Thursday, August 15, 2013

===አቤት በይ ካይሮ===


አወይ ካይሮ አወይ ቃሂራ!
የምፅራይም ፈርጥ የግብጽ የሚስራ
የዐረብ መዲና የከተሞች አውራ
የፈርኦኖች ዙፋን የስልጣኔ ሀድራ
የነፈርቲቲ ፍሬ የዚያች ክሊዎፓትራ
የናይል በረከት የአባይ ማረፊያ
የአል-ሱዩጢ ወንበር የአል-አዝሀር ጣቢያ፡፡

እነ ፈርኦን ኩፉ በፒራሚድ እንዳላስጌጡሽ
ቀብራራው ንጉሥ ኻፍሬ ስፊኒክስ እንዳልተከለብሽ
እን አምር አል-አስ በግንብ እንዳላጠሩሽ
እነ ሳላዲን አዩቢ ፍትሐዊ ፍርድ እንዳልሰጡብሽ
እነ ኢብን ኻልዱን በታሪክ እንዳልዘከሩሽ
እነ ነጂብ ማሕፉዝ “ኖቬላ” እንዳልቀመሩብሽ
ዛሬ ግን ተዋርደሽ የከተሞች ውራ ሆንሽ
አንቺም እንደ ባግዳድ በንጹሐን ደም ጨቀየሽ
እንደ ደማስቆ እና ካቡል በሬሳ ትርኢት ከረፋሽ፡፡

ካይሮ ምነው ጉዱ ይህንን ለምን ፈለግሽ
“ቃሂራ” ተናገሪ ይህንን እንዴት ተመኘሽ?

ጂኒ ወልደ ሰይጣን እንዴት ቢሆን ነው የነካሽ
የደም ግብር መክፈል ለምንድነው የጀመርሽ
ወዳጅ ጠላቱን ሁሉ እምባ በእምባ ያደረግሽ
የልበ ንጹሓን ልብ ክፉኛ የሰበርሽ

ካይሮ ምነው ጉዱ ይህንን ለምን ፈለግሽ
“ቃሂራ” ተናገሪ ይህንን እንዴት ተመኘሽ?

እኔ የሀረር ልጅ የኦሮሞ የኢትዮጵያ
በአባይ ፖለቲክ ሰበብ ባኮርፍሽም አንድ አጥቢያ
ከሳዳት ከሙባረክ ጋር ብገጥም እንካ ሰላንቲያ
የአፍሪቃ ኩራት መሆንሽ ሲታወሰኝ በ“ሲሪያ”
የዑለማ ሐድራነትሽ የአንቢያ የአውሊያ
የሐትሸፕሰት ውቅርነትሽ የፑንት ሚስጢር ማሰሪያ
የተውፊቅ አል-ሐኪም እናትነትሽ የተውኔቶቹ ማስተናበሪያ
ይህ ሁሉ ሲመላለስብኝ አዕምሮዬን ሲሞግተው
ፖለቲኩን እረሳና ከኩርፊያ እባንናለሁ
“ፖለቲክ ለፖለቲከኛ” እልና ያንቺ ቲፎዞ እሆናለሁ
ስላንቺ ታላቅነት ለማያውቁት እዘምራለሁ፡፡

የትላንቱ ግን ጉድ ነው ተመን የሌለው “ሙሲባ”
ለጠላቴም የማልመኘው እንኳን ላንቺ ለኔ አበባ
ህጻን ከሽማግሌ ያልለየ የደንታ ቢሶች ድብደባ
ሺዎችን በአንድ ጀንበር ትቢያ ያለበሰ ቅብቀባ
ዓለምን ያስበረገገ የወታደር ስለባ
ሚሊዮኖችን ያስመሸ አድርጎ እምባ በእምባ፡፡

ካይሮ ምነው ጉዱ ይህንን ለምን ፈለግሽ
“ቃሂራ” ተናገሪ ይህንን እንዴት ተመኘሽ?

አንቺ የአባይ ግርጌ የናይል ዞሮ ማረፊያ
የሀም ህዝቦች እምብርት የሴም ልጆች መኩሪያ
የኩሽ ልሳነ ምድር የሜምፊስ የኑቢያ
የዩሱፍ (ዮሴፍ) ገድል መዝገብ የሙሳ (ሙሴ) ብትር መሞከሪያ
ባንቺ የሚያምረው ጥበብ ነው የቅኔ መወድስ ዘረፋ
የእሳት ዳር ትረካዎች የወግ ኦሜጋና አልፋ
በበደዊ ተረቶች መሳቅ በዐረብ ትረባ መንፈቅፈቅ
በአንድ ሺህ አንድ ሌሊት (አልፍ ለይላ ወሌይላ) ግብዣዎች መፈንደቅ
“ደም” ነጃሳ ነው እርኩስ ነው ከመ ኢብሊስ (ዲያብሎስ)
ክብርሽን የሚደመስስ አውራነትሽን የሚገስስ
ጥበብሽን የሚሰለቅጥ ውበትሽን የሚያደበዝዝ
ሀይልሽን የሚያኮስስ ደረጃሽን የሚሰርዝ፡፡

ስለዚህ
ካይሮ ሆይ
አንቺ ፉስጣጥ አንቺ ቃሂራ
የምፅራይም ፈርጥ የግብጽ የሚስራ

የደም ግብሩን እምቢ በይ ሁለተኛ እንዳይለምድሽ
አምላክሽን ተማጸኚ በዚሁ በቃ እንዲልሽ
ወንዶችሽ አይለቁብሽ ሴቶችሽ አይዋረዱብሽ
ህጻናቱ ይቦርቁ ይፈንድቁ ይጫወቱብሽ
የባሩድ ሽታው ይወገድ አየርሽ ይጥራ ከአረር
አስፋልቱ ከደም ይንጻልሽ አደባባዩም ይሁን “ጧሂር”
ሀገሬው ወጥቶ ይግባ በአማን ዛፎችሽ ይለምልሙሽ  
ዛሬም ነገም ሁሌም የአላህ (አምላክ) ሰላም ይስፈንብሽ፡፡
-------
ግጥም፡ አፈንዲ ሙተቂ
ነሐሴ 9/2005
ፎቶ፡ Aljazeera English
መታሰቢያነቱ፡ ነሐሴ 8/2005 በካይሮ ከተማ ላለቁት በሺህ የሚቆጠሩ ግብጻዊያን ይሁን፡፡

Monday, August 12, 2013

ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች (የአሕመዲን ጀበል መጽሐፍ)


