Saturday, January 13, 2018

የገለምሶው ሸሪፍ ሙሐመድ ሐቢብን በጨረፍታ

                                     
ጸሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ
---
በከተማችን ነዋሪዎችና በሌሎች አካባቢዎችም ዘንድ በጣም የሚከበሩት ሸሪፍ ሙሐመድ ሐቢብ በትናንትናው እለት አርፈዋል፡፡ ሸሪፍ ሙሐመድ ሐቢብ ዕድሜአቸው ወደ መቶ ዓመት ሆኖአቸው ነበር፡፡ አላህ ዕድሜ ሰጥቶአቸው ብዙ ማየት ቢችሉም የሄዱት ተመልሰው ወደማይመጡበት ዓለም ነውና እርሳቸውን በማጣታችን መሪር ሐዘን ተሰምቶናል፡፡

ሸሪፍ ሙሐመድ ሐቢብ በአንድ ዘመን በገለምሶና በመላው የምዕራብ ሀረርጌ ዞን ፈክተው ይታዩ ከነበሩት እነ ሼኽ ሙሐመድ ጡልላብ (ጪሮ)፣ ሼኽ ሙሐመድ ረሺድ ሼኽ ቢላል (ጭረቲ)፣ ሐጂ ዑመር አርቦዬ (ደረኩ)፣ ሼኽ ኒብራስ ሙሐመድ (አሰቦት)፣ ሼኽ አሕመድ ሼኽ አቡበከር (ቡሶይቱ)፣ ሙፍቲ ሓጂ ዑስማን (ገርቢ ጎባ)፣ ሼኽ ሐሰን አነኖ፣ ሼኽ ሻቶ ሚኦ (ጉባ ቆርቻ)፣ ሼኽ ሙሐመድ ጀልዲ (ሂርና) የመሳሰሉትን ታላላቅ ዑለማ ያፈራው ወርቃማው ትውልድ አባል ነበሩ፡፡ ከነዚያ ዑለማ መካከል እስከ ለታሪክ ተርፈው ረጅም ዓመት መኖር የቻሉት እርሳቸውና የገለምሶው ሼኽ ሙሐመድ ሲራጅ ብቻ ናቸው፡፡ እርሳቸው አሁን አርፈዋል፡፡ ሼኽ ሙሐመድ ሲራጅ ብቻ ቀርተዋል (ዕድሜአቸውን ያርዝመውና)፡፡
*****
ሸሪፍ ሙሐመድ ሐቢብ የተጸውኦ ስማቸው “ሙሐመድ ሐቢብ” ነው፡፡ ሸሪፍ” ደግሞ የማዕረግ ስማቸው ነው፡፡ እኝህ ዓሊም እንደ ሌሎች ዑለማ ሼኽ ተብለው ያልተጠሩት በትውልዳቸው ሸሪፍ በመሆናቸው ነው (ሸሪፍ የዘር ሐረጋቸው ከነቢዩ ሙሐመድ (..) ቤተሰብ ለሚዘዝ ሰዎች የሚሰጥ ማዕረግ ነው፤ አንዳንድ ጊዜም “ሰይድ” ይባላሉ፤ ከነቢዩ ቤተሰብ የተወለዱ መሆናቸው የሚነገርላቸው ጎልማሶችና ዑለማ በአብዛኛው “ሸሪፍ” እየተባሉ ነው የሚጠሩት)፡፡

