Sunday, January 14, 2018

“ቡሩጁል ሱልጣን”ን በጨረፍታ


ጸሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ
----
በጥር ወር 2004 “ሀረር ጌይ” የተሰኘው መጽሐፌ በታተመበት ሰሞን ነው፡፡ አንድ ሰውዬ (ዘመድ ቢጤ ነው) “አፈንዲ! እኔ የምልህን ስማኝ!! አንድ ሁለት ፍሬ ይዘህ ከቢር እገሌ ጋ ሄደህ፣ ቀይ ዶሮ አሳርደህ እርሳቸው የገድ ኪታባቸውን እንዲቀሩበት ብታደርግ ውጤቱን በቶሎ ታየዋለህ” አለኝ፡፡ ከልቤ ሳቅኩኝ፡፡ “እፍረትም አያውቅ እንዴ ይሄ በዘበዛ?” በማለትም ተገረምኩኝ፡፡ እናም “ሲያምርህ ይቀራታል እንጂ. አላደርገውም” ብዬ አባረርኩት፡፡

   የአጋጣሚ ነገር ሆነና የመጽሐፉ ሽያጭ በመጀመሪያዎቹ ወራት በጣም ተንቀረፈፈ፡፡ ሰውዬውም በድጋሚ መጥቶብኝ “አይ አንተ ልጅ!.. አየህ መጽሐፍህ ገበያ እንዴት እንዳጣ!” ሲለኝ ጊዜ “አቦ ተወን ወደዚያ! ቢፈልግ ቤቴ ውስጥ እንደተቆለፈበት አይጥና አይጠ-መጎጥ ይብላው” አልኩትና በድጋሚ ጃስ አልኩት፡፡ ጊዜ እያለፈ ሲሄድ ግን የሽያጩ መንቀርፈፍ ከነከነኝና የዳሰሳ ጥናት አካሄድኩ፡፡ ችግሩንም ደረስኩበት፡፡ የችግሩ ምንጭም ሰብዓዊ ነበር እንጂ “የከቢር እገሌ ዛር ስለተቀየመኝ” አይደለም፡፡ ለምሳሌ “የኢትኖግራፊ ወጎች” የሚለውና በመጽሐፉ ሽፋን ላይ ያለው መለስተኛ ርእስ በአንባቢያን ዘንድ ግርታን ፈጥሮ ነበር፡፡ መጽሐፉን ያነበቡት ላላነበቡት ሰዎች ስለይዘቱ ሲያስረዱ ግን ሁኔታዎች እየተስተካከሉ ሄዱ፡፡ የልፋታችንን ዋጋ መመለስም ጀመርን!!
------
በቅርቡ “አዳል”ን ሳሳትምም ያንን ዘመዳችንን አስታወስኩት፡፡ ያ ሰውየ አሁንም አልተሻለውም፡፡ እንደለመደው “ፍየል ገዝተን፣ ቅጠል ዘንጥፈን እገሌ ጋ እንሂድ” ባይ ነው (ፈጣሪ ብርሃኑን ያብራለትና)፡፡ እርግጥ ከርሱ የሚብሱና እነ ኦፋ ዳኜን ከፈጣሪ በማስበለጥ ነፍሳቸውን ሊሰጧቸው የሚከጅሉ ድኩማን አሉ፡፡ “አባባ ታምራት ገለታ” እንደ ኩርኩር ሲነዳቸው የነበሩ “አሪፍ ነን” ባይ ወተቴዎች ባሉበት ሀገር ውስጥ እንደምንኖርም አልዘነጋንም፡፡ “ስኒ አስገልብጠህ ፈለጉን አስነብብ” ከሚሉት አንስቶ “ቡሩጁል ሱልጣን” አስደግመህ በኪስህ ውስጥ አድርገው” እያሉ የሚነዘንዙ በዘበዛዎችም ሞልተዋል (ነዑዙቢላህ)!! ሁሉንም መታዘብ ነው እንግዲህ!! “ዓለም ቲያትር ናት” አለ ያ ሼክስፒር!!