የወፍ በረር ዳሰሳ - በአፈንዲ ሙተቂ
--------------------------
 የመጽሐፉ ርዕስ፡ “ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች፡ የጭቆናና የትግል ታሪክ”
ደራሲ፡ አሕመዲን ጀበል
የገጽ ብዛት፡ 272
ዋጋ፡ 45.00 ብር
የታተመበት ዘመን፡ የካቲት 2003
--------------------------------------
የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ታሪክ በውጪ ምሁራን በሰፊው ተጽፏል። አቡ ፈድሉላህ አል-ዑመሪ እና ሙሐመድ አል-መቅሪዚን የመሳሰሉ የዐረብ ጸሐፍት ስለኢትዮጵያ ሙስሊሞች የኑሮ ዘይቤና የሱልጣኔታዊ መንግሥታት ታሪክ መጻፍ የጀመሩት ከ14ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ነው። ኤንሪኮ ቼሩሊ፣ ጆን ስፔንሰር ትሪሚንግሀም፣ ኢዋልድ ዋግነር፣ ኡልሪች ብራውኬምፐር እና ሌሎችም የአውሮጳ ጸሐፍት በዚህ ርዕስ ዙሪያ በርካታ መጻሕፍትንና ጥናታዊ ጽሁፎችን አበርክተዋል። ይሁንና የጉዳዩ ባለቤት የሆኑት የኢትዮጵያ ሙስሊም ምሁራን ታሪካቸውንና ማንነታቸውን በመጻፉ ረገድ የነበራቸው አስተዋጽኦ አነስተኛ ነው። የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲዎቹ ፕሮፌሰር ሁሴን አሕመድ እና ፕሮፌሰር አሕመድ ዘከሪያ እንዲሁም የአትላንታ ዩኒቨርሲቲው ፕሮፌሰር ሙሐመድ ሐሰንን የመሳሰሉ ምሁራን የሚችሉትን ያህል ከማድረግ አልተቆጠቡም። ሆኖም የነኝህ ምሁራን ጽሁፎች በአብዛኛው በውጪ ሀገራት የታተሙ በመሆናቸው በውጪ ሀገር ከሚኖሩት ኢትዮጵያዊያን በስተቀር በሀገር ቤት ለሚኖሩት አንባቢያን በቀላሉ የማይገኙ ሆነው ቆይተዋል።

በሀገር ውስጥ ያሉ ሙስሊም ምሁራን የኢትዮጵያ ሙስሊሞችን ታሪክ በመጻፉ ላይ ዝምታን አብዝተው ቆይተዋል። በተለይ በሀገርኛ ቋንቋዎች (አማርኛ፣ ኦሮምኛ ወዘተ…) የሚጻፉ መጻሕፍት አልነበሩም ለማለት ይቻላል። ከፈረንጆቹ 2000 ዓ.ል. ወዲህ ግን ዝምታው እየተሰበረ ነው። በጣም ጥሩ ጥሩ ስራዎችን እያየን ነው። ከነዚህ መካከል በቀዳሚነት የሚጠቀሰው “ሐበሻን የማቅናት ዘመቻ” የሚባለው ባለ ሁለት ቅጽ መጽሐፍ ነው። ይህ መጽሐፍ የኢማም አሕመድ ኢብራሂም አል-ጛዚ ዜና መዋዕል የሆነው “ፉቱሑል ሐበሽ” በሀረሪ ብሔራዊ ጉባኤ አማካኝነት ከዐረብኛ ወደ አማርኛ ቋንቋ የተተረጎመበት ነው። በ1997 ዓ.ል. ደግሞ የወለኔው ሼኽ ዑመር በሽር ከዛሬ 100 ዓመታት በፊት በዐረብኛ የጻፉት መጽሐፍ “ጥሮነ-የኢትዮጵያ ቀደምትና ታላላቅ ዑለማ ታሪክ” በሚል ርዕስ ተተርጉሞ ቀርቦልናል። አቶ ተሾመ ብርሃኑ ከማልም በ2000 ዓ.ል. “ኢማም አሕመድ ኢብራሂም” የተሰኘ ወጥ ስራ አቅርበውልናል። እነዚህ ሶስት ስራዎች በፈር-ቀዳጅነታቸውም ሆነ የማናውቃቸውን ሀቆች በማሳወቁ ረገድ የነበራቸው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው። ስለዚህ ጸሐፍቱ (ተርጓሚዎቹ) እና አሳታሚዎቹ በእጅጉ ሊመሰገኑ ይገባል። ይሁንና የተጠቀሱት ስራዎች በተወሰኑ ሰዎች ስብዕና ላይ ያተኮሩ ግለ-ታሪኮች (biographical works) በመሆናቸው ከመጠነ ሰፊው የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ታሪክ ጋር ሲመዘኑ “አባይን በጭልፋ” ያህል ነው የሚሆኑት።

በየካቲት ወር 2005 ግን በበርካታ ኢትዮጵያዊ የመጻሕፍት ወዳጆች ዘንድ መነጋገሪያ ሊሆን የበቃ የታሪክ መጽሐፍ ብቅ አለ። ጸሐፊው አሕመዲን ጀበል ይባላል። የመጽሐፉ ርዕስ “ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች፡ የጭቆናና የትግል ታሪክ” ይሰኛል። የዚህ መጽሐፍ ፋና ወጊነት በሁለት መልኩ ሊታይ ይችላል። አንደኛ የኢትዮጵያ ሙስሊሞችን የአንድ ሺህ ዓመታት ታሪክ በአማርኛ ቋንቋ የሚተርክ የመጀመሪያ መጽሐፍ ነው። ሁለተኛ በተመሳሳይ አውደ ርዕስ (subject) ምሁራዊ ፈር ሳይለቅ በአማርኛ ቋንቋ የተጻፈ የመጀመሪያ መጽሐፍ ነው።

“ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች፡ የጭቆናና የትግል ታሪክ” ከ615 እስከ 1700 ዓ.ል የነበረውን የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ታሪክ ይተርካል። ይህም እስልምና ወደ ኢትዮጵያ ከገባበት ጊዜ ጀምሮ የአውሳ ሱልጣኔት እስከ ወደቀበት ዘመን ድረስ መሆኑ ነው። አሕመዲን ጀበል መጽሐፉን ለመጻፍ ከፍተኛ ጥናት አካሂዷል። የዐረብና የአውሮጳ ጸሐፍት በርዕሰ ነገሩ ዙሪያ የደረሷቸውን በርካታ መጻሕፍትና ጥናታዊ ጽሁፎችን በጥልቀት መርምሯል። የሀገራችን ቀደምት ዑለማ የጻፏቸውን ያልታተሙ ሰነዶች ደጋግሞ ፈትሿል። የአፈ-ታሪክ መረጃዎችን በሰፊው አሰባስቧል። በአርኪኦሎጂ ቁፋሮ የተገኙ ስፍራዎችንና እንደ ሀረር እና ኢፋት ያሉ ቀደምት ኢስላማዊ የስልጣኔ አምባዎችን በአካል ጎብኝቷል። በዚህ ሁሉ ልፋትና ምርምር ያገኘውን ውጤት ነው በመጽሐፍ መልክ አሳትሞ ያቀረበልን።

