Friday, December 26, 2014

ዶ/ር ተወልደን በጨረፍታ

ጸሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ
---
በኢህአዴግ ዘመን ሲያገለግሉ ከነበሩት የኢትዮጵያ መንግሥት ባለስልጣናት መካከል በህዝብ ዘንድ ከፍተኛ ከበሬታና ተወዳጅነት ያላቸው በፎቶው ላይ የምትመለከቷቸው ዶ/ር ተወልደ-ብርሃን ገብረእግዚአብሄር ናቸው፡፡ ዶ/ር ተወልደብርሃን በአካባቢ ጥበቃ ዘርፍ ላደረጉት ምርምርና በጉዳዩ ዙሪያ ከፍተኛ ግንዛቤ እንዲፈጠር ላደረጉት ጥረት በፈረንጆቹ 2000 ዓመት ዓለም አቀፉን የአቋራጭ ኖቤል ሽልማት (በትክክለኛ ስሙ Right Livlihood Award የሚባለውን) ተሸልመዋል፤ ይህንን ፎቶ የተነሱትም ሽልማቱን በተቀበሉበት ወቅት ነው፡፡ ዶ/ር ተወልደ በፈረንጆቹ 2006 ዓመትም የተባበሩት መንግሥታት በአካባቢ ጥበቃ ዙሪያ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላደረጉ ሰዎች የሚሸልመውን Champions of the Earth ሽልማት አግኝተዋል፡፡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲም በ1997 የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ሰጥቶአቸዋል፡፡


እኚህ ሰው የሀገራችንን የብዝሀ-ህይወት ኢኒስቲትዩት ከማቋቋማቸውም በላይ ሀገር ዝርያቸው ለመጥፋት የተቃረበ ሀገር በቀል ዛፎችን በሰፊው በማጥናት ለዘራቸው ጥበቃ የሚደረግበት የኢትዮጵያ ጄኔቲክ ባንክ እንዲመሰረት ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል፡፡ የሀገራችንን የአካባቢ ጥበቃ ፖሊሲ የቀየሱትም እርሳቸው ናቸው፡፡ በተጨማሪም ዶ/ር ተወልደ የአፍሪቃ ሀገራት የአሜሪካና የአውሮጳ ኩባኒያዎች ወደ ከባቢ አየር በሚለቋቸው በካይ ጋሶች ለሚደርስባቸው ጉዳት ተመጣጣኝ የካሳ ክፍያ እንዲጠይቁ ካስተባበሩት መሪዎች አንዱ ናቸው፡፡
----
ዶ/ር ተወልደ ብርሃን በትግራይ ክልል በአድዋ ከተማ አቅራቢያ ባለችው “አዲ-እስላም” የተሰኘች የገጠር መንደር ነው የተወለዱት፡፡ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በ1955 ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከተቀበሉ በኋላ የማስትሬትና ዶክትሬት ዲግሬአቸውን ከዌልስ ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል፡፡ ዶ/ር ተወልደ በ1970ዎቹ መጀመሪያ ላይ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሳይንስ ፋኩልቲ ዲን ሆነው አገልግለዋል፡፡ ከ1975 እስከ 1982 በነበረው ዘመን ደግሞ የአስመራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ሆነው ሰርተዋል፡፡ አስመራ በህዝባዊ ግንባር ሓርነት ኤርትራ (ሻዕቢያ) ስትከበብ ደግሞ ወደ አዲስ አበባ መጥተው በያኔው ካቢኔ ውስጥ የባህል ሚኒስቴር ምክትል ሚኒስትር ሆነው አገለገሉ፡፡ የደርግ መንግሥት ከተወገደ በኋላም ለብዙ ዓመታት በሚታወቁበት የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተርነት አገልግለዋል፡፡ ከጥቂት ዓመታት በፊት ከመንግሥት ስራ በጡረታ ተገልለው በግል ሙያ ላይ ተሰማርተዋል፡፡

