Sunday, May 12, 2013

“አሚር ኑር ሙጃሂድ” እና “ጁገል” (ጀጎል)



 ጸሓፊ፡- አፈንዲ ሙተቂ

  የሀረር ከተማን ጥንታዊ ክፍል ለአምስት ምዕተ ዓመታት ከቦ የሚታየውን የጁገል (ጀጎል) ግንብ ያሰራው አሚር ኑር ሙጃሂድ ነው። የአሚር ኑር አባት ከኢማም አሕመድ ኢብራሂም አል-ጛዚ (ግራኝ) ሚኒስትሮች መካከል አንዱ የነበረው ወዚር ሙጃሂድ ዓሊ ሲሆን ይህ ሰው ኢማሙ ሐበሻን ለማቅናት ባደረገው ታላቅ ዘመቻ ውስጥ ቁልፍ ሚና ነበረው። በአንድ ወቅትም የቤጌምድር (ጎንደር) አስተዳዳሪ ሆኗል።
   የአሚር ኑር እናት የኢማም አሕመድ (ግራኝ) እህት ናት። ኢማሙ ከመሞቱ በፊት አሚር ኑርን በጣም ይወደውና  ከሌሎች ልጆችም የበለጠ ያቀርበው እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ። በዚህም የተነሳ አሚር ኑር ዘወትር ከኢማሙ አጠገብ አይጠፋም ነበር።
    ኢማም አሕመድ በ1543 ዓ.ል. በዘንተራ (ወይና ደጋ) ጦርነት ሲገደል አሚር ኑር ከዲል ወንበራ (የኢማሙ ሚስት) ጋር  በመሆን አስከሬኑን ካስቀበረ በኋላ ወደ ሀረር ተመለሰ። ከጥቂት ቆይታ በኋላ ዲል ወንበራን ለጋብቻ ሲጠይቃት የአጎትህን ደም ከተበቀልክልኝ ብቻ ነው የምታገባኝ አለችው። አሚር ኑርም ቅድመ ሁኔታውን ተቀብሎ ከአጼ ገላውዴዎስ ጋር ለመጋጠም ወደ ፈጠጋር (መካከለኛው ኢትዮጵያ) ዘመተ። ከአጼው ጋር ባደረገው ውጊያም በለስ ቀንቶት ድል አደረገ። አጼ ገላውዴዎስም በውጊያው ላይ ሞተ።
  አሚር ኑር በድል አድራጊነት ወደ ሀረር ሲገባ ከተማው በከፊል ተቃጥሎና ሱልጣን በረካት ዑመርዲን የሚባለውን የወላስማ ገዥ ጨምሮ በርካታ ሰዎች ተገድለው ጠበቁት። ይህንን ውድመት በከተማዋ ላይ ያደረሰው ራስ ሐመልማል የሚባለው የአጼ ገላውዴዎስ የጦር አበጋዝ (የአጼው የአጎት ልጅ) ነበር። አሚር ኑር የከተማዋን መቃጠል ሲያይ አንድ ነገር ማድረግ እንዳለበት አሰበና የከተማዋን ህዝብ ጌይ ሐምቡርጢ (የሀረር እምብርት) በሚባለው አካባቢ ለስብሰባ ጠራ። ከዚያምእንደዚህ ዓይነቱ ድንገተኛ ጥቃት ከተማችንን እንዳያጠፋት ለወደፊቱ ምን ማድረግ አለብን? የሚል ጥያቄ አቀረበ።
   እያንዳንዱ የስብሰባ ተሳታፊ የመሰለውን ተናገረ። አንዳንዶች የከተማዋን በቃ በእጥፍ መጨመር ይበጃል የሚል አስተያየት ሰጡ። ከፊሉም በርካታ መድፎችን ገዝተን በከተማዋ ዙሪያ ብናስቀምጣቸው ይሻላል አሉ። ይሁንና እነዚህ ሁሉ ለአሚር ኑር አልጣሙትም። በመጨረሻም ሸሪፍ አይደሩስ የሚባል ሰው ተነስቶ ከተማዋ ዙሪያ የግንብ አጥር ብንገባ ይሻላል በማለት ተናገረ። አሚር ኑርም በዚህኛው አስተያየት ስምምነቱን በመግለጽ ሁሉም የከተማዋ ነዋሪ ለሃሳቡ ተፈጻሚነት እንዲረባረብ ተዕዛዝ አስተላለፈ። በዚህም መነሻነት ዛሬ ጁገል (ጀጎል) የሚባለው የከተማዋ ግንብ ተወለደ።
