Tuesday, September 3, 2013

==የእብድ ወሬዎች==




ጸሓፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ
-----------
ብዙ እብዶች አሉን አይደል? እስቲ ለዛሬ ደግሞ ከእብዶቻችን መንደር ያገኘኋቸውን አስደሳች ወሬዎች በጥቂቱ ጀባ ልበላችሁ::
------
ሼኽ ሙሐመድ ሻንቆ ሀይለኛ ቃሚ ነበር፡፡ ጫት በወስላ (መቶ ኪሎ የሚይዝ ዝርግ ኬሻ) ቢቀርብለት እንኳ እጨርሰዋለሁ ባይ ነበር፡፡ አንድ ቀን ሐዘን ቤት ሳለን ሼኽ ሙሐመድ ሽንቱን በድንኳኑ ውስጥ ለቀቀው፡፡ ሰው ደነገጠና “ሼኸ መሀመድ ምን ሆንክ” ቢለው
 
 “ሰዓት የለንም እኮ፤ አንዱ ሰዓት የሰለዋት ነው፤ አንዱ የመቃሚያ ነው፤ ታዲያ ጊዜ ከየት አግኝተን ነው ውጪ ወጥተን የምንጸዳዳው?”
------
“ሹቡሹብ” በጣም ቀብራራ ነው፡፡ የሰውነቱ ንጽህናና የልብሱ ጽዳት ሌላ ነው፡፡ አይኑን እንደ ሴት ይኳላል፡፡ በእጁ በርከት ያሉ አበባዎች፣ ቄጤማ፣ ጠጅ ሳር፣ ልዩ ልዩ ባለመዓዛ ቅጠሎች ወዘተ… ይዞ ነው የሚዞረው፡፡ በዚህም የተነሳ አዲስ ሰው እብድ መሆኑን ለማወቅ ይቸግረዋል፡፡

ታዲያ “ሹቡሹብ” ጉራው አይጣል ነው፡፡ በተለይ ጉራውን የሚያሳየው ግን ወደ ማክሰኞ ገበያ በሚመጡ ሴቶች ላይ ነው፡፡ አቤት ሲሰድባቸው! ደግነቱ “እናትሽን…ቅብጥርሴ…ጂንኒ ጀቡቲ” የመሳሰሉ መጥፎ ስድቦችን አይደለም የሚሳደበው ፡፡ የሴቲቱን ንጽህናና ስንፍና ነው በሚገባት ቋንቋ የሚነግራት (ሴቲቱን ቢያውቃት ባያውቃት ጉዳዩ አይደለም)፡፡ አንድ ቀን የገዛ አክስቴን እንዲህ ብሎአት እንደነበር አስታውሳለሁ!
Yaa bada ta buusaa sooggida hinqabne nyaattu (ይህች ጨው የሌለው ወጥ የምትበላ)
Yaa bada ta kurumbaa ajaawaa nyaattu  (ይህቺ የገማ ጥቅል ጎመን የምትበላ)
Yaa bada ta faxiiraa killee hinqabne nyaattu (ይህቺ እንቁላል የሌለው ፈጢራ የምትበላ)

 “ሹቡሹብ” ለከተማ ሴቶችና ከገጠር ለሚመጡ ሴቶች የሚወረውራቸው ስድቦች ይለያያሉ፡፡ ለከተማ ሴቶች የሚወረውራቸው ብዙም ሀይለ ቃል የለባቸውም፡፡ ከገጠር በሚመጡት ላይ ግን ይጨክናል፡፡ ለምሳሌ ከገጠር የሚመጡትን በግጥም ዘይቤ እንዲህ ብሎ ይሰድባቸው ነበር፡፡

Hin hinnattu (በሂና አትዋብ)
Hin hallattu (አትነቀስ)
Hin qayyattu (“ቀያ” አታድርግ”፤ እንዲህ ሲል የሀረርጌ ሴቶች  መጥፎ ጠረን እንዳይኖራቸው በልዩ ልዩ መዓዛማ ጭሳጭስ ሰውነታቸውን የሚያጥኑበትን ባህላዊ ድርጊት መግለጹ ነው፡፡ በአማርኛ ምን ይባላል? እስቲ ንገሩን?)
Hin dhiqattu (አትታጠብ)
Hin miiccattu (ልብሶቿን አታጥብ)
Hin kuullattu (አይኗን አትኳል)
Dhadhaa matarra hin kaayyattu (በቅቤ ጸጉሯን አታርስ)

   ሹብሹብ እንዲህ ብሎ ሲሳደብ መላው ገበያተኛ በሳቅና በሆይታ ነው የሚያጅበው፡፡ አዳዲስ ሴቶች ግን የሰውዬው ንጽህና ስለሚያደናግራቸው ፍዝዝ ብለው ነው የሚያዩት፡፡

ሹብሹብ አንድ ጊዜ “አሪፍ” ቢዝነስ ጀምሮ ነበር፡፡ ከምሽቱ ሶስት ሰዓት ገደማ በከተማው ጎዳና ላይ የሚመላለሱ በጎችና ፍየሎችን ይይዛቸውና “Namni Hoolaan irraa bade! Namni re’een irraa bade” (በግ የጠፋው! ፍየል የጠፋው) እያለ ይለፍፋል፡፡ የፍየሎቹ/በጎቹ ባለቤቶች ሲመጡ “Afaan waraabeessa fidi” ይላቸዋል፡፡ “ከጅብ ያስተረፍኩበትን ዋጋ አምጣ” ማለቱ ነው፡፡ የፍየሎቹ/በጎቹ ባለቤቶችም “ምን ገዶኝ! እንካ ይኸው” ይሉና ሽልንግ ወይም ብር ይሰጡታል፡፡

