Monday, September 2, 2013

==“የጂንኒ” ወግ (ክፍል ሁለት)==



ጸሓፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ                                        
ክፍል ሁለት
-----------
ይህ ክፍል ሁለት የጂንኒ ወጋችን ነው፡፡ “አዑዙ ቢላሂ” ብለን ጀምረናል፡፡ ወደ ዋናው ወግ ከመግባታችን በፊት ግን አንድ ልጅ “እኛ እኮ ቢልቂሳ ነው የምንላት” ያለኝ ነገር ሆዴን እንደከነከነው ላወሳ እፈልጋለሁ፡፡

 የልጁ ዳር ዳርታ ገብቶኛል፡፡ “ጂንኒ ስሟን እንዲያነሷት ስለማትፈለግ በኮድ ብትጠቀም ይሻል” ማለቱ ይመስለኛል፡፡ እውነቱን ነው፡፡ ጂንኒ ስሟን ደጋግሞ የሚያነሳትን አትፈልግም፡፡ ድሮ ስለርሷ መነጋገር ስንፈልግ “ጀመዓታ” (ጀመዓዎቹ)፣ “ዋን አላ” (የውጪ ሰዎች)፣ “ጀረ” (ሰዎቹ) እያልን ነበር የምንጠራት፡፡ ሆኖም “ጂንኒ” ብንላትም እኛ ቦታዋ ድረስ ሄደን እስካልተተናኮልናት ድረስ ምንም አትለንም፡፡ እርሷም እኛን በተፈጥሮ ስማችን “ኢንሲ” (ሰዎች) እያለች ነው የምትጠራን፡፡ ከሰፈሯ አጠገብ ቆመን “ጂንኒ” ብንላት ግን “የማንነው ጭልፋ ፊት! ቤቴ ድረስ መጥቶ ነው እንዴ በነጠላ ቃል የሚጠራኝ” ብላ በጥፊ ዋጋችንን ትሰጠናለች፡፡ ስለዚህ እዚያ ስንሄድ ወዳጃችን እንዳለው “ቢልቂሳ” ወይንም ሌላ “ኮድ” መጠቀሙን አንርሳ፡፡ አሁን ግን “ጂንኒ” እያልን እንቀጥል፡፡

በነገራችን ላይ ከጂንኒዎቹ ውስጥ ደግ አድራጊዎችም እንዳሉ ጽፌላችሁም ነበር አይደል? እነዚያ ደጋግ ጂንኒዎች ምን የሚባሉ ይመስላችኋል?  “ሩሐኒይ” ተብለው ነው የሚጠሩት፡፡ “ሩሐኒይ” ከሆኑ ጂንኒዎች መካከል አንዳንዶቹ ጿሚዎችና ሰጋጆችም ናቸው፡፡
-----------
አንዳንድ ጂንኒዎች ቅቤ ይበላሉ ብያችሁ ነበር፡፡ አዎን በደንብ ይበላሉ! ታዲያ እነዚህኛዎቹ ጂንኒዎች ቅቤውን የሚያገኙት ከራሳቸው ከብት ሳይሆን ከየሰው ጓዳ እየሰረቁ ነው፡፡ አንዲት ጂንኒ ለቅቤ ስርቆት የምትሰማራው በአንድ እጇ “ቡቄ” የምትባል ትንሽ የቅቤ ቅል በመያዝ ነው፡፡ ቅቤውን ከሰው ጓዳ ገብታ ከሞጨለፈች በኋላ የቤቱ ባለቤቶች እንዳይነቁባት ውሃ፣ እጓት፣ አመድ፣ ወዘተ… ትጨምርበትና ፊት እንደነበረው መልሳ ትከድነዋለች፡፡ የቤቱ ሰዎች ሲመጡ ቅቤው መበከሉ ስለማይታወቃቸው እንደ እውነተኛ ቅቤ መጠቀማቸውን ይቀጥላሉ፡፡

