Tuesday, May 14, 2013

አሚር አብዱሸኩር ዩሱፍ- በሀረር


ከአፈንዲ ሙተቂ

    ሀረር ከ1647-1887 ዓ.ል. ድረስ በነበሩት ዓመታት ነጻ አሚሬታዊ ግዛት ነበረች። የዚህ አሚሬት መስራች ዓሊ ዳውድ የተባለ የጦር አበጋዝ ሲሆን አሚሬቱን የገዙት መሪዎች በሙሉ ከዚህ ሰው የዘር ሀረግ የተመዘዙ ናቸው። በመሆኑም ዓሊ ዳውድ በርሱ ስም የሚጠራው የሀረር የመጨረሻ ስርወ-መንግሥት (ሲልሲላ) መስራች ተደርጎ ይቆጠራል። ከዚህ የአሚር አሊ ዳውድ ሲልሲላ (Ali Ibn Dawud Dynasty) ከነገሱት የሀረር አሚሮች ስሙ ከፍ ብሎ የሚጠቀሰው መሪ አሚር አብዱሸኩር ዩሱፍ ነው። ምሁራን እንደሚናገሩት ከአሚር ኑር ሙጃሂድ ወዲህ እርሱን የሚስተካከል የሀረር ገዥ አልታየም። ይህ አሚር በስልጣን ላይ በቆየባቸው አስር ዓመታት (ከ1782-1792) እጅግ ስኬታማ ስራዎችን መስራቱ ተጽፏል።   

     አሚር አብዱሸኩር በስልጣን ላይ በቆየበት ዘመን ከፈጸማቸው ታላላቅ ተግባራት መካከል
·        በሀረር አሚሬትና በዙሪያው በሚኖሩት የኦሮሞ ማህበረሰቦች መካከል ያለውን ግንኙነት በሰላማዊና ጠንካራ መሰረት ላይ ማቆሙ
·        ልዩ ልዩ የትምህርት ተቋማትን በምስራቅ ኢትዮጵያ የተለያዩ ቦታዎች ማቋቋሙ
·        በአሚሬቱ መንግስት አወቃቀርና አሰራር ላይ ከፍተኛ የማሻሻያ እርምጃዎችን መውሰዱ እና እንደ ዲዋን (የአሚሬቱ ጽ/ቤት) እና ሲጂል (ሬጅስትራር) ያሉ ተቋማትን መመስረቱ
·        በእንፉቅቅ ሲጓዝ የነበረውን የሀረር ኢኮኖሚ ለማነቃቃት በወሰደው ቀረጥን የመቀነስ እርምጃ ሳቢያ የንግድ ፍሰቱ (trade volume) ከበፊቱ ሀያ እጥፍ ያህል ማደጉ
·        በሀረር ህዝብና በጎረቤት ማህበረሰቦቹ ዘንድ ያለው ተቀባይነት ከፍ ሲልም በባሌ (ዲሬ ሼኽ ሁሴን) የሚገኘውን መስጊድ ማሰራቱ
·        በኢፋት (ምስራቅ ሸዋ) የሚገኙትን አልዩ አምባና ሳር አምባ የሚባሉ የንግድ ማዕከሎችን በአሚሬቱ ስር ማስገባቱ ይጠቀሳሉ።
   
   አሚር አብዱ ሸኩር በዘመኑ ከነበሩት የአፍሪቃ ቀንድ አጼያዊና አካባቢያዊ ገዥዎች በበለጠ ሁኔታ ስሙን ከፍ ያደረገለትን ተግባር የፈጸመው በ1788 ዓ.ል. ነው። ይኸውም ከሶስት መቶ ዓመታት በፊት ጠፍቶ የነበረው የሀረር ገንዘብ የመስራት ጥበብ ዳግም እንዲያንሰራራ ማድረጉ ነው። በዚህም የሀረር አሚሬት በዘመኑ በራሱ ገንዘብ የሚገበያይ ብቸኛው የምስራቅ አፍሪቃ መንግሥት እንዲሆን አስችሏል (በዚያ ዘመን በአፍሪቃ ቀንድ ከነበሩት ሌሎች መንግሥታትና የአካባቢ አስተዳደሮች መካከል ከፊሎቹ በግብጽና በዐረቢያ ገንዘቦች ይገበያዩ ነበር፤ በተቀሩት ግዛቶች የሚኖሩት ህዝቦች ሸቀጥን በሸቀጥ ይለውጡ ነበር)።
  
    አሚር አብዱሸኩር በስራ ላይ ያዋለው ገንዘብ "አሽራፊ" የሚባል ሲሆን ይህም "መሐለቅ" በተሰኙ ሀያ ሁለት ሽርፍራፊዎች ይመነዘራል፡፡ ሰር ሪቻርድ በርተን ሀረርን በጎበኘበት ዓመት (1854) ያየውን ገንዘብ ሲገልጽ ገንዘቡ በአንድ በኩል ዷሪበተል ሀረር (የሀረር ገንዘብ) የሚል ጽሁፍ የያዘ ሲሆን በሌላ ጎኑ ደግሞ 1248 ዓመተ ሂጅራ የሚል ካሌንደር ተጽፎበታል ብሏል (1248 ዓመተ ሂጅራ የሚለው ገንዘቡ የታተመበት ዘመን ነው።   
******************************************
  
  ከላይ እንደጠቀስኩት አሚር አብሸኩር ዩሱፍ በሀረርና በአካባቢው ማህበረሰቦች መካከል ጠንካራ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ትስስርን ለመፍጠር ችሎ ነበር። በመሆኑም ከ19ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ጀምሮ በሀረር ዙሪያ ለነበሩት የኦሮሞና የሶማሊ ማህበረሰቦች የጎሳ መሪዎችን ሹመት የሚያጸድቀው የሀረሩ አሚር ነው። ለምሳሌ በሀረርጌ ኦሮሞ ህዝብ ዘንድ እስካሁን ድረስ የሚታወቁት ደሚን (ለነገድ መሪ የሚሰጥ) እና ገራድ (ለአንድ መንደር መሪ የሚሰጥ) የሚባሉት የማዕረግ ስሞች ከዚያ ዘመን የተወረሱ ናቸው።
    
  እነዚህ የጎሳ መሪዎች በየወረዳዎቻቸውና በየመንደሮቻቸው መፍትሔ ሊያበጁላቸው ያልቻሏቸውን የፍትሐ ብሄር ክርክሮች ወደ ሀረሩ አሚር ያስተላልፋሉ። የጎሳ መሪዎቹ በሚሰጡት ፍርድ ያልረካ ተሟጋችም እንደዚሁ ለሀረሩ አሚር ይግባኝ ይል ነበር።
******************************************
(አፈንዲ ሙተቂ: ሀረር ጌይ- የአስገራሚዋ ከተማ የኢትኖግራፊ ወጎች : ገጽ 171 እና ገጽ 224 )


References፡
1.     Mohammed Hassan: The City of Harar and the Spread of Islam among the Oromo in Harerghe 1999: pp 30-38፡
  1. Richard F. Burton፡ First Footsteps in East Africa, 1856, pp 345
3.     Ulrich Braukamper: Islamic History and Culture in Southern Ethiopia: 2004: pp 129-142 
4.     የሀረሪ አመጽ፡ 2000፡ ገጽ 26-27


No comments:

Post a Comment