ታዲያ ሹብሹብ ቢዝነሱ በጣም ስለጣመው ብሩ በርከት እንዲልለት ፈለገ፡፡ በመሆኑም በጸሐይ መግቢያ ገደማ ብዙ በጎችን/ፍየሎችን እያባረረ ከሰው አይን በመሰወር በሶስት ሰዓት ገደማ ወደ ዋናው መንገድ እያወጣቸው “በግ የጠፋበት! ፍየል የጠፋው” እያለ መለፈፍ ያዘ፡፡ በዚህም ብዙ ብር ማግኘት ጀመረ፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ግን ነገሩ ተነቃበት፡፡ የከተማው ሰዎች ፍየሎቻቸውን/በጎቻቸውን ከጅብ ማስተረፋቸው ቀረና ትግሎ ከሹብሹብ ጋር ሆነ፡፡ በተለይ ብዙ ፍየሉችና በጎች የመበራቸው ከተሜዎች ለሹብሹብ ብር መገበሩ አንገሸገሻቸው፡፡ ሹብሹብን ራሱን እንደ ጅብ ፈሩት፡፡ በዚህም የተነሳ በርካታ ቤተሰቦች ልጆቻቸውን “ፍየላችንን ጅብ እንዳይበላው ቶሎ አስገባው” ማለታቸው ቀርቶ “ፍየላችንን ሹብሹብ ሳይይዝብን ቶሎ አስገባው” ማለት ጀመሩ፡፡
 
 “ሹብሹብ”ም በዚህ መንገድ ከዚያ ጣፋጭ ቢዝነስ ጋር ተቆራረጠ፡፡ እስከ እኩለ ሌሊት ፍየሎቻቸውን ከመንገድ ላይ ማስገባት የማያውቁ በርካታ ሰዎች ለሹብሹብ የሚከፍሉትን ብር ለመሸሽ ሲሉ ጸባያቸውን አስተካከሉ፡፡ የቤት እንስሳትን በጊዜ ከመንገድ ላይ ማስገባትም ተለመደ፡፡
-------
ለዛሬ በዚህ ይብቃኝ፡፡ ቀሪውን በሚቀጥለው ክፍል እለጥፈዋለሁ፡፡ ታዲያ እናንተም የምታውቁትን ማዋጣቱን እንዳትረሱ፡፡
በወዳጅነታችን እንሰንብት፡፡
አፈንዲ ሙተቂ

Monday, September 2, 2013

==“የጂንኒ” ወግ (ክፍል ሁለት)==



ጸሓፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ                                        
ክፍል ሁለት
-----------
ይህ ክፍል ሁለት የጂንኒ ወጋችን ነው፡፡ “አዑዙ ቢላሂ” ብለን ጀምረናል፡፡ ወደ ዋናው ወግ ከመግባታችን በፊት ግን አንድ ልጅ “እኛ እኮ ቢልቂሳ ነው የምንላት” ያለኝ ነገር ሆዴን እንደከነከነው ላወሳ እፈልጋለሁ፡፡

 የልጁ ዳር ዳርታ ገብቶኛል፡፡ “ጂንኒ ስሟን እንዲያነሷት ስለማትፈለግ በኮድ ብትጠቀም ይሻል” ማለቱ ይመስለኛል፡፡ እውነቱን ነው፡፡ ጂንኒ ስሟን ደጋግሞ የሚያነሳትን አትፈልግም፡፡ ድሮ ስለርሷ መነጋገር ስንፈልግ “ጀመዓታ” (ጀመዓዎቹ)፣ “ዋን አላ” (የውጪ ሰዎች)፣ “ጀረ” (ሰዎቹ) እያልን ነበር የምንጠራት፡፡ ሆኖም “ጂንኒ” ብንላትም እኛ ቦታዋ ድረስ ሄደን እስካልተተናኮልናት ድረስ ምንም አትለንም፡፡ እርሷም እኛን በተፈጥሮ ስማችን “ኢንሲ” (ሰዎች) እያለች ነው የምትጠራን፡፡ ከሰፈሯ አጠገብ ቆመን “ጂንኒ” ብንላት ግን “የማንነው ጭልፋ ፊት! ቤቴ ድረስ መጥቶ ነው እንዴ በነጠላ ቃል የሚጠራኝ” ብላ በጥፊ ዋጋችንን ትሰጠናለች፡፡ ስለዚህ እዚያ ስንሄድ ወዳጃችን እንዳለው “ቢልቂሳ” ወይንም ሌላ “ኮድ” መጠቀሙን አንርሳ፡፡ አሁን ግን “ጂንኒ” እያልን እንቀጥል፡፡

በነገራችን ላይ ከጂንኒዎቹ ውስጥ ደግ አድራጊዎችም እንዳሉ ጽፌላችሁም ነበር አይደል? እነዚያ ደጋግ ጂንኒዎች ምን የሚባሉ ይመስላችኋል?  “ሩሐኒይ” ተብለው ነው የሚጠሩት፡፡ “ሩሐኒይ” ከሆኑ ጂንኒዎች መካከል አንዳንዶቹ ጿሚዎችና ሰጋጆችም ናቸው፡፡
-----------
አንዳንድ ጂንኒዎች ቅቤ ይበላሉ ብያችሁ ነበር፡፡ አዎን በደንብ ይበላሉ! ታዲያ እነዚህኛዎቹ ጂንኒዎች ቅቤውን የሚያገኙት ከራሳቸው ከብት ሳይሆን ከየሰው ጓዳ እየሰረቁ ነው፡፡ አንዲት ጂንኒ ለቅቤ ስርቆት የምትሰማራው በአንድ እጇ “ቡቄ” የምትባል ትንሽ የቅቤ ቅል በመያዝ ነው፡፡ ቅቤውን ከሰው ጓዳ ገብታ ከሞጨለፈች በኋላ የቤቱ ባለቤቶች እንዳይነቁባት ውሃ፣ እጓት፣ አመድ፣ ወዘተ… ትጨምርበትና ፊት እንደነበረው መልሳ ትከድነዋለች፡፡ የቤቱ ሰዎች ሲመጡ ቅቤው መበከሉ ስለማይታወቃቸው እንደ እውነተኛ ቅቤ መጠቀማቸውን ይቀጥላሉ፡፡

