Friday, November 28, 2014

የትግል ስም (Nom De Guerre)




ጸሓፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ

===ለመግቢያ ያህል====

    “የትግል ስም” ቃሉ እንደሚያመለክተው በትግል ዓለም ውስጥ ላለ ሰው ነው የሚያገለግለው፡፡ ታጋዩ በትግል ዓለም ውስጥ እያለ የሚጠቀምበት መጠሪያው ነው፡፡ ታጋዮች የትግል ስምን የሚጠቀሙት በልዩ ልዩ ምክንያቶች ነው፡፡ ዋነኛው ምክንያት ግን ታጋዩ በእውነተኛ ስም ሲጠቀም ሊደርስበት ከሚችል አደጋ ለመከላከል የሚል ነው፡፡
     
የትግል ስም እንደ ብዕር ስም በሚስጢራዊነት አይያዝም፤ ሰውዬው ድሮ የሚታወቅበትን ስም ተክቶ በስራ ላይ የሚውል ነው፡፡ ታጋዩ ወደ ትግል ዓለም ከገባ በኋላ የሚያገኛቸው የትግል ጓዶች በትግል ስሙ ነው የሚጠሩት፡፡ በመታወቂያም ሆነ በሌሎች ሰነዶች ጥቅም ላይ የሚውለውም የትግል ስም ነው፡፡ በተጨማሪም ታጋዩ ትግሉን በድል ካጠናቀቀ በኋላም በአብዛኛው በትግል ስሙ መገልገሉን ሲቀጥልበት ይታያል፡፡

   የትግል ስምን ለመጀመሪያ ጊዜ በጥቅም ላይ ያለው ማን እንደሆነ አይታወቅም፡፡ ሆኖም የሩሲያ ኮሚኒስቶች በትግል ስም በብዛት በመጠቀም ቀዳሚዎች ናቸው፡፡ ለምሳሌ እንደ ቭላድሚር ሌኒን፣ ጆሴፍ ስታሊን፣ ሊኦን ትሮትስኪ፣ ሉሊ ማርቶቭ ያሉ ስሞች በሙሉ የትግል ስሞች ናቸው፡፡ በሌሎች ሀገሮች የነበሩ ኮሚኒስቶችም በትግል ስም በብዛት ይጠቀሙ ነበር፡፡ ሆ ቺ ሚን፣ ኪም ኢል ሱንግ፣ ቼ ጉቬራ የመሳሰሉ መጠሪያዎች የትግል ስሞች ናቸው (የቼ ጉቬራ ትክክለኛ ስም “ኧርነስቶ ጉቬራ” ነው፤ የኪም ኢል ሱንግ ትክክለኛ ስም “ኪም ሱንግ ቹ” ነው)፡፡

====የትግል ስም በኢትዮጵያ===

   የትግል ስምን ለመጀመሪያ ጊዜ በስራ ላይ ያዋለው ኢትዮጵያዊ ማን እንደሆነ በትክክል አይታወቅም፡፡ ሆኖም ከተማሪዎች ንቅናቄ የፈለቁት ወጣቶች የፋኖነት ህይወት በጀመሩበት ዘመን በብዛት ስራ ላይ እንደዋሉት ይታወቃል፡፡ ታዲያ እነዚያ ፋኖዎች የትግል ስምን የሚጠቀሙበት ምክንያትና ስሙን በስራ ላይ የሚያውሉበት ዘይቤ አንድ ወጥ አልነበረም፡፡ በህቡዕ እና በትጥቅ ትግል መንግሥትን ለመለወጥ የሚታገሉ ድርጅቶች ከተመሰረቱ በኋላ በጣም ጎልብቶ የመጣው የትግል ስም አጠቃቀም ልማድም እንደ ፓርቲው ይለያያል፡፡ ከዚህ በማስከተልም በቀደምት ድርጅቶች ውስጥ ይሰራበት የነበረውን ልማድ በአጭሩ እናወሳለን፡፡

