶችን አፍርሱ” የሚል ትእዛዝ አላስተላለፈም፡፡ እንደዚያ ቢሆን ኖሮ በግብጽ፣ በሶሪያ፣ ኢራቅ (ሜሶጶጣሚያ)  እና ኢራን (ፋርስ) የሚታዩትን በሺህ የሚቆጠሩ ሀውልቶችን በዛሬው ዘመን በቁማቸው ባለገኘናቸው ነበር፡፡
  አዎን! እስልምና ወደነዚህ ሀገራት የገባው ነቢዩ “እጅግ ምርጥ ትውልድ” ባሉት በመጀመሪያው የሰሐባ ትውልድ ዘመን ነው፡፡ ሰሐባዎቹ በግብጽ ያሉትን ፒራሚዶች፣ ቤተ-መቅደሶች፣ ስፊኒክሶችና ልዩ ልዩ ሐውልቶች (ታላቁን የራምሰስ ሀውልትን ጨምሮ) “ንክች” አላደረጓቸውም፡፡ በኢራቅና በኢራን የነበሩትንም እንደዚያው፡፡ እነዚያን ጥንታዊ ሀውልቶችንና ቤተመቅደሶችን ማፍረስ በእስልምና የታዘዘ ቢሆን ኖሮ የነቢዩ ሰሐባዎች አንዳቸውንም ሳያስቀሩ ድምጥማጣቸውን ባጠፏቸው ነበር፡፡ ይሁንና ሰሓቦች እንደ አሁኖቹ ጽንፈኞች አዕምሮ ቢስ አልነበሩም፡፡ እነዚያ ጥንታዊ ግንባታዎች በልዩ ልዩ የዘመን ፈተናዎች ውስጥ አልፈው ወደነርሱ ዘመን እንደተሸጋገሩ ይረዳሉ፡፡ ስለዚህ አንድም ዓይነት የማጥፋት ሙከራ ሳይፈጽሙባቸው ጥንት እንደነበሩት ተዋቸው፡፡
  የዘመናችን ጽንፈኞች ሌላው መታወቂያ ዜጎች ዘመን ባፈራቸው የቴክኖሎጂ ውጤቶችና ቀልጣፋ አሰራሮች እንዳይጠቀሙ መከልከል ነው፡፡ ጽንፈኞቹ በዚህ አስተሳሰባቸው በጥንታዊ ጋርዮሽ ዘመን ከነበረ ሰው ጋር እንኳ የሚወዳደሩ አይደሉም፡፡ በጣም ልብ የሚነካው እስልምና በነዚህ ቴክኖሎጂዎችና ውጤታማ አሰራሮች መጠቀምን የሚከለክል አድርገው መለፈፋቸው ነው፡፡  “እግር ኳስ ለምን አየህ” በሚል ምክንያት ዜጎችን በጅራፍ መግረፍን የመሳሰሉ ቅጣቶችንም ይፈጽማሉ፡፡
  እስልምና አዳዲስ የቴክኖሎጂ ውጤቶችና በተቀላጠፈ አሰራር መጠቀምን ይከለክላል?… በጭራሽ!! ነቢዩ እንዲህ ዓይነት ትምህርት በጭራሽ አላስተማሩም፡፡ አላህ በቅዱስ ቁርኣን እርም ካደረጋቸው ድርጊቶችና መጠቀሚያዎች ውጪ ነቢዩ እርም ያደረጉት የተለየ ነገር የለም፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ነቢዩና ተከታዮቻቸው ድሮ የማያውቁት አዲስ ፈጠራ ወይንም አዲስ አሰራር እንዳለ ሲነገራቸው በስራ ላይ በማዋል አንደኛ እንደነበሩ የህይወት ታሪካቸው ያስረዳል፡፡ ለምሳሌ ያህል እነዚህን መጥቀስ እንችላለን፡፡
·        ነቢዩ በዘመናቸው ለነበሩት ነገሥታት ደብዳቤ መጻፍ አስፈለጋቸው፡፡ አንዱ ባልደረባቸው “ደብዳቤው ከርስዎ የተላከ መሆኑን የሚያረጋግጥ ማህተም ያስፈልግዎታል፤ ማህተም ቢያስቀርጹ መልካም ይመስለኛል” አላቸው፡፡ ነቢዩ የማህተም አስፈላጊነት ሲነገራቸው እምቢ አላሉም፡፡ ሃሳቡን ወዲያውኑ ተቀብለው አዲስ ማህተም አስቀረጹ፡፡
·        የቁሬይሽ ተዋጊዎች በመዲና ላይ ሶስተኛ ዙር ወረራ ሊፈጽሙ ተነሱ፡፡ ከቁሬይሾች ጋር በርካታ ማህበረሰቦች ማበራቸውም ተሰማ፡፡ ይህም ወሬ ለነቢዩ ደረሳቸው፡፡ ነቢዩ በጉዳዩ ላይ ከባልደረቦቻቸው ጋር ሲወያዩ ሳልማን አል-ፋርሲ የሚባለው ባልደረባቸው “በከተማችን ዙሪያ ምሽግ ብንቆፍር ጠላቶታችንን በቀላሉ መመለስ እንችላለን” አላቸው፡፡ ሳልማን የፋርስ (ኢራን) ተወላጅ ነው፡፡ በሀገሩ ሲደረግ ያየውን ነው ለነቢዩ የነበረው፡፡ እስከዚያ ጊዜ ድረስ “ምሽግ” በዐረቦች ዘንድ የማይታወቅም ነበር፡፡
በመሆኑም ነቢዩ ምሽግ በመቆፈሩ ብልሃት ተገረሙ፡፡ በተግባር ላይ ሊያውሉትም ተነሱ፡፡ የመዲና ከተማን ከዳር እስከ ዳር በምሽግ ቁፋሮ አጠሯት፡፡ የመካ ቁረይሾች እየፎከሩ ወደ መዲና ሲመጡ ምሽጉ ገደባቸው፡፡ በፈረስና በእግር እየዘለሉ ምሽጉን ለማለፍ ቢሞክሩም ምንም አልተሳካላቸውም፡፡ ይህ ሁኔታ ሌሊቱን ከጣለው ከባድ ዝናብ ጋር ተዳምሮ በጣም አስፈራቸው፡፡ በመሆኑም እቃቸውን እንኳ በወጉ ሳይሰበስቡ ወደመጡበት ፈረጠጡ፡፡
·        በርካታ መልዕክተኞች ወደ ነቢዩ ዘንድ ይመጡ ነበር፡፡ ታዲያ አንዱ የነቢዩ ባልደረባ “ንጉሦችና የጦር መሪዎች መልዕክተኞችን በሚቀበሉበት ጊዜ የአዘቦት ልብሳቸውን አይለብሱም፤ ለየት ያለ ልብስ ለብሰው በርሱ ላይ ካባ ይደርባሉ” አላቸው፡፡ ነቢዩም ምክሩን ተቀብለው በተግባር ላይ አውለውታል፡፡
·        በኸሊፋ ዑመር ጊዜ ታሪኮችን መመዝገብ ተጀምሮ ነበር፡፡ ታሪክ የሚመዘገብበት የቀን መቁጠሪያ ደግሞ በዐረቦች ዘንድ አይታወቅም፡፡ በመሆኑም ዑመር የነቢዩ ስደት (ሂጅራ) እንደ መነሻ ሆኖ እንዲያገለግል ውሳኔ አስተላለፉ፡፡ ይህም ተግባራዊ ሆኖ እስከ አሁኑ ዘመን ድረስ እየተሰራበት ይገኛል፡፡
·        አምስተኛው ኸሊፋ ሙአዊያ ኢብን አቡ-ሱፍያን ደግሞ በተማከለ አሰራር ደብዳቤዎችን ከግለሰቦች ተቀብሎ የሚያከፋፍል ተቋም በመመስረት በዓለም ታሪክ አዲስ አሰራር አስተዋውቀል፡፡ ዛሬ “ፖስታ ቤት” የሚባለውን ተቋም የፈጠሩት ኸሊፋ ሙአዊያ (ረ.ዐ) ናቸው፡፡
·        ዛሬ ዓለም በሙሉ የሚጠቀምበት “የሂንዱ-ዐረብ” የቁጥር ዘዴ የመጨረሻ ቅርጹን ያገኘው በሙስሊሞች አማካኝነት ነው፡፡ ከዚህም ባሻገር ለሂሳብ አቆጣጠር የሚያመቸው “የዜሮ ጽንሰ ሃሳብ” የተፈለሰፈው በ8ኛው ክፍለ ዘመን በባግዳድ ከተማ ነው፡፡
·        የሳይንስና የምርምር ዘርፍ ከፍተኛ እመርታ እንዲሳይ ያደረጉትን አል-ጀብራ፣ አልጎሪዝም እና ሎጋሪዝም የተሰኙ የሂሳብ ስልቶችን የፈጠረው ሙሐመድ ኢብን ሙሳ አል-ኸዋሪዝሚ የተባለ ሙስሊም ሳይንቲስት ነው፡፡
·        ሌላም ብዙ ብዙ መዘርዘር ይቻላል፡፡