  ይህንን ካልን ዘንዳ ዶ/ሩ የሚተቹበትን አንድ ነጥብ መጠቆም እንፈልጋለን፡፡ ከቅርብ ዓመታት ጀምሮ ከአውሮጳ የመጡ የአበባ አምራችና ላኪ ኩባኒያዎች ሀገራችንን አጥለቅልቀዋታል፡፡ እነዚህ አምራቾች አበባውን ወደ ውጪ ልከው የውጪ ምንዛሬ ማምጣታቸው ጥሩ ነገር ቢሆንም አበቦችን በማምረት ሂደቱ የሚጠቀሙባቸው ኬሚካሎች ከፍተኛ የአካባቢ ብክለትን የሚያስከትሉ መሆናቸው በልዩ ልዩ ምሁራን ሲገልጽ ቆይቷል፡፡ እነዚህ ኬሚካሎች በመሬት ውስጥ የሚኖሩ ጠቃሚ ነፍሳትን (micro organisms) ይገድላሉ ይባላል፡፡ የውሃ ዑደትንም እንደሚያዛቡ ይነገራል፡፡ በትነት መልክ እየቦነኑ አየሩን እንደሚበክሉም በሰፊው ሲጻፍ ቆይቷል፡፡ በዚህም የተነሳ በአበቦቹ ማሳ ዙሪያ የሚኖረው አራሽ ማህበረሰብ ጤናማ የምግብ ስርዓት እንደማይኖረው ተገልጿል (አንዳንዶቹ  ኩባኒያዎች በአካባቢ ላይ ሲያደርሱት በነበረው ጉዳት ምክንያት ከኬኒያና ከኡጋንዳ ተባረው መምጣታቸው በሰፊው ሲጻፍ የቆየ ጉዳይ ነው)፡፡

   ታዲያ “ዶ/ር ተወልደ የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣና ዳይሬክተር ሆነው እነዚህ ሀገር አጥፊ ኩባኒያዎች ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ እንዴት ፈቀዱ? ” የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ነው፡፡ እነዚህ ወገኖች “ዶ/ር ተወልደ በሌሎች መድረኮች ሲያሰሙት የነበረውን ድምጽ በነዚህ ኩባኒያዎችም ላይ ማሰማት ነበረባቸው” ባይ ናቸው፡፡ ይሁንና ዶ/ር ተወልደ በአንድ ወቅት በጉዳዩ ዙሪያ ከሪፖርተር ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ ነገሩን በቸልታ እንዳላለፉትና ኩባኒያዎቹን መቆጣጠሩ ከስልጣናቸው በላይ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ በጉዳዩ ዙሪያ እርሳቸውን ከሾመው መንግሥት ጋር ልዩነት እንደነበራቸውም አስታውቀዋል፡፡ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ የኬሚካሎቹን አጥፊነት ከመናገር እንዳልተቆጠቡም ተናግረዋል፡፡
------
ዶ/ር ተወልደ ብርሃን ገብረእግዚአብሄር የታዋቂው ደራሲ የስብሐት ገብረእግዚአብሄር ታናሽ ወንድም ሲሆኑ ባለቤታቸው ደግሞ እንግሊዛዊት ናት፡፡ በፌስቡክ የምናውቃት ገጣሚ ሮማን ተወልደም የርሳቸው ልጅ ናት፡፡ ጋሼ ስብሐት “ማስታወሻ” የሚል ርዕስ ባለው የዘነበ ወላ መፅሐፍ “ከተወልደ የሰማሁት ተረት ነው” ብሎ የገለጸውን እንጋብዛችሁና እናብቃ፡፡

  በአንዲት የገጠር መንደር ነው፡፡ አንድ ሰውዬ ከሩቅ ቦታ የመጣ የለቅሶ ድምጽ ይሰማል፡፡ ከዚያው ገደማ የመጣ ገበሬ ያይና “አንተዬ! ያቺ ሴትዮ ምን ሆና ነው የምታለቅሰው” በማለት ጠየቀው፡፡ ገበሬውም “እባክህ ተዋት! እርሷ ልጇ ሞታ ነው የምታለቅሰው፤ እኔ አለሁ አይደለም እንዴ ማረሻዬ ጠፍቶብኝ በፍለጋ የምንከራተተው” በማለት ያልጠበቀውን መልስ ሰጠው (ቂቂቂቂቂ… በጣም ነበር የሳቅሁት፤ ጋሽ ስብሐት እንዳለው ይህቺ ተረት ለዶ/ር ተወልደ ማስተር ፒስ ናት)፡፡
------
አፈንዲ ሙተቂ
መስከረም 6/2007
------
The writer, Afendi Muteki, is a researcher and author of ethnography and history with special focus on the peoples of East Ethiopia. You may follow him on his facebook page. Just click this link