  *****  *****  *****
  አሚር ኑር ጁገልን ያስገነባበት ዘዴ በሽማግሌዎች አንደበት ሲነገር በጣም ያስደምማል። በዚህ ላይ የሀረር ከተማ ታሪክ አዋቂዎች ያጫወቱኝን ወግ ከታች አወጋችኋለሁ። ወደዚያ ከመግባቴ በፊት ደግሞ ጁገል የማንንም አድናቆት የሚስብበትን አንዳንድ ውብ ገጽታዎቹን ዘርዘር ላድርግላችሁ፡፡
   ጁገል በሌሎች ስፍራዎች ከምናውቀው ማንኛውም ግንብ ጋር የማይመሳሰል መሆኑ የመጀመሪያው አስደናቂ ገጽታው ነው፡፡ ንድፉም ሆነ ኪነ-ህንጻው በየትኛውም ሀገር ካለ ተነጻጻሪ ግንባታ ጋር አይመሳሰልም፡፡ በሁለተኛ ደረጃም ጁገል ሙሉ በሙሉ ሀገር በቀል (domestic) ግብአቶችን ብቻ በመጠቀም የተሰራ መሆኑም ያስደንቃል፡፡ ከውጪ ሀገር የመጣ ብረትም ሆነ አርማታ፣ ሲሚንቶም ሆነ ገረጋንቲ  አይታይበትም (በምዕራባዊ ክፍሉ ላይ ጣሊያኖች በከፊሉ ከሰሩት የማሰማመሪያ ስራ በስተቀር)።
  ሶስተኛው ደግሞ የጭቃው ጉዳይ ነው፡፡ በጭቃና በድንጋይ ብቻ የተገነባ ግንብ በዝናብና በፀሀይ ሐሩር እንዳይፈራርስ የማጠናከሪያ ድጋፍ ይሻል፡፡ ቢያንስ ቢያንስ ተለስኖ በአሸዋ ይገረፋል፡፡ ጁገል ግን ልስንም ሆነ ግርፍ ሳይኖረው እስከ ዘመናችን ድረስ ቆይቷል (ከዚህ ጀርባ ያለውን ሚስጢር ከወደታች ትረዳላችሁ)።
  ጁገል በግንባታ ዘመኑ (16ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ) የነበረውን የምህንድስና ዕውቀት የሚናገር መሆኑም አራተኛው አስደናቂ ገጽታው ነው። ይህንን ለመረዳት ካሻችሁ ግንቡን በአትኩሮት ማየት ይጠበቅባችኋል፡፡ ለዚህም አንድ ምሳሌ ልስጣችሁ፡፡
   ጁገል የተገነባው ለጥ ባለ (ሜዳማ) መሬት ላይ አይደለም፡፡ ግንቡን መሀል ለመሀል ሰንጥቆ ከሚያልፈውና አሚር ኡጋ (የአሚር መንገድ) ከሚባለው ጎዳና ወዲያና ወዲህ ያለው የጁገል ውስጣዊ ከተማ በሙሉ አቀበትና ቁልቁለት ነው፡፡ በግንቡ ውስጥ ያሉት ቤቶችና መንገዶችም በዚህ ወጣ ገባ መሬት ላይ ነው የተደረደሩት፡፡ ታዲያ ከፍታውን ስትወጡና ስትወርዱ ዝናብ በሚጥልበት ወቅት የሚወርደው ጎርፍ ከግንቡ ውስጥ እንዴት ይወጣ ይሆን? የሚል ጥያቄ በአእምሮአችሁ መመላለሱ አይቀርም፡፡ የዚህን ጥያቄ ምላሽ በፍጥነት ማግኘት ካሻችሁ ግንቡን ከውጪ በኩል ማሰስ ይጠበቅባችኋል፡፡ ይህንን ወስናችሁ አሰሳችሁን በምታካሄዱበት ወቅት በጥቂት ሜትሮች የተራራቁ ቀዳዳዎችን ከግንቡ የታችኛው ጠርዝ ስር ትመለከታላችሁ። ቀዳዳዎቹ በክረምትም ሆነ በበጋ ፍሳሽ ስለማይታጣባቸው አገልግሎታቸውን ለማወቅ ነጋሪ አያሻችሁም፡፡ 
  አዎን! ከጁገል የሚፈሰውን ጎርፍና ከየቤቱ የሚወጣውን እጣቢ የሚያስወግዱት እነኝህ ቀዳዳዎች ናቸው፡፡ ሀረሪዎች ቀዳዳዎቹን ወራበ ኑዱል በማለት ይጠሯቸዋል፡፡ የጅብ ቀዳዳ እንደማለት ነው፡፡ ከጅብ ጋር ምን አገናኛቸውና ነው እንዲህ የተባሉት? ማለታችሁ አይቀርም መቼስ! እኔም ስያሜውን ስሰማ ግርታን ፈጥሮብኝ ነበር፡፡