 ጂንኒ በዚህ ምድር ላይ የምትፈራው ነገር የላትም፡፡ ከአንድ እንስሳ በስተቀር ሌሎቹን እንስሳት እንደፈለገችው ታንበረክካቸዋለች፡፡ ጂንኒ የማትችለው የትኛውን እንስሳ እንደሆነ ታውቃላችሁ? ጅብ ነው፡፡ በየሰፈሩ የሚልከሰከሰውና የሚቀላውጠው አያ ጅቦ ቀላል እንዳይመስላችሁ! ጂንኒን ድባቅ  የሚመታውና ድራሿን የሚያጠፋት እርሱ ብቻ ነው፡፡ በተለይ አያ ጅቦ ለስርቆት የምትሰማራውን ጂንኒ አይምራትም፡፡ እንደፈቀደው እየዘነጣጠለ ነው የሚያወራርዳት፡፡
  
ጂንኒዋ ጅብ በሚገጥማት ጊዜ ጅብዬው ሳያያት ከአካባቢው መሰወር ከቻለች በደህና አመለጠች ማለት ነው፡፡ ጅቡ ካያት ግን አይለቃትም፡፡ የገባችበት ገብቶ ለቀም ያደርጋትና እንክትክቷን ያወጣታል፡፡ ከዚያም እንደ ብሩንዶ እያጣጣመ ይበላታል፡፡ ሆኖም በርሱ የተበላው የጂንኒ ገላ በሆዱ ስለማያድር ወዲያው ያስታውከዋል፡፡ ጧት ጅቡ ጂንኒዋን ከበላበት ቦታ ብትሄዱ በትውከት የወጣውን ሁሉ እዚያው ታገኙታላችሁ፡፡ ነጭና ለስላሳ ጸጉር (ወደ ብርድ ልብስ የሚያደላ)፣ ጥቁር ከሰል የመሰለ ነጫጭባ! የተሰባበረ ቅል..ምናምን የተቀላቀለበት ጂንኒ ጀቡቲ…
   
ግን ጅብ ጂንኒን ሊበላት ሲያባርራት አይታችሁ ወይም ሰምታችሁ ታውቃላችሁ? አቤት ስታሳዝን! ዋ አንጀት ስትበላ!  የአስማትና የመተት ሀይሏ ሁሉ ነው የሚጠፋባት፡፡ አካሏን ወደ ሰውም ሆነ ወደ ዛፍ መቀየር አትችልም፡፡ ያላት ምርጫ “ኡ..ኡ..ኡ.. ኡ… አውጡኝ” እያለች የሰዎችን እርዳታ መማጸን ነው፡፡ በአካባቢው ሰዎች ካሉ ስርቅርቅ ድምጿ ያሳዝናቸውና ከጅቡ ያስጥሏታል፡፡ ጂንኒዋም ለውለታቸው እንዲሆን ከወርቅ የተሰራ ባለ ሉል ቀለበቷን አውልቃ ትሰጣቸዋለች፡፡ አልማዝና እንቁ ልትጨምርላቸውም ተስፋ ትሰጣቸዋለች፡፡ በማግስቱ ጣታቸውን ሲያዩት ግን ቀለበቱ የለም፡፡ “ማን ወሰደው?” ቢሉ ጂንኒዋ!

 እንዲህ አይነት ጂንኒ ካጋጠመቻችሁ ጅቡ ርቆ ሳይሄድ ቀለበቷን ላትወስደው መሀላ ማስገባት አለባችሁ፡፡ ጂንኒዋ መሀላ ከገባች ቀለበቱን በጭራሽ አትወስደውም፡፡ ጂንኒ መሀላ በማክበር ከሰው ልጅ በጣም ትበልጣለች፡፡ ደግሞ ቀለበቷ ተራ ወርቅ እንዳይመስላችሁ! ወርቁ በቀንም ሆነ በሌሊት ያበራል፡፡