ሸሪፍ ሙሐመድ ሐቢብ የተወለዱት በቀድሞው የጨርጨር አውራጃ (በአሁኑ ምዕራብ ሀረርጌ ዞን) በዶባ ወረዳ፣ ቢዮ ኸራባ በሚባለው መንደር ነው፡፡ ይሁን እንጂ የዕድሜአቸውን ግማሽ ያህል የኖሩት ሎዴ በተሰኘውና በገለምሶ ከተማ ዳርቻ ላይ ባለው መንደር ነው (መንደሩ ከከተማው ሶስት ኪሎሜትር ያህል ወጣ ብሎ ይገኛል)፡፡ ሸሪፍ ሙሐመድ በዚህ የሎዴ መንደር የከተሙት 1960ዎቹ መጀመሪያ ላይ ነው፡፡
------
ሸሪፍ ሙሐመድ ሐቢብ በመምህርነት፣ በአባትነት እና በሀገር ሽማግሌነት ህዝቡን ለረጅም ዓመታት አገልግለዋል፡፡ ታዲያ እኝህ ዓሊም ከሌሎች የገለምሶ ዑለማ በበለጠ ሁኔታ የሚታወሱበትና ስማቸውን የተከሉበት አንድ ቁምነገር አለ፡፡ ይኸውም ዘጠና ዘጠኙን የአላህ ስሞች (አስማኡላሂል ሑስና) እየጠሩ ዚክር ማድረግን ለአካባቢያችን ህዝብ በስፋት ያስተዋወቁ መሆናቸው ነው፡፡

የሸሪፍ ሙሐመድ ሐቢብ ደረሳ ሆኖ አስማኡል ሑስና ያልሓፈዘ (በቃሉ ያልያዘ) የለም ለማለት ይቻላል፡፡ “ሐርፍ” መቁጠር (ፊደል ማጥናት) ከጀመረው ህፃን አንስቶ ኪታብ እስከሚቀራው ደረሳ ያለው የሸሪፍ ሙሐመድ ተማሪ “እስቲ የአላህ ስሞችን ቁጠርልኝ” ብትሉት አንድ በአንድ ይነግራችኋል፡፡ እሳቸው ከኖሩበት መንደር ነዋሪዎች መካከልም ብዙዎች አስማኡል ሑስናን በቃላቸው ይዘዋል፡፡

 ታዲያ ይህ የሸሪፍ ሙሐመድ አስማኡል ሑስና አብዮት በሒፍዝ ብቻ የተገደበ አይደለም፡፡ ደረሳዎቻቸው በልዩ ልዩ ወቅቶች የሚያዜሟቸው ዚክሪዎችም አስማኡል ሑስና መሰረት ያደረጉ ናቸው፡፡ እነዚህ ዚክሮች በድቤ ታጅበው በዜማ የሚዘከሩ በመሆናቸው “መንዙማ” ይባሉ ይሆናል፡፡ በአካባቢያችን ልማድ መሠረት ግን “አስማኣ” ወይንም “አስማኡል ሑስና” ነው የሚባሉት፡፡

በኛ ዘንድ መንዙማ የሚባለው በግጥም እየተቀኘ የሚጻፈው ውዳሴ ነው፡፡ የሸሪፍ ሙሐመድ ሐቢብ “ዚክሪ” ግን ከአላህ ስሞች በስተቀር ሌላ ግጥም የለውም፡፡ ሸሪፍ ሙሐመድ የሚገጥሙት አዝማቹን ብቻ ነው፡፡ ተከታዮቹ ግጥሞች ደግሞ ዘጠና ዘጠኙ የአላህ ስሞች ናቸው፡፡ እስቲ ለወግ ያህል ሸሪፍ ሙሐመድ ሐቢብ ዜማና አዝማች እያወጡላቸው ያቀናበሩዋቸውን አንዳንድ የአስማኣ ዚክሪዎችን ላካፍላችሁ፡፡
------
አንዱ የሸሪፍ ሙሐመድ ሐቢብ ዚክሪ የሚከተለው አዝማች አለው(ተቀራራቢ ትርጉሙ በቅንፍ ውስጥ የተጻፈው ነው)፡፡

አላህ ቀሲሙን ዳኢሙ (አንተ የምትረዝቀው ሁሌም የምትኖረው አላህ ሆይ)
አላህ ቀሲሙን ዳኢሙ (አንተ የምትረዝቀው ሁሌም የምትኖረው አላህ ሆይ)
ሱብሓነከ ቃኢሙ (ከጉድለት ሁሉ የጠራኽ ነህ አንተ ዘወትር ያለኸው)

