Thursday, September 12, 2013

==የአሕመዶ ቦቴ ጨዋታዎች==


ጸሓፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ
-----
እንደ መግቢያ….
አንዳንዴ ትገርሙኛላችሁ! በሁሉም እንቶ ፈንቶ እየሳቃችሁ እነ “እገሌ” እንዲጀነኑብን አደረጋችኋቸው! ምን አለ ረጋ ብትሉ?…ቴቪ ላይ የታየ ሁሉ ኮሜዲያን ነው ያላችሁ ማን ነው?
  እርግጥ ክበበው ገዳ ነፍስ ነው፡፡ ያ የሞተው ተስፋዬ ካሳም ነፍስ ነው፡፡ እንግዳዘርና አበበ በለውም ነፍስ ነበሩ፡፡ እንዲሁም ሟቾቹ የብሄራዊ ቴአትር ተዋኒያን ዓለሙ ገብረአብና ሲራክ ታደሰ ሲተውኑ በሳቅ ያንፈርፍራሉ፡፡ ከኦሮምኛ አክተሮች አድማሱ ብርሃኑ (ብዙ ጊዜ ሽማግሌ ሆኖ የሚሰራው) ወደር የለውም፡፡ ሌላው ግን “ኮርጆ” ነው፡፡ አስቃለሁ ብሎ ጨጓራ ያበግናል፡፡

