Friday, January 12, 2018

አቡል ሚስክ፡ ግብጽን የገዛው ኢትዮጵያዊ ወዚር




አቡል ሚስክ፡ ግብጽን የገዛው ኢትዮጵያዊ ወዚር
ፀሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ
-----
“የኢትዮጵያ ታሪክ ከተጻፈው ያልተጻፈው ይበዛል” ይባላል፡፡ እውነት ነው፡፡ የዚህ አባባል ሐቀኝነት የሚገባችሁ ወደ ታሪክና ኢትኖግራፊ ምርምር ስትገቡ ነው፡፡ ታዲያ ከተጻፈው የሀገራችን ታሪክ መካከል እንኳ ከኛ ከባለቤቶቹ ይልቅ በሌሎች ዘንድ በስፋት የሚታወቅ ታሪክም አለ፡፡ በዚህ ጽሑፍ በጨረፍታ የምዘክረውን ግለሰብ ታሪክ ያገኘሁት ከውጪ ምንጮች ነው፡፡
----
ባለታሪካችን “አቡል ሚስክ ካፉር” ይባላል፡፡ በአስረኛው ክፍለ ዘመን የኖረ ትውልደ-ኢትዮጵያዊ የግብጽ ገዥ ነው፡፡ አቡል-ሚስክ ወደ ግብጽ የተወሰደው በጉርምስና ዕድሜው ባርነት ተሸጦ ነው፡፡ በዘመኑ ባሮችን መሰለብ በሰፊው ይተገበር ነበር፡፡ በመሆኑም አቡል-ሚስክም ወደ ግብጽ የተወሰደው ጃንደረባ (eunuch) ሆኖ ነው፡፡

አቡልሚስክ በ923 በአንዱ ቀን ለገበያ ቀርቦ ሳለ “የኢኽሺዲ” ስርወ-መንግሥት መስራች የነበረው ሱልጣን ሙሐመድ ኢብን ቱግጅ በድንገት አየው፡፡ ኢብን ቱጊን በብላቴናው ወጣትነት ተማረከ፡፡ ወደ ነጋዴዎቹ ቀረብ ካለ በኋላም “ይሄ ወጣት ከየት ሀገር ነው የመጣው?”በማለት ጠየቃቸው፡፡ ነጋዴዎቹም “ከሐበሻ ነው” በማለት መለሱ፡፡

ኢብን ቱግጅ የነጋዴዎቹን ምላሽ ሲሰማ የጥንቱ ቢላል ኢብን ረባህ ትዝ አለው፡፡ በደም ፍላት መንፈስም “የሐበሻን ልጅ ነው እንዲህ አስራችሁ ለሽያጭ ያመጣችሁት? የነጃሺ ውለታ ተረስቶ ነው ሐበሻ በሀገሬ ምድር በባርነት የሚሸጠው?” በማለት በንዴት ወረደባቸው፡፡ ነዴዎቹም “እኛ እኮ አይደለንም የፈነገልነው! ከሀገሩ ነጋዴዎች ነው ገዝተን ያመጣነው” በማለት መለሱለት፡፡

ኢብን ቱግጅ “በሉ ቶሎ ለኔ ስጡኝ! ሁለተኛ የሐበሻ ተወላጅ የሆነን ሰው በባርነት እንዳትሸጡት” በማለት አቡልሚስክን ከነጋዴዎቹ እጅ ተረከበው፡፡ ወደ ቤተ መንግሥቱ ወስዶትም ልብሱን ከቀየረለት በኋላ እዚያው እንዲኖር ፈቀደለት፡፡ በዘመኑ በታወቀው ኒዛሚያ መድረሳ የካይሮ ቅርንጫፍ አስመዝግቦት ትምህርቱን እንዲማርም አደረገው፡፡

