Monday, December 22, 2014

ሁለት ትራጄዲ ተረቶች





ፀሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ


-----
በህይወት እስካለን ድረስ ተረት መተረታችንን አናቆምም፡፡ እነሆ ለዛሬም በምሥራቁ የሀገራችን ክፍል እየተደጋገሙ የሚነገሩ ሁለት ትራጄዲ ተረቶችን አዘጋጅተንላችኋል፡፡

===የተንኮል ገበቴ===

እናት አንድ ልጅ ብቻ ነበራት፡፡ ይህንንም ልጅ በብዙ ልፋት ካሳደገችው በኋላ ለአቅመ አዳም ሲደርስ ዳረችው፡፡ ታዲያ የልጁ ሚስት እናትዬውን የምትወድ አልነበረችም፡፡ በብዙ አድራጎቷ ትበድላታለች፡፡ ይብስ ብሎ ደግሞ እናትየዋ ታወረች፡፡ ሚስትም በደሏን አጠናከረች፡፡ በተለይም ሴትዮዋን በጣም የምትበድለው ለእናትዮዋ በምታቀርበው ምግብ ነው፡፡

 ለምሳሌ ለእራት ገንፎ ስታቀርብላት ባሏም ሆነ ሌላ ሰው ዐይኑን እንዳይጥልበት በገንፎው ላይ ቅቤ ትጨምርበታለች፡፡ ነገር ግን ቅቤው ወደ መሬት እንዲፈስ ገንፎው የሚቀርብበትን ገበቴ በአንድ በኩል በስታዋለች፡፡ ልጁ እናቱ ገንፎ በቅቤ የበላች ስለሚመስለው ሚስቱን አይናገራትም፡፡ ሆኖም ገንፎው ቀስ እያለ ወደ መሬት ስለሚፈስ እናትዮዋ አታገኘውም (እናትዮዋ ዐይነስውር መሆኗን አስታውሱ)፡፡

ዘመን አለፈ፡፡ የልጁ እናትም አረፈች፡፡ ልጅየውም ካገባት ሚስቱ አንድ ልጅ ወልዶ ሞተ፡፡ የትናንትናዋ ሚስት የአዲሱ ልጅ እናት ሆነችና ከልጇ ጋር መኖር ጀመረች፡፡ ልጇ ለአቅመ አዳም ሲደርስ እርሷም በተራዋ ከአንዲት ወጣት ጋር በጋብቻ እንዲጣመር አደረገችው፡፡ ሶስቱ ሰዎች በአንድ ላይ መኖር ጀመሩ፡፡ እናት ስታረጅ እንደ ትልቋ እናት (የሞተችው የቧላ እናት) ታወረች፡፡ አንድ ቀን ምግብ ሲቀርብላት ገንፎው ቅቤ የሌለው ሆነባት፡፡ ወዲያውኑ የሆነ ነገር ትዝ አላትና ገበቴውን መዳበስ ጀመረች፡፡ በርግጥም እንደጠረጠረችው ገበቴው በአንድ በኩል የተበሳ ሆኖ አገኘችው፡፡ እናም ድሮ ስትፈጽመው የነበረውን በደል በማስታወስ ከልቧ አዘነች፡፡ እንዲህም አለች፡፡

“አይ ገበቴ! አይ ገበቴዋ! ከምኔው ዞረሽ ወደኔ መጣሽ?!! ግድ የለም፡፡ የእጄን ነው ያገኘሁት፡፡ ያኔ የባሌን እናት ባልበድል ኖሮ ዛሬ ምግቤ እኔ በቀደድኩት ገበቴ ባልተሰጠኝ ነበር”

የሴትዮዋ ንግግር ከልጁ ሚስት ጆሮ ጥልቅ አለ፡፡ እናም ሚስት በሰማችው ነገር ሽምቅቅ አለች፡፡ “ለካስ የኔም የወደፊት እጣ በዚህች ገበቴ መብላት ነው?” እያለች አሰላሰለች፡፡ ወዲያውኑ የባሏን እናት ይቅርታ ጠይቃ ያቺን የተንኮል ገበቴ እንክትክት አድርጋ ሰባበረቻት፡፡ እናትም ምግባቸው በጤነኛ ገበቴ ይቀርብላቸው ጀመር፡፡

