Friday, December 5, 2014

ሼርሎክ ሆምዝ




(አፈንዲ ሙተቂ)
------
  በ19ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ ላይ ነው፡፡ በታላቋ ብሪታኒያ ዋና ከተማ፡፡ በጊዜው አንድን አስገራሚ ገጸ-ባህሪ ያማከለ ተከታታይ የምርመራ ልብ ወለድ የሚጽፍ ወጣት ደራሲ ነበር፡፡፡ ታዲያ ይህ ደራሲ በዚያ ገጸ-ባህሪው ላይ ለአስር ዓመታት ከጻፈ በኋላ “ኤጭ! ይሄ ሰውዬ አሁንስ እጅ እጅ አለኝ፡፡ ስራ አስፈታኝ እኮ አቦ!… ከዚህ በኋላ ገድዬው ልረፍና ሌላ ድርሰት ልጻፍ” በማለት እራሱ የፈጠረውን ገጸ ባህሪ ይገድለዋል፡፡
 
     ይሁንና ገጸ-ባህሪውን የገደለው ደራሲ እንደተመኘው ሌሎች ድርሰቶችን በሰላም ሊጽፍ አልቻለም፡፡ ሺህ ምንተሺህ ደብዳቤዎች ከየአቅጣጨው ጎረፉለት፡፡ “አንተ ቀፋፊ፣ የማትረባ ወስላታ፣ አረመኔ ነህ” እየተባለ ተወቀሰ፤ ተወገዘ፡፡  “እኛ የምንወደውን ሰውዬ ገድለህ በሰላም መኖር አትችልም! አንተም ዋጋህን ታገኛታለህ” የሚሉ ማስፈራሪያዎችም እየተከታተሉ ደረሱት፡፡ በማስከተልም በሺህ የሚቆጠሩ አንባቢያን በለንደን ጎዳናዎች ላይ ሰላማዊ ሰልፍ በማድረግ ደራሲው የገደለውን ገጸ-ባህሪ ከሞት እንዲያስነሳው ጠየቁት፡፡

  ደራሲው በዚህ ጉዳይ ተጨነቀ፡፡ ተጠበበ፡፡ የህዝቡን ፍላጎት ካላሟላ አደጋ ሊከተለው እንደሚችል ገመተ፡፡ ስለዚህ ሳይፈልግ በግዴታ በራሱ ብዕር የገደለውን ገጸ-ባህሪ ነፍስ ዘርቶበት እንደገና ወደ ስነ-ጽሑፍ ዓለም መለሰው፡፡ ህዝቡም የተመኘውን በማግኘቱ “እፎይ!” አለ፡፡
                                                     *****
  ያ ሰላማዊ ሰልፍ የተወጣለት ገጸ-ባህሪ “ሼርሎክ ሆምዝ” (Sherlock Holmes) ይባላል፡፡ በስነ-ጽሑፍ ዓለም ምንጊዜም ከማይረሱ ልዩ ገጸ-ባህሪያት አንዱ ነው፡፡ ሼርሎክ ሆምዝ የግል ወንጀል መርማሪ ነው፡፡ የመንግሥት ባለስልጣናትም ሆኑ ግለሰቦች አዕምሮአቸውን ያስጨነቀ ወንጀል-ነክ ጉዳይ ሲያጋጥማቸው ወደ ቢሮው እየሄዱ ጉዳያቸውን ያዋዩታል፡፡ እርሱም ልዩ ልዩ ፍንጮችን እየተከተለ ጉዳዩን ከመረመረ በኋላ ውጤቱን ለባለጉዳዮቹ ያሳውቃል፡፡ በዚህም መሰረት ወንጀሉ ተፈጽሞ ከሆነ ወንጀለኛው ርቆ ሳይሄድ በቁጥጥር ስር እንዲውል ይደረጋል፡፡ ወንጀሉ ወደፊት ሊፈጸም የታቀደ ከሆነ ደግሞ ሼርሎክ ሆምዝ ወንጀሉ ከመፈጸሙ በፊት ወንጀለኛውን በቁጥጥር ስር ያውለውና ከነማስረጃው ለፖሊስ ያስረክባል፡፡

