Saturday, September 7, 2013

==ከትምህርት ቤት መዝሙሮቻችን በጥቂቱ (ለትዝታ)==


ጸሓፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ
-----
የአንደኛ ደረጃ ትምህርቴን ያጠናቀቅኩት በቁጥር ሁለት ት/ቤት ነው፡፡ የትምህርት ቤታችን ዋነኛ ህንጻ በስዕሉ ላይ የምትመለከቱት ነው፡፡ ይህንን ህንጻ የኢጣሊያ ወራሪዎች ናቸው የሰሩት፡፡ በከተማችን ውስጥ ለረጅም ዘመናት በቁመቱ ከርሱ ጋር የሚስተካከል ሰው ሰራሽ ግንባታ አልነበረም፡፡ በዚህም የተነሳ በኦሮምኛ ስሙ “Mana Dheeraa” (ረጅሙ ህንጻ) በማለት ነው የምንጠራው፡፡

  የትምህርት ቤቱ የኦፊሴል ስም ነው “ገለምሶ ቁጥር ሁለት አንደኛ ደረጃ ት/ቤት” ነው፡፡ በተለምዶ ህንጻውን የምንጠራበት “ቁጥር ሁለት” የተሰኘው የአማርኛ ስሙ የተገኘው ከዚሁ ነው፡፡

 “ቁጥር ሁለት” (“መነ ዴራ”) በኢጣሊያ ወራሪዎች ዘመን የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ነበር፡፡ ጣሊያኖቹ ሲወጡ የወረዳ ጽ/ቤት ሆኖ ማገልገል ጀመረ፡፡ ከዚያም ወደ አዳሪ ት/ቤት ተቀየረ፡፡ በ1962 ገለምሶ የአውራጃ ዋና ከተማ ስትሆን ደግሞ ህንጻው ወደ እስር ቤት ተቀየረ፡፡ በርሱ ምትክም ሌላ ትምህርት ቤት በከተማው የምስራቁ ክፍል ተሰራ፡፡

  “ቁጥር ሁለት” እስከ ዘመነ ቀይ ሽብር ድረስ እንደ እስር ቤት ካገለገለ በኋላ በ1972 ገደማ እንደገና ወደ ትምህርት ቤት ተቀየረ፡፡ ሁለቱን አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በስም ለመለየት በሚልም “ቁጥር ሁለት” የሚለው ስያሜ ተሰጠው፡፡ እያደገ የመጣውን የተማሪ ብዛት ለማስተናገድ እንዲችልም በርካታ ክፍሎች በግቢው ውስጥ ተሰሩለት፡፡ በማስከተልም ሌሎች በርካታ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በከተማው ውስጥ ተከፈቱ፡፡  

ስለ ቁጥር ሁለት ታሪክ ይህንን ያህል ካልኳችሁ ይበቃል፡፡ አሁን ደግሞ የዚህ ትምህርት ቤት ተማሪ ሳለሁ እንዘምራቸው ከነበሩት መዝሙሮች ጥቂቶቹን ላካፍላችሁ፡፡
 -----
ዝናብ ሲዘንብ በዝምታ አናሳልፍም፤ በከፍተኛ ድምጽ እንዘምራለን እንጂ! መዝሙሩን እኛ ብንረሳ እንኳ አስተማሪዎቻችን “ዘምሩ” ይሉናል፡፡ በዚህ በኩል እስከ አሁን ድረስ ትዝ የሚሉኝ የሚከተሉት ናቸው፡፡
  
ሀ/. ዋንታ ነሜራ
ዋንታ ነሜራ ዋሂራ ዋንታ ነሜራ
ዋንታ ነሜራ ዋሂራ ዋንታ ነሜራ
ዝናቡ ዘነበ ደጁ ረሰረሰ
አንዱን ሳላጠና ፈተና ደረሰ
ዋንታ ነሜራ ዋሂራ ዋንታ ነሜራ