ኮሚክ ከፈለጋችሁስ እነ “ቦቴ” አሉላችሁ!…. ጥርስ የማያስከድኑ የህይወት ቅመሞች…. ለጨዋታ የተፈጠሩ የጨዋታ አባቶች፡፡ እስቲ ከቦቴ ጨዋታዎች ትንሽ ልጨልፍላችሁ፡፡
---
  እኔ፣ “ቦቴ”፣ ሙሐመድ ነጃሽ እና ኢስሐቅ ዓሊ ባልንጀራሞች ነን፡፡ በእድሜ ብንበላለጥም የእህል ውሃ ነገር ጓደኛሞች አድርጎናል (ደግሞም አባቶቻችን ጓደኛሞች በመሆናቸው ፍቅራቸውን ወደኛ አስተላልፈዋል)፡፡ ታዲያ አራታችንም በአንዱ የረመዳን ምሽት ቦሌ በሚገኘው የመሐመድ ነጃሽ ቤት ተሰባስበናል፡፡ ከትንሽ ጊዜ በኋላም አንድ “ጥቁር እንግዳ” የኛን ጀመዓ ተቀላቀለ፡፡ ከመሐመድ ነጃሽ በስተቀር ሌሎቻችን አናውቀውም፡፡
   ሰውዬው እኛ የማንፈልገውን የፖለቲካ ወሬ መቅደድ ጀመረ፡፡ ለጥቂት ጊዜ በትዕግስት አደመጥነው፡፡ እያደርን ግን “ሰውየው ተልኮብን ይሆን?” እያልን ተጠራጠርን፡፡ ሆኖም በድፍረት የሚናገረው ጠፋ፡፡ ከቆይታ በኋላ ግን “ቦቴ” አንድ ብልሃት ታየው፡፡ እናም እንዲህ አለ፡፡
   “መሐመድ ነጃሽ፤ እንግዳህን አደብ አስይዘው፡፡ እኔ ቤት ውስጥ እንዲህ አይነት ወሬ እንዲያወራ አልፈቅድለትም፡፡ እምቢ ካለ ግን ያንተ ቤት ሄዳችሁ የፈለጋችሁትን ቅደዱ፡፡”
  በዚህም ቤቱ የቦቴ ሆነ፡፡ እኛም ልክ እንደ ቦቴ ቤት ማስመሰሉን ተያያዝነው፡፡ በተለይ ቦቴ “ይህንን ቤት ስሰራ እኮ በራሴ አንጡራ ሀብት ነው፡፡ የማንም ስሙኒ አልተቀላቀበትም፡፡ ለልጆቼ የማወርሰው ቅርስ ይህ ነው…ወዘተ..” በሚሉ ቃላቶች “አክት” እያደረገ ያስፈግገን ገባ፡፡ ሙሐመድ ነጃሽ ግን ድራማውን እያበላሸ አስቸገረን፡፡ ስልክ ሲደወል “እባክህ ያንን ስልክ አንሳው!” በማለት ትእዛዝ ይሰጣል፡፡ የቤት ሰራተኛውንም “እገሌ! ሻይ አፍይልን” ይላታል፡፡ በአይን ብንጠቅሰው አልገባው አለ፡፡ ይባስ ብሎ ደግሞ ግድግዳ ላይ የሚሄድ በረሮ በመጽሐፍ መትቶ ሊገድል ተነሳ፡፡ በዚህን ጊዜ ቦቴ አላስችልህ አለው፡፡ እናም በስጨት ብሎ እንዲህ አለ፡፡
   “አንተ መሐመድ! የኔን በረሮ ማን ግደልብኝ አለህ? ያንተ ቤት ሂድና የራስህን በረሮ ግደል እንጂ የኔን አትንካብኝ”፡፡
    በሳቅ የታፈንነው ሶስታችንም ቤቱን አበራየነው፡፡
 -----
አንዱ “ሀጂ ቅደደው” ቦቴ ባለበት ቦታ ቀደዳ ጀመረ፡፡ እንደፈለገው ቀደዳውን ለቀቀው፡፡ ቦቴ ዝም ብሎ ሰማው፡፡ በኋላ ሐጂው “ዱባይ ሄጂ፣ ባህሩን ዋኝቼ፣ በወደቡ ተጫውቼ ምናምን” ሲል ቦቴ “አኸ! አል-ፈላህ ሬስቶራንት ፊት ለፊት ያየሁት ለካስ አንተን ነው?” አለው፡፡ ይህንን የሰማው በቤቱ የነበረው ጀመዓ በሳቅ ሀገሩን አደበላለቀው፡፡
-----
የቦቴ ወንድም በአዲስ አበባ አንድ ቤት ሰርቷል፡፡ ነገር ግን “ቤቱ ህገወጥ ግንባታ ነው” ተብሎ በክፍለ ከተማው ሀላፊዎች ተከሰሰ፡፡ ቦቴ የክሱ ቦታ ወንድሙን ወክሎ ሄደ፡፡ እናም የግንባታ ሃላፊዎች “ይፈርሳል” አሉት፡፡
  “ለምንድነው የሚፈርሰው?”
“ጨረቃ ቤት ስለሆነ ነው”
 “አንተ ነህ ጨረቃ ያደረግከው? ኮከብ ነው የወንድሜ ቤት!”
-----
 ይህኛው ከጥቂት ሳምንታት በፊት የተከሰተ ነው፡፡ ከቦቴ ጋር ተገናኘንና ጨዋታ ጀመርን፡፡ በተለይ እኔና ጓደኛዬ ዘንድሮ የሞተውን አንድ በአራጣ ብድር ሀገር ያስመረረ ቱባ ነጋዴ ሀዘንን በማስመልከት በለከፋ አጣደፍነው፡፡ “ቦቴ ለቅሶ ደርሷል ሲሉ ሰምተናል፡፡ እውነት ነው? እውነት ከሆነ አንተም እንደርሱ የህዝብ ጠላት ነህ” አልነው፡፡
  “እውነት ነው፤ ሄጃለሁ” አለ ቦቴ፡፡
   “ለምን ሄድክ?” በማለት ወጠርነው፡፡ በዚህን ጊዜ ነው ቦቴ እጅግ አስደናቂና አስቂኝ የሆነ ታሪክ ያጫወተን፡፡ እንዲህ ልጻፍላችሁ፡፡
   -----
ድሮ ነበር ፤ በ1966 መጨረሻ ገደማ፡፡ ዒስማኢል አህመዩ፣ ሙሐመድ በከር (የቦቴ አባት)፣ ሙተቂ ሼክ ሙሐመድ (የአፈንዲ አባት) እና ነጃሽ ዒስማኢል (የመሐመድ ነጃሽ አባት) በፖለቲካ ተከሰው በሀረር ከተማ በአንድ ክፍል ታስረዋል፡፡ ከሁለት ቀናት በኋላ  እንደነርሱ በፖለቲካ የተጠረጠረ መገርሳ የሚባል ሰው ተጨመረባቸው፡፡
መገርሳ ለአራቱ ታሳሪዎች ራሱን አስተዋወቀ፡፡ እናም “የየት ሀገር ሰዎች ናችሁ?” አላቸው
 “ገለምሶ”
  “ገለምሶ ከተማ?”
  “አዎን”
  “ታደሰ የሚባለው የፖሊስ አዛዥ አለ?”
  በዚህን ጊዜ ሶስቱ ታሳሪዎች ለመናገር ፈሩ፡፡ ዒስማኢል አህመዩ ግን የፈለገው ይምጣ ብሎ ለመናገር ቆረጠ፡፡
  “ሞቷል ወዳጄ!”
   “እውነት ሞቷል?”
    “አዎን ሞቷል”
   “መቼ ነው የሞተው?”
   “አሁን በቅርቡ ነው የሞተው”