1.      ጀብሃ እና ሻዕቢያ

ጀብሃ እና ሻዕቢያ የትግል ስምን የመጠቀም ባህል የነበራቸው መሆኑ አልተመዘገበም (ወይም አላነበብኩም)፡፡ ሆኖም ሁለቱም ፓርቲዎች የሚስጢር ስም የመጠቀም ባህል የነበራቸው መሆኑ በስፋት ይታወቃል፡፡ በተለይም ታጋዮቹ ለየት ያለ ተልዕኮ በሚፈጽሙበት ወቅት በሚስጢር ስም እንዲጠቀሙ ይደረጋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በጀብሃና ሻዕቢያ ዘንድ ታጋዩን በቅጽል ስም መጥራት በጣም የተለመደ ነው፡፡ ለምሳሌ የጀብሃው “መሐመድ ቺክኒ”፣ የሻዕቢያዎቹ “ወልደ ዲንክል”፣ “ተክላይ አደን”፣ “ሀይሌ ጀብሀ” ይጠቀሳሉ፡፡ “የማነ ጃማይካ” የሚባለው የህወሐት ታጋይም ከድሮ የሻዕቢያ አባል በነበረበት ዘመን ሲጠራበት በነበረው ቅጽል ነው የሚታወቀው፡፡   

2.     ህወሐት

ህወሐት በትግል ስም የመጠቀም ሰፊ ልማድ አለው፡፡ በትጥቅ ትግሉ ዘመን ፓርቲው እያንዳንዱ ታጋይ በትግል ስም እንዲጠቀም ያደርግ ነበር፡፡ እነዚያ ታጋዮች ከትጥቅ ትግሉ ፍጻሜ በኋላም በትግል ስማቸው መጠራታቸውን ቀጥለዋል፡፡ በዚህ ረገድ ከፓርቲው የተገለሉትም ሆነ በፓርቲው ውስጥ ያሉት ተመሳሳይ መንገድ እየተከተሉ ነው፡፡

ህወሐቶች የትግል ስም የሚመርጡት ስማቸውን ሙሉ በሙሉ በመቀየር አይደለም፡፡ የታጋዩ የልደት ስም ብቻ ነው የሚለወጠው እንጂ የአባቱ ስም አይቀየርም፡፡ ከታዋቂ የህወሐት ሰዎች መካከል የሚከተሉትን ከትግል ስማቸው ጋር መጥቀስ ይቻላል፡፡

1.      እምባዬ መስፍን= ስዩም መስፍን
2.     ዘርዑ ገሠሠ= አግዓዚ ገሠሠ
3.     መሐሪ ተኽለ= ሙሴ ተኽለ
4.     አምሀ ጸሐየ= አባይ ፀሐየ
5.     ዮሐንስ ገ/መድህን= ዋልታ ገ/መድህን
6.     ስዕለ አብርሃ= ስዬ አብርሃ
7.     ወልደስላሤ ነጋ= ስብሐት ነጋ
8.     ለገሰ ዜናዊ= መለስ ዜናዊ
9.     ራስወርቅ ቀጸላ= አታኽልቲ ቀፀላ
10.    ገሰሰው አየለ= ስሁል አየለ
11.     መሐመድ ዩኑስ= ሳሞራ ዩኑስ
12.    ዮሐንስ እቁባይ= አርከበ እቁባይ
13.    ሐዱሽ አርኣያ= ሀየሎም አርኣያ

    ህወሐቶችም እንደ ሻዕቢያ ታጋዮቻቸውን በቅጽል ስም የመጥራት ልማድም አላቸው፡፡ ለምሳሌ ከህወሐት ታጋዮች የሚበዙት ሙሉጌታ ገ/ህይወትን “ጫልቱ”፣ ሰለሞን ተስፋዬን “ጢሞ”፣ ጄኔራል አበበ ተክለ ሀይማኖትን “ጀቤ”፣ ጄኔራል አብርሃ ወልደማሪያምን “ኳርተር”፣ ካሳ ገብረመድህንን “ሸሪፎ”፣ አብረሃ ታደሰን “መጅሙእ”፣ ጸጋይ በርሄን “ሀለቃ”፣ ጄኔራል ታደሰ በርሄን “ጋውና” እያሉ ነው የሚጠሩት፡፡ ግንቦት 20/1983 ከአዲስ አበባ ሬድዮ ጣቢያ “የዘመናት የህዝብ ብሶት የወለደው ጀግናው የኢህአዴግ ሰራዊት…” በማለት ያወጀውን ታጋይ በእውነተኛ ስሙ የሚያውቁት ጥቂቶች ናቸው፡፡ የታጋዩ ቅጽል ስም “ላውንቸር” ስለመሆኑ ግን ብዙዎቻችን እናውቃለን፡፡
 