“ዋንታ ነሜራ” የኩባ ዘፈን እንደሆነ ይታወቃል፡፡ አዝማቹ ብቻ ተወስዶ ወደ አማርኛ መዝሙር የተቀየረበትን መነሾ ግን አላውቅም፡፡
--
ለ/. “ዝናቡ ዘነበ”
ዝናቡ ዘነበ አትምጪ ስልሽ
ይኸው እንደፈራሁት ጎርፍ ወሰደሽ፡፡
በሀምሳ በሰላሳ ሲገዛ ፈረስ
በመቶ ብር ገዛሁ የሰው አጋሰስ፡፡

በዚህ ግጥም ውስጥ የወንድ ትምክህት አለ አይደል? ያኔ ግን ህጻናት ነበርና ምንነቱ አይታወቅንም ነበር፡፡ እንዲያውም አንዳንድ የአማርኛ ቃላትን ትርጉም እንኳ በፍጹም አናውቅም ነበር፡፡ ለምሳሌ “አጋሰስ” ምን ማለት እንደሆነ በኋላ ላይ ነው የተረዳሁት፡፡
-----
ብዙ መዝሙሮች የምንዘምረው በሙዚቃ ክፍለ ጊዜ ነበር፡፡ ከነዚያ መዝሙሮች መካከል ከየዘርፉ አንድ ሁለቱን ልጻፍላችሁ፡፡

  ሀ/. “አንቅልፍ ጨርሰን” (ስለግል ንጽህና)

እንቅልፍ ጨርሰን ጠዋት ስንነሳ
የምንሰራውን ልጆች እንዳንረሳ
ልብሳችንን ለብሰን ሽንት ቤት ደርሰን
ሳሙናና ውሃ ለፊት አቅርበን
እጅና ፊታችን ማጠብ አለብን፡፡
የጸጉርም ጽዳት መጠበቅ አለበት
በደንብ አበጥሮ ከተገኘም ቅባት
ቀብቶ መሄድ ነው ወደ ትምህርት ቤት፡፡

ለ/. ዝንቦች (ስለንጽህና)

ዝንቦች መጥፎ ናቸው
  “እሽ! እሽ!” ይበሏቸው፡፡
  ዐይንን ያጠፋሉ
  በሽታን ያመጣሉ
  እናባርር በሙሉ!!
   እናባርር በሙሉ፡፡
  
 ሐ/. አብዮታዊ ሰራዊት (ስለ አብዮታዊው ጦር)

አብዮታችን በጣም በጣም ደመቀ
የድል ጮራ ዳር እስከ ዳር ፈነጠቀ፡፡
በምስራቅ በደቡብ በመሀል አልፎ
ጠላቱን ወራሪ ማረፊያ አሳጥቶ
እንደ ካራማራ እን ጭናክሰን
ድል ተቀዳጅቶ ገስግሶ በሰሜን፡፡
ተዋግቶ ተዋግቶ
አጥንቱን ከስክሶ ደሙን አፍስሶ
አብዮታዊ ሰራዊት ድል አድርጎ ሲገባ
በሉለት ጉሮ ወሸባ! በሉለት ጉሮ ወሸባ!!

መ/. ውሸታሙ እረኛ (ስነ-ምግባር)

ውሸታሙ እረኛ
ሲያልፍ መንገደኛ
ቀበሮ መጣብኝ
በጎቼን በላብኝ፡፡
እያለ ዘወትር
ሲቀልድ ሲያስቸግር
በዚህ አድራጎቱ
ደግሞም በውሸቱ፡፡
አንድ ቀን ቀበሮ
መጣና በድንገት
በጎቹን በላበት፡፡
ውሸታሙ እረኛ
ዘወትር ልማደኛ
ኡኡ እያለ መጣ
የሚረዳውን አጣ፡፡
-----
በሙዚቃ ክፍለጊዜአችን በርካታ “ትርኪምርኪ” መዝሙሮችንም እንዘምራለን፡፡ እስቲ ሁለት “ትርኪምርኪ” መዝሙሮችን ልጋብዛችሁ፡፡

