Tuesday, September 10, 2013

በምስራቅ ዕዝ ሙዚቀኞች ላይ የደረሰው እልቂት (ታህሳስ 1980)


ከአፈንዲ ሙተቂ
-------
እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር በ1980 ገደማ በሀረር ከተማ ከአምስት ያላነሱ ኦርኬስትራዎች ነበሩ፡፡ ከነርሱም መካከል ሶስቱ ከሀረርጌ ክፍለ ሀገር አልፎ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ስም ነበራቸው፡፡ እነርሱም በተለምዶ “የምስራቅ እዝ ኪነት” የምንለውና በዘመኑ አጠራር ግን “የአንደኛው አብዮታዊ ሰራዊት ኦርኬስትራ” የሚባለው የኪነት ቡድን (እነ ንግሥት አበበ እና ኑሪያ ዩሱፍን የመሳሰሉ ከዋክብትን ያቀፈ)፣  “የምስራቅ በረኛ አብዮታዊ ፖሊስ የኪነት ጓድ” (እነ ኤልሳቤት ተሾመ፣ ፍቅሩ ቶሌራ፣ ሙሳ ቱርኪ፣ ፋንታሁን ፈረንጅ እና ግርማ ንጋቱ የነበሩበት) እና “ጎሐ ምስራቅ የኪነት ቡድን” (እነ ሰለሞን አካሉ፣ ሙሉጌታ አባተ፣ መፍቱሐ አባስ እና ሙስጠፋ አብዲ የመሳሰሉትን ያቀፈ) ናቸው፡፡

   ከሶስቱ ቡድኖች አንዱ የሆነው የምስራቅ ዕዝ ኪነት ቡድን ከሻዕቢያ ጋር ለሚፋለመው ሁለተኛው አብዮታዊ ሰራዊት ዝግጅቱን ለማቅረብ ወደ ሰሜን ተጓዘ፡፡ ግን በሰላም አልተመለሰም፡፡ ንግሥት አበበን ጨምሮ በርካታ አባላቱን በሞት አጣ፡፡ በቡድኑ ላይ የደረሰው እልቂት በኢትዮጵያ ሬድዮ ሲነገር በርካቶችን በእንባ አራጨ፡፡ በተለይ ከዘመኑ አፍለኛ ዘፋኞች አንዷ የነበረችው የንግሥት አበበ ሞት የብዙዎችን ልቦና የሰበረ ነበር፡፡ ያ አሳዛኝ ትራጄዲ እንዴት ተከሰተ? የቡድኑ አስተዋዋቂ የነበረውና ከሞት የተረፈው  ግርማ ከበደ (በቅጽል ስሙ “ግርማ ዲናሬ”) ሁኔታውን ለኢትኦጵ መጽሔት እንደሚከተለው አብራርቶ ነበር፡፡
-----
ኢትኦጵ፡- አንድ ጊዜ የምስራቅ እዝ ኪነት ቡድን ወደ ሰሜን አቅንቶ በሻዕቢያ ደፈጣ ተዋጊዎች እንደተመታ ሰምቻለሁ፡፡ በዚያን ጊዜ አንተ ነበርክ?

ግርማ፡ አዎን እኔም ነበርኩ፡፡ ደመናው ከልሎኝ ከተረፉት ጥቂቶች አንዱ እኔ ነኝ፡፡ ጊዜው 1980 ዓ.ም. ታሕሳስ 21 ቀን ነው፡፡ ዝግጅታችንን ግንባር ላለው ሰራዊት አቅርበን ወደ አስመራ ስንመለስ ጠላት አድፍጦ ይጠብቀን ነበርና 17 አርቲስቶች በዚያ ውጊያ ህይወታቸው ጠፋ፡፡ ካጀቡን ወታደሮችም 20 ያህሉ በውጊያው ተሰውተዋል፡፡ 14 አርቲስቶች ደግሞ ቆስለዋል፡፡ አራት ሰዎች ብቻ ምንም ጉዳት አልደረሰብንም፡፡

ኢትኦጵ፡- የምስራቅ እዝ የተዋጣላት ድምጻዊት ንግሥት አበበ በዚህ ውጊያ ላይ ነበር ህይወቷ ያለፈው?

ግርማ፡- አዎን (በሐዘን ስሜት አቀረቀረ)::

ኢትኦጵ፡- እስቲ ያንን ሁኔታ እንዴት ትገልጸዋለህ?