አሕመዲን ጀበል መጽሐፉን የጻፈበት ዘይቤ የሚያመረቃ ነው። የብዕር አጣጣሉ ለተራ አንባቢም ሆነ ለከፍተኛ ምሁራን የሚመች ነው። የጸሐፊውን ስልት እንደ ስነ ጽሁፍ ባለሙያ ሆነን ስንመዝነው “ኢ-መደበኛ” እና “መደበኛ” የመጣጥፍ አጻጻፍ በሚባሉት ዘይቤዎች መካከል ያለ ሆኖ ነው የምናገኘው። ጸሐፊው የሀገራችን የታሪክ መጻሕፍት ልዩ መታወቂያ እየሆነ የመጣውን የመደበኛነት ዘይቤ ሙሉ በሙሉ አልለቀቀም። ሆኖም በነዚያ መጻሕፍት የሚታየውን ጠንከር ያለ የአጻጻፍ ወግ አጥባቂነት አይከተልም። በዐረፍተ ነገር አወቃቀሩም ሆነ በሚጠቀማቸው ቃላት ከመደበኛው አጻጻፍ ላይ ችክ አይልም። ደረቅና ከበድ ያሉ ቃላትን ከማብዛትም ተቆጥቧል። በመሆኑም አንባቢው የመጽሐፉን 245 ገጾች በሙሉ በትልቅ ተመስጦ ነው የሚያነባቸው። ይህ ግልጽ እንዲሆንላችሁ ካሻችሁ የአሕመዲንን መጽሐፍ በቅርብ ዘመናት ከወጡ ታሪክ-ነክ መጻሕፍት (በአማርኛ የተጻፉ) ጋር ማወዳደሩ ይበቃችኋል። እነዚህ መጻሕፍት በትልቅ ልፋት የተዘጋጁ ሆነው ሳለ በአጻጻፋቸው ከሚከተሉት ድርቅ ያለ የወግ አጥባቂነት ባህሪ የተነሳ የአንባቢውን ቀልብ ብዙም ሲማርኩ አይታዩም። ደራሲ አሕመዲን ጀበል ይህንን ጉልህ የሆነ የአጻጻፍ ድክመት በማጤን ሁሉንም አንባቢ የሚማርክ ዘይቤ ወደ መምረጡ ያዘነበለ ይመስላል። በመሆኑም በጸሐፊው የተመረጠው ስልት በመጽሐፉ የተካተተውን ታሪክ ያህል አንባቢውን ሊማርክ ችሏል። ለዚህም ይመስለኛል መጽሐፉ በጥቂት ወራት ውስጥ ሶስት ጊዜ ያህል ለመታተም የበቃው። ከዚህ አኳያ ሲታይ አሕመዲን በመጽሐፉ ሊያስተምረው ከፈለገው የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ታሪክ በተጨማሪ ወደፊት ስለ ታሪክ መጻፍ የሚፈልጉ ጸሐፍት መከተል ያለባቸውን አቅጣጫ አሳይቶአቸዋል ብሎ መደምደም ይቻላል። በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ ማለት እንዲህ ነው!  




*****  *****  *****
ደራሲው የተጠቀመው የአጻጻፍ ስልት በጣም ሸጋ ነው-ከላይ እንደተገለጸው። ሆኖም ጸሐፊው ትኩረቱን ለአጻጻፉ ብቻ አላደረገውም። የታሪክ መጻሕፍት የሚጻፉበትን ምሁራዊ ፈርጅ ከሞላ ጎደል ጠብቋል። መረጃዎችን ያገኘባቸውን ምንጮች በቅንፍ እና በግርጌ ማስታወሻዎች ይጠቁማል። ትረካዎቹን በፎቶግራፍ እያስደገፈ የበለጠ ለማብራራት ሞክሯል። የመጽሐፉ የአርትኦት ስራም በበሰለ ሁኔታ ተከናውኗል (አልፎ አልፎ የፊደላት ስህተት ቢታዩበትም እንኳ)። ፊደላቱ ለዐይን ማራኪ ከመሆናቸውም በላይ ጤናማ እይታ ላለው ማንኛውም ሰው ጉልህ ሆነው ይታያሉ።
 
  መጽሐፉ በይዘቱም ቢሆን ማለፊያ ነው። እስልምና ወደ ኢትዮጵያ ከገባበት ዘመን ጀምሮ መነገር ያለባቸው አንኳር የሆኑ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ታሪካዊ ክንዋኔዎች ተዳስሰዋል። ከሸዋ ሱልጣኔት ጀምሮ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች የመሰረቷቸው ታዋቂ የአካባቢና ሀገር አቀፍ መንግሥታት ታሪክ በመልክ በመልኩ ቀርበዋል። እንዲሁም ከመኽዙሚ ነገሥታት ጀምሮ የወላስማ፣ የአዳል እና አውሳ ስርወ መንግሥታት ታሪኮች  ተዳስሰዋል። በምስራቅ፣ በደቡብና በመካከለኛው ኢትዮጵያ አብበው የነበሩት ሰባቱ የኢፋት፣ የደራ፣ የሀዲያ፣ የዳዋሮ፣ የባሊ፣ የአረባባኒ እና የሻርኻ እስላማዊ ሱልጣኔቶች አነሳስ፣ እድገትና የመጨረሻ ውድቀታቸው አጠር አጠር ባለ መልኩ ተተርኳል። በኢትዮጵያ ሙስሊሞች ታሪክ ውስጥ ሰፊ ስምና ዝና ተክለው ያለፉት ኢማም አሕመድ ኢብራሂም አል-ጛዚን የመሳሰሉ መሪዎች ስብዕና በተገቢ ሁኔታ ተፈትሿል። በአጠቃላይ ከ615 ዓ.ል. እስከ 1750 ዓ.ል ድረስ ያለው የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ታሪካዊ ጉዞ ሚዛናዊ በሆነ ሁኔታ ተተርኳል። ደራሲው እነዚህን ታሪኮች ሲተርክልን በአንዳንድ መጻሕፍት ውስጥ ገኖ የሚታየውን የትረካዎች ተቃርኖ ለመከላከል ብርቱ ጥንቃቄ ያደረገ ይመስላል። ስለዚህ መጽሐፉን ጀምረን እሰከምናጠናቅቀው ድረስ ልባችን በታሪክ ፈረስ ወደ ጥንታዊው ዘመን ይበርራል። 272 ገጽ እየጣፈጠን ነው የሚያልቀው።
*****  *****  *****
  “ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች” በእውነቱ የሚደነቅ ስራ ነው። ደራሲው የአንድ ሺህ ዓመት ታሪካችንን በ45 ብር ብቻ በቀላል አማርኛ እንድናውቀው ስላደረገን መቼም የማንረሳው ባለውለታችን አድርገን ነው የምንወስደው። ለወደፊቱም በምርምር የተደገፈ እጅግ የተሻለ ስራ እንዲያስነብበን እንጠብቃለን። ታዲያ ደራሲው ወደፊት ሊያሻሽላቸው የሚገባቸውን አንዳንድ ህጸጾች ሳንጠቁም ብናልፍ አድናቆታችን ፈሩን ይለቅና “መጽሐፉ ሙሉ በሙሉ ፍጹም ነው” የሚል የዘመድና የወዳጅ ሆይ ሆይታ ይመስልብናል። ስለዚህ የመጽሐፉን ይዘት ወደፊት በስፋት እዳስሰዋለሁ።  ይህንን ግምገማ ከማጠናቀቄ በፊት ግን በፊት ሽፋኑ ላይ የሚታዩትንና ለኔ ያልጣሙኝን ሶስት ነጥቦች ጠቆም ላድርግ።