ሀ/ ጋሼ ደያስ
 
አራቱንም ጣቴ ጋሼ ደያስ
  ቢላዋ ቆርጦኛል ጋሼ ደያስ
  አንዱ ብቻ ቀርቶኝ ጋሼ ደያስ
  ያንገበግበኛል ጋሼ ደያስ

ጋሼ ደያስ ተክሌ የሁለተኛ ክፍል የአማርኛ መምህራችን ነበር፡፡ በተጨማሪም የፈረቃ መሪ (ዩኒት ሊደር) ነበር፡፡
-
ለ/. ኦኬ ኦኬ

 ኦኬ ኦኬ ኦኬ ስራ
ሰላም ሰላም ወደ አስመራ
አናግረኝና አናግርሃለሁ
በአሜሪካ ሽጉጥ አዳፍንሃለሁ፡፡
 ሁለትና ሁለት ሲደመር አራት
ፍቅርሽ ይጣፍጣል ከማር ከወተት፡፡
  -----
በሙዚቃ ፔሬድ መዝሙር መዘመር ብቻ ሳይሆን እየዘፈኑ ዳንስ መደነስም ነበር፡፡ እያንዳንዱ ተማሪ የሚያውቀውን ዘፈን እየዘፈነ ይደንሳል፡፡ እኛም ክብ ሰርተን ከሳር ላይ ተቀምጠን ዘፈኑን ከደናሹ ተማሪ እየተቀበልነው እናጨበጭባለን፡፡ 
 
ተማሪው የሚዘፍነው ዘፈን ከካሴት ላይ የተገኘ፣ በሬዲዮ የተለቀቀ፣ በቀበሌ ኪነትና የአካባቢ ሚሊሻ የተዘፈነ ወዘተ ሊሆን ይችላል፡፡ ይሁንና አብዛኛው ተማሪ ተመሳሳይ ነገር ስለሚደጋግም ያሰለቻል፡፡ አንዳንድ ተማሪዎች ግን ከየት እንደተገኙ በማይታወቁ አስገራሚ ዘፈኖች እየደነሱ ያዝኑናል፡፡ ከነርሱም መካከል የሁለተኛ ክፍል አለቃችን የነበረው አያሌው አብነት ፈጽሞ የሚረሳ ሰው አይደለም፡፡

   “አያሌው  ለማ ከፈረስ ወድቆ ከንፈሩ ደማ” የሚለውን ዘፈን ለመጀመሪያ ጊዜ የሰማሁት ከአያሌው አብነት ነው፡፡ አያሌው “ያ ማሙሹ መለሜላ” የሚል የኦሮምኛ ዘፈንም ነበረው፡፡ ሲፈልግ ደግሞ “ሎሜ ሎሜ አይሳ!” እያለ ወላይትኛ ሊዘፍን ይሞክራል (“ሎሜ ሎሜ” ከሚለው ሐረግ በስተቀር ሌላው በሙሉ አማርኛ ነው፤ ያኔ ግን እንደ ወላይትኛ ነው የምንቆጥረው)፡፡ አያሌው ሲያሻው እንግሊዝኛ ልዝፈንላችሁ ይልና አስረሽ ምችው ያስነካል፡፡ እስቲ የርሱን እንግሊዝኛ ዘፈን ልጋብዛችሁና ልሰናበት፡፡

      አይ ጌቾ ጌቾ ( እኛ “ፐረስ ፐረስ” እያልን እንቀበለዋን)
     አይ ጌቾ ቤቢ
     ማዘር ከፋዘር
     ወለዱ ሲስተር
    ሄዱ በአየር
    ገቡ ጎንደር
  -----
   በወዳጅነታችን እንሰንብት፡፡
አፈንዲ ሙተቂ
ጳጉሜ 2/2005
  -----

No comments:

Post a Comment