Saturday, December 20, 2014

ሁለቱ የጎንደር ነገሥታት



ፀሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ
-----

በጎንደር የነገሡት የኢትዮጵያ ነገሥታት በታሪካዊ ሚናቸው በእኩል ሚዛን ላይ አይቀመጡም፡፡ አንዳንዶቹ በሰሩት ስራ ስማቸው ዘመንን ተሻግሮ ይዘከራል፡፡ አንዳንዶቹ ግን ስልጣን አልባ ሆነው በስም ብቻ “ንጉሥ” እየተባሉ ይጠሩ ነበር፡፡ የሁላቸውንም ታሪክ መዘርዘር የኛ ዓላማ ባለመሆኑ እርሱን ለታሪክ መጻሕፍት እንተወው፡፡ ለበረካ ያህል ግን ሁለት ነገሥታትን በትንሹ እናውሳቸው፡፡

===ተረት መሳዩ ንጉሥ===
ከስሙ ጀምሮ ሁለመናው ይገርማል፡፡ ታሪኩ እንደ ተረት ያስደምማል፡፡ አንዳንዴ የሚሰራቸው ነገሮች ደግሞ ከባግዳዱ ኸሊፋ ሀሩን አል-ረሺድ ጋር ያመሳስሉታል፡፡

ይህ ንጉሥ “ባካፋ” ይባላል፡፡ አጼ ባካፋ የነገሠው በአድማ ነው፡፡ አጼ ዳዊት ሳልሳዊ በሚባለው ወንድሙ ላይ አምጾ ነው ስልጣንን የተቆጣጠረው፡፡ ታዲያ ለአመጽ ሲነሳ መጀመሪያ ላይ በለስ አልቀናውም፡፡ በውጊያ ስለተሸነፈ ራሱን ሸሽጎ ከአንድ ደብር ለመኖር ተገደደ፡፡ በዚያ ደብር እያለም በአንድ መምህር ስር ቅኔና ዜማ መማር ጀመረ፡፡ እያደር ከዚሁ መምህር ጋር ሚስጢረኛ ሆነ፡፡ ታሪኩንም አንድ በአንድ አጫወተው፡፡

  በአንድ ውድቅት ሌሊት እርሱና መምህሩ ለመጸዳዳት ይወጣሉ፡፡ እዚያ እያሉም ባካፋ ለመምህሩ “መሪጌታ! የኔን ነገር እንዴት ነው የሚያዩት?.. ይህንን ወንድሜን አሸንፌ መንገሥ የምችል ይመስልዎታል?” የሚል ጥያቄ አቀረበ፡፡ መምህሩም “የምትነግሥ ይመስለኛል፤ ነገር ግን ጸሎት ማብዛት አለብህ፣ በጸሎት ሀይል የማይቻል የለም፤ ታዲያ ቀኙ ያንተ ሆኖ አልጋውን በወሰድክ ጊዜ እኔን እንዳትረሳኝ” አለው፡፡ ባካፋም በፍጹም ላይረሳው ቃል ገባለት፡፡

   ዓመታት አለፉ፡፡ ባካፋም ወንድሙን ድል አድርጎ ነገሠ፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ድሪቶ የለበሰ ባላገር መጥቶ ከቤተ መንግሥቱ ፊት ቆመ፡፡ ዘበኞቹንም እንዲህ የሚል መልዕክት ለባካፋ እንዲያደርሱለት ለመናቸው፡፡

“ታስታውሳለህ ባካፋ የተባባልነውን
እኔ የአብረሃምን አባት ሆኜ አንተ ሚስቱን”

   ዘበኞቹ የባላገሩን ንግግር እንደ እብድ ወሬ ቆጠሩትና ለባካፋ ላለመንገር ለገሙ፡፡ አንዱ “ነቄ” ዘበኛ ግን ሰውዬው ቅኔ የተናገረ ስለመሰለው “ንጉሡ መልዕክቱን መስማት አለባቸው” በማለት ወደ አጼ ባካፋ ሄዶ ተናገረ፡፡ ባካፋም “እንዴ?! የቅኔ መምህሬ ናቸው፤ በቶሎ አስገቡልኝ” በማለት ዘበኞቹን አዘዛቸው፡፡ በዚህ መንገድ ባካፋ ከጥንቱ መሪ ጌታ ጋር ተገናኘ፡፡ ያኔ የገባውንም ቃል ተግባራዊ አደረገ፡፡

