Sunday, November 30, 2014

በልጅ እያሱ አሟሟት ዙሪያ


ፀሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ
------
የልጅ እያሱ ሞት ይፋ የወጣው በህዳር ወር 1928 ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሤ ወደ ማይጨው ከመዝመታቸው ሶስት ቀን አስቀድሞ ነው። በአሟሟታቸው ዙሪያ ከሚነገሩት መካከል

·        ልጅ እያሱ የተገደሉት ሀረር ውስጥ ነው::
·        ልጅ እያሱ የተገደሉት አዲስ አበባ ገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት ውስጥ ሲሆን የተቀበሩትም ከቤተ መንግሥቱ ቅጥር ግቢ ውስጥ ከሚገኘው ቅዱስ ማርቆስ ቤተ ክርስቲያን ክልል ነው::
·        ልጅ እያሱ የቀብራቸው ስነ-ስርዓት የተከናወነው ደብረ ሊባኖስ ነው::
·        ልጅ እያሱ የተቀበሩት ሰንዳፋ ውስጥ ነው የሚሉት ይገኙባቸዋል።

የልጅ እያሱን አሟሟት አውቃለሁ በማለት እማኝነታቸውን ከሰጡ ግለሰቦች መካከል አገልጋያቸው የነበሩ አዛውንት ኢጣሊያኖች አቤቶ እያሱን ከጋራሙለታ እስር ቤት ለማስወጣት ሙከራ አድርገው እንደነበር በመግለጽ እንዲህ ይላሉ።
 
 “የኢጣሊያ ወኪሎች አባጤናን ከግራዋ እስር ቤት ለማስወጣት ከሞከሩ ጀምሮ ልዑልነታቸው በእስር ቤቱ ክልል እየተከዙ ወዲያ ወዲህ ይንጎራደዱ ነበር። አንድ ቀን ምሽት አንዲት አውቶሞቢል ወደ እስር ቤቱ መጣች። እርሳቸውም ይፈሩት የነበረው ሰው መኖር አለመኖሩን ጠየቁ። በቀጣዩ ቀን “የመጡት አባ ሐና ብቻ ናቸው” አልኳቸው። ነገር ግን ጥቂት ዘግይቶ ሁለተኛዋ አውቶሞቢል ሁለት ሰዎችን አሳፍራ መጣች። ከሁለቱ አንዱ ፊታውራሪ ነበር። እስኪጨልም ቆይተው እያደቡ ወደ እስር ቤቱ ተጠጉ። መዝጊያው ሰፋፊ ስንጥቆች ያሉት በመሆኑ ልዑልነታቸው በስንጥቆቹ ውስጥ አዘውትረው ምራቃቸውን ጢቅ ይሉ ስለነበር ሲያነጣጥሩባቸው ሳያዩአቸው አልቀረም። በተኮሱባቸው ጊዜ የመስኮቱን መቃኖች ጨምድደው ጨበጡ። ኃይለኛ ስለነበሩ ቤቱን በሙሉ ያናጉትና የሚናድ መስሎኝ ፈርቼ ነበር። ተንገዳግደው ወለሉ ላይ ሲወድቁ ሰማሁ። ሬሳቸው በባቡር ተጭኖ ወደ አዲስ አበባ ከመወሰዱ በፊት ሁለቱ ነፍስ ገዳዮች እንደ ባላዛር ሬሳቸው ላይ ተጎንብሰው አጓሩ። ሬሳቸው አዲስ አበባ እንደደረሰ ከፍተኛ ባለስልጣን ለባላምባራስ አበበ አረጋይ አስረከቡ። እንግዲህ ሬሳቸው ለዘላለም ያረፈበትን ቦታ የሚያውቁት ባላምባራስ አበበ አረጋይ ብቻ ናቸው። ይሁንና እኒሁ ሰው ደግሞ በ1953 በተሞከረው የመንግሥት ግልበጣ ጊዜ የመከላከያ ሚኒስትር ሆነው ነበርና በአረንጓዴው የገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት ታዛ ወለል ላይ ደማቸው ፈስሶ ሞቱ። አባ ሃና ጂማም ተመሳሳይ እጣ ገጠማቸው”።