  ታዲያ ሸርሎክ ሆምዝ የሚፈጽማቸውን ጀብዱዎች የምንሰማው ከርሱ አንደበት አይደለም፡፡ የዕለት ተዕለት ውሎውን እየተከታተለ ለኛ የሚዘግብልን ዶ/ር ጆን ኤች ዋትሰን የሚባል ጓደኛው ነው፡፡ ዶ/ር ዋትሰን የሼርሎክ ሆምዝ የልብ ጓደኛ እና ሚስጢረኛው ነው፡፡ ሁለቱ ሰዎች ለብዙ ጊዜ አይለያዩም፡፡ አንድ ልዩ ኦፕሬሽን የሚካሄድ ከሆነ ሼርሎክ ሆምዝ ጓደኛው ዶ/ር ዋትሰን እንዲሳተፍበት ያደርጋል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ዋትሰን ከሎንዶን ወደ አውሮጳ እየተላከ ሼርሎክ ሆምዝ የሚፈልጋቸውን መረጃዎች እንዲያሰባስብ ይደረጋል፡፡
 
    በዶ/ር ዋትሰን ገለጻ መሰረት ሼርሎክ ሆምዝ ቀጠን ዘለግ ያለ እንግሊዛዊ ነው፡፡ ቢሮው በደቡብ ለንደን በሚገኘው የቤከር ጎዳና ነው፡፡ አንዲት የነተበች ባርኔጣ ይለብሳል፡፡ አጭር ከዘራም ከእጁ አያጣም፡፡ ሼርሎክ ሆምዝ በጣም አጫሽ ነው፡፡ ፒፓውን ከአፉ የማይነጥል የትምባሆ ሱሰኛ! ደግሞ ግማሽ ጭልፋ የምታክል ሌንስ (አጉሊ መነጽር) ከኪሱ አትጠፋም፡፡ በርሷ ብዙ ነገሮችን ይመረምራል፡፡ በተለይም የሰው ዱካ የሚመረምረው በዚህች ሌንስ ነው፡፡ 
 
    የሼርሎክ ሆምዝ ወንጀል መርማሪነት እንዲህ ቀለል ያለ አይደለም፡፡ ኬሚካሎችንና ቅመማ ቅመሞችን በደንብ ለይቶ ያውቃል፡፡ የሲጋራዎችን አመድ በማየት ብቻ አንድ ሰው ምን ዓይነት ሲጋራ እንደሚያጨስ ለይቶ ያውቃል፡፡ ደግሞም ሼርሎክ ሆምዝ የጁዶ ጥበበኛ ነው፡፡ ወንጀለኞች ሊያጠቁት ከመጡ በጁዶ ይዘርራቸዋል፡፡ በመላው ለንደን በርካታ ሰላዮች አሉት፡፡ ሊስትሮዎች፣ ለማኞች፣ ጎዳና ተዳዳሪዎች፣ ሴተኛ አዳሪዎች፣ የባንክ ሰራተኞች ወዘተ… ልዩ ልዩ መረጃዎች እንዲያመጡለት ይቀጥራቸዋል፡፡ ከነዚህ ምንጮች በሚያገኛቸው መረጃዎች ላይ የራሱን የምርመራ ጥበብ እያከለ አስደናቂ ውጤቶችን ያገኛል፡፡
                                                     *****
    ሼርሎክ ሆምዝን የፈጠረው ደራሲ ሰር አርተር ኮናን ዶይል ይባላል፡፡ በዓለም የስነ-ጽሑፍ ታሪክ ዘወትር ከሚታወሱ ድንቅ ደራሲዎች አንዱ ነው፡፡ ኮናን ዶይል የስኮትላንድ ተወላጅ ነው፡፡ በጉርምስናው ዕድሜ ላይ ህክምናን ሊያጠና ኤዲንበርግ ዩኒቨርሲቲ ይገባል፡፡ ታዲያ እዚያ እያለ ፕሮፌሰር ጆሴፍ ቤል ከሚባሉት አስተማሪው ላይ ባየው ነገር በጣም ይመሰጣል፡፡ እኝህ ፕሮፌሰር ሀኪም ጭምር ናቸው፡፡ የህመምተኞችን በሽታ በትክክል ለማወቅ የሚጠቀሙበት የተጠየቅ (logic) አካሄድና ጥቃቅን የሆነችውን ነገር ሁሉ ለማወቅ የሚያደርጉት ጥረት በወጣቱ ተማሪ አርተር ኮናን ዶይል ላይ የማይረሳ ትውስታ ጥሎ ያልፋል፡፡
   
