Monday, January 22, 2018

አልኸዋሪዝሚ- የአልጄብራ አባት





ጸሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ

------
እነሆ ስለሒሳብና ስለ እውቁ የሒሳብ ጀግና በጥቂቱ ልናወጋችሁ ነው፡፡ ጀግናችን ፎቶግራፍ ከተፈጠረበት ዘመን አስቀድሞ የኖረ በመሆኑ ፎቶውን ልናሳያችሁ አንችልም መቼስ!. በምስሉ ላይ የምትመለከቱት የሒሳቡ ጀግና የተወለደበት 1200 ዓመት ሲከበር ታላቋ የሶቪየት ህብረት ያሳተመችውን  የመታሰቢያ ቴምበር ነው፡፡ ሰውየውን ከሶቪየቶች ጋራ ምን አገናኘው? ከወደታች እንመጣበታለን፡፡ አሁን ወጋችንን በመሰረታዊ ጉዳዮች እንጀምር፡፡
          *****
  እስቲ ከዜሮ ጀምሩና በቅደም ተከተል የሚመጡትን ቁጥሮች ጻፉ፡፡ 1 2 3 .. አስር ስትደርሱ ሌላ ቁጥር ለማግኘት አትችሉም አይደል? አዎን! አስር ለማለት ከፈለጋችሁ አንድና ዜሮን ጎን ለጎን በማድረግ ትጽፋላችሁ፡፡ ሌሎቹንም ቁጥሮች ለመጻፍ ከፈለጋችሁ በነዚህ ቁጥሮች ትጠቀማላችሁ፡፡

   በጥንት ዘመን ግን እንዲህ ዓይነት ነገር አልነበረም፡፡ የጥንት ግብጻዊያን ይገለገሉበት በነበረው የሄሮግሊፍ (hieroglyphic) አጻጻፍ ሁሉንም ነገር በተለየ ምስል ስለሚመስሉ የሚጠቀሙባቸው ቁጥሮች ብዛትም ማለቂያ አልነበረውም፡፡ ሮማዊያን በበኩላቸው ፊደልን እንደ ቁጥር ሲጠቀሙ ነው የኖሩት፡፡ ይህኛው የቁጥር ዘዴም ወጥ የሆነ ቀመር ስለሌለው ትልልቅ ቁጥሮችን ለመጻፍ ይቅርና በመቶና በአንድ ሺህ መካከል ያሉ ቁጥሮችን እንኳ ሳይደናግሩ ሊጽፉበት ይከብዳል፡፡ በሌሎች የዓለም ክፍሎች ያሉ የቁጥር ዘዴዎችም (numeration systems) ተመሳሳይ ጉድለቶች አሏቸው፡፡ በመሆኑም ከጭንቀት ለመገላገል የሚፈልግ ሰው በመግቢያዬ ወደጠቀስኩት የአቆጣጠር ዘዴ መመለሱ የግድ ነው፡፡

  ይህ ዘዴ የሂንዱ-ዐረብ የቁጥር ዘዴ (Indo-Arabic Numeration System) ይባላል:: ከስያሜው እንደምትረዱት ህንድ ዐረቢያ በጋራ በመሆን ለዓለም ህዝብ ያበረከቱት ታላቅ ገጸ-በረከት ነው፡፡ የቁጥሮቹ መሰረት የሆኑት ምልክቶች የተወጠኑት ከክርስቶት ልደት በፊት በሀገረ-ህንድ ነው፡፡ እነዚያ ምልክቶችም 1-እስከ 9 ያሉትን ቁጥሮች ብቻ የሚወክሉ ነበሩ፡፡ ከክርስቶስ ልደት በኋላ በመጀመሪያው ምእተ- ዓመት ምልክቶቹ ከህንድ ተሻግረው ወደ ፋርስ፣ ግብጽ፣ ሜሶጶጣሚያ፣ ሶሪያና ዐረቢያ ገቡ፡፡ በነዚህ ሀገራት የሂሳብ ሊቃውንትና በነጋዴዎች እጅ ሲሸከረከሩም ቆዩ፡፡ 800 .. ገደማ ግን አንድ ሰው ከባግዳድ ተነሳና ምልክቶቹን በማሻሻል አሁን ያሉትን ቁጥሮች አስገኘ፡፡

