Thursday, May 29, 2014

“ሰይድ ኸሊፋ” ሲዘከር



ጸሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ
--------

ቃር ቃር የሚለውን የሰሞኑ የጭንቀት ሰቀቀን በምንፈልገው መጠን  እንድንጫወት ባይፈቅድልንም በተገኘችው አጋጣሚ ሩሓችን “ኢስቲራሓ” እንድታደርግ ልንፈቅድላት ይገባል፡፡ በዛሬ ውሎአችን የሚያናፍሰን ደግሞ አንጋፋው ሱዳናዊ ድምጻዊ ሰይድ ኸሊፋ ነው፡፡ ጉዞ ወደ ቢላድ- አስ-ሱዳን! ጉዞ ወደ ኻርቱም! ጉዞ ወደ ኡምዱርማን! ጉዞ ወደ ከሰላ፣ ጉዞ ወደ ዋዲ ሀልፋ፣ ጉዞ ወደ ገዳሪፍ፣ ጉዞ አል-ኡቤይድ! ጉዞ ወደ ኮርዶፋን! ዳይ!!
---------
ከየትኛው እንጀምር እንግዲህ! ሰውዬው በበርካቶቻችን አዕምሮ ውስጥ የገዘፈ ምስል ጥሎብን ያለፈ በመሆኑ “ከሀ እስከ ፐ” እያሉ ስለርሱ ማውራቱ ያስቸግራል፡፡ ለማንኛውም በካይሮ ከተፈጠረ አንድ ክስተት ብንጀምር ጥሩ ይመስለኛል፡፡

ዘመኑ ራቅ ብሏል፡፡ በ1940ዎቹ አጋማሽ ነው፡፡ እውቁ የካይሮ ዩኒቨርሲቲ ለዓለም አቀፍ ተማሪዎች በሰጠው የስኮላርሺፕ እድል በመጠቀም በርካታ ሱዳናዊያን በዩኒቨርሲቲው ይማሩ ነበር፡፡ ከነዚያ ወጣቶች መካከል አንዱ በሙዘቃ ትምህርት ቤት የተመደበ ጠይም ዘለግ ያለ ኮበሌ ነው፡፡ ያ ወጣት በቤተሰቡ ወደ ግብጽ የተላከው ህግ አጥንቶ ጥሩ ዳኛ እንዲሆን ነበር፡፡ እርሱ ግን በራሱ ፍላጎት ምርጫውን ወደ ሙዚቃ አዞረ፡፡ በመሆኑም በእውቁ የዐረብ ሙዚቃ አካዳሚ ሊማር ተመዘገበ፡፡ ወጣቱ ሱዳናዊ ሙዚቃን በሀገር ቤት ያንጎራጉር ነበር፡፡ በትምህርት ቆይታውም በሀርሞኒካ እየተጫወተ ጓደኞቹን ያዝናናል፡፡

   አንድ ቀን ዩኒቨርሲቲው ለተማሪዎቹ ባዘጋጀው ታላቅ የሙዚቃ ድግስ ላይ እንዲዘፍን የተጋበዘው ፈሪድ አል-አጥራሽ የተባለው የዘመኑ ታዋቂ ግብጻዊ ዘፋኝ በሰዓቱ ይመጣል ተብሎ ሲጠበቅ የውሃ ሽታ ሆኖ ይቀራል፡፡ አዳራሹን ከዳር እስከ ዳር ያጨናነቁት ተማሪዎች በትዕግስት ጠበቁ፡፡ ነገር ግን ፈሪድ አል-አጥራሽን የበላ ጅብ አልጮኽ አለ፡፡ በመጨረሻም በአዳራሹ የነበረው ታዳሚ በጩኸትና በፉጨት ንዴቱን መግለጽ ጀመረ፡፡ ታላቁን ዘፋኝ ሲጠባበቅ የነበረው መድረክም በንዴተኛ ተማሪዎች ረብሻ ትርምስምሱ ወጣ፡፡
  
