Tuesday, August 20, 2013

===“ራብዓ አል-አደዊያ====


ጸሓፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ
----------------
“ራብዓ” ከሰሞኑ የግብጻዊያን ተቃውሞና የእልቂት ዜና ጋር ተያይዞ በሁሉም ዘንድ መነጋገሪያ ሊሆን የበቃ ስም ነው፡፡ ስያሜው በቀጥታ ሲተረጎም “አራተኛዋ” እንደማለት ነው፡፡ ይሁንና “ራብዓ” ከቁጥር አመልካችነቱ ባሻገር በደንብ የሚታወቀው በርካታ ሴቶች የሚጠሩበት ስም በመሆኑ ነው፡፡
   ዐረቦችም ሆኑ ሌሎች ሙስሊሞች ሴት ልጆቻቸውን በዚህ ስም መጥራታቸው እንግዳ ነገር አይደለም፡፡ በተለይ ግን “ራብዓ” የሚመረጠው የየቤተሰቦቹ አራተኛ ልጆች ለሆኑ ሴት ልጆች ነው፡፡ ታዲያ አራተኛ ልጃቸውን “ራብዓ” ብለው የሚሰይሙ ቤተሰቦች ሶስተኛ ልጃቸውን “ሣሊሣ” በማለት የሚጠሩበት ሁኔታ አይስተዋልም፡፡ አምስተኛ ልጃቸውንም “ኻሚሳ” የሚሉበት ዘይቤም እምብዛም አይታወቅም፡፡ ምክንያቱ ምንድነው? “ራብዓ” ቁጥር አመልካች ከሆኑት አቻዎቹ ይበልጥ ተመራጭ የሆነው ከጀርባው ምን የተለየ ነገር ቢኖረው ነው?
  *****  *****  *****
   መጠነ ሰፊውን የግብጽ አመጽ በአንክሮ የተከታተላችሁ ሰዎች እንደተረዳችሁት ለ“ኢኽዋነል ሙስሊሚን”  (Muslim Brotherhood) ማህበር አባላትና ለደጋፊዎቹ ለስድስት ሳምንታት ያህል የተቃውሞ ማዕከል ሀኖ ያገለገላቸው በምስራቃዊ ካይሮ የሚገኘው የራብዓ አል-አደዊያ መስጊድና በዙሪያው ይገኝ የነበረው ሰፊ አደባባይ ነው፡፡ መስጊዱ በስሟ የተጠራላት “ራብዓ አል-አደዊያ” የተባለችው ሴት በረጅሙ የእስልምና ታሪክ ውስጥ በቅዱስነታቸው የብዙዎችን ምስክርነት ካገኙ ሰዎች መካከል ትጠቀሳለች፡፡ የዚህች ሴት ገድል በበርካቶች ዘንድ የምርጥ ሴት የህይወት ተመክሮ ሆኖ ይዘከራል፡፡ “ራብዓ” የኖረችው ቀለል ያለ ሕይወትና ለአላህ የነበራት ገደብ የለሽ ፍራቻ (ተቅዋ) የምርጦች ምርጥ አስብሏታል፡፡ በህይወት ታሪኳ ዙሪያ ልዩ ልዩ ድርሳናት ተጽፈዋል፡፡
   “ራብዓ” የተወለደችው በደቡብ ኢራቅ በምትገኘው የበስራ ከተማ ነው፡፡ ዘመኑ ደግሞ እ.ኤ.አ. 717 ነው፡፡ ራብዓ ለቤተሰቧ አራተኛ ልጅ ናት፡፡ ቤተሰቡ እጅግ የተጎሳቆለ ኑሮ ይኖር ነበር፡፡ የቤቱ አባወራ ሲሞት የቤተሰቡ የጉስቁልና ኑሮ ተባባሰ፡፡ የልጆቹ እናትም ለተሻለ ኑሮ ፍለጋ ልጆቿን ይዛ ወደ ሌላ ከተማ ለመሰደድ ወሰነችና ከሲራራ ነጋዴዎች ጋር ጉዞ ጀመረች፡፡ ይሁንና ይህ ተጓዥ ቡድን በሽፍቶች እጅ ወደቀ፡፡ ሽፍቶቹም የገደሉትን ገድለው ንብረታቸውን ከዘረፉ በኋላ ምርኮኛ የሆኑትን በባርነት ሸጧቸው፡፡ “ራብዓ”ም በባርነት ከተሸጡት አንዷ ነበረች፡፡
    “ራብዓ”ን የገዛት ሰውዬ የልጅቷን የደም ግባትና የድምጻን ማማር በደንብ አስተዋለ፡፡ ስለዚህ በየሰርግ ቤቱና እና በየድግሱ  እየደነሰችና ሙዚቃ እየተጫወተች ገንዘብ እንድታመጣለት አደረጋት፡፡ በዚህም ከፍተኛ ገቢ ይዝቅባት ገባ፡፡ ራብዓ ይህንኑ ስራ እስከ ሰላሳዎቹ አጋማሽ ድረስ ቀጠለችበት፡፡ ሰላሳ ስድስት ዓመት ሲሆናት ግን ህይወቷ በቅጽበት ተለወጠ፡፡ አላህን መዘከር፣ ሌሊቱን በሰላት (ስግደት) ማሳለፍ፣ ቀኑን መጾም ወዘተ… የርሷ መለያዎች ሆኑ፡፡