ግርማ፡- ወደ አስመራ ስንመለስ ትልቅ ስጋት ነበረብን፡፡ ሻለቃ ታደሰ የተባሉ አዛዣችንም ጥንቃቄ እንድናደርግ ደጋግመው አሳስበውናል፡፡ እሳቸውም እዚያው ነው የተሰውት፡፡ ሻለቃው እንደሰጉት እኛም አንዳች አደጋ ሊገጥመን ይችላል ብለን ፈርተን ነበርና አልቀረልንም፡፡ አደጋው መጣ፡፡ ንግሥት በፈንጂ ደረቷ ስር ተመትታ ነው የወደቀችው፡፡ ብዙ ቦንብ ነበረ የሚወረውሩብን፡፡ አጃቢዎቻችን ለመከላከል ብዙ ሞከሩ፤ ግን አልሆነም፤ አለቁ፡፡ እነርሱን መጨረሳቸውን ሲረዱ አርቲስቶች ወዳሉበት መኪና ተኩስ ከፈቱ፡፡ እየተላቀስን በጥይት ቀጠቀጡን፡፡ “ሁሉንም ጨርሰናል” ብለው ካደፈጡበት ወጡ፡፡ የተረፈ እንዳለ ፈተሹ፡፡ እኔ አንድ ስርቻ የሞተ መስዬ ተደበቅኩ፡፡ መቼም ፈጣሪዬን እንደዚያ ቀን የተማፀንኩበት ጊዜ አልነበረም፤ ተረፍኩ፡፡

ኢትኦጵ፡- ያንን አደጋ እንጠብቀው ነበር ስትል?

ግርማ፡ ብዙ ጭንቀት ነበረብን፡፡ ለምሳሌ ንግሥት አበበ የሶስት ወር አራስ ነበረች፡፡ ዝግጅታችንን ስናቀርብ “ለጥምቀት ሀረር አንደርስም ወይ? እኔ ልጄን ክርስትና አስነሳለሁ፤ እንደምንም ብለን በዚህ ጊዜ መጨረስ አለብን” ትል ነበር፡፡ አዛዣችንም ጉዞ ስንጀምር “እኔም ለልጆቼ፣ እናንተም ለቤተሰቦቻችሁ ስትሉ በጉዞ ላይ ጥንቃቄ አድርጉ” ይሉን ነበር፡፡ ይህንን ስንሰማ ሁላችንም ስጋታችን አየለ፡፡ እንደፈራነው ያን ዓይነት እልቂት ጠበቀን፡፡ ሀዘኑ እስከ ህይወቴ ፍጻሜ የሚጠፋ አይመስለኝም፡፡ በጠቅላላው የምስራቅ እዝ ኦርኬስትራ ነው የተመታው፡፡ የት ይደርሳሉ የሚባሉ አርቲስቶች ናቸው በዚያ ጨካኝ ትዕይንት ያለቁት፡፡
-------
(ኢትኦጵ መጽሔት፣ ቅጽ 4፣ ቁጥር 7፣ ሰኔ 1994፣ ገጽ 40)
እንዲህ ነው እንግዲህ አደጋው የተፈጠረው! ንግስትን ጨምሮ በርካቶች ያለቁት በዚያ አደጋ ነው፡፡ ታዲያ ሻዕቢያ በተመሳሳይ ወቅት ናደው የሚባለውን እዝ አጥቅቶ እጅግ ወሳኝ የሆነ ድል መቀዳጀቱም ይታወሳል፡፡

ከዚያ አደጋ ቆስለው ከተረፉት አርቲስቶች አንዷ የነበረችው የኦሮምኛ ዘፋኟ ኑሪያ ዩሱፍ በቅርቡ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይታለች (ኑሪያ በአደጋው አንድ እግሯን አጥታለች)፡፡ ግርማ ዲናሬ በአሁኑ ወቅት አዲስ አበባ ነው የሚኖረው፡፡ ፒያሳን የሚያዘወትሩ ሰዎች ሊያገኙት ይችላሉ፡፡

  በነገራችን ላይ አንዳንዶች በስህተት “በአደጋው ያለቁት የምስራቅ በረኛ ፖሊስ የኪነት ጓድ አባላት ናቸው” እያሉ ሲናገሩ ሰምቻለሁ፡፡ ትክክለኛው ታሪክ ግን በግርማ ዲናሬ አንደበት ከላይ የተገለጸው ነው፡፡ ሰላም!
------
You can get also more articles on this page https://www.facebook.com/afendimutekiharar

Saturday, September 7, 2013

==ከትምህርት ቤት መዝሙሮቻችን በጥቂቱ (ለትዝታ)==


ጸሓፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ
-----
የአንደኛ ደረጃ ትምህርቴን ያጠናቀቅኩት በቁጥር ሁለት ት/ቤት ነው፡፡ የትምህርት ቤታችን ዋነኛ ህንጻ በስዕሉ ላይ የምትመለከቱት ነው፡፡ ይህንን ህንጻ የኢጣሊያ ወራሪዎች ናቸው የሰሩት፡፡ በከተማችን ውስጥ ለረጅም ዘመናት በቁመቱ ከርሱ ጋር የሚስተካከል ሰው ሰራሽ ግንባታ አልነበረም፡፡ በዚህም የተነሳ በኦሮምኛ ስሙ “Mana Dheeraa” (ረጅሙ ህንጻ) በማለት ነው የምንጠራው፡፡