   የዩኒቨርሲቲው መምህራንና ሰራተኞች የተማሪዎቹን ቁጣ ለማብረድ አልቻሉም፡፡ ይሁንና ከሱዳናዊው ወጣት ተማሪ ጋር ይቀራረብ የነበረው አንድ አስተማሪ ወጣቱን እየገፋ ወደ መድረኩ አስገባውና “ዝፈን” አለው፡፡ ወጣቱ ሙዚቃን ለራሱና ለጓደኞቹ መደሰቻ ያህል ነበር የሚጫወተው፡፡ ህዝብ በተሰበሰበት አዳራሽ ላይ ቆሙ መዝፈኑን ቢመኘውም በዚያ ዕድሜው በባዕድ ሀገርና በባዕድ ታዳሚ ፊት ምኞቴን አደርገዋለሁ የሚል ሀሳብ አልነበረውም፡፡ እስከዚያን ጊዜ ድረስ በህዝብ ፊት መዝፈንን አልተለማመደውም፡፡ ስለዚህ የአስተማሪው ግብዣ በፍርሃት ማጥ ውስጥ ወረወረው፡፡

ይሁንና ወጣቱ ግብዣውን “እምቢ” ብሎ ከመድረኩ ለመውረድ አልሞከረም፡፡ እንደዚያ ቢያደርግ በፈሪድ አል-አጥራሽ መቅረት የተቃጠሉት ተማሪዎች ቁጭታቸውን በርሱ ላይ የሚወጡ መሰለው፡፡ ከተማሪዎቹ ቁጣ ለመዳን ሲልም እንደ አቅሙ ዘፍኖ ከመድረኩ ለመውረድ ወሰነ፡፡ በመሆኑም በፍርሃት እየራደና እየተርበተበተ ማይክራፎኑን ጨበጠ፡፡ የአዳራሹ ጸጥታ “ረጭ” ሲልም በቀጭን ድምጽ “አል-ማምቦ ሱዳኒ” (የሱዳን ጭፈራ) እያለ ዘፋፈነ፡፡ በፈሪድ አል-አጥራሽ መጥፋት የበገኑት ተማሪዎች ድንገት በመድረኩ ላይ በተከሰተው ሱዳናዊ ወጣት የድምጽ ቅላጼ ተማረኩ፡፡ ወጣቱ ዘፈኑን ሲጨርስ በከፍተኛ የአድናቆት ጭብጨባ አዳራሹን ቀወጡት፡፡ ዘፈኑንም ደግሞ እንዲዘፍንላቸው ጠየቁት፡፡

ሱዳናዊው ወጣት የስድብ ናዳ እንጂ የአድናቆት ጭብጨባ አልጠበቀም ነበር፡፡ የተማሪዎቹ ምላሽ የአድናቆት ጭበጨባ ሲሆንበት ግን መንፈሱ መለስ አለለት፡፡ በፍርሃት መንቀጥቀጡንም አስወገደ፡፡ እናም ዘና በማለት “አል-ማምቦ ሱዳኒን” እየደጋገመ ዘፈነ፡፡ የአዳራሹ ታዳሚ ከፊት በበለጠ ጭበጭባና አድናቆት አሞገሰው፡፡

የሱዳናዊው ወጣት ገድል በዚያ መድረክ ብቻ አልተገደበም፡፡ ስለድምጹ ማማርና ስለ ቅላጼው የሰማው ሁሉ በድግስና በሙዚቃ ኮንሰርት እንዲዘፍንለት ይጋብዘው ጀመር፡፡ በዘመኑ በካይሮ የሚኖሩት ከመቶ ሺህ በላይ የሚሆኑ ሱዳናዊያንም ወጣቱን የሀገር አለኝታና መታወቂያ አድርገው ወሰዱት፡፡ በየአጋጣሚው በሚያዘጋጇቸው የሙዚቃ ድግሶችም ወጣቱን ቁጥር አንድ ምርጫ በማድረግ አስዘፈኑት፡፡