Tuesday, December 23, 2014

እስላማዊ ኪነ-ህንጻ እና “ሲናን”ን በጨረፍታ




ፀሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ                                  
-----
በ7ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ የተጠነሰሰው እስላማዊ ኪነ-ህንጻ በአስራ አራት ክፍለ ዘመናት ውስጥ እያደገ ብዙ ፈርጆች ያሉት የጥበብ  ዘይቤ ሊሆን በቅቷል፡፡ በዓለም ዙሪያ ከፍተኛ አድናቆት የተቸራቸው ቋሚ ግንባታዎችንም አበርክቷል፡፡ በካይሮ ከተማ የሚገኘው የአል-አዝሃር መስጊድ፣ የደማስቆው “የበኑ ኡመያ” መስጊድ (the Omayyad Mosque)፣ የኢስታንቡል “ሱሌይማኒያ” መስጊድ፣ በኢስፋሓን የሚገኘው የኢማም አደባባይና መድረሳ (Midyyan-e-Imami)፣ የህንዱ ታጅማሃል፣ ታላቂ የቁርጡባ መስጊድ (Great Mosque of Cordoba)፣ የግሪናዳ ከተማ መከላከያ ግንብ (fortress) እና ልዩ ልዩ ግንባታዎች፤ የፌዝ ከተማ የመከላከያ ግንብና ጥንታዊው የቃራዊያን መስጊድ (ሞሮኮ)፣ ከጭቃ የተሰሩት የቲምቡክቱ መስጊዶች ወዘተ… ከተደናቂ እስላማዊ ግንባታዎች ጥቂቶች ናቸው፡፡




እስላማዊ ኪነ-ጥበብ ብዙ ፈርጆች እንዲኖሩት ያደረገው በባህሪው “ሆደ ሰፊ” በመሆኑ ነው፡፡ ይህም ሲባል ከሙስሊሙ ዓለም የተገኙት የኪነ-ህንጻ ጠቢባን በየሀገራቸው የነበሩትን ጥንታዊ የንድፍ ዘይቤዎች ከእስልምና መርሆች ጋር በማጣጣም አዳዲስ የኪነ-ህንጻ ዘይቤዎችን ይፈጥሩ ነበር ለማለት ነው፡፡ ለምሳሌ በኢስታንቡል ከተማ የሚገኙት ታላላቅ መስጊዶች የተሰሩት የጥንቱን የቤዛንታይን ኪነ-ህንጻ ከዐረቢያና ከፋርስ ኪነ-ህንጻ ጋር በማዋሃድ በተፈጠረው የቱርክ ኪነ-ህንጻ ዘይቤ ነው፡፡ የቲምቡክቱ መስጊዶችም የማሊን ጥንታዊ የኪነ-ህንጻ ጥበብ መሰረት በማድረግ ነው የተሰሩት፡፡

ጥንት ከተገነቡት እስላማዊ ቅርሶች መካከል ከፊሎቹ ጠፍተዋል፡፡ ግማሽ ያህሉ ግን ዛሬም ቋሚ ሆነው ታሪክን ይመሰክራሉ፡፡ በእስላማዊ ግንባታዎቻቸው በዓለም ዙሪያ የተደነቁት ከተሞች የሚከተሉት ናቸው፡፡

1.      መካ
2.     መዲና
3.     እየሩሳሌም
4.     ባግዳድ (ኢራቅ)
5.     ሰመራ (ኢራቅ)
6.     ቡኻራ (ኡዝቤኪስታን)
7.     ሰመርቀንድ (ኡዝቤኪስታን)
8.     ደማስቆ (ሶሪያ)
9.     ኢስታንቡል (ቱርክ)
10.    ሂራት (አፍጋኒስታን)
11.     መዘር-ኢ-ሸሪፍ (አፍጋኒስታን)
12.    ቁርጡባ (ስፔን)
13.    ግሪናዳ (ስፔን)
14.    ካይሮ (ግብጽ)
15.    ሰንዓ (የመን)
16.    ዘቢድ (የመን)
17.    ፌዝ (ሞሮኮ)
18.    መራኪሽ (ሞሮኮ)
19.    ቱኒስ (ቱኒዚያ)
20.   ቲምቡክቱ (ማሊ)
21.    ጄኔ (ማሊ)
22.   ሀረር (ኢትዮጵያ)
23.   ዛንዚባር (ታንዛኒያ)
24.   ኒሻፑር (ኢራን)
25.   ኢስፋሓን (ኢራን)
26.   ሺራዝ (ኢራን)
27.   ቴህራን (ኢራን)
28.   ጠብሪዝ (ኢራን)
29.   ዴልሂ (ህንድ)
30.   አግራ (ህንድ)
---
እስላማዊ ኪነ-ህንጻ ሲጠቀስ በቀዳሚነት ከሚወሱት ጠቢባን መካከል አንዱ ከ1489 እስከ 1588 የኖረው ቱርካዊው “ሲናን” ነው፡፡ ቱርኮች ይህንን ሰው ሲጠሩት “ኮጃ ሚማር ሲናን”፣ ማለትም “ታላቁ አርክቴክት ሲናን” ይሉታል፡፡ ችሎታውን ሲገልጹም “እርሱን የመሰለ የኪነ-ህንጻ ጠቢብ አልተፈጠረም” ነው የሚሉት፡፡ በርግጥም በመቶ የሚቆጠሩ “እጹብ ድንቅ” የተባሉ ስራዎቹን ያየ ሰው በከፊልም ቢሆን የቱርኮችን አባባል መጋራቱ የማይቀር ነው፡፡

