Wednesday, December 10, 2014

ሃየሎም አርኣያን በጨረፍታ




(አፈንዲ ሙተቂ)
------
በኢትዮጵያ የታሪክ ሂደት የተፈጠሩ የፖለቲካ ድርጅቶችና ሽምቅ ተዋጊ ቡድኖች በትግል ዘመናቸው ከወደቁ ሰማዕቶቻቸው ሁሉ አግዝፈው የሚመለከቱት አንዳንድ ጀግና አላቸው፡፡ ለምሳሌ የተጋድሎ ሓርነት ኤርትራ ( ጀብሃ) ትልቁ ሰማዕት “ዑመር እዛዝ” ይባላል፡፡ የህዝባዊ ግንባር ሓርነት ኤርትራ (ሻዕቢያ) ታላቅ ሰማዕት ደግሞ “ኢብራሂም አፋ” ነው፡፡ የኢትዮጵያ ህዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢህአፓ) ትልቁ ሰማዕት “ተስፋዬ ደበሳይ” ነው፡፡ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) “ታላቁ ሰማዕት” ኤሌሞ ቂልጡ ይባላል፡፡ የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) አባላት በበኩላቸው እንደ ትልቁ ሰማዕት የሚያዩት ሃየሎም አርኣያን ነው፡፡

Hayelom Ar'aya


  ታዲያ ሃየሎም ከሌሎቹ ሰማዕታት የሚለይበት አንድ ጠባይ አለ፡፡ ይህም በጀግንነቱ በህወሓት ብቻ ሳይሆን የህወሓት ቀንደኛ ጠላት በሚባሉ ግለሰቦችና ቡድኖች ጭምር የሚወደስ መሆኑ ነው፡፡ እርግጥ ስለሃየሎም ጀግንነት በስፋት መጻፍ የጀመረው እርሱ ከተገደለ በኋላ ነው፡፡ ሆኖም ሃየሎም በህይወት እያለ እንኳ ስለጀግንነቱ ሲሰጡ የነበሩ የምስክርነት ቃሎችን በልዩ ልዩ የፕሬስ ውጤቶች ላይ አንብበናል፡፡ ለምሳሌ የቀድሞው የኢህዴን ሊቀመንበር ያሬድ ጥበቡ (ጌታቸው ጀቤሳ) “መስታወት” በተሰኘ መጽሔት ላይ በጻፉት አንድ ጽሑፍ ሁሉንም የኢህአዴግ መሪዎች በፈሪነት ከፈረጇቸው በኋላ ሃየሎም አርኣያን ብቻ በጀግንነት አወድሰዋል፡፡ በኤርትራና በትግራይ ሲዋጉ የነበሩ የደርግ የጦር መኮንኖችም በተለያዩ መጽሔቶች ስለሃየሎም ኣርኣያ ጀግንነት ሲያወሱ ነበር፡፡

 በመሆኑም በሃየሎም የጦር ሜዳ ጀግንነትና በወታደራዊ ጥበብ አዋቂነቱ ላይ ጥርጣሬ የሚቀርብ አይመስለኝም፡፡ ሆኖም የሃየሎምን አሟሟት ያየ ሰው “ሰውዬው ሰማዕት ነው ሊባል ይችላልን?” የሚል ጥያቄ ሊያቀርብ ይችላል፡፡ ምክንያቱም በተለምዶ ሰማዕታት የሚባሉት በትግሉ ሂደት ሲዋጉ የወደቁ ሰዎች ናቸውና፡፡ ሃየሎም የተገደለው ግን የትጥቅ ትግሉ ካበቃ ከአራት ዓመታት በኋላ በተከሰተ ጸብ ነው፡፡