   “ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች” የሚለው ትልቅ ርዕስ የመጽሐፉን ይዘት በበቂ ሁኔታ ይገልጻል። ከርሱ ስር ያለው “የጭቆናና የትግል ታሪክ” የሚለው አነስተኛ ርዕስ ግን ከመጽሐፉ ይዘት ጋር አለመጣጠን ይታይበታል። መጽሐፉን ያነበበ ማንኛውም ሰው በቀላሉ እንደሚገነዘበው ደራሲው ያቀረበልን ታሪክ የጭቆናና የትግል ታሪክ ብቻ አይደለም። ንግዱ፣ እደ ጥበቡ፣ የከተማ ግንባታው፣ የመንግስት አስተዳደሩ፣ የተፈጥሮ ሐብቱ ወዘተ.. የተቻለውን ያህል ተዳስሰዋል። “የጭቆናና የትግል ታሪክ” የሚለው ንዑስ ርዕስ ከእነኝህ ዘርፎች ጋር በተዘዋዋሪ ካልሆነ በስተቀር የቀጥታ ተዛምዶ የለውም። ስለዚህ አሕመዲን ከሚቀጥሉት እትሞች ላይ ይህንን ንዑስ ርዕስ ማንሳት ይጠበቅበታል።

ሁለተኛው ነጥብ ደግሞ ሞቃዲሾ ያለው የኢማም አሕመድ ኢብራሂም ሀውልት በሽፋኑ ላይ መካተቱ ነው። የኢማም አሕመድ ታሪክ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ታሪክ አካል ነው። ሆኖም የሞቃዲሾው ሀውልት ጄኔራል ዚያድ ባሬ ኢትዮጵያን በወረረበት ወቅት ለፕሮፓጋንዳ ያሰራው ከመሆኑ ውጪ ከኢማም አሕመድም ታሪክም ሆነ ከኢትዮጵያ ሙስሊሞች ጋር አንዳች ተዛምዶ የለውም። ደግሞም የሀውልቱ ትርጓሜ ኢማም አሕመድ ሶማሊያዊ እንጂ ኢትዮጵያዊ አይደለም የሚል ነው። ዚያድ በሬ በ1969 ኢትዮጵያን ሲወር ሀውልቱንና የኢማሙን ታሪክ እንደ ቅስቀሳ መሳሪያ በሰፊው ተጠቅሞበታል። በዚህም ኢማሙ የኛ እንጂ የናንተ አይደለም የሚል የታሪክ ሽሚያ አካሂዷል። ታዲያ አሕመዲን ጀበል ይህንን የመሰለ ደባ ከጀርባው ያነገበውን ሀውልት በፊት ገጹ ላይ ማሳየት ነበረበት? በፍጹም አልነበረበትም! ከርሱ ይልቅ ኢማሙ ዋና ከተማውን የቆረቆረበት የደምቢያ ጎራ፣ ወይንም የመጀመሪያውን ታላቅ ድል ያጣጣመበትን የሽምብራ ኩሬ ሜዳ፣ ወይ ደግሞ ኢማሙ የሞተበትን የዘንተራ በር በሽፋኑ ላይ ቢያትም ኖሮ ምንኛ ያምርበት ነበር!? ስለዚህ አሕመዲን ጀበል ወደፊት በሚታተሙት መጻሕፍቱ ሽፋን ላይ ከታሪካችን ጋር አግባብነት የሌላቸውን ስዕሎች ባያሳየን መልካም ነው እላለሁ።

ሶስተኛው መጽሐፉ የታጠረበት የጊዜ ክልል ነው። ደራሲው በዚህኛው ቅጽ (ቅጽ አንድ) ከ615-1700 ያለውን ታሪክ ነው የጻፍኩት ብሎናል። ከዚያ ወዲህ ያሉት 300 ዓመታት ብቻ ናቸው። እነዚህ ዓመታት ከበፊቱ 1100 ዓመታት በእጅጉ ያንሳሉ። በነዚህ የኋለኞቹ ክፍለ ዘመናት የተከናወኑት ድርጊቶችም በቀደሙት ዘመናት ከተከናወኑት አንጻር ሲታዩ በአነስተኛ ሚዛን ላይ የሚቀመጡ ናቸው። ለምሳሌ ኢማም ማሕፉዝ፣ ኢማም አሕመድና አሚር ኑር ሙጃሂድ በፊተኛው ዘመን የነበሩ ታላላቅ መሪዎቻችን ነበሩ። በኋለኞቹ ክፍለ ዘመናት የታየ ማንኛውም ሙስሊም ኢትዮጵያዊ  መሪ ከነዚያ ሶስት መሪዎች ጋር በጭራሽ አይወዳደርም። የኋለኞቹ መሪዎች ያካሄዷቸው ዘመቻዎች አንድ ላይ ቢደመሩ አሚር ኑር ሙጃሂድ ብቻውን ከፈጸማቸው ዘመቻዎች ጋር አይተካከሉም። ታዲያ አሕመዲን ለ1100 ዓመታት 250 ገጾች ያሉት አንድ ቅጽ መድቦ ለ300 ዓመታትም በተመሳሳይ መልኩ ሌላ ቅጽ መመደቡ አግባብ ነው? አይመስለኝም። እንደኔ ከሆነ የመጀመሪያው ቅጽ ከዘመነ ነጃሺ ጀምሮ እስከ ኢማም አሕመድ መነሳት ድረስ ያለውን ታሪክ ቢዘግብና ሁለተኛው ቅጽ ከኢማም አሕመድ መወለድ ወዲህ ያሉትን የ500 ዓመታት ታሪካችንን ቢተርክ እጅግ የተዋጣለት ይሆን ነበር። ስለዚህ አሕመዲን ሚዛናዊ  መስሎ ላልታየኝ ለዚህ የዘመናት አከፋፈል ማብራሪያ እንዲሰጠን ይጠበቅበታል።
*****  *****  *****
ባጠቃላይ “ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች፣ የጭቆናና የትግል ታሪክ” ብዙሀኑ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ታሪካቸውን በራሳቸው ቋንቋ እንዲያነቡና እንዲያጠኑ አብይ ምዕራፍ ከፍቷል። ጸሐፊዎቻችንም በርዕሰ ጉዳዩ ላይ እንዴት መጻፍ እንዳለባቸው በቂ ግንዛቤ የሰጣቸው ይመስለኛል። በዚህ ድርሰት ፋና ወጊነት ሌሎች ጸሐፍትም ተቀስቅሰው ያሉንን የታሪክ ማስረጃዎችና ማስተማሪያ መጻሕፍት እንዲያበራክቱልን እንጠብቃቸዋለን። ፈጣሪ ለውዱ ጸሐፊያችን ለአሕመዲን ጀበል እድሜና ጤና ሰጥቶት ሌሎች ስራዎቹንም እንድናጣጥም ያድርገን! ሰላም
አፈንዲ ሙተቂ
አዲስ አበባ  