እነዚያ የጥንት ሙስሊሞች በአዳዲስ ፈጠራዎች ከመጠቀም አልፈው ለራሳቸውም ልዩ ልዩ ፈጠራዎችን አስተዋውቀዋል፡፡ በአዳዲስ ፈጠራዎች መጠቀም “ውግዝ” ቢሆን ኖሮ ነቢዩና ባልደረቦቻቸው “እርም፤ ነው አትጠጉት” በማለት ክልከላ ያስቀምጡበት ነበር፡፡ ይሁንና የዘመናችን ጽንፈኞች እንዲህ ዓይነቶቹን ታሪኮች ያነበቧቸው አይመስሉም (በጣም የሚያስቀው ነገር ለራሳቸው በዘመናዊ ጠመንዣዎችና በኢንተርኔት ይጠቀማሉ፣ ሌሎችን ግን ከመጠቀም ያግዳሉ)፡፡
 ይህ በፈጠራዎች የመጠቀም ጉዳይ ከተነሳ ዘንድ ግን አንድ ነገር መታወቅ አለበት፡፡ ይኸውም በጥቅም ላይ የሚውለው አዲስ ፈጠራና አሰራር የአላህ ክልከላ ያደረገበትን ድንበር ማለፍ የሌለበት መሆኑ ነው፡፡ ለምሳሌ ማንኛውም የእስልምና ሙፍቲ “አስካሪ መጠጥ ለጤና ይጠቅማችኋል፣ ድንበር ሳታልፉ ጠጡ” በማለት ውሳኔ መስጠት አይችልም፡፡ ቁማርን ህጋዊ ማድረግም በፍጹም አይቻልም፡፡ በሰብዓዊ መብት ስም ግብረ-ሰዶምን ህጋዊ ማድረግም ተቀባይነት የለውም፡፡ ጽንፈኞቹ ግን በነዚህ ላይ ልል አቋም ያላቸው ነው የሚመስሉት፡፡ ለምሳሌ እርግጠኛ ማስረጃ ባይኖረንም ከጽንፈኞቹ መካከል ብዙዎቹ በአደንዛዥ እጽ ንግድ ውስጥ የተዘፈቁ መሆናቸውን እንሰማለን፡፡