 የኢህአዴግ ሰዎች “ሃየሎም በሰላም ጊዜ በሚደረገው ትግል መሃል የወደቀ ጓዳችን በመሆኑ ሰማዕት ነው” እንደሚሉ ይታወቃል፡፡ ከሰማዕታቱ መካከል የተናጥል ሃውልት ያቆሙትም ለርሱም ብቻ ነው፡፡ ሌሎች ወገኖችስ በሰማእትነቱ ላይ ምን ይላሉ? በጉዳዩ ላይ ያላቸውን አቋም እንዲነግሩን እንጠብቃለን፡፡
*****
ሃየሎም አርኣያ ህወሓት (በኋላም ኢህአዴግ) ባካሄዳቸው ዋና ዋና ዘመቻዎች ላይ የመሪነት ሚና ነበረው፡፡ ከነዚያ ዘመቻዎች መካከል ከስሙ ጋር ተቆራኝቶ የቀረው በየካቲት ወር 1978 የተካሄደው “ኦፕሬሽን አግአዚ” ነው፡፡ ይህንን ኦፕሬሽን የሚመለከት ጽሑፍ ለመጀመሪያ ጊዜ ያነበብኩት በሚያዚያ 1985 በታተመው “እፎይታ” መጽሔት ላይ ነው፡፡ ተራኪው ደግሞ ሃየሎም አርኣያ ራሱ ነበረ፡፡

 ታዲያ ጽሑፉ በጣም የሚያስደምም በመሆኑ ብዙዎች ታሪኩን በመጠራጠር “ሰውዬው የተናገረው ልብወለድ ነው እንጂ እውነተኛ ነገር  አይደለም” ብለው ነበር፡፡ በዘመኑ ከኢህአዴግ በታቃራኒነት የተሰለፉት የደርግ ከፍተኛ ባለስልጣናት “ኦፕሬሽን አግአዚ” በትክክል የተፈጸመ ዘመቻ መሆኑን መናገር ሲጀምሩ ግን የሃየሎም ትረካ እውነተኛት ሊረጋገጥ በቅቷል፡፡ በዚህ ረገድ የመጀመሪያውን ምስክርነት የሰጡት ጓድ መንግሥቱ ኃይለማሪያም እራሳቸው ናቸው (በ1994 የታተመውን የሌ/ኮ/ መንግሥቱ ኃይለማሪያም ትዝታዎችን ያስታውሱ)፡፡ በማስከተልም “ነበር” የተሰኘውን ተወዳጅ መጽሐፍ የጻፉት ገስጥ ተጫኔ (ዘነበ ፈለቀ) “ኦፕሬሽን አግአዚ” በትክክል መፈጸሙን አረጋግጠዋል፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው፡፡

   “ኦፕሬሽን አግአዚ” በመቀሌ እስር ቤት ታስረው የነበሩ ከሶስት ሺህ የሚበልጡ የህወሐት ታጋዮችንና ደጋፊዎችን የማስለቀቅ ተልዕኮ ነበረው (ኦፕሬሽኑ የተሰየመለት “አግዓዚ” የሚባለው ታጋይ ከህወሐት መስራቾች አንዱ ነው፤ “አግዓዚ” የትግል ስሙ ሲሆን እውነተኛ ስሙ “ዘርዑ ገሠሠ” ነበር)፡፡ እንደ ጄኔራል ሃየሎም አርኣያ አገላለጽ ኦፕሬሽኑን ለማካሄድ የሚያስፈልገው ቅድመ ዝግጅት ለስድስት ወራት ያህል ተካሄዷል፡፡ በኦፕሬሽኑ የሚሳተፉ ኮማንዲስቶች በሚስጢር ነው የሰለጠኑት፡፡ ሆኖም ሰልጣኞቹ በስልጠናው ላይ በነበሩበት ወቅት ስለኦፕሬሽኑ ምንም መረጃ አልነበራቸውም፡፡ በመሆኑም እነዚያ ሰልጣኞች ለስልጠናው ወደተዘጋጁት የአሸዋ ቤቶች በሚወሰዱበት ጊዜ ከፊሉ “ይህ የመቀሌ ቤተ መንግሥት ነው” ይሉ የነበረ ሲሆን የተቀሩት ደግሞ “አይ! የአየር ማረፊያው ነው” እያሉ ልዩ ልዩ መላምቶችን ይደረድሩ ነበር፡፡

  “ኦፕሬሽን አግአዚ” በታቀደለት ጊዜ ተካሄደ፡፡ የህወሓት አሸማቂዎችም ማንም ባልጠበቀው ሁኔታ ወደ መቀሌ እስር ቤት በመግባት የሚፈልጓቸውን ታሳሪዎች በሙሉ አስለቀቁ፡፡ በማግስቱ ወሬው በአዲስ አበባ ሲሰማ በሊቀመንበር መንግሥቱና በጦር ጄኔራሎቻቸው ዘንድ ከፍተኛ ቁጣ ተቀሰቀሰ፡፡ መቀሌ ያሉ የጦር መሪዎችም ለአስቸኳይ ግምገማ ተጠሩ፡፡ በግምገማው ማብቂያም “ለኦፕሬሽኑ መሳካት ትልቁን ሚና የተጫወተው በአካባቢው የነበረው አብዮታዊ ጦር አዛዥ የነበረው ብ/ጄኔራል ታሪኩ ዐይኔ ያሳየው እንዝህላልነት ነው” ተባለ፡፡