    የዚህ ለውጥ ምንጭ በትክክል አይታወቅም፡፡ አንዳንዶች “ራብዓ በህልሟ ነቢዩ ሙሐመድን (ሰ.ዐ.ወ) በማየቷ ነው” ይላሉ፡፡ የርሷን የህይወት ታሪክ በሚዘግብ አንድ ፊልም ላይ እንዳየሁት ከሆነ ደግሞ አንድ ታዋቂ ሼኽ የያዘችውን ክፉ ጎዳና ትታ ጉዞዋን ወደ አላህ እንድታደርግ ሲመክራትና ሲገስጻት ነው የቀድሞ ኑሮዋን ትታ አዲስ የህይወት ጎዳና የጀመረችው፡፡
   ራብዓ ከሰላሳ ስድስተኛ ዓመቷ በኋላ እንደ ቀድሞው እየዘፈነች ለአሳዳሪዋ ብር ማስገኘቱን እንቢ አለች፡፡ በዚህ የተናደደው ጌታዋ ልዩ ልዩ ቅጣቶችን ይፈጽምባት ጀመር፡፡ ግርፋት፣ ከአቅም በላይ ማሸከም፣ እሾህ በተደረደረበት መንገድ ላይ ማስኬድና ሌሎችንም ድርጊቶች ፈጸመባት፡፡ ይሁንና ወጣቷ ከአቋሟ የምትመለስ አልሆነችም፡፡
   የራብዓ አሳዳሪ ሁሉንም ሞክሮ ሲሰለቸው ወደ ገበያ ወስዶ ሸጣት፡፡ ሁለተኛው ጌታዋ ግን በወጣቷ ጾምና ጸሎት ተማረከ፡፡ ወዲያው ነጻ እንድትወጣ አደረጋትና ለጋብቻ ጠየቃት፡፡ እርሷ ግን ለመልካም ምግባሩ ካመሰገነችው በኋላ አላህን ከመገዛት ውጪ ጋብቻ እንደማትፈልግ ነገረችው፡፡ ሰውየውም እንደፈቃዷ ትሆን ዘንድ ተዋት፡፡ (አንዳንድ ምንጮች ግን ራብዓ ባል አግብታ እንደነበር ያወሳሉ፤ ለምሳሌ የካቲት/መጋቢት 1985 የታተመው “ቢላል” መጽሔት “ራብዓ ባል ነበራት” ይላል)፡፡
  *****  *****  *****
“ራብዓ” የበርካታ አስደናቂ ወጎች ማዕከል ናት፡፡ በተለይ ከገድሎቿ መካከል ጎላ ብሎ የሚወሳላት አላህን ስለ ማምለክ የተናገረችው ነገር ነው፡፡ ታሪኩ እንዲህ ነው፡፡
   ሶስት መሻኢኾች (ሼኮች) ከራብዓ ጋር ይወያዩ ነበር፡፡ እናም ራብዓ “አላህን ለምንድነው የምናመልከው?” የሚል ጥያቄ አቀረበች፡፡ ሼኮቹ “ጀንነትን ስለምንፈልግና የጀሀነም እሳትን ስለምንፈራ ነው” የሚል ምላሽ ሰጡ፡፡ ራብዓ ግን “እኔ አላህን የማመልከው ዒባዳ (አምልኮ) የሚገባው ብቸኛ አምላክ በመሆኑ ነው፡፡ በትንሳኤ ቀንም የምፈልገው እርሱን መገናኘት ነው” በማለት ተናገረች፡፡
  *****  *****  *****
    በአንድ ወቅት አንድ ታዋቂ ዓሊም (ምሁር) ራብዓን ሊፈትናት ተነሳ፡፡ አመሻሽ ላይ ወደ ቤቷ መጣና “እኔ የታወቅኩ ወሊይ (ፃድቅ) ነኝ፣ ልዩ ልዩ ተአምራትን መስራት እችላለሁ” አላት፡፡ ራብዓም “ምን ዓይነት ተአምር ትሰራለህ?” አለችው፡፡
   “በውሃ ላይ በእግሬ እየተራመድኩ መሄድ እችላለሁ”
    “ይህንንማ እንቁራሪቶችም ያደርጉታል፤ ሌላ ምን ተአምር አለህ?”
    “በሰማይ ላይ መብረር እችላለሁ”
    “ይህም ወፎች በየደቂቃው የሚሰሩት ነገር ነው፡፡ ሌላስ?”
    “ጧት በጸሐይ መውጫ ሰግጄ ከሰዓት በጸሐይ መግቢያ ልታይ እችላለሁ”
    “አንተ እንዲያም ቀርፋፋ ነህ፤ ሸይጣን እኮ በትንሽ ጊዜ ነው ይህችን ምድር የሚያዳርሳት”
 ሰውዬው ተስፋ ቆርጦ “ታዲያ  ወሊይ መባል የምችለው እንዴት ነው?” በማለት ጠየቃት፡፡ ራብዓም “ወሊይ ማለት አላህ በቅዱስ ቃሉ እንደተናገረው በአላህ ያመነ እና እርሱን በእጅጉ የሚፈራ ሰው ማለት ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ሌላ አትጠብቅ” በማለት መለሰችለት፡፡
        *****  *****  *****
የራብዓ ታሪክ በጣም ሰፊ ነው፡፡ ኢንተርኔቱን ብትጎለጉሉ በርካታ መረጃዎችን ታገኛላችሁ፡፡ ታዲያ በራብዓ ስም ብዙ የፈጠራ ወሬዎችም የሚወሩ በመሆናቸው በታሪኮቹ ላይ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል፡፡ ሰላም!
       አፈንዲ ሙተቂ

No comments:

Post a Comment