የጂንኒ ዋናው መዳኛዋ ግን ይህ አይደለም፡፡ በዋነኛነት በደህና ጊዜ ከምስጥ ጋር የተዋዋለችውን ውል በመጠቀም ነው አያ ጅቦ ከሚያደርስባት አደጋ ለማምለጥ የምትሞክረው፡፡ እስቲ ምስጥ የሚሰራውን ኩይሳ ተመልከቱ! በርግጥ በርሱ ችሎታ ብቻ ነው የተሰራው? አይደለም ወዳጆቼ! የጂንኒ እጅ አለበት፡፡ ምስጥ አፈሩን እየፈረፈረና እንደማስቲካ እያቦካ አንዱን ቅንጣት በአንዱ ላይ የማነባበር ትልቅ ችሎታ አለው፡፡ በዚህ በኩል ማንም አይደርስበትም፡፡ ግን አፈሩን የሚያርስበትን ውሃ ከየት ነው የሚያመጣው? ከመሬት ውስጥ እያወጣ ይመስላችኋል? እንዲያ አይደለም፡፡ ውሃውን የምታቀርብለት ጂንኒ ናት፡፡ በየቀኑ በብዙ መቶ በርሜሎች የሚቆጠር ውሃ ነው የሚቀርብለት፡፡ የጂንኒዎች አንዱና ትልቁ ስራም ምስጥን ማገዝ ነው፡፡ ምስጡ የኩይሳው ርዝመት ይበቃኛል ብሎ ግንባታውን እስካላቆመ ድረስ ጂንኒ ውሃውን ያለምንም ማንገራገር ትቀዳለታለች፡፡ የጂንኒ ልጆችም በዚህ ላይ ያግዟታል፡፡
 
 ይህ ኩይሳው በምስጥ የተገነባ ቢሆንም ጂንኒም በሚገባ ትጠቀምበታለች፡፡ ጅብ ሊበላት የሚያሳድዳት ማንኛዋም ጂንኒ በአቅራቢያዋ “ኩይሳ” ካገኘች ከአደጋው አመለጠች ማለት ነው፡፡ አያ ጅቦ ሊደፍረው የማይችለው ብቸኛው ምሽግ የምስጥ ኩይሳ ነው፡፡ ጅቡ ሊበላት ሲንደረደርባት ጂንኒዋ ወደ ኩይሳው ጥልቅ! ከዚያ ውስጥ ሆና “አያ ጅቦ ስጋዬ እንዳማረህ ይቅር” እያለች ትዘንጥበታለች፡፡ ሞኙ አያ ጅቦ ጂንኒዋ ተዘናግታ የምትወጣ ስለሚመስለው እዚያው ኩይሳ ስር ያድራታል! ግን ልፋቱ ከንቱ ነው፡፡

   አዎን! የምስጥ ኩይሳ ለጅንኒ ህይወት መቀጠል ትልቁን ሚና ተጫውቷል፡፡ ጂንኒ በኩይሳው ለመጠቀም ከምስጥ ጋር የተዋዋለችው ጥንት ነበር አሉ (ያንን ዘመን ካሌንደር አያውቀውም)፡፡ ይኸው ሁለቱም በኩይሳው እየተጠቀሙ እዚህ ደርሰዋል፡፡ በጋራ መስራት ለግንባታ ብቻ ሳይሆን ለአደጋ ጊዜም ፋይዳ አለው፡፡ በነገራችን ላይ በጋራ የመስራትን ጥበብ የፈለሰፉት ጂንኒ እና ምስጥ መሆናቸውን ታውቃላችሁ? እኛ ከታሪካችን የሰማነው እርሱን ነው፡፡ ሌላው “ተረት” ነው፡፡
                *****  *****  *****
   አንዳንድ ሰዎች “ጅንኒዎች ፍቅር ናቸው” ይላሉ፡፡ “አንተ ግልጽና ንጹህ ሆነህ ከቀረብካቸው እንደፈቀድከው ይሆኑልሃል፤ ልጃቸውን ለጋብቻ ከጠየቅክ ቆንጆ የሆነችውን መርጠው ይሰጡሀል፤ በችግር በተወጠርክ ጊዜም ቶሎ ይደርሱልሃል፤ በጨዋታ ጊዜም እንደፈለግከው ያጫውቱሃል፤ ጅንኒ ቁልቋል..ጅንኒ ጀቡቲ..ጂንኒ ጃንካ…
  እስቲ አንድ ሁለቱን ላጫውታችሁ፡፡ ራሴ ያየሁትንና የሰማሁትንም እጨምርበታለሁ (ማመን አለማመን መብታችሁ ነው… )፡፡
 