  የትምህርት ቤቱ የኦፊሴል ስም ነው “ገለምሶ ቁጥር ሁለት አንደኛ ደረጃ ት/ቤት” ነው፡፡ በተለምዶ ህንጻውን የምንጠራበት “ቁጥር ሁለት” የተሰኘው የአማርኛ ስሙ የተገኘው ከዚሁ ነው፡፡

 “ቁጥር ሁለት” (“መነ ዴራ”) በኢጣሊያ ወራሪዎች ዘመን የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ነበር፡፡ ጣሊያኖቹ ሲወጡ የወረዳ ጽ/ቤት ሆኖ ማገልገል ጀመረ፡፡ ከዚያም ወደ አዳሪ ት/ቤት ተቀየረ፡፡ በ1962 ገለምሶ የአውራጃ ዋና ከተማ ስትሆን ደግሞ ህንጻው ወደ እስር ቤት ተቀየረ፡፡ በርሱ ምትክም ሌላ ትምህርት ቤት በከተማው የምስራቁ ክፍል ተሰራ፡፡

  “ቁጥር ሁለት” እስከ ዘመነ ቀይ ሽብር ድረስ እንደ እስር ቤት ካገለገለ በኋላ በ1972 ገደማ እንደገና ወደ ትምህርት ቤት ተቀየረ፡፡ ሁለቱን አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በስም ለመለየት በሚልም “ቁጥር ሁለት” የሚለው ስያሜ ተሰጠው፡፡ እያደገ የመጣውን የተማሪ ብዛት ለማስተናገድ እንዲችልም በርካታ ክፍሎች በግቢው ውስጥ ተሰሩለት፡፡ በማስከተልም ሌሎች በርካታ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በከተማው ውስጥ ተከፈቱ፡፡  

ስለ ቁጥር ሁለት ታሪክ ይህንን ያህል ካልኳችሁ ይበቃል፡፡ አሁን ደግሞ የዚህ ትምህርት ቤት ተማሪ ሳለሁ እንዘምራቸው ከነበሩት መዝሙሮች ጥቂቶቹን ላካፍላችሁ፡፡
 -----
ዝናብ ሲዘንብ በዝምታ አናሳልፍም፤ በከፍተኛ ድምጽ እንዘምራለን እንጂ! መዝሙሩን እኛ ብንረሳ እንኳ አስተማሪዎቻችን “ዘምሩ” ይሉናል፡፡ በዚህ በኩል እስከ አሁን ድረስ ትዝ የሚሉኝ የሚከተሉት ናቸው፡፡
  
ሀ/. ዋንታ ነሜራ
ዋንታ ነሜራ ዋሂራ ዋንታ ነሜራ
ዋንታ ነሜራ ዋሂራ ዋንታ ነሜራ
ዝናቡ ዘነበ ደጁ ረሰረሰ
አንዱን ሳላጠና ፈተና ደረሰ
ዋንታ ነሜራ ዋሂራ ዋንታ ነሜራ

“ዋንታ ነሜራ” የኩባ ዘፈን እንደሆነ ይታወቃል፡፡ አዝማቹ ብቻ ተወስዶ ወደ አማርኛ መዝሙር የተቀየረበትን መነሾ ግን አላውቅም፡፡
--
ለ/. “ዝናቡ ዘነበ”
ዝናቡ ዘነበ አትምጪ ስልሽ
ይኸው እንደፈራሁት ጎርፍ ወሰደሽ፡፡
በሀምሳ በሰላሳ ሲገዛ ፈረስ
በመቶ ብር ገዛሁ የሰው አጋሰስ፡፡

በዚህ ግጥም ውስጥ የወንድ ትምክህት አለ አይደል? ያኔ ግን ህጻናት ነበርና ምንነቱ አይታወቅንም ነበር፡፡ እንዲያውም አንዳንድ የአማርኛ ቃላትን ትርጉም እንኳ በፍጹም አናውቅም ነበር፡፡ ለምሳሌ “አጋሰስ” ምን ማለት እንደሆነ በኋላ ላይ ነው የተረዳሁት፡፡
-----
ብዙ መዝሙሮች የምንዘምረው በሙዚቃ ክፍለ ጊዜ ነበር፡፡ ከነዚያ መዝሙሮች መካከል ከየዘርፉ አንድ ሁለቱን ልጻፍላችሁ፡፡

  ሀ/. “አንቅልፍ ጨርሰን” (ስለግል ንጽህና)

እንቅልፍ ጨርሰን ጠዋት ስንነሳ
የምንሰራውን ልጆች እንዳንረሳ
ልብሳችንን ለብሰን ሽንት ቤት ደርሰን
ሳሙናና ውሃ ለፊት አቅርበን
እጅና ፊታችን ማጠብ አለብን፡፡
የጸጉርም ጽዳት መጠበቅ አለበት
በደንብ አበጥሮ ከተገኘም ቅባት
ቀብቶ መሄድ ነው ወደ ትምህርት ቤት፡፡