===እንደ ማጠቃለያ===

  እነዚህ ጽንፈኞች በየትኛውም ሙስሊም አልተወከሉም፡፡ እስልምናን እንወክላለን ቢሉም ማንም አይቀበላቸውም፡፡ ይሁንና አንዳንድ ሰዎች እስልምናን በነዚህ ጽንፈኞች አድራጎት ሊመዝኑት ይሞክራሉ፡፡ ይህንን ጽንፈኝነት እንደ ሰበብ በመቁጠር እስልምናን ጥላሸት ለመቀባት ይሞክራሉ፡፡ ታዲያ ጽንፈኞቹ እንዲስፋፉ እና እንዲጠናከሩ እያደረጉ ካሉት ምክንያቶች አንዱ የእስልምና ጠላቶች በሀይማኖቱ ላይ የሚያካሄዱት ይህንን የመሰለ የስም ማጥፋት ዘመቻ ነው፡፡ ሙስሊሞችም ሆኑ ሙስሊም ያልሆኑ ምሁራን እንዲህ ዓይነት ምግባሮችን አይተው እንዳላዩ ሆነው ማለፍ የለባቸውም፡፡ በተቻለው መጠን ጽንፈኞቹ የሚፈጽሙት አድራጎት ነቢዩ ያስተማሩትን እስልምና እንደማይወክል ማስረዳት ይገባቸዋል፡፡
በሁለተኛ ደረጃ “ጽንፈኝነት” በሀይማኖት ያልተገደበ ስለመሆኑም መታወቅ አለበት፡፡ ጽንፈኛ ቡድኖች ከየትኛውም ሀይማኖት ሊመነጩ ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ በጥንት ዘመን “Masada” የተሰኘ የአይሁዳዊያን ጽንፈኛ ቡድን ነበር፡፡ ዛሬም በእስራኤል ውስጥ በመቶ የሚቆጠሩ እጅግ ጽንፈኛ ቡድኖች አሉ፡፡ በ7ኛው ክፍለ ዘመን ደግሞ “ኸዋሪጃ” የሚባሉት ጽንፈኞች ከሙስሊሙ ዓለም ተነስተዋል፡፡ በዘመናችንም አል-ሸባብ፣ አል-ቃኢዳ፣ ቦኮ ሀራም የመሳሰሉት ተፈጥረዋል፡፡ ከክርስትናው ዓለምም በ“መስቀል ጦርነት” የሚያምኑ ጽንፈኛ ቡድኖች በተለያዩ ዘመናት ተነስተዋል፡፡ በዘመናችን በሰሜን ኡጋንዳ ጫካዎች ውስጥ መሽጎ ልዩ ልዩ ሰቆቃዎችን የሚፈጽመው Lords Resistance Army የተባለው ሚሊሺያ “ኡጋንዳን በወንጌልና በአስርቱ ትዕዛዛት እመራታለሁ” እያለ የሚለፍፍ ጽንፈኛ ቡድን ነው፡፡ ከሶስት ዓመታት በፊት ከሰማኒያ የሚበልጡ ንጹሃንን የጨፈጨፈው የኖርዌይ ጽንፈኛ ግለሰብም በሃይማኖቱ ክርስቲያን ነው፡፡ በጃፓን ሜትሮ (የምድር ውስጥ ባቡር) ላይ በመርዝ ጋዝ ንጹሃንን የፈጀው የኡም-ሺኖሮኪዮ ሀይማኖታዊ ቡድን “የፈጣሪን ትዕዛዝ” እተገብራለሁ የሚል ጽንፈኛ ነው፡፡ በሀይማኖት የማያምኑ (ማቴሪያሊስቶች፣ ኮሚንስቶች ወዘተ…) ጽንፈኛ ቡድኖችም በልዩ ልዩ ዘመናት ተነስተዋል፡፡ ስለዚህ ጽንፈኞች የትኛውንም ሀይማኖት መጠቀሚያ በማድረግ ሊነሱ እንደሚችሉ መታወቅ ይገባል፡፡ በዚህ ረገድ ሚዲያዎች ወደ አንድ ሀይማኖት ብቻ ጣታቸውን መጠንቆላቸውን በማቆም ሐቁን እየተነትኑ ማስረዳት ይጠበቅባቸዋል፡፡
   በሶስተኛ ደረጃ ደግሞ ጽንፈኞቹ የሚፈጽሙትን አድራጎት በመመልከት ብቻ አሜሪካና አጋሮቿ የሚፈጽሟቸውን ህገ-ወጥ ድርጊቶች የሚያወድሱ ሰዎችም መታረም አለባቸው፡፡ አሜሪካ ለብሄራዊ ጥቅሟ ስትል የምትፈጽማቸው ድርጊቶች ሁሉ በህገ-ወጥነት መታየት አለባቸው እንጂ ጽንፈኞቹ ከሚፈጽሟቸው አድራጎቶች ጋር መተካካት የለባቸውም፡፡ አሜሪካ ኢራቅን መውረሯ መቼም ቢሆን ህገ-ወጥ ነው (የርሷ እርምጃ ነው የአሁኑን ትርምስምስ ያስከተለው)፡፡ እስራኤል ፍልስጥኤምን አላግባብ ይዛ ህዝቡን መጨፍጨፏ መቼም ቢሆን ህገ-ወጥ ነው፡፡ የጽንፈኞችን ነውረኛ ድርጊቶች ተመልክቶ እነዚህን ህገ-ወጥ ስራዎች ማወደስ በምንም መልኩ ተቀባይነት የለውም፡፡ ሁሉም በየራሱ መንገድ መመዘን አለበት፡፡
*****
---
አፈንዲ ሙተቂ
ነሐሴ 7/2006
ገለምሶ-ሀረርጌ
------

ይህ ጽሑፍ የኔ (የጸሐፊው) ወጥ ስራ ነው እንጂ ጥቂት ሰዎች እንደገመቱት “ትርጉም” አይደለም፡፡ ከዚህ በፊት በየትኛውም ቋንቋ አልቀረበም፡፡ ጽሑፉ ብዙዎች ዘንድ እንዲደርስ Share ብታደርጉት ምስጋናዬ እጅግ የላቀ ነው፡፡ በመጽሔትና በጋዜጣ ማሳተምም ይቻላል፡፡ 

Monday, August 11, 2014

ትኩረት-ከውጪ ቋንቋዎች ለተወረሱ ቃላት


ጸሓፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ
--------
የሀገራችን ቋንቋዎች ከውጪ ቋንቋዎች በርካታ ቃላትን ወርሰዋል፡፡ ይህም ከብሉይ ዘመን ጀምሮ ይታይ የነበረ ክስተት ነው፡፡ የመወራረሱ አድማስ ስፋቱን የጨመረው ግን በአስራ ዘጠነኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ ላይ ነው፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በቀጣዮቹ አንድ መቶ ሀያ ዓመታት ውስጥ የታዩት ሀገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ክስተቶች የሀገራችን ቋንቋዎችን ለውጪ ቋንቋዎች ተጽእኖ የበለጠ ክፍት እንዲሆኑ አድርገዋቸዋል፡፡  

  ታዲያ ከሶስት ሺህ ከሚልቁት የውጪ ቋንቋዎች መካከል ለሀገራችን ቋንቋዎች ብዙ ቃላትን ለማውረስ የበቁት አራቱ ብቻ ናቸው፡፡ እነርሱም ዐረብኛ፣ ፈረንሳይኛ፣ ጣሊያንኛና እንግሊዝኛ ናቸው፡፡ የቱርክ እና የጀርመን ቋንቋዎችም ጥቂት ቃላትን ለሀገራችን ቋንቋዎች አበርክተዋል፡፡
*****
   ዐረብኛ በሀገራችን ቋንቋዎች ላይ ተጽእኖ ለመፍጠር የቻለው በዋናነት የእስልምና ሀይማኖት የአምልኮና የትምህርት ቋንቋ ስለሆነ ነው፡፡ በመሆኑም ከእስልምና እምነት ጋር በተያያዘ ለአምልኮና ለትምህርት አገልግሎት ላይ የሚውሉ ቃላት በአብዛኛው ከዐረብኛ የተገኙ ናቸው፡፡ ለምሳሌ መስጊድ/መስጂድ፣ ኢማም፣ ቃዲ፣ አዛን፣ መጅሊስ፣ መድረሳ ወዘተ… የመሳሰሉትን መጥቀስ ይቻላል፡፡ በሂደት ደግሞ የዐረብኛ ቃላት በአምልኮ ውስጥ ካላቸው አስፈላጊነት አልፈው በተራው ሰው ንግግር ውስጥም ገብተዋል፡፡ ይህ ክስተት በስፋት የሚስተዋለው ግን አብላጫው ነዋሪ ህዝብ ሙስሊም በሆነባቸው እንደ ወሎ፣ ሀረርጌ፣ ባሌ፣ ጅማ፣ ሶማሊ (ኦጋዴን)፣ ቤኒሻንጉልና አፋር አካባቢዎች ነው፡፡ በነዚህ አካባቢዎች ከሚነገሩት ቋንቋዎች “መርሐባ”፣ “አሕለን”፣ “ፉጡር”፣ “ሀድራ”፣ “ሙሐባ”፣ “መናም”፣ “ጂስም”፣ “አዛ”፣ “ኩርሲ”፣ “ማዕና”፣ “ዒልም”፣ “አስል” እና ሌሎች በርከት ያሉ የዐረብኛ ቃላትን በቀላሉ ለይቶ ማውጣት ይቻላል፡፡