    “አብዲ ፈረስሌ” ይባላል፡፡ በአንድ ከተማ በጉርብትና አብረን እንኖር ነበር፡፡ አብዲ ወደ ገለምሶ የመጣው ከጎለመሰ በኋላ ነው፡፡ ልደቱና እድገቱ በምስራቅ ሀረርጌዋ የሀረማያ ከተማ ነው፡፡ አንድ ቀን ታናሽ ወንድሜ አብዲ ስለ ጂንኒ ትዝታዎቹ ያጫወተውን ነገረኝ፡፡ እኔም ታሪኩ ደስ ስላለኝ በሳምንቱ አብዲ እንዲደግመኝ ጠየቅኩት፡፡

  “አዎን! እዚያው ሀረማያ ነው፡፡ ከጂንኒ ጋር የተጫወትነውን ሸጎዬ መቼም ቢሆን አልረሳውም፡፡ ሸጎዬ ከሰው ጋር ስትጫወት እኮ  ለጨዋታው ያለህ ስሜት ቶሎ አይነቃቃም፡፡ አንዳንዴ ግጥሙ ሁሉ ይጠፋብሃል፡፡ ደግሞም ብዙ ጊዜ የወንዶቹ ቁጥር ከሴቶቹ ቁጥር ስለሚበልጥ ያንተ ተራ እስኪደርስ ብዙ መጠበቅ ይኖርብሃል፡፡ ከጅንኒ ጋር ስትጫወት ግን አንድም ችግር የለም፡፡ ጅንኒዋን እቅፍ አድርገህ ከወዲያ ወዲህ ስታወዛውዛት አየር ላይ የምትንሳፈፍ ነው የሚመስለህ፡፡ ደግሞ የጂንኒዋ ውበትስ? ከመላእክት ጋር መጫወት እኮ ነው ባክህ! ድምጿስ ቢሆን? እንደርሷ የሚያምር ድምጽ ያለው ፍጥረት ከየት ነው የሚገኘው?… አይ ጂንኒ! ተጫወትነው አቦ! በህይወቴ እንደዚያ ደስ ብሎኝ አያውቅም፡፡”
  
      አብዲ ሸጎዬ ብሎ የጠራው ጨዋታ የሀረርጌ ወጣቶችና ኮረዶች በጠራ ሌሊት የሚጫወቱት ባህላዊ ዳንኪራ ነው፡፡ ወጣቶቹ በቀን ስለማይፈቀድላቸው ነው በውድቅት ሌሊት (ቤተሰብ በእንቅልፍ ሲዘናጋ) ከቤት ጠፍተው ሸጎዬን የሚጫወቱት፡፡ ለጨዋታው የሚመረጠው ቦታ ከሰፈር ራቅ ያለ ነው፡፡ በተለይ ወጣቶቹ ሲዘፍኑ ድምጹ ወደ ሰፈር እንዳይሄድ ስለሚፈለግ የተራራ ግርጌ ወይንም ገደላማ ቦታ  ይመረጣል፡፡ የጨዋታው ጊዜም ጨረቃዋ አስረኛ ቀኗን ከደፈነች በኋላ ያሉት ቀናት ናቸው (ያኔ ሌሊቱ ደመቅ ይላልና)፡፡

አብዲ እንዳለው ወጣቶቹ እንዲህ በርከት ብለው ሸጎዬ ሲጫወቱ የጂንኒ ወጣቶችም ከነርሱ ጋር የመቀላቀል ልማድ አላቸው፡፡ በተለይ ጂንኒዎቹ በጨዋታው ላይ ከገቡ በጣም ስለሚመሰጡ እንደፈለግከው ልታደርጋቸው ትችላለህ፡፡ ያሻህንም ሊፈጽሙልህ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ጨዋታው ካለቀ በኋላ ተጠንቀቅ!! እነርሱን ወደቤታቸው እሸኛቸዋለሁ ብለህ እግርህን አታንሳ፡፡ እንዲያ ካደረግህ ጂንኒዋ ሰፈሯ ከደረሰች በኋላ በእጇ “ጠቅ” ታደርግህና ለዘላለሙ “ሽባ” ትሆናለህ፡፡ ወይ አፍህ በአንድ በኩል ይጣመማል፤ ወይ ሙሉ ሰውነትህ ፓራላይዝ ይሆናል… ወይ ደግሞ…ጂንኒ ጀቡቲ..ጂንኒ ጃንካ….ትሆናለህ፡፡