   ሀረሪ ወዳጆቼ እንዳጫወቱኝና በዶ/ር ካሚላ ጊብ ከተዘጋጀው ጥናታዊ ጽሁፍ እንደተረዳሁት በአንድ ወቅት ጅቦች በነዚህ ቀዳዳዎች ወደ ጁገል ይገቡና አሰስ ገሰሱን ይለቃቅሙ ነበር፡፡ በዚህ ዘመን በቀዳዳዎቹ ወደ ጁገል የሚገባ  ወራባ (ጅብ) ባይኖርም የቀዳዳዎቹ ስም አልተቀየረም፡፡  
*****  *****  *****
 አሁን ከላይ የጠቀስኩትን የጁገል ግንባታ ጥበብ በትንሹ ላጫውታችሁ፡፡
  ጁገል የተገነባበት የድንጋይ አይነት "ሐሺ ኡን" ይባላል፡፡ ይህም በአማርኛ ቋንቋ የበሃ ድንጋይ ተብሎ የሚጠራው ነው፡፡ የሀረሪ  ሽማግሌዎች ሐሺ ኡን በጣም ቀለል ያለ በመሆኑ ለግንባታው እንደተመረጠ ያስረዳሉ፡፡ ይህም ሲባል ግንቡ ከተገነባ በኋላ ግድግዳው ሚዛኑን መጠበቅ አቅቶት እንዳይወድቅ ይታደገዋል ለማለት ነው፡፡
   ግንቡ የተገነባባቸው ድንጋዮች በመጠናቸው ተነባብረዋል፡፡ ማለትም ወደ ግንቡ መሰረት ተጠግተው ያሉት ድንጋዮች ተለቅ ይላሉ፡፡ የግንቡ ከፍታ ሲጨምር የድንጋዮቹ መጠንም እያነሰ ይሄዳል፡፡ በሁለት ትልልቅ ድንጋዮች መካከል ያለ ማንኛውም ክፍተት በአነስተኛ (ቁርጥራጭ) ድንጋዮች ተከድኗል:: ግንቡን ስትጠጉት ከድንጋይ በተጨማሪ የጣውላ ግንዲላዎች በድንጋዮቹ መካከል ተዘርግተው ትመለከታላችሁ። የሀረሪ ምሁራንና ሽማግሌዎች እንደሚናገሩት እነዚህ ጣውላዎች የግንቡን ውሃ ልክ የማስጠበቅ ሚና አላቸው።
   ከላይ እንደገለጽኩት ድንጋዮቹ በጭቃ ብቻ ነው የተጣበቁት፡፡ ጭቃው ግን ተራ ጭቃ እንዳይመስላችሁ፡፡ ይህንን መጽሐፍ በምጽፍበት ወቅት ትልቅ የመረጃ ምንጭ ሆነው የረዱኝ የሀረሪ ባህልና ታሪክ አዋቂ አቶ አብዱሰመድ ኢድሪስ እንደነገሩኝ ጭቃው ለሁለት ወራት እንዲብላላ ተደርጓል።
   ጭቃው የተዘጋጀበትን የአፈር ዓይነት ስታዩት በብዙ አካባቢዎች በስፋት የሚታወቀው ቀይ (መረሬ) አፈር ሊመስላችሁ ይችላል፡፡ አቶ አብዱሰመድ እንዳጫወቱኝ ይህኛው (ጁገል የተገነባበት) የአፈር አይነት ጀጀባ ይባላል። ግንቡ ተገንብቶ ካበቃ በኋላም የላይኛው ጠርዙ በራሳ በተሰኘ ሌላ የአፈር አይነት ተደምድሟል፡፡ ይህም የተደረገው በራሳ ሁለት ጥቅሞች ስላሉት ነው፡፡
   አንደኛ በራሳ አንዳች ነገር ቢዘራበት አያበቅልም። በመሆኑም ወፍ ዘራሽ አረምም ሆነ ሳር በግንቡ ጫፍ ላይ እየበቀለ ግንቡን ለጉዳት የሚዳርግበት ዕድል አነስተኛ ነው፡፡ ሁለተኛ በራሳ በዝናብ ጊዜ የሚወርደው ውሃ ወደ ውስጥ እየሰረገ በግንቡ ላይ አደጋ እንዳያደርስ ይታደገዋል (አፈሩ ዉሃ አያስተላልፍምና)። ታዲያ ሌሎች አደጋዎችን ለማስቀረትስ ምን ተደርጎ ነበር? በማለት ጠይቄም ነበር፡፡ አቶ አብዱሰመድ ኢድሪስ ጥያቄዬን የመለሱት አንድ ምሳሌ በመውሰድ ነው፡፡