  ኮናን ዶይል ትምህርቱን ካጠናቀቀ በኋላ የራሱን ክሊኒክ ከፍቶ መስራት ይጀምራል፡፡ ነገር ግን ጀማሪ በመሆኑ የሚመጣለት በሽተኛ በጣም ትንሽ ነበር፡፡ ታዲያ ኮናን ዶይል አልሰነፈም፡፡ የመጡለትን በሽተኞች ካከመ በኋላ በሚኖረው ትርፍ ጊዜ ቁም-ነገር ለመስራት ወሰነ፡፡  በመሆኑም የዩኒቨርሲቲ አስተማሪውን ሁኔታ እያሰበ የሚመጣለትን ሃሳብ በወረቅ ጫር ጫር ማድረግ ጀመረ፡፡ የጻፈውንም The Study in the Scarlet የሚል ርዕስ ሰጠውና Beeton’s Christmas Annual  በተሰኘ መጽሔት ላይ አሳተመው፡፡

     ጽሑፉ “ሼርሎክ ሆምዝ” የተባለ ወንጀል መርማሪ በአስገራሚ የተጠየቅ ዘዴ ወንጀሎችን እንዴት እንደሚመረምር የሚተርክ አጭር ልብ ወለድ ነው፡፡ አንባቢያን ጽሑፉን ስለወደዱት The Strand የሚባል መጽሔት በቋሚነት የሼርሎክ ሆምዝን ታሪክ እንዲጽፍለት ቀጠረው፡፡ ደራሲው ኮናን ዶይልም ለአምስት ዓመታት ያለመሰልቸት የሼርሎክ ሆምዝን ታሪክ ጻፈ፡፡ በአምስተኛው ዓመት በታተመው አንድ ጽሑፍ ላይ ግን “ሼርሎክ ሆምዝ ሌሎች የልብ ወለድ ስራዎችን እንዳልጽፍ እያደረገኝ ነው” በማለት ገድሎት ሊገላገለው ወሰነ፡፡ The Final Problem የሚል ርዕስ የተሰጠው አጭር ልብ ወለድ ጻፈና ሼርሎክ ሆምዝን  በብዕሩ ገደለው፡፡ ደራሲው እንዲህ ሲያደርግ “ሼርሎክ ሆምዝ ሞቷል፤ ከእንግዲህ ታሪኩን አትጠብቁ” ማለቱ ነው፡፡

    ይሁንና ከላይ እንደገለጽኩት ህዝቡ በጄ አላለውም፡፡ “ሼርሎክ ሆምዝን ገድለህ አንተም በሰላም አትኖራትም!” በማለት ማስጠንቀቂያና ዛቻ ላከለት፡፡ ከዚህ ሌላም  ሃያ ሺህ የስትራንድ መጽሄት ቋሚ ደንበኞች (Subscribers) ደንበኝነታቸውን አቋረጡ፡፡ የእንግሊዝ ንጉሣዊያን ቤተሰብ ንዴቱንና ብስጭቱን ለደራሲው ገለጸለት፡፡ የስትራንድ መጽሔት አዘጋጅ ኮናን ዶይልን ክሊኒኩ ድረስ ሄዶ ለመነው፡፡ “መጽሔታችን በኪሳራ ሊዘጋ ነው፤ ያ እንዳይሆን እባክህ ሼርሎክ ሆምዝን ከሞት ቀስቅሰውና ታሪኩን ጻፍልን” አለው፡፡

   ኮናን ዶይል የመጽሔቱ አዘጋጅ ቢሮው ድረስ ሲመጣበት ይሉኝታ ያዘውና “እምቢ!” ማለት አቃተው፡፡ ስለዚህ በዘዴ ላባርረው በማለት “በወር ሃያ አምስት ፓውንድ የምትከፍሉኝ ከሆነ እጽፋለሁ” በማለት በዘመኑ ተሰምቶ የማይታወቅ ከፍተኛ ክፍያ ጠየቀ፡፡ የስትራንድ መጽሔት አዘጋጅ “አሳምሬ እከፍላለሁ! አንተ ብቻ ጻፍልኝ እንጂ” አለው፡፡ ኮናን ዶይል ከዚያ በፊትም ከህዝቡ የመጣበትን ዛቻ ፈርቶ ሼርሎክ ሆምዝን ሊቀሰቅሰው ወስኖ ስለነበረ የስትራንድ መጽሔት አዘጋጅ ክፍያውን ሲጨምርበት አዲስ ጉልበት አገኘ፡፡ በመሆኑም ሼርሎክ ሆምዝን ከሞት ሊያስነሳው ወሰነ፡፡ እናም "The Adventure of the Empty House" የሚል ርዕስ የሰጠውን ልብ ወለድ ጻፈና ዝነኛውን ገጸ-ባህሪ እንደገና ከሞት ቀሰቀሰው፡፡ አንባቢዎቹም ሼርሎክ ሆምዝ አለመሞቱን ሲረዱ በደስታ ፈነደቁ፡፡

