Wednesday, May 14, 2014

“አንድ ሺህ አንድ ሌሊት”


 አፈንዲ ሙተቂ
------
  ከዐረቡ ዓለም የተገኘው ታላቅ የስነ-ጽሑፍ ቅርስ “አልፍ ለይላ ወለይላ” በመባል ይታወቃል፡፡ በቀጥታ ሲተረጎም “አንድ ሺህ አንድ ሌሊት” (1001 nights) እንደማለት ነው፡፡ ይህ መጽሐፍ ብዙዎች ያለመሰልቸት እየደጋገሙ ካነበቧቸው ድርሰቶች መካከል ይመደባል፡፡ በብዙ ቋንቋዎች ከተተረጎሙ ምርጥ መጻሕፍት መካከልም አንዱ ነው፡፡ በመጽሐፉ ውስጥ ካሉት የጀብድና የትንግርት ተረቶች መካከል በርካቶቹ የሌሎች ህዝብ ስነ-ቃል አካል እስከ መሆን ደርሰዋል፡፡

የ“አልፍ ለይላ ወለይላ” ታሪኮች በጥንት ዘመን በአፍ ሲነገሩ ነው የኖሩት፡፡ ከጊዜ በኋላ ግን ዐረቦች ታሪኮቹን በመጽሐፍ ሰብስበዋል፡፡ በመሆኑም የምዕራቡ ዓለም መጽሐፉን “Arabian Nights” በማለት ይጠራዋል፡፡ ይህ ማለት ግን ታሪኮቹ በሙሉ የዐረቦች ናቸው ማለት አይደለም፡፡ መጽሐፉን የመረመሩ ሊቃውንት የአልፍ ለይላ ወለይላ ተረቶች ከቻይና እስከ ግብጽ ድረስ ካሉት ህዝቦች የተገኙ መሆናቸውን አረጋግጠዋል፡፡ ከጥንታዊ የግሪክ ተረቶች ጋር የሚመሳሰሉ ታሪኮችም አሉበት፡፡

  ===የመጽሐፉ መነሻ===

“አልፍ ለይላ ወለይላ”ን ለመጀመሪያ ጊዜ በመጽሐፍ ያጠናቀረው ሰው በውል አይታወቅም፡፡ በታሪኮቹ አጻጻፍ ላይ የሚታየውን ልዩነት ያጠኑ ምሁራን መጽሐፉ በአንድ ደራሲ የተጻፈ ሊሆን እንደማይችል ይናገራሉ፡፡ በተጨማሪም ታሪኮቹ በተለያዩ የዐረብኛ ዘዬዎች የተጻፉ በመሆናቸው መጽሐፉ በአንድ ሀገር ብቻ የተጠናቀረ እንዳልሆነ ይወሳል፡፡ በብዙዎች ግምት መሰረት የመጽሐፉ ጥንስስ የተዋቀረው በኢራቅ ዋና ከተማ ባግዳድ ውስጥ ነው፡፡ መጽሐፉ የመጨረሻ ቅርጹን ያገኘው ደግሞ በግብጽ ነው፡፡

  ለመጀመሪያ ጊዜ ስለ ታሪኮቹ የተናገረው አል-መስዑዲ የሚባል ታዋቂ የዐረብ ታሪክ ጸሐፊ ነው፡፡ መስዑዲ በ947 ባጠናቀረው ኢንሳይክሎፒዲያ መሰል መጽሐፉ አራናዊያን “ሐዛር አፍሳና” (Hazaar Afsaana) በሚል ስያሜ የሚጠራ ተረቶችን የመጨዋወት ወግ እንደነበራቸው ተናግሯል፡፡ ይህም ዘወትር ማታ ማታ አንድ ሺህ ተረቶችን እየተረኩ የሚጨዋወቱበት ልማድ ነው (“ሀዛር አፍሳ” በፋርሲ ቋንቋ “አንድ ሺህ ተረቶች” ማለት ነው)፡፡ በመስዑዲ ዘገባ መሰረት ኢራናዊያኑ የሚጨዋወቷቸው ተረቶች ከኢራን፣ ዐረቢያ፣ ህንድና ግሪክ የተገኙ ናቸው፡፡ እንግዲህ የዐረቦቹ  “አልፍ ለይላ ወለይላ” የተፈጠረው የኢራናዊያኑ “ሃዛር አፍሳና”ን እንደ አርአያ በማድረግ ነው ተብሎ ይገመታል፡፡