    እንደ አዛውንቱ ምስክርነት ከሆነ አባ ሐና ጅማም ሆነ አበበ አረጋይ የልጅ እያሱን አስከሬን በተረካከቡበት ቦታ ላይ ስለተገደሉ ምስጢሩ አብሮ ሞቷል ማለት ነው።
ሌላኛዋ ለቤተ መንግሥቱ ቅርበት ያላቸው ሴት ደግሞ ለጎበዜ ጣፈጠ እንዲህ ብለው ነበር የተናገሩት (“አባ ጤና እያሱ” ከተሰኘው የጎበዜ ጣፈጠ ድርሰት የተወሰደ ነው)።

    “ዕለቱን አላስታውስም። ቢሆንም ልጅ እያሱ አርፈዋልና ቤተ መንግሥት እንድትመጡ የሚል መልዕክት ተላለፈ። እኛም ማልደን ወደ ቤተ መንግሥቱ ሄድን። አዲስ አበባ ውስጥ የምንገኝ ወይዛዝርትና መኳንንት ተሰብስበን ስንላቀስ ዋልን። ሬሳ ግን አልነበረም። እቴጌ መነን በጣም አዝነውና ተክዘው እንባቸውን ያፈሱ ነበር።  ጃንሆይ በርኖሳቸውን ገልብጠው ደርበው ወንድሜ ወንድሜ በማለት ያለቅሱ ነበር።”

ልጅ እያሱን በታሸገ ባቡር አሳፍሬ ወደ አዲስ አበባ ልኬአቸኋለሁ በማለት እማኝነታቸውን የሚሰጡት ብላቴን ጌታ ዶ/ር ሎሬንዞ ታዕዛዝ በበኩላቸው የቅዱስ ማርቆስ ቤተክርስቲያን ቄስ የነበሩ ገ/መድህን የተባሉ ግለሰብ እንዲህ በማለት ነግረውኛል ይላሉ።

“በቅዱስ ማርቆስ ቤተክርስቲያን ትይዩ የዱክ ቤት ይባል በነበረው ህንጻ ሰገነት ላይ አንድ እጆቹን በሰንሰለት የታበተ ሰው ከቀትር በኋላ ዘወትር ሲመላለስ እናየው ነበር። ነገር ግን ጃንሆይ ወደ ጦርነቱ ከመዝመታቸው በፊት ሌሊቱን ጸሎተ ፍትሐት እንድናደርግ ታዘዝን። ሆኖም የሟቹን ሰው የክርስትና ስም የሚነግረን አልነበረም። ከዚያ በኋላ ያ ሰውዬ ይመላለስበት ከነበረው ሰገነት ላይ አልታየም። እኛም የሞቱት ልጅ እያሱ እንደሆኑ ተረዳን።

(ምንጭ፡- ጎህ መጽሄት፣ ቅጽ 1 ቁጥር 5፣ ጥቅምት 1993፣ ገጽ 6/22)
-----------------
ለዚሁ መጽሄት ቃለ-ምልልስ የሰጡት የልጅ እያሱ የልጅ ልጅ ፕሮፌሰር ግርማ ዮሐንስ እያሱ ቄስ ገ/መድሕን የተባሉት ሰው ከሰጡት ምስክርነት ጋር የሚጣጣም ቃል አሰምተዋል። ፕሮፌሰር ግርማ እንዳሉት ልጅ እያሱ በስድስት ኪሎ ዩኒቨርሲቲ ቅጥር ግቢ ባለው የዱክ ቤት (አሁን Law Faculty ዋና ህንጻ የሆነው) መታሰራቸው እውነት ነው። “አጼ ኃይለ ስላሴ ወደ ማይጨው ሀሙስ ከመዝመታቸው በፊት ማክሰኞ ሌሊት ልጅ እያሱ ተገድለው አሁን የዩኒቨርሲቲው የእግር ኳስ ሜዳ ከሆነውና ያኔ የቅዱስ ማርቆስ ቤተክርስቲያን አጸድ ከነበረው ስፍራ ተቀብረዋል” ይላሉ ፕሮፌሰር ግርማ።
---------------
አፈንዲ ሙተቂ
ሰኔ 22/2005
ሀረር- ምስራቅ ኢትዮጵያ

No comments:

Post a Comment