Tuesday, March 19, 2013

የገለምሶው “አቦ ደርጂ” ጨዋታዎች (ክፍል አንድ)



ጸሓፊ- አፈንዲ ሙተቂ

በተወለድኩባት ከተማ ስማቸው ገኖ ከሚወራላቸው ጥቂት ሰዎች መካከል አንዱ ናቸው። እኝህ ሰው የናጠጠ ቱጃር ወይንም የመሬት ከበርቴ አልነበሩም። “የሼኽ እገሌ ቤተሰብ አባል” ወይም “የሸሪፍ እገሌ ዝሪያ” የሚባሉ አይነትም አይደሉም። ይሁንና የከተማችን ተወላጆች ከመሬት ከበርቴም ሆነ ከናጠጠ ቱጃር በላይ ያስታዉሷቸዋል። በተለይ ከእርሳቸው ጋር በጉርብትናና በአጥቢያ (ሰፈር) የምናዛመድ ሰዎች ዘወትር አንዘነጋቸውም።

የአቦ ደርጂ መኖሪያ ቤት በፎቶው ላይ ከሚታየው ታፔላ ፊት ለፊት ያለው ነው (photo by: Ramzi Jamaal)
   ደርጂ ሙሳ ይባላሉ። ተወላጅነታቸው በጭሮ (ዐሰበ ተፈሪ) ቢሆንም ከጣሊያን ዘመን ጀምሮ ህይወታቸው እስክታልፍ ድረስ በገለምሶ ከተማ ነው የኖሩት። በቀልደኝነታቸውና በጨዋታ አዋቂነታቸው የከተማው ሰው በሙሉ ይወዳቸዋል። መከራ በገጠማቸው ጊዜ ከጥቃት ለማምለጥ የሚፈጥሯቸው ብልሀቶችም የብዙዎችን አድናቆት አስገኝተውላቸዋል። በዚህም የተነሳ የከተማችን ነዋሪዎች “አቦ ደርጂ” እያሉ ነው የሚጠሯቸው። (“አቦ” በኦሮምኛ “አባት” እንደማለት ነው። ታዲያ ይህኛው “አቦ” ሲነበብ ጠበቅ ይላል። ላልቶ ከተነበበ ትርጉሙ ይለወጥና “አንተ” እንደማለት ይሆናል)። የ“አቦ ደርጂ” ጨዋታ አዋቂነትና አባ-መላነት ከከተማችንም አልፎ በአጎራባች ከተሞች ጭምር በመናኘቱ በህይወት እያሉ ተረት እስከመሆን ደርሰዋል (ልክ እንደ ጋሼ ስብሃት ማለት ነው)። እነሆ እኔም ከአቦ ደርጂ ጨዋታዎች መካከል ለበረካ ያህል አንዳንዶቹን አጫውታችኋለሁ።
******************
አንድ ጊዜ ጓድ ሊቀመንበር መንግስቱ ኃይለማርያም በገለምሶ አቅራቢያ ያለችውን “ዴፎ” የተሰኘች አነስተኛ ከተማ ለመጎብኘት እንደሚመጡ ይነገራል። የገለምሶ ህዝብም “ቆራጡ መሪያችን በከተማችን ሲያልፉ ሰላምታ እንድትሰጧቸው” የሚል አስገዳጅ ጥሪ ተላልፎለታል። በጥሪው መሰረትም “አቦ ደርጂ” ለጓድ ሊቀመንበር አብዮታዊ ሰላምታ ለመስጠት ከአካባቢው ሰዎች ጋር በሱቃቸው ፊት ለፊት በሚያልፈው መንገድ ዳር ይቆማሉ። ሆኖም “መንጌ” በተባለው ጊዜ አልደርስ አሉ። ለረጅም ሰዓት መንገድ ዳር መቆሙ ያሰለቻቸው አቦ ደርጂ “ለአንድ ሰው ብለው ስራ ያስፈቱናል፤ ይህንን ሁሉ ህዝብ መንገድ ዳር ለረጅም ሰዓት ማስቆም አግባብ ነው? ስራ ፈት ካድሬ ሁሉ!” እያሉ ማጉተምተም ጀመሩ። ለካስ አንድ ነጭ ለባሽ (ሲቪል ለባሽ የደህንነት ሰው) ከአጠገባቸው ቆሞ ይሰማቸው ኖሯል? ወዲያውኑ ፖሊሶችን ጠርቶ “እርምጃ ይወሰድባቸው” ከሚል ትዕዛዝ ጋር ወደ አውራጃው ፖሊስ ጣቢያ አስወሰዳቸው።