 ታዲያ ይህ ሰው ቁጥሮችን በማስገኘቱ ብቻ አላበቃም፡፡ ከዚያ በፊት የማይታወቁ የሂሳብ ጽንሰ-ሐሳቦችንም ለዓለም አስተዋውቋል፡፡ ከነዚያ ጽንሰ-ሐሳቦች መካከል የመጀመሪያው the concept of Zero” ይባላል፡፡ ሰውዬው ዘጠኙ ቁጥሮች በትክክል ሊሰሩ የሚችሉት ዜሮ ከታከለችባቸው ብቻ መሆኑ ገብቶታል፡፡ በዚህም መሰረት ዜሮን በራሱ በመፈልሰፍ በአስሩ ቁጥሮች ሁሉንም ዐይነት ህልቅ (number) ለመጻፍ እንደሚቻል አሳይቷል፡፡ በተጨማሪም በቁጥሮቹ በትክክል ለመጠቀም ከተፈለገ የሂሳቡ ዓምድ አስር (base ten) መሆን እንዳለበት አስገንዘቧል (ከዚያ በፊት ሂሳቡ ወጥ ዓምድ አልነበረውም፡፡ ግሪኮች አስራ ሁለትን ወይንም ደርዘን ነበር እንደ ዓምድ የሚጠቀሙት፡፡ ለባቢሎኒያ እና ለአሶሪያ ሰዎች ደግሞ የሂሳቡ ዓምድ ስድሳ ቁጥር ነበረ)፡፡
          *****
ለጥንት ሰዎች ሂሳብ ማለት ሁለት ነገር ነው፡፡ አንደኛው በየቀኑ ነገሮችንና የምንደምርበት፣ የምንቀንስበት፣ የምናባዛበትና የምንቀንስበት መሰረታዊው የሂሳብ ዘርፍ ነው፡፡ ይህም አርቲሜቲክ ይባላል፡፡ ሌላኛው ደግሞ ስፋት፣ ርዝመት፣ ወርድ፣ መጠነ ዙሪያ፣ ቁመት ወዘተ የመሳሰሉትን ለመስፈር የምንጠቀምበት ጂኦሜትሪ ነው፡፡

 ታዲያ ከላይ የጠቀስነው የባግዳዱ ሰውዬ ከሁለቱ የሂሳብ ዘርፎች ወጣ በማለት መመራመር ጀመረ፡፡ የምርምሩን ውጤትም ሒሳቡል ጀብር ወል-ሙቃበላ በሚል ርዕስ አሳተመ፡፡ መጽሐፉ በልዩ ልዩ ምሁራን እጅ ሲገባም ጥንት ያልነበሩ የሂሳብ ስልቶችን፣ ስሌቶችንና ዘዴዎችን አጭቆ የያዘ አዲስ የሂሳብ ዘርፍ እንደፈጠረ ታወቀለት፡፡ በመሆኑም አዲሱ የሒሳብ ዘርፍ በመጽሐፉ ስም ሒሳቡል-ጀብር ተብሎ ተሰየመ፡፡ መጽሐፉ ወደ ላቲን ሲተረጎም ደግሞ ስያሜው አልጄብራ ተብሎ ተቀየረ፡፡
          *****
የሒሳብ ሊቅ ሙሐመድ ኢብን ሙሳ ይባላል፡፡ የተወለደውና አብዛኛውን ዘመኑን ያሳለፈው በአሁኗ የኢራቅ መዲና በባግዳድ ውስጥ ነው፡፡ ይሁንና ወላጆቹ ኸዋሪዝም ከምትባለው የመካከለኛው እስያ ክፍለ ሀገር (በአሁኗ ኡዝቤኪስታን ውስጥ የምትገኝ) ወደ ባግዳድ የመጡ በመሆናቸው ራሱን ሲጠራ አል-ኸዋሪዝሚ በሚል ቅጥያ በስሙ ላይ ይጨምር  ነበር፡፡ የዓለም ህዝብም እርሱን በደንብ የሚያውቀው  በተጸውኦ ስሙ ሳይሆን በዚሁ ቅጥያ ነው፡፡ የሒሳብ ሊቃውንት በበኩላቸው ስራዎቹ ዘወትር ይታወሱ ዘንድ አልጎሪዝም (algorithm) የተባለውን የስሌት ዘዴ በስሙ ሰይመውለታል፡፡

