Thursday, August 14, 2014

እስልምና፣ “ጂሃድ” እና ሰሞነኛው የኢራቅ ሚሊሻ


ፀሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ
--------
ኢራቅ በሳዳም ሁሴን አገዛዝ ስር በነበረችበት ዘመን ከሞላ ጎደል ሰላምና መረጋጋት ነበራት፡፡ ሀገራዊ አንድነቷም የተጠበቀ ነው፡፡ አሜሪካ አንድም ማስረጃ ባልነበረው ወሬ ተነሳስታ በ2003 (እ.ኤ.አ) ሀገሪቷን ከወረረቻት በኋላ ግን አንድነቷም ሆነ ሰላሟ ተናግቷል፡፡ በኤፍራጥስና ጤግሮስ ወንዞች ላይ የከተመችው ውቢቷ ባግዳድም በየዕለቱ የቦንብና የፈንጂ ፍንዳታ ማስተናገድ ምሷ ሆኗል፡፡ 
    ከዚህ ባሻገር ሀገሪቷ ክቡር የሆነውን የእስልምና አስተምህሮ እንዳሻቸው እየተረጎሙ ስውር አጀንዳዎቻቸውን ለማስፈጸም የሚተጉ ጽንፈኛ ግለሰቦችና ቡድኖች መፈልፈያ ሆናለች፡፡ አቡ ሙስዓብ አል-ዘርቃዊን የመሳሰሉ ጽንፈኞች ኢራቅን የእቶን እሳት መቀጣጠያ ሲያደርጓት እንደከረሙ ተመልክተናል፡፡ በዘንድሮው ዓመት ደግሞ ድሮ ከምንሰማቸው እጅግ የከፋ ጽንፈኛ ቡድን በዚያው ምድር ላይ እጆቹን ሲዘረጋ ለመታዘብ በቅተናል፡፡
  ራሱን “የኢራቅና የሻም ኢስላማዊ መንግሥት” እያለ የሚጠራው (ከቅርብ ጊዜ ወዲህ “ኢስላማዊ መንግሥት” በሚለው አጭር ስያሜ ብቻ የሚጠራው) ቡድን ከየት ተገኘ?.. እንዴት ተመሰረተ?… መስራቾቹስ እነማን ናቸው?… ከጀርባ የሚገፉትስ እነ ማን ናቸው?…. የመጨረሻ ዓላማው ምንድነው?…. እነዚህን ጥያቄዎች ለመመለስ የነጠረ መረጃ ሊኖረን ይገባል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ግን ብዙዎቹን ጥያቄዎች ለመመለስ አይቻልም፡፡ ስለዚህ ጥያቄዎቹን ጊዜ ይመልሳቸው ማለቱ ይሻላል፡፡ ቡድኑ ለሚተግብራቸው የጽንፈኝነት አድራጎት እስልምናን እንደ ማስረጃ እየጠቀሰ ማነብነቡ ግን በጣም ያሳምመናል፡፡
   በዘመናችን የሚታዩትና በእስልምና ስም የሚነግዱ ጽንፈኞች በሙሉ “ጂሃድ እያደረግን ነው” እያሉ ነው የሚፎክሩት፡፡ ለብዙ ክፍለ ዘመናት በሙስሊሞች መሀል በሰላም ሲኖሩ የነበሩ ማህበረሰቦች ሀይማኖታቸውን እንዲቀይሩ ማስገደድም ጀምረዋል፡፡ “ጂሃዳቸው” ግብ መትቶ ሀገር ከተቆጣጠሩ በኋላ የሚመሰርቱት “ኋላቀር” መንግሥት ምን ዓይነት እንደሆነም ምልክቱን እያየን ነው፡፡ በርግጥ በእስልምና እይታ እንዲህ ዐይነቱ ጽንፈኝነት “ጂሃድ” ማድረግ ነው ተብሎ ሊጠራ ይችላልን?… እስልምናስ “ኋላቀርነትን” የሚናፍቅ እምነት ነውን?… በነዚህ ነጥቦች ዙሪያ አንዳንድ ነገሮችን ለመናገር አስቤ ነው ይህንን መጣጥፍ የጻፍኩት፡፡