 ጂንኒ በዚህ ምድር ላይ የምትፈራው ነገር የላትም፡፡ ከአንድ እንስሳ በስተቀር ሌሎቹን እንስሳት እንደፈለገችው ታንበረክካቸዋለች፡፡ ጂንኒ የማትችለው የትኛውን እንስሳ እንደሆነ ታውቃላችሁ? ጅብ ነው፡፡ በየሰፈሩ የሚልከሰከሰውና የሚቀላውጠው አያ ጅቦ ቀላል እንዳይመስላችሁ! ጂንኒን ድባቅ  የሚመታውና ድራሿን የሚያጠፋት እርሱ ብቻ ነው፡፡ በተለይ አያ ጅቦ ለስርቆት የምትሰማራውን ጂንኒ አይምራትም፡፡ እንደፈቀደው እየዘነጣጠለ ነው የሚያወራርዳት፡፡
  
ጂንኒዋ ጅብ በሚገጥማት ጊዜ ጅብዬው ሳያያት ከአካባቢው መሰወር ከቻለች በደህና አመለጠች ማለት ነው፡፡ ጅቡ ካያት ግን አይለቃትም፡፡ የገባችበት ገብቶ ለቀም ያደርጋትና እንክትክቷን ያወጣታል፡፡ ከዚያም እንደ ብሩንዶ እያጣጣመ ይበላታል፡፡ ሆኖም በርሱ የተበላው የጂንኒ ገላ በሆዱ ስለማያድር ወዲያው ያስታውከዋል፡፡ ጧት ጅቡ ጂንኒዋን ከበላበት ቦታ ብትሄዱ በትውከት የወጣውን ሁሉ እዚያው ታገኙታላችሁ፡፡ ነጭና ለስላሳ ጸጉር (ወደ ብርድ ልብስ የሚያደላ)፣ ጥቁር ከሰል የመሰለ ነጫጭባ! የተሰባበረ ቅል..ምናምን የተቀላቀለበት ጂንኒ ጀቡቲ…
   
ግን ጅብ ጂንኒን ሊበላት ሲያባርራት አይታችሁ ወይም ሰምታችሁ ታውቃላችሁ? አቤት ስታሳዝን! ዋ አንጀት ስትበላ!  የአስማትና የመተት ሀይሏ ሁሉ ነው የሚጠፋባት፡፡ አካሏን ወደ ሰውም ሆነ ወደ ዛፍ መቀየር አትችልም፡፡ ያላት ምርጫ “ኡ..ኡ..ኡ.. ኡ… አውጡኝ” እያለች የሰዎችን እርዳታ መማጸን ነው፡፡ በአካባቢው ሰዎች ካሉ ስርቅርቅ ድምጿ ያሳዝናቸውና ከጅቡ ያስጥሏታል፡፡ ጂንኒዋም ለውለታቸው እንዲሆን ከወርቅ የተሰራ ባለ ሉል ቀለበቷን አውልቃ ትሰጣቸዋለች፡፡ አልማዝና እንቁ ልትጨምርላቸውም ተስፋ ትሰጣቸዋለች፡፡ በማግስቱ ጣታቸውን ሲያዩት ግን ቀለበቱ የለም፡፡ “ማን ወሰደው?” ቢሉ ጂንኒዋ!

 እንዲህ አይነት ጂንኒ ካጋጠመቻችሁ ጅቡ ርቆ ሳይሄድ ቀለበቷን ላትወስደው መሀላ ማስገባት አለባችሁ፡፡ ጂንኒዋ መሀላ ከገባች ቀለበቱን በጭራሽ አትወስደውም፡፡ ጂንኒ መሀላ በማክበር ከሰው ልጅ በጣም ትበልጣለች፡፡ ደግሞ ቀለበቷ ተራ ወርቅ እንዳይመስላችሁ! ወርቁ በቀንም ሆነ በሌሊት ያበራል፡፡

የጂንኒ ዋናው መዳኛዋ ግን ይህ አይደለም፡፡ በዋነኛነት በደህና ጊዜ ከምስጥ ጋር የተዋዋለችውን ውል በመጠቀም ነው አያ ጅቦ ከሚያደርስባት አደጋ ለማምለጥ የምትሞክረው፡፡ እስቲ ምስጥ የሚሰራውን ኩይሳ ተመልከቱ! በርግጥ በርሱ ችሎታ ብቻ ነው የተሰራው? አይደለም ወዳጆቼ! የጂንኒ እጅ አለበት፡፡ ምስጥ አፈሩን እየፈረፈረና እንደማስቲካ እያቦካ አንዱን ቅንጣት በአንዱ ላይ የማነባበር ትልቅ ችሎታ አለው፡፡ በዚህ በኩል ማንም አይደርስበትም፡፡ ግን አፈሩን የሚያርስበትን ውሃ ከየት ነው የሚያመጣው? ከመሬት ውስጥ እያወጣ ይመስላችኋል? እንዲያ አይደለም፡፡ ውሃውን የምታቀርብለት ጂንኒ ናት፡፡ በየቀኑ በብዙ መቶ በርሜሎች የሚቆጠር ውሃ ነው የሚቀርብለት፡፡ የጂንኒዎች አንዱና ትልቁ ስራም ምስጥን ማገዝ ነው፡፡ ምስጡ የኩይሳው ርዝመት ይበቃኛል ብሎ ግንባታውን እስካላቆመ ድረስ ጂንኒ ውሃውን ያለምንም ማንገራገር ትቀዳለታለች፡፡ የጂንኒ ልጆችም በዚህ ላይ ያግዟታል፡፡
 