ወጣቱ አቡልሚስክ በትምህርት ቆይታው ዐጃኢበኛ ተማሪ ወጣው፡፡ በትምህርት መደቡ ከሁሉም ተማሪ መካከል አንደኛ እየወጣ ይሸለም ጀመር፡፡ ሌሎች ተማሪዎች ብዙ ዓመታት የሚወስድባቸውን የዒልም ጉዞ እርሱ በጥቂት ዓመታት ውስጥ አጠናቀቀው፡፡ ሱልጣን ሙሐመድ ኢብን ቱግጅ የአቡል ሚስክን ጉብዝና ሲያይ እርሱን ከነጋዴዎቹ እጅ መንጭቆ የወሰደበትን ቀን አወደሰው፡፡

የመድረሳው ኃላፊዎች አቡልሚስክን “ሙዓሊም” (ፕሮፌሰር) አድርገውት ሊቀጥሩት ፈልገው ነበር፡፡ ሱልጣን ሙሐመድ ግን “እርሱን ለከፍተኛ ስራ ስለምፈልገው አስተማሪ አይሆንም” በማለት ከለከላቸው፡፡ ወደ ቤተ መንግሥቱ ወስዶትም ዋና አማካሪው አድርጎ ሾመው፡፡ ልጆቹ እንደርሱ ጎበዝ እንዲሆኑለት ስለተመኘም ከስራ ሰዓት ውጪ የግል መምህራቸው ሆኖ እንዲያስተምራቸው መደበው፡፡ የአቡልሚስክ መኖሪያም እዚያው ያደገበት ቤተመንግስት ሆነ፡፡ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ጄኔራሎቹ ሱልጣኑን ሊገለብጡት ሲሞክሩ ደግሞ አቡልሚስክ በፊት ከነበረው ሹመት በተጨማሪ የቤተመንግስቱ ጠባቂዎች አዛዥ ሆኖ ተመደበ፡፡
----
ይህ በእንዲህ እያለ በግብጹ ሱልጣን ስር ይገዙ በነበሩት ሶሪያና ሒጃዝ አመጽ ፈነዳ፡፡ ሱልጣን ሙሐመድ የመደባቸው ጄኔራሎች እየተሸነፉ ከግዛቶቹ ተባረሩ፡፡ ሱልጣኑ አመጹን ለመቆጣጠር እንዲመቸው አዲስ ጦር አዘጋጀ፡፡ አቡልሚስክንም የዚህ ጦር አዛዥ አድርጎ አዘመተው፡፡ አቡልሚስክ ወደ ሶሪያና ሒጃዝ ገብቶ አማጺዎቹን ድል በማድረግ ሱልጣኑ በግዛቶቹ ላይ የነበረውን የበላይነት አስከበረ፡፡