ለ/. ዝንቦች (ስለንጽህና)

ዝንቦች መጥፎ ናቸው
  “እሽ! እሽ!” ይበሏቸው፡፡
  ዐይንን ያጠፋሉ
  በሽታን ያመጣሉ
  እናባርር በሙሉ!!
   እናባርር በሙሉ፡፡
  
 ሐ/. አብዮታዊ ሰራዊት (ስለ አብዮታዊው ጦር)

አብዮታችን በጣም በጣም ደመቀ
የድል ጮራ ዳር እስከ ዳር ፈነጠቀ፡፡
በምስራቅ በደቡብ በመሀል አልፎ
ጠላቱን ወራሪ ማረፊያ አሳጥቶ
እንደ ካራማራ እን ጭናክሰን
ድል ተቀዳጅቶ ገስግሶ በሰሜን፡፡
ተዋግቶ ተዋግቶ
አጥንቱን ከስክሶ ደሙን አፍስሶ
አብዮታዊ ሰራዊት ድል አድርጎ ሲገባ
በሉለት ጉሮ ወሸባ! በሉለት ጉሮ ወሸባ!!

መ/. ውሸታሙ እረኛ (ስነ-ምግባር)

ውሸታሙ እረኛ
ሲያልፍ መንገደኛ
ቀበሮ መጣብኝ
በጎቼን በላብኝ፡፡
እያለ ዘወትር
ሲቀልድ ሲያስቸግር
በዚህ አድራጎቱ
ደግሞም በውሸቱ፡፡
አንድ ቀን ቀበሮ
መጣና በድንገት
በጎቹን በላበት፡፡
ውሸታሙ እረኛ
ዘወትር ልማደኛ
ኡኡ እያለ መጣ
የሚረዳውን አጣ፡፡
-----
በሙዚቃ ክፍለጊዜአችን በርካታ “ትርኪምርኪ” መዝሙሮችንም እንዘምራለን፡፡ እስቲ ሁለት “ትርኪምርኪ” መዝሙሮችን ልጋብዛችሁ፡፡

ሀ/ ጋሼ ደያስ
 
አራቱንም ጣቴ ጋሼ ደያስ
  ቢላዋ ቆርጦኛል ጋሼ ደያስ
  አንዱ ብቻ ቀርቶኝ ጋሼ ደያስ
  ያንገበግበኛል ጋሼ ደያስ

ጋሼ ደያስ ተክሌ የሁለተኛ ክፍል የአማርኛ መምህራችን ነበር፡፡ በተጨማሪም የፈረቃ መሪ (ዩኒት ሊደር) ነበር፡፡
-
ለ/. ኦኬ ኦኬ

 ኦኬ ኦኬ ኦኬ ስራ
ሰላም ሰላም ወደ አስመራ
አናግረኝና አናግርሃለሁ
በአሜሪካ ሽጉጥ አዳፍንሃለሁ፡፡
 ሁለትና ሁለት ሲደመር አራት
ፍቅርሽ ይጣፍጣል ከማር ከወተት፡፡
  -----
በሙዚቃ ፔሬድ መዝሙር መዘመር ብቻ ሳይሆን እየዘፈኑ ዳንስ መደነስም ነበር፡፡ እያንዳንዱ ተማሪ የሚያውቀውን ዘፈን እየዘፈነ ይደንሳል፡፡ እኛም ክብ ሰርተን ከሳር ላይ ተቀምጠን ዘፈኑን ከደናሹ ተማሪ እየተቀበልነው እናጨበጭባለን፡፡ 
 
ተማሪው የሚዘፍነው ዘፈን ከካሴት ላይ የተገኘ፣ በሬዲዮ የተለቀቀ፣ በቀበሌ ኪነትና የአካባቢ ሚሊሻ የተዘፈነ ወዘተ ሊሆን ይችላል፡፡ ይሁንና አብዛኛው ተማሪ ተመሳሳይ ነገር ስለሚደጋግም ያሰለቻል፡፡ አንዳንድ ተማሪዎች ግን ከየት እንደተገኙ በማይታወቁ አስገራሚ ዘፈኖች እየደነሱ ያዝኑናል፡፡ ከነርሱም መካከል የሁለተኛ ክፍል አለቃችን የነበረው አያሌው አብነት ፈጽሞ የሚረሳ ሰው አይደለም፡፡

   “አያሌው  ለማ ከፈረስ ወድቆ ከንፈሩ ደማ” የሚለውን ዘፈን ለመጀመሪያ ጊዜ የሰማሁት ከአያሌው አብነት ነው፡፡ አያሌው “ያ ማሙሹ መለሜላ” የሚል የኦሮምኛ ዘፈንም ነበረው፡፡ ሲፈልግ ደግሞ “ሎሜ ሎሜ አይሳ!” እያለ ወላይትኛ ሊዘፍን ይሞክራል (“ሎሜ ሎሜ” ከሚለው ሐረግ በስተቀር ሌላው በሙሉ አማርኛ ነው፤ ያኔ ግን እንደ ወላይትኛ ነው የምንቆጥረው)፡፡ አያሌው ሲያሻው እንግሊዝኛ ልዝፈንላችሁ ይልና አስረሽ ምችው ያስነካል፡፡ እስቲ የርሱን እንግሊዝኛ ዘፈን ልጋብዛችሁና ልሰናበት፡፡