  በነገራችን የቅኔውን ሚስጢር አግኝታችሁታል አይደለም?… የአብረሃም አባት “ታራ” ነው፡፡ የአብረሃም ሚስት ደግሞ “ሳራ” ናት፡፡ ስለዚህ መምህሩ ለማስተላለፍ የፈለገው መልዕክት “እኔ ሳራ አንተ ታራ” የሚል ነው፡፡ ይህም ሁለቱ ሰዎች ሲጸዳዱ ያደረጉትን ውይይት የሚያስታውስ ነው፡፡
*****
    በሌላ ጊዜ ደግሞ ባካፋ እንደ ባግዳዱ ኸሊፋ “ሃሩን አል-ረሺድ” ማንነቱን ቀይሮ ሀገሩን ይጎበኝ ነበር፡፡ ከአንድ ምንጭ አጠገብ ሲደርስ አንድ እረኛ ገጠመውና “የዚህ ሀገር ንጉሥ እንዴት ነው?” አለው፡፡ እረኛውም “ጥሩ ነው፤ ተስማምቶናል፤ ሀገሩ ጥጋብ ነው፤ ደሀን አይበድልም” የሚል መልስ ሰጠው፡፡ ይሁንና ባካፋ ሆን ብሎ እረኛውን መተንኮስ ጀመረ፡፡ “ምን ጥጋብ ነው ትላለህ? እንዲህ ዓይነት ግፈኛ ንጉሥ ነግሦም አያውቅ፤ ደሀውንም እንደርሱ የሚበድል የለም” አለው፡፡ እረኛው “ሰውዬ! እኔ አልዋሸሁም፤ ይህንን ነገረኛነትን ተወኝ፤ ምላስህን ያዝልኝ” አለው፡፡ ባካፋ ግን ትንኮሳውን ቀጠለ፡፡ በዚህ ጊዜ እረኛው ሽመሉን መዝዞ “እምቢ ካልከኝ በዚህ ዝም ትላለህ” በማለት ባካፋን እስኪበቃው ድረስ ደበደበው፡፡

     ከሳምንት በኋላ እረኛው ወደ ቤተመንግሥት ተጠራ፡፡ “ለምን” ብሎ ቢጠይቅ መልስ አልተሰጠውም፡፡ በመሆኑም ፍርሃት ወረረው፡፡ “ምን አጥፍቼ ይሆን?” እያለ ተጨነቀ፡፡ እንዲሁ በጭንቀት እንደተወጠረ ቤተመንግሥት ሲደርስ ከሳምንት በፊት የደበደበው ሰውዬ በዙፋን ላይ ቁጭ ብሎ አገኘው፡፡ እረኛው የባሰውኑ ተርበተበተ፡፡ ይሁንና ንጉሡ የፈገግታ ምልክት ሲሰጠው ልቡ መለስ አለችለት፡፡ ንጉሡም እንዲህ አለው፡፡
  “ከሳምንት በፊት ላሳየሁ ሐቀኝነት አንድ መቶ ከብቶችን ተሸልመሃል”