==“ጂሃድ” እና ጽንፈኞች=

  ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) በህይወት ዘመናቸው ከብዙ ባላንጣዎቻቸው ጋር ተጋድለዋል፤ ተዋግተዋል፡፡ ይሁንና እሳቸውም ሆኑ ተከታዮቻቸው ከባላንጣዎቻቸው ጋር የተጋደሉት ሰዎች እስልምናን በጉልበት እንዲቀበሉ ለመጫን በሚል አይደለም፤ እነዚያ ባላንጣዎቻቸው ሊያጠፏቸው ስለተነሱባቸው ነው ራሳቸውን ለመከላከል የተዋጉት፡፡ ጠላቶቻቸው ከመካ ከተማ ጀምሮ ሊያጠፏቸው ሲዶልቱ፣ ሴራ ሲሸርቡና ቅጥረኞችን ሲልኩባቸው ነበር፡፡ ይባስ ብሎም “ሀይማኖታችንን አርክሶ አዲስ እምነት የጀመረው ሙሐመድ ተላልፎ ካልተሰጠን በስተቀር ከማንም ጋር ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ግንኙት እንዲያደርግ አይፈቀድለትም” ተብሎ ለሁለት ዓመታት ያህል ነብዩ በተገኙበት የበኒ ሐሺም ቤተሰብ ላይ ማዕቀብ ተጥሏል፡፡ የነቢዩ ቤተሰብም “ሙሐመድን አሳልፈን አንሰጥም” በማለት እቀባው እስኪነሳለት ድረስ ከመካ ከተማ ተሰዶ ለመኖር ተገዷል፡፡ በርሳቸው ተከታዮች ላይ የደረሰው ሰቆቃና ችግር ደግሞ በቀላሉ አይነገርም፡፡ በተለይ ደካሞችና ተከላካይ ያልነበራቸው እንደ አማር ቢን ያሲር እና ወላጆቹ፣ ኢትዮጵያዊው “ቢላል”፣ ወዘተ… የመሳሰሉት የሰቆቃና የስቃይ መሞከሪያ ሆነው ነበር ለማለት ይቻላል፡፡ ይህ ስቃይ ሲባባስ ነው ነብዩ ግማሾቹን ተከታዮቻቸውን በስውር ወደ ኢትዮጵያ የሰደዱት፡፡ በመጨረሻም ነቢዩና ተከታዮቻቸው በሙሉ ከመካ ወደ መዲና ለመሰደድ የበቁት ከቁሬይሽ መኳንንቶች ከሚመጣባቸው ጥቃትና በደል ለመሸሽ ሲሉ ነው፡፡
  የነቢዩ ጠላቶች ግን እዚያም አላረፉላቸውም፡፡ “ሙሐመድ ሀይል ገንብቶ እኛን ከማጥፋቱ በፊት እዚያ ሄደን ልናጥፋው ይገባናል” በማለት የክተት አዋጅ አውጀው እስከ መዲና ድረስ ሄዱላቸው፡፡ በዚህን ጊዜ ነው አላህ በቅዱስ ቁርኣን “ለነዚያ በእምነታቸው ምክንያት አላግባብ ለተፈተኑት ሙስሊሞች መዋጋት ተፈቀደላቸው” በማለት ጠላቶቻቸውን በጦርነት እንዲዋጉዋቸው መንገዱን ያሳያቸው፡፡ “ጂሃድ” (ተጋድሎ) የተሰኘው ጽንሰ-ሐሳብም ያኔ ነው የተፈጠረው፡፡
  “ጂሃድ” ቃሉ ራሱ እንደሚያመለክተው “ትግል” ወይንም “ተጋድሎ” ማለት ነው፡፡ ሐቀኛ ሰው ሐቁን ላለማስደፈር የሚያደርገው ትግል ነው በዚህ ስም የሚጠራው፡፡ አንድን ውጥን ከግብ ለማድረስ የሚደረግ ርብርብም “ጂሃድ” ሊባል ይችላል፡፡ ሀጢአተኛ ሰው ነፍሱን ከሐጢአት ለማጽዳት የሚያደርገው ትግልም ጂሀድ ነው፡፡ ነገር ግን አንዳንዶች አላግባብ “ቅዱስ ጦርነት” እያሉ ይፈቱታል፡፡ ፍቺውን ሲያሰፉትም “እስልምናን ለማስፋፋትና በሸሪዓ የሚተዳደር መንግሥት ለመመስረት የሚደረግ ጦርነት ነው” ይላሉ፡፡ ስህተት ነው፡፡ በጣም ስህተት! ጦርነት በባህሪው አውዳሚ ነው፡፡ የትኛውም ጦርነት “ቅዱስ” ሊባል አይችልም፡፡ የትኛውም ሀይማኖት ጦርነትን “ቅዱስ ነው” ብሎ አይባርክም፡፡ ነቢዩ ሙሐመድም ጦርነትን፣ ሁከትና ብጥብጥን አውግዘዋቸዋል፡፡
  ይሁንና አንተ የማታውቀው ጠላትህ አንተን አጥፍቶ ሀገርህን ሊወርስብህ ሲመጣብ ቆመህ አትጠብቀውም፤ የራስህን ሀይማኖት ትተህ የርሱን እምነት እንድትከተል ሲወጋህም በዝምታ አትመለከተውም፡፡ ያኔ በምትችለው መንገድ ሁሉ ትዋጋዋለህ፤ ቢቻል በዲፕሎማሲያዊ መንገድ እንዲመለስ ታደርገዋለህ፤ እምቢዮው ካለ ግን በሚገባው የጦርነት ቋንቋ ታናግረዋለህ፡፡ “ጂሃድ” የሚባለውም እንዲህ ዐይነቱ ፍትሐዊ ትግል ነው፡፡
    ለሀገርህ፣ ለህዝብህና ለሀይማኖትህ የምታደርገው ተጋድሎ በሰላማዊ መንገድ ካልተቋጨ ብቻ ነው የጦርነትን አማራጭ የምትከተለው፡፡ ታዲያ ጦርነቱን የምታከናውነው እንዲሁ በዘፈቀደ አይደለም፡፡ ለ“ጂሃድ” ስትሰለፍ በማንኛውም መልኩ ገደቡን አታልፍም፤ አንተን በቀጥታ ከሚወጉት ውጪ ሌሎችን አታጠቃም፤ በጦርነቱ ውስጥ የሌለውን ሰላማዊ ህዝብ አትነካም፡፡ በተለይም በጦርነት እሳት ቀዳሚ ተጠቂ በሆኑት ህጻናት፤ ሴቶችና አረጋዊያን ላይ በጭራሽ እጅህን አታነሳም፤ በማሳ ላይ ያለ አዝመራ፣ በበረት ውስጥ ያሉ ከብቶች፣ ህዝብ የሚጠቀምበት የጉድጓድ ውሃ፣ መስጊድ፣ ቤተክርስቲያን፣ ምኩራብ (የአይሁድ ቤተ-ጸሎት) ወዘተ… አታጠቃም፡፡ እነዚህን እያጠፋህ “ጂሃድ እያካሄድኩ ነው” ብትል በእስልምና ሚዛን አንድም ተቀባይነት አታገኝም፡፡
*****
ለ“ጂሀድ” የወጣ ጦር ከውጊያ ሜዳው ከደረሰ በኋላ እንኳ ውዝግቡ በሰላም እንዲያልቅ የሚቻለውን ጥረት ያደርጋል፡፡ የሰላሙ ጥረት መፍትሔ ካላገኘ ብቻ ነው ወደ ውጊያ የሚገባው፡፡ ለምሳሌ ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) በህይወት ዘመናቸው 27 ዘመቻዎችን አድርገዋል፡፡ ከነዚህ ዘመቻዎች መካከል ውጊያ የተደረገው በስምንቱ ብቻ ነው፡፡ አስራ ዘጠኙ ዘመቻዎች ያለ አንዳች ጦርነት ነው የተጠናቀቁት፡፡
  ከዚህ ሌላም ሁኔታዎች አስገደድውት በጦርነት ውስጥ የገባ “ሙጃሂድ” (ታጋይ) ጦርነቱ እንዳይራዘም እና አውዳሚ ባልሆነ መልኩ እንዲጠናቀቅ የተለያዩ ዘዴዎችን መጠቀም ይኖርበታል፡፡ ለምሳሌ ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) በመዲና ዙሪያ ምሽግ በመቆፈር በአምስት እጥፍ የሚበልጣቸው የአህዛብ ሰራዊት በፍርሐት ተርበድብዶ እንዲመለስ አድርገውታል፡፡ እንዲሁም ደግሞ በስምንተኛው ዓመተ-ሂጅራ የመካ ከተማን በአነስተኛ ውጊያ (13 ሰው ብቻ የሞተበት) ለመቆጣጠር የቻሉት ሰራዊታቸውን በአራት አቅጣጫዎች በማሰማራት ከተማዋን ለመክበብ በመቻላቸው ነው፡፡ በዚህም በመካ ከተማ ላይ አንድም ውድመት እንዳይሰከት ለማድረግ ችለዋል፡፡
     በጂሃድ ውስጥ ሌላው ውግዝ ተግባር ደግሞ ጦርነትን በጠቅላላ ድምሰሳ (total destrcuction) ስልት ለማሸነፍ መሞከር ነው፡፡ የጠላትን ሀይል በሚቻለው ዘዴ ሁሉ ለማንበርከክ እስከ መጨረሻው ድረስ መታገል ይቻላል፡፡ ይህ ዘዴ ግን ከተዋጊው ውጪ በጦርነቱ ውስጥ ባልተሳተፈው ሲቪል ህዝብ ላይ አደጋ የሚያደርስ መሆን የለበትም፡፡ አንድን ከተማ መቆጣጠር ሲያቅትህ በጅምላ ጥቃት ከተማዋን ማውደም በጭራሽ ከ“ጂሃድ” አይቆጠርም፡፡
  ለምሳሌ ነቢዩ ሙሐመድና ተከታዮቻቸው “ሐዋዚን” ከሚባለው የዐረብ ጎሳ ተዋጊዎች ጋር ውጊያ ገጥመው አሸንፈውታል፡፡ በጦርነቱ የተሸነፉት የሀዋዚን ተዋጊዎች “ጧኢፍ” በምትባለው ከተማ መሸጉ፡፡ ነቢዩ ጣኢፍን ለበርካታ ቀናት ከበቡ፤ የሀዋዚን ተዋጊዎችም እጃቸውን እንዲሰጡ ጠየቁ፡፡ ባላንጣዎቻቸው ግን አምቢኝ አሉ (ጣኢፍ በዘመኑ ሉአላዊነት ያላት የከተማ መንግሥት ነበረች)፡፡ ይባስ ብሎም በከተማዋ ግንቦች ጫፍ ላይ ሆነው በነቢዩና በተከታዮቻቸው ላይ ልዩ ልዩ የባለጌ ስድቦችን ያወርዱ ጀመር፡፡ ይሁንና ነቢዩ በምላሹ ተናድደው የጧኢፍ ከተማዋን አላወደሟትም፡፡ የሀዋዚን ተዋጊዎችን እንቅስቃሴ በዐይነ ቁራኛ የሚጠብቅ ጦር በከተማ አቅራቢያ መድበው ለራሳቸው በክብር ወደ መዲና ተመለሱ፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ደግሞ እዚያ የመደቡትን ጦር አስነሱ፡፡ ከዓመት በኋላ በጦርነት ያልተቻሉት የሀዋዚን ተዋጊዎች በራሳቸው ፈቃድ እጅ ሰጡ፡፡ ሁሉም በፍላጎታቸው እስልምናን ተቀበሉ፡፡