    ከዚህ በተጨማሪ ህወሐትና ሻዕቢያ ታጋዮቻቸውን “ወዲ እገሌ” (የእገሌ ልጅ) እያሉ በሰሜኑ የሀገራችን ስም በሚሰራበት ባህላዊ ዘይቤ መጥራትን ያዘወትራሉ፡፡ በኦፊሴላዊ ደብዳቤዎች ጭምር “ወዲ እገሌ” የሚለውን ልማድ ሲጠቀሙ ይስተዋላል (በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅት ይፋ የሆኑትን የአቶ ኢሳያስና የአቶ መለስን ደብዳቤዎች አስታውሷቸው)፡፡

3.     መኢሶን

የመኢሶን ሰዎች በትግል ላይ በነበሩበት ወቅት በልደት ስማቸው ነው የሚጠቀሙት፡፡ ሆኖም ከዋነኛ ስማቸው በተጨማሪ በሚስጢር ስምም ይገለገሉ እንደነበር ከልዩ ልዩ ሰነዶች የተገኘው መረጃ ያረጋግጣል፡፡ በዚህ መሰረት የመኢሶን መስራቾች ከሚታወቁበት የሚስጢር ስሞች የሚከተሉት ይጠቀሳሉ፡፡
a.     ሀይሌ ፊዳ= መላኩ
b.     ነገደ ጎበዜ= ነጋልኝ
c.     አብዱላሂ ዩሱፍ= አደም
d.     አንዳርጋቸው አሰግድ= ወልዴ
e.     ፍቅሬ መርዕድ= ሳሙኤል
f.      ከበደ መንገሻ= ነጋ
g.     ሲሳይ ታከለ= አሸናፊ
h.     ንግስት አዳነ= አይዳ
i.      ተረፈ ወልደጻዲቅ= ሚካኤል

ታዲያ እነዚህ ስሞች ሚስጢራዊ ደብዳቤ በሚጻፍበት ወቅት ወይም ሚስጢራዊ ስብሰባ በሚካሄድበት ጊዜ ብቻ ነው የሚያገለግሉት፡፡ መኢሶኖች በመታወቂያም ሆነ በፓስፖርት የሚገለገሉት በዋነኛ ስማቸው ነው እንጂ በሚስጢር ስም አይደለም፡፡

4.     ኢህአፓ

ኢህአፓዎችም በትግል ላይ ሳሉ ዋነኛ ስማቸውን በመተው በፓርቲው በሚሰጣቸው ስም ይገለገሉ ነበር፡፡ ፓርቲውን ወክለው በሚገኙበት መድረክ ሁሉ በዚያው ስም ነበር የሚጠቀሙት፡፡ ለታጋዮቹ የትግል ስም የሚሰጥበት ዘይቤ ግን አንድ ወጥ አይደለም፡፡ አንዳንድ ታጋዮች የልደት ስማቸውን ብቻ ይለውጡና ሌላ ቅጥያ ሳያስከትሉበት በዚያው ይጠራሉ (ለምሳሌ “ጋይም” እና “አያልነሽ”ን መጥቀስ ይቻላል)፡፡ አንዳንዶች ግን የአባታቸውን ስም ጭምር ይለውጣሉ፡፡ ከዚህ ሌላም ብዙዎቹ የኢህአፓ ታጋዮች ከትግሉ ዓለም ከተገለሉ በኋላ ወደ ቀድሞ ስማቸው ሲመለሱ ይታያል፡፡ ከኢህአፓ አባላት የትግል ስሞች የሚከተሉትን መጥቀስ ይቻላል፡፡

a.     ክፍሉ ታደሰ= ታዬ አስራት
b.     መላኩ ተገኝ= ያፌት
c.     ገብረ እግዚአብሄር ወልደሚካኤል= ጋይም
d.     የዓለም ገዥ ከበደ= አያልነሽ
e.     መርሻ ዮሴፍ= በላይነህ ንጋቱ
  