 አል-ኸዋሪዝሚ በመላው ዓለም የተከበረ ምሁር ነው፡፡ በዓለም ታሪክ ከፍተኛ ተጽእኖ ፈጣሪ ናቸው ከሚባሉት 100 ሳይንቲስቶች መካከልም ስሙ አለ፡፡ በዚህም የተነሳ እርሱ የተወለደባት ኢራቅ፣ ለተወሰነ ጊዜ የኖረባት ኢራን እና ወላጆቹ የተገኙባት ኡዝቤኪስታን የኔ ነው በሚል ይወዛገቡበታል፡፡ እንግዲህ የቀድሞዋ ሶቪየት ህብረት በምስሉ ላይ የምትመለከቱትን የመታሰቢያ ቴምብር ያሳተመችው አል-ኸዋሪዝሚ የኔ ነው በሚል መነሻ ነው (ኡዝቤኪስታን 1924 እስከ 1991 የሶቪየት ህብረት አካል እንደነበረች አስታውሱ)፡፡
  
ቢሆንም አል-ኸዋሪዝሚን የአንድ ሀገር ብሄራዊ ጀግና ብቻ አድርጎ ማየቱ ለዚህ ዘመን ሰው አይስማማም፡፡ ስራው መላውን ዓለም ያዳረሰ በመሆኑ የሁሉም ህዝቦች ብሄራዊ ሀብት ተደርጎ ቢታይ ነው የሚመረጠው፡፡
  -----
አፈንዲ ሙተቂ
ህዳር 8/2007
በገለምሶ ከተማ ተጻፈ፡፡
---


Sunday, January 21, 2018

ስለ“አዳል” በጥቂቱ




(አፈንዲ ሙተቂ)
------
በመካከለኛው የታሪክ ዘመን (Medieval Era) ኢትዮጵያን፣ ኤርትራን፣ ጅቡቲን፣ ሶማሊላንድን እና ሶማሊያን በሚያቅፈው የአፍሪቃ ቀንድ ቀጣና የተለያየ ቅርጽና አወቃቀር የነበራቸው መንግሥታት ተመሥርተዋል፡፡ ከነዚያ መንግሥታት መካከል ከአስር የማያንሱት የሙስሊም ሱልጣኔቶች ነበሩ፡፡ ከሱልጣኔቶቹ መካከል ስሙ በጣም ገንኖ የነበረውና በአፍሪቃ ቀንድ ሕዝቦች ታሪክ፣ ጂኦ-ፖለቲካ እና የህዝቦች ስብጥር ላይ መጠነ-ሰፊ አሻራ ትቶ ያለፈው ደግሞ ዋና ከተማውን በዘይላ እና በሀረር ያደረገው የአዳል ሱልጣኔት ነው። እንግዲህ በዚህ መጽሐፍ የተጻፈው የዚያ ሱልጣኔታዊ መንግሥት ታሪክ ነው፡፡
               
የአዳል ሱልጣኔት ታሪክ ከሌሎች ታሪኮች ጋር ተዳብሎ ሲጻፍ ተመልክተናል፡፡ ይሁን እንጂ ሙሉ ትኩረታቸውን በሱልጣኔቱ ታሪክ፣ ጥንታዊ ባህል፣ ትውፊቶችና ቅሪቶች ላይ ያደረጉ መጻሕፍት በጣም ጥቂት ናቸው፡፡ እስከ ዛሬ ድረስ የአዳል ሱልጣኔትን ታሪክ በተናጥል ለመጻፍ የጣሩት ከሶስት የማይበልጡ ደራሲዎች ብቻ ናቸው (ዝርዝሩ በመጽሐፉ መግቢያ ላይ በሰፊው ቀርቧል)፡፡

