Saturday, January 14, 2017

ከግብጻዊው ወጣት ጋር


(አፈንዲ ሙተቂ)
----
ወደ ዱባይ በመጣሁ በሁለተኛው ሳምንት ይመስለኛል። እኔና ባለቤቴ "ኮርኒች" ከሚባለው የቱሪስቶችና የዋናተኞች መናኸሪያ በሚገኝ ካፍቴሪያ ላይ ተሰየምን። ወዲያውኑ አንድ ልጅ እግር አስተናጋጅ እየተጣደፈ መጣ።

"ዐላ ኺድማቲኩም ሰይዳቲ" አለን በዐረብኛ። "ልታዘዛችሁ ዝግጁ ነኝ" ማለቱ ነው። ባለቤቴ ጭማቂ አዘዘች። እኔ ሳንድዊች መብላት አምሮኝ ስለነበረ "ሳንዱች መውጁድ?" አልኩት ("ሳንድዊች አላችሁ እንዴ" እንደማለት ነው)። "ኤይዋ መውጉድ" በማለት መለሰልኝ!! ልጁ ግብጻዊ እንደሆነ ገባኝና "አንት ሚን መስር?" አልኩት። "ኤይዋ! አነ ሚን መስር" (አዎ! ከግብጽ ነኝ!) ብሎኝ የታዘዘውን ሊያመጣ ሄደ። ያ ልጅ በጣም የሚጣደፍ ከመሆኑ የተነሳ ግብጻዊ መሆኑን እንዴት እንዳወቅኩ አልጠየቀኝም። ቢሆንም ፎርሙላውን ለናንተ ልጻፈው።

ከዐረብኛ በርካታ ዘዬዎች መካከል የግብጹ ዘዬ በአንድ ነገር ይለያል። ይኸውም "ጀ" የሚባል ድምጽ የሌለው መሆኑ ነው። በዋናው የአል-ፉስሐ ዐረብኛ (Classical Arabic) የተጻፈና "ጀ" የሚል ድምጽ ያለበት ቃል በግብጾች ዘዬ በ"ገ" ድምጸት ነው የሚነበበው። ለዚህም ነው ግብጾች ታዋቂ መሪያቸውን "ጀማል ዐብዱናስር" በማለት ፈንታ "ገማል ዐብዱናስር" እያሉ የሚጠሩት። ያ ግብጻዊ ወጣትም "መውጁድ" በማለት ፈንታ "መውጉድ" ብሎ የመለሰልኝ ለዚሁ ነው (ይህ "ጀ"ን ወደ "ገ" የመቀየር አካሄድ ለቅዱስ ቁርአን ብቻ አይሰራም። በቁርአን ምንባብ ወቅት ሁሉም ፊደል በትክክለኛው ድምጽ መነበብ አለበት)።

በሌላ ምሽት በዚያው ስፍራ በእግር እየተንሸራሸርን ነበር። ያ ግብጻዊ ወጣት ወደ አስፋልቱ ወጥቶ በመንገዱ ላይ የሚያልፈውን ሰው ሁሉ "ጥሩ እራት! ከጥሩ መስተንግዶ ጋር! ወደኛ ሬስቶራንት ይግቡ" እያለ ይለማመጣል። በመሃሉ አንድ ቆነን ያለ ወፍራም ወጣት "ወደዚያ ሂድልን ባክህ!! መንገዱን ትዘጋብናለህ እንዴ!!" በማለት ገፍትሮት አለፈ። ግብጻዊውም "አረ ባክህ ተወን! ለራስህ መለይካ እየመሰልክ ትረማመዳለህ፥ እኛም ሰርተን ይለፍልን እንጂ" እያለ ለፈለፈ።

ታዲያ አንድ ነገር ውልብ አለብኝ። በልቤ "በዚህ ግብጻዊ ላይ ሙድ መያዝ አለብኝ" አልኩ። እናም ተጠጋሁትና "ኸሊ ያ ጋሊ! ሃዳ መጅኑን" አልኩት (ወዳጄ ተወው! ይሄ እኮ እብድ ነው" እንደማለት ነው)። ታዲያ ልጁም በሰውዬው አድራጎት ቅጥል ብሎ ኖሮ ጠንከር ባለ አነጋገር "ኤይዋ ሃዳ መግኑን" አለኝ። ባሰብኩት መንገድ ስለመለሰልኝ ከልቤ ሳቅኩ። እርሱም ከጣሪያ በላይ እያንባረቀ ከኔ ጋር ሳቅ። ( እኔ የሳቅኩት "መጅኑን" የሚለውን ቃል በግብጻዊው ስልት "መግኑን" ብሎ ስለተናገረው ነው። እርሱ ግን በዚያ አውደልዳይ መንገደኛ የሳቅኩ ነበር የመሰለው)።

ግብጻዊው አቀራረቤ ስላማረው ነው መሰለኝ የመጣሁበትን ሀገር ጠየቀኝ። ከኢትዮጵያ መሆኔን ነገርኩት። እርሱም ለመሸኛ የሚሆነኝን ንግግር እንዲህ በማለት አሸከመኝ!
"ኢትዮጵያ በለድ ገሚል"
እኔም ደግሜ ሳቅ አከናነብኩት። እርሱም በሃይለኛው ከኔ ጋር ሳቀ!!
(ሚስኪን!! እርሱ እኮ "ኢትዮጵያ ቆንጆ ሀገር ናት" እያለኝ ነበር። እኔ ግን "ጀ"ን ወደ "ገ" ቀይሮት ሲናገረው  ልስማው ብዬ ነበር ያዋራሁት። አላህ ይቅር ይበለኝ እንግዲህ!!)
----
"አንተ ስለ ሰው አነጋገር ምን አሳሳበህ?" ትሉኝ ይሆናል። በኢትኖግራፊ ምርምር ውስጥ ስትገቡ እንዲህ ነው የሚያደርጋችሁ። ስለሰዎች አነጋገር፣ የቃላትና የዐረፍተ ነገር አሰካክ፣ አለባበስ፣ አመጋገብ፣ ጌጣጌጦች፣ የጸጉር አሰራር፣ ልዩ ልዩ ልማዶች ወዘተ በሰፊው ለማወቅ ትጨነቃላችሁ። ታዲያ ይህ አመልና አምሮት ያለጊዜውና ያለቦታው መዋል የለበትም። ተወዳጁ ገጣሚ ጀላሉዲን ሩሚ ይህንኑ በአንድ ወግ አጫውቶን ነበር።

ሰውዬው የነህዊ (ሰዋስው) መምህር ናቸው። ማንኛውም ሰው የሰዋስው ህግን ጠብቆ ያናግረኝ ባይ ነበሩ። በአነጋገሩ ስህተት የፈጸመውን ሁሉ "ያንተ ሰዋስው ችግር አለበት" ይሉት ነበር። ታዲያ እኚህ ሰውዬ በአንድ ሰፈር ሲያቋርጡ የውሃ ጉድጓድ ውስጥ ይወድቃሉ። እዚያ ሆነው ቢጣሩ ማንም ሊደርስላቸው አልቻልም። ወደ ውሃው ለመስጠም ሲቃረቡ ግን በመንገዱ በማለፍ ላይ የነበረ ገበሬ በድንገት ድምጻቸውን ሰምቶ ሊረዳቸው መጣ። መምህሩ ነፍሳቸውን በማዳን ፈንታ የገበሬው አነጋገር አስጨነቃቸው። እናም "ወዳጄ! ስትናገር እኮ የሰዋስው ህግ ጥሰኻል" አሉት።

"ደግ ነው እንግዲህ!" አለ ገበሬው፡ "ሰዋስው ተምሬ እስክመጣ ድረስ እዚሁ ይቆዩኝ!"

ከእንደዚህ ዓይነቱ ይሰውረን!! መልካም ጊዜ ለሁላችሁም ተመኝተናል!!
-----
አፈንዲ ሙተቂ
ዱባይ፥ የተባበሩት ዐረብ ኢማራት
January 13/2017

Tuesday, January 19, 2016

ፕሮፌሰር አቢር እና ፕሮፌሰር ሀጋይ ኤርሊክ


አፈንዲ ሙተቂ
---
የስራ ግዴታዬ ሆኖ ከህዳር ወር 2007 (November 2014) ጀምሮ በመካከለኛው ዘመን የኢትዮጵያ ታሪክ ዙሪያ የተጻፉ ሰነዶችን እየመረመርኩ ነው፡፡ በዚህም ድሮ የማላውቃቸውን አስደናቂና አስገራሚ ታሪኮች ለማወቅ ችያለሁ፡፡ ለረጅም ጊዜ እንቆቅልሽ ሆነው ሲያስቸግሩኝ ለነበሩት ጉዳዮችም ምላሽ አግኝቻለሁ፡፡ ለብዙ ዓመታት ስፈልጋቸው የነበሩትን ምርጥ መጻሕፍትንም አግኝቼ ይዘታቸውን በቅርበት ለማወቅ ችያለሁ፡፡
 
ታዲያ በዚህ ምርመራዬ ያስተዋልኳቸው ሌሎች ጉዳዮችም አሉ፡፡ ከነርሱም አንዱ አንዳንድ ጮሌዎች ታሪክን በመጻፍ ስም ፖለቲካን የሚያሸከረክሩበት ጥበብ ነው፡፡ ለዚህ ዋቢ ይሆነኝ ዘንድ የአንድ ሀገር ዜጋ የሆኑ ሁለት ምሁራንን ልጥቀስ፡፡
----
ሞርዴኻይ አቢር (Mordechai Abir) የሚባል ስም ታውቃላችሁ?…. አዎን! ስለ “ዘመነ መሳፍንት” የተጻፉ ጽሑፎችን ያነበበ ሰው “አቢር” የሚለውን ስም በደንብ ያስታውሳል፡፡ እኝህ ሰው የቀድሞው “ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሤ ዩኒቨርሲቲ” (የአሁኑ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ) የታሪክ ፕሮፌሰር ነበሩ፡፡ ደርግ ስልጣን ከተቆጣጠረ በኋላ ደግሞ ወደ እስራኤል በመጓዝ በኢየሩሳሌም በሚገኘው የሂብሩ ዩኒቨርሲቲ መምህርነት አገልግለዋል፡፡ አቢር “The Era of Princes” በሚል ርዕስ የጻፉት መጽሐፍ በምሁራን ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት አለው፡፡ እኔም በአንድ ወቅት (የዛሬ አስር ዓመት ገደማ) መጽሐፉን አንብቤው ነበር፡፡

 አቢር በጣም ዝነኛ የሆነ ሌላ መጽሐፍም አላቸው፡፡ ርዕሱ “Ethiopia and the Red Sea” ይሰኛል፡፡ በየትኛውም ወገን ሆኖ ስለኢትዮጵያ ታሪክ የሚጽፍ ሰው ይህንን መጽሐፍ እየደጋገመ ይጠቅሳል፡፡ ታደሰ ታምራት፣ ሪቻርድ ፓንክረስት፣ ነጋሶ ጊዳዳ፣ መርዕድ ወልደ አረጋይ፣ ሙሐመድ ሐሠን፣ ላጵሶ ድሌቦ፣ ኡልሪች ብራውኬምፐር፣ አባስ ሐጂ ገነሞ፣ አሌሳንድሮ ጎሪ እና ሌሎችም ፕሮፌሰሮች የአቢርን መጽሐፍ እንደ ምንጭ ይጠቀሙበታል፡፡ ሰለሰሜን ኢትዮጵያም ሆነ ስለደቡቡ ክፍል በተጻፈ መጽሐፍ ውስጥ “Abir” የሚለውን ስም በግርጌ ማስታወሻ እና በመጽሐፉ ማጣቀሻ ክፍል ውስጥ ማየት የተለመደ ነው፡፡ ነገር ግን “Ethiopia and the Red Sea”ን ለረጅም ጊዜ አይቼው ስለማላውቅ በምሁራን ዘንድ ተመራጭ የሆነበትን ምክንያት ለመረዳት ስቸገር ቆይቻለሁ፡፡ ዘንድሮ ግን ፈጣሪ ብሎልኝ  አግኝቼዋለሁ፡፡  ብዙ ጊዜ እየመላለስኩ ካየሁት በኋላም መጽሐፉ በምሁራን ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት ያገኘበትን ምክንያት ለመረዳት ችያለሁ!!

አዎን! ፕሮፌሰር አቢር ከልቡ ምሁር ናቸው፡፡ እውነተኛ ምሁር! መጽሐፋቸውን ያጠናቀሩት በእውነተኛ ምሁራዊ መንገድ ነው፡፡ ብዙዎችን እንቅ አድርጎ ሊያሰምጣቸው የሚታገላቸው ኢ-ምሁራዊ ሸፍጥና ውንብድና በመጽሐፋቸው ውስጥ የለም፡፡ አድሎ፣ መረጃ ማምታታት፣ የተወላገደ እይታ፣ ማስመሰል፣ መሸፈጥ ጂንኒ ጀቡቲ በመጽሐፉ ውስጥ አይታዩም፡፡ በመሆኑም “Ethiopia and the Red Sea” በህይወቴ ከገጠሙኝ አጃዒበኛ መጻሕፍት መካከል አንዱ አድርጌ መዝግቤዋለሁ፡፡ እውቀትን መገብየት ለሚሻ ሰው ግሩም መማሪያ ነው፡፡ ለተመራማሪዎችና ለተማሪዎች እጅግ በጣም አስፈላጊ የሆነ ማጣቀሻ ነው፡፡

ፕሮፌሰር አቢር በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ስድስት መጻሕፍትን ጽፈዋል፡፡ ሁሉም መጻሕፍት በምሁራን ዘንድ ከፍተኛ ከበሬታ አላቸው፡፡ ከነርሱ መካከል ከላይ የጠቀስኳቸው ሁለት መጻሕፍት የዓለማችን ቁጥር አንድ ኢንሳይክሎፒዲያ በሆነው “ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ” ቀዳሚ የማጣቀሻ ምንጮች በመሆን recommend ተደርገዋል፡፡
                       
ፕሮፌሰር አቢር እስራኤላዊ ናቸው፡፡ ታዲያ በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ ምርምር ሲያደርጉ የነበሩት እስራኤላዊ እሳቸው ብቻ አልነበሩም፡፡ ሌሎችም በዘርፉ ብዙ ስራዎችን አቅርበዋል፡፡ ከነርሱም አንዱ ሀጋይ ኤልሪክ ነው፡፡ “ሐጋይ ኤርሊክ” የሚለውን ስም ካወቅኩ አስራ አምስት ዓመታት አልፏል፡፡ ነገር ግን ከመጽሐፎቹ ያነበብኩት Ethiopia and the Middle East የሚል ርዕስ ያለውን ብቻ ነው፡፡ ሀጋይ ከመጽሐፎቹ ይልቅ በሴሚናሮችና ዓለም አቀፍ ኮንፈረንሶች ላይ የሚያቀርባቸውን በርካታ አጫጭር ጽሑፎችን ነው ያነበብኩት፡፡ ከህዳር 2007 ወዲህ ባለው ጊዜ ውስጥ ግን ሶስት ያህል መጽሐፎቹን አይቼለታለሁ፡፡ እናም አጃዒብ አልኩ!!