  የደርግ መንግሥት ባለስልጣናት ታሪኩን ሲጽፉ “የህወሓት ጦር በእስር ቤቱ ላይ ወረራ በፈጸመበት ወቅት የእስር ቤቱ ሃላፊ ወደ ጄኔራል ታሪኩ በመደወል “በወንበዴ ተወርሬአለው፤ ባሉኝ ጠባቂዎች መከላከል ስለማልችል ረዳት ጦር በአስቸኳይ ይላኩልኝ” በማለት ሲጠይቀው ጄኔራል ታሪኩ “እኔ መደበኛ ወታደር እንጂ የእስር ቤት ጠባቂ ዘበኛ አይደለሁም” የሚል የሹፈት መልስ ሰጥቶት ከቤቱ ገብቶ ተኝቷል፤ የአንድ አብታዊ ጦር ዋና ዓላማ ሀገሩን ከውጭ ወራሪዎችና ከውስጥ ወንበዴዎች መከላከል ሆኖ ሳለ ጄኔራል ታሪኩ ረዳት ጦር ለወህኒ ቤቱ እንዳይደርስ በማድረጉ ወያኔ ታሳሪዎቹን በቀላሉ ለማስመለጥ ችሏል፤ በዚህም ጄኔራሉ የወንበዴዎቹ ዓላማ ተባባሪ ሆኗል” ይላሉ፡፡

 በተለይ ግን ጓድ መንግሥቱ ኃይለማሪያም “ኦፕሬሽን አግአዚ”ን በምሬት ነው የሚያነሱት፡፡ ጓድ መንግሥቱ “ወያኔ በዚያ ድንገተኛ ወረራ ሊያመልጡ የማይገባቸውን ወንጀለኞች ለማስለቀቅ ችሏል” በማለት ለጋዜጠኛ ገነት አየለ አንበሴ ነግረዋታል፡፡ ሆኖም ለወንበዴዎቹ ድጋፍ ሰጥተዋል በተባሉት ጄኔራል ታሪኩ ዐይኔ ላይ መጥፎ እርምጃ አልተወሰደም፡፡ ጓድ መንግሥቱ ይህንንም ሲያብራሩ “የታሪኩ ጓደኛ የሆኑ የጦር መሪዎች በአማላጅነት ወደኔ መጥተው “ጓድ ሊቀመንበር! ታሪኩን በዚሁ ብቻ ከምንመዝነው ወደ ኤርትራ ይላክና ችሎታውን ያሳይ” ስላሉኝ እኔም ቃላቸውን በመቀበል ወደ አፋቤት ልኬዋለሁ” ብለዋል (ሆኖም ጄኔራል ታሪኩ ወደ አፋቤት ቢቀየርም ከአራት ዓመታት በኋላ ተረሽኗል)፡፡

እነ ሃየሎም አርኣያ በበኩላቸው በጄኔራል ታሪኩ ላይ የቀረበውን ክስ አይቀበሉም፡፡ ሃየሎም ስለጉዳዩ ሲናገር “ጄኔራሉ ጦሩን ለማንቀሳቀስ ያልቻለው በእንዝህላልነት ሳይሆን የኛ ጦር በመቀሌ ከተማ የተለያዩ ስፍራዎች የማዘናጊያ ውጊያዎችን በመክፈቱ መደበኛው ወታደር በነዚያ ውጊያዎች ስለተወጠረ ነው፤ እኛም የማዘናጊያ ውጊያዎቹን ሽፋን በማድረግ ያለምንም ስጋት እስረኞቹን ለማስለቀቅ ችለናል” ብሏል፡፡ 