Saturday, July 20, 2013

Peace TV network crosses 200 million viewership

 Source: Arab News

Peace TV, a major Islamic satellite television network, has crossed the 200-million viewership mark, with a record global viewership exceeding more than 100 million for Peace TV English, 80 million for Peace TV Urdu and more than 20 million for the newly launched Peace TV Bangla.

Zakir Naik, Peace TV founder president and a scholar who has delivered public lectures across the world, including Saudi Arabia, on Islam and comparative religion, told a public meeting organized by India Islamic Cultural Center (IICC) in Riyadh recently that the network’s viewership is growing considerably.

Beginning in January 2006, Peace TV (English) has been telecast to more than 150 countries around the world, including in Asia, Europe, Africa, Australia and North America recording more than 100 million viewership.
He added that Peace TV Urdu, which was launched in 2009, has 80 million viewership.

Peace TV Bangla, which was launched on April 22, 2011, has
crossed 20 million mark, he said, adding that the Bangla channel has reached its popularity in a short span of time.
Naik said that the launch of Peace TV Arabic is on the cards. The Islamic Research Foundation (IRF), which owns Peace TV, has finalized plans to launch a 24-hour Arabic-language Islamic channel.

There are several Arabic channels today, but Peace TV Arabic will be different and unique in content and technology, he added.

A nonprofit network, Peace TV broadcasts programs around the clock and also provides free-to-air telecasts.

Sunday, July 14, 2013

Sheikh Abdurahim Al-Bur’ai and His “Nasheeda” Revolution


Written by Afendi Muteki
-------------------------
Some 20 years ago, in the holy month of Ramadan, whenever you visited many of the coffee houses (“shayi bet” in Amharic)  in Mercato, Adare Sefer and other counties of Addis Ababa and in the cities of Dire Dawa, Harar, Adama, Jimmaa, Dessie, Asosa etc, what you hear from the tape recorders put besides the cashiers were mostly the Sudanese songs of Muhammad Wardi, Ahmad Al-Mustafa and Sayyid Khalifa. It seemed to me that most of the youth of the time used to consider those Sudanese songs a meaningful spiritual melodies. Since 2000 G.C., however, this habit started to change slowly where the songs were being replaced by the marvelous Sudanese “Nasheeda” (properly called “Madeeh”). And, from the Ramadan of 2003 (1995 E.C.) onwards, the evenings of the caffes, restaurants, music shops etc of Addis Ababa and other towns are dominated by these Sudanese “Madeeh”. Such a dramatic change happened, as I think, with the emergence of the highly mystique Sudanese “Nasheeda” album titled “Al-Adnani”. 

I heard one “Madeeh” included in the album “Al-Adnani” in 1996 from the Sudanese “Radio Omdurman”. But at that time, it seemed to me that a worldly singer sung it just as some Ethiopian singers were doing.  As time passes, I came to know that there are thousands of Sudanese individuals and groups who entirely dedicated their life for “Madeeh” only. And the group that sung “Al-Adnani”, known as “Firqatu Sahwa” (meaning “the revivalists” or “the awakeners”), was one and the best known Sudanese Madeeh group along with “Al-Asala” group. And in recent years, so many individuals are joining the “Madeeh” genre. Among them is the blind super star called “Hanan Al-Niel”.
*****  *****  *****



In most cases, the Sudanese “Madeeh” singers don’t write their own “Nasheeda”. They usually took the “Madeeh” poetry written by old Sheikhs and perform it in their own lyrics. Among these sheikhs of “Madeeh” poetry, the most influential and highly gifted one was Sheikh Abdurahim Muhammad Al-Bura’i. 

Sheikh Abdurahim Al-Bura’i was born in 1923 in North Kordofan.  He was educated in many parts of the Sudan under different sheiks. Up on the completion of his education, he settled in his home Kordofan where he served as the people’s teacher for nearly 50 years. He lived there until his death.

Sheikh Al-Bur’ai was a highly gifted and influential teacher. But most notably, he is known for his “Nasheeda” revolution. As I said in the above section, most of the Sudanese “Munshids” (performers of “Nashedaa”) use his poetry for their “Madeeh”. His influence can be felt still after his death. I (the writer of this small article) can witness that I learned many things through his poetry.

In his poetry, Sheikh Bu’rai stressed deep spiritually and Islamic way of life. He wrote about staying firm on “Ibadah” (worship of “Allah”), making “da’wa” (preaching), having a good family, respecting the  parents, giving charity, having good manners, etc... He also teaches the story of the Sahaba (companion’s of the prophet , s.a.w) in a resplendent way. However, I admire the poetry of Sheikh Al-Bur’ai mostly for their advices of the youth. For example, in one poetic Madeeh performed by “Firqatu-Sahwa”, the Sheikh advised the youngs on the importance of “Halal” marriage in the following manner.

“Ahfaz Li nisfa-Diini
Bi ziwaajin zatu-Ddini.
Sharikatu fi hayaatuk
Aanisatu fi bayaatuk
Abadun walaa tzlimha
Wa-ddiinin Haanif allimha
Ni’mak laa tahrimhaa
Wa ra’ hurmatuha wa akrimhaa”
 
Here is the approximate meaning of the poetry in English

“Hold the half of your faith (i.e. Islam)
By marrying a wife that held her faith.
She is your friend in your life
And she is the strength of your family.
Never do a wrong on her
Educate her with best of the faith
Don’t restrict her from using your property (since it belongs to both of you)
Keep her dignity, and be generous to her.”
*****  *****  *****
Sheikh Al-Bur’ai’s “Nasheeda” revolution got him accredition from many directions. And in 2002, the University of Khartoum awarded him an Honorary Doctorate of Literature for his popularization of the “Madeeh” poetry in the Sudan and other countries, which he received from the hand of the Sudanese President Umar Hassan Ahmad Al-Bashir.
Sheikh Al-Burai died in 2005. May Allah award him Jannah.
-------------------------
Afendi Muteki
Ramadan 6/1431