  ይገርማል!! ፕሮፌሰር ሃጋይ አወዛጋቢ ሰው ሆኖ ብቅ ያለው በቅርብ ዘመናት በሚጽፋቸው ጽሑፎቹ ይመስለኝ ነበር፡፡ ነገር ግን ሰውየው ከመነሻው ጀምሮ የተወላገደ እይታ ያለው መሆኑን ነው ያስተዋልኩት፡፡ ምሁራዊ ውንብድና በመጽሐፎቹ ውስጥ እግሩን አንሰራፍቷል፡፡ ከሀጋይ መጽሐፍ ፖለቲካ እንጂ አንዳች የታሪክ እውቀት አይጨበጥም፡፡ ደግሞም የብዙዎቹ መጻሕፍት ጭብጥ “ኢትዮጵያ ራሷን ካልጠበቀች በሙስሊም አክራሪዎች ልትዋጥ ትችላለች” የሚል ነው፡፡ ባጭሩ “ሃጋይ” የእስራኤሉ ሞሳድ በኛ ላይ የተከለው የማስፈራሪያ ሳይኮሎጂስት እንጂ የታሪክ ምሁር ሆኖ አልተገኘም፡፡

በጣም የሚገርመው ደግሞ ሃጋይ ሌሎች ፀሐፊዎችን የሚፈርጅበት ድፍረቱ ነው፡፡ አንድን ክስተት ከርሱ በተለየ አኳኋን ለጻፉ የታሪክ ምሁራን በቶሎ ስም ያወጣላቸዋል፡፡ ሰውዬው ክርስቲያን ከሆነ “ኮሚኒስታዊ አስተሳሰብ ስላለው ነው” ይለዋል፡፡ ሙስሊም ምሁራንን ደግሞ ሁለት ሰሞችን ይሸልማቸዋል፡፡ ጸሐፊው የመካከለኛው ዘመን ሰው ከሆነ “Fanatic writer” ይለዋል፡፡ ፀሐፊው የዘመናችን ሰው ከሆነ ግን “Radical Islamist writer” ይለዋል፡፡ ከርሱ የሚቃረን ትርክት የጻፉ ሰዎችን እንዲህ ብሎ በሚፈርጅ ሰው የተጻፈ መጽሐፍ የታሪክ ማጣቀሻ የሚሆንበት አግባብ በጭራሽ የለም፡፡

የሀጋይ የላሸቀ ምሁራዊ በዚህ ብቻ የተገታ አይደለም፡፡ የታሪክ መረጃዎችን ለራሱ እንደሚመቸው እየገለባበጠ ይጽፋል፡፡ ለምሳሌ ቅዱስ ቁርኣን የአማርኛ ትርጉም በብዙ ምሁራን ተሳትፎ የተከወነ ሆኖ ሳለ (ዋነኞቹ ተርጓሚዎች ሼኽ ሰይድ ሙሐመድ ሳዲቅ እና ሃጂ ሙሐመድ ሣኒ ሐቢብ ቢሆኑም) እርሱ ግን “ትርጉሙን ያከናወኑት ሃጂ ዩሱፍ ዐብዱራሕማን ነው” ይለናል፡፡ ሀጋይ እንዲህ የሚለው ሃጂ ዩሱፍን ለማድነቅ እንዳልሆነ ልብ በሉ፡፡ ይህንንም ትረካ የፈጠረው እርሱ በአድናቆት አቅሉን የሚስትላቸው ሼኽ ዐብዱላሂ ሙሐመድ (ዐብዱላሂ አል-ሐበሺ) በ1948 ከኢትዮጵያ የተባረሩት ሃጂ ዩሱፍ ዐብዱራሕማን በዶለቱት ሴራ ነው በሚል ለሚዘበዝበው ትረካ እንደማስረጃ ለመጠቀም ፈልጎ ነው፡፡ አንባቢያን “ሃጂ ዩሱፍ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሤን አባብለው ሼኽ ዐብዱላሂ ከሀገር እንዲጠፉ የማድረግ አቅም ነበራቸው እንዴ” ብለው ሲጠይቁ የሃጋይ ኤርሊክ ጽሑፍ “ሰውዬው እንዲያ ማድረግ ይቅርና በቅቤ ምላሳቸው ንጉሡን በማሳመን ቅዱስ ቁርኣን እንዲተረጎም ያደረጉ ሼኽ ነበሩ” የሚል መልስ ይሰጣቸዋል ማለት ነው፡፡ ይህቺ ነች ዘዴ!! ይህቺ ነች ሸፍጥ!!

በሌላ በኩል ሃጋይ ኤርሊክ በቀጥታ ጠብ ጫሪነትን የሚያንጸባርቁ ጽሑፎችንም ይጽፋል፡፡ ለምሳሌ የሃጋይ አንዱ ጽሑፍ “The Grandchildren of Abraha” የሚል ርዕስ አለው፡፡ አብረሃ ነቢዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) በተወለዱበት ዘመን የመንን ሲገዛ የነበረው የአክሱም ንጉሥ እንደራሴ ነው፡፡ ታዲያ ሀጋይ በዚህ ጽሑፍ የአሁኖቹን የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ መሪዎች “የአብረሃ የልጅ ልጆች ናቸው” ይላቸውና “እነዚህ ጀግኖች የተስፋፊውን የአክራሪውን የእስልምና ጂሃዲስቶች ድባቅ መምታት ይችላሉ” የሚል እድምታ ያለው ትረካ ይተረትራል፡፡ አብረሃ የጥንቱ የአክሱም ንጉሣዊ ግዛት ተወላጅ እንደነበረ ማንም አይክድም፡፡ ይሁን እንጂ የዛሬዎቹን የኢትዮጵያ ገዥዎች የአብረሃ ዝርያዎች ማለትም ሆነ የጥንቷ አክሱም ሌጋሲ አስቀጣይ አድርጎ ማቅረብ ስህተት ነው፡፡ የጥንቷ አክሱም በማህበራዊ ስብጥሯ ህብረ-ብሄር እንጂ የአንድ ብሄር ሀገር አልነበረችም፡፡ ግዛቷ ደግሞ ከትግራይ ባሻገር ኤርትራን፣ ሰሜን ምስራቃዊ ሱዳንና አብዛኞቹን የሰሜን ኢትዮጵያ ክልሎች ይጠቅላል፡፡  አብረሃ ከነዚህ ሁሉ ግዛቶች በየትኛው እንደተወለደ በትክክል አይታወቅም፡፡ በሁለተኛ ደረጃ የዘመናችን የኢትዮጵያ መሪዎች የጥንቱ አብረሃ ሌጋሲ ወራሾች ናቸው የሚያስብል የታሪክና የአንትሮፖሎጂ ማስረጃ የለም፡፡
  
 የጽሑፉ አደገኛነት ግን ይህ አይደለም፡፡ የሃጋይ ምሁራዊ ሸፍጥ የሚያስከፋው ጥንት የተፈጸመን ታሪክ አሁን ካለው ጂኦ-ፖለቲካዊ ትርምስ ጋር እየቀላቀለ የጠብ ጫሪነት ስሜትን ለማንገሥ በመጣሩ ነው፡፡ የታሪክ ምሁር ዋነኛ ግብ የሰው ልጆች ትናንት የፈጸሟቸው ስህተቶችን እንዳይደግሙ ማስተማር እና ድሮ የነበራቸውን በጎ የአዕምሮና የማቴሪያል እሴቶችን ጠብቀው ወደ ቀጣዩ ትውልድ እንዲያስተላልፉ ማስቻል ነው፡፡ ሀጋይ ግን ታሪክን ሸርና ብጥብጥን ለማውረስ ሲል ብቻ የሚጠቀምበት ነው የሚመስለው፡፡
----
ከላይ የጠቀስኳቸው ሁለት ምሁራን (ሞርዴኻይ አቢር እና ሀጋይ ኤርሊክ) ይሁዲዎች ናቸው፡፡ ነገር ግን ሁለቱም የተለያየ ምሁራዊ ልቀትና ርትእ ያላቸው ሆነው ተገኝተዋል፡፡ ምሁራን “የአቢርን መጽሐፍ ማንበብ አለብህ” እያሉ ሲናገሩ የነበሩት “በአቢር መጽሐፍ ውስጥ እውቀት አለልህ” ማለታቸው እንደሆነ ገብቶኛል፡፡  ሀጋይ ኤርሊክ ግን በታሪክ ስም ጽዮናዊ ፖለቲካውን የሚያሰራጭ ሸፍጠኛ ነው እንጂ የምሁር “ኳሊቲ” የለውም፡፡

አንድ ነገር ግን አለ፡፡ ይሁዲ በሙሉ መጥፎ ነው የሚሉ ሰዎች አሉ፡፡ ስህተት ነው፡፡ በጣም ስህተት!! ይህ የአዶልፍ ሒትለርና የመሰሎቹ አስተሳሰብ ነው እንጂ የጤናማ ሰው አስተሳሰብ አይደለም፡፡ አይሁድ በሙሉ መጥፎ እንዳልሆነ ለመረዳት የሚሻ ሰው የፕሮፌሰር አቢርን መጽሐፍ ብቻ ማንበብ ይበቃዋል፡፡ የህዝብን አንድነት የሚያናጉትን እንደ ሀጋይ ኤርሊክ ዓይነቶቹን መሰሪ ጸሐፊዎች ግን ጠንቀቅ በሏቸው፡፡ 
-----
First written on August 13/2015
Re-written on January 19/2016


Friday, October 2, 2015

የኢሬሳ/ኢሬቻ በዓል ትውፊትና አከባበር


ፀሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ
-----
የኢሬቻን በዓል በማስመልከት አንድ ጽሑፍ እናበረክታለን ባልነው መሰረት ይህንን ኢትኖግራፊ ቀመስ ወግ ጀባ ልንላችሁ ነው፡፡ ታዲያ እኛ ባደግንበት አካባቢ በሚነገረው ትውፊት በዓሉ “ኢሬሳ” እየተባለ ስለሚጠራ በዚህ ጽሑፍ ውስጥም “ኢሬሳ” የሚለውን ስም መጠቀሙን መርጠናል፡፡ ወደ ነገራችን ከመግባታችን በፊት በዚህ ጽሑፍ የሚወሱት ጉዳዮች Carcar and the Ittu Oromo በተሰኘው የኢትኖግራፊ ጥናት ውስጥ በሰፊው የሚዳሰሱ በመሆናቸው ጥያቄ ያላችሁ ሰዎች የጥናቱን የመጨረሻ ውጤት እንድትጠባበቁ እጠይቃለሁ፡፡ ምክንያቱም በጽሑፉ ውስጥ ከቀረበው ትረካ በላይ ሄጄ ወደ ዝርዝር ጉዳዮች እንዳልገባ ጥናቱን የማከናውንበት ደንብ ስለሚያግደኝ ነው፡፡
----
ጽሑፋችንን የተሳሳቱ ምልከታዎችን በማስተካከል እንጀምራለን፡፡

የዋቄፈንና እምነት ተከታይ የሆኑት ኦሮሞዎች በሙሉ የኢሬሳን በዓል ያከብሩታል፡፡ ይሁንና በዚህ ዘመን በዓሉ በከፍተኛ ድምቀት የሚከበረው የቱለማ ኦሮሞ ይዞታ በሆነው የቢሾፍቱ ወረዳ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ታዲያ የበዓሉ ማክበሪያ በሆነው ስፍራ ቆሪጥን የመሳሰሉ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ስምና ዝና ያላቸው ጠንቋዮች የከተሙ በመሆናቸው ብዙ ሰዎች ኢሬቻን ጠንቋዮቹ የዛር መንፈሳቸውን በህዝቡ ላይ የሚያሰፍኑበት ዓመታዊ የንግሥ በዓል አድርገው ይመለከቱታል፡፡ አልተገናኝቶም!!