የአውራጃው ፖሊስ አዛዥም ከፊቱ የቆሙትን አቦ ደርጂ እያየ “እህስ ሽሜ! ቅድም ምን ስትል ነበር?” በማለት ይጠይቃቸዋል። ነገሩ ክፉ አደጋ ሊያስከትልባቸው እንደሚችል አስቀድሞ የተረዱት አቦ ደርጂም “አሃ! ጫቱን ነው?” አንተ ካልክ እሺ! አንተ እንደፈለግክ አደርጋለሁ!” በማለት በአፋቸው የሚያመነዥኩትን ጫት በፊታቸው ላይ ይለቀልቁት ገቡ። ነገሩ ያስደነገጠው የፖሊስ አዛዥ “አንተ ሰውዬ! ምን እያደረግክ ነው? ማን ነው በጫት ፊትህን አበላሸው ያለህ?” በማለት ደነፋ። አቦ ደርጂም ምንም ሳይሸበሩ “አንተ ካልክ አደርገዋለሁ! ምን ገዶኝ! ይኼው አደርገዋለሁ!” በማለት የታጠቁትን ሽርጥ ፈትተው ጣሉትና ከወገብ በታች ራቁታቸውን ቆሙ። ይሄኔ አዛዡ በጣም ተደናገረና በአቅራቢያው የነበረውን አንድ ፖሊስ ጠርቶ “አንተ ወታደር! ሽማግሌው እብድ ነው! ቶሎ ከዚህ አስወጣው” በማለት ትዕዛዝ ሰጠ። አቦ ደርጂም በዚያች በቅጽበት በፈጠሩት መላ ህይወታቸውን ከሞት አተረፏት።
******************

በደርግ ውድቀት ማግስት አቦ ደርጂ አዲስ ሚስት አገቡ። ይህች ሚስት የደም ግባቷ በጣም የተወራላት ከመሆኗም በላይ በእድሜዋ በሀያዎቹ መጨረሻ ገደማ የምትገኝ ነበረች። እናም ሽማግሌው አቦ ደርጂ ወጣት ሚስት ማግባታቸው በመላው የገለምሶ መንደሮች መነጋገሪያ ሆኖ ነበር። በነገሩ የተገረሙት አንድ ጎልማሳም ወደ አቦ ደርጂ ዘንድ ይሄዱና “አንተ ለራስ ጥርስ የለህ፣ አርጅተሃል፣ ምን ልሁን ብለህ ነው በስተ እርጅና ሚስት የምታገባው?” በማለት ይጠይቁአቸዋል። አቦ ደርጂ በነገሩ እየሳቁ “ወይ ጉድ! እናንተ ጥርሰ በረዶዎች ሚስቶቻችሁን በጥርሶቻችሁ ነው የምትነካከሱት እንዴ?” በማለት ጥያቄውን በጥያቄ መለሱት።
******************

በዚህች ወጣት ሚስታቸው ሳቢያ ነገር የበዛባቸው አባ ደርጂ ሌሎች ሰዎች ሚስቴን ሊያስኮበልሉብኝ ይችላሉ የሚል ፍራቻ አድሮባቸው ነበር ይባላል። ታዲያ ነጅብ ኢድሪስ የሚባለው የከተማችን ነጋዴ በዚያው ሰሞን የደረሰበትን አንድ ነገር እንደሚከተለው አጫውቶኝ ነበር።

አቦ ደርጂ ለቅሶ (ታዚያ) ለመድረስ ራቅ ወዳለ ሰፈር ይሄዱና ይመሽባቸዋል። ወደቤታቸው ለመመለስ ቢፈልጉም የጨለማው ነገር የሽማግሌ አይናቸውን የማይመጥን ሆኖ ያገኙታል። ስለዚህ ለታዚያ (ለቅሶ) በተተከለው ድንኳን ውስጥ ያሉትን ሰዎች ወደ ቤታቸው እንዲያደርሷቸው ትብብር ይጠይቃሉ። በዚህ መሰረትም ከላይ የጠቀስኩት ነጅብ ኢድሪስ ፈቃደኛ ሆኖ እስከቤታቸው ድረስ ሊወስዳቸው ይነሳል።

ሁለቱ ሰዎች መንገዳቸውን ጀመሩ። ነጅብ ባትሪውን ለአቦ ደርጂ ሰጥቶ ለራሱ ፊት ቀድሞ መጓዝ ጀመረ። እናም በአጭር ጊዜ ውስጥ  ከቤታቸው አደረሳቸው። ነጅብ መንገዱን ሳይስት ከቤታቸው መድረሱ ያስገረማቸው አቦ ደርጂ ምስጋናቸውን ካቀረቡለት በኋላ “Ammoo Kharaa mana khiyaa khana akkamitti akkati haffazde?” (“ግን ወደቤቴ የሚያደርሰውን መንገድ እንዴት ነው እንዲህ የሸመደድከው?”) በማለት ከልቡ አሳቁት።