      አይ ጌቾ ጌቾ ( እኛ “ፐረስ ፐረስ” እያልን እንቀበለዋን)
     አይ ጌቾ ቤቢ
     ማዘር ከፋዘር
     ወለዱ ሲስተር
    ሄዱ በአየር
    ገቡ ጎንደር
  -----
   በወዳጅነታችን እንሰንብት፡፡
አፈንዲ ሙተቂ
ጳጉሜ 2/2005
  -----

Wednesday, September 4, 2013

==የሀረላ ወግ==



ጸሓፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ
----------

ከታችኛው አዋሽ አካባቢ ተነስታችሁ እስከ ጅጅጋ ድረስ በተዘረጋው መሬት ባሉት መንደሮች ውስጥ ስትጓዙ የጥንታዊ ግንባታ ፍርስራሾች በብዛት ያጋጥሟችኋል። የየመንደሮቹን ነዋሪዎች ስለግንባታዎቹ እንዲነግሯችሁ ብትጠይቋቸው ሀረላ የሚባል ጥንታዊ ነገድ መኖሪያዎች እንደነበሩ ያወጓችኋል። ስለዚያ ጥንታዊ ነገድ የበለጠ ማወቅ አምሯችሁ ወግ ቢጤ ብትጀምሩ ደግሞ በጣም የሚነሽጡ ወጎችን ያጫውቱአቸዋል፡፡ እስቲ የሀረላ ወጎችን በጥቂቱ ልጻፍላችሁ፡፡
*****     *****   *****
     የሀረላ ነገድ ሰዎች ቁመተ ረጃጅም ነበሩ፡፡ አንድ የሀረላ ሰው በቁመቱ የዘመናችንን ሰው ስድስት ጊዜ ያህል ይበልጠዋል፡፡ ግዝፈቱ ደግሞ ለከት የለውም። ትከሻው በጣም ሰፊ ነው። እጅግ በጣም ጠንካራ በመሆኑ ትልልቅ ቋጥኞችን በቀላሉ እየፈነቀለ ይወረውራል። ቤቱን የሚገነባውም ከተራራ ላይ ቋጥኝ እየፈነቀለ ነው። በሸለቆ ውስጥ የሚፈሱ ወንዞችን እየጠለፈ ሽቅብ እንዲፈሱ በማድረግ ውሃው ወደ እርሻው እንዲደርስ የሚያደርግበትን ብልሀት ተክኗል።
 
    ሀረላ ገበሬ መኖሪያ ቤቱ በልበሌቲ (ምዕራብ ሀረርጌ) ቢሆን እርሻው አሰቦት ያህል ሊሆን ይችላል። በየቀኑም ከበልበሌቲ ተነስቶ እርሻው ወዳለበት አሰቦት አካባቢ ይሰማራል። ሚስቱ ሆጃ እና ላቀን (ምሳ) እዚያ ድረስ ትወስድለታለች። ከዚያም ሲመሽ ሀረላው በሬዎቹን እየነዳ ወደቤቱ ያዘግማል። ሀረላው ይህንን ረጅም ርቀት (በደርሶ መልስ 250 ኪ.ሜ. የሚሆን) የሚጓዘው ዘና ብሎ ነው።

     ሀረላ ገበሬ ምሽት ላይ ወደ ቤቱ የሚመለሰው ባዶውን አይደለም፤ በእጁ የአትክልትና ፍራፍሬ መአት ተሸክሞ ነው እንጂ። ይህም ድርጊት ዓመቱን በሙሉ ዘላቂ ሆኖ ይቆያል። ምክንያቱም እርሻው ውሃ አያጣምና። በክረምት ጊዜ ዝናብ አለ፡፡ በበጋ ጊዜ ሀረላው ተራራውን እየሰረሰረ ውሃ ያወጣል፡፡ ስለዚህ እርሻው ለዘወትር በመስኖ ውሃ እንደረጠበ ነው የሚቆየው፡፡