ጠንቋዮቹ በቅርብ ዘመን የበቀሉ ሀገር አጥፊ አራሙቻዎች ናቸው፡፡ ከበዓሉ ጋር አንድም ግንኙነት የላቸውም፡፡ ኖሮአቸውም አያውቅም፡፡ የኢሬቻ በዓል ግን ከጥንቱ የኦሮሞ ህዝብ የዋቄፈና እምነት የፈለቀ እና ለብዙ ክፍለ ዘመናት ሲተገበር የኖረ ነው፡፡ ጠንቋዮቹ በዚያ አካባቢ የሰፈሩት ከጣሊያን ወረራ ወዲህ ባለው ጊዜ ነው፡፡ እነዚህ ጠንቋዮች እዚያ የሰፈሩበት ምክንያት አለ፡፡ የገላን፤ የቢሾፍቱ እና የዱከም  ወረዳዎች በጥንታዊው የቱለማ ኦሮሞ ደንብ መሰረት የነገዱ ፖለቲካዊና መንፈሳዊ ማዕከላት ናቸው፡፡ እነዚህ መሬቶች በቱለማ ኦሮሞ ዘንድ “ቅዱስ” ተብለው ነው የሚታወቁት፡፡ “ቃሉ” የሚባለው የህዝቡ መንፈሳዊ መሪም የሚኖረው በዚህ አካባቢ ነው፡፡ የቱለማ ኦሮሞ ኢሬቻን የመሳሰሉ ታላላቅ በዓላት የሚያከብረውም በዚሁ ስፍራ ነው፡፡

በ19ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ ላይ የኦሮሞ ህዝብ በነዚህ መሬቶች የሚያካሄደውን በዓላትን የማክበርና “ዋቃ”ን የማምለክ ተግባራት እንዳያከናውን ታገደ (ዝርዝሩን ለማወቅ የጸሐፌ ትዕዛዝ ገብረ ሥላሤን “ታሪክ ዘመን ዘዳግማዊ ምኒልክ”፣ ወይንም የኤንሪኮ ቼሩሊን The Folk Literature of The Oromo ያንብቡ)፡፡ ይሁንና ልዩ ልዩ የኦሮሞ ጎሳዎች እየተደበቁም ቢሆን ወደ ስፍራው መሄዳቸውን አላቋረጡም፡፡ በጣሊያን ዘመን ደግሞ እንደ ጥንቱ ዘመን ሰብሰብ ብለው በዓሉን ማክበር ጀመሩ፡፡ ጣሊያን ሲወጣ እንደገና በጅምላ ወደስፍራው እየሄዱ በዓሉን ማክበሩ ቀረ፡፡ ነገር ግን ኦሮሞዎች ከጣሊያን በኋላም በተናጠልና በትንንሽ ቡድኖች እየሆኑ መንፈሳዊ በዓላቸውን በስፍራው ማክበራቸውን አላቋረጡም (እዚህ ላይ ጣሊያንን ማድነቃችን አይደለም፤ ታሪኩን መጻፋችን ነው እንጂ)፡፡

 እንግዲህ በዚያ ዘመን ነው ጠንቋዮቹ በአካባቢው መስፈር የጀመሩት፡፡ እነዚህ ጠንቋዮች ይህንን ስፍራ ምርጫቸው ያደረጉበት ዋነኛ ምክንያት አለ፡፡ ጠንቋዮቹ ህዝቡ መሬቱን እንደ ቅዱስ ምድር የሚመለከት መሆኑን ያውቃሉ፡፡ “ቃሉ” የሚባለው የጥንቱ የኦሮሞ ሀገር በቀል እምነት መሪ በስፍራው እየኖረ የህዝቡን መንፈሳዊ ተግባራት ይመራ እንደነበረም ያውቃሉ፡፡ የኦሮሞ ቃሉ በህዝቡ ከፍተኛ ክብር እንደሚሰጠው እና ንግግሩ በሁሉም ዘንድ ተቀባይነት እንዳለውም ይገነዘባሉ፡፡ “ቃሉ” አስፈላጊ ሆኖ በተገኘበት ጊዜ ከ“ዋቃ” የተሰጠውን ገደብ ሳይጥስ “ራጋ” የማከናወን ስልጣን እንዳለውም ይረዳሉ፡፡

እንግዲህ ጠንቋዮቹ የዘረፋ ስትራቴጂያቸውን ሲወጥኑ በጥንታዊው የኦሮሞ የዋቄፈና እምነት ተከታዮች ዘንድ እንደ ቅዱስ የሚወሰደው ያ ማዕከላዊ ስፍራ ብዙ ገቢ ሊዛቅበት እንደሚችል ታያቸው፡፡ በመሆኑም በዚያ ቅዱስ ስፍራ ከትመው ከጥንቱ የኦሮሞ ቃሉ ስልጣንና ትምህርት የተሰጣቸው እየመሰሉ ህዝቡን ማጭበርበርና ማወናበድ ጀመሩ፡፡ ለረጅም ዘመን ማንም ሃይ ባይ ስላልነበራቸው የውንብድና ስራቸውን በሰፊው ሄደውበታል፡፡ አሁን ግን ሁሉም እየነቃባቸው ነው፡፡

ታዲያ በሁሉም የሀገራችን አካባቢዎች የሚኖሩት ጠንቋዮች ተመሳሳይ ስትራቴጂ የሚጠቀሙ መሆናቸውን ልብ በሉ፡፡ ለምሳሌ በወሎ፣ በሀረርጌ፣ በባሌና በጂማ የሚኖሩት ጠንቋዮች እነ ሼኽ ሑሴን ባሌ፣ እነ ሼኽ አባዲር፣ እነ አው ሰዒድ፣ እነ ሼኽ አኒይ ወዘተ… የመሳሰሉት ቀደምት ሙስሊም ዑለማ በመንፈስ እየመሯቸው መጪውን ነገር እንደሚተነብዩና ድብቁን ሁሉ እንደሚፈትሹ ይናገራሉ፡፡ በሰሜን ሸዋ፣ ጎንደር፣ ጎጃም ወዘተ… አካባቢዎች ያሉ ጠንቋዮች ደግሞ ቅዱስ ገብርኤልና ሚካኤል ራዕይ እያስተላለፉላቸው መጻኢውን ነገር ለመተንበይ እንዳበቋቸው ያወራሉ፡፡ ነገር ግን ሁላቸውም አጭበርባሪዎች ናቸው፡፡ እነዚህን ጠንቋዮች ከክርስትናም ሆነ ከእስልምና ጋር የሚያገናኛቸው ነገር እንደሌለ ሁሉ ከዋቄፈንና እምነትም ጋር የሚያገናኛቸው ነገር የለም፡፡ ሶስቱም እምነቶች ጥንቆላን ያወግዛሉ፡፡ እናም የቢሾፍቱ ቆሪጦች እና ኢሬቻ በምንም መልኩ አይገናኙም፡፡ ስለዚህ ኢሬቻን ከጥንቆላም ሆነ ከባዕድ አምልኮ ጋር ማያያዝ ስህተት ነው፡፡

ከዚሁ ጋር ተያይዞ መወሳት ያለበት ጉዳይ ለጠንቋዮች መጠሪያ ሆኖ የሚያገለግለውን “ቃልቻ” የተሰኘውን ስም ይመለከታል፡፡ ይህ ስም በአንድ ጎኑ “ቃሉ” የሚለውን የኦሮሞ መንፈሳዊ አባት ያመለክታል፡፡ በሌላኛው ጎኑ ይህ መንፈሳዊ አባት የተወለደበትን ጎሳም ያመለክታል፡፡
የቃሉ ሹመት እንደ አባገዳ በምርጫ የሚከናወን ሳይሆን ከአባት ወደ ልጅ የሚተላለፍ ነው፡፡ ይህ መንፈሳዊ አባት አባል የሆነበት ጎሳም በዚሁ ስም “ቃሉ” እየተባለ ነው የሚጠራው፡፡ የጎሳው አባላት የሆኑ ሰዎች ሃላፊነት ህዝቡን በመንፈሳዊ ተግባራት ማገልገል ነው፡፡ የዚህ ጎሳ ተወላጆች በከፍተኛ ደረጃ ይከበራሉ፡፡ ቃላቸው በሁሉም ዘንድ ተሰሚ ነው፡፡ ይሁንና የፖለቲካ መሪ እና የጦር መሪ ለመሆን አይችሉም፡፡ የአባገዳ ምርጫ ሲከናወንም ለእጩነት አይቀርቡም፡፡ እንግዲህ “ቃሊቻ” የሚባሉት ከዚህ የተከበረ ጎሳ የተወለዱ ወንዶች ናቸው፡፡ ሴቶቹ ደግሞ “ቃሊቲ” በሚለው የማዕረግ ስም ይጠራሉ፡፡ የሁለቱም ትርጉም “የቃሉ ሰው” እንደማለት ነው፡፡ ጠንቋዮቹ “ቃሊቻ” ነን ማለት የጀመሩት ቃሉዎች በኦሮሞ ህዝብ ዘንድ ያላቸውን ክብር ስለሚያውቁ ነው፡፡ ነገር ግን “ቃሊቻ” እና ጠንቋይ የሰማይና የመሬትን ያህል የተራራቁ ናቸው፡፡
*******
እነሆ አሁን ወደ ኢሬሳ ገብተናል!!

በጥንቱ የኦሮሞ የዋቄፈንና እምነት መሰረት ብዙዎቹ በዓላት ወርሃዊ ናቸው፡፡ እነዚህ ወርሃዊ በዓላት የሚከበሩት በየአጥቢያው ባሉት መልካዎች፣ በኦዳ (ዋርካ) ዛፍ ስር እና “ገልመ ቃሉ” በሚባለው ቤተ እምነት ነው፡፡ ኢሬሳን የመሳሰሉት ታላላቅ በዓላት የሚከበሩት ግን በነገድ (ቆሞ) ደረጃ ሲሆን በዓላቱን የማክበሩ ስርዓቶች የሚፈጸሙትም በዞን ደረጃ ባሉ የበዓል ማክበሪያ ስፍራዎች ነው፡፡ እነዚህ የክብረ በዓል ስፍራዎች የሚገኙትም የእያንዳንዱ የኦሮሞ ነገድ የፖለቲካና የመንፈሳዊ ማዕከላት ባሉበት አቅራቢያ ነው፡፡ ምሳሌ ልስጣችሁ፡፡

ከአዲስ አበባ ወደ ሀረር ስትመጡ “አዴሌ” እና “ሀረማያ” የተሰኙትን ሐይቆች ታገኛላችሁ አይደል?… አዎን! የአዴሌን ሐይቅ አልፋችሁ ወደ ሀረማያ ከመድረሳችሁ በፊት ወደ ጋራሙለታ አውራጃ የሚገነጠለው የኮረኮንች መንገድ ይገጥማችኋል፡፡ መንገዳቸው ወደ ጋራ ሙለታ የሆነ ተጓዦች እዚያ ከመድረሳቸው በፊት የአውቶቡሱ ረዳት በዚያ ስፍራ እንዲያወርዳቸው ይነግሩታል፡፡ ታዲያ ስፍራውን ምን ብለው እንደሚጠሩት ታውቃላችሁ?….. Mudhii Irreessaa ነው የሚሉት፡፡ ቃል በቃል ሲተረጎም “የኢሬሳ ወገብ” እንደማለት ነው፡፡ አውዳዊ ፍቺው ግን “የኢሬሳ በዓል ማክበሪያ ስፍራ” እንደማለት ነው፡፡

በዚህ ስፍራ በአሁኑ ወቅት የኢሬሳ በዓል አይከበርም፡፡ በጥንት ዘመናት ግን የምስራቅ ሀረርጌው የአፍረን ቀሎ ኦሮሞ የኢሬሳን በዓል የሚያከብረው በዚህ አካባቢ ነው፡፡ በዓሉ ይከበርበት የነበረውን ትክክለኛ ስፍራ ለማወቅ ካሻችሁ በዋናው የአስፋልት መንገድ ላይ ለጥቂት ሜትሮች እንደተጓዛችሁ ከመንገዱ በስተቀኝ በኩል ፈልጉት፡፡ በዚያ ስፍራ ላይ ከትንሽዬ ኮረብታ ስር የተጠጋ ሰፊ መስክ ራቅ ብሎ ብሎ ይታያል፡፡ ይህ ረግረጋማ ስፍራ በጥንቱ ዘመን  አነስተኛ ሐይቅ እንደነበረበት ልብ በሉ፡፡ ሐይቁ ከጊዜ ብዛት ስለደረቀ ነው በረግረግ የተዋጠው መስክ እንዲህ አግጥጦ የሚታየው፡፡ እናም የአፍረን ቀሎ ኦሮሞ የዋቄፈንና እምነት ተከታይ በነበረበት የጥንት ዘመናት የኢሬሳን በዓል የሚያከብርበት ቅዱስ ስፍራ በዚህ የደረቀ ሐይቅ ዳርቻ የነበረው መሬት ነው፡፡

Mudhii Irreessa የሚባለው ስፍራ ከደረቀው ሐይቅ አቅራቢያ መሆኑና ይኸው ስፍራ አሁን ካሉት የሐረማያ እና የአዴሌ ሐይቆች አቅራቢያ መገኘቱ የአጋጣሚ ነገር እንዳይመስላችሁ፡፡ በነገድ ደረጃ የኢሬሳ በዓል የሚከበርባቸው ማዕከላት በሙሉ በሐይቅ ዳርቻ የሚገኙ ናቸው፡፡ ይህም ምክንያት አለው፡፡ አንደኛው ምክንያት የጥንቱ የኦሮሞ የዋቄፈንና እምነት “ፍጥረት የተገኘው ከውሃ ነው” የሚል አስተምህሮ ያለው በመሆኑ “ዋቃ” ፍጥረተ ዓለሙን በጀመረበት የውሃ ዳርቻ በዓሉንና የአምልኮ ተግባሩን መፈጸም ተገቢ ነው ከሚል ርዕዮት የመነጨ ነው፡፡ ይሁንና ሁሉም የውሃ አካል ለዚህ ክብር አይመጥንም፡፡ ኦሮሞ ከሰው ልጅ ነፍስ ቀጥሎ ለከብቶቹ ነፍስ በእጅጉ ይጨነቃል፡፡ በመሆኑም ኢሬሳን የመሳሰሉ ታላላቅ በዓላት በዳርቻው የሚከበርበት የውሃ አካል ከሰዎች በተጨማሪ ለከብቶች ህይወት አስፈላጊ መሆኑም ይጠናል፡፡ ይህም ማለት ውሃው በኦሮሞ ስነ-ቃል “ሃያ” (ቦጂ) እየተባለ የሚጠራው ጨዋማ ንጥረ ነገር ያለው ሊሆን ይገባል ለማለት ነው፡፡ በዚህ ማዕድን በአንደኛ ደረጃ የሚታወቁት ደግሞ “ሆራ” የሚባሉት በከፍተኛ ስፍራዎች ላይ ያሉ ሐይቆች ናቸው፡፡