ጀመዓው ድቤ እየመታና በአንድ ሼኽ እየተመራ ይህንን ዚክሪ እየደጋገመ ያዜማል፡፡ በዚህ በኩል የሸሪፍ ሙሐመድ ሐቢብ ዚክሪዎች በሌሎች አካባቢዎች ከምታውቋቸው መንዙማዎች ልዩነት የላቸውም፡፡ ሼኹ ዚክሪውን ሲመራው ግን የአላህ ስሞችን እንደሚከተለው ይጠራቸዋል፡፡

ራሕማን ረሒም አላህ (ጀመዓው አላህ ቀሲሙን ዳኢሙ እያለ ይቀበላል)
ደያኑን ቡርሓን አላህ (አሁንም ጀመዓው አላህ ቀሲሙን ዳኢሙ ይላል)
አወሉን አኺር አላህ 
ወሊዩን ከቢር አላህ
 (ሼኹ የመጨረሻዎቹን ሁለት ግጥሞች በአንድ ላይ ስለሚላቸው ጀመዓው በጸጥታ ያሳልፋል)፡፡

ሼኹ ይህንን ተናግሮ ፋታ ሲወስድ ጀመዓው እንደገና አላህ ቀሲሙን ዳኢሙ ይዘምራል፡፡ ከዚያም ሼኹ ሌሎች የአላህ ስሞችን ይጠራል፡፡ ጀመዓው እንደገና አላህ ቀሲሙን ዳኢሙ ያዜማል፡፡ እንደገና ሼኹ ሌሎች የአላህ ስሞችን ይጠራል፡፡ እንዲህ እንዲህ እየተባለ ሼኹ ሁሉንም የአላህ ስሞች ጠርቶ እስኪያበቃ ድረስ ዚክሪው ይሄዳል፡፡

ታዲያ ሼኹ ሁሉንም የአላህ ስሞች ጠርቶ ገቢሩን የሚዘጋው በነቢዩ ሙሐመድ ላይ ሰለዋት በማውረድ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ለሁሉም ዚክሪዎች የሚያገለግለው አንድ ባለ አራት መስመር ግጥም ነው፡፡ ግጥሙ እንዲህ ይሄዳል፡፡

መዐ-ስ-ሰላሚላህ መዐ-ስ-ሰላሚላህ (ከአላህ ሰላም ጋር፣ ከአላህ ሰላም ጋር)
ዐላ ሙሐመዲን ወ ኸይሩ ኸልቂላህ (የፍጡራን ሁሉ በላጭ በሆነው ሙሐመድ ላይ በሚወርደው)
ወል አህሊ ወሳህቢ ወማ ፊ ዲኒላህ (በቤተዘመዶቹ፣ በባልደረቦቹና በአላህ ዲን ውስጥ ባለው ሰው ሁሉ)
ዐላ ሙሐመዲን ወኩሊ ጁንዲላህ (በሙሐመድ እና በአላህ ሰራዊትም ላይ)

*****
ሸሪፍ ሙሐመድ “አስማኣዎቹ”ን በየጊዜው ነው የሚያወጡት፡፡ እነርሱን በቃል መያዝ ደግሞ በጣም ቀላል ነው፡፡ በሸሪፍ ሙሐመድ ሐቢብ ከተደረሱት ዝነኛ የአስማኣ ዚክሮች መካከል የሚከተሉትን ማስታወስ ይቻላል፡፡