===ሁለቱ አባቶችና ሁለቱ ልጆች===

ልጅና አባት አብረው ይኖሩ ነበር፡፡ አባት ልጁ ትዳር እንዲይዝ ካደረገው በኋላ ሁሉንም ነገር አስረከበው፡፡ ለራሱም ጡረተኛ ሆኖ ከልጁ ቤት ጀርባ ከነበረች አንዲት አነስተኛ ጎጆ መኖር ጀመረ፡፡ ይሁንና አባትዬው በጸባዩ ነጭናጫ ነው፡፡ በተለይ ልጅ ለስራ ወደሌላ ቦታ በሚሄድበት ጊዜ የልጁን ሚስት በሆነ ባልሆነው ይነዘንዛታል፡፡ ሚስትም በንጭንጩ ተማረረችና ባሏ ሲመጣ “ወይ አባትህን ከዚህ ቤት አርቅልኝ፤ ወይ ደግሞ ፍታኝ” አለችው፡፡

ልጁ ወደ አባቱ ሄደና “አባቴ! እዚህ ቤት ስትኖር አፍህን ዝጋልኝ!! ካልሆነ ግን ወደ ገደል እወረውርሃለው” በማለት አስጠነቀቀው፡፡ አባትም “አረ አትወርውረኝ! ከእንግዲህ አፌን እይዛለሁ” በማለት ተማፀነው፡፡ በመሆኑም አባት ከነርሱ ጋር መኖሩን ቀጠለ፡፡ ነገር ግን አባት ቃሉን ሊያከብር አልቻለም፡፡ ልጁ ከቤት እስኪወጣ ጠብቆ ሚስትዬውን ይጨቀጭቃት ገባ፡፡ በዚህ የተናደደችው ሚስት ወደ ባሏ ሄዳ “ነገ አባትህን ከዚህ ቤት ካላስወጣህልኝ እሄድልሃለሁ” አለችው፡፡ ባልም “ግድ የለም! ነገ ገደል ውስጥ እጥለዋለሁ” አላት፡፡

በንጋቱ ልጅየው ሽማግሌ አባቱን ወደ ገደል ሊወረውረው ተነሳ፡፡ ከገደሉ ጫፍ ላይ ካደረሰው በኋላም “አባቴ! ብትፈልግ ገደል ግባ! ብትፈልግ የፈለግከውን ሁን፡፡ አባቴ ስለሆንክ ግን በራሴ እጅ አልወረውርህም፡፡ ትዳሬንም እወዳለሁና ከቤቴ እንድትመለስ አልፈቅድልህም” አለው፡፡ አባትየውንም እዚያው ትቶት ሄደ፡፡

ዘመን አለፈ፡፡ የድሮው ልጅ በተራው አባት ሆነ፡፡ ልጁም አገባ፡፡ አባትም ከልጁ ጋር መኖር ጀመረ፡፡ ታዲያ እርጅና ሲመጣ ይህኛውም  አባት ልክ እንደ ድሮው አባት ጨቅጫቃ ሆነ፡፡ የልጁን ሚስት በረባ ባልረባው ይጨቀጭቃት ጀመር፡፡ ልጁም ጭቅጭቁ ሲሰለቸው አባትዬውን ወደ ገደል ሊወረውረው ተሸክሞት ተነሳ፡፡ ረጅም ርቀት ከተጓዙ በኋላ የታዘለው አባት ልጁን እንዲህ አለው፡፡
  “እዚሁ ጋ ብትተወኝ ይሻለኛል፤ እኔም ያኔ አባቴን ከዚህ አላሳለፍኩትም”፡፡
*****
  አያድርስ ነው ወገን! “ሁሉም የዘራውን ነው የሚያጭደው” የሚለው ምሳሌ አሁን ላይ የማይሰራ ቢመስልም ጊዜው ሲደርስ እውነት መሆኑ አይቀርም፡፡ አላህ ከእንዲህ ዓይነት ክፋት ይጠብቀን፡፡

በነገራችን ላይ የመጀመሪያውን ተረት የነገሩን ጎረቤቴ የነበሩት “ሀቦ ኑሪያ” ናቸው፡፡ ሁለተኛውን ተረት የአባቴ የቅርብ የስጋ ዘመድ ከሆኑት ሼኽ ሙሐመድ ሑሴን ቲርሞ የሰማሁት ነው (በኋላ ላይ ስብሐት ገብረእግዚአብሄር ጽፎት ባነበውም ተረቱን በቅድሚያ የሰማሁት ከሼኽ ሑሴን አንደበት ነው)፡፡
------
አፈንዲ ሙተቂ
ግንቦት 26/2006
አዳማ!!
-----
Afendi Muteki is a researcher and author of the ethnography and history with special focus on the peoples of East Ethiopia. You may follow him on his blog and his facebook page by clicking the following links



No comments:

Post a Comment