ያ ወጣት የሙዚቃ ትምህርቱን በሚገባ ካጠናቀቀ በኋላ በ1946 ገደማ ተመረቀ፡፡ በታሪክ ሙዚቃን በአካዳሚ ደረጃ ያጠና የመጀመሪያው ሱዳናዊ ሆኖ ተመዘገበ፡፡ ከምርቃቱ በኋላ ወደ ሀገሩ ተመለሰ፡፡
---------
ይህ ነው እንግዲህ የሰይድ ኸሊፋ የዘፈን ጥንስስ! በዚህ መንገድ ነው እንግዲህ ዝነኛው ሱዳናዊ የጥበብ ጉዞውን የጀመረው፡፡ ይሁን እንጂ ሰይድ ኸሊፋ በመነሻው ላይ በካይሮ የተቀዳጀውን ዝና በሀገሪቱ ለመድገም አልቻለም፡፡ እንዲያውም መጀመሪያ ላይ የሱዳን ህዝብ “ዘፈን ሳያውቅ እዘፍናለሁ ብሎ የተነሳ መደዴ” የሚል የጥላቻ ቅጽል ለጥፎለት ነበር፡፡ ይህም የተፈጠረበት ምክንያት ሰይድ ኸሊፋ ይዞት የመጣው አዲስ የአዘፋፈን ዘውግ እና የግብጽና የኑቢያ ሙዚቃዎች ውህድ የሆነው የዘፈኖቹ ቅኝት ለሱዳናዊያን ጆሮ እንግዳ በመሆኑ ነው፡፡ ሱዳናዊያን በወቅቱ የለመዱት የአንጋፋዎቹን የነ በሺር አባስንና የነ አሕመድ አል-ሙስጠፋን የአዘፋፈን ስልት ነው፡፡ በመሆኑም እንደ ካሊፕሶ እና ዲስኮ ሞቅ እያለ የሚጓዘው የሰይድ ኸሊፋ ዘውግ ለነርሱ አልጣማቸውም፡፡

  እያደር ግን ሁሉም ነገር መስተካከል ጀመረ፡፡ ሱዳናዊያን ከሰይድ ኸሊፋ ስልት ጋር ተላመዱ፡፡ ከጥቂት አመታት በኋላ “መደዴ ዘፋኝ” የተባለው ወጣት የሁሉም ሱዳናዊ አርቲስቶች ቁንጮ ሆኖ ተገኘ፡፡ በተለይም “ኢዘየኩም” የተሰኘው ነጠላ ዜማው በኦምዱርማን ሬድዮ ሲለቀቅ ሱዳናዊያን ከዳር እስከ ዳር በአንድ ልብ አደመጡት፡፡ ስለቤተሰብና ፍቅርና ክብር የሚዘምረውን ዘፈኑን የሱዳን ብሄራዊ ዘፈን እስኪመስል ድረስ ተቀባበሉት፡፡

በ1950ዎቹ አጋማሽ ላይ የሰይድ ኸሊፋ ዝና በአባይ ግርጌ ካሉት ግብጽና ሱዳን ተነስቶ የአባይ ምንጭ ወደሆነችው ወደ ኢትዮጵያ ተሻገረ፡፡ ኢትዮጵያዊያንም ዘፈኖቹን ከመስማት አልፈው በአማርኛ፣ በኦሮምኛና በሶማሊኛ ቋንቋዎች እየተረጎሙ ዘፈኑት፡፡ በዚህም መሰረት ምኒልክ ወስናቸው “ጃሩ አነ ጃሩ” የሚለውን ዘፈኑን “ትዝታ አያረጅም” በሚል ቀይሮት ተጫወተው፡፡ ጥላሁን ገሠሠ ደግሞ “ወጠነል ጀማል” የሚለውን ተወዳጅ ዜማውን በአማርኛ ቋንቋ “እዩዋት ስትናፍቀኝ” በማለት ተጫወተው፡፡
-----
1961፡፡ የማይረሳ ዓመት፡፡ ኢትዮጵያዊያን በድምጹ ብቻ የሚያውቁትን ታዋቂ ዘፋኝ ያዩበት ዓመት፡፡ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሤ መንግሥት ከሱዳን ሪፐብሊክ መንግሥት ጋር ባደረገው የባህልና የኢኮኖሚ ግንኙነቶች ማዳበሪያ ስምምነት መሰረት አንጋፋና ወጣት ድምጻዊያን የተካተቱበት የሱዳን የሙዚቃ ቡድን ወደ ኢትዮጵያ መጣ፡፡ ዝግጅቱንም በቀድሞው ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሤ ቴአትር (በአሁኑ ብሄራዊ ቴአትር) ማቅረብ ጀመረ፡፡ አሕመድ አል-ሙስጠፋ፣ በከር ሙስጠፋ፣ ኢብራሂም አውድ፣ ሳላህ ቢን ባዲያ እና ሌሎችም በታዳሚው ፊት ዘፈኑ፡፡ ከቆይታ በኋላ ግን ብዙዎች ሊያዩት የሚጓጉለት ሰይድ ኸሊፋ ወደ መድረኩ ተጋበዘ፡፡ አዳራሹ በአድናቆት ጭብጨባ ተናወጠ፡፡