ታዲያ የእነዚህ “ሆራ” ሐይቆች ልዩ ባህሪ ነጠላ ሆነው አለመገኘታቸው ነው፡፡ በተለያዩ ክልሎች ያሉት ሆራዎች በቡድን ተሰባጥረው  ነው የሚገኙት፡፡ በአንዳንድ ስፍራዎች እስከ ሶስት ያህል ሆራዎች አሉ፡፡ በአንዳንድ ስፍራዎች ደግሞ እስከ ስምንት የሚደርሱ ሆራዎች ይገኛሉ፡፡ ብዙዎቹ የኦሮሞ ነገዶች እነዚህን በማዕድናት ክምችት የበለጸጉ ሐይቆች ወጥ በሆነ ሁኔታ “ሆረ” (Hora) እያሉ ነው የሚጠሩት፡፡ የአፍረን ቀሎ ኦሮሞ ግን “ሀረ” ነው የሚለው፡፡ “ሀረ ማያ” የሚለው የሐይቁ ስያሜም የሚያመለክተው ይህንኑ ነው፡፡ እንግዲህ ኢሬቻ የሚከበረው በእንዲህ ዓይነት ሐይቆች አቅራቢያ ነው፡፡
*******
ከላይ ስጀምር “የኢሬሳ በዓል ማክበሪያ ስፍራ ለነገዱ የፖለቲካና የሃይማኖት ማዕከል የቀረበ ነው” ብዬ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ የ“ሀረ ማያ”ን ሐይቅ ያየ ሰው በአባባሌ መደናገሩ አይቀርም፡፡ ነገሩ ግን እውነት ነው፡፡ በዛሬው ዘመን “ሃረ ማያ” በትውፊት ውስጥ ያለው አስፈላጊነት እየተረሳ የመጣው የአፍረን ቀሎ ኦሮሞ የኢኮኖሚ ስርዓቱን ከከብት እርባታ ወደ ግብርና ማዞር በጀመረበት ዘመን እስልምናንም እየተቀበለ በመምጣቱና የፖለቲካ ማዕከሉም በዚሁ ሂደት ውስጥ በመረሳቱ ነው፡፡ ነገሩን ጠለቅ ብሎ ያየ ሰው ግን የጥንቱን የአፍረን ቀሎ የፖለቲካ ማዕከል ከሀረማያ ከተማ በቅርብ ርቀት ላይ ያገኘዋል፡፡ ይህም “ቡሉሎ” የሚባለው ስፍራ ነው (ስፍራው ለወተር ከተማ ይቀርባል)፡፡ በዚህ መሰረት የዛሬዎቹ የሀረማያ እና የቀርሳ ወረዳዎች የጥንቱ የአፍረን ቀሎ ኦሮሞ የፖለቲካና የመንፈሳዊ ማዕከላት ነበሩ ማለት ነው፡፡

ከአፍረን ቀሎ ኦሮሞ ምድር ወደ ምዕራብ ተጉዘን “ጨርጨር” በሚባለው የኢቱ ኦሮሞ መሬት ውስጥ ስንገባ ደግሞ ነገሩ በግልጽ ይታየናል፡፡ የኢቱ ኦሮሞ የኢሬሳን በዓል የሚያከብርበት ስፍራ በአሁኑ የምዕራብ ሀረርጌ ዞን የቁኒ ወረዳ፣ በደነባ ቀበሌ ውስጥ ይገኛል፡፡ ስፍራው እስከ አሁን ድረስ Mudhii Irressa እየተባለ ይጠራል፡፡ ይህ ስፍራ ከዝነኛው “ኦዳ ቡልቱም” በሁለት ኪሎሜትር ያህል ብቻ ነው የሚርቀው፡፡ “ኦዳ ቡልቱም” የኢቱ ኦሮሞ ጥንታዊ የፖለቲካና የእምነት ማዕከል ሲሆን በኢቱ ኦሮሞ ትውፊት መሰረት ስድስት “ሆራዎች” አሉት፡፡ እነርሱም “ሆረ ባዱ”፣ “ሆረ ቃሉ”፣ “ሆራ ቁኒ”፣ “ሆረ ባቴ”፣ “ሆረ ጎሄ” እና “ሆረ ዲማ” ይባላሉ፡፡

እነዚህ ሃይቆች በበጋ ወቅት አነስ ብለው ቢታዩም ሙሉ በሙሉ የጠፉበት ሁኔታ አልተከሰተም፡፡ ከነርሱ መካከል ትልቁ “ሆራ ዲማ” ሲሆን በተለምዶ “ሀሮ ጨርጨር” እየተባለም ይጠራል፡፡ “ሆረ ዲማ” የምስራቅ ኢትዮጵያ ትልቁ ሐይቅ ነው (የአስፋልቱ መንገድ ወደዚያ ስለማይደርስ የመሃል ሀገር ሰዎች በአብዛኛው ሃረማያን ነው የሚያውቁት፤ ይሁንና “ሆረ ዲማ” በስፋቱ የሀረማያን ሶስት እጥፍ ይሆናል)፡፡ “ሆራ ባዱ” ደግሞ ለኦዳ ቡልቱም በጣም የቀረበው ሐይቅ ነው፡፡ የኢቱ ኦሮሞ የኢሬሳን በዓል የሚያከብረው ግን “ሆረ ቃሉ” ከተሰኘው ሐይቅ አጠገብ ነው፡፡ ይህም ሃይቅ ከሆረ ባዱ በስተምስራቅ ይገኛል፡፡

ስድስቱ ሐይቆች ካሉበት ስፍራ ጀምሮ እስከ ገለምሶ ከተማ ድረስ ያለው መሬት በኢቱ ኦሮሞ አጠራር “ፎዱ” ይባላል፡፡ “ማዕከል” ማለት ነው፡፡ ይህ ማዕከላዊ ወረዳ ለሶስት ጉዳዮች ብቻ የተከለለ ነው፡፡ አንደኛ “አባ ቦኩ” የሚባለው ርእሰ መስተዳድርና “ቃሉ” የተባለው መንፈሳዊ መሪ መኖሪያ ነው፡፡ ሁለተኛ የኦዳ ቡልቱም የገዳ ስርዓት ማዕከላዊ ተቋማት፣ የህዝቡ መንፈሳዊ ተቋማት እና የዞን አቀፍ በዓላት ማክበሪያ ስፍራዎች የሚገኙበት ክልል ነው፡፡ ሶስተኛ ለህዝብ ጠቀሜታ ብቻ የሚውሉት ስድስቱ ሆራዎች የሚገኙበት ክልል ነው፡፡ በመሆኑም የኢቱ ኦሮሞ ተወላጆች በሙሉ በዓመት ወይንም በሁለት ዓመት አንዴ ከብቶቻቸውን ወደነዚህ ሐይቆች እያመጡ ውሃ ያጠጧቸዋል፡፡ የኢቱ ሽማግሌዎች እንደሚናገሩት ከብቶች የሆራን ውሃ ካልጠጡ እንዳሻቸው ሳር አይመገቡም፡፡ ስለዚህ ከብቶቹን ወደ ሆራ መውሰዱ እጅግ አስፈላጊ ተግባር ተደርጎ ይቆጠራል፡፡ ይህ ስርዓት Nadha Baasuu ይባላል፡፡

 የቱለማ ኦሮሞ የኢሬቻን በዓል የሚያከብርበትንም ስፍራ ካያችሁ ተመሳሳይ ነገር ታገኛላችሁ፡፡ በኦዳ ቡልቱም ዙሪያ ያሉት ስድስት ሐይቆች በቱለማ ምድርም አሉ፡፡ እነርሱም “ሆረ አርሰዲ”፣ “ሆረ ኪሎሌ”፣ “ሆረ ሀዶ”፤ “ሆረ ገንደብ”፣ “ሆራ ዋርጦ” እና “ሆረ ኤረር” ይባላሉ፡፡ የቱለማ ኦሮሞ ኢሬቻን የሚያከብረው “ሆረ አርሰዲ” በተሰኘው ሐይቅ ዳርቻ ነው፡፡

እነዚህ ስድስት ሐይቆች የቱለማ ኦሮሞ የፖለቲካ ማዕከል ከሆነው “ኦዳ ነቤ” በቅርብ ርቀት ላይ ነው የሚገኙት፡፡ ይህ ኦዳ ነቤ በዱከም ወረዳ ውስጥ ከሸገር በ37 ኪሎሜትር ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ በዚሁ የፖለቲካ ማዕከል ዙሪያም ህዝቡ ሃይማኖታዊ ጉዞ የሚያደርግባቸው Sadeettan Tulluu Waaqaa (ስምንቱ የአምላክ ተራራዎች) የሚባሉት የሸዋ ከፍተኛ ስፍራዎች ይገኛሉ፡፡ እነዚህም “ቱሉ ጩቃላ”፣ “ቱሉ ኤረር”፣ “ቱሉ ፉሪ”፣ “ቱሉ ገላን”፣ “ቱሉ ዋቶ ዳለቻ”፣ “ቱሉ ፎየታ”፣ “ቱሉ ወጨጫ” እና “ቱሉ ኤግዱ” የሚባሉት ናቸው፡፡ የህዝቡ አባ ገዳዎች መቀመጫ የሆኑት የአዋሽ መልካ በሎ እና የገላን ደንጎራ መስኮች የሚገኙትም በዚሁ ወረዳ ነው፡፡ እንግዲህ የቱለማ ኦሮሞ የኢሬቻን በዓል የሚያከብርበት “ሆራ አርሰዲ” ያለው እነዚህ የፖለቲካና የሃይማኖት ማዕከላት ባሉበት መሬት ላይ ነው፡፡

እላይ ከጠቀስናቸው ሶስት ነገዶች በተጨማሪ ሌሎች የኦሮሞ ነገዶችም በዓሉን ያከብሩታል፡፡ ይሁን እንጂ ከኦሮሞ ነገዶች መካከል ከፍተኛ የህዝብ ብዛት ያላቸው የአርሲ እና የመጫ ነገዶች በዓሉን በአንድ ስፍራ የሚያከብሩት አይመስለኝም (መረጃው ያላችሁ አካፍሉን)፡፡ታዲያ ከቱለማ በስተቀር ሁሉም ኦሮሞዎች በዓሉን “ኢሬሳ” እያሉ ነው የሚጠሩት፡፡ ቱለማ ግን “ኢሬቻ” ነው የሚለው፡፡ ይህ ልዩነት ግን ሌላ ሚስጢር የለውም፡፡ በሌሎች ዘዬዎች በምንናገርበት ጊዜ በ“ሳ” ድምጽ የምናሳርገውን ቃል በቱለማ ዘዬ “ቻ” እያሉ መናገር የተለመደ በመሆኑ ነው፡፡ ለምሳሌ “ለሜሳ”፣ “ከሌሳ”፣ “በሬሳ”፣ “ሙርቴሳ” የመሳሰሉት ቃላት በቱለማ ዘዬ “ለሜቻ”፣ “በሬቻ”፣ “ሙርቴቻ”፣ “ከሌቻ” በሚል ድምጸት ነው የሚነገሩት፡፡
*******
ለመሆኑ የኢሬሳ በዓል የሚከበረው ለምንድነው?……
 የኦሮሞ ሽማግሌዎች ይህንን ጥያቄ ሲመልሱን “የኢሬሳ በዓል የሚከበረው ለዋቃ ምስጋና ለማቅረብ ነው” ይላሉ፡፡ መነሻውንም ሲያስረዱ “ዋቃ ክረምቱን በሰላም ስላሳለፈልንና ከሰማይ ባዘነበው ውሃ መልካም ፍሬ ስለሰጠን ያለ ክፍያ በቸርነቱ ለሚንከባከበን አምላክ ምስጋና ማቅረብ የተገባ በመሆኑ ነው” ይሉናል፡፡ “ዋቃ” ፍጥረተ ዓለምን ያስገኘውና ሂደቱንም የሚያስተናብረው አንድ አምላክ ማለት ነው፡፡ ኦሮሞ ችግር ሲገጥመው አቤቱታውን የሚያቀርበው “ለዋቃ” ነው፡፡ በደስታ ጊዜም ተሰብስቦ “ዋቃ”ን ያመሰግናል፡፡ ኢሬሳ የዚህ ዓይነቱ የምስጋና ማቅረቢያ በዓል ነው፡፡

ኢሬሳ በክረምቱ የወንዞች ሙላት ምክንያት ተቆራርጠው የነበሩ ቤተ ዘመዶችና ልዩ ልዩ ጎሳዎች የሚገናኙበት በዓል ነው፡፡ በመሆኑም በበዓሉ የተገኙት ሁሉ ይቅር ይባባሉ፡፡ ገንዘባቸውን ለሌሎች ያበደሩ ሰዎችም በሌሎች ላይ ያላቸውን እዳ ይሰርዙላቸዋል፡፡ በዓሉ የሚከበርበት ቀን የዓመቱ መጀመሪያ ተደርጎ የሚቆጠር በመሆኑ ዓመቱ የደስታና የብልጽግና ይሆን ዘንድ የመልካም ምኞት መግለጫዎች ይጎርፋሉ፡፡ የህዝቡ መንፈሳዊ መሪ የሆነው “ቃሉ” ለህዝቡና ለሀገሩ “ኤባ” (ምርቃት) ያደርጋል፡፡ ታዲያ ማንኛውም ሰው ወደ በዓሉ ስፍራ ሲሄድ አለባበሱን ማሳመር ይጠበቅበታል፡፡ በእጁም የወይራ ቀንበጥ፣ እርጥብ ሳር አሊያም የአደይ አበባን ይይዛል፡፡ 

በነገራችን ላይ በጥንቱ ዘመን ከዚሁ የኢሬሳ በዓል ትይዩ ሌላ በዓል ይከበር እንደነበርም ልብ በሉ፡፡ ይህኛው በዓል የሚከበረው የክረምቱ ዝናብ ሊጀምር በሚያስገመግምበት የሰኔ ወር መግቢያ ላይ ነው፡፡ የበዓሉ ማክበሪያ ስፍራዎች ደግሞ ተራሮችና ኮረብታዎች ናቸው፡፡ ይህ በዓል “መጪው ክረምት መልካም የዝናብና የአዝመራ ወቅት እንዲሆንልን ለዋቃ ጸሎት ማድረስ” በሚል መንፈስ ነው የሚከበረው፡፡ በዓሉ በምዕራብ ሀረርጌው የኢቱ ኦሮሞ ዘንድ “ደራራ” እየተባለ ነው የሚጠራው፡፡ የቱለማ ኦሮሞ ደግሞ “ኢሬቻ ቱሉ” (የተራራ ላይ ኢሬሳ) ይለዋል፡፡ በዓሉ በሌሎች ኦሮሞዎች የሚጠራበትን ስም ግን አላውቅም፡፡ በደራራ ጊዜ የሚፈለገው ትልቁ ነገር “ጸሎት” (Kadhaa) ማብዛት ነው፡፡ መዝፈንና መጨፈር አይፈቀድም፡፡ በኢሬሳ ጊዜ የሚፈለገው ግን “ምስጋና” (Galata) ማብዛት እና ደስታን ማብሰር ነው፡፡ በዚህኛው በዓል ዘፈንና ጭፈራ ይፈቀዳል፡፡