   “ኦፕሬሽ አግዓዚ”ን በተመለከተ አከራካሪ ሆኖ የዘለቀ አንድ ጉዳይ አለ፡፡ ይህም ኦፕሬሽኑን ለማካሄድ የወሰደውን ጊዜ የሚመለከት ነው፡፡ ጄኔራል ሃየሎም አርኣያ “ኦፕሬሽኑ የተካሄደው በአስራ አምስት ደቂቃ ውስጥ ነው፤ በዚህ ጊዜ ውስጥ ስራችንን ሙሉ በሙሉ መጨረስ እንደምንችል ያወቅነው ስልጠናው በሚካሄድበት ወቅት ነው” ብሏል፡፡ የደርግ ባለስልጣናት ይህንን ጉዳይ በተመለከተ ዘርዘር ያለ ነገር ባይጽፉም ኦፕሬሽኑ በአጭር ጊዜ ውስጥ መፈጸሙን በደፈናው ያምናሉ፡፡  (በነገራችን ላይ የ“ኦፕሬሽን አግአዚ”ን ታሪክ መሰረት ያደረጉ ሁለት ፊልሞች ተሰርተዋል፤ አንደኛውን ፊልም ያዘጋጀው ታዋቂው አርቲስት ኪሮስ ኃይለ ሥላሤ ሲሆን የሁለተኛውን ፊልም አዘጋጅ ማንነት በትክክል አላውቅም፤ ሆኖም ሁለቱ አዘጋጆች “ኦሪጂናሌው ታሪክ የኔ ነው” በሚል ውዝግብ ፈጥረው እንደነበረ አስታውሳለሁ)፡፡
*****
ሃየሎም አርኣያ የተገደለው በየካቲት ወር 1988 ነው፡፡ ታዲያ የርሱ ሞት ከፍተኛ የመነጋገሪያ ርዕስ ሆኖ ነበር፡፡ በኦፊሴል የወጣው የኢትዮጵያ መንግሥት መግለጫ አሟሟቱን ሲያስረዳ “ጄነራል ሃየሎም አርኣያ ጀሚል ያሲን ከሚባል ኤርትራዊ ወጣት ጋር በተፈጠረ ጸብ ተገድሏል” ነው ያለው፡፡ ጥቂት የማይባሉ ሰዎች ግን የሞቱን ምክንያት ሲያስረዱ “ኤርትራ በሓኒሽ ወደቦች ምክንያት ከየመን ጋር በተጣላችበት ወቅት ሃየሎም አርኣያ “ከኤርትራ መንግስት ጋር ያለን ግንኙነት እንደማንኛውም ኢንተርናሽናል ግንኙነት መታየት አለበት፤ በተለይም በወታደራዊ መስክ ያለን ግንኙነት በሀገራችን ላይ አደጋ የሚጋብዝ መሆን የለበትም፤ ከኤርትራ ጎን ሆነን የምንዋጋበት ምክንያት ሊኖር አይገባም” የሚል አቋም በማራመዱ የሻዕቢያ ጥይቶች ሰለባ ለመሆን በቅቷል” ብለው ነበር፡፡ እነዚህ ወገኖች “የሃየሎም አርኣያ ገዳይ ኤርትራዊ መሆንም ይህንኑ ያረጋግጣል” በማለትም አክለዋል፡፡ ከዚህም አልፎ “በስልጣን ላይ የነበረው የአቶ መለስ ዜናዊ አመራር የግድያው ተባባሪ ነው” የሚሉ በርካታ ሰዎች አሉ፡፡

  ሃየሎምን ተኩሶ የገደለው ወጣት ጀሚል ያሲን ከመሞቱ በፊት ከእፎይታ መጽሔት ጋር ባደረገው ቃለ-መጠይቅ “በምሽቱ ሐሺሽ ወስጄ ነበር፤ በሐሺሽ ተገፋፍቼ ነው የገደልኩት እንጂ የተለየ ጠብ ኖሮን አይደለም” የሚል ቃል ነው የተናገረው፡፡ ሃየሎም በሞተበት ወቅት በአጠገቡ የነበሩት ሰዎችም “ወጣት ጀሚል በስካር ጥንብዝ ብሎ ሃየሎምን በባለጌ ስድቦች ይሳደብ ነበር፤ ሃየሎም ለረጅም ጊዜ ከታገሰው በኋላ ትዕግስቱ ሲያልቅበት ሁለት ጥፊ አቀመሰው፣ በዚህ የተናደደው ጀሚል ሽጉጡን ከመኪናው ውስጥ አምጥቶ ገደለው” የሚል ምስክርነት ሰጥተዋል፡፡