ታዲያ አቡልሚስክ ከድሉ በኋላ የሱልጣኑን ተቃዋሚዎች አልተበቀለም፡፡ ከዚያ ይልቅ የአመጹን መንስኤ ለማወቅ ነበር የሞከረው፡፡ ከህዝቡ ጋር ባደረገው ውይይትም የአመጹ መንስኤ ሀገሩን ያስተዳደሩ የነበሩት ገዥዎች በህዝቡ ላይ ሲፈጽሙት የነበረው በደልና የተዘፈቁበት የስልጣን ብልግና እንደሆነ ተረዳ፡፡ ይህንንም ለሱልጣኑ ግልጽ አድርጎ አስረዳው፡፡ ሱልጣኑም በግዛቶቹ የተፈጠሩትን ችግሮች ለመቅረፍ ሰፊ ስራ ሰራ፡፡
---
ሱልጣን ሙሐመድ ኢብን ቱግጅ ከልጆቹ መካከል እርሱን የሚተካ ወራሽ እንደሌለው በጊዜ ነበር ያወቀው፡፡ በመሆኑም “ጠላቶቼ በብዙ ልፋት ያስከበረውን የግዛቱን ሉዓላዊነት ሊደመስሱት ይችላሉ” በማለት ስጋት ገባው፡፡ በተለይም ከሁለት መቶ አመታት በፊት በሽንፈት የተባረሩት ሮማዊያን ግብጽን በድጋሚ ሊነጥቁ ማቆብቆባቸው አሳሰበው፡፡ ስለዚህ በበሽታ ተለክፎ አልጋ ላይ በዋለበት ጊዜ ቤተዘመዶቹን ሁሉ ጠርቶ “ንግሥናውን ለልጆቼ አውርሼአለሁ፡፡ ሀገሩን በበላይነት የማስተዳደሩን ስልጣን ግን ለአቡልሚስክ አስረክቤአለሁ፣ ማንም ሰው በስራው ጣልቃ እየገባ እንዳያስቸግረው” በማለት ተናዘዘ፡፡ አቡልሚስክም የሱልጣኑን አደራ በመረከብ የሀገሩ “ዋና ወዚር” (ጠቅላይ ሚኒስትር) ሆኖ መግዛት ጀመረ፡፡
----           
አቡልሚስክ በስልጣን ላይ ሳለ ከፈጸማቸው ዋና ተግባራት አንዱ ትምህርትን ማስፋፋቱ ነው፡፡ በዚህም መሠረት በግብጽ ምድር በመቶ የሚቆጠሩ መድረሳዎችን ገነባ፡፡ ለትምህርት የሚሆን መደበኛ ፈንድም መሠረተ፡፡ ለአስተማሪዎች በቂ ክፍያ እንዲፈጸምም አደረገ፡፡ በዘመኑ ተዳክሞ የነበረው የአልኬሚ ምርምር እንዲጠናከር በትጋት ሠራ፡፡

አቡልሚስክ ኢኮኖሚውንም ለማንሰራራት ጥረት አድርጎ ነበር፡፡ በዚህም መሠረት ለነጋዴዎች የግብር ቅናሽ አደረገ፡፡ ከሀገር ሀገር እየተዘዋወሩ ለሚነግዱት ሲራራ ነጋዴዎች ጥበቃ እንዲደረግላቸውም አዘዘ፡፡ በዘመኑ ዋጋው ወድቆ የነበረውን የግብጽ ዲናር የሚተካ አዲስ የወርቅ ገንዘብ አሰራ (ፎቶውን ይመልከቱ)፡፡
-----
አቡልሚስክ በዘመኑ መለኪያ በቂ በሚባል ደረጃ የተማረ ሰው ቢሆንም እውቀትን ጠግቦ አያውቅም፡፡ በመሆኑም በመንፈሳዊውም ሆነ በዓለማዊው እውቀት የመጠቁ ምሁራንን ወደ ቤተመንግሥቱ እየጠራ ያወያያቸው ነበር፡፡ ለገጣሚዎችም ፍቅርና ክብር ነበረው፡፡ በዚህ ሁኔታ ወደ ቤተመንግስቱ ከመጡት አንዱ ታዋቂው ገጣሚ “አል-ሙተነቢህ” ነው፡፡

አል-ሙተነቢህ ጎበዝ ገጣሚና ባለቅኔ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይሁንና ከገጣሚነቱ ባሻገር ስልጣንና ገንዘብም በብዛት ይወድ ነበር፡፡ ወደ ካይሮ ከተማ የመጣውም የሶሪያው ገዥ ስልጣን ስላልሰጠው “የርሱ የበላይ ከሆነው የግብጽ ሱልጣን ዘንድ ሄጄ ፍላጎቴን መፈጸም እችላለሁ” በሚል ምኞት ነበር፡፡