   እነዚህ ጥቂት ሥራዎች የአዳል ሱልጣኔትን ታሪክ በማሳወቅ ረገድ ከፍተኛ ጠቀሜታ አላቸው፡፡ ነገር ግን ድርሰቶቹ ብዙኃኑ የሀገራችን ተደራሲ በማያነበው የዐረብኛ ቋንቋ ነው የተጻፉት፡፡ በሁለተኛ ደረጃም መጻሕፍቱ በቀላሉ ተፈልገው የሚገኙ አይደሉም፡፡ እንግዲህ የአዳል ሱልጣኔትን ታሪክ በተናጥል እንድጽፈው ያነሳሳኝ ቀዳሚ ነጥብ በዘርፉ ያሉን ድርሰቶች ውስን መሆናቸውና እስከ አሁን የተጻፉትም ከታሪኩ ባለቤቶች ዘንድ በሰፊው አለመድረሳቸው ነው፡፡

    በሌላ በኩል ከላይ የተጠቀሱት መጻሕፍትም ሆኑ ሌሎች ድርሰቶች ያልዳሰሷቸው የሱልጣኔቱን ታሪክ የሚመለከቱ ጉዳዮች አሉ፡፡ ለምሳሌ ሱልጣኔቱ የተመሠረተበት ታሪካዊ ዳራ (historical background) በጽሑፍ ምንጮች በደንብ አልተፈተሸም፡፡ ለአዳል ሱልጣኔት ምሥረታ መንስኤ የሆኑ ማኅበረ-ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ሁኔታዎችም በወጉ አልተዳሰሱም፡፡ እንደዚሁም ደግሞ በርካታ ጸሐፍት ሱልጣኔቱ በተማከለባቸው ግዛቶች የሚኖሩት ህዝቦች የሚናገሯቸውን ትውፊቶች በጽሑፍ ከሚታወቀው ታሪክ አንጻር ለመመዘን ሲጥሩ አይታዩም፡፡ ይህንን መጽሐፍ እንድጽፍ የቀሰቀሰኝ ሁለተኛ ነጥብም ከአዳል ታሪክ ጋር መነሳት ያለባቸው በርካታ አንኳር ጉዳዮች ከግራና ከቀኝ በደንብ አለመዳሰሳቸው፣ እንደዚሁ ደግሞ በጽሑፍ ምንጮች ያልተወሱና የአዳል ሱልጣኔት ታሪክ ግንዛቤአችንን ሊያጎለብቱ የሚችሉ ርካታ ጉዳዮች መኖራቸው ነው፡፡  

  በሶስተኛ ደረጃ መወሳት ያለበት በሱልጣኔቱ ታሪክ አጻጻፍ ላይ የሚታየው ከፍተኛ ጉድለት ነው፡፡ የተለያዩ ደራሲዎች ስለሱልጣኔቱ ታሪክ የጻፏቸው ዘገባዎች በአብዛኛው ወገናዊነት ያጠቃቸዋል፡፡ ወገናዊ ካልሆኑት ጸሐፊዎች መካከል ደግሞ አንዳንዶቹ ታሪካዊ መረጃዎችን በአግባቡ አያሰፍሩም፡፡ አንዳንዶቹ ደራሲዎችም የሰበሰቧቸውን የቃልና የጽሑፍ መረጃዎችን በደንብ አይተነትኑም፡፡ የአዳልን ታሪክ ለማጥናት ያነሳሳኝ ሳልሳይ ነጥብም በሱልጣኔቱ ታሪክ አጻጻፍ፣ የመረጃ ትንታኔ እና የታሪክ ምዝገባና አስተምህሮ ዐውዶች (historiography) ላይ የሚታዩት ዘርፈ ብዙ ችግሮች ናቸው፡፡

  እነዚህንና ሌሎችንም አስፈላጊ ነጥቦች እንደ መነሻ በማድረግ በሱልጣኔቱ ታሪክ ላይ ያተኮረ ጥናት በተለያዩ ዘዴዎችና በልዩ ልዩ አካባቢዎች ሳከናውን ከቆየሁ በኋላ ይህንን መጽሐፍ አዘጋጅቼአለሁ፡፡
***** 
   አሁን የምታነቡት መጽሐፍ ለብቻው ከላይ የዘረዘርኳቸውን ክፍተቶች ያሟላል ብዬ ለመናገር አልደፍርም፡፡ በአዳል ሱልጣኔት ታሪክ አጻጻፍ ላይ የሚታዩት ዘርፈ-ብዙ ችግሮች በዚህ መጽሐፍ ብቻ ይቀረፋሉ የሚል እሳቤም የለኝም፡፡ ቢሆንም የሱልጣኔቱን ታሪክ በማጥናት መሰል ሥራዎችን ለማሳተም ለሚፈልጉ ወገኖች እንደ አቅጣጫ ጠቋሚ ሊያገለግል ይችላል ብዬ አምናለሁ፡፡