===“ሻህረዛድ” እና “ሻህሪያር”===

የ“አልፍ ለይላ ወለይላ” ታሪኮች የተደረደሩት እንደ ሌሎች የተረት መጻሕፍት አይደለም፡፡ መጽሐፉ በቀዳሚነት የሁለት ገጸ-ባህሪያት ታሪክ ነው፡፡ ከነዚህ ገጸ-ባህሪያት መካከል አንዱ ሻህሪያር ይባላል፡፡ ሻህሪያር የአንዲት ሀገር ሱልጣን (ንጉሥ) ነበር፡፡ ይህ ሰው መጀመሪያ ካገባት ሚስቱ ጋር ሲኖር ሴቲቱ ከአንድ የርሱ ባለስልጣን ጋር ስትባልግ ይይዛታል፡፡ በዚህም የተነሳ ልቡ በሐዘን ይሰበራል፡ ሚስቱንም ያለ ርህራሄ ይገድላታል፡፡

   ሻህሪያር ሚስቱን በመግደል ብቻ ንዴቱ አልበረደለትም፡፡ “ሴቶች ታማኝ ፍጡራን አይደሉም፤ ከምድር ላይ መጥፋት አለባቸው” የሚል እምነት በልቡ አሳደረ፡፡ በመሆኑም በየቀኑ አዲስ ሚስት እያገባ አብሯት ካደረ በኋላ በማግስቱ ይገድላት ጀመር፡፡ በዚህ የጭካኔ መንገድ ብዙ ኮረዳዎች አለቁ፡፡ ታዲያ አንድ ቀን አዲስ ሚስት የሚመለምልለት ወዚር (ሚኒስትር) ለርሱ የምትሆን ልጃገረድ ቢያጣ ከቤቱ ቁጭ ብሎ መተከዝ ጀመረ፡፡ “ሻህረዛድ” የተባለችው ልጁ ያዘነበትን ምክንያት እንዲነግራት ስትጠይቀው የንጉሡን የጭካኔ አድራጎት አንድ በአንድ አጫወታት፡፡ በታሪኩ ልቧ የተነካው ሻህረዛድ የሌሎች ሴቶችን ህይወት ለመታደግ ራሷን ቤዛ ለማድረግ ወሰነች፡፡ በመሆኑም አባቷ ለንግሡ እንዲድራት ጠየቀችው፡፡ አባቷ ሀሳቧን ሊያስቀይራት ቢሞክርም እርሷ ግን ውሳኔዋን እንደማትቀለብስ ነገረችው፡፡ “ንጉሡን አግብቼ ጀብዱ ስሰራ ታየኛለህ” በማለትም አግባባችው፡፡ አባቷም በልበ-ሙሉነቷ ተገርሞ ለንጉሡ ሊድራት ተስማማ፡፡
    -------
    ንጉሥ ሻህሪያር አዲሱን ሚስት (ሻህረዛድን) አገባት፡፡ የመጀመሪያውን ቀን አብሯት ካሳለፈ በኋላ መሸ፡፡ ሁለቱ ጥንዶች ሊተኙ አልጋ ላይ ወጡ፡፡ ሻህሪያር “እንግዲህ ካሳደርኳት በኋላ ሊነጋጋ ሲል እገድላታለሁ” እያለ ሲያስብ ሻህረዛድ አንድ ቆንጆ ተረት ታወራለት ጀመር፡፡ ይሁንና ተረቱን ሳትጨርሰው “የቀረውን ነገ ማታ አጫውትሃለሁ፤ አሁን እንተኛ” አለችው፡፡ ሻህሪያር የተረቱን መጨረሻ ለማወቅ ስለፈለገ እርሷን የመግደሉን ሀሳብ ለሚቀጥለው ሌሊት አስተላለፈ፡፡