እድለኛ ከሆንክ ግን ታሪኩ ሌላ ነው የሚሆነው፡፡ ለምሳሌ ጂንኒዋ ከመመላለስ ብዛት ከወደደችህ የጋብቻ ጥያቄ ታቀርብልሃለች፡፡ ጂንኒ እዚህ ደረጃ ከደረሰች በእውነት አሸንፈሃታል ማለት ነው፡፡ ጂንኒ ስትወድህ ከልቧ ነው፡፡ በውሸት ሞቼልሃለሁና አግባኝ አትልህም፡፡ እንዲህ በለስ ቀንቶህ የምትወልደው ልጅ ምን እንደሚባል ታውቃለህ? “ኢፍሪት” የሚባል ልጅ ነው የሚወለደው፡፡ የሰው ቁመናና መልክ ያለው፤ ነገር ግን እናቱ ከሆነችው ከጂንኒዋ ባለቤትህ ልዩ ልዩ “ፓወር” የሚወርስ ልጅ… ጥበብ ትላለህ ገንዘብ፤ አስማት ትላለህ ፍልሰፋ የማይችለው ነገር የለም! አይ ኢፍሪት!! የጂንኒ ክልስ!
                *****  *****  *****
ከቢር አህመዴ የቅድመ- አያቴ ወንድም ናቸው፡፡ በልዩ ልዩ ችሎታ ጂንኒዎችን እያላመዱ እንደ ሰው ይገለገሉባቸው ነበር አሉ፡፡ ታዲያ የርሳቸው ጂንኒዎች “ሩሐኒ” በመሆናቸው ሰዎችን አይተናኮሉም፡፡ ከቢር አሕመዴ የተጣሉትን ሰው ግን አይምሩትም፡፡
  
  በአንድ ወቅት ከቢር አህመዴና ከቢር ዑመራ የተባሉት ወንድማቸው ተጣሉ፡፡ የከቢር አሕመዴ ጂንኒዎችም ለጌታቸው በማገዝ ከቢር ዑመራን ሊበቀሉላቸው ተነሱ፡፡ ከቢር ዑመራ በመስገጃ ቦታቸው ላይ እያሉ እንደ ፌንጣ ሆነው ከበቧቸው፡፡ ከዚያም እንደ ፌንጣ እየጮኹ ይረብሿቸው ጀመር፡፡ ከቢር ዑመራም “አዑዙቢላሂ” ብለው አንዱን ፌንጣ በተስቢ (ሙስበሐ) ቢመቱት እግሩን ስብር አደረጉት፡፡ በዚህን ጊዜ ሌሎቹ ፌንጣዎች ደንግጠው እየበረሩ ከአካባቢው ጠፉ፡፡ በእውነተኛ መልካቸው ወደ ከቢር አሕመዴ ሲመለሱ አደም የተባለው “ሩሐኒ” ጂንኒ እግሩ ተሰብሮ ተገኘ፡፡ ከቢሩ ነገሩን ቢጠይቋቸው ጂንኒዎቹ የተፈጠረውን ሁሉ አጫወቷቸው፡፡ ከቢር አሕመዴም ጂንኒዎቹ ያለፈቃዳቸው ዑመራን ሊረብሹ በመሄዳቸው በጣም ተቆጡ፡፡ አደምም አንካሳ እግሩን ታቅፎ ቀረ፡፡በሰፈሩም “አደም ኦኮላ” (አንካሳው አደም) እየተባለም ይጠራ ጀመር፡፡