በሁለቱም በዓላት የዋቃ ስም ይለመናል፡፡ ለዋቃ መስዋእት ይቀርባል፡፡ ለመስዋእት የሚታረደው ጥቁር በሬ አሊያም ጥቁር ፍየል ነው፡፡ ይህም በጣም መሰረታዊ ነገር መሆኑን ልብ በሉ፡፡ በበሬው ቆዳ ላይ ቀይ ወይንም ነጭ ነጥብ በጭራሽ መኖር የለበትም፡፡ የበሬው ገላ ከጭረትና ከእከክ የነጻ መሆን አለበት፡፡ በተጨማሪም በሬው በደንብ የበላና የደለበ ሊሆን ይገባል፡፡

 አንዳንድ ሰዎች “የበሬው ቆዳ ጥቁር መሆን አለበት” የሚለውን አስተርዮ እንደ ባዕድ አምልኮ እንደሚያዩት ይታወቃል፡፡ ነገሩ ግን እንዲያ አይደለም፡፡ የበሬው ቆዳ ጥቁር መሆኑ የሚፈለገው በዋቄፈንና እምነት መሰረት “ሰዎችን የፈጠረውና በሰዎች የሚመለከው አምላክ ጥቁር ነው” ተብሎ ስለሚታመን ነው፡፡ ይህም  “አምላክ በመልኩ ጥቁር ነው” ማለት ሳይሆን “ዋቃ በስራው እንጂ በአካሉም ሆነ በሚስጢሩ ለሰው ልጅ በጭራሽ አይታወቅም” ለማለት ነው፡፡ በመሆኑም የጥንቱ ኦሮሞዎች ዋቃን ሲለማመኑት እንዲህ ነበር የሚሉት፡፡

Yaa Waaqa (አንተ አምላክ ሆይ)
Jabaa hundaa olii (ከሁሉም በላይ ጥንካሬ ያለህ)
Tolchaa bobbaa fi galii (ወጥቶ መግባቱንም የሚያሳምረው)
Guraacha garaa garbaa (ጥቁሩ እና ሆደ ሰፊው)
Tokicha maqaa dhibbaa (በመቶ ስም የሚጠራው አንድዬ)

ይህ የጥቁር ነገር ከተነሳ ዘንዳ በኦሮሞ ባህል መሰረት ጥቁር በሬ ከፍተኛ ዋጋ ያለው መሆኑን ልብ በሉ፡፡ የቢሾፍቱና የገላን አካባቢ የኦሮሞ አርሶ አደር ሁለት ነጭ በሬዎች የሚገዙበትን ዋጋ ለአንዱ ጥቁር በሬ ብቻ ሊያወጣ ይችላል፡፡
*******
የኢሬሳ እና የደራራ በዓላት በጥንቱ ዘመን ከኦሮሞ ህዝብ በተጨማሪ የምስራቅ ኩሻዊያን (Eastern Cushitic People) በሚባሉት የቤጃ፣ የሳሆ እና የሶማሊ ህዝቦችም ይከበሩ እንደነበረ ተረጋግጧል፡፡ እነዚህ ህዝቦች ቀደም ብለው የእስልምናን እምነት   በመቀበላቸው በዓላቱን ማክበሩን ትተውታል፡፡ ይሁንና እንደነርሱ የኩሻዊ ቋንቋ ተናጋሪ የሆነው የአፋር ህዝብ እስከ ቅርብ ዘመን ድረስ የኢሬሳን በዓል ያከብር እንደነበረ ልዩ ልዩ ጥናቶች ያስረዳሉ፡፡

ሁለቱ በዓላት የሚከበሩባቸውን ወቅቶች፣ የየበዓላቱን ዓላማ እና በዓላቱ የሚከሩባቸውን አውዶች ያጠኑ ምሁራን በዓላቱ በጥንት ግብጻዊያንም ይከበሩ እንደነበረ አረጋግጠዋል፡፡ ይሁንና ተመራማሪዎቹ “የበዓላቱ ምንጭ ጥንታዊት ግብጽ ነች ወይንስ ከግብጽ በታች የሚኖሩት የኩሽ (ኑቢያ) ህዝቦች?” የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ተቸግረዋል፡፡ ጥያቄውን አስቸጋሪ ያደረገው የግብጻዊያኑ እምነት ብዝሃ አማልክት (Polytheism) የተቀላቀለበት መሆኑ ነው፡፡ ኩሻዊያኑ ግን “ዋቃ”፣ “ዋቅ፣ “ዋቆ” እያሉ በተቀራራቢ ቃላት ከሚጠሩት አንድ አምላክ በስተቀር ሌሎች አማልክት የሏቸውም፡፡ በዚህ ረገድ የሚደረገው ጥናት ሲጠናቀቅ ውጤቱ የሚታወቅ ይሆናል፡፡

ይህንን ጽሑፍ ከማጠናቀቄ በፊት አንድ ነገር ልናገር፡፡ ይህም “ኢሬቻ ባህል ነው” እየተባለ የሚነገረውን ይመለከታል፡፡ ሁሉም የምርምር ውጤቶች እንደሚያሳዩት ኢሬሳ በመሰረቱም ሆነ በይዘቱ ሃይማኖታዊ በዓል ነው፡፡  አከባበሩም የዋቄፈንና እምነትን ደንብ የተከተለ ነው፡፡ ስለዚህ ሚዲያዎች በዓሉን ሲያስተዋውቁ “ኢሬቻ ሁሉን አቀፍ ባህል ነው” ማለታቸውን መተው አለባቸው፡፡ ምክንያቱም ከራሱ እምነት አንጻር በዓሉን ማክበሩ የማይሆንለት በርካታ ኦሮሞ ስላለ ነው፡፡ ወደ ክብረ በዓሉ ስፍራ መሄድ የሚፈልግ ማንኛውም ሰው መሄድ ይችላል፡፡ የማይፈልገውም እንደዚያው!
አንዳንዶች እንደሚያደርጉት “ኢሬቻ የኦሮሞነት መለያ ነው” ማለቱ ግን አግባብ አይደለም፡፡ ለምሳሌ እኔ ስለበዓሉ እዚህ የጻፍኩት ሙስሊም ነኝ፡፡ ጽሑፉን የጻፍኩትም በምርምር ሂደት ያገኘሁትን መረጃ በማቀናበር ነው እንጂ በዓሉን ስለማከብር አይደለም፡፡ ለሁሉም ግን ኢሬሳን ለሚያከብሩት የዋቄፈንና እምነት ተከታይ የኦሮሞ ወገኖቻችንን መልካም በዓል እንዲሆንላቸው እመኛለሁ!!
-----
አፈንዲ ሙተቂ
መስከረም 22/2008
ሀረር -ምስራቅ ኢትዮጵያ
------
ምንጮች
1.      Afendi Muteki: The Ittu Oromo of Carcar, Origin, Institutions and Dispersions (A Project on Progress)
2.      Gada Melba: Oromia, An Introduction to History of the Oromo People: Khartum 1988
3.      Enrico Cerulli: A Falk Literature of the Oromo People: Harvard: 1922
4.      Johann L. Krapf, :Travels, Researches and Missionary Labors during an Eighteen Year's Residence in Eastern Africa, London, 1860
5.      Mohammed Hasasan: The City of Harar and the Islamization of the Oromo in Hararge, Atlanta, 1999
6.      የኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ፣በገዳ ስርዓት የቱለማ ኦሮሞ ፖለቲካ ፊንፊኔ፣ 2000

7.      ልዩ ልዩ ቃለ ምልልሶች

Friday, September 25, 2015

የቢቢሲ አፋን ኦሮሞ ዘመቻ ለምን?


(አፈንዲ ሙተቂ)
----




ዘመቻው የተጀመረው የዛሬ ሁለት ሳምንት ገደማ ይመስለኛል፡፡ ለመጀመሩ ምክንያት የሆነው ደግሞ “ቢቢሲ ትኩረቱን በኢትዮጵያ እና በኤርትራ ላይ ያደረገ የስርጭት ፕሮግራም ይጀምራል” የሚል ዜና መነገሩ ነው፡፡ ታዲያ ይህንን ዜና ተከትሎ “የስርጭት ቋንቋዎቹ አማርኛ እና ትግርኛ ናቸው” የሚል ወሬ ተደመጠ፡፡ ነገሩ እስከ አሁን ገፍቶ ባይመጣም በትክክል ተብሎ ሊሆን ይችላል፡፡ ምክንያቱም የውጪ ሰዎች እንዲህ ዓይነቱን ነገር ለመወሰን ሲነሱ በቅድሚያ የሚያዩት በየሀገራቱ ውስጥ በኦፊሴል የሚሰራባቸውን ቋንቋዎች ነው፡፡ ትግርኛ በኤርትራ፣ አማርኛም በኢትዮጵያ የኦፊሴል ቋንቋ የመባል ደረጃ ያላቸው በመሆናቸው ቢቢሲ በዚሁ ምክንያት ፕሮግራሙን በሁለቱ ቋንቋዎች ለማስተላለፍ ወስኖ ሊሆን ይችላል፡፡ በየሀገራቱ ውስጥ ያሉት ቋንቋዎች ተናጋሪ ብዛት ሲታይ ግን አፋን ኦሮሞ ከሁሉም ይቀድማል፡፡

እንደሚታወቀው በሬድዮ የሚተላለፍ ፕሮግራም የሚሻው አድማጭ እንጂ አንባቢ አይደለም ፡፡ ስለዚህ በኤርትራና በኢትዮጵያ ላይ የሚያተኩረው አዲሱ የቢቢሲ የስርጭት ፕሮግራም አድማጮችን ታሳቢ ያደረገ መሆን ይገባል፡፡ እናም ይህንን ያዩ ተመልካቾች “ቢቢሲ የቪኦኤን ሞዴል መከተል ይገባል፤ አፋን ኦሮሞም ከሁለቱ ቋንቋዎች ጋር መደመር አለበት” በማለት በኢንተርኔት የድጋፍ ፊርማ ማሰባሰብ ጀመሩ፡፡ እኛም ዘመቻው ተገቢ ሆኖ ስላገኘነው ፊርማችንን ሰጠነው፡፡ ሌሎችም እንዲፈርሙ መቀስቀሱንም ተያያዝነው፡፡

በእስካሁኑ ሂደት የፈረመው ሰው ብዛት ወደ ሳላሣ ሺህ እየተጠጋ ነው፡፡ በኢንተርኔት ላይ ሆነን እንደታዘብነው ሂደቱ በጥሩ ሁኔታ እየሄደ ነው፡፡ ሁሉም ወገኖች ዘመቻውን በበጎ መልኩ እያዩት ነው፡፡ እነ አትሌት ደራርቱ ቱሉ እና ዓሊ ቢራን የመሳሰሉ ታላላቅ ሰዎችም የድጋፍ ፊርማቸውን ሰጥተዋል፡፡ ሌሎችም ድጋፍ እንዲሰጡም እየቀሰቀሱ ነው፡፡ ይህ በጣም ጥሩ ነው፡፡ በተለይም የኢንተርኔቱ ዓለም ከሚታወቅበት “ጽንፋዊ” (polarized) አካሄድ ወጥተን ሁላችንም ፊርማችንን ማኖራችን በእጅጉ የሚያስደስት ነገር ነው፡፡
---
የድጋፍ ፊርማችንን ያኖርነው በሙሉ በጎን የማሰብ ዓላማ እንጂ ሌላ ተቀጥላ መነሻ የለንም፡፡ ታዲያ እነዚህ ምክንያቶች በደንብ የተብራሩ ስላልመሰለኝ ይህንን ጽሑፍ አሰናድቼአለሁ፡፡

እንደሚታወቀው “አፋን ኦሮሞ” (ኦሮምኛ) በአፍሪቃ ምድር እጅግ ብዙ ተናጋሪዎች ካሉት ቋንቋዎች አንዱ ነው፡፡ 40 ሚሊዮን የሚሆን ህዝብ ቋንቋውን በአፍ መፍቻነት ይናገረዋል፡፡ ከስድስት ሚሊዮን የማያንሱ ህዝቦችም ኦሮምኛን በሁለተኛ ደረጃ ይናገራሉ፡፡ ይሁንና ኦሮምኛን ከሚናገረው ህዝብ መካከል ከ3/4 የሚልቀውና በገጠር የሚኖረው ህዝብ ከኦሮምኛ ውጪ ሌላ ቋንቋን አይናገርም፤ አይሰማም (ነገሩን በተነጻጻሪነት ለማወቅ ካሻችሁ የኦሮሚያ ክልል የህዝብና ቤቶች ቆጠራ ውጤትን ይመልከቱ)፡፡ ስለዚህ የቢቢሲ ስርጭት ኦሮምኛን ከዘነጋ ይህ ህዝብ ቢቢሲ የፕሮግራሙ ተጠቃሚ ላይሆን ነው ማለት ነው፡፡

ታዲያ የሚገርመው ደግሞ በሬድዮ የሚሰማውን ፕሮግራም ከማንም በላይ የሚከታተለው የገጠሩ ህዝብ ነው፡፡ የከተማው ህዝብ በዝንባሌው ለቴሊቪዥን፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህም ለኤፍ ኤም ሬድዮ ነው የሚያደላው፡፡  ቢቢሲ በሬድዮ ፕሮግራሙን ሲጀምር ተጨማሪ አማራጭ የሚፈጠርለት በአብዛኛው ለገጠሬው ህዝብ ነው፡፡ ነገር ግን ኦሮምኛ ከአዲሱ ፕሮግራም ውስጥ ከተዘነጋ የገጠሩ የኦሮሞ ህዝብ ሌሎች ቋንቋዎችን ባለመቻሉ እድሉ ሊያመልጠው ነው፡፡ እንግዲህ ቢቢሲ አፋን ኦሮሞን በስርጭት ሽፋኑ ውስጥ እንዲያካትት በድጋፍ ፊርማ መጠየቁ የተፈለገበት አንደኛው ምክንያት ይህ ነው፡፡

ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ ለህዝቡ አማራጭ የመፍጠር ጉዳይ ነው፡፡ ይህም ከላይ የተገለጹትን ብቻ ሳይሆን ሁሉንም የኦሮምኛ ተናጋሪዎች የሚመለከት ነው፡፡ እንደሚታወቀው በሶስተኛው ዓለም ሀገር በአጭር ሞገድ የሚተላለፉ ሬድዮዎች በመንግሥታት የተያዙ በመሆናቸው ህዝቦች መረጃን ከነጻ ምንጭ የማግኘቱ ጉዳይ ይቸግራቸዋል፡፡ በግል፤ በፖለቲካ ፓርቲ እና በኮሚኒቲ እየተቋቋሙ ወደ አፍሪቃ ምድር ስርጭታቸውን የሚያስተላልፉ ሚዲያዎችም መንግሥታቱን ለማጋለጥ በሚል ነገሮችን ከልክ በላይ እየለጠጡና እያጋነኑ ለአድማጩ ስለሚተርኩ ግራ መጋባትንና መደናገርን ይፈጥራሉ፡፡ ቢቢሲ፣ ቪኦኤ፣ ዶቼ ቬሌ ወዘተ.. የመሳሰሉት ግን ከሁሉም የተሻሉ ነጻ ሚዲያዎች በመሆናቸው በነርሱ የሚተላለፉት ዘገባዎች ለእውነታ የቀረቡ መሆናቸው ይታመናል፡፡ እናም ቢቢሲ በአፋን ኦሮሞ ፕሮግራም ጀመረ ማለት ኦሮምኛን የሚሰማውና የሚናገረው ህዝብ ነጻ መረጃ የሚያገኝበት እድል ጨመረ ማለት ነው፡፡

ሶስተኛው ምክንያት ደግሞ የቢቢሲ በኦሮምኛ ፕሮግራም መጀመር ለአፋን ኦሮሞ እድገት ወሳኝ ሚና የሚጫወት መሆኑ ነው፡፡ ቢቢሲ ሁሉንም አቀፍ እና በቢሊዮን የሚቆጠሩ አድማጮች ያሉት ተቋም ነው፡፡ ፕሮግራሙ በተመራጭነቱ ቀዳሚ እንዲሆን ያስቻለው በሚያስተላልፈው ጭብጥና ይዘት ብቻ ሳይሆን ቀዳሚነቱን ለማስቀጠል በሚያከናውናቸው ተያያዥ መርሐ ግብሮች ጭምር ነው፡፡ ከነዚህም አንዱ ስርጭቱን የሚያስተላልፍባቸው ቋንቋዎችን ለማዘመን፣ ለማሳደግ እና ለማስተዋወቅ የሚያደርጋቸው ጥረቶች ናቸው፡፡ ተቋሙ ፕሮግራሙን ሲያስተላልፍ የዘፈቀደ የቋንቋ አጠቃቀምን አይከተልም፡፡ ቢቢሲ እያንዳንዱን ቋንቋ በማጥናት የቋንቋው አድማጮች ሁሉ ሊረዱት የሚችሉትን አቀራረብ ይወጥንና በዚያ መሰረት ስርጭቱን ያስተላልፋል፡፡ ራሱ የሚገለገልበት BBC-Standard የተባለ የቋንቋ አጠቃቀም ዘይቤም አለው፡፡

 በሌላ በኩል ቢቢሲ ስርጭቱን በሚያስተላልፍባቸው ቋንቋዎች ዙሪያ በሚደረጉት ምርምሮችም ተሳትፎ ያደርጋል፡፡ ቋንቋውንም ለማስተማር ልዩ ልዩ ጥረቶችን ያደርጋል (ለምሳሌ የቢቢሲ የዐረብኛው ፕሮግራም Learn BBC Arabic የተባለ ፕሮግራም አለው)፡፡ በቋንቋው የሚሰለጥኑ ተማሪዎችንም ይደግፋል፡፡ በቋንቋው የሚጻፉ የስነ-ጽሑፍ ውጤቶችን ያበረታታል፡፡ በሬድዮ ጣቢያውም ድርሰቶቹን ያስተዋውቃል፡፡ እነዚህ ተግባራት ለኦሮምኛ ቋንቋ እድገት እጅግ በጣም ይጠቅማሉ፡፡

እንግዲህ “ቢቢሲ አፋን ኦሮሞ” የተሰኘውን ዘመቻ ለመደገፍና ሌሎችም ድጋፋቸውን እንዲሰጡት ለመቀስቀስ የወሰንኩት እነዚህን ሁሉ መነሻዎች ካጤንኩ በኋላ ነው፡፡ በመሆኑም ለቋንቋው እድገት የሚቆረቆር እና በተለይም በገጠሩ የሚኖረው ህዝባችን አማራጭ ሚዲያ እንዲፈጠርለት የሚሻ ሰው በሙሉ ሊሳተፍበት የሚገባ ታሪካዊ ዘመቻ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ከዚህ ቀደም “ኦሮምኛን መማር እፈልጋለሁ” ፣ “ኦሮምኛ ከሌሎች ቋንቋዎች ጋር ያለው ተዛምዶ ለማጥናት ወስኛለሁ”፣ “የዓሊ ቢራን ዘፈን ግጥሞች ትርጉም ማወቅና በርሱ ዙሪያ መጻፍ እሻለሁ” ወዘተ… ስትሉኝ ለነበራችሁት ወዳጆቼ ደግሞ ዘመቻው የናንተንም ሆነ ተመሳሳይ ፍላጎትና ዝንባሌ ያላቸው ሌሎች ሰዎች ምኞቸውን  እውነት ሊያደርጉ የሚችሉበትን ውጤት ለማምጣት የሚረዳ በመሆኑ ተሳትፎአችሁ በእጅጉ ይጠበቃል፡፡
---
ይህ ዘመቻ ማንንም የመጉዳት ዓላማ የለውም፡፡ ዘመቻውን የጀመሩት ሰዎችም ሆኑ በሂደት የተቀላቀሉት ሁሉ ይህንን ጉዳይ በይፋ አስታውቀዋል፡፡ እያሳወቁም ነው፡፡ እኔም ደግሞ አስታውቃለሁ፡፡ ለምሳሌ ቢቢሲ የአማርኛውንም ሆነ የትግርኛውን ፕሮግራም እንዲያስቀር በጭራሽ አልተጠየቀም፡፡ ሊጠየቅም አይችልም፡፡ እንዲህ ብሎ መጠየቁ ከመጥፎ ምሳሌነቱ ሌላ ጥያቄው ተቀባይነት እንዳይኖረው ማድረግ ነው፡፡ ጥያቄው የቀረበው ቢቢሲ የቪኦኤን አርአያ በመከተል ስርጭቱን በሶስቱ ቋንቋዎች እንዲጀምር ነው (ስርጭቱን የሚያስተላልፍበትን የጊዜ መጠን የመወሰኑ ስልጣን የጣቢያው ነው፤ ያንን እኛ አንወስንለትም)፡፡ በመሆኑም ይህ በግልጽ ሊታወቅ ይገባል፡፡
----
ስለዚህ ወዳጆቻችን ሆይ!

ይህ የዘመቻ የተቀደሰ ሃሳብ ያለው ነው፡፡ የድጋፍ ፊርማችሁን በማኖር የዘመቻው ደጋፊ እንድትሆኑ በአክብሮት ትጠየቃላችሁ፡፡ ለዚህ ደግሞ መሰዋት አያስፈልጋችሁም፡፡ ሶስት ደቂቃ ብቻ ወስዳችሁ ለዚህ የተዘጋጀውን petition መፈረምንና ወደሚፈለግበት ቦታ send ማድረግን ብቻ ነው የሚጠይቀው፡፡ እናም ቀጥሎ የተመለከተውን ሊንክ ከፍታችሁ ፔቲሽኑን ፈርሙልን!! ዳይ

https://www.gopetition.com/petitions/bbc-consider-afan-oromo-for-new-broadcasts-to-ethiopiaeritrea-as-a-matter-of-priority.html#fbbox
----
ማስታወሻ
ፔቲሽኑን መፈረም ማለት ሊንኩን ከፍቶ ፎርሙን መሙላት ነው::  ስለዚህ ሊንኩን ከፍታችሁ ፔቲሽኑን ፈርሙልን፡፡

ፔቲሽኑን ለመፈረም የግዴታ የኤ-ሜይል አድራሻችሁን ማስገባት አለባችሁ፡፡ ከዚያም የቀረቡትን ጥያቄዎች በመከተል ፎርሙን መሙላት ይገባችኋል፡፡ መጨረሻ ላይ የተሞላውን ፎርም send አድርጋችሁ ስታበቁ ፊርማውን ስለመስጠታችሁ ማረጋገጫው በኢ-ሜይል ይላክላችኋል፡፡

ይህንን አጭር ጽሑፍ “ሼር” በማድረግ ብትተባበሩን ደግሞ የበለጠ እንፋቀራለን፡፡

Wednesday, September 23, 2015

“ዐረፋ” እና “ዒድ አል-አድሐ”

ፀሐፊ ፡ አፈንዲ ሙተቂ
---
በ1982 ነው፡፡ ባልሳሳት ዕለቱ ሰኔ 26 ይመስለኛል፡፡ የኢድ አል አድሐን በዓል ለማክበር በገለምሶው የሼኽ ዑመር ዓሊይ ሐድራ ተሰብስበናል፡፡ የዕለቱ የክብር እንግዳ የሐብሮ አውራጃ ኢሠፓ ኮሚቴ አንደኛ ጸሐፊ የነበሩት ጓድ ዓለሙ መንገሻ ነበሩ፡፡ የመድረክ መሪው ጓድ ዓለሙን ንግግር እንዲያደርጉ ጋበዛቸው፡፡ እሳቸውም ንግግራቸውን እንዲህ በማለት ጀመሩ፡፡

“የአረፋ በዓል ታላቅ በዓል ነው፡፡ የእስልምና እምነት እንደሚያስተምረው ዐረፋ የሚለው ቃል በዐረብኛ “አወቀ” እንደማለት ነው፡፡ ይህም ታሪክ አለው፡፡ አዳምና ሔዋን ወይንም አደምና ሀዋ ከጀንነት ወደ ምድር ከወረዱ በኋላ ለብዙ ዘመናት ተጠፋፍተው ነበር፡፡ ለረጅም ጊዜ ሲፈላለጉ ከቆዩ በኋላ በዚህ ዕለት በሳዑዲ ዐረቢያ ባለው የአረፋ ተራራ ላይ ተገናኙ፡፡ እዚያም “ዐረፍቱከ… ዐረፍቱኪ” ተባባሉ፡፡ “አወቅኩህ! አወቅኩሽ” ማለታቸው ነው፡፡ ይህንን ታሪክ ለመዘከር ሲባል ነው የዐረፋን በዓል ማክበር የተጀመረው”

ጓድ ዓለሙ የገለጹት ታሪክ የሚመለከተው የዙልሒጃን ወር ዘጠነኛ ቀን ነው እንጂ አስረኛውን ቀን አይደለም፡፡ ነገር ግን ይህንን ታሪክ ከሙስሊም ዓሊሞች ሳልሰማው ከእሳቸው አንደበት መስማቴ በጣም ደንቆኛል፡፡ ለዚያውም የሳቸው ፓርቲ በይፋ “ኤቲይዝምን” የሚሰብክ ሆኖ እያለ ነው እሳቸው ታሪኩን ያወጉን፡፡

እውነት ነው፡፡ ሐጅ በሚባለው አምስተኛው የእስልምና ማዕዘን (አርካን) ውስጥ ከሚፈጸሙት መንፈሳዊ ስርዓቶች መካከል በዙልሒጃ ወር ዘጠነኛ ቀን የሚከናወነው “አል-ዉቁፍ ቢዐረፋት” (በዐረፋ ቆሞ ጸሎት ማድረግ) ቀዳሚው መሰረቱ ከነቢዩ አደም ጋር የተገናኘው ታሪኩ ነው፡፡ ከመላው ዓለም የተሰባሰቡ ሐጃጆች ብሄር፣ ጾታ፣ ቀለም፣ አህጉር፣ ሀገር፣ ክፍለ ሀገር፣ መደብ፣ ስልጣን፣ የስራ መደብ፣ ወዘቱ ሳይገድባቸው በአንድ ቦታ ቆመው ሁላቸውም የአዳም ልጆች መሆናቸውን ያስመሰክራሉ፡፡

ታዲያ በዚሁ ቀን ሁለት ትልቅ ድርጊቶች ተከናውነዋል፡፡ ከነዚህም መካከል አንዱ ነቢዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) በታሪክ ገጾች The Masterpiece Sermon of Mohammed እየተባለ የሚጠራውን ታላቅ ዲስኩራቸውን ያሰሙበት እለት መሆኑ ነው፡፡ ነቢዩ ንግግራቸውን የጀመሩት “ሰዎች ሆይ! ከዚህ በኋላ በናንተ መካከል ላልገኝ እችላለሁ፤ ስለዚህ ልብ ብላችሁ አድምጡኝ” በሚል ዐረፍተ ነገር ነው፡፡ በርግጥም ነቢዩ ከዚህ የመሰናበቻ ንግግራቸው በኋላ በህይወት ብዙም አልቆዩም፡፡ ቢሆንም ከነቢዩ ንግግሮች መካከል በደንብ የተመዘገበው ይህ ንግግራቸው ነው፡፡ በሐዲስ ምሁራን ዘንድ የቃላትና የሐረጋት ልዩነት ሳይደረግበትና በእውነተኛነቱ ላይ ጥርጣሬ ሳይጣልበት (“ሰሒሕ” እና “ደዒፍ” ሳይባል) ተቀባይነትን ያገኘው ይህ የሐጀቱል ወዳዕ ንግግራቸው ነው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ንግግሩ በመቶ ሺህ ህዝብ የተሰማ መሆኑ ነው፡፡
   