   ይህ የነቢዩ አድራጎት ያስገርማል፡፡ “ጧኢፍ” ነቢዩ በመልዕክተኛነት ከተላኩ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ስደትን የሞከሩባት ከተማ ናት፡፡ ነቢዩና ጥቂት ተከታዮቻቸው ወደ ከተማዋ ደርሰው ነዋሪቿ እስልምናን እንዲቀበሉ ጠየቋቸው፤ በከተማዋ ለመኖር እንዲፈቀድላቸውም ለመኑ፡፡ የጧኢፍ ነዋሪዎች ግን ነቢዩን የድንጋይ ውርጅብኝ አከናነቧቸው፤ ጧኢፍ ውስጥ የነበሩ ህጻናትና ታዳጊዎች ተሰባስበው ያንን አሰቃቂ ትርኢት በጩኸትና በዘፈን አዳመቁት፡፡ የትኛውም ከተማ ነቢዩን በእንደዚያ ዓይነቱ ወራዳ ምግባር አላስተናገደም (በመካ ከተማ ካዩት ስቃይና ሰቆቃ በስተቀር)፡፡ ከአስር ዓመታት በኋላ ያቺ ከተማ በነቢዩና በተከታዮቻቸው ተከበበች፡፡ በከተማዋ የመሸጉት የሀዋዚን ተዋጊዎች አስነዋሪ ስድቦችን እየተሳደቡ ተፈታተኗቸው፡፡ ይሁንና ነቢዩ የጥንቱን የድንጋይ ወገራ ትዝታቸውን ከሀዋዚን ጦረኞች ስድብ ጋር በመደመር ከተማዋን አላጠፏትም፡፡ በራሷ ጊዜ ከእጃቸው እንደምትገባ በመተማመን ወደ መናገሻ ከተማቸው ተመለሱ፡፡ በዚያ ዘመን የነበረ ሌላ መሪ እንዲህ ሲያደርግ አልታየም፡፡ አንድ ከተማ እጅ አልሰጥም ካለች ከተማዋን ማውደም ነው እንጂ ጦሩን ይዞ ወደ ኋላ መመለስ በዚያ ዘመን አይታወቅም፡፡ ሰውዬው ግን ነቢይ ነውና  ለ“ጠቅላላ ድምሰሳ” (total destrcuction) አልቸኮለም፡፡  የኢራቅ ጽንፈኛ ሚሊሻስ?…. አሜሪካስ?…. እስራኤልስ?.. አል-ሸባብስ?… ሂትለርስ?… ሁሉም በጠቅላላ ድምሰሳ (total destrcuction) ስልት ያምናሉ፡፡
*****
“ጀሃድ” በትንኮሳ የሚፈጸምም አይደለም፡፡ ሌሎች ሳይደርሱብህ የሰው ሀገርና ድንበር ወርረህ “ለእስልምና ነው የምዋጋው” ማለት የለም፡፡ በቅዱስ ቁርኣን በተጻፈውም ሆነ ነቢዩ በአንደበታቸው ባስተማሩት መልዕክት ውስጥ “እንዲሁ ከመሬት ተነስህ ሌሎችን ተዋጋ” የሚል ነገር አናነብም፡፡ እያንዳንዱ እርምጃህ የመነሻ ምክንያት ሊኖረው ግድ ይላል፡፡ ነቢዩ ያካሄዷቸው ዘመቻዎች በሙሉ በቂ ምክንያቶች ነበሯቸው፡፡ ጠላቶቻቸው ከተነኮሷቸው በኋላ ነው ነቢዩ ለጂሃድ የወጡት (ሰ.ዐ.ወ)፡፡ በኋለኞቹ ሁለት ዓመታት ውስጥ የተደረጉት ዘመቻዎች ደግሞ ነቢዩ ዐረቢያ ማዕከላዊ መንግሥት መሪነታቸው የሀገሩን ጸጥታና ዳር ድንበር ለማስከበር ያካሄዷቸው ናቸው እንጂ ውጊያ በመሻት የተደረጉ አልነበሩም፡፡
      ከነቢዩ ህልፈት በኋላ የነቢዩ ተከታዮች ከፋርስና ከሮማዊያን ጋር ያኳሄዷቸው ጦርነቶች ብዙ መነሻዎች ነበሯቸው፡፡ ከጀርባቸው የነበረው ዋነኛ ምክንያት ግን አንድና አንድ ብቻ ነው፡፡ ይህም ሮማዊያንና ፋርሶች ከዐረቢያ የተነሳውን አዲስ ሀይል በቅኝ ግዛቶቻቸው ላይ የተጋረጠ አደጋ አድርገው መውሰዳቸው ነው፡፡ በዚህም የተነሳ ሁለቱም ሀይሎች የነቢዩን መንግሥት በስውርና በግልጽ ውጊያ ሊያጠፉት ሞክረዋል፡፡ ይሁንና አዲሱ ሀይል የሚበገርላቸው አልሆነም፡፡ ሮማዊያንንና ፋርሶችን በከፍተኛ ወኔ እየተዋጋቸው ከያዟቸው የእስያ፣ የመካከለኛው ምስራቅና የሰሜን አፍሪቃ (ስፔንን ጨምሮ) ቅኝ ግዛቶች በሙሉ አባሮአቸል፡፡ ከነዚህ ቄሳራዊ ቅኝ ገዥዎች የነጠቃቸውን ግዛቶች በአዲስ የኸሊፋ መንግሥት ስር አጠቃሎአቸዋል፡፡ የሮም መንግሥት በደንበኛው መሬቱ (hinterland) ላይ ከተገደበ በኋላ ከሙስሊሞች ጋር በጉርብትና የመኖር ፖለሲን ስለተከተለ ከርሱ ጋር የሚደረገው ጦርነት ቆሟል፡፡ የፋርሶች መንግሥት ግን በጄ አላለም፡፡ በሙስሊሞች ላይ ትንኮሳ መፈጸሙንና ከተሞችን ማውደሙን ስለቀጠለ ውድቀቱን በራሱ እጅ አፋጥኗል፡፡
*****
የጅሃድ እስላማዊ ግንዛቤ ይህ ነው፡፡ በትክክል ጂሃድ ማድረግ ማለት እንዲህ ነው፡፡ አላህ ታጋዮችን ሊረዳቸው ቃል የገባው ይህንን መርህ ተከትለው የታገሉ እንደሆነ ነው፡፡ ነቢዩንና ተከታዮቻቸውን “አንድ ከልቡ የሚታገል ሙጃሂድ ለአስር ጠላቱ ይበቃል” በማለት ያወደሳቸው በዚህ መመሪያ መሰረት ይታገሉ ስለነበር ነው፡፡ ጥቂቶች ሆነው በብዙ እጥፍ የሚበልጧቸውን የሮምና የፋርስ የጦር ሀይሎችን ለማሸነፍ የበቁት ሐቁን ይዘው በወኔና በቆራጥነት ስለተዋጓቸው ነው፡፡
  የዘመናችን ጽንፈኛ ሀይላት ከዚህ መርህ ጋር በጭራሽ የሚተዋወቁ አይደሉም፡፡ ለጂሃድ የጨፈገገ ትርጓሜ እየሰጡት በአሉታዊ መልኩ እንዲታይ አድርገውታል፡፡ ቅዱስ ቁርአንንና የነቢዩን ሐዲሶች እንዳሻቸው እየተረጎሙ የድብቅ ፍላጎታቸው ማስፈጸሚያ ያደርጉአቸዋል፡፡ በሴፕቴምበር 11/2001 እንደታየው አውሮፕላኖችን እየጠለፉ በሺህ የሚቆጠሩ ንጹሐንን ይፈጃሉ፡፡ በህዝብ ማጓጓዣ ባቡሮችና አውቶቡሶች ላይ ቦንብ ያጠምዳሉ፡፡ የመኖሪያ ህንጻዎችን በፈንጂ ያጋያሉ፡፡ እንደ ሶማሊያው አል-ሸባብ የአንድ አባት ልጆችን ያጋድላሉ፡፡ እንደ ቦኮ-ሀራም በምንም ውስጥ የሌሉ ሴቶችን እየጠለፉ መደራደሪያ ያደርጉአቸዋል፡፡ አልፎ ተርፎም የነርሱን ድርጊት የማይደግፈውን “ሙስሊም አይደለህም” እያሉ ይረሽኑታል፡፡ ይህ ነው እንግዲህ ጽንፈኝነት ማለት!
  ነቢዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ዓይነት ጽንፈኛ ቡድኖች ወደፊት እንደሚነሱ ተንብየዋል፡፡ የጽንፈኝነቱ የመጀመሪያው ምልክትም በኸሊፋ ዑመር (ረ.ዐ) ዘመን ታይቷል፡፡ ከዚያም የዑስማን መንግሥት በነዚህ ጽንፈኞች ታውኳል፤ ኸሊፋ ዑስማንም በነርሱ እጅ ተገድለዋል፡፡ በኸሊፋ ዓሊ ዘመን ደግሞ ጽንፈኞቹ ለይቶላቸው ከኸሊፋቸው ጋር በግልጽ ተዋግተዋል፤ ከኸሊፋው ጋር የቆሙትንም “ከእስልምና የወጡ ካፊሮች” በማለት ፈርጀዋቸዋል፡፡ በመጨረሻም የዓሊ ህይወት በነርሱ እጅ ጠፍቷል፡፡
   በዚህ ዘመን የተነሱት ጽንፈኞችም የነዚያዎቹ ተከታዮች ናቸው፡፡ ነገር ግን ክርር ያለው አካሄዳቸው ለየትኛውም ሰው ስለማይመች ተቀባይነት አያገኙም፡፡ በተጨማሪም ከክር የቀጠነው ጽንፈኝነታቸው አንድነታቸውን ጠብቀው እንዲሄዱ አያስችላቸውም፡፡ በታሪክ እንደታየው እንዲህ ዓይነት ቡድኖች በጥቂት ዓመታት ውስጥ በብዙ ቡድኖች ተፈረካክሰው እርስ በረስ መባላት ይጀምራሉ፡፡ በዓሊ ዘመን የተነሱት የ“ኸዋሪጃ” ጽንፈኞች ተፈረካክሰው እንደጠፉት ሁሉ በሌሎች ዘመናት የተነሱ ጽንፈኞችም ራሳቸውን በራሳቸው ያጠፋሉ፡፡ የአሁኖቹም መንገዳቸው ይኸው ነው፡፡