   ይህ አደም ከከቢር አሕመዴ ሞት በኋላ ረጅም እድሜ ኖሯል፡፡ እኔም እርሱ ይገኝበታል የተባለውን ቦታ በተደጋጋሚ ጊዜ ጎብኝቼዋለሁ፡፡ አንድ ቀንማ አክስቴ (የአባቴ እህት) “ነጭ ለብሶ በዚህ በኩል ይመጣል” ስትለኝ ከቤቷ በታች ካለው የጂልቦ (አንጎራ) ዛፍ አጠገብ ቆሜ ስጠብቀው አደርኩ፡፡ ግን ላየው አልቻልኩም፡፡ ታዲያ አንድ ቀን ምሽት የኡኡታ ድምጽ ሰማሁ፡፡ በኦሮምኛ “Narraa baasaa” (አውጡኝ! አስጥሉኝ!) እያለች የምትጮህ የሴት ድምጽ ነበር፡፡
አክስቴን ማን ነው የሚጮኸው ብዬ ጠየቅኳት፡፡
   “ጂንኒ ናት፡፡ ጅብ እያባረራት ነው”
   “ከየት የመጣች ጂንኒ?”
   “እኔ እንጃ! አደም ሊሆን ይችላል”
    “አደም ወንድ አይደለም እንዴ?”
  “አይ! ጂንኒ ሁሉ ጅብ ሲመጣበት በሴት ድምጽ ነው የሚጮኸው”
   በጣም አዘንኩ፡፡ እኔ እርሱን ለማየት ስዋትት ከርሜ እርሱ በጅብ ለመበላት በመቃረቡ ተናደድኩ፡፡ የፈራሁት አልቀረም፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ “አደም በጅብ ተበላ” ተባለ፡፡ እኔን ይብላኝ!
                *****  *****  *****
እንቀጥል እንዴ? ብቀጥል ደስ ይለኛል፡፡ አንዳንድ ሰዎች ግን “እየፈራን ነውና አሳጥረው” ብለውኛል፡፡ ጂንኒዋ ሳትቆጣኝ እነርሱ መፍራታቸው ቢገርመኝም ፍላጎታቸውን ለመጠበቅ ስል በዚሁ ላበቃ ተገድጃለሁ፡፡
 
 ግን ግን…. አንድ የዋሸኋችሁ ነገር አለ፡፡ በትናንቱ መግቢያዬ ላይ “እንደኔ ከጂንኒ ጋር እየተጋፋችሁ መጻፍ የምትችሉ” እያልኩ ዘባርቄ ነበር አይደል? ውሸቴን ነው፡፡ ነጭ ውሸት! እኔ ነኝ እንዲህ ጽናት ኖሮኝ ስለጂንኒ የምጽፈው? አዲስ አበባ፣ ገለምሶ፣ ጭሮ ወይንም አዳማ ብሆን ኖሮ አንድ ገጽ እንኳ የምጽፍላችሁ አይመስለኝም፡፡ ሀረር ስላለሁ ነው ይህንን ሁሉ የተረተርኩት፡፡ “ልዩነቱ ምንድነው?” ካላችሁ የኔ መልስ “እዚህ ጂንኒ የለም” የሚል ይሆናል፡፡

 አዎን! ሀረር ጅብ ከሰው ጋር እየተጋፋና እየተላፋ የሚኖርባት ከተማ ናት፡፡ አያ ጅቦ ጂንኒዋን ከዚህች ከተማ ካባረራት ስንትና ስንት ዘመን ሆኖታል፡፡ ሀረሪዎች ዛሬ ጂንኒን የሚያውቁት በትዝታ ብቻ ነው፡፡ እኔም ድሮ እንጂ በዛሬው ዘመን ጂንኒን አይቻት አላውቅም፡፡
     ለማንኛውም ጂንኒዋ ብትኖርም ባትኖርም “አዑዙ ቢላሂ” እንበልና እናብቃ!
--------
አፈንዲ ሙተቂ
ነሐሴ 26/2006
ሀረር-ምስራቅ ኢትዮጵያ
--------

No comments:

Post a Comment