አቦ ደርጂ ወጣት ሚስት ከቤት ውስጥ እንዳላቸው የሚያውቀው ነጅብ “ኖራ ነጭ ነው” እንዲሉት አይጠብቅም። ለዚህም ነው በነገሩ ከአንጀቱ የሳቀው (እኔም ከአቦ ደርጂ ጨዋታዎች ሁሉ በጣም ያሳቀኝ ይህኛው ነው)።
******************

በደርግ ጊዜ ሁሉም ጎልማሶች መሰረተ ትምህርት እንዲማሩ በሚያስገድደው ደንብ መሰረት አቦ ደርጂም ለትምህርት ገብተው ነበር። ግን የትምህርቱ አሰልቺነት በወቅቱ ከነበሩበት የኑሮ ሁኔታ ጋር ተዳምሮ አቦ ደርጂን ያነጫንጫቸው ገባ (በወቅቱ የመጀመሪያ ባለቤታቸውን በሞት የተነጠቁት አቦ ደርጂ ልጆቻቸውን እንደ እናትም እንደ አባትም ሆነው ያሳድጉ ነበር)። በዚህም የተነሳ አንድ ሰበብ ፈጥረው ከትምህርቱ ገበታ ለመጥፋት ወሰኑ። በዚህ ሁኔታ ላይ እያሉም ትምህርቱን የሚያስተምረው አስተማሪ አንድ ቀን የሂሳብ ጥያቄ ያቀርብላቸዋል።
“አቦ ደርጂ፣ አንድ ሲቀነስ አንድ ስንት ነው የሚሆነው?”
“እኔ ስለመቀነስ አላውቅም፤ መደመር ጠይቀኝ”
“እንዴት አያውቁም? ነጋዴ አይደሉም?”
“ነጋዴ ብሆንም ስለመቀነስ አላውቅም”
 
ነገሩ ግራ የገባው አስተማሪ በምሳሌ ማስረዳት አማረውና “ለምሳሌ አቦ ደርጂ፤ አንድ ሙዝ አለኝ እንበል። እርሱን ብበላው ምን ያህል ይቀረኛል?” በማለት ይጠይቃል። አቦ ደርጂም “አይ አስተማሪው! ልጣጩ እንጂ ምኑ ነው የሚቀረው” የሚል ምላሽ ሰጡት። ይህንን የሰሙት በክፍሉ ውስጥ የነበሩት ጎልማሳ ተማሪዎች በሙሉ በሳቅ ያውካካሉ። አስተማሪው ግን በነገሩ ይናደድና ቂም ቢጤ ይቋጥራል።

በሌላ ጊዜ ደግሞ አስተማሪው አንድ ስነ-ግጥም በጥቁር ሰሌዳው ላይ ይጽፍና ተማሪዎቹን “በደብተራችሁ ገልብጣችሁ አሳዩኝ” በማለት ያዛቸዋል። አቦ ደርጂም በደብተራቸው ላይ ምንነቱ የማይገባ ነገር ሙጭርጭር አድርገው ይጽፉና ለማሳረም አስተማሪው ዘንድ ይወስዱታል። ታዲያ መምህሩ ነገሩን ሲያይ በአቦ ደርጂ አድራጎት እጅግ ተደንቆ “ይህ ደሞ ምንድነው?” በማለት ይጠይቃቸዋል። እርሳቸውም “ጽሁፍ ነው” በማለት በአጭሩ ይመልሳሉ። መምህሩም “የምን ጽሁፍ ነው? እንዴትስ ተደርጎ ነው የሚነበበው?” በማለት መልሶ ሲጠይቅ አቦ ደርጂም ዘና በማለት “አስተማሪው! ጽሁፉን ከቻልክ አንብበው፤ ካልቻልክ ለበላይ አካል አስተላልፈው፤ ራስህን ብዙም አታስጨንቀው” የሚል አብሻቂ መልስ ሰጡት። የአቦ ደርጂ ነገር ያልጣመው አስተማሪ “እርስዎ ትምህርት አይፈልጉም፤ስለሆነም ሁለተኛ እዚህ እንዳይመጡብኝ” በማለት አሰናበታቸው። በዚህም ብልሃት አቦ ደርጂ ከመሰረተ ትምህርቱ መድረክ ተለዩ።
(ይቀጥላል)

No comments:

Post a Comment