በነገራችን ላይ ድሮ የኢህአፓ ታጋዮች የነበሩት የአሁኖቹ የኢህዴን/ብአዴን ዋነኛ ባለስልጣናት በትግል ስማቸው ነው የሚጠሩት፡፡ እንደምሳሌም መብራቱ ገ/ህይወት (በረከት ስምኦን)እና ፍቅሩ ዮሴፍን (ህላዌ ዮሴፍ) መጥቀስ ይቻላል፡፡ ጌታቸው ጀቤሳ በበኩሉ ለረጅም ጊዜ በትግል ስሙ ሲጠቀም ከቆየ በኋላ ከኢህዴን ሲወጣ “ያሬድ ጥበቡ” የተሰኘውን እውነተኛ ስሙን መጠቀምን መርጧል፡፡

5.     ኦነግ
 
 ከላይ የጠቀስኳቸው ድርጅቶች የትግል ስምን በስራ ላይ የሚያውሉበት ዋነኛ ምክንያት የታጋዮቻቸውንና ደህንነት ለማስጠበቅ በሚል ነው፡፡ በተለይም ታጋዩ በተወለደበት አካባቢ ለውጊያም ሆነ ለሌላ ተልዕኮ የሚሰማራ ከሆነ በዋነኛ ስሙ ቢጠቀም ህይወቱ አደጋ ላይ ይወድቃል ተብሎ ስለሚታመን ነው በትግል ስም እንዲጠቀም ሲደረግ የነበረው፡፡ በተጨማሪም ታጋዩ በትግል ስም ቢጠቀም በወላጆቹና በሌሎች ዘመዶቹ ላይ አደጋ እንዳይደርስባቸው ለመከላከል ይረዳል የሚል ምክንያት ከድርጅቶቹ ይቀርብ ነበር፡፡

    የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ባህል ግን ከዚህ ይለያል፡፡ በዚህ ድርጅት ውስጥ ያለ ታጋይ የትግል ስም እንዲጠቀም የሚደረገው በዋነኛነት ለታጋዩ ደህንነት ተብሎ አይደለም፡፡ ከታጋዩ ደህንነት በላይ ለድርጅቱ አንድነት ጠቃሚ ነው ተብሎ ስለሚታመን ነው፡፡ የኦነግ ሰዎች ታጋዮቻቸው በትግል ስማቸው ቢጠቀሙ ሀይማኖትና ክፍለ ሀገርን አስታክኮ የሚመጣ መከፋፈልን ለመከላከል ይረዳል በማለት ያምናሉ፡፡ አንድ ታጋይ በስሙ ብቻ ተለይቶ ጥቃት እንዳይደርስበት ለመታደግም ጠቃሚ ነው በማለት ያስረዳሉ፡፡ 
     በዚህም መሰረት የኦሮሞ ስም የሌለው ታጋይ (አሕመድ፣ አብደላ፣ አበበ፣ ከበደ ወዘተ… በመሳሰሉት የሚጠራ) ወደ ድርጅቱ ሲመጣ ቀዳሚ ስሙን ይተውና በኦሮሞ ስም እንዲጠራ ይደረጋል፡፡ የታጋዩ የአባት ስም ኦሮምኛ ካልሆነ እርሱንም ይቀይራል፡፡ ታዲያ ታጋዩ የአባቱን ስም የሚመርጠው በዘፈቀደ አይደለም፡፡ የዘረግ ሀረጉን ወደላይ ሲቆጥር መጀመሪያ የሚመጣበትን የኦሮሞ ስም (የኦሮሞ ስም ያለው ቅመ-አያት የሚጠራበትን) ነው እንደ አባቱ ስም የሚገለገልበት፡፡ የአባቱ ስም ኦሮምኛ ከሆነ (ለምሳሌ እንደ ዮሐንስ ለታ) የራሱን ስም ብቻ ነው የሚቀይረው፡፡ ታጋዩ ይዞት የመጣው ሰው ሙሉ በሙሉ ኦሮምኛ ከሆነ ግን በስሙ ላይ የሚደረግ ለውጥ የለም (እንደ ምሳሌም ባሮ ቱምሳ፣ ኢብሳ ጉተማ፣ አባቢያ አባጆብር የመሳሰሉትን መጥቀስ ይቻላል)፡፡ ሆኖም ጥቂት የኦነግ ሰዎች ይህንን ልማድ አልተከተሉም፡፡ ከዚህ አሰራር ጋር በማይጣጣም መንገድ ነው የትግል ስማቸውን የመረጡት፡፡ እንደ ምሳሌም በተከታታይ የኦነግ ሊቀመንበር ሆነው የተመረጡትን በሪሶ ዋቤ፣ ገላሳ ዲልቦ እና ዳውድ ኢብሳን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ድርጅቱን ከውጪ ሀገር የተቀላቀሉትም እንደ አዲስ የትግል ስም ሲሰጣቸው አይታይም (ለምሳሌ ጣሃ አብዲ፣ በያን አሶባ ወዘተ.. ይጠቀሳሉ)፡፡ ከታዋቂ የኦነግ ሰዎች መካከል የጥቂቶቹ የትግል ስም እንደሚከተለው ነው፡፡