===ጽንፈኞችና ሽብር===

ቀደም ብዬ እንደገለጽኩት ለጂሃድ የወጣ ሰው የሚዋጋው መሳሪያ ታጥቆ ለውጊያ ከተሰለፈ ሀይል ጋር ነው፡፡ በውጊያው ውስጥ ባልተሰለፉ ሲቪል ዜጎች ላይ ጥቃት ማድረስ በፍጹም አይፈቀድለትም፡፡ የዘመናችን ጽንፈኞች ግን ከዚህ መርህ ጋር የሚተዋወቁ አልሆኑም፡፡ ዓላማቸውን ለማሳካት የሚጠቀሙበት ዋነኛ ዘዴ ሽብር ፈጠራ ነው፡፡ ጽንፈኞቹ በሚያደርሱት ጥቃት የሚሸበሩትም ሆኑ የሚሞቱት በአብዛኛው ሲቪሎች ናቸው፡፡ ንጹሐንን እየቀጠፉ ነው “ለእስልምና ነው የምንታገለው” የሚሉት፡፡
እስልምና ግን እንዲህ የዘቀጠ ርዕዮት አይደለም፡፡ ኢስላም የሰው ልጅ ከየትኛውም ፍጥረት በላይ የተከበረ መሆኑን ነው የሚያስተምረው፡፡ ቅዱስ ቁርኣን “አንዲት ነፍስን ያለ ሐቅ ያጠፋ ሰው በምድር ላይ የሚኖሩ ሰዎችን በሙሉ እንደገደለ ይቆጠራል” ይላል፡፡ ጽንፈኞች በምን ማስረጃ ነው ይህንን ቁርኣናዊ ህግ የሚሞግቱት?… “ለአሜሪካ መንግሥት ታክስ የሚከፍል ሁሉ የእስልምና ጠላት ነው” የሚል ሎጂክ በጭራሽ ኢስላማዊ መሰረት የለውም፡፡ ኢስላም በግልጽ በተደነገገ ህግ ነው የሚተገበረው፡፡ እንደ ኒኮሎ ማኪያቬሊ “ወደ እውነት ለመድረስ በብዙ ውሸቶች ውስጥ መዘፈቅ” ወይንም “ዜጎችን እየጨረሱ ወደ ውጤት መድረስ” የሚል መመሪያ በእስልምና ውስጥ የለም፡፡ ሽብር ምን ጊዜም ቢሆን ሽብር ነው፡፡