   ኧረ እንዲያውም ሌላውን ወደ ጎን እናድርግና ስለ“ቡሩጁል ሱልጣን” ትንሽ እንጨዋወት!! ይሄ “ቡሩጁል ሱልጣን” ከሁሉም የከበደው “ሲሕር” ነው ይባላል፡፡ “ሳሒሮቹ” ድግምቱን ሲሰሩ በመጀመሪያ የአንተንና የእናትህን ስም ይወስዳሉ (የእናት ስም የሚወሰደው “የአንድ ሰው ትክክለኛ እናቱ እንጂ ትክክለኛ አባቱ አይታወቅም” የሚለውን ጥንታዊ እሳቤ በመንተራሰስ ነው)፡፡ ከዚያም በስሞቹ ውስጥ ያሉት ሆሄያት በጥንታዊው ዐረብኛ ይሰራበት በነበረው የ“አብጀድ” የፊደል ገበታ ላይ ያላቸውን ክብደት አስልተው ይደምሩታል (እዚህ ጋ አንድ ነገር ልብ በሉ!! ፊደላቱ በአብጀድ ቅደም ተከተል ተድርድረው የተለያየ ክብደት የተሰጣቸው በመሠረቱ ለጥንቆላና ለመተት ስራ ሲባል አይደለም፡፡ በድሮ ዘመን ነገሮችንና ክስተቶችን በፊደላቱ ክብደት ልክ መሰየም በጣም ስለሚወደድ ነው ይህ ልማድ የተፈጠረው፡፡ ለምሳሌ “ሀረር” ሲባል “405” እንደማለት ነው፡፡ ዝርዝሩን “ሀረር ጌይ” በተሰኘው መጽሐፌ በሰፊው ገልጬዋለሁ)፡፡
   በማስከተልም ሳሒሮቹ “ሀዛ ቡሩጁል ሱልጣኑን ወል-ሀመሉን ወል-ሚርሪዙን” እያሉ ህብረ-ቃሉን ይደጋግሙታል፡፡ በመጨረሻም የፊደላቱን መጠሪያ በመለዋወጥ እኛ “ቢልቂሳ” የምንላትን ጂንኒ ይጠሩባታል (ለምሳሌ “ሲን” የሚባለውን የዐረብኛ ፊደል ሲጠሩት “ኺጥ” ይላሉ፤ “ሷድ”ን ደግሞ “ቃድ” ይሉታል፣ “ዋው”ን ደግሞ “ዋር” ይሉታል፡፡ “ካፍ”ንም “ራፍ” ይሉታል ወዘተ…)፡፡ ይህንን ሁሉ ደረጃ አልፎ የሚታሰረው መተትና የሚሠራው ድግምት በታንክና በቢ-ኤም እንኳ አይፈራርስም ይባላል፡፡ እነ እገሌ ሀብታም የሆኑትም በርሱ ነው ይባል ነበር (ዋ!! እኛ ሲባል የሰማነውን ነው የጻፍነው)፡፡
   ታዲያ በዛሬው ዘመን “ኢሉሚናቲ”ን በመሳሰሉ ተረቶች የሚያምን በርካታ የሩቅ መንገደኛ መኖሩ ቢያስገርመኝ “ይሄንን ወፈ-ሰማይ አጩሌ በቡሩጁል ሱልጣን እያቀዣበርኩ በዘበዛ ላድርገው እንዴ?” አሰኝቶኝ ነበር!! (በሹክሹክታ አንድ ሚስጢር እናጫውታችሁ! ባሎቻችሁ አርፎ አልቀመጥ ያላችሁ ሴቶች!! እንኳን ደስ አላችሁ!! ለዚህ ፍቱን መድኃኒቱ ይኸውላችው!! ቡሩጁል ሱልጣንን በወረቀት ላይ አስደግማችሁ በሰውዬአችሁ ሙንታታ ውስጥ ጣሉለት!! ሰውዬአችሁ ሌላ ሴት ባሰበ ጊዜ “ነገርዬው” ኩንታል ሙሉ ጅልቦ እንደተሸከመ “ሀምማል” ተዝለፍልፎ ይወድቃል ይባላል!! ዘዴው ውጤታማ ነው አሉ ሚስጢሩን ያጫወቱኝ ሰዎች! ስስስሽሽሽሽ…! ሚስጢር ነው እንግዲህ)!!
----                           
አፈንዲ ሙተቂ   
ሀምሌ 2009

በአዳማ ከተማ ተጻፈ፡፡

No comments:

Post a Comment