ታዲያ ሰይድም ከህዝቡ ለተቸረው አድናቆትና ክብር አጸፋውን በአስገራሚ መልኩ መለሰ፡፡ በሁለት ሌሊቶች ውስጥ ያጠናቸውን የአማርኛ ቃላት ከዐረብኛ ጋር በማሰናኘት “ኢዘየኩም”ን እንዲህ ተጫወተው፡፡

 ኢዘየኩም ኬፍ ኢነኩም (2)
አነ-ሌ ዘማን ማ ሹፍቱኩም፡፡ (2)
“ጤና ይስጥልኝ እንደምን ናችሁ (2)
ከሱዳን መጣን ልናያችሁ” (2)
አነ ሌ ዘማን ማሹፍቱኩም፡፡

 በአዳራሹ የታደመው ኢትዮጵያዊ ተመልካች በሰማው ነገር እየተገረመ ጭብጨባውን አጠናክሮ ቀጠለ፡፡ በዚያች ቀን ተመልካቹን ለማስገረም ብቻ የተላከ ይመስል የነበረው ሰይድ ኸሊፋም ሌላ ዜማ ማከል አስፈለገው፡፡ እና ለሱዳናዊያን እንግዳ የሆነውን “ትዝታን” በተሰባበረ አማርኛ ተጫወተው፡፡ ተመልካቹም በሳቅ ፍርስ እያለ አጨበጨበለት፡፡
-------
አዎን! ሰይድ ኸሊፋ በኢትዮጵያዊያን ልብ ከነገሱ የሱዳን የኪነ-ጥበብ ፈርጦች መካከል ቀዳሚው ነው፡፡ “ሱዳን” ሲባልም ከሁሉ በፊት ለኛ ትዝ የሚሉን “ኢዘየኩም” እና የሰይድ ኸሊፋ የተሰባበረ አማርኛ ናቸው፡፡ ይህ አንጋፋ የጥበብ ፈርጥ በእጅጉ ከሚታወቅበት የምስራቅ አፍሪቃ ክልል ባሻገር በመካከለኛው ምስራቅ፣ በአውሮጳ እና በአሜሪካ ከፍተኛ ተወዳጅነትን ለመቀዳጀት በቅቷል፡፡ ለዚህ ይበልጥ የረዳው ደግሞ “ኢዘየኩም”ን በሄደበት ሀገር ቋንቋ ሁሉ ለመዝፈን የሚሞክር መሆኑ ነው፡፡ በመሆኑም እኛ “ጤና ይስጥልን፣ እንደምን ናችሁ” እያልን የምንዘምረው “ኢዘየኩም” በሀውሳ፣ በሰዋሂሊ፣ በእንግሊዝኛ፣ በጀርመንኛና በፈረንሳይኛ ቋንቋዎችም አቻ ትርጉሞች አሉት፡፡ ይህም ሰይድ ኸሊፋ ሙዚቃን ከመጫወት አልፎ የሌሎችን ቋንቋና ባህል ለማጥናት የነበረውን ጉጉት በአጭሩ ያስረዳል፡፡
------
ሰይድ ኸሊፋ እንደ ብሄራዊ መዝሙር ከሚዘፍነው “ኢዘየኩም” ባሻገር በመቶ የሚቆጠሩ ሌሎች ዜማዎች አሉት፡፡ በሀገራችን አድማጮች ዘንድ ተወዳጅ ከሆኑት ዜማዎቹ መካከል “ኢንቲ ያ ጀሚላ”፣ “ሐቢበተል በለዲያ”፣ “ወሽወሾ ሀምሳ”፣ “ጃሩ አነ ጃሩ”፣ ዚድኒ ሚን ደለክ ሺወይያ”፣ “አል-ዋሒድ ኸሊ ዓለል ዋሒድ”፣ “ተዓሊ ተዓሊ”፣ “ሳምባ”፣ “መሽጉል ባለኪ”፣ “ሲደ-ንናስ ሐደር”፣ “አህላ ገራም”፣ “ያ ዒቅደል ሉሊ” የመሳሰሉትን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ሰይድ ኸሊፋን በመላው ዓለም ተወዳጅ ያደረጉት ግን አራት  ዜማዎች ናቸው፡፡ እነርሱም  “ዘኑባ”፣ “ኢዘየኩም”፣ “አወድዳዕኩም” እና “አል-ማምቦ ሱዳኒ” የተሰኙት ናቸው፡፡