a.     አብዱልከሪም ኢብራሂም= ጃራ አባገዳ (ከኦነግ በልዩነት ወጥቶ “የኦሮሞ ነጻነት እስላማዊ ግንባር” የተሰኘውን ድርጅት ቢመሰርትም ከኦነግ መስራቾችም አንዱ ነበር)
b.     መገርሳ በሪ= በሪሶ ዋቤ
c.     ዮሐንስ በንቲ= ገላሳ ዲልቦ
d.     ፍሬው ኢብሳ= ዳውድ ኢብሳ
e.     ቃሲም ሑሴን= ነዲ ገመዳ
f.      ዮሐንስ ለታ= ሌንጮ ለታ
g.     አብረሃም ለታ= አባጫላ ለታ
h.     ዮሐንስ ኖጎ= ዲማ ኖጎ
i.      አብዱልፈታህ ሙሳ= ቡልቱም ቢዮ
j.      ጀማል ሮበሌ= ጉተማ ሀዋስ
-------------
መጋቢት 28/2006
አፈንዲ ሙተቂ

Thursday, November 27, 2014

“አል-ካብሊ”፤ “ሸዛ ዛሂር” እና “ዓሊ ቢራ”



 ጸሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ
-----
አንጋፋውን ሱዳናዊ ድምጻዊ ዐብዱልከሪም አል-ካብሊን ከዚህ ቀደም ተዋውቀነው ነበር፡፡ ታዲያ የዚህን ጎምቱ ሰው ድምጽ ዛሬ ከአንድ ጓደኛዬ “አይፓድ” ውስጥ ሰማሁትና በሃሳብ ወደ ልጅነቴ ወሰደኝ፡፡ እናም ከርሱ ጋር “ሸዛ ዛሂር” እያልኩ ሳንጎራጎር “ስለዚህ ዘፈን ለምን አንድ ነገር አልጽፍም?” የሚል ሃሳብ መጣብኝ፡፡ እነሆ ጻፍኩላችሁ!!
*****
Abdul-Keriem Al-Kabli, the legendary Sudanese music icon.

አል-ካብሊ ከሌሎች ሱዳናዊያን ድምጻዊያን ከሚለይባቸው ባህሪዎች አንዱ አብዛኛውን ጊዜ ሙዚቃዎቹን በራሱ የሚጽፋቸው መሆኑ ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ በሙዚቃዎቹ ውስጥ ከሱዳን የዐረብኛ ዘይቤ ይልቅ ብዙ ጊዜ የጥንቱን “ዐረቢያ አልፉስሓ” (Classical Arabic) የሚጠቀም መሆኑ ነው፡፡ ሦሥተኛው ደግሞ ግጥሞቹን በሚጽፈበት ጊዜ ጥንታዊ የሆኑትን “ቀሲዳ”፣ “ቡርዳ” እና “ሙዓለቃት” የሚባሉት የዐረብኛ የስነ-ግጥም ዘይቤዎችን የሚጠቀም መሆኑ ነው፡፡