==ጽንፈኞችና ብዝሐነት==

የጽንፈኛውን የኢራቅ ሚሊሻ መነሳትን ተከትሎ የዓለም ሚዲያዎችን የተቆጣጠረው ሌላኛው ርዕስ “ሙስሊም ያልሆኑ ወገኖች በግዴታ እስልምናን እንዲቀበሉ ተደርገዋል” የሚል ነው፡፡ ጽንፈኞች ለዚህኛው አድራጎታቸውም “እስልምና እንደዚያ እንድናደርግ አዟል” ይሉናል፡፡ ለመሆኑ ቅዱስ ቁርኣን “ሌሎችን በግዴታ እንዲሰልሙ አድርጉ” ይላል? በፍጹም! ቅዱስ ቁርኣን እንዲህ ነው የሚለው፡፡

لَاۤ اِکۡرَاہَ فِی الدِّیۡنِ ۟ۙ قَدۡ تَّبَیَّنَ الرُّشۡدُ مِنَ الۡغَیِّ

“በሀይማኖት ማስገደድ የለም፤ ቀጥተኛው ጎዳና ቀጥተኛ ካልሆነው በርግጥ ተብራርቷል”
(አል-በቀራህ-266)

ነብዩ እና ተከታዮቻቸው በዘመናቸው የነበሩ የበርካታ እምነት ተከታዮች እምነታቸውን እንዲቀይሩ ያላስገደዱት በዚሁ ቁርአናዊ መመሪያ ስለሚመሩ ነው፡፡ ክርስቲያኖች፣ አይሁዶች፣ ዞራስትሪያኖች (መጁስ)፣ ሳቢኢን (የጥንታዊ የሜሶጶጣሚያ እምነት ተከታዮች)፣ ቂብጢዎች (የጥንታዊ የግብጽ እምነት ተከታዮች)፣ የዚዲዎችና ሌሎችም ከሙስሊሞች ጋር በሰላም ይኖሩ ነበር፡፡ አሁን እንደምንሰማው ቤተክርስቲያንና ምኵራብ ማፍረስም ሆነ ቄስና ካህን መግደል በዚያ ዘመን በጭራሽ አልነበረም፡፡ ጽንፈኞች የሚነዙት ወሬ ከየትኛውም እስላማዊ መመሪያ ጋር አይጣጣምም፡፡
   በዚያ ዘመን ነቢዩና ተከታዮቻቸው በግልጽ የተዋጉት ከአይሁዶች ጋር ነው፡፡ ይህም በሀይማኖታቸው ምክንያት አይደለም፡፡ አይሁዶቹ የመዲና ከተማን ደንብ አክብረው ለመኖር የገቡትን ቃል-ኪዳን አፍርሰው ከነቢዩ ጠላቶች ጋር በመወገን ስለተዋጓቸው ነው፡፡ በዚህም  የተነሳ አይሁዶቹ ለጥፋታቸው ተመጣጣኝ ቅጣት ከፍለው በከተማዋ እንዲኖሩ፤ አሊያም ከተማዋን ለቀው እንዲሄዱ ምርጫ ተሰጣቸው፡፡ ጥቂቶች ቅጣቱን ለመክፈል ተስማማሙ፡፡ አብዛኞቹ ግን ከተማዋን ለቀው ወደ ተቡክ (አሁን ሳዑዲና ዮርዳኖስ ድንበር) ተሰደዱ፡፡
  ነብዩ በሀይማኖት የተነሳ ከክርስቲያኖች ጋር የተጋጩበት የታሪክ አጋጣሚ የለም፡፡ በዑመር (ረ.ዐ) ዘመን ደግሞ አስገራሚ ድርጊት ተፈጽሟል፡፡ በወቅቱ ሙስሊሞቹ ከሮማዊያን ጋር በፍልስጥኤም ምድር እየተዋጉ ነበር፡፡ ሙስሊሞቹ አሸንፈው ከተማዋን በያዙበት ቀን ዑመር ሳይጠበቁ ወደ ከተማዋ መጡ፡፡ እኚህ መሪ የትልቅ ግዛት ገዥ ሆነው በመናኛ አለባበስ፣ ያለ አንዳች አጃቢ ወደ ከተማዋ በመግባታቸው ብዙዎች ተደነቁ፡፡ ከሁሉም በላይ በድርጊቱ የተደነቁት ግን የእየሩሳሌም ፓትሪያርክ ነበሩ፡፡ ፓትሪያርኩ “ የሙስሊሞቹ መሪ ይህ መናኛ ልብስ የለበሰ እና አጃቢ የሌለው ሰውዬ ከሆነ በርግጥም ይህ ሰው ቅዱስ ነው” በማለት ደመደሙ፡፡ በመሆኑም ዑመር ከቤተ ክርስቲያናቸው ገብተው በሙስሊሞቹ ስርዓት “ሰላት” እንዲሰግዱ ጋበዟቸው፡፡ ዑመርም ግብዣውን ተቀበሉ፡፡ ነገር ግን ከቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ ሳይገቡ በቅጥረ-ግቢው ውስጥ “ሁለት ረከዓ” ሰላት ሰገዱ፡፡ (ዑመር ይህንን ያደረጉት ሙስሊሞች ወደፊት “ዑመር የሰገደበት ቤተክርስቲያን ለኛ የተገባ ነው” የሚል ውዝግብ ሊፈጥሩ ይችላሉ በሚል ምክንያት ነው እንጂ ወደ ውስጥ መግባቱን ጠልተውት አይደለም” )፡፡
*****
ሙስሊሞች፣ ክርስቲያኖች፣ አይሁዶችና ሌሎችም የሃይማኖት ቡድኖች ከዚያ ዘመን ጀምሮ ለብዙ ዘመናት በጉርብትና አብረው ኖረዋል፡፡ የኦቶማን ቱርኮች ኢምፓየር እስከፈረሰበት ድረስ በሙስሊሞች የበላይነት በተመራው ኢስላማዊ ኸሊፌት ውስጥ ክርስቲያኖችም ሆኑ አይሁዶች ሀይማኖታቸውን በግዳጅ እንዲቀይሩ የተደረገበት ዘመን የለም፡፡
  አዳዲሶቹ ጽንፈኞች ግን ከነብዩ ዘመን አስቀድሞ በመካከለኛው ምስራቅ የሚኖሩ የልዩ ልዩ እምነት ተከታዮች ሀይማኖታቸውን እንዲቀይሩ ያስገድዱአቸዋል፡፡ እንዲህ ዓይነት ትምህርት ከእስልምና ጋር ሆድና ጀርባ ነው፡፡ እስልምና እንደዚህ ዓይነት ርዕዮት ያለው ቢሆን ኖሮ በዛሬዋ ኢራቅ ምድር ከአስር የሚበልጡ ጥንታዊ የሀይማኖት ቡድኖች ባልተገኙም ነበር (ከነዚህ ቡድኖች መካከል አንዳንዶቹ ከጥንቱ የሀሙራቢ ዘመን የተረፉ ናቸው)፡፡