 ይህ ኩይሳው በምስጥ የተገነባ ቢሆንም ጂንኒም በሚገባ ትጠቀምበታለች፡፡ ጅብ ሊበላት የሚያሳድዳት ማንኛዋም ጂንኒ በአቅራቢያዋ “ኩይሳ” ካገኘች ከአደጋው አመለጠች ማለት ነው፡፡ አያ ጅቦ ሊደፍረው የማይችለው ብቸኛው ምሽግ የምስጥ ኩይሳ ነው፡፡ ጅቡ ሊበላት ሲንደረደርባት ጂንኒዋ ወደ ኩይሳው ጥልቅ! ከዚያ ውስጥ ሆና “አያ ጅቦ ስጋዬ እንዳማረህ ይቅር” እያለች ትዘንጥበታለች፡፡ ሞኙ አያ ጅቦ ጂንኒዋ ተዘናግታ የምትወጣ ስለሚመስለው እዚያው ኩይሳ ስር ያድራታል! ግን ልፋቱ ከንቱ ነው፡፡

   አዎን! የምስጥ ኩይሳ ለጅንኒ ህይወት መቀጠል ትልቁን ሚና ተጫውቷል፡፡ ጂንኒ በኩይሳው ለመጠቀም ከምስጥ ጋር የተዋዋለችው ጥንት ነበር አሉ (ያንን ዘመን ካሌንደር አያውቀውም)፡፡ ይኸው ሁለቱም በኩይሳው እየተጠቀሙ እዚህ ደርሰዋል፡፡ በጋራ መስራት ለግንባታ ብቻ ሳይሆን ለአደጋ ጊዜም ፋይዳ አለው፡፡ በነገራችን ላይ በጋራ የመስራትን ጥበብ የፈለሰፉት ጂንኒ እና ምስጥ መሆናቸውን ታውቃላችሁ? እኛ ከታሪካችን የሰማነው እርሱን ነው፡፡ ሌላው “ተረት” ነው፡፡
                *****  *****  *****
   አንዳንድ ሰዎች “ጅንኒዎች ፍቅር ናቸው” ይላሉ፡፡ “አንተ ግልጽና ንጹህ ሆነህ ከቀረብካቸው እንደፈቀድከው ይሆኑልሃል፤ ልጃቸውን ለጋብቻ ከጠየቅክ ቆንጆ የሆነችውን መርጠው ይሰጡሀል፤ በችግር በተወጠርክ ጊዜም ቶሎ ይደርሱልሃል፤ በጨዋታ ጊዜም እንደፈለግከው ያጫውቱሃል፤ ጅንኒ ቁልቋል..ጅንኒ ጀቡቲ..ጂንኒ ጃንካ…
  እስቲ አንድ ሁለቱን ላጫውታችሁ፡፡ ራሴ ያየሁትንና የሰማሁትንም እጨምርበታለሁ (ማመን አለማመን መብታችሁ ነው… )፡፡
 
    “አብዲ ፈረስሌ” ይባላል፡፡ በአንድ ከተማ በጉርብትና አብረን እንኖር ነበር፡፡ አብዲ ወደ ገለምሶ የመጣው ከጎለመሰ በኋላ ነው፡፡ ልደቱና እድገቱ በምስራቅ ሀረርጌዋ የሀረማያ ከተማ ነው፡፡ አንድ ቀን ታናሽ ወንድሜ አብዲ ስለ ጂንኒ ትዝታዎቹ ያጫወተውን ነገረኝ፡፡ እኔም ታሪኩ ደስ ስላለኝ በሳምንቱ አብዲ እንዲደግመኝ ጠየቅኩት፡፡

  “አዎን! እዚያው ሀረማያ ነው፡፡ ከጂንኒ ጋር የተጫወትነውን ሸጎዬ መቼም ቢሆን አልረሳውም፡፡ ሸጎዬ ከሰው ጋር ስትጫወት እኮ  ለጨዋታው ያለህ ስሜት ቶሎ አይነቃቃም፡፡ አንዳንዴ ግጥሙ ሁሉ ይጠፋብሃል፡፡ ደግሞም ብዙ ጊዜ የወንዶቹ ቁጥር ከሴቶቹ ቁጥር ስለሚበልጥ ያንተ ተራ እስኪደርስ ብዙ መጠበቅ ይኖርብሃል፡፡ ከጅንኒ ጋር ስትጫወት ግን አንድም ችግር የለም፡፡ ጅንኒዋን እቅፍ አድርገህ ከወዲያ ወዲህ ስታወዛውዛት አየር ላይ የምትንሳፈፍ ነው የሚመስለህ፡፡ ደግሞ የጂንኒዋ ውበትስ? ከመላእክት ጋር መጫወት እኮ ነው ባክህ! ድምጿስ ቢሆን? እንደርሷ የሚያምር ድምጽ ያለው ፍጥረት ከየት ነው የሚገኘው?… አይ ጂንኒ! ተጫወትነው አቦ! በህይወቴ እንደዚያ ደስ ብሎኝ አያውቅም፡፡”
  
      አብዲ ሸጎዬ ብሎ የጠራው ጨዋታ የሀረርጌ ወጣቶችና ኮረዶች በጠራ ሌሊት የሚጫወቱት ባህላዊ ዳንኪራ ነው፡፡ ወጣቶቹ በቀን ስለማይፈቀድላቸው ነው በውድቅት ሌሊት (ቤተሰብ በእንቅልፍ ሲዘናጋ) ከቤት ጠፍተው ሸጎዬን የሚጫወቱት፡፡ ለጨዋታው የሚመረጠው ቦታ ከሰፈር ራቅ ያለ ነው፡፡ በተለይ ወጣቶቹ ሲዘፍኑ ድምጹ ወደ ሰፈር እንዳይሄድ ስለሚፈለግ የተራራ ግርጌ ወይንም ገደላማ ቦታ  ይመረጣል፡፡ የጨዋታው ጊዜም ጨረቃዋ አስረኛ ቀኗን ከደፈነች በኋላ ያሉት ቀናት ናቸው (ያኔ ሌሊቱ ደመቅ ይላልና)፡፡