    ታዲያ የሀረላ ነገድ በሚኖርበት ዘመን የኛን ዓይነት ሰዎችም (የኛ ቅድመ አያቶች) ይኖሩ ነበር፡፡ እነዚያ ቅድመ አያቶቻችን ከሀረላ ጋር በአንድ መሬት ላይ ቢኖሩም ከሀረላ ጋር ብዙም ቀረቤታ አልነበራቸውም። ሀረላዎች ዘራችንን ያበላሻሉ በማለት ከነርሱ ጋር አይቀራረቡም፤ አይጋቡምም፡፡ ሀረላዎች በቅድመ አያቶቻችን አጭር ሰውነት እየተገረሙ በሽምብራ ጥላ ስር የሚጋደሙ ድንክዬዎች ይሏቸው ነበር፡፡ የኛ ቅድመ አያቶች እንደጥላ የሚያርፉባቸው ዛፎች በቁመታቸው የሀረላ ገበሬ ከሚዘራው ሽንብራ ስለማይበልጡ ነው ሀረላዎቹ ቅድመ አያቶቻችንን እንዲያ ብለው የሚያናንቁት፡፡

   አንድ የኛ ቅድመ አያት ወደ ሀረላ እርሻ ተደብቆ በመግባት ስርቆት ከፈጸመ ብዙም የሚያጎድለው ነገር ስለሌለ ሀረላዎች እርሻቸው መሰረቁ አይታወቃቸውም፡፡ ሰውየው እሰርቃለሁ ቢል ከአንድ ቲማቲም በላይ መሸከም አይችልምና፡፡ ይህ ሰው በእርሻው ውስጥ ሳለ ሀረላ ድንገት ከያዘው ለቅጣቱ ብዙም አይጨነቅም፡፡ ከሽምብራው ዛፍ ላይ ትንሽ ቅርንጫፍ ይቆርጥና ሌባውን ቅድመ አያታችንን ሶስት ጊዜ ያህል ሾጥ ሾጥ ያደርገዋል፡፡ ሌባው ወዲያውኑ ከዚህች ዓለም ይሰናበታል፡፡
   
   ቅድመ አያቶቻችን የሟቹን ደም ለመበቀል በርከት ብለው ጦርነት ሲያውጁ ደግሞ ሰባት ሀረላ ብቻ ይመረጥና ይላክባቸዋል፡፡ እነዚያም ሰባት ሀረላዎች ለጦርነቱ ቀስትም ሆነ ደጋን አይታጠቁም፡፡ አምስት ያህል ድንጋይ ብቻ ይይዙና ለውጊያ ይሰለፋሉ፡፡ ቅድመ አያቶቻችን ውጊያውን ሲጀምሩ ሀረላዎቹ ለጥቂት ጊዜ ቆም ብለው ያዩዋቸዋል፡፡ ቅድመ አያቶቻችን በአንድ ቦታ በርከት ሲሉላቸው ሀረላዎቹ አንዳንድ ድንጋይ ይወረውሩባቸዋል፡፡ አንዱ የሀረላ ድንጋይም አንድ ሻምበል ጦር (100 ሰው) ይገድላል፤ (ምክንያቱም የሀረላው ድንጋይ በኛና በቅድመ አያቶቻችን ስሌት መሰረት  የተራራ ቋጥኝ ነውና)፡፡ ቀሪው ጦርም ይህንን ሲያይ በፍርሃት ይበተናል፡፡
*****     *****   *****
      ሀረላ በጣም ሀብታም ነው፡፡ እያንዳንዱ ሀረላ ለመቶ ዓመት የሚሆነውን ቀለብ ቀደም ብሎ አጠራቅሟል፡፡ በየዓመቱ የሚያገኘውን አዲስ ምርት ለፈንጠዚያና ለፌሽታ ነው የሚያውለው፡፡ ሁሉም ያሰኘውን ነገር ስለሚያገኝ ገበያ ሄዶ መሸጥና መግዛት የለም፡፡
 
      ታዲያ የሀረላ ፌሽታ የዋዛ እንዳይመስላችሁ! በተለይ ሰርግ ሲሰረግ ከሙሽራው ቤት አንስቶ እስከ ሙሽሪት ቤት ድረስ እንጀራ ይነጠፍና ሰርገኞች በዚያ ላይ እንዲሄዱ ይደረጋል። የሰርጉ ታዳሚዎች እጃቸውን የሚታጠቡትም በወተት ነው።  ማርና ቅቤው ሀያ አራት ሰዓት ይበላል፡፡ ጭፈራና ዳንኪራው ይቀልጣል፡፡ በአጠገባቸው የሚኖሩትን አጫጭር ሰዎች (የኛ ቅድመ አያቶች) ሲመጡ ወደ ድግሳቸው አያስጠጓቸውም፡፡ በረሀብ ቢሞቱ እንኳ ዞር ብለው አያዩዋቸውም፡፡ በተለይ በአንድ ወቅት ሀይለኛ ረሀብ በሀገሩ ገብቶ አጫጭሬዎቹ ለእርዳታ ቢማጸኗቸው ሀረላዎች የሜሪ አንቷኔትን ለምን ኬክ አይበሉም? ዓይነት መልስ ሰጧቸው፡፡ እንዲያውም ጥርግ ብትሉንና ያለ አንዳች ቀለዋጭ በደስታ በኖርን! አሏቸው፡፡
 