==ጽንፈኞች እና ዘመናዊነት==

እነዚህ ጽንፈኞች እስልምና ኋላቀር እምነት ተደርጎ እንዲታይ የሚፈልጉ አሻጥረኞችም ይመስላሉ፡፡ በየትኛውም ሀገር ሲነሱ በቅድሚያ የሚፈጽሟቸው ሁለት ነገሮች አሉ፡፡ አንደኛው በጥንት ዘመናት የተሰሩ ታሪካዊ መዘክሮችንና ቅርሶችን ማውደም ነው፡፡ ሁለተኛው ዘመን ያፈራቸውን የቴክኖሎጂ ትሩፋቶች እርም ማድረግ ነው፡፡ ለዚህም የሚጠቅሱት ምክንያት “በእስልምና ያልተፈቀዱ ናቸው” የሚል ነው፡፡ ይሁንና የእስልምና አስተምህሮ ከነዚህ ጽንፈኞች አባባል ጋር በጭራሽ አይገጣጠምም፡፡ እስቲ በምሳሌዎች ላስረዳ፡፡
  “ጣሊባን” የተባለው ጽንፈኛ ቡድን እ.ኤ.አ በግንቦት ወር 2001 በአፍጋኒስታን ምስራቃዊ ክፍል የነበሩ ሁለት የቡድሃ ሀውልቶችን በታንክ ደምስሷል፡፡ ለእርምጃው የሰጠው ምክንያት “ሀውልት በእስልምና የተከለከለ ነው” የሚል ነው፡፡ በርግጥ በሰው ልጅ አምሳል ሀውልት ማቆም በእስልምና አይፈቀድም፡፡ ይሁንና እስልምና “አዲስ ሀውልት ለራሳችሁ አትገንቡ” ነው የሚለው እንጂ “በጥንት ዘመን የተገነቡ  ሀውልቶችን አፍርሱ” የሚል ትእዛዝ አላስተላለፈም፡፡ እንደዚያ ቢሆን ኖሮ በግብጽ፣ በሶሪያ፣ ኢራቅ (ሜሶጶጣሚያ)  እና ኢራን (ፋርስ) የሚታዩትን በሺህ የሚቆጠሩ ሀውልቶችን በዛሬው ዘመን በቁማቸው ባለገኘናቸው ነበር፡፡
  አዎን! እስልምና ወደነዚህ ሀገራት የገባው ነቢዩ “እጅግ ምርጥ ትውልድ” ባሉት በመጀመሪያው የሰሐባ ትውልድ ዘመን ነው፡፡ ሰሐባዎቹ በግብጽ ያሉትን ፒራሚዶች፣ ቤተ-መቅደሶች፣ ስፊኒክሶችና ልዩ ልዩ ሐውልቶች (ታላቁን የራምሰስ ሀውልትን ጨምሮ) “ንክች” አላደረጓቸውም፡፡ በኢራቅና በኢራን የነበሩትንም እንደዚያው፡፡ እነዚያን ጥንታዊ ሀውልቶችንና ቤተመቅደሶችን ማፍረስ በእስልምና የታዘዘ ቢሆን ኖሮ የነቢዩ ሰሐባዎች አንዳቸውንም ሳያስቀሩ ድምጥማጣቸውን ባጠፏቸው ነበር፡፡ ይሁንና ሰሓቦች እንደ አሁኖቹ ጽንፈኞች አዕምሮ ቢስ አልነበሩም፡፡ እነዚያ ጥንታዊ ግንባታዎች በልዩ ልዩ የዘመን ፈተናዎች ውስጥ አልፈው ወደነርሱ ዘመን እንደተሸጋገሩ ይረዳሉ፡፡ ስለዚህ አንድም ዓይነት የማጥፋት ሙከራ ሳይፈጽሙባቸው ጥንት እንደነበሩት ተዋቸው፡፡
  የዘመናችን ጽንፈኞች ሌላው መታወቂያ ዜጎች ዘመን ባፈራቸው የቴክኖሎጂ ውጤቶችና ቀልጣፋ አሰራሮች እንዳይጠቀሙ መከልከል ነው፡፡ ጽንፈኞቹ በዚህ አስተሳሰባቸው በጥንታዊ ጋርዮሽ ዘመን ከነበረ ሰው ጋር እንኳ የሚወዳደሩ አይደሉም፡፡ በጣም ልብ የሚነካው እስልምና በነዚህ ቴክኖሎጂዎችና ውጤታማ አሰራሮች መጠቀምን የሚከለክል አድርገው መለፈፋቸው ነው፡፡  “እግር ኳስ ለምን አየህ” በሚል ምክንያት ዜጎችን በጅራፍ መግረፍን የመሳሰሉ ቅጣቶችንም ይፈጽማሉ፡፡
  እስልምና አዳዲስ የቴክኖሎጂ ውጤቶችና በተቀላጠፈ አሰራር መጠቀምን ይከለክላል?… በጭራሽ!! ነቢዩ እንዲህ ዓይነት ትምህርት በጭራሽ አላስተማሩም፡፡ አላህ በቅዱስ ቁርኣን እርም ካደረጋቸው ድርጊቶችና መጠቀሚያዎች ውጪ ነቢዩ እርም ያደረጉት የተለየ ነገር የለም፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ነቢዩና ተከታዮቻቸው ድሮ የማያውቁት አዲስ ፈጠራ ወይንም አዲስ አሰራር እንዳለ ሲነገራቸው በስራ ላይ በማዋል አንደኛ እንደነበሩ የህይወት ታሪካቸው ያስረዳል፡፡ ለምሳሌ ያህል እነዚህን መጥቀስ እንችላለን፡፡
·        ነቢዩ በዘመናቸው ለነበሩት ነገሥታት ደብዳቤ መጻፍ አስፈለጋቸው፡፡ አንዱ ባልደረባቸው “ደብዳቤው ከርስዎ የተላከ መሆኑን የሚያረጋግጥ ማህተም ያስፈልግዎታል፤ ማህተም ቢያስቀርጹ መልካም ይመስለኛል” አላቸው፡፡ ነቢዩ የማህተም አስፈላጊነት ሲነገራቸው እምቢ አላሉም፡፡ ሃሳቡን ወዲያውኑ ተቀብለው አዲስ ማህተም አስቀረጹ፡፡
·        የቁሬይሽ ተዋጊዎች በመዲና ላይ ሶስተኛ ዙር ወረራ ሊፈጽሙ ተነሱ፡፡ ከቁሬይሾች ጋር በርካታ ማህበረሰቦች ማበራቸውም ተሰማ፡፡ ይህም ወሬ ለነቢዩ ደረሳቸው፡፡ ነቢዩ በጉዳዩ ላይ ከባልደረቦቻቸው ጋር ሲወያዩ ሳልማን አል-ፋርሲ የሚባለው ባልደረባቸው “በከተማችን ዙሪያ ምሽግ ብንቆፍር ጠላቶታችንን በቀላሉ መመለስ እንችላለን” አላቸው፡፡ ሳልማን የፋርስ (ኢራን) ተወላጅ ነው፡፡ በሀገሩ ሲደረግ ያየውን ነው ለነቢዩ የነበረው፡፡ እስከዚያ ጊዜ ድረስ “ምሽግ” በዐረቦች ዘንድ የማይታወቅም ነበር፡፡
በመሆኑም ነቢዩ ምሽግ በመቆፈሩ ብልሃት ተገረሙ፡፡ በተግባር ላይ ሊያውሉትም ተነሱ፡፡ የመዲና ከተማን ከዳር እስከ ዳር በምሽግ ቁፋሮ አጠሯት፡፡ የመካ ቁረይሾች እየፎከሩ ወደ መዲና ሲመጡ ምሽጉ ገደባቸው፡፡ በፈረስና በእግር እየዘለሉ ምሽጉን ለማለፍ ቢሞክሩም ምንም አልተሳካላቸውም፡፡ ይህ ሁኔታ ሌሊቱን ከጣለው ከባድ ዝናብ ጋር ተዳምሮ በጣም አስፈራቸው፡፡ በመሆኑም እቃቸውን እንኳ በወጉ ሳይሰበስቡ ወደመጡበት ፈረጠጡ፡፡
·        በርካታ መልዕክተኞች ወደ ነቢዩ ዘንድ ይመጡ ነበር፡፡ ታዲያ አንዱ የነቢዩ ባልደረባ “ንጉሦችና የጦር መሪዎች መልዕክተኞችን በሚቀበሉበት ጊዜ የአዘቦት ልብሳቸውን አይለብሱም፤ ለየት ያለ ልብስ ለብሰው በርሱ ላይ ካባ ይደርባሉ” አላቸው፡፡ ነቢዩም ምክሩን ተቀብለው በተግባር ላይ አውለውታል፡፡
·        በኸሊፋ ዑመር ጊዜ ታሪኮችን መመዝገብ ተጀምሮ ነበር፡፡ ታሪክ የሚመዘገብበት የቀን መቁጠሪያ ደግሞ በዐረቦች ዘንድ አይታወቅም፡፡ በመሆኑም ዑመር የነቢዩ ስደት (ሂጅራ) እንደ መነሻ ሆኖ እንዲያገለግል ውሳኔ አስተላለፉ፡፡ ይህም ተግባራዊ ሆኖ እስከ አሁኑ ዘመን ድረስ እየተሰራበት ይገኛል፡፡
·        አምስተኛው ኸሊፋ ሙአዊያ ኢብን አቡ-ሱፍያን ደግሞ በተማከለ አሰራር ደብዳቤዎችን ከግለሰቦች ተቀብሎ የሚያከፋፍል ተቋም በመመስረት በዓለም ታሪክ አዲስ አሰራር አስተዋውቀል፡፡ ዛሬ “ፖስታ ቤት” የሚባለውን ተቋም የፈጠሩት ኸሊፋ ሙአዊያ (ረ.ዐ) ናቸው፡፡
·        ዛሬ ዓለም በሙሉ የሚጠቀምበት “የሂንዱ-ዐረብ” የቁጥር ዘዴ የመጨረሻ ቅርጹን ያገኘው በሙስሊሞች አማካኝነት ነው፡፡ ከዚህም ባሻገር ለሂሳብ አቆጣጠር የሚያመቸው “የዜሮ ጽንሰ ሃሳብ” የተፈለሰፈው በ8ኛው ክፍለ ዘመን በባግዳድ ከተማ ነው፡፡
·        የሳይንስና የምርምር ዘርፍ ከፍተኛ እመርታ እንዲሳይ ያደረጉትን አል-ጀብራ፣ አልጎሪዝም እና ሎጋሪዝም የተሰኙ የሂሳብ ስልቶችን የፈጠረው ሙሐመድ ኢብን ሙሳ አል-ኸዋሪዝሚ የተባለ ሙስሊም ሳይንቲስት ነው፡፡
·        ሌላም ብዙ ብዙ መዘርዘር ይቻላል፡፡