  በቀጣዩ ሌሊት ሻህረዛድ የጀመረችውን ተረት ካጠናቀቀች በኋላ ሌላ ረጅም ተረት ጀመረችለት፡፡ ሆኖም ተረቱን ልብ በሚያንጠለጥበት ቦታ አቋረጠችው፡፡ ለሻህሪያርም “አሁን ስለደከመኝ ልተኛ፤ የቀረውን በሚቀጥለው ሌሊት እጨርስልሃለሁ” አለችው፡፡ ሻህሪያርም የልቡን በልቡ አድርጉ ሃሳቧን ተቀበላት፡፡ “ነገ ከጨረሰችልኝ በኋላ እገድላታለሁ” በማለት ግድያውን አስተላለፈ፡፡ በሚቀጥለው ሌሊትም ሻህረዛድ የጀመረችውን ታሪክ ከጨረሰችለት በኋላ ሌላ አዲስ ታሪክ ታወጋለት ጀመር፡፡ ሆኖም ተረቱን ሳታጠናቅቀው “ነገ እጨርስልሃለው” አለችው፡፡ ሸህሪያርም የግድያ ውጥኑን ለቀጣዩ ሌሊት አስተላለፈ፡፡

    ሻህረዛድ “ቀጣዩን ነገ እጨርስልሃለው” ስትለው ሻህሪያርም “እሺ” እያለ የግድያ እቅዱን ሲያስተላልፍ አንድ ሺህ አንድ ሌሊቶች አለፉ፡፡ ሻህረዛድ አንድ ሺህ አንደኛውን ተረት ስታወራለት ከቆየች በኋላ “እስቲ እንደሚገድለኝ አያለሁ” በማለት ለነገ ሳትል መጨረሻውን ነገረችው፡፡ ይሁንና ሻህሪያር ድሮ ሲያደርግ እንደነበረው ሻህረዛድን አልገደላትም፡፡ ምክንያቱም እርሷ በየቀኑ ተረቱን ስታወጋለት የርሱም ልብ በየቀኑ እየተለወጠች በመሄድ ላይ ስለነበረች ነው፡፡ ልቡን የሞላው የጥላቻና የበቀል መንፈስ ቀስ በቀስ እየተጠረገ በፍቅርና ይቅር ባይነት ተተክቶ ነበር፡፡ በመሆኑም ድሮ ሲፈጸም የነበረውን የጭካኔ አድራጎት ለሻህረዛድ ከተናዘዘላት በኋላ ከርሷ ጋር በፍቅር ለመኖር ወሰነ፡፡
-------
ከላይ የቀረበው የመጽሐፉ አስኳል ታሪክ (frame strory) ነው፡፡ በዚህ ታሪክ መሰረት በመጽሐፉ የቀረቡትን 1001 ተረቶች የምታጫውተን ሻህረዛድ ናት፡፡ በመሆኑም እኛ አንባቢያን እንደ ሻህሪያር ሆነን ነው ታሪኮቹን የምናነበው ማለት ነው፡፡ ታዲያ ሻህሪያር እና ሻህረዛድ በእውነታው ዓለም የነበሩ ሰዎች ስለመሆናቸው እስከ አሁን ድረስ ማረጋገጫ አልቀረበለትም፡፡ ሆኖም የዓለም ህዝብ “ሻህረዛድ” የምትባለው ትውፊታዊ ንግሥት ያወራቻቸውን ታሪኮች በደንብ ያውቃቸዋል፡፡

No comments:

Post a Comment