===የቤተመንግሥቱ ጭውውትና ታሪክ ቀያሪው ፋኖ====

አሁን ደግሞ በጎንደር ቤተ-መንግሥት የተደረገ አንድ ጭውውት እንጥቀስላችሁ፡፡

1ኛ ተናጋሪ (እቴጌ መነን)
አረ ለመሆኑ ምን ይሆን አሳቡ
ሸፍቶ የሄደው ከነቤተሰቡ?
*****
2ኛ  ተናጋሪ (ራስ ዓሊ)
ሰውዬው ኩሩ ነው የተነፋ ልቡ
ይዞ ማዋረድ ነው ይበርዳል ጥጋቡ::
*****
3ኛ ተናጋሪ (አንድ መነኩሴ)
ሰውዬው ብርቱ ነው ስሙ የተጠራ
ጎበዝ እኔ ነኝ ባይ ሀይልን የማይፈራ
በዘዴ በትዕግስት ማባበል ይሻላል
በሀይል ብንለው በጣም ያውከናል፡፡
*****
4ኛ (እቴጌ መነን)
እንዲህ ስትሉ ነው ስሙ የገነነው
የፈራነው መስሎት አገር የሚያብጠው
ዘዴ መላ አታብዙ ጦር ይታዘዝና
ቢቻል ከነነፍሱ ይምጣ ይያዝና
እምቢ ካለም ይሙት በገዛ ጥፋቱ
ላንድ ወንበዴ ሽፍታ አይስጋ መንግሥቱ፡፡
*****
  ይህ ጭውውት በ1840ዎቹ በጎንደር ቤተመንግሥት እልፍኝ ከተደረገ ምክክር የተቀነጨበ ነው፡፡ ይህም “ቴዎድሮስ” በተሰኘው የደጃች ግርማቸው ተክለሃዋሪያት መጽሐፍ የመጀመሪያ ገጽ ላይ የሚገኝ ነው፡፡ በጭውውቱ ውስጥ “ለምን ሸፈተ” ተብሎ እንደ አጀንዳ የቀረበው የያኔው ደጃች ካሳ ሀይሉ ጉዳይ ነው፡፡ በዚያን ወቅት ካሳ ሀይሉ ከተራ ቤተሰብ ተወልዶ በአስገራሚ ሁኔታ የቤተ መንግሥቱ አባል ሆኖ ነበር፡፡ ታሪክ አለው፡፡
  
ደጃች ካሳ በወጣትነቱ ሽፍታ ሆኖ በቋራና በደምቢያ ይዘዋወር ነበር፡፡ በዚያን ጊዜ ኢትዮጵያዊያን ሱዳንን ከሚቆጣጠሩት የቱርክ/ግብጽ ገዥዎች ጋር የድንበር ላይ ውጊያ ያካሄዱ ነበር፡፡ ታዲያ በአንዱ ውጊያ ላይ የዘመኑ ዋና መስፍን የነበሩት የራስ ዓሊ ልጅ የሆነችው ወይዘሪት ተዋበች ተማረከች፡፡ ይህም ወሬ ለካሳ ጆሮ ደረሰ፡፡ ካሳ በወቅቱ ሽፍታ ቢሆንም የኢትዮጵያዊያን መሸነፍና በምርኮ መጋዝ በጣም አበሳጨው፡፡ በመሆኑም በቱርኮች ላይ ድንገተኛ አደጋ ጥሎ አተረማመሳቸው፡፡

  ካሳ ይህንን ሲያደርግ ተዋበች ምርኮኛ መሆኗ በቁጭት ውስጥ ጥሎአት በመርዝ ጩቤ ሰውነቷን ወግታ ራሷን ለማጥፋት ሙከራ በማድረግ ላይ ነበረች፡፡ ይሁንና ካሳ በቦታው ደርሶ መርዙ ወደ ሰውነቷ ጠልቆ ሳይገባ ከደሟ ውስጥ መጥጦ ተፋው፡፡ በዚህም የተዋበች ህይወት ተረፈች፡፡ ካሳም ተዋበችን በጀርባው አዝሎ ከውጊያው ስፍራ እየሮጠ ወጣ፡፡ ወታደሮቹም በቶሎ እንዲያፈገፍጉ ትዕዛዝ ሰጣቸው፡፡