   ቅድመ-አያቶቻችን በሀረላ ጭካኔ አዘኑ፡፡ እምባ ለእምባ ተራጩ! ወደ ፈጣሪ ጮሁ፡፡ ፍርድህን በቶሎ አሳየን! አሉት፡፡ ፈጣሪም ጸሎታቸውን ሰማቸው፡፡ ፍርዱንም እንደሚከተለው በየነ፡፡
   
       ሁሉም ሀረላዎች ለትልቅ ጉባኤ በመተሀራ ተሰበቡ፡፡ ጉባኤውንም አደረጉ፡፡ ከጉባኤው በኋላም እንደለመዱት ፌሽታቸውን ጀመሩ፡፡ በዚህን ጊዜም ከየት መጣህ የማይሉት እሳተ ጎመራ ፈነዳ፡፡ ምድር ተቀወጠች፡፡ ሀረላዎች ነደዱ፡፡ ለወሬ ነጋሪ እንኳ አንድ ሰው ሳይተርፍላቸው ሁሉም አለቁ፡፡
 
   በሀረላ ከርሰ መቃብርም ላይ የአሁኑ የመተሀራ (በሰቃ) ሀይቅ ፈለቀ፡፡ አንድ ጥቅም የሌለው መርዝ የሆነ ውሃ! ጥም የማይቆርጥ ለእርሻ የማይሆን ግም ውሃ!! ለምን እንደሆነ ታውቃላችሁ ግን? ሀረላዎች ያኔ ሲፈነጥዙ የሸኑት ሽንት እኮ ነው!! ግም አሲዳም ውሃ! ሽንተ ርጉማን ዘኮነ ዘብሄረ ሀረላ!! ወዘተ...ጂንኒ ጀቡቲ.......
  
------
አፈንዲ ሙተቂ
ነሐሴ 30/2005

Tuesday, September 3, 2013

==የእብድ ወሬዎች==




ጸሓፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ
-----------
ብዙ እብዶች አሉን አይደል? እስቲ ለዛሬ ደግሞ ከእብዶቻችን መንደር ያገኘኋቸውን አስደሳች ወሬዎች በጥቂቱ ጀባ ልበላችሁ::
------
ሼኽ ሙሐመድ ሻንቆ ሀይለኛ ቃሚ ነበር፡፡ ጫት በወስላ (መቶ ኪሎ የሚይዝ ዝርግ ኬሻ) ቢቀርብለት እንኳ እጨርሰዋለሁ ባይ ነበር፡፡ አንድ ቀን ሐዘን ቤት ሳለን ሼኽ ሙሐመድ ሽንቱን በድንኳኑ ውስጥ ለቀቀው፡፡ ሰው ደነገጠና “ሼኸ መሀመድ ምን ሆንክ” ቢለው
 
 “ሰዓት የለንም እኮ፤ አንዱ ሰዓት የሰለዋት ነው፤ አንዱ የመቃሚያ ነው፤ ታዲያ ጊዜ ከየት አግኝተን ነው ውጪ ወጥተን የምንጸዳዳው?”
------
“ሹቡሹብ” በጣም ቀብራራ ነው፡፡ የሰውነቱ ንጽህናና የልብሱ ጽዳት ሌላ ነው፡፡ አይኑን እንደ ሴት ይኳላል፡፡ በእጁ በርከት ያሉ አበባዎች፣ ቄጤማ፣ ጠጅ ሳር፣ ልዩ ልዩ ባለመዓዛ ቅጠሎች ወዘተ… ይዞ ነው የሚዞረው፡፡ በዚህም የተነሳ አዲስ ሰው እብድ መሆኑን ለማወቅ ይቸግረዋል፡፡

ታዲያ “ሹቡሹብ” ጉራው አይጣል ነው፡፡ በተለይ ጉራውን የሚያሳየው ግን ወደ ማክሰኞ ገበያ በሚመጡ ሴቶች ላይ ነው፡፡ አቤት ሲሰድባቸው! ደግነቱ “እናትሽን…ቅብጥርሴ…ጂንኒ ጀቡቲ” የመሳሰሉ መጥፎ ስድቦችን አይደለም የሚሳደበው ፡፡ የሴቲቱን ንጽህናና ስንፍና ነው በሚገባት ቋንቋ የሚነግራት (ሴቲቱን ቢያውቃት ባያውቃት ጉዳዩ አይደለም)፡፡ አንድ ቀን የገዛ አክስቴን እንዲህ ብሎአት እንደነበር አስታውሳለሁ!
Yaa bada ta buusaa sooggida hinqabne nyaattu (ይህች ጨው የሌለው ወጥ የምትበላ)
Yaa bada ta kurumbaa ajaawaa nyaattu  (ይህቺ የገማ ጥቅል ጎመን የምትበላ)
Yaa bada ta faxiiraa killee hinqabne nyaattu (ይህቺ እንቁላል የሌለው ፈጢራ የምትበላ)