“ዘኑባ” የፍቅር ዜማ ነው፡፡ በዘፈኑ ውስጥ “ዘኑባ” የተባለላት ወጣት የኑቢያ ተወላጅ ናት፡፡ ሰይድ ለዚያች ወጣት “ሐረቀት ገልቢ መሐባታ” (ፍቅርሽ ልቤን አቃጠለው) እያለ ልመናውን ይደረድርላታል፡፡ “ዘኑባ ያ ቢንተል ኒል”ም ይላታል፡፡ “አንቺ ኒል (አባይ) ያበቀላት የኑቢያ ወጣት” ማለት ነው፡፡ ሰይድ ኸሊፋ ይህንን ዘፈን ወደ ኢትዮጵያ በመጣበት ወቅት “ዘነበች” እያለ በአማርኛ አዚሞታል፡፡ እርሱ “ቢንት ኢትዮጵያ፣ ዘነበች” እያለ ሲዘፍን ዘነበች ታደሰ (ጭራ ቀረሽ) ደግሞ ከርሱ ጎን ቆማ ትደንስ ነበር፡፡ 

   “ኢዘየኩም” የሰላምታና የናፍቆት መጠየቂያ ነው-ቀደም ብዬ እንደገለጽኩት፡፡ ታዲያ ሰይድ በዚህ ዘፈን የተጠቀመው “ኢዘየኩም” የተሰኘው ቃል ሰላምታን ከመግለጽ ባሻገር ትልቅ ታሪካዊ ፍካሬን ተሸክሟል፡፡ “ኢዘይ” (እንዴት) የሚለው ቃል መሰረቱ ዐረብኛ አይደለም፡፡ ይህ ቃል ከጥንታዊው የኑቢያ ቋንቋ ተወርሶ ከዐረብኛ ጋር የተደባለቀ ነው፡፡ በግብፅና በሰሜን ሱዳን ጠረፍ በሚነገረው የዐረብኛ ዘዬ ውስጥ ጉልህ ሆኖ ይሰማል፡፡ በኻርቱም አካባቢ በሚነገረው የዐረብኛ ዘዬ ውስጥ ግን የለም፡፡ የሰይድ ኸሊፋን ዜማዎች ያጠኑ ተመራማሪዎች እንደሚናገሩት ሰይድ ይህንን ቃል በዘፈኑ ውስጥ የተጠቀመው የናፍቆት ሰላምታን ከማስተላለፍ በተጨማሪ የጥንቷ ኑቢያ በታሪክ ውስጥ የነበራትን ሚና ለማስታወስ በሚል ነው፡፡