ታዲያ የዐረብኛ ቃላትን የመውረሱ ተግባር በኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች ብቻ የተገደበ አይደለም፡፡ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በእኩል ደረጃ የሚጠቀምባቸው በርከት ያሉ የዐረብኛ ቃላትንም ወርሰናል፡፡ ይህም ክስተት የተፈጠረው ከንግድ መስፋፋት ጋር ነው፡፡ በተለይ እስከ አስራ ዘጠነኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ ድረስ የሀገራችንን ንግድ በበላይነት ተቆጣጥረው የነበሩት ሲራራ ነጋዴዎች ዐረብኛን በንግድ ቋንቋነት በስፋት ይጠቀሙበት የነበረ ከመሆኑ የተነሳ በሀገራችን ቋንቋዎች ውስጥ መሰረት ያልነበራቸው በርካታ ቃላት እንዲወረሱ ምክንያት ሆነዋል፡፡ ለምሳሌ ዛሬ የአማርኛ ቃላት አድርገን የምንጠቀምባቸው እንደ  ሀዋላ፣ ጉምሩክ፣ ሰንዱቅ፣ ሱቅ፣ መጋዘን፣ ሽርክና፣ ወኪል፣ ሰነድ፣ ደላላ፣ መሃለቅ ወዘተ የመሳሰሉት የአማርኛ ቃላት ምንጫቸው ዐረብኛ ነው፡፡ እንደ ሐዲድ፣ ባቡር እና መኪና የመሳሰሉ ቃላትም ከዐረብኛ ነው የተወረሱት፡፡ ይሁንና ዐረብኛና አማርኛ ሴማዊ ቋንቋዎች በመሆናቸው የሚጋሯቸውን ቃላት እንደ ውርስ ቃላት ማየት ስህተት ነው፡፡ ለምሳሌ ሰላም፣ ደም፣ ቤት፣ ፎቅ፣ ክፍል፣ ዐይን፣ ፈረስ፣ ዘመን፣ ሐሩር፣ ሚዛን የመሳሰሉ ቃላት በሁለቱም ቋንቋዎች ውስጥ አሉ፡፡ ሁለቱም ቋንቋዎች ሴማዊ በመሆናቸው ነው እነዚህን ቃላት የተጋሩት፡፡ የነዚህ ቃላት መነሻ የሁሉም ሴማዊ ቋንቋዎች አባት እንደሆነ የሚታመንበት ግንደ-ሴማዊ ቋንቋ (Proto-Semetic Language) ነው፡፡
*****
     አዲስ አበባን ከጅቡቲ ጋር የሚያገናኘው የኢትዮ-ጅቡቲ የምድር ባቡር መስመር ሲሰራ ደግሞ ፈረንሳይኛ ወደ ሀገራችን ቋንቋዎች እየሰረገ መግባት ጀምሮ ነበር፡፡ የተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤትም በ1910ዎቹ ውስጥ ሲከፈት የፈረንሳይኛ ተጽእኖ በጣም ተጠናክሯል፡፡ የዘመኑ የትምህርት ካሪኩለምም ከፈረንሳይ የተቀዳ በመሆኑ የትምህርት ቤቱ ተማሪዎችና ምሩቃኑ ፈረንሳይኛን ይናገሩ ነበር፡፡ በነዚያ ምሩቃን በተሞላው ሲቪል ሰርቪስም ሆነ በአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ውስጥ ፈረንሳይኛ እንደ ሁለተኛ ቋንቋ ሆኖ አገልግሏል፡፡ ለመንግሥታዊ አገልግሎት የሚያስፈልጉ ሰነዶችና የስራ መመሪያዎችም ከፈረንሳይኛ ሲተረጎሙ ነው የኖሩት (የመጀመሪያው ህገ-መንግሥትም ከፈረንሳይ የተቀዳ ነው)፡፡  በዚህም ሂደት በርካታ የፈረንሳይኛ ቃላት በአማርኛ ተወርሰዋል፡፡ ከፈረንሳይኛ ከወረስናቸው ቃላት መካከል “ኦፊሴል”፣ “ሞኖፖል”፣ “ሌጋሲዮን”፣ “ኮሚስዮን”፣ “ፔኒስዮን”፣ “ዲክላራሲዮን”፣ “ኦፕራሲዮን”፣ “ካሚዮን”፣ “ፍሪሲዮን”፣ “ሬኮማንዴ”፣ “ለገሀር (ላጋር)፣ “ቡፌ”፣ “ሌሲ ፓሴ”፣ “ዴኤታ”፣ “ ካፌ”፣ “ራንዴቩ”፣ የመሳሰሉት ይጠቀሳሉ፡፡