Saturday, July 13, 2013

አል-አሚን በዚያች ምሽት


ጸሓፊ፡ ረሺድ ቢላል
--------------------------------------
በሰባተኛው ክፍለ ዘመን የመጀመሪያዎቹ ዓመታት በዐረባይቱ የመካ ከተማ ይኖር የነበረውን “አል-አሚን”ን ብዙዎች ይወዱታል። ይህ ሰው አደራን ጠበቅ አድርጎ ስለሚይዝና የሰዎችን ገንዘብ የሚያምታታ ባለመሆኑ ነበር “አል-አሚን” የተሰኘውን ቅጽል ያገኘው። “አል-አሚን” ከጥንት ጀምሮ ሐኒፍ ነበር። ራዕይ (ወሕይ) ባይገለጽለትም ዓለምንና ፍጥረቱን ሁሉ የሰራ አንድ ሀያል አምላክ እንዳለ በልቦናው ያውቀዋል። በመሆኑም እንደ ዘመኑ ህዝቦች ለጣኦታት በጭራሽ ሰግዶ አያውቅም የሞተ እንስሳ ስጋ አይበላም። ፍትህ አዋቂነቱ በጣም ያስመካል። አራጣ በማበደር ሰዎችን አያማርርም። በሐሰት አይምልም። የዕድሌን ዳራ በጥንቆላና በመተት ልፈልግ አይልም።
አል-አሚን በዚህ መልካም ባህሪው ከልጅነት እስከ እውቀት ዘልቋል። በተፈጥሮው ብሩህ የሆነ አዕምሮ ነበረው። ይሁንና ማንበብና መጻፍ በጭራሽ አያውቅም።  