“አወድዳዕኩም” የተሰኘው ዘፈኑ ደግሞ የ“ኢዘየኩም” ተቃራኒ ነው፡፡ ሰይድ ኸሊፋ በዚህ ዘፈን “ልለያችሁ ነው፤ ልሰናበታችሁ ነው” ነው የሚለው፡፡ ብዙ ጊዜ ሙዚቃውን ለታዳሚዎቹ ሲያቀርብ ሁለቱን ዘፈኖች መክፈቻና መዝጊያ ያደርጋቸዋል (ማለትም በ“ኢዘየኩም” የተጀመረውን ዝግጅት በ“አወድዳዕኩም” ይዘጋዋል)፡፡ ሁለቱን ዘፈኖች የሚዘፍንበት ስሜትም እንደ ዘፈኖቹ ይለያያል፡፡ “ኢዘየኩም”ን በፍልቅልቅ ፈገግታና በደስታ ተሞልቶ ነው የሚጫወተው፡፡ “አወድዳዕኩም”ን ግን ጭንቅ ጥብብ እያለ ልብን በሚነካ ስልት ያስኬደዋል፡፡ አንዳንዴም አልቅሶ ታዳሚውን ያስለቅሳል፡፡ ታዲያ ሰውዬው ሰይድ ኸሊፋ ነውና ሁለቱም ያምሩለታል፡፡ በፈገግታ ሲፍለቅለቅም ሆነ ጉንጮቹን በእምባ ሲያርስ ታዳሚውን የመነቅነቅ ሀይሉ ከፍተኛ ነው፡፡
--------
ከሰይድ ኸሊፋ ታላላቅ ዘፈኖች መካከል ጉልህ ሆኖ የሚጠቀሰው “አል-ማምቦ ሱዳኒ” ነው፡፡ ቀደም ብዬ እንደገለጽኩት “አል-ማምቦ ሱዳኒ” በመድረክ ላይ የተጫወተው የመጀመሪያ ዜማው ነው፡፡ ሰይድ ኸሊፋ “አል-ማምቦ ሱዳኒን”ን በወጣትነቱ ሲጫወተው “እኛም ሀገር እንዲህ ዐይነት ተአምር አለና ተመልከቱ” ለማለት ያህል ነው፡፡ ከጊዜ በኋላ የዘፈኑ ግጥም በሙዚቃ ኤክስፐርቶች ሲጠና ግን በርካታ ተአምራትን አጭቆ የያዘ እንደሆነ ተደረሰበት፡፡  እስቲ ሙሉ ግጥሙን ልጻፍላችሁ፡፡
----- 
(አዝማቹ)
አል-ማምቦ ሱዳኒ
አልማምቦ ፊኪያኒ
ፊዑዲ ፊከማኒ
ወአጅመል አልሓኒ
ማምቡ….!
----
(1ኛ ተከታይ ግጥም)
ያ ሐቢበ መሕላኪ
አል-ማምቦ ፊጊናኪ
አል-ለሕኑ ኸልላኪ
ቲትማየሊ ፊኹጣኪ
ዐላ-አንጋሚል ማምቡ
----
አልማምቦ ሱዳኒ
---
(2ኛ ተከታይ ግጥም)
ያ ሐቢበ የዑዲክ
ያ ወርደ ፊኹዱዲክ
አድኔቲ መርዩዲክ
ሚን ቡክረ መውዑዲክ
የርጉስ በሃኪ ጀንቡ
-----
ዐላ አንጋሚል ማምቦ
-----
(3ኛ ተከታይ ግጥም)
ረንነት ኹጣኪ አል-ሓን
ያ ወርደ ፊ ቡስታን
አነ ቀልቢ ባት ሐይራን
ማካን ያሬት ማካን
ማዱግና ናር ሑብቡ
------
የውም ረግሰተል ማምቦ
------
(4ኛ ተከታይ ግጥም)
በረደን-ነሲም ያሌል
ያሡረይያ ናዲ ሱሄል
ኩል ኺል መዓህ ኸሊል
አነ ወሕዲ ጀመል-ሽሼል
ዐሰረል-ሀዋ ገልቡ
------
የውም ረግሰተል ማምቦ
-----