   የኢጣሊያ ወረራ ከተወልን ማስታወሻዎች መካከል ትልቁ በሀገራችን ቋንቋዎች ውስጥ የሚታየው የጣሊያንኛ ተጽእኖ ነው፡፡ በአማርኛ፣ ኦሮምኛና ትግርኛ ውስጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ የጣሊያንኛ ቃላትን መቁጠር ይቻላል፡፡ በተለይም በቀድሞ ዘመናት ከተሽከርካሪ እና ትራንስፖርት እንቅስቃሴ፣ እንዲሁም ከኢንዱስትሪ ጋር በተያያዘ ከሚሰራባቸው ቃላት መካከል ብዙዎቹ የጣሊያንኛ መሰረት ያላቸው ናቸው፡፡ ዛሬም ድረስ የነዚያ ቃላት ቅሪቶች በሀገርኛ ቋንቋዎች ውስጥ ይስተዋላሉ፡፡ ከጣሊያንኛ ከወረስናቸው ቃላት መካከል “ፓስታ”፣ “ማካሮኒ”፣ “ላዛኛ”፣ “ስፓጌቲ”፣ “ስልስ” (ሳልሳ)፣ “አሮስቶ”፣ “ፋብሪካ”፣ “ጋዜጣ”፣ “ሊቼንሳ”፣ “ፉርኖ”፣ “ቪያጆ” (በመኪና የሚደረግ ጉዞ)፣ “ላቫጆ”፣ “ካሮሴሪያ”፣ “ካምቢዮ”፣ “ሞቶሪኖ”፣ “ፍሬን”፣ “ፊልትሮ”፣ “ሳልቫታዮ”፣ “ፖርቶ መጋላ”፣ “ፒንሳ”፣ “ቺንጊያ” ፣ “ፈረፋንጎ”፣ “ኩሽኔታ” “ኪያቤ”፣ “ካቻቢቴ” “ባሌስትራ”፣ “ቸርኬ” “ፒስታ” “ኮማርዳሬ” “ጎሚኒ” “ሮንዴላ” “ዲፍረንሻሌ” “ስፒናታ” “ሳልዳሬ” “ቡኮ”፣ “ፖምፓ” (ቧንቧ)፣ “አውታንቲ”፣ “ማኖ”፣ “ኢሊ ጎሬ”፣ “ቴስታ”፣ “ፑንቶ”፣ “ቦጦሎኒ”፣ “ካምቦ” ወዘተ…. የመሳሰሉት ተጠቃሽ ናቸው፡፡
*****
ጣሊያኖች ከተባረሩ በኋላ እንግሊዝኛ በሀገርኛ ቋንቋዎች ውስጥ ሰርጾ መግባት ጀመረ፡፡ በተለይ እንግሊዞች በኢትዮጵያ ውስጥ በነበሩባቸው አስር ዓመታት የእንግሊዝኛ ቃላት በሀገራችን ቋንቋዎች በብዛት ተወረሱ፡፡ በዚያን ጊዜ ከተወረሱት ቃላት ውስጥ እስከ አሁን ድረስ በአገልግሎት ላይ ያሉትን እንደ “ፖሊስ”፣ “ባንክ”፣ “ሚኒስቴር”፣ “ካፒታል”፣ “ኤሌክትሪክ”፣ “ኮሌጅ”፣ “አካዴሚ”፣ “ኤክስፐርት”፣ “ዲሬክተር” የመሳሰሉትን መጥቀስ ይቻላል፡፡ እንዲሁም እንደ ፕሮፌሰር፣ ዶክተር፣ ኢንጂነር፣ ጄኔራል፣ አድሚራል፣ ኮሞዶር፣ ኮሎኔል እና ካፒቴን የመሳሰሉ የማዕረግ ስሞችም የተወረሱት ከእንግሊዝኛ ነው፡፡

    በእንግሊዝኛ ወደ ኢትዮጵያ መምጣት የተነሳ ፈረንሳይኛና ጣሊያንኛ በሀገራችን ቋንቋዎች ላይ የነበራቸው ተጽእኖ በፊት ከነበረበት ደረጃ ሊያድግ አልቻለም፡፡ ነገር ግን በሀገራችን ቋንቋዎች የተወረሱት የጣሊያንኛና የፈረንሳይኛ ቃላት በዘመኑ አገልግሎት መስጠታቸውን አላቆሙም፡፡ ለምሳሌ በቀዳማዊ ኃይለሥላሤ ዘመን “ኮሚሲዮን” እንጂ “ኮሚሽን” የሚባል የአማርኛ ቃል አይታወቅም፡፡ ከፈረንሳይኛና ከጣሊያንኛ የተወረሰ የሀገርና የከተማ አጠራርም ቢሆን በአማርኛ ቋንቋ አንዳች ለውጥ ሳይደረግበት ያገለግል ነበር፡፡ እንደ ምሳሌም “ቤልጅግ”፣ “ስዊስ”፣ “ሎንዶን”፣ “መስኮብ”፣ “ብሩክሴል” የመሳሰሉትን የሀገርና የከተማ ስሞች መጥቀስ ይቻላል፡፡

    ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሤ መንግሥት ውድቀት በኋላ ግን ከፈረንሳይኛና ከጣሊያንኛ የተገኙ የሀገርና የከተማ ስያሜዎች ከእንግሊዞች በተወረሱ ስሞች ተተክተዋል፡፡ በዚህም መሰረት “ቤልጅግ” ወደ “ቤልጅየም”፤ “ስዊስ” ወደ “ስዊትዘርላንድ.፣ “ብሩክሴል” ወደ “ብራሰልስ”፣ “መስኮብ”ም ወደ “ሞስኮ” ተለውጠዋል፡፡ በመሆኑም ከልዩ ልዩ  ቋንቋዎች በተገኙ የቦታ ስያሜዎችና ቃላት ተውቦ ይታይ የነበረው አማርኛ የመኮማተር ባህሪን ለማዳበር ተገዷል፡፡

   ይህ ቀደምት ውርስ ስሞችን በእንግሊዝኛ አጠራሮች የመተካቱ ሂደት ሳያቋርጥ በመቀጠሉ ከሁለቱ ቋንቋዎች (ከፈረንሳይኛና ጣሊያንኛ) የተወረሱ የሀገር ስሞችን ከማራገፍ አልፎ በጥንታዊው አማርኛ ውስጥ መሰረት የነበራቸውን የሀገር ስሞችንም በእንግሊዝኛ ስያሜዎች መለወጥ ተጀምሯል፡፡ ለምሳሌ የዓለም ትልቋ ሀገር ከጥንት ጀምሮ በአማርኛ ስትጠራ “ሩሲያ” ነው የምትባለው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን “ራሽያ” የሚለው አጠራር እያየለ መጥቷል፡፡ “ስጳኝ” የሚለው ትክክለኛ የአማርኛ አጠራር “ስፔን” በሚለው የእንግሊዝኛ ቅጂ ተቀይሯል፡፡ “አርመን” የሚለው አጠራርም በ“አርሜኒያ” ተተክቷል፡፡ “ቤልጅግም” ወደ “ቤልጅየም” ተቀይሯል፡፡ “ቆጵሮስ” የሚለውን ጥንታዊ የአማርኛና የግዕዝ አጠራር “ሳይፕረስ” በሚለው አዲስ ደራሽ የቅጂ ስም የሚለውጡ ሰዎችም እየበረከቱ ነው፡፡ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን በኦፊሴል ያገለግሉ የነበሩት እንደ “ነምሳ” (አውስትሪያ) እና “ናርበጅ” (ኖርዌይ) የመሳሰሉ የሀገራት መጠሪያዎች በዚህ ዘመን በአማርኛ ቋንቋ አገልግሎት መስጠታቸውን አቁመዋል፡፡