አብዲ እንዳለው ወጣቶቹ እንዲህ በርከት ብለው ሸጎዬ ሲጫወቱ የጂንኒ ወጣቶችም ከነርሱ ጋር የመቀላቀል ልማድ አላቸው፡፡ በተለይ ጂንኒዎቹ በጨዋታው ላይ ከገቡ በጣም ስለሚመሰጡ እንደፈለግከው ልታደርጋቸው ትችላለህ፡፡ ያሻህንም ሊፈጽሙልህ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ጨዋታው ካለቀ በኋላ ተጠንቀቅ!! እነርሱን ወደቤታቸው እሸኛቸዋለሁ ብለህ እግርህን አታንሳ፡፡ እንዲያ ካደረግህ ጂንኒዋ ሰፈሯ ከደረሰች በኋላ በእጇ “ጠቅ” ታደርግህና ለዘላለሙ “ሽባ” ትሆናለህ፡፡ ወይ አፍህ በአንድ በኩል ይጣመማል፤ ወይ ሙሉ ሰውነትህ ፓራላይዝ ይሆናል… ወይ ደግሞ…ጂንኒ ጀቡቲ..ጂንኒ ጃንካ….ትሆናለህ፡፡

እድለኛ ከሆንክ ግን ታሪኩ ሌላ ነው የሚሆነው፡፡ ለምሳሌ ጂንኒዋ ከመመላለስ ብዛት ከወደደችህ የጋብቻ ጥያቄ ታቀርብልሃለች፡፡ ጂንኒ እዚህ ደረጃ ከደረሰች በእውነት አሸንፈሃታል ማለት ነው፡፡ ጂንኒ ስትወድህ ከልቧ ነው፡፡ በውሸት ሞቼልሃለሁና አግባኝ አትልህም፡፡ እንዲህ በለስ ቀንቶህ የምትወልደው ልጅ ምን እንደሚባል ታውቃለህ? “ኢፍሪት” የሚባል ልጅ ነው የሚወለደው፡፡ የሰው ቁመናና መልክ ያለው፤ ነገር ግን እናቱ ከሆነችው ከጂንኒዋ ባለቤትህ ልዩ ልዩ “ፓወር” የሚወርስ ልጅ… ጥበብ ትላለህ ገንዘብ፤ አስማት ትላለህ ፍልሰፋ የማይችለው ነገር የለም! አይ ኢፍሪት!! የጂንኒ ክልስ!
                *****  *****  *****
ከቢር አህመዴ የቅድመ- አያቴ ወንድም ናቸው፡፡ በልዩ ልዩ ችሎታ ጂንኒዎችን እያላመዱ እንደ ሰው ይገለገሉባቸው ነበር አሉ፡፡ ታዲያ የርሳቸው ጂንኒዎች “ሩሐኒ” በመሆናቸው ሰዎችን አይተናኮሉም፡፡ ከቢር አሕመዴ የተጣሉትን ሰው ግን አይምሩትም፡፡
  
  በአንድ ወቅት ከቢር አህመዴና ከቢር ዑመራ የተባሉት ወንድማቸው ተጣሉ፡፡ የከቢር አሕመዴ ጂንኒዎችም ለጌታቸው በማገዝ ከቢር ዑመራን ሊበቀሉላቸው ተነሱ፡፡ ከቢር ዑመራ በመስገጃ ቦታቸው ላይ እያሉ እንደ ፌንጣ ሆነው ከበቧቸው፡፡ ከዚያም እንደ ፌንጣ እየጮኹ ይረብሿቸው ጀመር፡፡ ከቢር ዑመራም “አዑዙቢላሂ” ብለው አንዱን ፌንጣ በተስቢ (ሙስበሐ) ቢመቱት እግሩን ስብር አደረጉት፡፡ በዚህን ጊዜ ሌሎቹ ፌንጣዎች ደንግጠው እየበረሩ ከአካባቢው ጠፉ፡፡ በእውነተኛ መልካቸው ወደ ከቢር አሕመዴ ሲመለሱ አደም የተባለው “ሩሐኒ” ጂንኒ እግሩ ተሰብሮ ተገኘ፡፡ ከቢሩ ነገሩን ቢጠይቋቸው ጂንኒዎቹ የተፈጠረውን ሁሉ አጫወቷቸው፡፡ ከቢር አሕመዴም ጂንኒዎቹ ያለፈቃዳቸው ዑመራን ሊረብሹ በመሄዳቸው በጣም ተቆጡ፡፡ አደምም አንካሳ እግሩን ታቅፎ ቀረ፡፡በሰፈሩም “አደም ኦኮላ” (አንካሳው አደም) እየተባለም ይጠራ ጀመር፡፡