ታሪካዊው የሂራ ዋሻ
 ታዲያ አል-አሚን ዘወትር በረመዳን ወር ከሰው ተገልሎ እውነትን የመተንተንና የማስተንተን ልማድ ነበረው። ለዚህም የመረጠው ሂራ የሚባለውንና ከመካ ከተማ በቅርብ ርቀት ላይ የነበረውን ዋሻ ነው። አል-አሚን አርባ ዓመት እስኪሞላው ድረስ በዚህ ባህሪው ተጓዘ። በአርባኛው ዓመቱ በወርሃ ረመዳን እንደ ልማዱ ስንቁን ሰንቆ ወደ ሂራ ዋሻ በመግባት ነገረ-ፈጣሪንና ነገረ ዓለምን በመተንተን (ተፈኩር በማድረግ) ላይ ሳለ ግን ያልጠበቀው አስገራሚ ፍጡር ከፊቱ ተደቀነ።
*****  *****  *****
   ያ አስገራሚ ፍጡር እንደ ወተት የነጣ ልብስ ለብሷል። ውበቱ ለጉድ ነው። ግርማ ሞገሱ በጣም ያስፈራል። በዚያ ላይ ሰውነቱ ብርሃን በብርሃን ሆኗል። ፍጥረቱ በትክለ ሰውነቱ ከሰው ልጅ ጋር ይመሳሰላል። ግዝፈቱ ግን ሌላ ነው። በዚያ ላይ ትልልቅ ክንፎች አሉት። አል አሚን ባየው ፍጥረት ቢረበሽም በድንጋጤ አቅሉን አልሳተም።
ግዙፉ ፍጡር ወደ አል-አሚን ተጠጋና ከሐር በተሰራ ወረቀት መሳይ ቅጠል ላይ የተጻፈ ጽሑፍ እያቀረበለት “አንብብ” አለው። አል-አሚን ግን “እኔ ማንበብ አልችልም” አለው። እንግዳው ፍጡርም አል-አሚንን በመዳፎቹ ውስጥ አስገብቶ ላብ በላብ እስኪሆን ድረስ ወደ መሬት ተጫነው። ከዚያም በድጋሚ ጽሑፉን እያቀረበለት “አንብብ” አለው። አል-አሚንም እንደ በፊቱ “እኔ ማንበብ አልችልም” የሚል መልስ ሰጠው። ግዙፉ ፍጡር አል-አሚንን በድጋሚ አፈፍ አድርጎት ወደ መሬት ተጫነው (የሀጂ ሙሐመድ ሣኒ ሀቢብን ቋንቋ ልዋስና “ሰውነቱን ጭቁን” አደረገው)።
እንግዳው ፍጡር ለሶስተኛ ጊዜ ጽሑፉን እያሳየው “አንብብ” አለው። በዚህ ጊዜ አል-አሚን “እኔ ማንበብ አልችልም፤ ቢሆንም የትኛውን ነው የማነበው?” የሚል ጥያቄ አዘል ምላሽ ሰጠ። እንግዳውም ጽሑፉን ወደ ራሱ አስጠግቶ የሚከተሉትን አናቅጽ አነበበለት።
“አንብብ፣ በዚያ (ዓለምን) በፈጠረው ጌታህ ስም።
ሰውን ከረጋ ደም በፈጠረው።
አንብብ ጌታህ በጣም ቸር ነውና።
ያ በብዕር (መጻፍን) ባስተማረው።
የሰውን ልጅ የማያውቀውን ሁሉ ያሳወቀው።”
(አል-ዐለቅ፣ 1-5)
አል-አሚን የተነበበለትን በብሩህ አዕምሮው ከቀረጸ በኋላ አንድም ፊደልና ቃል ሳያጓድል ለእንግዳው ፍጡር አነበበለት። በዚህን ጊዜም ግዙፉ ፍጡር “ከአንድ አላህ በስተቀር ሌላ አምላክ የለም፤ አንተን ባሪያውና መልዕክተኛው እንድትሆን መርጦሃል፣ እኔም የፈጣሪዬን መልዕክት ወደ ደጋግ ባሮቹ የማደርሰው ጂብሪል ነኝ” አለው። ከዚያች ቅጽበት በኋላም ከቦታው ተሰወረ።
  አል-አሚን በድንጋጤ ወባ እንደያዘው ሰው ተንቀጠቀጠ። ከዚያም ከዋሻው ወጣና ለአፍታ እንኳ ወደ ኋላው ሳይገላመጥ በከፍተኛ ፍጥነት እየገሰገሰ ከቤቱ ደረሰ። ከቤቱ ውስጥ የነበረችው ባለቤቱ የአል-አሚንን ሁኔታ ስታይ አንጀቷ ተላወሰ። ወደ ባለቤቷ ተጠግታ “የቃሲም አባት ሆይ! ምን አጋጥሞህ ነው?” በማለት ጠየቀችው (ቃሲም የመጀመሪያ ወንድ ልጃቸው ነው)። እርሱ ግን ለጥያቄው መልስ ሳይሰጣት “እባክሽን መተኛት እፈልጋለሁ፤ ልብሶችን ደራርቢልኝ” አላት። ሚስቱ “ምን ሆንክ ውዴ!” እያለች ልታወጣጣው ብትሞክርም ምንም አልተነፈሰም። በመሆኑም ባለቤቱ በጥያቄዋ መግፋቱን ተወችውና በተጠየቀችው መሰረት ልብሶችን ደራረበችለት። የአል-አሚንን ሁኔታ ለማወቅ ብትጓጓም ከመኝታው እስኪነቃ ድረስ መጠበቁን መረጠች።
     ታዲያ አል-አሚን ገና ከመጋደሙ በዋሻው የተገናኘው ግዙፍ ፍጡር መልኩን በሰው አስመስሎ መጣበትና “አንተ ተከናናቢው ሆይ! ከሌሊቱ የሚበዛውን ክፍል በስግደት አሳልፍ። ወይም ግማሹን፣ አሊያም ከዚህ ላላነሰ ጊዜም ቢሆን ለአምላክህ በመስገድ አሳልፍ፤” የሚሉ ውብ ቃላትን አነበበለት (አል-ሙዘሚል 1-3)። እነዚያም ቃላት በአል-አሚን ልቦና ላይ ታትመው ቀሩ።
      አል-አሚን ለተወሰነ ጊዜ ከተኛ በኋላ ሚስቱን “አሁን ቀለል ብሎኛልና የሆንኩትን ሁሉ ልነግርሽ እችላለሁ” አላት። ከዚያም ያጋጠመውን ሁሉ አንድ በአንድ ተረከላት። ባለቤቱም “አይዞህ! አንተ ደግነት እንጂ ክፋት የለብህም። ዘመዶችህን ካሉበት ሄደህ ትጠይቃቸዋለህ። ለተቸገረ ሰው ፈጥነህ ትደርሳለህ። የሌሎችን ገንዘብ አትመዘብርም። አደራ የተባልከውን ነገር ከልብህ ትጠብቃለህ። ውሸት ታይቶብህ አይታወቅም። ጌታችን በአንተ ላይ ደጉን እንጂ ክፉውን እንደማያመጣብህ እርግጠኛ ነኝ” እያለች አበረታታችው። “ለማንኛውም ግን” አለች የአል-አሚን ባለቤት በማስከተል “ለማንኛውም ወረቃ ኢብን ነውፈል የሚባለው የአጎቴ ልጅ ተውራትና ኢንጂል የሚባሉትን ቀደምት መጻሕፍት በደንብ ያጠና በመሆኑ ወደርሱ እንሂድና የተፈጠረውን ሁሉ እንንገረው” አለችው። አል-አሚንም በባለቤቱ ሃሳብ ተስማማ።
   ሁለቱ ሰዎች ወደ “ወረቃ” ዘንድ ሄዱና የሆነውን ሁሉ ነገሩት። ወረቃም ነገሩን ካዳመጠ በኋላ “ይህማ ነቢዩ ሙሳን የገጠመው ቢጤ ነው። በዋሻው የተገናኘህ አስገራሚ ፍጡር መልዐኩ ጂብሪል ነው። እነሆ ሲጠበቅ የነበረው የመጨረሻው ነቢይ ወደ ዓለም የሚላክበት ቀን ደረሰ። ዋ! ዕድሜ ሰጥቶኝ ወገኖችህ ከዚህ ከተማ በሚያባርሩህ ጊዜ ያንተ ረዳትና ጋሻ መከታ በሆንኩ!” አለ። አል-አሚን ወረቃ የተናገረውን በደንብ ከሰማ በኋላ “በእርግጥ ወገኖቼ ከዚህ ከተማ ያባርሩኛል?” በማለት ጠየቀ። ወረቃም “በትክክል!” የሚል ማረጋገጫ ከሰጠው በኋላ “ነቢይ ሆኖ ችግርና መከራ ያልደረሰበት የለም። ችግሩን ሁሉ ችለህ ካሳለፍክና መከራውን መቋቋም ከቻልክ አሸናፊነቱ ያንተ መሆኑ አይቀርም” የሚል ምክር አዘል መልዕክት ጣለለት። ሆኖም ወረቃ በጣም አርጅቶ ነበርና የአል-አሚንን የታሪክ ጉዞ ለማየት ሳይታደል ቀረ። ይህንን ከተናገረ ከጥቂት ወራት በኋላም አረፈ። አል-አሚን ግን ታሪካዊውን ግዳጅ ለመፈጸም ተነሳ።
    እነሆ በወረቃ ኢብን ነውፈል አንደበት እንደተመሰከረው አል-አሚንና ያ እንግዳ ፍጡር በሂራ ዋሻ ያደረጓት አጭር የቃላት ምልልስ (dialogue) እና በጋራ የከወኑት አቻ-የለሽ ኪናዊ ገቢር የሰው ልጆች ወደ ሐቅ እንዲመጡና ከዘላለም ቅጣት ይድኑ ዘንድ ታላቁ አዋጅ የታወጀባት ታላቅ ቅጽበት ሆና በዓለም ታሪክ ተመዘገበች። እጅግ አስገራሚ የሆነው የአል-አሚን የ23 ዓመታት የህይወት ጉዞም በዚያች ቅጽበት “አሐዱ” ተብሎ ተጀመረ።