   ለሌሎች አገልግሎቶች የሚውሉ የፈረንሳይኛና የጣሊያንኛ ውርስ ቃላትም ቢሆኑ የመጥፋት እጣ ደርሶአቸዋል፡፡ ለምሳሌ በዛሬው ዘመን ከፈረንሳይኛ በተወረሰው “ኮሚሲዮን” የሚገለገል ሰው የለም፡፡ በአማርኛና በኦሮምኛ ቋንቋዎች በስፋት ሲያገለግል የነበረው “ኦፕራሲዮን”ም በዚህ ዘመን “ቀዶ ጥገና” እና “ኦፕሬሽን” በሚሉት ስሞች ተተክቷል፡፡ “ፔኒሲዮን” የሚለው ቃልም ሙሉ በሙሉ አገልግሎቱን አቁሟል፡፡
*****
 “እነዚህ ቃላት ድሮውንም የውጪ ቃላት በመሆናቸው ከአማርኛ መጥፋታቸው የሚያስነሳው አቧራ የለም” ይባል ይሆናል፡፡ ነገሩን በታሪክና በአንትሮፖሎጂ መነጽር ካየነው ግን ትልቅ ጉዳት አለው፡፡ ምክንያቱም የነዚህ ቃላት በቋንቋዎቻችን ውስጥ መኖር የ20ኛው ክፍለ ዘመን ታሪካችን የተጓዘበትን መንገድና የእኛነታችንን ህብርነት የሚያሳይ በመሆኑ ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ ሰው የፈረንሳይኛ ቃላት በአማርኛ ውስጥ በመኖራቸው ተገርሞ “ይህ እንዴት ተከሰተ?…” የሚል ጥያቄ ቢያቀርብ የጅቡቲው ምድር ባቡርና የተፈሪ መኮንን ትምህርት ታሪክ ይተረክለታል፡፡ በጣሊያንኛ ቃላት ላይ ጥያቄ ለሚያቀርብ ሰውም የአምስቱ ዓመቱ የኢጣሊያ ወረራና የአርበኞቻችን የተጋድሎ ታሪክ ይነገረዋል፡፡

በሌላ በኩል በአንድ ቋንቋ ውስጥ ያሉ ውርስ ቃላትና ሀረጋት የታሪካዊ ምርምር መሰረቶች የሚሆኑበት አጋጣሚም ሞልቷል፤ ቃላቱና ሐረጋቱ እንደ ታሪክ ማስረጃ የሚያገለግሉበት ሁኔታም አለ፡፡ ብዙ የታሪክ እንቆቅልሾች በቃላትና በሀረጋት መነሻነት ሊፈቱ ችለዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር ዛሬ በግዴለሽነት ከኦሮምኛና ከአማርኛ ቋንቋ ውስጥ እየተወገዱ ያሉት የፈረንሳይኛና የጣሊያንኛ ውርስ ቃላቶቻችን ጠሊቅ የሆኑ ኪነታዊ ስራዎች የሚወጠኑበት መሰረቶች ሆነው ሲያገለግሉ ታይተዋል፡፡ እንደምሳሌም የቴዲ አፍሮን “ሼ-መንደፈር” እና “ላምባ ዲና”ን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ቴዲ እየረሳናቸው ያሉትን አንድ የፈረንሳይኛና አንድ የጣሊያንኛ ቃላትን ወስዶ የሁለት ውብ ዜማዎች መሰረት አድርጎአቸዋል፡፡ በመሆኑም ውርስ ቃላቱን በነበሩበት ሁኔታ ማስቀጠሉ ተገቢ ነው፡፡  

   በዚህ ረገድ የሀገራችን ሚዲያዎችና ፕሬሶች ሃላፊነት በጎደለው ሁኔታ እያካሄዱት ያለውን አጥፊ ሚና መግታት አለባቸው፡፡ ፈረንሳይም ሆነ እንግሊዝ፣ ጣሊያንም ሆነ ጀርመን ሁሉም ባዕድ ነው፡፡ ፊት የመጣውንና በህዝቡ ውስጥ የቆየውን ቃል አስወግዶ በሌላ የባዕድ ቃል መተካት በምንም መልኩ የስኬት መለኪያ አይሆንም፡፡ በተለይ ግን በረጅም ዘመናት የታሪክ ጉዞአችን ያዳበርናቸውንና እኛ ብቻ የምንጠቀምባቸውን ጥንታዊ የሀገርና የከተማ አጠራሮች (ሩሲያ፣ ቆጵሮስ፣ አርመን፣ ደማስቆ፣ ስዊስ፣ ኡክራኒያ፣ ቱርክ፣ ኢጣሊያ፣ ሮማ፣ አቴና፣ ሶሪያ፣ ፍልስጥኤም፣ ሊባኖስ፣ ግብጽ ወዘተ.. የመሳሰሉትን) ከእንግሊዝኛ በተኮረጁ ስሞች (ራሽያ፣ ሳይፕረስ፣ ደማስከስ፣ ፓለስታይን፣ ኢጂፕት ወዘተ..) መተካት ይቅርታ የማይሰጠው ጥፋት ነው፡፡ ቴክኖሎጂንና የተቀላጠፈ አሰራርን መኮረጅ እንጂ ነባር ቃላትን ማጥፋት የእድገት መሰረት ሊሆን አይችልም፡፡ ዐረቦችም ሆኑ ፈረንጆች፣ ቱርኮችም ሆኑ ህንዶች እንዲህ ዓይነት ጥፋት ሲያጠፉ አይታዩም፡፡ እኛም ይህንኑ ፈለግ መከተል አለብን፡፡ ስለዚህ የሚመለከተው ሁሉ ለጉዳዩ አጽንኦት ሊሰጠው ይገባል፡፡
--------
አፈንዲ ሙተቂ
ግንቦት 13/2006
ሸገር-አዲስ አበባ


“አንድ በላተኛ” ጠመንጃዎች በኢትዮጵያ


ጸሓፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ
---------
በዲሞትፈር፣ አርገው ገፍተር
በወጨፎ፣ አርገው ቀፎ
በሰናድር፣ አርገው ክንችር
በምንሽር፣ ያዘው አብሽር
ባጭር አልቤን፣ ደረት ልቤን፡፡