 “ሲናን” የተወለደው “አጊርናዝ” በተባለች የቱርክ አነስተኛ ከተማ ነው፡፡ በልጅነቱ በአባቱ ስር የአናጺነትና ድንጋይ የማሳመር ጥበብን ተማረ፡፡ አንድ ቀን ግን ህይወቱን የቀየረ አጋጣሚ ተፈጠረ፡፡ በዚያ ቀን (በ1521) የኦቶማን ቱርክ ወታደራዊ ኦፊሰሮች ወደ ሲናን መንደር ሄደው ለውትድርና የሚቀጠሩ ወጣቶችን ይመዘግቡ ነበር፡፡ የሲናን ወታደራዊ አቋም የሚያመረቃ ሆኖ ስለተገኘ እርሱንም መዘገቡትና ወደ ቁስጥንጥንያ (የአሁኗ ኢስታንቡል) ወሰዱት፡፡ እዚያም ልዩ ልዩ ትምህርቶችን እንዲያጠና አደረጉት፡፡

የሲናን የጥበብ ተሰጥኦ መታየት የጀመረው በ1530 ድልድዮችንና ልዩ ልዩ ወታደራዊ ግንባታዎችን መስራት ሲጀምር ነው፡፡ በ1539 ግን ከውትድርናው ዓለም ተሰናብቶ የሲቪል ግንባታዎችን ጀመረ፡፡ በቀጣዮቹ 40 ዓመታትም ቱርክን በዓለም ዙሪያ ያስጠሯትን የልዩ ልዩ ግንባታዎችን ንድፍ እየወጠነ በራሱ አመራር በማስገንባት ለአግልግሎት አበቃ፡፡

ሲናን በህይወት ዘመኑ 79 መስጊዶችን፣ 34 ቤተ መንግሥቶችን፣ 33 የህዝብ የመታጠቢያ ገንዳዎችን (በተለምዶ “Turkish bath የሚባሉት)፣ 19 የመቃብር ስፍራዎችን፣ 55 ትምህርት ቤቶችን፣ 16 የድኾች መኖሪያ ማዕከላትን፣ 7 የከፍተኛ ደረጃ መድረሳዎችን፣ 12 ታላላቅ ምግብ ቤቶችን ሰርቷል፡፡ የፍሳሽ መውረጃዎች፣ ፋውንቴኖች፣ ሆስፒታሎችና ሌሎችንም ገንብቷል፡፡ የሁሉንም ግንባታዎች ንድፍ (ዲዛይን) የሰራው ራሱ ሲሆን በመሃንዲስነት አስጀምሮ የሚጨርሰውም እርሱ ነበረ፡፡

ከሲናን ግንባታዎች መካከል በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሱት የሱሌይማኒያ መስጊድ (በፎቶው ላይ ያለው)፣ የሻሕ ዛድ መስጊድ እና የሰሊም መስጊድ ናቸው (የመጀመሪያዎቹ ሁለቱ በኢስታንቡል ነው የሚገኙት፤ የሰሊም መስጊድ ግን በኢድሪን ከተማ ነው የተሰራው)፡፡ ሲናን የኔ ምርጥ ስራ ነው የሚለው “የሻህ ዛድ መስጊድ”ን ነው፡፡ የኪነ-ህንጻ ጠበብት በጣም የሚያደንቁት ግን የሱለይማኒያ መስጊድን ነው፡፡
----
አፈንዲ ሙተቂ
ህዳር 6/2007
----
The writer, Afendi Muteki, is a researcher and author of the ethnography and history of the peoples of East Ethiopia.  You may like his facebook page and stay in touch with his articles and analysis: Just click the following link to go to his page.