መገርሳ እየየውን አቀለጠው፡፡ “ኡኡኡ” እያለ ያለቃቅስ ገባ፡፡ አራቱ ታሳሪዎች ተረበሹ፡፡ የሚያደርጉት ጠፋቸው፡፡ በዚህም ምክንያት ሙሐመድ በከር ዒስማኢልን ተቆጣው፡፡ “አንተን መርዶ ነጋሪ ማን አደረገህ? ዘመዱ ከሆነስ ብለህ አትጠረጥርም ነበር?… ይኸው አስለቀስከው.. እንግዲህ እንዳስለቀስከው አንተው ራስህ አፉን አስይዘው” አለው፡፡

መገርሳ ለቅሶውን ቀጠለበት፡፡ “ታዴ ኮ! ወይ ታዴ ኮ” እያለ አለቃቀሰ፡፡ ዒስማኢል ተጨነቀ፡፡ ከመቅጽበት ግን የመገርሳ ቅላጼና የሚወረውራቸው ቃላት በተቃራኒው መሄድ ጀመሩ፡፡ እናም በኦሮምኛ እንዲህ አለ፡፡
  “Yaa Waaqa ofumaaf uumtee ofumam ajjeesta! Maalo maaloo maaloo! Ajeechaa nuti yoo sigargaarree maaluma qaba. Kan akka Taaddasaa kana nuutuu ni nigeenyaafi bari. Yaa Waaqa Maaloo Maloo…..”
ትርጉሙ እንዲህ ይሆናል
    “አዬ ጌታዬ! አንተው ራስህ ፈጥረህ አንተው ራስህ ትገድላለህ! በመግደሉ ላይ እኛ ብናግዝህ ምን አለበት? ለታደሰ ዓይነቱ እኛ ራሳችን እኮ እንበቃዋለን እኮ፡፡ አይ ፈጣሪ! ታደሰን ስትገድለው ብትጠራኝ ምን አለበት?”
  
 መገርሳ እንዲያ እያለ ለቅሶውን ቀጠለበት፡፡ አራቱ ሰዎች ይህንን ሲሰሙ በጣም ተገረሙና ተያዩ፡፡ እናም ሙሐመድ በከር ለዒስማኢል አህመዩ እንዲህ አለው፡፡
  “እንኳንም ነገርከው! ይህንን የመሰለ ወሬ ልትደብቀው ነበር?.. እንኳንም ነገርከው! አበጀህ! እንኳን ነገርከው!…”
ለካስ ታደሰ አገር ያቃጠለ የፖሊስ መቶ አለቃ ነበር? መገርሳም ያለጥፋቱ ከእስር ቤት ወደ እስር ቤት ሲንከራተት የነበረው መቶ አለቃ ታደሰ በከፈተበት ሀሰተኛ ክስ ሳቢያ ነው፡፡

ቦቴ ይህንን ታሪክ ካጫወተን በኋላ እንዲህ አለ፡፡
  “ለቅሶ የሚሄደው ሁሉ ለሟቹ የሚያለቅስ መሰላችሁ?… እንደ መገርሳ የምስጋና ለቅሶ የሚያለቅስም ሞልቷል እኮ! ለናንተም ለቅሶአችሁን የደስታ ያድርግላችሁ”
-----
እንደ ማሳረጊያ…

  “ቦቴ” በትክክለኛ ስሙ አህመድ ሙሐመድ በከር ነው፡፡ እርሱ ባለበት ቦታ ጨዋታ አይጠፋም፡፡ ሲቀመጥም ሆነ ሲሄድ ሰውን ማሳቅ ይችልበታል፡፡ እናንተ ተጠባችሁ የፈጠራችሁትን ጆክ ለርሱ ብትሰጡት የሳቅ ጎርፍ እንዲያፈልቅ አድርጎት ይቀምመዋል፡፡ ድሮ በህጻንነታችን የሰማናቸው ተረቶች በርሱ አንደበት በመነገራቸው ብቻ ሰውን በሳቅ ሲያፈነዱት አይቼ  “ይህስ የፈጣሪ ጸጋ ነው” እያልኩ ተገርሜአለሁ፡፡

ታዲያ አንዳንዴ እርሱን ራሱ በቅጽል ስሙ መጥራት ሳቅ የሚፈጥር ትዕይንት ሆኖ ይገኛል፡፡ በተለይ ብዙ ሽማግሌዎች “ቦቴ” እላለሁ ይሉና “ቮልቮ” ይሉታል፡፡ አንዳንዶቹ “ጎማ” ሲሉት ያጋጥማሉ፡፡ አንዳንዶቹ ጭራሽ “ቱርቦ” ይሉታል፡፡
  በርግጥም “ቦቴ” ሁሉንም ነው፡፡ የማያልቅበት የሳቅ “ቦቴ”፣ የሳቅ “ቮልቮ”፣ የሳቅ “ጎማ”፣ የሳቅ “ቱርቦ” ወዘተ…ጂንኒ ጀቡቲ….ምናምን…
------ 
አፈንዲ ሙተቂ
መስከረም 2/2006
     

No comments:

Post a Comment