 “ሹቡሹብ” ለከተማ ሴቶችና ከገጠር ለሚመጡ ሴቶች የሚወረውራቸው ስድቦች ይለያያሉ፡፡ ለከተማ ሴቶች የሚወረውራቸው ብዙም ሀይለ ቃል የለባቸውም፡፡ ከገጠር በሚመጡት ላይ ግን ይጨክናል፡፡ ለምሳሌ ከገጠር የሚመጡትን በግጥም ዘይቤ እንዲህ ብሎ ይሰድባቸው ነበር፡፡

Hin hinnattu (በሂና አትዋብ)
Hin hallattu (አትነቀስ)
Hin qayyattu (“ቀያ” አታድርግ”፤ እንዲህ ሲል የሀረርጌ ሴቶች  መጥፎ ጠረን እንዳይኖራቸው በልዩ ልዩ መዓዛማ ጭሳጭስ ሰውነታቸውን የሚያጥኑበትን ባህላዊ ድርጊት መግለጹ ነው፡፡ በአማርኛ ምን ይባላል? እስቲ ንገሩን?)
Hin dhiqattu (አትታጠብ)
Hin miiccattu (ልብሶቿን አታጥብ)
Hin kuullattu (አይኗን አትኳል)
Dhadhaa matarra hin kaayyattu (በቅቤ ጸጉሯን አታርስ)

   ሹብሹብ እንዲህ ብሎ ሲሳደብ መላው ገበያተኛ በሳቅና በሆይታ ነው የሚያጅበው፡፡ አዳዲስ ሴቶች ግን የሰውዬው ንጽህና ስለሚያደናግራቸው ፍዝዝ ብለው ነው የሚያዩት፡፡

ሹብሹብ አንድ ጊዜ “አሪፍ” ቢዝነስ ጀምሮ ነበር፡፡ ከምሽቱ ሶስት ሰዓት ገደማ በከተማው ጎዳና ላይ የሚመላለሱ በጎችና ፍየሎችን ይይዛቸውና “Namni Hoolaan irraa bade! Namni re’een irraa bade” (በግ የጠፋው! ፍየል የጠፋው) እያለ ይለፍፋል፡፡ የፍየሎቹ/በጎቹ ባለቤቶች ሲመጡ “Afaan waraabeessa fidi” ይላቸዋል፡፡ “ከጅብ ያስተረፍኩበትን ዋጋ አምጣ” ማለቱ ነው፡፡ የፍየሎቹ/በጎቹ ባለቤቶችም “ምን ገዶኝ! እንካ ይኸው” ይሉና ሽልንግ ወይም ብር ይሰጡታል፡፡

ታዲያ ሹብሹብ ቢዝነሱ በጣም ስለጣመው ብሩ በርከት እንዲልለት ፈለገ፡፡ በመሆኑም በጸሐይ መግቢያ ገደማ ብዙ በጎችን/ፍየሎችን እያባረረ ከሰው አይን በመሰወር በሶስት ሰዓት ገደማ ወደ ዋናው መንገድ እያወጣቸው “በግ የጠፋበት! ፍየል የጠፋው” እያለ መለፈፍ ያዘ፡፡ በዚህም ብዙ ብር ማግኘት ጀመረ፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ግን ነገሩ ተነቃበት፡፡ የከተማው ሰዎች ፍየሎቻቸውን/በጎቻቸውን ከጅብ ማስተረፋቸው ቀረና ትግሎ ከሹብሹብ ጋር ሆነ፡፡ በተለይ ብዙ ፍየሉችና በጎች የመበራቸው ከተሜዎች ለሹብሹብ ብር መገበሩ አንገሸገሻቸው፡፡ ሹብሹብን ራሱን እንደ ጅብ ፈሩት፡፡ በዚህም የተነሳ በርካታ ቤተሰቦች ልጆቻቸውን “ፍየላችንን ጅብ እንዳይበላው ቶሎ አስገባው” ማለታቸው ቀርቶ “ፍየላችንን ሹብሹብ ሳይይዝብን ቶሎ አስገባው” ማለት ጀመሩ፡፡
 
 “ሹብሹብ”ም በዚህ መንገድ ከዚያ ጣፋጭ ቢዝነስ ጋር ተቆራረጠ፡፡ እስከ እኩለ ሌሊት ፍየሎቻቸውን ከመንገድ ላይ ማስገባት የማያውቁ በርካታ ሰዎች ለሹብሹብ የሚከፍሉትን ብር ለመሸሽ ሲሉ ጸባያቸውን አስተካከሉ፡፡ የቤት እንስሳትን በጊዜ ከመንገድ ላይ ማስገባትም ተለመደ፡፡
-------
ለዛሬ በዚህ ይብቃኝ፡፡ ቀሪውን በሚቀጥለው ክፍል እለጥፈዋለሁ፡፡ ታዲያ እናንተም የምታውቁትን ማዋጣቱን እንዳትረሱ፡፡
በወዳጅነታችን እንሰንብት፡፡
አፈንዲ ሙተቂ