(ወዳጄ ካሳሁን አለማየሁ ከጻፈው ሀገርኛ ግጥም የተወሰደ)
*****
ጠመንዣ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሀገራችን የገባው በ16ኛው ክፍለ ዘመን መግቢያ ላይ ነበር፡፡ በዚያ ዘመን ከሰለሞናዊ አጼ ንጉሠ ነገሥቶች ጋር ሲፋለሙ የነበሩት የአዳል ሱልጣኔት ገዥዎች ናቸው ጠመንዣን ወደ ሀገራችን ያስገቡት፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ደግሞ የሰለሞናዊ ነገሥታት ወታደሮችም ጠመንዣን ለመታጠቅ ችለዋል፡፡ ወታደሮች ሙሉ በሙሉ በጠመንዣ መዋጋት የጀመሩት ግን በአድዋው ጦርነት ማግስት ነው፡፡ እስከ አድዋው ጦርነት ድረስ ጦርና ጎራዴን ከጠመንጃ ጋር በማፈራረቅ ይጠቀሙ ነበር፡፡

    እንደዚህም ሆኖ ግን የያንዳንዱ ዘመን የቴክኖሎጂ ውጤት የሆነ ጠመንዣ ወደ ኢትዮጵያ ይገባ እንደነበረ ይታመናል፡፡ የውጪ መንግሥታት ለኢትዮጵያ ነገሥታት ከሚያቀርቧቸው ገጸ-በረከቶች መካከል አንዱ ጠመንዣ ስለመሆኑም በስፋት ተጽፏል፡፡ ከነዚያ የጠመንዣ ዓይነቶች መካከል አንዳንዶቹ እስከዚህ ዘመን ድረስ ይደነቃሉ፡፡ ለምሳሌ በጅማ ከተማ በሚገኘው የአባጅፋር ሙዚየም ውስጥ አነስተኛ ከዘራ የሚመስል አንድ ጠመንዣ አለ፡፡ ያ መሳሪያ ጠመንዣ መሆኑን የምትረዱት አስጎብኚው አተኳኮሱን ሲያሳችሁ ብቻ ነው፡፡ በሌላ ቦታ ብታዩት ትንሽዬ ከዘራ ነው ብላችሁ የምታልፉት ይመስለኛል (ኮ/ል መንግሥቱ ኃይለማሪያም እንደዚያ ዓይነት የከዘራ ጠመንዣ እንደነበራቸው አንድ የቀድሞ ጦር አባል ጥቅምት 1985 በታተመው በእፎይታ መጽሔት ላይ አስነብበውን ነበረ)፡፡

   ጠመንዣ በኢትዮጵያ ውስጥ በስፋት የተሰራጨው በሀያኛው ክፍለ ዘመን ነው፡፡ ከነዚያ ጠመንዣዎች ውስጥ አንዳንዶቹ ዛሬም ድረስ ያገለግላሉ፡፡ አንዳንዶቹ ግን የአገልግሎት ዘመናቸው አብቅቶ ስሞቻቸው ብቻ ቀርተውናል፡፡ በዚህ ጽሑፍ ውስጥ በጥቅሉ “አንድ በላተኛ” የሚባሉትን ጠመንጃዎች በጥቂቱ እንቃኛለን፡፡
*****
“አንድ በላተኛ” ኦቶማቲክ ያልሆኑ ጠመንዣዎች በወል የሚጠሩበት የአማርኛ ስም ነው፡፡ እነዚህ ጠመንዣዎች በኦሮምኛ “ተከ ኛቴ” (takka nyaattee) ይባላሉ፡፡ ጠመንዣዎቹ እንዲህ እየተባሉ የሚጠሩት አንድ ጥይት ብቻ ስለሚጎርሱ ሳይሆን የጎረሱትን ጥይት አንድ በአንድ የሚተኩሱ በመሆናቸው ነው፡፡ ይህም ማለት ጠመንዣው ተቀባብሎ አንዴ ከተተኮሰበት በኋላ እንደገና ማቀባበልን ይጠይቃል፡፡ በመሆኑም “አንድ በላተኛ” ከተሰኘው ስያሜ በተጨማሪ “ቆመህ ጠብቀኝ” የሚል የፉገራና የስላቅ ስያሜም ወጥቶላቸዋል፡፡

    “አንድ በላተኛ” የሆኑ ጠመንዣዎች በአብዣኛው አምስት ያህል ጥይቶችን ነው የሚጎርሱት፡፡ እነዚህም ጥይቶች ትልልቆች ናቸው፡፡ ጥይቱ ከተተኮሰ በኋላ በርቀት ላይ የሚገኝን ነገር መትቶ የመጣል ሀይሉም ከፍተኛ ነው ይባላል፡፡ በመሆኑም “አንድ በላተኛ” ጠመንዣዎች በተለይ ለአደን ስራ በጣም ተመራጭ ናቸው፡፡

  በድሮው ዘመን ለውጊያ ይፈለጉ የነበሩት እነዚህ “አንድ በላተኛ”ዎች በሰለጠነው ዓለም እምብዛም አያገለግሉም፡፡ በኛ ሀገር ግን አስከ አሁን ድረስ በጥበቃ ስራ ላይ የተሰማሩ ዘበኞችና የአካባቢ ሚሊሻዎች በብዛት የሚያነግቱት “አንድ በላተኛ” ጠመንጃዎችን ነው፡፡  

   በሀገራችን ውስጥ የብዙ ሀገራት ስሪት የሆኑ “አንድ በላተኛ” ጠመንዣዎች አሉ፡፡ እነዚህን ጠመንዣዎች የምንጠራባቸው የተለምዶ ስያሜዎች በፋብሪካ የተሰጧቸው የሞዴል ስሞች ናቸው ብሎ ለመናገር ይከብዳል፡፡ የሆነው ሆኖ በኛ ሀገር ሲያገለግሉ ከነበሩት የጠመንዣ ዓይነቶች መካከል ጥቂቶቹን እንተዋወቃቸው፡፡  

1.      ምንሽር፡

“ምንሽር” ጣሊያን ሰራሽ ጠመንዣ ነው፡፡ በሀገራችን ውስጥ በስፋት ያገለግል ነበር፡፡ በተለይም የኢትዮጵያ አርበኞች የጣሊያን ወራሪዎችን የተፋለሙበት ዓይነተኛው የጠመንዣ ዓይነት ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ ጠረፎችና በትግራይ ገጠሮች በአገልግሎት ላይ ያለ መሆኑ ይነገራል፡፡ በሌሎች ክልሎች ግን እምብዛም አይታይም፡፡  

2.     አልቤን:

የአልባኒያ ስሪት የሆነ የጠመንጃ ዐይነት ነው፡፡ በዚህ ዘመን ብዙም የማይታየው ይህ ጠመንጃ በኢጣሊያ ወረራ ዘመን ከፍተኛ አገልግሎት ሰጥቷል፡፡