እነዚያ የጥንት ሙስሊሞች በአዳዲስ ፈጠራዎች ከመጠቀም አልፈው ለራሳቸውም ልዩ ልዩ ፈጠራዎችን አስተዋውቀዋል፡፡ በአዳዲስ ፈጠራዎች መጠቀም “ውግዝ” ቢሆን ኖሮ ነቢዩና ባልደረቦቻቸው “እርም፤ ነው አትጠጉት” በማለት ክልከላ ያስቀምጡበት ነበር፡፡ ይሁንና የዘመናችን ጽንፈኞች እንዲህ ዓይነቶቹን ታሪኮች ያነበቧቸው አይመስሉም (በጣም የሚያስቀው ነገር ለራሳቸው በዘመናዊ ጠመንዣዎችና በኢንተርኔት ይጠቀማሉ፣ ሌሎችን ግን ከመጠቀም ያግዳሉ)፡፡
 ይህ በፈጠራዎች የመጠቀም ጉዳይ ከተነሳ ዘንድ ግን አንድ ነገር መታወቅ አለበት፡፡ ይኸውም በጥቅም ላይ የሚውለው አዲስ ፈጠራና አሰራር የአላህ ክልከላ ያደረገበትን ድንበር ማለፍ የሌለበት መሆኑ ነው፡፡ ለምሳሌ ማንኛውም የእስልምና ሙፍቲ “አስካሪ መጠጥ ለጤና ይጠቅማችኋል፣ ድንበር ሳታልፉ ጠጡ” በማለት ውሳኔ መስጠት አይችልም፡፡ ቁማርን ህጋዊ ማድረግም በፍጹም አይቻልም፡፡ በሰብዓዊ መብት ስም ግብረ-ሰዶምን ህጋዊ ማድረግም ተቀባይነት የለውም፡፡ ጽንፈኞቹ ግን በነዚህ ላይ ልል አቋም ያላቸው ነው የሚመስሉት፡፡ ለምሳሌ እርግጠኛ ማስረጃ ባይኖረንም ከጽንፈኞቹ መካከል ብዙዎቹ በአደንዛዥ እጽ ንግድ ውስጥ የተዘፈቁ መሆናቸውን እንሰማለን፡፡