   ይህ አደም ከከቢር አሕመዴ ሞት በኋላ ረጅም እድሜ ኖሯል፡፡ እኔም እርሱ ይገኝበታል የተባለውን ቦታ በተደጋጋሚ ጊዜ ጎብኝቼዋለሁ፡፡ አንድ ቀንማ አክስቴ (የአባቴ እህት) “ነጭ ለብሶ በዚህ በኩል ይመጣል” ስትለኝ ከቤቷ በታች ካለው የጂልቦ (አንጎራ) ዛፍ አጠገብ ቆሜ ስጠብቀው አደርኩ፡፡ ግን ላየው አልቻልኩም፡፡ ታዲያ አንድ ቀን ምሽት የኡኡታ ድምጽ ሰማሁ፡፡ በኦሮምኛ “Narraa baasaa” (አውጡኝ! አስጥሉኝ!) እያለች የምትጮህ የሴት ድምጽ ነበር፡፡
አክስቴን ማን ነው የሚጮኸው ብዬ ጠየቅኳት፡፡
   “ጂንኒ ናት፡፡ ጅብ እያባረራት ነው”
   “ከየት የመጣች ጂንኒ?”
   “እኔ እንጃ! አደም ሊሆን ይችላል”
    “አደም ወንድ አይደለም እንዴ?”
  “አይ! ጂንኒ ሁሉ ጅብ ሲመጣበት በሴት ድምጽ ነው የሚጮኸው”
   በጣም አዘንኩ፡፡ እኔ እርሱን ለማየት ስዋትት ከርሜ እርሱ በጅብ ለመበላት በመቃረቡ ተናደድኩ፡፡ የፈራሁት አልቀረም፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ “አደም በጅብ ተበላ” ተባለ፡፡ እኔን ይብላኝ!
                *****  *****  *****
እንቀጥል እንዴ? ብቀጥል ደስ ይለኛል፡፡ አንዳንድ ሰዎች ግን “እየፈራን ነውና አሳጥረው” ብለውኛል፡፡ ጂንኒዋ ሳትቆጣኝ እነርሱ መፍራታቸው ቢገርመኝም ፍላጎታቸውን ለመጠበቅ ስል በዚሁ ላበቃ ተገድጃለሁ፡፡
 
 ግን ግን…. አንድ የዋሸኋችሁ ነገር አለ፡፡ በትናንቱ መግቢያዬ ላይ “እንደኔ ከጂንኒ ጋር እየተጋፋችሁ መጻፍ የምትችሉ” እያልኩ ዘባርቄ ነበር አይደል? ውሸቴን ነው፡፡ ነጭ ውሸት! እኔ ነኝ እንዲህ ጽናት ኖሮኝ ስለጂንኒ የምጽፈው? አዲስ አበባ፣ ገለምሶ፣ ጭሮ ወይንም አዳማ ብሆን ኖሮ አንድ ገጽ እንኳ የምጽፍላችሁ አይመስለኝም፡፡ ሀረር ስላለሁ ነው ይህንን ሁሉ የተረተርኩት፡፡ “ልዩነቱ ምንድነው?” ካላችሁ የኔ መልስ “እዚህ ጂንኒ የለም” የሚል ይሆናል፡፡

 አዎን! ሀረር ጅብ ከሰው ጋር እየተጋፋና እየተላፋ የሚኖርባት ከተማ ናት፡፡ አያ ጅቦ ጂንኒዋን ከዚህች ከተማ ካባረራት ስንትና ስንት ዘመን ሆኖታል፡፡ ሀረሪዎች ዛሬ ጂንኒን የሚያውቁት በትዝታ ብቻ ነው፡፡ እኔም ድሮ እንጂ በዛሬው ዘመን ጂንኒን አይቻት አላውቅም፡፡
     ለማንኛውም ጂንኒዋ ብትኖርም ባትኖርም “አዑዙ ቢላሂ” እንበልና እናብቃ!
--------
አፈንዲ ሙተቂ
ነሐሴ 26/2006
ሀረር-ምስራቅ ኢትዮጵያ
--------

==ከቀልደኛ አስተማሪዎቻችን በጥቂቱ==


ከአፈንዲ ሙተቂ
------------
የአንደኛ ደረጃ ተማሪ ሳለሁ ያጋጠሙኝ አስተማሪዎች ቀልድ የለባቸውም፡፡ ተረት ካልሆነ በስተቀር ቀልድ እየነገሩ ወይንም እየኮመኩ ተማሪዎችን ማሳቅ አያውቁበትም፡፡ በተቃራኒው ብዙዎቹ ተማሪው በሚፈጥራቸው ቀልዶችና በያንዳንዱ ተማሪ ባህሪና ገጠመኝ ከልባቸው ይስቁ ነበር፡፡ ሆኖም እነዚያ አስተማሪዎቻችን ከፍተኛ የፈጠራ ችሎታ እንደነበራቸው አይካድም፡፡ አንድ ሁለቱን ግን በጣም እጠላቸው ነበር፡፡ ለምሳሌ ዘነበ ከበደ የሚባለው የአራተኛ ክፍል ስፖርት አስተማሪያችን “ዛሬውኑ በአየር ላይ ተገልበጡ” የሚል ዓይነት ሰው ስለነበረ በጣም ነበር የምንጠላው (በግልበጣው ከሚደርስብን መላላጥና መፈንከት በላይ የርሱ ግርፊያ ነበር የሚያስፈራን)፡፡
 
እጅግ የማይረሱ ቀልደኛ አስተማሪዎች የገጠሙኝ በሀይስኩል ነው፡፡ በቀለ ካሳ፣ ተስፋዬ ራሺያ፣ ዳንኤል አሰፋ፣ መሐመድ አብደላ ወዘተ… በፍጹም አይረሱኝም፡፡ እስቲ ከቲቸር ዳንኤልና ከጋሽ ተስፋዬ ቀልዶች ጥቂቱን ላጋራችሁ፡፡
------
ጋሽ ተስፋዬ በአስረኛና አስራ አንደኛ ክፍል የኬሚስትሪ አስተማሪዬ ነበር፡፡ በቅጽል ስሙ “ተስፋዬ ራሺያ” እያልን ነበር የምንጠራው፡፡ ጋሽ ተስፋዬ ስለኬሚስትሪ ጠለቅ ያለ እውቀት አለው፡፡ ግን ውጪ አውጥቶ በመናገር በኩል ችግር አለበት፡፡ ታዲያ ጋሽ ተስፋዬ ክፍል ከገባ አስር ደቂቃ ያህል በቀልድ ነው የሚያሳልፈው፡፡
 