  መንግሥታት በርካታ ጉዳዮችን ሚስጢራዊ ማድረጋቸው የተለመደ ቢሆንም የሃየሎም ሞት ሙሉ በሙሉ ሚስጢራዊ ሆኖ ቀርቷል ለማለት ምንም ዋስትና የለንም፤ እንዲህ የምንለው ከበርካታ ማዕዘናት በመነሳት ነው፡፡ ለምሳሌ የህወሐት (ኢህአዴግ) ባለስልጣናት በየጊዜው ፓርቲውን ለቀው ይኮበልላሉ፡፡ ሆኖም ከነዚያ ባለስልጣናት መካከል አንዳቸውም ቢሆኑ “ሃየሎም ሻዕቢያ በሸረበው ሴራ ነው የተገደለው” በማለት ሲናገሩ አልሰማናቸውም፡፡ ከአቶ መለስ ጋር ተጋጭተው ከድርጅቱ የወጡትና ከመለስ በላይ ሃየሎምን በቅርበት የሚያውቁት አቶ አረጋዊ በርሀም አቶ መለስን በሃየሎም ግድያ ሲከሷቸው አልተሰሙም፡፡ ከህወሐት ጋር ታሪካዊ ጠላት ሆነው የዘለቁት አቶ አብረሃም ያየህም “ኤርትራ ኢትዮጵያን የወረረችው በአቶ መለስ ዜናዊ አደፋፋሪነት ነው” እያሉ ቢጽፉም ለሃየሎም ሞት ሻዕቢያንም ሆነ አቶ መለስ ዜናዊን ተጠያቂ ሲያደርጉ አላየናቸውም፡፡ ከህወሓት ያፈነገጡት እነ ተወልደ ወልደማሪያምና ስየ አብረሃም ለሻዕቢያ ወረራ በየጊዜው የአቶ መለስን ቡድን ተጠያቂ ማድረጋቸው እንደተጠበቀ ሆኖ የሃየሎምን ግድያ ከኤርትራ ጉዳይ ጋር  ሲያገናኙት አልተደመጡም፡፡

ሻዕቢያ ሃየሎምን አስገድሎት ሊሆን ይችላል የሚሉ ሰዎች በበኩላቸው “ሴራውን ይገልጻሉ” የሚሏቸውን አንዳንድ ምልክቶችን ይደረድራሉ፡፡ ለምሳሌ ሃየሎም ከሞተበት ዕለት ጀምሮ የኤርትራ ሚዲያዎችና ዌብሳይቶች ሰውዬውን በጀግንነቱ ሲያደንቁት እንጂ በአሉታዊ መልኩ ሲያነሱት አይታዩም፡፡ የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት በሚካሄድበት ወቅት እንኳ የኤርትራ ሬድዮ “የአቶ መለስ አገዛዝ ሃየሎምን የመሰለ የጦር ጀግና ያስበላ የወንበዴ ቡድን ነው” ይል ነበር፡፡ እናም በርካታ ሰዎች “እነዚህ የኤርትራ ሚዲያዎች ሃየሎምን የሚያደንቁት የግድያው ሚስጢር እንዳይወጣ ለማፈን ቢሆንስ?” የሚል የጥርጣሬ ጥያቄ ያቀርባሉ፡፡

 በኛ በኩል “ተጨባጩ እውነታ ይህ ነው” ብለን ምስክርነት መስጠት አንችልም!! በግድያው ዙሪያ በኢንተርኔትም ሆነ በፕሬስ ሲጻፍ የነበረው ሁሉ ጥርጣሬ እንጂ ሐቅ ነው ለማለት አያስደፍርም፡፡ ጥርጣሬ እውነትም ሊሆን ይችላል፤ ውሸትም ሊሆን ይችላል፡፡ ሆኖም የታሪክ ተመራማሪዎች  አንድ ቀን ሐቁን ያሳውቁናል ብለን ተስፋ እናደርጋለን!! በዚህ አጋጣሚ የማንክደው ነገር ቢኖር ሃየሎም አርኣያ የጦር ሜዳ ጀግና የነበረ መሆኑን ነው፡፡
----
  አፈንዲ ሙተቂ
ጥቅምት 7/2007
ገለምሶ-ሀረርጌ

No comments:

Post a Comment