አቡልሚስክ የአልሙተነቢህን ቅኔዎች ቢያደንቅም ሌሎች ሰዎችን እየተነኮሰ መዘባበቻ እንደሚያደርጋቸውም ያውቅ ነበር፡፡ ስለዚህ ወደ ቤተመንግሥቱ በጣም እንዲቀርብ አልፈቀደለትም፡፡ በከተማዋ አንድ ቤት ሰጥቶት ለኑሮው መደገሚያ የሚሆን ተቆራጭ ብቻ ይልክለት ነበር፡፡ አልሙተነቢህ አቡልሚስክን በቅኔዎቹ እየደጋገመ ቢያሞግሰውም ወዚሩ ፊት አልሰጠውም፡፡ ገጣሚው አልሙተነቢህ ለሶስት ዓመታት (ከ957-960) የገዥውን ልብ ለማማለል ያደረገው ሙከራ ስላልተሳከለት ከግብጽ ወደ ኢራቅ ለመሰደድ ወሰነ፡፡ ታዲያ ወደ ባግዳድ ሲሄድ በልቡ የተደበቀውን በሽታ ይፋ ያወጣበትንም ድርጊት ፈጸመ፡፡ አቡልሚስክ በባርነት ተፈንግሎ ወደ ግብጽ የመጣ ኢትዮጵያዊ ጃንደረባ መሆኑን እየጠቀሰ አንድ ገጽ የሚሆን ቅኔ ጻፈበት፡፡
         
ይሁንና በዚህም በኩል የርሱ ምኞት አልተሳካለትም፡፡ ቅኔው አቡልሚስክን ሊያሳጣው ቀርቶ በተቃራኒው በአል-ሙተነቢህ ላይ ከባድ መዘዝ ነው ያስከተለበት፡፡ በሄደበት ሀገር ሁሉ ህዝቡ “የቢላልን ታሪክ ረስቶ በሐበሻው ብላቴና ላይ የተሳለቀ” እያለ ወረደበት፡፡ እርሱ ያነጋገራቸው የአውራጃና የክፍለ ግዛት ገዥዎች ድሮ በግጥሞቹ እንዳልተንሰፈሰፉለት ሁሉ በአቡልሚስክ ላይ በፈጸመው ድርጊት የተነሳ ሊያነጋገሩት እንኳ ተጠየፉ፡፡ አልሙተነቢህም ተስፋ ቆርጦ ከዐረቡ ዓለም ወደ ኢራን ተሰደደ፡፡ ታዲያ በዚያም ከዓመት በላይ ለመቆየት አልቻለም፡፡ የግዛቱ ገዥ ሊያቀርበው ስላልፈቀደ በተሸነፈ መንፈስ ወደ ኢራቅ ለመመለስ ወሰነ፡፡ ሆኖም ካሰበው ስፍራ ሳይደርስ በመንገድ ላይ ባደፈጡ ወንበዴዎች ተገደለ፡፡
-----
አቡልሚስክ ግብጽንና በርሷ ስር የነበሩትን ግዛቶች (ሂጃዝ፣ ሶሪያ፣ ፈለስጢን) ለሀያ ዓመታት ከገዛ በኋላ በ966 የገዥነቱን ስልጣን ዓሊ ለተባለው የሱልጣን ሙሐመድ ልጅ አስረከበ፡፡ ከመንግሥት ስራ ሙሉ በሙሉ ተገልሎም በዒባዳና ሌሎችን በማስተማር ህይወቱን መግፋት ጀመረ፡፡ በ968 ግን በተስቦ በሽታ ተለክፎ አረፈ፡፡

በትረ መንግሥቱን ከአቡልሚስክ የተረከበው የሱልጣን ሙሐመድ ልጅ አባቱ እንደገመተው ጠንካራ ገዥ ለመሆን አልቻለም፡፡ ለአንድ ዓመት ብቻ እንደነገሠ ከቱኒዚያ አካባቢ የመጡትና “የነቢዩ ሙሐመድ ቤተሰብ አባላት ነን” የሚሉ ጎሳዎች መንግሥቱን ገለበጡት፡፡ በዚህም ለሀምሳ ዓመታት በስልጣን ላይ የቆየው የኢኽሺድ ስርወ-መንግሥት ፍጻሜ ሆነ፡፡ አዲሶቹ መሪዎችም “ፋጢሚይ” የሚባለውን ስርወ መንግሥት መሠረቱ፡፡
------
አፈንዲ ሙተቂ
ጥር 3/2010

በሸገር ተጻፈ፡፡

No comments:

Post a Comment