Monday, December 22, 2014

ሁለት ትራጄዲ ተረቶች





ፀሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ


-----
በህይወት እስካለን ድረስ ተረት መተረታችንን አናቆምም፡፡ እነሆ ለዛሬም በምሥራቁ የሀገራችን ክፍል እየተደጋገሙ የሚነገሩ ሁለት ትራጄዲ ተረቶችን አዘጋጅተንላችኋል፡፡

===የተንኮል ገበቴ===

እናት አንድ ልጅ ብቻ ነበራት፡፡ ይህንንም ልጅ በብዙ ልፋት ካሳደገችው በኋላ ለአቅመ አዳም ሲደርስ ዳረችው፡፡ ታዲያ የልጁ ሚስት እናትዬውን የምትወድ አልነበረችም፡፡ በብዙ አድራጎቷ ትበድላታለች፡፡ ይብስ ብሎ ደግሞ እናትየዋ ታወረች፡፡ ሚስትም በደሏን አጠናከረች፡፡ በተለይም ሴትዮዋን በጣም የምትበድለው ለእናትዮዋ በምታቀርበው ምግብ ነው፡፡

 ለምሳሌ ለእራት ገንፎ ስታቀርብላት ባሏም ሆነ ሌላ ሰው ዐይኑን እንዳይጥልበት በገንፎው ላይ ቅቤ ትጨምርበታለች፡፡ ነገር ግን ቅቤው ወደ መሬት እንዲፈስ ገንፎው የሚቀርብበትን ገበቴ በአንድ በኩል በስታዋለች፡፡ ልጁ እናቱ ገንፎ በቅቤ የበላች ስለሚመስለው ሚስቱን አይናገራትም፡፡ ሆኖም ገንፎው ቀስ እያለ ወደ መሬት ስለሚፈስ እናትዮዋ አታገኘውም (እናትዮዋ ዐይነስውር መሆኗን አስታውሱ)፡፡

ዘመን አለፈ፡፡ የልጁ እናትም አረፈች፡፡ ልጅየውም ካገባት ሚስቱ አንድ ልጅ ወልዶ ሞተ፡፡ የትናንትናዋ ሚስት የአዲሱ ልጅ እናት ሆነችና ከልጇ ጋር መኖር ጀመረች፡፡ ልጇ ለአቅመ አዳም ሲደርስ እርሷም በተራዋ ከአንዲት ወጣት ጋር በጋብቻ እንዲጣመር አደረገችው፡፡ ሶስቱ ሰዎች በአንድ ላይ መኖር ጀመሩ፡፡ እናት ስታረጅ እንደ ትልቋ እናት (የሞተችው የቧላ እናት) ታወረች፡፡ አንድ ቀን ምግብ ሲቀርብላት ገንፎው ቅቤ የሌለው ሆነባት፡፡ ወዲያውኑ የሆነ ነገር ትዝ አላትና ገበቴውን መዳበስ ጀመረች፡፡ በርግጥም እንደጠረጠረችው ገበቴው በአንድ በኩል የተበሳ ሆኖ አገኘችው፡፡ እናም ድሮ ስትፈጽመው የነበረውን በደል በማስታወስ ከልቧ አዘነች፡፡ እንዲህም አለች፡፡

“አይ ገበቴ! አይ ገበቴዋ! ከምኔው ዞረሽ ወደኔ መጣሽ?!! ግድ የለም፡፡ የእጄን ነው ያገኘሁት፡፡ ያኔ የባሌን እናት ባልበድል ኖሮ ዛሬ ምግቤ እኔ በቀደድኩት ገበቴ ባልተሰጠኝ ነበር”

የሴትዮዋ ንግግር ከልጁ ሚስት ጆሮ ጥልቅ አለ፡፡ እናም ሚስት በሰማችው ነገር ሽምቅቅ አለች፡፡ “ለካስ የኔም የወደፊት እጣ በዚህች ገበቴ መብላት ነው?” እያለች አሰላሰለች፡፡ ወዲያውኑ የባሏን እናት ይቅርታ ጠይቃ ያቺን የተንኮል ገበቴ እንክትክት አድርጋ ሰባበረቻት፡፡ እናትም ምግባቸው በጤነኛ ገበቴ ይቀርብላቸው ጀመር፡፡