===እንደ ማጠቃለያ===

  እነዚህ ጽንፈኞች በየትኛውም ሙስሊም አልተወከሉም፡፡ እስልምናን እንወክላለን ቢሉም ማንም አይቀበላቸውም፡፡ ይሁንና አንዳንድ ሰዎች እስልምናን በነዚህ ጽንፈኞች አድራጎት ሊመዝኑት ይሞክራሉ፡፡ ይህንን ጽንፈኝነት እንደ ሰበብ በመቁጠር እስልምናን ጥላሸት ለመቀባት ይሞክራሉ፡፡ ታዲያ ጽንፈኞቹ እንዲስፋፉ እና እንዲጠናከሩ እያደረጉ ካሉት ምክንያቶች አንዱ የእስልምና ጠላቶች በሀይማኖቱ ላይ የሚያካሄዱት ይህንን የመሰለ የስም ማጥፋት ዘመቻ ነው፡፡ ሙስሊሞችም ሆኑ ሙስሊም ያልሆኑ ምሁራን እንዲህ ዓይነት ምግባሮችን አይተው እንዳላዩ ሆነው ማለፍ የለባቸውም፡፡ በተቻለው መጠን ጽንፈኞቹ የሚፈጽሙት አድራጎት ነቢዩ ያስተማሩትን እስልምና እንደማይወክል ማስረዳት ይገባቸዋል፡፡
በሁለተኛ ደረጃ “ጽንፈኝነት” በሀይማኖት ያልተገደበ ስለመሆኑም መታወቅ አለበት፡፡ ጽንፈኛ ቡድኖች ከየትኛውም ሀይማኖት ሊመነጩ ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ በጥንት ዘመን “Masada” የተሰኘ የአይሁዳዊያን ጽንፈኛ ቡድን ነበር፡፡ ዛሬም በእስራኤል ውስጥ በመቶ የሚቆጠሩ እጅግ ጽንፈኛ ቡድኖች አሉ፡፡ በ7ኛው ክፍለ ዘመን ደግሞ “ኸዋሪጃ” የሚባሉት ጽንፈኞች ከሙስሊሙ ዓለም ተነስተዋል፡፡ በዘመናችንም አል-ሸባብ፣ አል-ቃኢዳ፣ ቦኮ ሀራም የመሳሰሉት ተፈጥረዋል፡፡ ከክርስትናው ዓለምም በ“መስቀል ጦርነት” የሚያምኑ ጽንፈኛ ቡድኖች በተለያዩ ዘመናት ተነስተዋል፡፡ በዘመናችን በሰሜን ኡጋንዳ ጫካዎች ውስጥ መሽጎ ልዩ ልዩ ሰቆቃዎችን የሚፈጽመው Lords Resistance Army የተባለው ሚሊሺያ “ኡጋንዳን በወንጌልና በአስርቱ ትዕዛዛት እመራታለሁ” እያለ የሚለፍፍ ጽንፈኛ ቡድን ነው፡፡ ከሶስት ዓመታት በፊት ከሰማኒያ የሚበልጡ ንጹሃንን የጨፈጨፈው የኖርዌይ ጽንፈኛ ግለሰብም በሃይማኖቱ ክርስቲያን ነው፡፡ በጃፓን ሜትሮ (የምድር ውስጥ ባቡር) ላይ በመርዝ ጋዝ ንጹሃንን የፈጀው የኡም-ሺኖሮኪዮ ሀይማኖታዊ ቡድን “የፈጣሪን ትዕዛዝ” እተገብራለሁ የሚል ጽንፈኛ ነው፡፡ በሀይማኖት የማያምኑ (ማቴሪያሊስቶች፣ ኮሚንስቶች ወዘተ…) ጽንፈኛ ቡድኖችም በልዩ ልዩ ዘመናት ተነስተዋል፡፡ ስለዚህ ጽንፈኞች የትኛውንም ሀይማኖት መጠቀሚያ በማድረግ ሊነሱ እንደሚችሉ መታወቅ ይገባል፡፡ በዚህ ረገድ ሚዲያዎች ወደ አንድ ሀይማኖት ብቻ ጣታቸውን መጠንቆላቸውን በማቆም ሐቁን እየተነትኑ ማስረዳት ይጠበቅባቸዋል፡፡
   በሶስተኛ ደረጃ ደግሞ ጽንፈኞቹ የሚፈጽሙትን አድራጎት በመመልከት ብቻ አሜሪካና አጋሮቿ የሚፈጽሟቸውን ህገ-ወጥ ድርጊቶች የሚያወድሱ ሰዎችም መታረም አለባቸው፡፡ አሜሪካ ለብሄራዊ ጥቅሟ ስትል የምትፈጽማቸው ድርጊቶች ሁሉ በህገ-ወጥነት መታየት አለባቸው እንጂ ጽንፈኞቹ ከሚፈጽሟቸው አድራጎቶች ጋር መተካካት የለባቸውም፡፡ አሜሪካ ኢራቅን መውረሯ መቼም ቢሆን ህገ-ወጥ ነው (የርሷ እርምጃ ነው የአሁኑን ትርምስምስ ያስከተለው)፡፡ እስራኤል ፍልስጥኤምን አላግባብ ይዛ ህዝቡን መጨፍጨፏ መቼም ቢሆን ህገ-ወጥ ነው፡፡ የጽንፈኞችን ነውረኛ ድርጊቶች ተመልክቶ እነዚህን ህገ-ወጥ ስራዎች ማወደስ በምንም መልኩ ተቀባይነት የለውም፡፡ ሁሉም በየራሱ መንገድ መመዘን አለበት፡፡
*****
---
አፈንዲ ሙተቂ
ነሐሴ 7/2006
ገለምሶ-ሀረርጌ
------

ይህ ጽሑፍ የኔ (የጸሐፊው) ወጥ ስራ ነው እንጂ ጥቂት ሰዎች እንደገመቱት “ትርጉም” አይደለም፡፡ ከዚህ በፊት በየትኛውም ቋንቋ አልቀረበም፡፡ ጽሑፉ ብዙዎች ዘንድ እንዲደርስ Share ብታደርጉት ምስጋናዬ እጅግ የላቀ ነው፡፡ በመጽሔትና በጋዜጣ ማሳተምም ይቻላል፡፡ 

No comments:

Post a Comment