*****  *****  *****
    አል-አሚን ከዚህ ስም በተጨማሪ “አስ-ሷዲቅ” የሚል ቅጽልም ነበረው። “እውነተኛው” ወይንም “ዋሽቶ የማያውቀው” እንደ ማለት ነው። በእርግጥም ይህ ሰው በቀልድ እንኳ ዋሽቶ አያውቅም። ድሮ በነበረው መልካም ጸባይ ላይ ነቢይነትን ሲደርብ ራሱን ብቻ ሳይሆን የዓለም ታሪክን ለመቀየር በቅቷል። Michael Hart የሚባለው አሜሪካዊ  በሚሊዮን ኮፒዎች በተሸጠለት “100 Influential Persons in History” በተሰኘው መጽሐፉ በዓለም ታሪክ ላይ ከባድ ተጽእኖ መፍጠር የቻሉ 100 ሰዎችን የህይወት ተመክሮ ሲተርክ አል-አሚንን በአንደኛ ደረጃ ላይ ያስቀምጠዋል። በእርግጥም ህላዌአቸውን በብዙ ሺህ ክፍለ ዘመናት ከሚቆጥሩት ቀደምት ህዝቦች መካከል በሚመደቡትና ነገር ግን እስከ 7ኛው ክፍለ ዘመን ድረስ የረባ ቁምነገር ማስመዝገብ ባልቻሉት ኋላቀር የዐረቢያ ጎሳዎች መካከል ተወልዶ ቢሊዮኖችን በደቀ መዛሙርትነት ማሰለፍ እንዲህ በቀላሉ የሚነገር ተአምር አይደለም። የርሱ አስተምህሮ ዘመን አይሽሬ በመሆኑ ዛሬም ድረስ እየተተገበረ ነው። ዛሬም ድረስ እየተሰበከ ነው። በነገው እለትም ይቀጥላል። 
ይህ ሰው “ኢቅረእ” የሚለውን አዋጅ ማሰማት ሲጀምር ከማንም ቀድማ አዋጁን በይሁንታ የተቀበለችው ከላይ የተጠቀሰችውና በተጸውኦ ስሟ “ኸዲጃህ ቢንት ኹወይሊድ” የምትባለው ውድ ባለቤቱ ነበረች (ረ.ዐ.)። ዛሬ ግን ከዓለም ህዝብ ሩብ ያህሉ እርሱ በለኮሰው መንፈሳዊ ጎዳና ላይ እየተጓዘ ነው። የርሱ ተከታይ ካልሆኑትም የሚበዙቱ በክፉም ሆነ በደጉ ስሙን ያነሱታል።
   አል-አሚን የነቢይነቱንና የመልዕከተኝነቱን ካባ ከደራረበ በኋላ የርሱን ምትክ የለሽነት የሚገልጹ በርካታ ቅጽሎችን ተጎናጽፏል። “ሲራጅ” (ጸሐዩ ወይንም እንደ ጸሐይ የሚያበራው” ማለት ነው) “ሙኒር” (“አብሪው” ወይም “ብርሃኑ” ለማለት ነው) “አል-ሙኽታር (“ምርጡ” ወይም “የተመረጠው” እንደማለት ነው) “አል-ሙስጠፋ” (“ተመራጩ” ማለት ነው) ወዘተ… እያልን መዘርዘር እንችላለን። እንደርሱ “ሐኒፍ” (ለአንዱ አምላክ እንጂ ለጣኦታት የማይሰግድ) የነበረው ዐብዱል ሙጠሊብ የሚባለው አያቱ ያወጣለት ስም ግን “ሙሐመድ ነው” (ሰ.ዐ.ወ) ነው። ይሁንና እኛ በዚህ የተጸውኦ ስሙ ከምንጠራው “ነቢዩ” ወይንም የአላህ መልዕክተኛ” ማለቱን እንመርጣለን (ሰ.ዐ.ወ)።
*****  *****  *****
    አዎን! ረመዳን የመዳኛ ወር ነው። የሀጢአት ጭቅቅታችንን በተውባ (ንስሓ) እና በኢስቲግፋር (ማርታ) ለማጠብ የምንተጋበት የዓመቱ ታላቅ ድግሳችን ነው። ስግብግብነትና ግለኝነት የሚፈታተኑትን ደካማ ስሜታችንን የምናገራበት የተግባር ትምህርት ቤታችን ነው። ከዚህ ባሻገር ረመዳንን የምንዘክረው ግን የመጨረሻው ነቢይ (ሰ.ዐ.ወ) ለዓለም ህዝብ የተላኩበት ታላቅ ወር በመሆኑ ነው። ይህ ብስራት የተነገረውም ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) ከጂብሪል ጋር በሂራ ዋሻ በተገናኙባትና “ኢቅራእ” የሚለው የፈጣሪያችን አዋጅ በተነበበባት በዚያች ውብ ተአምረኛ ቅጽበት ነው። ያች አዋጅም ረመዳንን “የቁርኣን ወር” አሰኝታዋለች። በእርግጥም ጌታችን “እንድትጾሙ የተደገነነው ቅዱስ ቁርኣን በወረደበት የረመዳን ወር ነው” በማለት ወርሃ-ረመዳንን ባርኮታል (አል-በቀራህ፣ 185)።
     እንኳን አላህ የነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) ተከታዮች አደረገን። እንኳንም አል-ሙስጠፋን (ሰ.ዐ.ወ) አስነሳልን። እንኳን ለወርሃ ረመዷን አደረሰን።
ረሺድ ቢላል
ረመዷን 3/1431
--------------------------------------
ማስታወሻ፡
1.      አንዳንድ ምንጮች “ጂብሪል አላህ የመጨረሻ መልዕክተኛ እንድትሆን መርጦሃል” የሚለውን ቃል ያሰማው ነቢዩ ከዋሻው ወጥተው በሩጫ ወደ ቤት በመመለስ ላይ እያሉ ነው” የሚል ዘገባ አሰምተዋል። እኔ እዚህ ያቀረብኩት ትረካ ግን በኢብኑ ሒሻም የተዘገበውን ነው። ሐጂ ሙሐመድ ሣኒ ሐቢብም የነቢዩን ታሪክ በአማርኛ በጻፉበት ወቅት ይህንኑ ትረካ መዝግበውታል።
   በሁለቱም አቀራረብ የረመዳንን ልቅና ያገዘፈውን ገቢር ማስመሰከር ይቻላል። ሁለቱም “ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) የመጨረሻው መልዕክተኛ መሆናቸው በረመዳን ወር ታወጀ” ከሚለው አባባል ጋር ይጣጣማሉ።
2.     “ነቢዩ በሂራ ዋሻ ሳሉ ጂብሪል በሰው መልክ ተመስሎ መጣባቸው” የሚሉ ምሁራን አሉ። ነገር ግን ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) ጂብሪልን ሁለት ጊዜ በትክክለኛ ቁመናው እንዳዩት በቁርአንም ሆነ በሐዲስ ተረጋግጧል። እነርሱም የመጀመሪያውን ወህይ (ራዕይ) ያዩባት ምሽት እና ወደ ሰማይ ያረጉባት ሌሊት ናቸው (“ሱረቱን-ነጅም” የሚባለው የቁርኣን ምዕራፍ የመጀመሪያ አንቀጾች ስለሁለቱ ኩነቶች ነው የሚተርኩት)።
3.     ነቢዩን (ሰ.ዐ.ወ) “እርሱ” እያልኩ የጠራሁት ወጋችን እንዲጣፍጥልን በማለት ነው (እናንተ ደስ ካላችሁ “አንቱ” እያላችሁ አንብቡት”)።
*****  *****  *****
የትረካ ምንጮች
  1. አል-ቁርአኑል ከሪም፡ (ቅዱስ ቁርኣን በዐረብኛ)
  2. ቅዱስ ቁርአን፡ የአማርኛ ትርጉም በሰይድ መሀመድ ሳዲቅና በሐጂ ሙሐመድ ሣኒ ሐቢብ፣ አዲስ አበባ፣ 1963
  3. Holy Qur'an፡ English Translation By Abdullah Yusuf Ali, London, 1945
  4. ሰሒሕ አል-ቡኻሪ፣ ቅጽ 1፣ አንደኛ መጽሐፍ፣ ሐዲስ ቁጥር 3
  5. ዐብዱል መሊክ ኢብኑ ሒሻም፣ ሲረቱ ረሱሉላህ” (የአላህ መልዕክተኛ የህይወት ታሪክ)
  6. ሐጂ ሙሐመድ ሣኒ ሐቢብ፡ እስልምና እና የታላቁ ነቢይ  የሙሐመድ ታሪክ፣ አዲስ አበባ፣ 1988