ይህ ቀን የሚታወስበት ሁለተኛው ታላቅ ክስተት የቅዱስ ቁርአን የመጨረሻው አያህ (አንቀጽ) የወረደበት ዕለት መሆኑ ነው፡፡ አዎን!! “ኢቅራእ” በሚለው መለኮታዊ ቃል የጀመረው መጽሐፍ በዚህ ዕለት በሱረቱል ማኢዳ ውስጥ በሚገኘው ሶስተኛው አንቀጽ ተጠናቅቋል፡፡ በዚሁ አንቀጽ ውስጥ እስላማዊውን ርእዮት ለዓለም የማዳረሱ ተልዕኮ በከፍተኛ ስኬት መጠናቀቁን የሚገልጸው ዐረፍተ ነገር ይገኛል፡፡ እንዲህም ይላል፡፡
“ዛሬ ለናንተ ሃይማኖታችሁን ሞላሁላችሁ፤ ጸጋዬንም በናንተ ላይ ፈጸምኩ፤ እስልምናንም በሃይማኖትነት ወደድኩላችሁ”
(ሱረቱል ማኢዳ፤ 3)
---
ነቢዩ ሙሐመድ እንዲህ ብለዋል
“በዐረፋ ቀን ለጾመ ሰው አላህ ያለፈውን ዓመትና የቀጣዩን ዓመት ሐጢአቱን ይቅር ይለዋል”

በኛ ሀገር በተለምዶ ዐረፋ የሚባለው የኢድ አል አድሓን በዓል የምናከብርበት አስረኛው እለት ነው፡፡ በሸሪዓው እይታ ግን ዐረፋ የሚባለው የዙልሒጃ ወር ዘጠነኛው ቀን ነው፡፡
--
የዒድ አል-አድሓ ታሪካዊ ዳራ ደግሞ ነቢዩ ኢብራሂም ልጃቸውን ለአላህ ለመሰዋት ያደረጉት ቁርጠኝነት የተመላበት ውሳኔ እና ለመስዋዕትነት የቀረበው ልጅ ያሳየው የተለየ ጽናት ነው፡፡ ነቢዩ ኢብራሂም (ዐ.ሰ) የበኩር ልጃቸው የሆነውን ዒስማኢልን (ዐ.ሰ.) ያገኙት በእርጅና ዘመናቸው ነው፡፡ ታላቅ ሚስታቸው ሳራ ለፍሬ ባለመብቃቷ “ያ አላህ ያለ ዘር አታስቀረኝ፤ እኔን የሚተካ ሷሊህ የሆነ ልጅ ስጠኝ” በማለት ዱዓ አደረጉ፡፡ በዚሁ መሰረት በሳራ ፈቃደኝነት ሐጀራ የምትባለውን የቤት ሰራተኛቸውን አገቡ፡፡ ሐጀራም ዒስማኢል የተባለ ልጃቸውን ወለደችላቸው፡፡ ይህ ልጅ በአላህ ፈቃድ በመካ ከተማ እንዲያድግ የተወሰነ ስለነበረ ኢብራሂም ሐጀራን እና ዒስማኢልን ወደ ዐረቢያ ከተማ ወሰዷቸው፡፡

ዒስማኢል ካደገ በኋላ ደግሞ አላህ “ልጅህን እንድትሰዋ ታዘሃል” የሚል ትዕይንት በህልማቸው አሳያቸው፡፡ የነቢያት ህልም ደግሞ ከራዕይ የሚቆጠር ነው፡፡ ስለዚህ ኢብራሂም በህልማቸው ያዩትን በዝምታ አላለፉትም፡፡ በወቅቱ የሆነውን ቅዱስ ቁርኣን እንዲህ ይተርካል፡፡

“ከርሱ ጋር ለስራ በደረሰ ጊዜም “ልጄ ሆይ! እኔ በህልሜ የማርድህ ሆኜ አይቻለሁ፤ (እስቲ አንተም ነገሩን) ተመልከት፡፡ “ምን ይታይሃል” አለው፡፡ (ልጁም) አባቴ ሆይ! የታዘዝከውን ፈጽም፤ አላህ ቢሻ ከታጋሾቹ ሆኜ ታገኘኛለህ አለ”
(ሱረቱ -ሷፍፋት፤ 102)

አባትና ልጅ በዚህ መንገድ ከአላህ የተላለፈውን ትዕዛዝ ሊፈጽሙ ተነሱ፤ ነቢዩ ኢብራሂም ልጃቸውን እንዲሰው የታዘዙት ከዐረፋት መሬት ብዙም ባልራቀ ቦታ ላይ ስለነበረ ወደዚያው ጉዞ ጀመሩ፡፡ በመንገዳቸው ግን ኢብሊስ በሰው ተመስሎ በጣም ተፈታተናቸው፤ ሶስት ጊዜ ያህል እየወጣ “ከስንት ዓመት በኋላ ያገኘኸውን አንድዬ ልጅህን ስትሰዋ ምንም አይጸጽትም?… እንዴት ጅል ትሆናለህ” እያለ ሞገታቸው፡፡ ከአላህ ትዕዛዝ ፍንክች የማይሉት ኢብራሂም ግን ድንጋይ ከመሬት በማንሳት “አዑዙቢላሂ ሚነ-ሸይጣኒ ረጂም” እያሉ ኢብሊስን ወገሩት፡፡

ኢብራሂም ዒስማኢልን ሊያርዱት አጋደሙት፡፡ ልጁም ምንም ሳያንገራግር ከመሬቱ ላይ ተኛ፡፡ ኢብራሂም ልጁን ሊያርዱት ሲሞክሩ ግን ቢላዋው አላርድ አላቸው፡፡ ኢብራሂም እንደገና ቢላዋውን ገዘገዙት፡፡ ነገር ግን ቢላዋው ፈጽሞ ዶለዶመ፡፡ ልጁ የሆነው ነገር አልገባውም፡፡ አባቱ ቶሎ ስላላረደው ተገረመና “አባዬ! ፣ ምናልባት የአባትነት ፍቅር ይዞህ ይሆናል በቶሎ ያላረድከኝ፤ እስቲ ዐይኔን በጨርቅ ሸፍነውና እርዱን ሞክር” የሚል አስተያየት ሰጠ፡፡

በዚህን ጊዜ ግን ከወደ ሰማይ ጥሪ መጣ፡፡ የአላህ መልአክ “ኢብራሂም ታላቅነትህን አስመስክረሃልና እርዱን አቆየው” በማለት አወጀ፡፡ በምትኩም መልአኩ ከገነት ያመጣውን በግ እንዲያርድና ልጁን ወደቤቱ እንዲወስደው ነገረው፡፡ በዚህም መሰረት በጉ ታረደ፡፡ ኢብራሂምና ዒስማኢልም ወደ መካ ከተማ ተመለሱ፡፡ ሁለቱ ሰዎች ለፈጣሪ መታዘዝን በግልጽ ያሳዩባት ያቺ ዕለት የዒድ አል-አድሓ በዓል ሆና እንድትከበርም ተወሰነ፡፡ ዒስማኢል ለመስዋእትነት የቀረበበት ድርጊት ደግሞ በዚሁ ዕለት የሚታረደው “ኡድሒያ” መነሻ ሆነ፡፡
----
ዒድ አል-አድሐ የመስዋዕትነትና የመዳን በዓል ነው፡፡ የሐጅ ጸሎት የሚፈጽም ሰው በዚህ ዕለት “ኡድሒያ” የማረድ ግዴታ አለበት፡፡ እኛም ወደ ሐጅ ያልሄድነው ደግሞ ከተቻለ በዚሁ ዕለት በየቤታችን እንስሳት እያረድን ለ“ኡድሒያ” እንድናቀርብ ታዘናል፡፡ ታዲያ ኡድሒያው “ኡድሒያ” ተብሎ የሚመዘገብልን እርዱም ሆነ አጠቃቀሙ ነቢዩ ያስተማሩትን መንገድ የተከተለ ከሆነ ብቻ ነው፡፡ ለምሳሌ አንዳንድ ሰዎች ፍየሉን ያርዱና ለበዓል የሚሆናቸውን ያህል ካስቀሩለት በኋላ ሌላውን ወደ ፍሪጅ ውስጥ ይከቱታል፡፡ ይህ ግን ራስን መጋበዝ ነው እንጂ ኡድሒያ ተብሎ አይመዘገብም፡፡

ነቢዩ እንዳስተማሩት ለኡድሒያ ከታረደው ስጋ አንድ ሶስተኛው በቀጥታ ለድሆች መከፋፈል አለበት፡፡ አንድ ሶስተኛው ለዘመድና ለወዳጅ ነው የሚሰጠው፡፡ የተቀረው አንድ ሶስተኛ ብቻ ነው ለቤተሰቡ አገልግሎት የሚውለው፡፡ ስለዚህ በዚህ እለት የሚፈጸመው መስዋእት “ኡድሒያ” ሆኖ እንዲመዘገብልን ካሻን ትክክለኛውን መንገድ መከተል አለብን፡፡ በተለይ ከታረደው ስጋ የድሆች ድርሻ የሆነውን “ሡሉሥ” ከሁሉም አስቀድመን ለባለቤቶቹ እናስረክብ ዘንድ የአደራ መልዕክታችንን እናስተላልፋለን፡፡

ዒድ ሙባረክ
አፈንዲ ሙተቂ
----
መስከረም 12/2008
ሀረር-ምስራቅ ኢትዮጵያ
----


Sunday, September 20, 2015

Mirriga- An Elite Song of the Oromo People

Mirriga- An Elite Song of the Oromo People
----
Written by : Afendi Muteki
----
Mirriga (also called “Mirriysa) is an epic song very popular among the Eastern Oromos. It is commonly known in the traditions of the tribes of Ittu, Karrayyu and Afran Qalloo. However, from these three groups, Mirriga highly deepens its root among the Ittu Oromos of Carcar (West Harerghe). The reason is that “Ittu” is the Oromo group to whom the foundation and preservation the famous Oda Bultum is ascribed, and Mirriga is the main genre of a song that dominates the events commemorating the ancient caffee assembly of Oda Bultum.

“Mirriga” is considered the power house of knowledge and wisdom. The Ittu Oromos say that their tradition, customs, history and ethics are highly enshrined in the Mirriga song. Furthermore, many of the Ittu Oromo tribal laws can be learned easily from the Mirriga poems. Thus the Ittus Oromos say

Fooni nyaatti malee adurree ilkaan meetaa
Namaatu hinbeyne malee mirrigaa kheessi heera.

Meaning
The cat eats a meat yet her teeth are “silver”
Mirriga is a law internally, yet many people don’t understand.

Mirriga is a highly elicitic song that can’t be sung by everybody except those who have a knowledge. It isn’t sung also at everywhere. It is usually performed on two occasions. One is when a senior leaders of a clan and the men at their service come together to discuss an issue that needs consideration at a clan level, or when the leaders and deputies of all clans of Ittu Oromo discuss a tribal issue. The other occasion is the one I said above. That is the celebration of special events like the congress of Oda Bultum.
*****
The Mirriga poems are of two types, the existing (traditional) poems and the non-traditional ones. The traditional poems are those which have been transmitted orally from one generation to the next. The themes of these poems are the Oromo history, culture, tradition and law. These traditional poems are known by most of the clan leaders of Ittu Oromo although there may be variations on the usages of the words of the poems. For a person to be elected as a leader of a clan, the other posts in the leadership of the clan, to be the member of the congress of Oda Bultum or to be elected in the tribal office of Ittu Oromo, he must have a good knowledge of the traditional Mirriga poems. The best example of the traditional Mirriga poem is the following one which the Ittu Oromos regard as “The golden Constitution of Oda Bultum”

Afuriin Odaa bule shaniin “Darrabbaa” bule
Darraabbaa halkan heeraa gaariin maal hasaasaa bule
Okholee saddeetin heeree, okkotee saddeetin heeree
Khorma saddeet heeree, khilla saddeet heeree
Ciicoo saddeet heeree, haqaaraa saddeet heeree
Siinqee saddeet heeree, Dhibaayyuu saddeet heere
Waraana saddeetiin heere, fal’aana saddeetin heeree
Eela saddeet heere, goojjoo saddeet heeree
Daadhii Bookhaa nannaqee, deyma wal-kheessa tufe
Mee akka galaana kufee siitu garaa nadhufe.
-----
The poem can be translated as follows.

The four have passed the night at Odaa, the five passed the night at Darrabaa
What did the “wise” whispered in the law-making night of Darrabbaa?
He Decreed eight “Okholee”, and eight pots
He decreed eight bulls and eight “Khilla”
He decreed eight “Ciicoo” and eight “Haqaaraa”
He decreed eight Siinqee and eight “Dhibaayyuu”
He decreed eight spears and he decreed eight spoons
He decreed eight wells and eight huts
He prepared a drunk from pure honey, and he breath the same
Oh my blood! You have come to my mind as a traveling flood.

In the poem, the verse “the four have passed the night at Odaa” refers to the four clans composing the “Galaan” moiety of Ittu Oromo.  They are called Baabbo, Alga, Gaadulla and Elelle. According to the tradition of Oda Bultum, these four clans discuss and draft new laws under the oda tree (Qallu is the fifth clan grouped under this moiety but it is prohibited by the tradition to participate in political affairs; thus the Qallu clan don't participate in the formulation of new laws and the assumption of political power. Qallu are usually the religious leaders of the people).

“The five who passed the night at Darrabba” refers to the five clans consisting the “Khura” branch of Ittu Oromo. They are called Addayyo, Waayye, Gaamo, Arroojjii and Baaye. These five clans discuss new laws under “Garbii Darrabbaa”- a big acacia tree found two kilo meters north of Oda Bultum. The law drafted at the two places will be brought together at Oda Bultum for the ratification by the tribal assembly. It was only after this process was accomplished that the new laws would be proclaimed at Oda Bultum in the last night of the event.