3.     ውጅግራ፡

ይህኛው ጠመንዣ ድምጹ ብራቅ ነው ይባልለታል፡፡ እንደ ከርከሮ እና ጅግራ ያሉት እንስሳት ወደ ሰብል ማሳ እንዳይጠጉ ለመከላከል ከተፈለገ አንድ የውጅግራ ጥይት ይበቃቸዋል፡፡

4.     ረሽ፡

ብዙ ጊዜ ለአደን ስራ የሚያገለግል ነው፡፡ ለዚህም ያግዝ ዘንድ በጠመንዣው ላይ የማነጣጠሪያ “ቴሌስኮፕ ተገጥሞለታል፡፡ ብዙ ሰዎች “መተሬ” (sniper) እያሉ የሚጠሩት ጠመንዣ እርሱ ሳይሆን ይመስለኛል፡፡

 ይህ ጠመንዣ ጥይት በሚጎርስበት ጊዜ ከሰደፉ በኩል ሰበር ብሎ ይቆለመማል፡፡ በተጨማሪም ሁለት አፈሙዝ ነው ያለው፡፡ ጥይቱ ከተተኮሰ በኋላ በአየር ላይ ስለሚበተን እንደ ጅግራ፣ ቆቅና ዳክዬ መሳሰሉ አዕዋፋት በመንጋ በሚበሩበት ወቅት ለማደን ተመራጭ ነው፡፡ ረሽ በሰሜን ኢትዮጵያ ገጠሮች “ግንጥል” የሚል ስያሜ እንዳለው “እንዳላማው አበራ” የሚባል የፌስቡክ ጓደኛዬ አጫውቶኛል፡፡

5.     ዲሞትፈር

በኢትዮጵያ ውስጥ በብዛት የተሰራጨ የጠመንጃ ዓይነቶች አንዱ ነው፡፡ የዘንጉ ርዝማኔ ይለያያል፡፡ ከዚህ ጠመንዣ ጋር በተያያዘ በሀገራችን ውስጥ ታሪካዊ እና አወዛጋቢ የሆነ አንድ አባባል ተፈጥሯል፤ “ዲሞን በዲሞትፈር” የሚል፡፡ አባባሉ የተፈጠረው በዘመነ ቀይ ሽብር ነው፡፡ “ዲሞ” እየተባሉ የተጠሩት የኢህአፓ አባላትና ደጋፊዎች ናቸው፡፡ (“ዲሞ” የኢህአፓ ልሳን ከነበረችው “ዲሞክራሲያ” ጋዜጣ ስያሜ ላይ የተቀነጨበ ነው)፡፡

   ይህ አባባል ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰማው ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማሪያም ጥር 26 ቀን 1969 በተቀናቃኝ የደርግ አባላት ላይ  የወሰዱትን እርምጃ ለመደገፍ በሚል በቀጣዩ ቀን በተዘጋጀው ሰላማዊ ሰልፍ ላይ ነው፡፡ ብዙ ጸሐፍት እንደሚሉት “ዲሞን በዲሞትፈር” የሚለውን አባባል ፈጥረው ወደ አደባባይ ያወጡት የመኢሶን አመራሮች ናቸው፡፡ መኢሶን ግን ነገሩን ያስተባብላል፡፡ ያም ሆነ ይህ አባባሉ “ዲሞትፈር” ጠመንዣ በቀይ ሽብር አፈጻጸም ውስጥ የነበረውን ሚና የሚያስረዳ ይመስለኛል፡፡

ዲሞትፈር በሀገራችን ውስጥ አሁንም በስፋት ያገለግላል፡፡ ይሁንና በጎንደርና ጎጃም ክፍለ ሀገራት ይበልጥ የሚታወቀው “ጓንዴ” በሚለው ስም ነው፡፡
  
6.     ቺኮዝ


በደርግ ዘመን የመጨረሻ ዓመታት በቀበሌ ደረጃ የተደራጁ የአብዮት ጥበቃ ጓዶች ሲታጠቁ የነበሩት ጠመንዣ ነው፡፡ ከስያሜው ለመረዳት እንደሚቻለው ጠመንጃው የተሰራው በቼኮዝሎቫኪያ ነው፡፡ ቼኮዝ ግራጫ ቀለም ያለው ጠመንዣ ነው፡፡

ቺኮዝ በጣም አደገኛ መሳሪያ ነው፡፡ ጥይቱ ወደ ሰውነት ሲገባ ቀዳዳው ትንሽ ነው፡፡ ሲወጣ ግን አካልን በሰፊው ቦድሶ ነው የሚወጣው፡፡ አንድ ሰው በቺኮዝ መመታቱን ለማወቅ ጥይቱ የገባበትንና የወጣበትን ቦታ ብቻ መመልከት ይበቃል፡፡

7.     ቤንቶቭ

“አንድ በላተኛ” ጠመንዣዎች ሁሉ ለመሸከም የማይከብደው ይህኛው ነው፡፡ የጠመንዣው እንጨትም ጥቁር ቡናማ መልክ አለው፡፡ በደርግ ዘመን የቀበሌ ጥበቃ ጓዶች ከቺኮዝ ቀጥሎ በብዛት ይታጠቁ የነበሩት ቤንቶቭን ነው፡፡
*****

እላይ ከዘረዘርናቸው መሳሪያዎች ሌላ ወጨፎ፣ ቤልጅግ፣ መውዜር፣ ሰናድር፣ ናስማሰር፣ ጉንጮ፣ ስኩዌር ወዘተ… የሚባሉ “አንድ በላተኛ” ጠመንዣዎች በሀገራችን ውስጥ በስፋት ያገለግሉ እንደነበረ መዛግብትና የቃል ምንጮች ያስረዳሉ፡፡ ከላይ እንደገለጽኩት በውጪው ዓለም በከፍተኛ ፍጥነት እየተለወጠ በመሄድ ላይ የሚገኘው የመሳሪያና የወታደራዊ ምህንድስና ቴክኖሎጂ እነዚህን አንድ በላተኛ ጠመንጃዎች ከአገልግሎት ውጪ አድርጎአቸዋል፡፡ በሀገራችንም ውስጥ ብዙዎቹ ለጥበቃ ስራ ቢያገለግሉም በቅርብ ዓመታት አገልግሎታቸውን ማቋረጣቸው እንደማይቀር ይታመናል፡፡ ቢሆንም አባቶቻችን ታሪክ ሲሰሩ የነበሩት በነርሱ ነውና የያንዳንዱን መሳሪያ ስርጭትና የአገልግሎት አድማስ መዝግቦ ለመጪው ትውልድ ማቆየት ይገባል፡፡ ሰላም!!