===ሁለቱ አባቶችና ሁለቱ ልጆች===

ልጅና አባት አብረው ይኖሩ ነበር፡፡ አባት ልጁ ትዳር እንዲይዝ ካደረገው በኋላ ሁሉንም ነገር አስረከበው፡፡ ለራሱም ጡረተኛ ሆኖ ከልጁ ቤት ጀርባ ከነበረች አንዲት አነስተኛ ጎጆ መኖር ጀመረ፡፡ ይሁንና አባትዬው በጸባዩ ነጭናጫ ነው፡፡ በተለይ ልጅ ለስራ ወደሌላ ቦታ በሚሄድበት ጊዜ የልጁን ሚስት በሆነ ባልሆነው ይነዘንዛታል፡፡ ሚስትም በንጭንጩ ተማረረችና ባሏ ሲመጣ “ወይ አባትህን ከዚህ ቤት አርቅልኝ፤ ወይ ደግሞ ፍታኝ” አለችው፡፡

ልጁ ወደ አባቱ ሄደና “አባቴ! እዚህ ቤት ስትኖር አፍህን ዝጋልኝ!! ካልሆነ ግን ወደ ገደል እወረውርሃለው” በማለት አስጠነቀቀው፡፡ አባትም “አረ አትወርውረኝ! ከእንግዲህ አፌን እይዛለሁ” በማለት ተማፀነው፡፡ በመሆኑም አባት ከነርሱ ጋር መኖሩን ቀጠለ፡፡ ነገር ግን አባት ቃሉን ሊያከብር አልቻለም፡፡ ልጁ ከቤት እስኪወጣ ጠብቆ ሚስትዬውን ይጨቀጭቃት ገባ፡፡ በዚህ የተናደደችው ሚስት ወደ ባሏ ሄዳ “ነገ አባትህን ከዚህ ቤት ካላስወጣህልኝ እሄድልሃለሁ” አለችው፡፡ ባልም “ግድ የለም! ነገ ገደል ውስጥ እጥለዋለሁ” አላት፡፡

በንጋቱ ልጅየው ሽማግሌ አባቱን ወደ ገደል ሊወረውረው ተነሳ፡፡ ከገደሉ ጫፍ ላይ ካደረሰው በኋላም “አባቴ! ብትፈልግ ገደል ግባ! ብትፈልግ የፈለግከውን ሁን፡፡ አባቴ ስለሆንክ ግን በራሴ እጅ አልወረውርህም፡፡ ትዳሬንም እወዳለሁና ከቤቴ እንድትመለስ አልፈቅድልህም” አለው፡፡ አባትየውንም እዚያው ትቶት ሄደ፡፡

ዘመን አለፈ፡፡ የድሮው ልጅ በተራው አባት ሆነ፡፡ ልጁም አገባ፡፡ አባትም ከልጁ ጋር መኖር ጀመረ፡፡ ታዲያ እርጅና ሲመጣ ይህኛውም  አባት ልክ እንደ ድሮው አባት ጨቅጫቃ ሆነ፡፡ የልጁን ሚስት በረባ ባልረባው ይጨቀጭቃት ጀመር፡፡ ልጁም ጭቅጭቁ ሲሰለቸው አባትዬውን ወደ ገደል ሊወረውረው ተሸክሞት ተነሳ፡፡ ረጅም ርቀት ከተጓዙ በኋላ የታዘለው አባት ልጁን እንዲህ አለው፡፡
  “እዚሁ ጋ ብትተወኝ ይሻለኛል፤ እኔም ያኔ አባቴን ከዚህ አላሳለፍኩትም”፡፡
*****
  አያድርስ ነው ወገን! “ሁሉም የዘራውን ነው የሚያጭደው” የሚለው ምሳሌ አሁን ላይ የማይሰራ ቢመስልም ጊዜው ሲደርስ እውነት መሆኑ አይቀርም፡፡ አላህ ከእንዲህ ዓይነት ክፋት ይጠብቀን፡፡

በነገራችን ላይ የመጀመሪያውን ተረት የነገሩን ጎረቤቴ የነበሩት “ሀቦ ኑሪያ” ናቸው፡፡ ሁለተኛውን ተረት የአባቴ የቅርብ የስጋ ዘመድ ከሆኑት ሼኽ ሙሐመድ ሑሴን ቲርሞ የሰማሁት ነው (በኋላ ላይ ስብሐት ገብረእግዚአብሄር ጽፎት ባነበውም ተረቱን በቅድሚያ የሰማሁት ከሼኽ ሑሴን አንደበት ነው)፡፡
------
አፈንዲ ሙተቂ
ግንቦት 26/2006
አዳማ!!
-----
Afendi Muteki is a researcher and author of the ethnography and history with special focus on the peoples of East Ethiopia. You may follow him on his blog and his facebook page by clicking the following links