The other verses of the poem refer to the items (Khilla, Khorma, Haqaara) and materials (okholee, okkotee, waraana, siinqee, goojjoo etc) needed to undertake certain ritual ceremonies at Oda Bultum. These rituals were undertaken side by side with the drafting of new laws.  The poem says “the eight” because only eight clans undertake these rituals and two clans of Ittu Oromo were exempted from conducting the rituals. One of the two clans exempted from the rituals was the Waayyee clan who had a responsibility of monitoring the security during the celebration of the congress of Oda Bultum. The second clan was the Qallu who are regarded the people of blessing and healing.
*****
The non-traditional Mirriga poems are those which are composed on specific events or those which an individual poet-singer called “qondaala” composes on his own will. Most of these poems are short lived; they have little chance of spreading in the society and establishing themselves at equal level with the traditional poems. However, they are the determinants in examining the wisdom and eloquence of the “qondaala”. They are also some of the denominators that determine the status the “qondaala” will have in the society and the future prospects he may assume. If the “qondaala” is an incumbent leader of an Ittu clan, then the fame he would get because of his poems may bring him more respects; moreover, his role as a clan leader may increase.  If the “qondaala” that composes the new exciting poems is of young age, then it is very likely for him to be the future leader of his clan and to get a place in the leadership of Oda Bultum.

Although it heavily relies on the poetry skills of “qondaala”, Mirriga is not a solo song; it is performed by a group. Its performance requires usually the elites (hayyuu) of a clan or certain group gathered in a house or under a shade of a tree. When the singing starts, the qondaala (poet-singer) of the clan stands within the crowd by holding his “halangee” (a whip made from skin) and howls the rhythmic Mirriga poems. He starts his singing by the famous two verses.

Dhagayi Dhageeffadhu (Hear me, and Listen to me)
Guurii gurraa guuradhu (Take way the dust from your ears)

Then after, he starts his singing. Whenever he utters one verse of the poem, the crowd will accompany him by replaying with the famous Oromo word “hayyee” (meaning “let it be”). And when the “qondaala” show his ability by composing an extra ordinary poem, the members of the crowd will express their excitement by words like “buli” (long live), “kormoomi” (be strong as a roaring bull), “irra aani” (be able to defeat your enemy) etc…..

The best place where one can see the Mirriga in its natural beauty is a clan assembly. This clan assembly is usually lead by the leader of the clan called “abba gosaa” or more commonly “damiina”. The “damiina” is assisted by councilors called “hayyuu”. The “qondaala”, who are known for their Mirriga skills, also act as assistants of the “damiina”. It is the presence of such skilled people in the assembly that would be the source of the beauty of Mirriga.

It must be noted that the clan assembly wouldn’t be gathered for a mere purpose of singing Mirriga. There should be other reasons for hayyus (clan leaders, elders and other elites) to meet at certain place and deal at a clan level. For example, the hayyus may assemble to find solutions for a dispute between two people or to collect finance to be paid as a blood money of a killed person. This act is usually called “gosa bulchuu” (letting the clan to pass the night at certain place or house). The event is sponsored by the person who summoned the clan leaders to resolve his issue; and the clan assembly holds its meeting until it finds out the best way of resolving the problem. It is after the accomplishment of this task that the clan assembly opens the way for Mirriga. And wherever an act of “gosa bulchuu” took place, it is common to see a performance of Mirriga. Thus the Ittu Oromos say

Bakka guuzni oole darasiidhaan beekhani
Bakka gosti bulte ammo mirrigaadhaan beekhani

It can be translated approximately as follows

A place where guuzaa passed the day is known by the voice of “Darasii”
A place where the clan passed the night is known by the performance of Mirriga
---
The Mirriga poems are some of the best preserved examples of the ancient Oromo customs. They are still being transmitted by oral narrations. However, as they are the stores of Oromo tradition and history, they should be documented and made ready for further ethnographic studies.

Afendi Muteki
September 20/2015
Harar


Thursday, July 16, 2015

በዒድ ዋዜማ ምሽት


ጸሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ
----
ነገ የዒድ አል-ፈጥር በዓልን ልናከብር ነው፡፡ ድሮ ልጆች ሳለን በዚህ የዋዜማ ምሽት በየቤቱ ላይ እየዞርን የምንዘምረው ህብረ ዜማ ነበረን፡፡ ይህ ዝማሬ አሁንም ድረስ አለ፡፡ ይሁንና የአሁኖቹ ልጆች በኛ ጊዜ ያልነበሩ ግጥሞችንም ጨመርመር እንዳደረጉ ተነግሮኛል፡፡ ለምሳሌ ህጻናቱ ጠቀም ያለ ጉርሻ ከተሰጣቸው “ያ ቢጢ ቢጢ… ጀንነተ ሊጢ” (“አንተ የቤቱ ባለቤት ጀንነት ግባ” ለማለት ነው) የሚል ምርቃት ያወርዳሉ ሲባል ሰምቻለሁ፡፡ ምንም ነገር ሳይሰጣቸው የሚያሰናብታቸውንም ሰው “ያ ቢጢ ቢጢ… አዛባ ሊጢ” (“የቤቱ ባለቤት ሆይ ጀሀነም ግባ” ለማለት ነው) እያሉ ይረግሙታል የሚል መረጃ ተሰጥቶኛል (“ቢጢ” የሚለው ቃል ለግጥሙ ማሳመሪያ ሲባል የገባ ነው፤ ጠበቅ ተደርጎ ሲነበብ “እንጎቻ” እንደማለት ነው፤ ላላ ተደርጎ ሲነበብ ግን ምንም ትርጉም የለውም፤ ህጻናቱ “ላላ” በማድረግ ነው በግጥሙ ውስጥ ያስገቡት)፡፡

  በኛ ዘመን እንዲህ የሚል ግጥም አልነበረም፡፡ ከዚህ ወልካፋ ግጥም በስተቀር ዜማው እንዳለ የያኔው ነው፡፡ ያ ህብረ ዝማሬ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲሸጋገር ነው ለኛ የደረሰው፡፡ ለዜማው ለየት ያለ መጠሪያ አላበጀንለትም፡፡ በጥቅሉ የምንጠራው “ሙሐመዶ” በሚል ስያሜ ነው፡፡

“ሙሐመዶ” የዝማሬው የመጀመሪያ ቃል ነው፡፡ ይህንን ዝማሬ የምንዘምረው በአንድ ልጅ መሪነት ነው፡፡ ልጁ የግጥሙን ስንኞች እያከታተለ ሲያወርድልን ሌሎች ጓደኞቹ “ሙሐመድ ሰይዲና ሙሐመድ” እያልን እንቀበለዋለን፡፡ የህብረ-ዜማው ሙሉ ግጥም የሚከተለው ነው (ግጥሙ በኦሮምኛ ነው የተገጠመው፤ በቅንፍ ውስጥ በአማርኛ ተርጉሜዋለሁ)፡፡

ሙሐመዶ (ሙሐመድ ሆይ)
ሙሐመድ ጄንኔ (ሙሐመድ እያልን)
ነቢ ፋርሲኔ (ነቢዩን እናወድሳለን)
ያ ነቢ ባህሩ (አንተ እንደ ባህር የሆንከው ነቢዩ)
ዛሂድ ኢኒ ሂንአሩ (አላግባብ የማትናደድ ነህ)
ፋጢማ ነቢ ኢልኬን ቲሚራ (የነቢ ልጅ የሆነችው ፋጢማ ጥርሷ እንደ ቴምር ነው)
ዲና ነቢዳ ኢልኬን ዲጊራ (የነቢዩ ጠላት ጥርሱ እንደ “ድግር” ነው)
ሶመንኒ ገሌ  (ረመዳን ሄዷል)
ሲዲስቶ መሌ (ከስድስቶ/ሸዋል በስተቀር)
ያ ሀደ ዲራ (የቤቱ ባለቤት ሆይ)
ገድ ደርቢ ሊራ (እስቲ ሊራ ወርወር አድርጊልን)
ሊራ አፉሪ (አራት ሊራ ሰጥተሽን)
ሉብቡን ኑፉሪ (ከልባችን አስደስቺን)፡፡
ሙሐመድ ሰለላሁ ዐላ
ሙሐመድ ሰለላሁ ዐላ ሙሐመድ፡፡
-----
“ሙሐመዶ” በበርካታ ከተሞች የታወቀ ህብረ-ዜማ ነው፡፡ በልጅነቱ እርሱን ሳይዘምር ያደገ ልጅ የለም፡፡ የክርስቲያን ልጆች እንኳ ከኛ ጋር ተቀላቅለው “ሙሐመዶ”ን ይዘምሩ ነበር፡፡ ይሁንና በርሱ ብቻ መቆየቱ ስለማይበቃን ሌሎች ዜማዎችንም እንጨምር ነበር፡፡ እነዚህ ተጭማሪ ህብረ ዝማሬዎች ግን አንድ ወጥ አይደሉም፡፡ በአንድ ከተማ ውስጥ ባሉ ሁለት ቀበሌዎች ውስጥ የሚኖሩ ልጆች እንኳ የተለያዩ ዜማዎችን ሊዘምሩ ይችላሉ፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን “ጀማሉል ዓለም” የተሰኘው ህብረ-ዝማሬ ከመሐመዶ ቀጥሎ በሌሎችም አካባቢዎች በደንብ የሚታወቅ ይመስለኛል፡፡ “ሙሐመዶ”ን የማይዘምሩት የሶማሊ ልጆች እንኳ “ጀማሉል ዓለም”ን ሲዘምሩት በአንድ የነሺዳ ሲዲ ውስጥ አይቼአቸው ነበር፡፡ የ“ጀማሉል ዓለም” አዝማች የሚከተለው ነው፡፡

ጀማሉል ዓለም (ሸሊላ)
ጀማሉል ዓለም (ሸሊላ)
ባህረ ሙስጠፋ (ሸሊላ)
ያ ባህረ ጁህዲ ጁንዲላ

“ጀማሉል ዓለም” ማለት “አንተ የዓለም ውብ የሆንከው” እንደማለት ነው፡፡ እንዲህ የተባሉት ነቢዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ናቸው፡፡ ታዲያ ከአዝማቹ ቀጥሎ የሚዜሙት አንዳንድ ግጥሞች ከአዝማቹ ጋር የማይሄዱ (“አንታራም” ግጥሞች) መሆናቸውን ሳስብ ድንቅ ይለኛል፡፡ ለምሳሌ በዝማሬው ውስጥ እንዲህ የሚል ግጥም ነበር፡፡

“ጋረራ ያና ቦሮፋ ካፍና
ጆልሌ ኑቲ ካቲ ዱኬ ኢቲ ካፍና
ዱኬ ማል ካስና ጋረራ ባፍና”

የአማርኛው ትርጉም የሚከተለው ነው፡፡

“ጋራ ላይ እንሄዳለን ድኩላ እናባርራለን
የሚተናኮሉንን ልጆች እናርበደብዳቸዋለን
የምን ማርበድበድ ብቻ! ጋራው ላይ እንነዳቸዋለን”

በተለምዶ እንዲህ ዓይነት ግጥሞች የሚገጠሙት የሁለት ሰፈር ልጆች በሚጣሉበት ጊዜ ነው፡፡ የተጣሉ ልጆች በዱላ እየተመካከቱ የሚበሻሸቁበት ግጥም መሆኑን ካደግን በኋላ ነው የተረዳነው፡፡ እኛ ግን ምኑም ሳይገባን የዒድ ማድመቂያ አደረግነው፡፡ አይ ልጅነት ደጉ!!

የገንደ ሀድራ ልጆች ደግሞ አሉ! አንዱን ዝማሬ ለነርሱ ብቻ በሞኖፖል የተሰጠ አድርገው የሚያስቡ፡፡ ያንን ዝማሬ የኛ ሰፈር ልጆች ካዜሙት የቃል ማስጠንቀቂያና ማስፈራሪያ ይለቁብናል፡፡ ዝማሬውን ከደገምነው ግን በዱላ ጭምር ያዋክቡን ነበር፡፡ የዝማሬው አዝማች የሚከተለው ነበር፡፡

“አወይ ነቢ ሰላም ዐላ (አንተ ነቢ ሰላም ላንተ ይሁን)
ኑር ሐቢቢ ሶላት ዐላ (አንተ ነቢ ሶላት ላንተ ይሁን)

ከዚህ አዝማች ጋር ብዙ ግጥሞችን ይደረድራሉ፡፡ በመሃሉም እንዲህ የሚል ባለሁለት መስመር ግጥም አለ፡፡

“አክካ አዱ ጎላ ባቱ (ከጎሬዋ እንደምትወጣ ጮራ)
ከን ዱራ ዱብኒ አዳቱ” (ፊቱም ኋላውም የሚያበራ)

የሀድራ ልጆች በጣም ብዙ ነበሩ፡፡ ብዛታቸውን ተመክተው ነው “አወይ ነቢ ሰላምን አትዘምሩት” እያሉ የሚጫኑን፡፡ እኛም በምሽቱ መጀመሪያ ላይ ትዕዛዛቸውን እናከብርና “ሙሐመዶ”ን ወይንም “ጀማሉል ዓለም”ን ብቻ እንዘምራለን፡፡ በሶስት ሰዓት ገደማ ግን የሀድራ ልጆች ለሚያደርጉብን ጭቆና ብድሩን እንከፍላለን በማለት ከላይ የጻፍኩትን ግጥም እንዲህ እያበላሸን እንዘምራለን፡፡

አክከ አዱ ጎላ ባቱ (ከጎሬዋ እንደምትወጣ ጮራ)
ሚጪዮ ፉልሊ አዳቱ  (የልጅቷ ፊት ሲያበራ)

እንዲህ እያልን የምንዘምረው የሀድራ ልጆች እንዲሰሙን ድምጻችንን ከፍ በማድረግ ነው፡፡ ሀድራዎች በንዴት ዱላቸውን እየወዘወዙ በሩጫ ሲመጡብን በጨለማው ውስጥ እንበታተንና ወደቤታችን እንመርሻለን!! አይ ልጅነት ደጉ!!

እኛ ነቢዩን አልነካንም!! ሐድራዎች ዝማሬው የኛ ብቻ ነው እያሉ ስለሚጫኑን እነርሱን ለመበቀል የነበረን አማራጭ መንገድ ይኸው ብቻ ነው፡፡ ቢሆንም ለነቢዩ የተገጠመን ግጥም ማጣመም ልክ አልነበረም፡፡ በመሆኑም ሐራምና ሐላሉን በደንብ ስንረዳ “አስተግፊሩላህ” ብለናል!! አሁንም አስተግፊሩላህ!! ወደፊትም አስተግፊሩላህ!!
----
እንኳን ለዒድ አል-ፈጥር በዓል አደረሰን!!
ዒድ ሙባረክ!!