ከአል-ካብሊ ዘፈኖች መካከል በጣም የሚደነቀው “ሸዛ ዛሂር” ይባላል፡፡ “ሸዛ ዛሂር” የሚደነቀው በጥንቱ ዐረቢያ ፉስሓ የተገጠመ በመሆኑ ብቻ ሳይሆን ዜማውም በጣም ማራኪ በመሆኑ ነው፡፡ የዘፈኑ አዝማች በኢራኖቹ “ሩባኢያት” ስልት የተጻፈ ሲሆን ተከታዮቹ ግጥሞች ግን በዐረብኛው “ሙዓለቃት” ስልት ነው የተጻፉት፡፡
 *****
“ሸዛ ዛሂር” በጣም የተደነቀው ግን በግጥሞቹ ውበት ሳይሆን በመልእክቱ እና ደራሲው ግጥሙን ሲጽፍ በተከተለው ለየት ያለ ተምሳሌታዊ (allegorical) ዘይቤ ነው፡፡ ግጥሙ ሲጀምር “ሸዛ ዛሂር” ይላል፡፡ “አበባው ፈነዳ… መዓዛው ምድሩን ሞላ” እንደማለት ነው፡፡ ታዲያ በዘፈኑ ውስጥ በአበባ የሚያስመስለው ሰው ሴት ሳትሆን ወንድ ነው፡፡ ወንድን አበባ እያሉ ማሞገስ አለ እንዴ?… በሌላ ቦታ አይታወቅም፡፡ አል-ካብሊ ግን አደረገው፡፡

   አል-ካብሊ የወደደውን ወንድ ሲያሞግስ “ወአንዙሩ ላ አራ በድረን አንተ ለይለተል በድሩ” ይለዋል፡፡ “ወደ ሰማይ ሳንጋጥጥ ሙሉውን ጨረቃ ለማለት አልቻልኩም፤ ምክንያቱም ያንተ ብርሃን ጨረቃውን አጨልሞታል” እንደማለት ነው፡፡ በተጨማሪ ደግሞ “አንተ ረሒቁን ለና” እስከማለት ደርሷል (“አንተ የኛ Nectar ነህ” እንደማለት ነው፤ Nectar ወፎችና ንቦች የሚቀስሙት የአበባ ጣፋጬ ክፍል ነው፤ በአማርኛ ምን ይባላል)፡፡

አል-ካብሊ ከዚህም ርቆ ይሄድና የወደደውን ሰውዬ “ለደቱ አል-ኸምረ ዐን ሸፈቲ፤ ለዐለ ጀማለከል ኸምሩ” ይለዋል፡፡ “አንድም የመጠጥ ብርጭቆ ወደ ከንፈሬ አላስጠጋሁም፤ ነገር ግን ውበትህ “ኸምር” ሆኖ አስክሮኛል” ማለቱ ነው፡፡ ለመሆኑ ሰውዬው ምን ነክቶት ነው ወንድን እንዲህ የሚያሞግሰው (አንዳንዱ ሰው ምናልባት… Gay ሳይሆን አይቀርም ይል ይሆናል….ቂቂቂቂ)

የሰውዬውን ማንነት ከኋላ ትመጡበታላችሁ፡፡ አሁን የዘፈኑን ግጥም ተመልከቱ፡፡

(አዝማች)
ሸዛ ዛህሪን ወላ-ዛህሩ
ፈዐይነ ዚሉ ወን-ነህሩ
ረቢዑ ሪያዲና ወላህ
አሚን አህ ፊከ አን-ነሽሩ
-----
ወሐዘ ነሁሩ የብሱሙሊ ዐኒ-ድ-ዱንያ ወየፍተሩ
ወአንዙሩ ላ አራ በድረን አአንተ ለይለተል በድሩ፡፡
-----
ወቢሂ ሱክሩን ተመለከኒ ወዐጀቡን ከይፈ ቢሂ ሱክሩ
ረድቱ አል-ከእሳ ዐን ሸፈቲ ለዐለ ጀማለከል ኸምሩ፡፡
----
ነዐም አንተ ረሒቁን ለና ወአንተ ሲሕሩ ወልኢጥሩ
ወአንተ ሲሕሩ ሙቅተዲረን ወገይረል ሀይ ወሀዋ ሲሕሩ፡፡
---
ኹዙ ዱኒያ ቢዐጅማኢሀ ሐቢቡን ዋሒዱን ዙኽሩ
ኢዛ ጃአት መጣሊኡሁ ፈኩሉ ሰማኡና በድሩ፡፡
---
ኹዙ ዱኒያኩሙ ሃዚሂ ፈዱኒያዋቱና ኩስሩ፡፡
ኹዙ ዱኒያኩሙ ሃዚሂ ፈዱኒያቱና ኩስሩ፡፡
*****
የአል-ካብሊ ግጥም ቅኔያዊ ፍቺ በመጨረሻው ስንኝ ላይ ነው የሚገኘው፡፡ “ኹዙ ዱኒያኩሙ ሃዚሂ ፈዱኒያቱና ኩስሩ” ማለት “ዱኒያ ይህቺ ናትና እዩዋት፤ መጨረሻ ላይ ተሰባሪ ናት” ማለት ነው፡፡ እውነትም ዱኒያ ተሰባሪ ናት፡፡ አል-ካብሊ ግን ሰውዬን አድንቆት ሲያበቃ “ዱኒያ ተሰባሪ ናት ብሎ” ዘጋው፡፡ ከፊት የተናገረውን መቃረን ይሆናል አይደል…?