      ታዲያ ኮናን ዶይል ሼርሎክ ሆምዝን የቀሰቀሰው እንዴት መሰላችሁ?….. ጓደኛው ዶ/ር ዋትሰን ቢሮው ውስጥ ሆኖ ሲተክዝ ቆፍጣናው ሼርሎክ ሆምዝ በድንገት ወደ ቢሮው ይገባል፡፡ ዋትሰን ዐይኑን ማመን አቃተው፡፡ ካለበት በደስታ ተነስቶ አቀፈው፡፡ ከናፍቆት ሰላምታ በኋላ ዋትሰን “ሞተሃል ተብሎ አልነበረም እንዴ?…” ይለዋል፡፡ ሼርሎክ ሆምዝም “ሆን ብዬ ያስወራሁት ወሬ ነው፡፡ በጋዜጣም ማስታወቂያ እንዲነገር ያደረግኩት እኔ ነኝ፡፡ አየህ! አንድ የምከታተለው አደገኛ ወንጀለኛ አለ፡፡ ያ ወንጀለኛ አልያዝ ብሎ አስቸግሮኛል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ዱካው ጠፍቶብኝ ነበር፡፡ ስለዚህ መሞቴን በጋዜጣ አሳወቅኩ፡፡ እንደዚያ ያደረግኩት ወንጀለኛው መሞቴን ሲረዳ ከተደበቀበት እንደሚወጣ ስለማውቅ ነው” በማለት ትረካውን ይጀምርለታል፡፡ ከዚያም ዝርዝሩን አንድ በአንድ ለዶክተር ዋትሰን ያጫውተዋል፡፡ ከዚያች አጭር ልብ ወለድ በኋላም ሼርሎክ ሆምዝ እንደ አዲስ መነበብ ይጀምራል፡፡
                                                      *****
    አርተር ኮናን ዶይል የሼርሎክ ሆምዝን ድንቅ ምርመራዎች የሚተርኩ 56 አጫጭር ታሪኮችንና አራት ሙሉ ልብ ወለዶችን ጽፏል፡፡ እርሱ ከሞተ በኋላ ደግሞ ሼርሎክ ሆምዝ በሺህ በሚቆጠሩ ፊልሞች፣ ቲያትሮችና ልዩ ልዩ የጽሑፍ ውጤቶች ውስጥ ለጥበብ ታዳሚዎች ቀርቧል፡፡ በዓለም ዙሪያ በርካታ የሼርሎክ ሆምዝ ቡድኖች አሉ፡፡ በለንደን ከተማ በየዓመቱ ሁለት ጊዜ የሼርሎክ ሆምዝ ፌስቲቫል ይካሄዳል፡፡ ከዚህም በላይ ደግሞ በሺህ የሚቆጠሩ ቱሪስቶች ሼርሎክ ሆምዝ ይኖርበታል ተብሎ የተጠቀሰውንና በቤከር ጎዳና የሚገኘውን የቤት ቁጥሩ 212B የሆነውን ህንጻ በየዓመቱ ይጎበኙታል፡፡ በህንጻው ውስጥ በሼርሎክ ሆምዝ አምሳል የተሰራ አዳፋ ኮፍያ የያዘ፣ ከዘራ ያነገተና ፒፓውን በአፉ የጎረሰ አርቲፊሻል ሰው ቆሞበታል፡፡
 
  ይህ ሁሉ ክብርና ፍቅር የሚሰጠው በምናብ ለተፈጠረ ገጸ-ባህሪ ነው፡፡ ክላሲክ የሚባሉት ጸሐፍት እንደ ሼርሎክ ሆምዝ ያሉትን ከሰው ልብ የማይጠፉ ልዩ ገጸ-ባህሪያትን የመፍጠር ብቃት ነበራቸው፡፡ ዣንቫልዣ፣ ዶን ኪኾቴ፣ አንክል ቶም፣ ራስኩልኒኮቭ፣ ሐምሌት፣ ኦቴሎ፣ ወዘተ የመሳሰሉ ገጸ-ባህሪያትን የሚያውቁ የስነ-ጽሑፍ አፍቃሪዎች ሼርሎክ ሆምዝንም ዘወትር ያስታውሱታል፡፡ እኛም ዘወትር እናስታውሰለዋን፡፡
ሰላም!
  ----
መጋቢት 26/2006
አፈንዲ ሙተቂ

No comments:

Post a Comment