“ማምቦ” የላቲን አሜሪካ የጭፈራ ዐይነት የሚጠራበት ስም ነው እንጂ ኦሪጅናሌ የሱዳን ቃል አይደለም፡፡ ሰይድ ኸሊፋም ግጥሙን ሲጀምር በፈረንጆቹ ዘይቤ “ማምቦ” ብሎታል፡፡ በማሳረጊያው ላይ ግን ቃሉን ወደ ዐረብኛ በመጎተት “ማምቡ” አድርጎታል፡፡ ይህንንም ያደረገው አዝማቹን ከተከታዮቹ ግጥሞች ጋር ለማስማማት እንዲያመቸው ነው፡፡

  ተከታዮቹ ግጥሞች ባለ አምስት መስመር ናቸው (ስድስተኛው መስመር ዘፈኑን ለማሳመር የሚደጋገም መነባንብ ነው እንጂ የግጥሞቹ አካል አይደለም፤ ለዚህም ነው ለብቻው የጻፍኩት)፡፡ ከአምስቱ መስመሮች መካከል አራቱ በተመሳሳይ ፊደል ነው የሚያሳርጉት፡፡ በአምስተኛ መስመር ላይ ያሉት ሁሉም ስንኞች ግን “ቡ” በተሰኘው ፊደል ነው የሚያበቁት፡፡ ይህም ከአዝማቹ ጋር በሚጣጣም መልክ መሆኑ ነው (አዝማቹም ባለአምስት መስመር መሆኑን ልብ በሉ)፡፡

እንዲህ ዓይነት ግጥም በዘመናዊው ዐረብኛ ውስጥ የለም፡፡ በጥንታዊው ዐረብኛ (Classical Arabic) ግን የግጥሙን ውበት መጠበቅ ግዴታ ነው፡፡ ገጣሚዎች ስለስንኙ መልዕክት ብቻ ሳይሆን የግጥሙን ውበት በሚያበለጽጉ ቴክኒካዊ ጉዳዮችም ላይ ይጨነቃሉ፡፡ የያንዳንዱ ስንኝ ቃላትና ፊደላት ብዛት፣ ስንኙ ቤት የሚመታበት ሁኔታ፣ ከተከታይ ስንኞች ጋር ያለው ትስስር ሁሉ ትኩረት ይሰጠዋል፡፡ ሰይድ ኸሊፋም በአል-ማምቦ ሱዳኒ ውስጥ ያንጸባረቀው ይህንኑ ነው፡፡ (በነገራችን ላይ ቋንቋው የሱዳን ዐረብኛ ዘዬ ነው፤ ግጥሙ ግን በጥንታዊው ዐረብኛ ስልት ነው የተጻፈው)፡፡
--------
ሰይድ አሕመድ አል-ኸሊፋ በ1923 ከኻርቱም አጠገብ ከነበረችው “ሙንቀተ-ዲባባ” በተሰኘች መንደር ተወለደ፡፡ የመጀመሪያና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በኻርቱም ካጠናቀቀ በኋላ ለከፍተኛ ትምህርት ወደ ካይሮ ተላከ፡፡ በክፍል አንድ እንደጻፍኩት ሙዚቃን በካይሮ አሐዱ ብሎ ከጀመረ በኋላ ወደ ሀገሩ በመመለስ እስከ ህይወቱ ፍጻሜ ድረስ ተጓዘበት፡፡