የዚህን መጽሐፍ ይዘት በጥቅሉ እንደሚከተለው ማቅረብ ይቻላል፡፡

·       መጽሐፉ ስድስት ክፍሎች አሉት፡፡ የመጀመሪያው ክፍል ክፍል ጥናቱ የተካሄደበትን ጊዜ እና ዘዴ፣ ለጥናቱ ያገለገሉትን ዋነኛ የመረጃ ምንጮች፣ ደራሲው የተጠቀማቸውን የመረጃ ትንተና እና የማስረጃ ምዘና ስልቶች፣ መጽሐፉ የተቀናበረበትን መንገድና አንባቢያን በንባባቸው ወቅት ሊገነዘቧቸው የሚገቡ መመሪያዎችን ይዘረዝራል፡፡

·       ሁለተኛው ክፍል ለአዳል ሱልጣኔት ምሥረታ መንስኤ በሆኑ ኩነቶችና የሱልጣኔቱ መነሻ በነበሩት ቀደምት  መስተዳድሮች ታሪክ ላይ ያተኩራል፡፡ በዚህም መሠረት በቅድሚያ እስልምና በኢትዮጵያና በአፍሪቃ ቀንድ የተስፋፋበትና እስላማዊ መስተዳደሮች የተመሠረቱባቸው ሂደቶች ተዳስሰዋል፡፡ በማስከተል ደግሞ በሀገራችንም ሆነ በአፍሪቃ ቀንድ ቀጣና ስም ተክለው ያለፉት የሸዋ-መኽዙሚ ሱልጣኔት ታሪክ እና የኢፋት-ወላስማ ሱልጣኔት ታሪክ በሰፊው ቀርበዋል፡፡

·       ሶስተኛው ክፍል የአዳል ሱልጣኔት ከተመሠረተበት ዘመን ጀምሮ የተለመደው የሱልጣኔቱ የአመራር ዘይቤ በ1492 ገደማ እስከተለወጠበት ጊዜ ድረስ የነበረውን ታሪክ ይዳስሳል፡፡ በተለይም በአዳል-ወላስማ ሱልጣኖችና በኢትዮጵያ ሰለሞናዊ ዐፄዎች መንግሥት መካከል የተካሄደው ትንቅንቅ በስፋት የቀረበው በዚህኛው ክፍል ነው፡፡ ከዚህ ሌላም በዚህኛው ክፍል የአዳል ሱልጣኔት መሬት፣ ህዝብ፣ የግዛት ወሰን፣ አውራጃዎችና ግዛቶች፣ ከተሞች፣ የሱልጣኔቱ የአስተዳደር ሁኔታና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች፣ እንዲሁም ከርሱ ጋር በተጻራራሪነት የቆመው የኢትዮጵያ ሰለሞናዊ ዐፄዎች መንግሥት የስልጣን ተዋረድ፣ የአስተዳደር አወቃቀርና የአገዛዝ ፍልስፍና፣ የጦር ኃይል፣ ኢኮኖሚ (በተለይም የመሬት ስሪት)፣ የሃይማኖት ተዋስኦ፣ የውጪ ግንኙነቶች ወዘተ… ተዳስሰዋል፡፡

·       አራተኛው ክፍል ከ1492 ጀምሮ ኢማም አሕመድ ኢብራሂም የአዳልን መራሄ መንግሥትነት ስልጣን ሙሉ በሙሉ እስከተቆጣጠረበት ጊዜ ድረስ በነበረው የሱልጣኔቱ ታሪክ ላይ ያተኩራል፡፡ ይህ ክፍል ከሌሎቹ የሚለየው በክፍሉ የቀረበው ትረካ በአዳል የጦርና የፖለቲካ መሪዎች (አሚር ማሕፉዝ፣ ገራድ አቡን፣ ኢማም አሕመድ እና ሱልጣን አቡበከር) ዙሪያ የተዋቀረ በመሆኑ ነው፡፡

