Thursday, August 15, 2013

===አቤት በይ ካይሮ===


አወይ ካይሮ አወይ ቃሂራ!
የምፅራይም ፈርጥ የግብጽ የሚስራ
የዐረብ መዲና የከተሞች አውራ
የፈርኦኖች ዙፋን የስልጣኔ ሀድራ
የነፈርቲቲ ፍሬ የዚያች ክሊዎፓትራ
የናይል በረከት የአባይ ማረፊያ
የአል-ሱዩጢ ወንበር የአል-አዝሀር ጣቢያ፡፡

እነ ፈርኦን ኩፉ በፒራሚድ እንዳላስጌጡሽ
ቀብራራው ንጉሥ ኻፍሬ ስፊኒክስ እንዳልተከለብሽ
እን አምር አል-አስ በግንብ እንዳላጠሩሽ
እነ ሳላዲን አዩቢ ፍትሐዊ ፍርድ እንዳልሰጡብሽ
እነ ኢብን ኻልዱን በታሪክ እንዳልዘከሩሽ
እነ ነጂብ ማሕፉዝ “ኖቬላ” እንዳልቀመሩብሽ
ዛሬ ግን ተዋርደሽ የከተሞች ውራ ሆንሽ
አንቺም እንደ ባግዳድ በንጹሐን ደም ጨቀየሽ
እንደ ደማስቆ እና ካቡል በሬሳ ትርኢት ከረፋሽ፡፡

ካይሮ ምነው ጉዱ ይህንን ለምን ፈለግሽ
“ቃሂራ” ተናገሪ ይህንን እንዴት ተመኘሽ?

ጂኒ ወልደ ሰይጣን እንዴት ቢሆን ነው የነካሽ
የደም ግብር መክፈል ለምንድነው የጀመርሽ
ወዳጅ ጠላቱን ሁሉ እምባ በእምባ ያደረግሽ
የልበ ንጹሓን ልብ ክፉኛ የሰበርሽ

ካይሮ ምነው ጉዱ ይህንን ለምን ፈለግሽ
“ቃሂራ” ተናገሪ ይህንን እንዴት ተመኘሽ?

እኔ የሀረር ልጅ የኦሮሞ የኢትዮጵያ
በአባይ ፖለቲክ ሰበብ ባኮርፍሽም አንድ አጥቢያ
ከሳዳት ከሙባረክ ጋር ብገጥም እንካ ሰላንቲያ
የአፍሪቃ ኩራት መሆንሽ ሲታወሰኝ በ“ሲሪያ”
የዑለማ ሐድራነትሽ የአንቢያ የአውሊያ
የሐትሸፕሰት ውቅርነትሽ የፑንት ሚስጢር ማሰሪያ
የተውፊቅ አል-ሐኪም እናትነትሽ የተውኔቶቹ ማስተናበሪያ
ይህ ሁሉ ሲመላለስብኝ አዕምሮዬን ሲሞግተው
ፖለቲኩን እረሳና ከኩርፊያ እባንናለሁ
“ፖለቲክ ለፖለቲከኛ” እልና ያንቺ ቲፎዞ እሆናለሁ
ስላንቺ ታላቅነት ለማያውቁት እዘምራለሁ፡፡

የትላንቱ ግን ጉድ ነው ተመን የሌለው “ሙሲባ”
ለጠላቴም የማልመኘው እንኳን ላንቺ ለኔ አበባ
ህጻን ከሽማግሌ ያልለየ የደንታ ቢሶች ድብደባ
ሺዎችን በአንድ ጀንበር ትቢያ ያለበሰ ቅብቀባ
ዓለምን ያስበረገገ የወታደር ስለባ
ሚሊዮኖችን ያስመሸ አድርጎ እምባ በእምባ፡፡

ካይሮ ምነው ጉዱ ይህንን ለምን ፈለግሽ
“ቃሂራ” ተናገሪ ይህንን እንዴት ተመኘሽ?

አንቺ የአባይ ግርጌ የናይል ዞሮ ማረፊያ
የሀም ህዝቦች እምብርት የሴም ልጆች መኩሪያ
የኩሽ ልሳነ ምድር የሜምፊስ የኑቢያ
የዩሱፍ (ዮሴፍ) ገድል መዝገብ የሙሳ (ሙሴ) ብትር መሞከሪያ
ባንቺ የሚያምረው ጥበብ ነው የቅኔ መወድስ ዘረፋ
የእሳት ዳር ትረካዎች የወግ ኦሜጋና አልፋ
በበደዊ ተረቶች መሳቅ በዐረብ ትረባ መንፈቅፈቅ
በአንድ ሺህ አንድ ሌሊት (አልፍ ለይላ ወሌይላ) ግብዣዎች መፈንደቅ
“ደም” ነጃሳ ነው እርኩስ ነው ከመ ኢብሊስ (ዲያብሎስ)
ክብርሽን የሚደመስስ አውራነትሽን የሚገስስ
ጥበብሽን የሚሰለቅጥ ውበትሽን የሚያደበዝዝ
ሀይልሽን የሚያኮስስ ደረጃሽን የሚሰርዝ፡፡

ስለዚህ
ካይሮ ሆይ
አንቺ ፉስጣጥ አንቺ ቃሂራ
የምፅራይም ፈርጥ የግብጽ የሚስራ

የደም ግብሩን እምቢ በይ ሁለተኛ እንዳይለምድሽ
አምላክሽን ተማጸኚ በዚሁ በቃ እንዲልሽ
ወንዶችሽ አይለቁብሽ ሴቶችሽ አይዋረዱብሽ
ህጻናቱ ይቦርቁ ይፈንድቁ ይጫወቱብሽ
የባሩድ ሽታው ይወገድ አየርሽ ይጥራ ከአረር
አስፋልቱ ከደም ይንጻልሽ አደባባዩም ይሁን “ጧሂር”
ሀገሬው ወጥቶ ይግባ በአማን ዛፎችሽ ይለምልሙሽ  
ዛሬም ነገም ሁሌም የአላህ (አምላክ) ሰላም ይስፈንብሽ፡፡
-------
ግጥም፡ አፈንዲ ሙተቂ
ነሐሴ 9/2005
ፎቶ፡ Aljazeera English
መታሰቢያነቱ፡ ነሐሴ 8/2005 በካይሮ ከተማ ላለቁት በሺህ የሚቆጠሩ ግብጻዊያን ይሁን፡፡

No comments:

Post a Comment