   ሰዎች ለፍተው የገነቡትን ቤትና ሌሎችንም ግንባታዎች ከሚተናኮሉ ፍጡራን መካከል አንዱ ምስጥ ነው፡፡ ይህ ተራ የሚመስለው ትንሽዬ ፍጡር በአፈር የተሰራ ነገር ሲገጥመው በቀላሉ ዶግ አመድ የማድረግ ችሎታን ተክኗል። ታዲያ አቶ ምስጥ ጁገልን ወርሮ አደጋ እንዳያደርስበት የጥንቷ ሀረር ጌይ የግንባታ ሙያተኞች አስደናቂ ዘዴ ነበር የተጠቀሙት፡፡     
   ሽማግሌዎችና ታሪክ አዋቂዎች እንደሚናገሩት ምስጥ በእጅጉ የሚፈራው ዘመሚት (በእንግሊዝኛው አጠራር red ant) የሚባለውን ፍጥረት ነው። ስለዚህ ምስጥን ከጁገል አካባቢ ለማባረር ተመራጩ ዘዴ ዘመሚትን መጥራት ነበር፡፡ ይህንን ለማሳካት የተወሰደው እርምጃም ዘመሚቱ የሚወደውን እርጥብ አጥንት በግንቡ ዙሪያ በብዛት መቅበር ነው፡፡
   የዘመሚት መንጋ አጥንቱን ለመውረር በሚመጣበት ጊዜ የምስጥ መንጋ በስፍራው ሲክለፈለፍ ከታየው አጥንቱን ይተውና በምስጡ ላይ ይዘምታል፡፡ ከምስጦቹ ውስጥ በዘመሚት የተበላው ተበልቶ ከጥቃቱ የተረፈውም እግሬ አውጪኝ ብሎ ይፈረጥጣል። ምን ይሄ ብቻ! ምስጥ የሚባል ፍጥረት ዳግመኛ ወደዚያ አካባቢ ለመምጣት አይቃጣም፡፡
     ሀረሪ ሽማግሌዎች እንደሚናገሩት ይህ ተግባር የአንድ ወቅት ኩነት ብቻ ሳይሆን በተደጋጋሚ ጊዜያት ተፈጽሟል። ግንቡ በተገነባባቸው የመጀመሪያዎቹ ዓመታት ውስጥ በግንቡ ዙሪያ ፍተሻ ይካሄድና ምስጥ መሳይ ነገር ከተገኘ ከላይ በገለጽኩት መንገድ ዘመሚት ይጠራበት ነበር። ይሁንና ይህ ድርጊት ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ ቆሟል። ምክንያቱም ጭቃው በደንብ ድርቅ ብሎ ከጠነከረ በኋላ በምስጥ ይበላል ተብሎ ስለማይታሰብ ነው (ምስጥ አዳዲስ የቤት ግድግዳዎችን እንጂ የድሮ ቤቶችን እንደማያጠቃ ልብ ይሏል)።
*****  *****  *****
   የሀረሩ የጀጎል ግንብ (በሀረሪዎች አጠራር ጁገል) የተሰራበት ጥበብ ከብዙ በጥቂቱ ይህንን ይመስላል። በነገራችን ላይ አሚር ኑር ግንቡን አሰርቶ ካጠናቀቀ ከሁለት ዓመታት በኋላ ሞቷል። አሚሩ የሞተው በ1567 ዓ.ል. የአፍሪቃ ቀንድ ሀገራትን በከፍተኛ ሁኔታ ባጠቃው ታላቅ ረሃብና እርሱንም ተከትሎ በተከሰተው ወረርሽኝ ወቅት ነው። በዚያ አስከፊ የችጋር ወቅት ሰው ሰውን እስከ መብላት እንደደረሰ የታሪክ ድርሳናት ያወሳሉ። ይሁንና ዲል ወንበራ (የአሚር ኑር ባለቤት) ከዚያ መቅሰፍት ተርፋ ከአሚሩ በኋላ ለብዙ ዓመት ኖራለች። ከሞተችም በኋላ ከምትወደው ባለቤቷ ከአሚር ኑር አጠገብ ተቀብራለች።
  አሚር ኑር ጥንት ሞቷል። ሆኖም ጁገልን የመሰለ ድንቅ ማስታወሻ ትቶልናል። ይህ ግንብ ዛሬም እንደ ጥንቱ ሳይቀየር አለ። ግርማ ሞገስን ተላብሶ በከተማዋ መሃል ላይ ቀጥ ብሎ ቆሟል። እስከ አሁኑ ደቂቃ ድረስ የአሚር ኑርን ታሪክ ይናገራል።
*****  *****  *****
(አፈንዲ ሙተቂ፡ ሀረር ጌይ-የአስገራሚዋ ከተማ የኢትኖግራፊ ወጎች፡ 2004፡ ገጽ  129-134)

No comments:

Post a Comment