ነገሩ ወዲህ ነው፡፡ አል-ካብሊ እንዲህ ያደነቀው ሰው ጓደኛው ነበረ፡፡ ይህ ጓደኛው ገጣሚ ሲሆን በጣም ውብ የሆኑ ግጥሞችን በመጻፍ ይታወቃል፡፡ አንድ ቀን ግን ሳይጠበቅ “ጭጭ” አለ፡፡ ምንም ሳይታመም ነፍሲያው ወጣች፡፡ አል-ካብሊ በዚህ ድንገተኛ አደጋ ተደናገጠ፡፡ ልቡ ተሰበረች፡፡

ጓደኛው ከተቀበረ ከጥቂት ቀናት በኋላ በሐዘኑ የተጎዳው አል-ካብሊ በምሽት ከቤቱ ወጥቶ ሰማይ ሰማዩን ማየት ጀመረ፡፡ ሰማዩን እያየ ሟች ጓደኛውን ሲያስታውስ ይህ ግጥም መጣለት፡፡ ወዲያውኑ “ሸዛ ዛሂር”ን ጻፈውና መጫወት ጀመረ፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ደግሞ በአንድ አልበም ውስጥ አካተተው፡፡ ግጥሙ በሱዳኖች ዘንድ ሲሰማ ዐጂብ ተባለ፡፡ የሙዚቃ ገምጋሚዎች በበኩላቸው የአል-ካብሊ የምንጊዜም ምርጥ ዘፈን በማለት ሰየሙት፡፡
*****
አል-ካብሊ “ሸዛ ዛህር”ን ከጻፈው በኋላ እንደ መግቢያ የሚጠቀምበት አጭር እንጉርጉሮም አክሎለታል፡፡ ዘፈኑ ለገጣሚው ጓደኛው የተጻፈ መሆኑን በግልጽ የሚያሳውቀው በዚህ እንጉርጉሮ ውስጥ ነው፡፡ ይህ እንጉርጉሮ በተለምዶ “ማለሁ” እየተባለ የሚጠራው ነው (አል-ካብሊ እንጉርጉሮውን “ማለሁ” በማለት ነው የሚጀምረው፤ ዐረብኛ እንዲህ ሲባል “ለምን ሲል ነው?” የሚል ዘይቤአዊ ፍቺ አለው)፡፡ ታዲያ አል-ካብሊ ብዙ ጊዜ ዘፈኑን ከእንጉርጉሮው በመለየት ነው የሚጫወተው፡፡ አንዳንዴ ግን ሁለቱንም በአንድ ላይ ይዘፍናቸዋል፡፡ ሁለቱ ግጥሞች ሲዘፈኑ የተለያየ የድምጽ ውጣ-ውረድን ስለሚጠይቁ ማንም ዘፋኝ ነኝ ባይ በአንድ ላይ ሊዘፍናቸው ይቸገራል፡፡ እኔ ባለኝ ልምድ ግን አንድ ሰው ሁለቱንም በአንድነት ዘፍኖአቸው ተሳክቶለት አይቼአለሁ፡፡

አዎን! ዓሊ ቢራ ነው፡፡ ዓሊ በ1998 የእንቁጣጣሽ በዓልን በማስመልከት በሸራተን አዲስ በተዘጋጀው የሙዚቃ ኮንሰርት ላይ እንጉርጉሮውንና ሸዛ ዛህርን አንድ ላይ ዘፍኖአቸዋል፡፡ የዓሊ ቢራ አዘፋፈን ውብ መሆኑን ለማየት በዩ-ቲዩብ ላይ የተጫነውን ቪዲዮ ይመልከቱ፡፡
(ቪዲዮውን ለማለት የሚከተለውን ሊንክ ክፈቱ)፡፡