·       ክፍል አምስት የመጽሐፉ መደምደሚያ የተጻፈበትና የአዳል ሱልጣኔት ታሪክን በበለጠ ሁኔታ አሟልቶ በሰነድ ለማስቀመጥ መከናወን ያለባቸው ሥራዎች የተጠቆሙበት ነው፡፡ በጥናቱ ሂደት ድጋፋቸውን ለለገሱ ግለሰቦችና ተቋማት ምስጋና የቀረበውም በዚህኛው ክፍል ነው፡፡

·       ክፍል ስድስት የተለያዩ አባሪዎች፣ የዋቢ ሰነዶች ዝርዝር እና የመጽሐፉ መጠቁም (index) የተካተቱበት ነው፡፡ ከመጽሐፉ አባሪዎች መካከል ሁለቱ በጥንት ዘመን በዐረብኛ ቋንቋ የተጻፉትና ብዙዎች (እኔን ጨምሮ) ለዓመታት ሊያገኟቸው ሲቸገሩባቸው የነበሩት “የመኽዙሚ ሱልጣኖች ዜና መዋዕል” እና “የወላስማ ሱልጣኖች ዜና መዋዕል” የሚባሉት የታሪክ ሰነዶች ናቸው፡፡ ተመራማሪዎችና የሱልጣኔቱን ታሪክ ለማጥናት የሚሹ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ሰነዶቹን በቀላሉ ያገኟቸው ዘንድ በተጻፉበት የዐረብኛ ቋንቋ ታትመዋል፡፡
----
ታሪክን የማጥናት አጋጣሚ የተፈጠረልኝ በ2001 ዓ.ል. የጥንታዊቷ የሀረር ከተማ ነዋሪ ለመሆን በመብቃቴ ነው፡፡ የአዳል ሱልጣኔትን ታሪክ የማጥናት ልዩ ፍላጎት ያሳደሩብኝ ግን የሰሜን ምሥራቅ አፍሪቃ ሀገራትንና የህዝቦቻቸውን ታሪክና አንትሮፖሎጂ በሰፊው የጻፉት የዶ/ር ኤንሪኮ ቼሩሊ እና የፕሮፌሰር ኡልሪች ብራውኬምፐር ሥራዎች ናቸው፡፡ በመሆኑም መጽሐፉ ለነዚህ ምሁራን መታሰቢያ እንዲሆን ተበርክቷል፡፡

ይህ መጽሐፍ በአዳል ሱልጣኔት ታሪክ ዙሪያ ልጽፋቸው ካሰብኳቸው ድርሰቶች መካከል የመጀመሪያው ነው፡፡ የርሱ ቀጣይ የሆነው ሁለተኛ መጽሐፍም ሙሉ በሙሉ ተጠናቅቆ የኅትመት ጊዜውን እየጠበቀ ይገኛል፡፡ ወቅቱን ባላውቅም በቅርቡ ወደ አንባቢያን አደርሰዋለሁ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። የመጽሐፉን ሶስተኛ ክፍል ለማዘጋጀት የሚደረገው እንቅስቃሴም ተጀምሯል፡፡ እርሱንም በቅርብ ጊዜያት ለማጠናቀቅ እሞክራለሁ፡፡ ለሁሉም ፈጣሪያችን ዕድሜና ጤና ይስጠን! አሚን!
  
አፈንዲ ሙተቂ                              
ሀረር፣ ምሥራቅ ኢትዮጵያ
ሀምሌ 2009 ዓ.ል.
---------
ü መጽሐፉ በአዲስ አበባም ሆነ በክልል ከተሞች ይገኛል፡፡ የመጽሐፉ ዋና አከፋፋይ አዲስ አበባ ለገሀር አካባቢ የሚገኘው ጃዕፈር መጻሕፍት መደብር ነው (ስልክ ቁጥሩ 0911-12 53 24 ነው)፡፡
ü የአንዱ መጽሐፍ መሸጫ ዋጋ 130 ብር ነው (በውጭ ሀገራት 30 ዶላር ነው)፡፡