አንድ ቀን ጋሽ ተስፋዬ ወደ ክፍል ለመግባት በሶምሶማ “ላፍ ላፍ” እያለ ወደኛ መጣ፡፡ መሬቱ ግን በሀይለኛ ዝናብ በስብሶ ስለነበር እንኳንስ በሶምሶማ፣ በቀስታም ለመሄድ አዳጋች ነበር፡፡ ጋሽ ተስፋዬ እንደፈራነው ወደኛ ክፍል ሳይደርስ አዳልጦት ወደቀ፡፡ በአቅራቢያው የነበሩ ተማሪዎችም ሮጥ ብለው ደጋግፈው አነሱት፡፡
   ጋሽ ተስፋዬ አንዴ መሬቱን አንዴ በጭቃ የተበላሸ ልብሱን እያየ እንዲህ አለ፡፡
    “ጎበዝ እዚህ አካባቢ ግራቪቲ የለም እንዴ?”
   በስፍራው የነበርነው በሙሉ ሳቃችንን ለቀቅነው፡፡

  (“ግራቪቲ” የስበት ኃይል መሆኑን ላስታውሳችሁ እሻለሁ! እንዲህ ሳደርግ ታዲያ አሁን ስሙ ተቀይሮ ከሆነ ብዬ ነው እንጂ ነገሩን ትረሱታላችሁ በማለት እንዳልሆነ እወቁልኝ)፡፡
------
ጋሽ ተስፋዬ ኬሚስትሪን ሲያስተምር ስለያንዳንዱ ኬሚስት ህይወት አስደናቂ ወሬዎችን ያወጋናል፡፡ እኛም በተመስጦ እናዳምጠዋለን፡፡ አንዳንድ ጊዜ ግን ተአማኒ ያልሆኑ ወሬዎችንም ይቀላቅላል፡፡ ለምሳሌ አንድ ጊዜ “የአሲድ ጣዕም ምን ዐይነት ነው?” የሚለውን ሲያስረዳን እንዲህ ብሎን ነበር፡፡
   
  “የአሲድን ጣዕም እኮ ያገኙት ሁለት ባልና ሚስት ናቸው፡፡ ደግሞም የህይወት ዋጋ ከፍለውበታል፡፡ ይህ እንዴት የሆነ ይመስላችኋል? ባል ሚስቱን ይጠራና “እኔ አሲድን ቀምሼ ጣዕሙ ምን ዓይነት እንደሆነ እጽፋለሁ፣ አሲዱ በድንገት ከገደለኝ ግን አንቺ እኔ የጀመርኩትን ትጨርሽዋለሽ” አላት፡፡ ሚስትም “እሺ” አለችው፡፡

በዚህ ስምምነት መሰረት ባል አሲዱን ጠጣ፡፡ ወዲያኑ ተንዘፍዝፎ ወደቀ፡፡ ከመሞቱ በፊት ግን “S” የተሰኘውን የእንግሊዝኛ ፊደል ጻፈ፡፡ ሚስትም ከርሱ ተከትላ አሲዱን ጨለጠችውና ወዲያኑ ተንዘፍዝፋ ወደቀች፡፡ እርሷም ከመሞቷ በፊት ግን ባሏ በጻፈው አንድ ፊደል ላይ “O”ን ጨመረችበትና “SO” አደረገችው፡፡ ዓለምም አሲድ “sour” (ጎምዛዛ) መሆኑን በዚህ መንገድ አወቀ፡፡ ያኔ ሚስት ባሏን ተከትላ ባትሞት ኖሮ አሲድ “sour” (ጎምዛዛ) ወይስ “salt” (ጨዋማ) የሚለው ክርክር ይቀጥል ነበር”፡፡
 ------
ዳንኤል አሰፋ የአስራ አንደኛ ክፍል የሒሳብ አስተማሪያችን ነበር፡፡ ጎብዝናው ይገርማል! እኛ ተማሪዎቹ የዳንኤልን ችሎታ የጂኦሜትሪ ሳይንስን ከጀመረው “ኢኩሊድ” የሚባል የግሪክ ፈላስፋ ጋር እናወዳድረው ነበር፡፡ በህይወቴ እንደርሱ እየመሰጠኝ የተማርኩባቸው አስተማሪዎች ቢኖሩ ሰለሞን የሚባል የአስራ አንደኛ ክፍል እንግሊዝኛ መምህሬ፣ የሶፎሞር እንግሊሽ አስተማሪዬ የነበረው ወልዱ ሚካኤል (በኋላ ዶ/ር ሆኗል) እና ለአንድ ዓመት ተኩል ያህል History of Economic Thought እና Development Economics የሚባሉ ኮርሶችን ያስተማረኝ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ብቻ ናቸው (እዚህ ዘንድ ፖለቲካ እየሰራን እንዳልሆነ ልብ በሉ፡፡ ነገሩን በፖለቲካ ዐይን የምታዩ ካላችሁ ዶ/ር ወልዱ የመንግሥት ደጋፊ፣ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ የመንግሥት ተቃዋሚ መሆናቸውን እወቁልኝ)፡፡ በነገራችን ላይ ሁለቱ የዩኒቨርሲቲ አስተማሪዎቼ በውጤት ጊዜም ለተማሪው ልፋት ተገቢውን ዋጋ ይሰጡ እንደነበር ማስታወስ እፈልጋለሁ፡፡