  ሰይድ ኸሊፋ ከሌሎች ሱዳናዊ ድምጻዊያን የሚለይበት አንድ ገጽታ አለው፡፡ ይህም ከማንም ጋር ሳይዳበል በራሱ ጥረት ብቻ ከከፍተኛ ደረጃ ላይ ለመድረስ የበቃ የመጀመሪያው ድምጻዊ መሆኑ ነው፡፡ የጥንቱ የሱዳን ዘፋኞች ሙዚቃን የሚጀምሩት በሌላ ታዋቂ ዘፋኝ ጥላ ስር በመሆን ነው፡፡ ለጥቂት ጊዜ ከዋናው ዘፋኝ ጋር እየተጫወቱ ይቆዩና በህዝቡ ውስጥ መታወቅ ሲጀምሩ የራሳቸውን ነጻ ኦርኬስትራ ይመሰርታሉ፡፡ ሰይድ ኸሊፋ ግን “አል-ማምቦ” ሱዳኒን በካይሮ ከዘፈነበት ጊዜ ጀምሮ ራሱን ችሎ ለብቻው ነው የተጓዘው፡፡ በዚህም ከርሱ ኋላ ለመጡት በርካታ ድምጻዊያን አርአያ ሊሆን በቅቷል፡፡ ሰይድ ኸሊፋ ለዘፈኖቹ ዜማ የሚሰራው ለራሱ ነው፡፡ ብዙዎቹን ግጥሞች ግን ከሌሎች አርቲስቶች ነው የወሰደው፡፡ ከሰይድ ኸሊፋ የዘፈን ግጥሞች መካከል ብዙዎቹን የጻፉት ኢድሪስ ጀማል እና ሙሐመድ ዓሊ የተባሉ ገጣሚያን ናቸው፡፡

ሰይድ ኸሊፋ ሁለት ጊዜ አግብቷል፡፡ የመጀመሪያ ጋብቻው በፍቺ የተቋጨ ሲሆን በሁለተኛ ጋብቻው ከተጣመራት ሴት ጋር እስከ ህይወቱ መጨረሻ ድረስ ኖሯል፡፡ በዚህ ጋብቻም አራት ልጆችን አፍርቷል፡፡ ይሁንና ከልጆቹ መካከል አንዳቸውም በርሱ መንገድ አልተጓዙም፡፡
------
ሰይድ ኸሊፋ በህይወቱ መጨረሻ ላይ በልብ ህመም መሰቃየት ጀመረ፡፡ በሀገሩ ውስጥ ባሉ ክሊኒኮችና ሆስፒታሎች ለመታከም ሞከረ፡፡ ነገር ግን ከህመሙ ሊፈወስ አልቻለም፡፡ ወደ ዩናይትድ ስቴት እየተመላለሰ ቢታከምም ምንም ለውጥ ሊያገኝ አልቻለም፡፡ በሰኔ ወር 1993 (እንደኛ አቆጣጠር) የልብ ህመሙ ከጫፍ ላይ አደረሰው፡፡ የሱዳን ሪፐብሊክ መንግሥትም ነፍሱን ለማትረፍ ወደ ዮርዳኖስ ዋና ከተማ “አማን” ሰደደው፡፡ የዮርዳኖሱ አል-ኻሊዲ ሆስፒታል የህክምና ባለሙያዎችም በድንገት እጃቸው ላይ የወደቀውን ታላቅ የጥበብ ገበሬ ህይወት ለማትረፍ ተጣጣሩ፡፡ ነገር ግን ሁሉም ነገር በምድራዊ ሀይል የማይመለስ ሆነ፡፡ ያ ዝነኛ አርቲስት ሰኔ 26/1993 የመጨረሻ እስትንፋሱን ተነፈሰ፡፡ ሩሑ ለህክምና በሄደበት ሀገር ከስጋው ተለየች፡፡

በቀጣዩ ቀን አስከሬኑ ወደ ኻርቱም ሲመለስ የሱዳን ፕሬዚዳንት ዑመር ሐሰን አል-በሺርና ከፍተኛ ባለስልጣናት የጀግና አቀባበል አደረጉለት፡፡ ቀብሩም በመቶ ሺህ የሚቆጠር ህዝብ በተገኘበት ተፈጸመ፡፡
--------
ግንቦት 16/2006
ሸገር-አዲስ አበባ
-------
የመረጃ ምንጮች
1.      ሱዳን ትሪቢዩን ዌብሳይት
2.     ዐረብ ኦን ላይን ዌብ ሳይት
3.     የሱዳን ቴሌቪዥን ጣቢያ ያሰራጫቸው ፕሮግራሞች
4.     በሬድዮ ኦምዱርማን የተሰራጩ ፕሮግራሞች
5.     ሰይድ ኸሊፋ ያሳተማቸው አልበሞች
6.     ልዩ ልዩ የቃል መረጃዎች
  


No comments:

Post a Comment