   ካሳ ነፍሲያዋን ያተረፈላትን ተዋበችን ለአባቷ ለራስ ዓሊ አስረከባት፡፡ ራስ ዓሊም በጀግንነቱ ተደስተው እሷኑ ዳሩለት፡፡ ሽፍትነቱን ትቶ በቤተመንግሥት እንዲኖርም አደረጉት፡፡ ይሁንና የቤተመንግሥቱ ህይወት በነጻነት መኖርን ለለመደው ካሳ የግዞት ያህል ሆነበት፡፡ በዚያ ላይ መኳንንቱ “የኮሶ ሻጭ ልጅ” እያሉ የሚያሳዩት ንቀት በጣም አቃጠለው፡፡ ተዋበችም በባሏ ላይ በሚደርሰው ንቀትና ማሽሟጠጥ በገነች፡፡ እናም በአንድ ውድቅት ላይ “አንተ ካሳ! ጎራዴህን ታጠቅና ተነሳ፤ ምንጊዜም ከጎንህ ነኝ” አለችው፡፡ ካሳም ሸፈተ፡፡
*****
  እንግዲህ ከላይ የቀረበው ጭውውት ካሳ በሸፈተ በማግስቱ የተደረገ ነው፡፡ በዚያ ቀን በተደረገው ምክክር ደጃች ወንድይራድ የካሳን እጅ ይዞ እንዲመጣ ታዘዘ፡፡ ወንድይራድም ከቤተመንግሥቱ ቀርቦ እየጎረነነ ትዕዛዝ መቀበሉን አረጋገጠላቸው፡፡ ይሁንና ከልክ ያለፈው የወንድይራድ ጉራ ያልጣማቸው ራስ ዓሊ “አንተ ወንድይራድ! ካሳ እንደ ሌላው ሽፍታ አይምሰልህ፤ ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚያስፈልገው አደገኛ ተዋጊ ነው” በማለት ምክር ቢጤ ቢወርውሩለት ዳጃች ወንድይራድ እንዲህ የሚል የንቀት መልስ ሰጣቸው፡፡
አይስሙ ጌታዬ ሰው የሚለውን
አያስፈራም ካሳ ይንዛ ጉራውን፡፡
ገና መጣ ሲሉት አገር ጥሎ ይሸሻል
ወይንም ካንዱ ደብር ገብቶ ይደውላል፡፡
እንኳን አንድ ሽፍታ ቀማኛ ወንበዴ
ብዙ እመልሳለሁ በጦር በጎራዴ፡፡
እኔ ነኝ ወንድይራድ ታማኝ አሽከርሽ
ያን የኮሶ ሻጭ ልጅ የምቀጣልሽ፡፡

    የወንድይራድ ፉከራና ድንፋታ ከካሳ ጆሮ ገባ፡፡ ካሳም “እናቴን እንዲህ የሰደበውን ባለጌ ባላሳየው እኔ ካሳ አይደለሁም” በማለት መሃላውን አስቀመጠ፡፡ ሁለቱ ሀይሎች ተገናኙ፡፡ ውጊያው ገና ከመጀመሩ የወንድይራድ ፉከራ የአሸዋ ላይ ቤት ሆኖ ፈረሰ፡፡ እቴጌ መነን (የራስ ዓሊ እናት) የተመኩበት ዳጃች ወንድይራድም ተማረከ፡፡ ካሳም መሃላውን ተግባራዊ አደረገ፡፡ ወንድይራድን ቀንና ማታ ኮሶ እያጠጣው ገደለው፡፡

   ከዚያ በኋላ ካሳ በሀገሩ ላይ ገነነ፡፡ ማን ይቻለው እንግዲህ? ደጃች ውቤም ሆኑ ራስ ዓሊ፣ ደጃች ተድላ ጓሉም ሆኑ ደጃች ጎሹ ሁሉም ተራ በተራ ተሸነፉ፡፡ ካሳን ያሸንፋሉ ተብለው የተጠበቁት እቴጌ መነንም በናቁት አማቻቸው እጅ ምርኮኛ ሆነው ወደቁ፡፡ የጥንቱ የቋራ ሽፍታም “ዳግማዊ ቴዎድሮስ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ” ተብሎ ነገሠ፡፡ ንጉሥ ለስሙ ብቻ ቤተመንግሥት የሚቀመጥበት ዘመነ መሳፍንትም አበቃ፡፡ ኢትዮጵያም አዲስ ታሪካዊ ጉዞዋን ተያያዘችው፡፡
-----
አፈንዲ ሙተቂ
ግንቦት 23/2007
አዳማ
------
(ማስታወሻ፡ ይህ ጽሑፍ ከቀጣዩ መጽሐፌ የተቀነጨበ ነው፡፡ ጽሑፉን በኢንተርኔት ማውጣት ቢቻልም በየትኛውም የህትመት ሚዲያ ማተም ክልክል ነው)

Afendi Muteki is a researcher and author of the ethnography and history with special focus on the peoples of East Ethiopia. You may follow him on his blog and his facebook page by clicking the following links



No comments:

Post a Comment