1.  ሐስቡነላህ ወኒዕመል ወኪሉ
ሐስቡነላህ ወኒዕመል ወኪሉ
ኒዕመል መውላ ወኒዕመ-ንነሲሩ

2.  ቢስሚላሂ ራሕማኒ-ረሒም
አልሐምዱሊላህ ወሱብሓነላህ
ረብቢ ሰልሊ ዐላ ሙሐመድ

3.  አላሁ አላህ አላሁ አላህ
ሱብሓነከ ያ ሳቲረል ዑዩብ
ጋፊረ ዙኑብ

4.  አላሁ አላሁ ሚንከል መደዱ
አላሁ አላሁ ሚንከል መደዱ
ጀማል ከውኒ አንተል አሐዱ

5.  አላሁ አላህ ያ አላህ
ራሕማን ያ ረሒም
ኢርሐምና ወል-ሙስሊሚና
በርሩ ያ ከሪም

*****
ሸሪፍ ሙሐመድ ሐቢብ በአንድ ወቅት የደረሱት “አስማኣ” በህብረተሰቡ ዘንድ መነጋገሪያ ሆኖ ነበር፡፡ አስማኣ የሚከተለው አዝማች ነበረው፡፡ 

አላሁ አላህ አላህ ዘልፈረጂ
በሺር ረብበና ቢል ቢል-ኢማን ኩለል ፈረንጂ
የአማርኛ ትርጉሙ እንደሚከተለው ሊሆን ይችላል፡፡

አንተ የፈረጃ ባለቤት የሆንከው አላህ ሆይ
ፈረንጆችን ሁሉ በኢማን አብስራቸው (ኢማን ሙላባቸው)፡፡

ሸሪፍ ሙሐመድ ይህንን ዚክሪ ለምን እንደጻፉ ሲጠየቁ የሚከተለውን ምላሽ ሰጥተው ነበር፡፡
እነኝህ ፈረንጆች ኢማን ባይኖራቸውም አብዛኞቹ ደግ ናቸው፡፡ የሚሰሩት ነገርም ደግ ነው፡፡ ከአውሮፕላን እስከ መኪና፣ ከመርከብ እስከ ባቡር የተሰሩት በእነርሱ ነው፡፡ እነርሱ በሰሯቸው መጓጓዣዎች ነው ወደ ሐጂ የምንሄደው፡፡ የምግብ ማብሰያ ቡታጋዝና ማታ የምናበራውን ፋኖስ የፈለሰፉት እነርሱ ናቸው፡፡ ሰዎች የሚለብሷቸው አልባሳትም በአብዛኛው በነርሱ የሚሰራው፡፡ ሌላው ይቅርና ድርቅ ሀገራችንን በሚያጠቃበት ወቅት የእርዳታ እህል የሚመጸውቱን እነርሱ ናቸው፡፡ በመሆኑም ነው እነዚህ ደጋግ ፈረንጆች ኢማን ኖሯቸው አላህ ጀንነት እንዲሰጣቸው የተመኘሁት” 
    
*****
እኝህ ሸሪፍ ሙሐመድ ሐቢብ አስማኣን ከመቀመር በተጨማሪ የሚታወቁባቸው አስገራሚ ጸባዮችም ነበራቸው፡፡ ለምሳሌ ጉዳይ ሲይዛቸው ከመንደራቸው እስከ ገለምሶ የሚመጡት በእግር ነው፡፡ የመልስ ጉዞውንም የሚያደርጉት በእግር ነው፡፡ በመንገዱ ላይ የሚዘዋወሩ መኪናዎች ሲቆሙላቸው በጭራሽ አይሳፈሩም፡፡ በእጃቸውም እንደ ሽማግሌ ከዘራ አይዙም፡፡ በተጨማሪም በሐድራቸው ከመቶ ከማያንሱ ደረሳዎቻቸውና ልጆቻቸው ጋር እየኖሩ አንድም ሰው በጉዞአቸው እንዲያጅባቸው አይፈቅዱም፡፡ ይህ በብዙ ሼኾች ዘንድ ያላየሁት ጸባያቸው ነው፡፡

ሸሪፍ ሙሐመድ ሐቢብን ለመጨረሻ ጊዜ ያየኋቸው የዛሬ ሁለት ዓመት ገደማ ነበር፡፡ አንድ ቀን ተመልሼ የሕይወት ታሪካቸውን በስፋት አጠናለሁ የሚል ሐሳብ ነበረኝ፡፡ ነገር ግን ሐሳቤ ሳይሞላልኝ እርሳቸው ቀድመውኝ ወደ አኺራ ሄዱ፡፡ አላህ በጀንነት ያብሽራቸው፡፡ መልካም ስራቸውን ይቀበላቸው፡፡
------
አፈንዲ ሙተቂ
መጀመሪያ ሐምሌ 10/2006 በገለምሶ ከተማ ተጻፈ፡፡
እንደገና ተሻሽሎ ጥር 5/2010 በሸገር ተጻፈ፡፡


No comments:

Post a Comment