ወደ  ቲቸር ዳንኤል ቀልዶች እንመለስ፡፡ በሳምንቱ ቀናት ሁሉ ሒሳብ እንማር ነበር፡፡ ማክሰኞ ደግሞ ለሁለት ክፍለ ጊዜያት (ደብል ፔሬድ) ነበር የምንማረው፡፡ ቲቸር ዳንኤል በአንዱ ፔሬድ ሲያስተምር ከቆየ በኋላ ሁለተኛውን ፔሬድ እስኪጀምር ድረስ በመሀሉ የአምስት ደቂቃ እረፍት ይሰጠናል፡፡ ታዲያ እርሱ አምስት ደቂቃ ሲለን አንዳንዶቻችን ለስምንት ደቂቃ፣ አንዳንዶቻችንም እስከ አስር ደቂቃ እንቆይ ነበር፡፡ ቲቸር ዳንኤል ይህንን ጉራማይሌ ሁኔታ ለትንሽ ጊዜ በትዕግስት አሳለፈው፡፡ አንድ ቀን ግን ትዕግስቱ አለቀበትና እንዲህ አለን፡፡

    “ፕላኔቶች ከጸሐይ በሚርቁበት ልክ በየፕላኔቱ ላይ የሚደረገው የጊዜ አሰፋፈርም ይለያያል፡፡ ሜርኩሪ ላይ ሁለት ደቂቃ ማለት መሬት ላይ አምስት ደቂቃ ማለት ሊሆን ይችላል፡፡ ጁፒተር ላይ ስምንት ደቂቃ፣ ሳተርን ላይ ሀያ ደቂቃ ወዘተ… እና የጁፒተር ሰዎች ከዛሬ በኋላ አደብ ግዙልኝ፡፡ እምቢ ካላችሁ ወደ ጁፒተር ሂዱልኝ”
--------
ይህኛው ደግሞ በሌላ ክላስ (11ኛ C) የተፈጠረ ተብሎ ነው የተነገረኝ፡፡
  
ቲቸር ዳንኤል ሲያስተምር አንዱ ተማሪ ከወዲያ ወዲህ ውርውር ይላል፡፡ ዳንኤል በትዕግስት አሳለፈው፡፡ ተማሪው ግን በፍጹም አላርፍ አለ፡፡  ይሄኔ ቲቸር ዳንኤል ተናደደና እንዲህ አለ፡፡
    “አንተ ልጅ አርፈህ አንድ ቦታ ቁጭ በልልኝ፡፡ እምቢ ካልክ ግን ይህንን ትሪያንግል የመሰለ ፊትህን ፔንታጎን አስመስልልሀለሁ”፡፡
(በሂሳብ መሳደብ እንዲህ ነው!)
--------
በአስራ ሁለተኛ ክፍል የፊዚክስ አስተማሪ ቢቸግረን ቲቸር ዳንኤል “የኔ ማይነር ፊዚክስ ነው፤ አይዞአችሁ! እኔ ራሴ አስተምራችኋለሁ” ብሎ ገባልን፡፡ እናም አንድ ቀን ሲያስተምረን “a metal rod which is uniformly distributed” የሚል ነገር ተናገረ፡፡ “ውፍረቱ በሁሉም በኩል እኩል የሆነ ብረት” ለማለት ፈልጎ ነው፡፡ ግን አንድ ተማሪ ተደናገረና “ቲቸር ምን ማለት ነው?” በማለት ጠየቀው፡፡ ቲቸር ዳንኤል በአማርኛ ተርጉሞ ነገረው፡፡ ተማሪው ግን አልገባህ አለው፡፡ ይህ ተማሪ አስተማሪዎችን በጥያቄ የመወጠር አመል እንዳለው ሁሉም ሰው ያውቃል፡፡ በመሆኑም ቲቸር ዳንኤል ከተማሪው ጋር በቀጥታ መዳረቁን ተወና ነገሩን እንዲህ አብራራለት፡፡
  
   “ለምሳሌ ከቀበሌና ከሻይ ቤት የሚገዛውን ዳቦ ተመልከት፣ ውፍረቱ በሁሉም በኩል እኩል አይደለም፡፡ አንድ እናት እርሱን ገዝታ ለሶስት ልጆች አከፋፍላለሁ ብትል የዳቦውን የመሀለኛውን ክፍል ካገኘው ልጅ በስተቀር ሌሎቹ እንደሚያለቅሱ አትጠራጠር፡፡ ሴትዮዋ “ሽልጦ ዳቦ” ከጉልት ብትገዛላቸው ግን በሁሉም በኩል እኩል በመሆኑ ሁሉም ልጆች ያለ አንዳች ቅሬታ ነው የሚቀበሉት”፡፡
  ቲቸር ዳንኤል ሽልጦን ምሳሌ በማድረግ ከተማሪው ጭቅጭቅ ተገላገለ፡፡
----------
ቲቸር ዳንኤል የአዲስ አበባ ልጅ ነው፡፡ በቅርብ ዓመታት እንደሰማሁት የመምህርነት ሙያውን ትቶ ከዘመዶቹ ጋር በአዲስ አበባ ቢዝነስ እየሰራ ነው፡፡ ጋሽ ተስፋዬ (ራሺያ) ግን እዚያው የኛ ከተማ ቤት ሰርቶ፣ ልጆች ወልዶ እየኖረ ነው፡፡

     አስተማሪዎቻችን ባለውለታችን ናቸው፡፡ በተለይ የአንደኛ ደረጃ እና የሁለተኛ ደረጃ አስተማሪዎቻችን ውለታ መቼም ቢሆንም አይረሳም፡፡ በማትረባ ደመወዝ የማይረባ ኑሮ እየኖሩ ስንቶቻችንን ለቁምነገር አብቅተዋል፡፡ በሰለጠነው ዓለም ከሁሉም ተቀጣሪ በላይ ከፍተኛ ክፍያ የሚያገኙት እነርሱ ናቸው አሉ፡፡ በሀገራችን ግን ሁሉም ነገር የተገላቢጦሽ ነው፡፡ እስቲ ይሁና! “መቼስ ማልጎዸኒ” አለ የሀገሬ ሰው!!

አፈንዲ ሙተቂ
ነሐሴ 27/2005