በነገራችን ላይ ዓሊ ቢራ “ሸዛ ዛህር”ን ብቻ ሳይሆን ሌሎች የሱዳን ዘፈኖችንም ሲጫወት በጣም ይሳካለታል፡፡ የዚህ ስኬት አንደኛው ምክንያቱ ደግሞ ዓሊ ግጥሞቹ የተጻፉበትን “ዐረቢያ አል-ፍስሓ”ን በትክክል መናገር የሚችል መሆኑ ነው፡፡ (ዐረቢያ አል-ፉስሓ ሃያ ስምንቱን የዐረብኛ ድምጾች በትክክል ማውጣትን ይጠይቃል)፡፡
*****
አፈንዲ ሙተቂ
ህዳር 18/2007
--

Wednesday, November 26, 2014

“ጥጋብ አይቻልም”



ጸሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ
-----
እነሆ በድጋሚ ወደ ተረት ዓለም ልወስዳችሁ ነው፡፡ ድሮ የሰማሁት አንድ ተረት ከሰው ልጅ ደካማ ባህሪያት መካከል የሚቆጠረውን “ጥጋብ”ን በተዋበ መንገድ እንዴት እንደሚሄሰው እዩት፡፡
-----
በአንዲት መንደር የሚኖር አንድ ደሃ ሰው የሚበላውን እያጣ ይቸገር ነበር፡፡ ሰውዬው ብዙ ዘመን በችግር ካሳለፈ በኋላ “በተወለድኩበት ምድር በረሃብ ከምሞት ወደ ሌላ ሀገር ልሂድና ሲሳዬን ልፈልግ” በማለት ተሰደደ፡፡ ብዙ ከሄደ በኋላ ድካም ሲጀምረው ከአንድ ዛፍ ስር አረፍ አለ፡፡ ልክ እንደተቀመጠም ከዛፉ ላይ የነበረችው አንዲት በቀቀን “ጥጋብ አይቻልም” እያለች መዘመር ጀመረች፡፡ ሰውዬውም ወደላይ እያንጋጠጠ “እንዲህ ስትይ አታፍሪም እንዴ?! ረሃብ ነው የማይቻለው እንጂ ጥጋብማ በደንብ ነው የሚቻለው” በማለት አጸፋውን መለሰላት፡፡

  ሰውዬው የሚበቃውን ያህል ካረፈ በኋላ ጉዞውን ቀጠለ፡፡ ብዙ ከተጓዘ በኋላም ወደ አንዲት ትንሽ ከተማ ገባ፡፡ እዚያም ልመናውን ጀመረ፡፡ ብዙ ቤቶችን አዳረሰ፡፡ የከተማዋ ሰዎችም ያላቸውን ሰጡት፡፡ ሰውዬው ምሽቱን ከአንድ በረንዳ ስር አሳለፈ፡፡ በማግስቱም ልመናውን በመቀጠል ከአንድ ሰፊ ግቢ ደረሰ፡፡ እዚያም “ስለ አላህ! ያላችሁን ስጡኝ! ተዘከሩኝ” በማለት ልመናውን ተያያዘው፡፡ የቤቱ ባለቤት የግቢውን በር ከፈተችና ለማኙን አየችው፡፡ ሰውዬው ከመጎሳቆሉ በስተቀር መልከ መልካም ነው፡፡ አንድም የአካል ጉዳት የለበትም፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ሰው መለመኑ ስላስገረማት “አንተ ሰው! እንደዚህ ጤነኛ ሆነህ ነው እንዴ የምትለምነው?” አለችው፡፡ “ምን ላድርግ እመቤቴ ተቸግሬ ነው እኮ!” በማለት መለሰላት፡፡
“ለምን ሰርተህ አትበላም?”
“ስራ የለኝም፤ ትናንት ነው ከሌላ ሀገር የመጣሁት”
“እና ልትለምን ነው የመጣኸው?”
“አዎና እመቤቴ! ስራ የለኝም እኮ”
“ስራ ቢሰጥህ ትሰራለህ?”
“አዎን እሰራለሁ”

ሴትዮዋ የሀብታም ሰው ሚስት ነበረች፡፡ ባሏ በድንገት ሲሞትባት ከባሏ በወረሰችው ገንዘብ እየነገደችና እያስነገደች ትኖር ነበር፡፡ በመሆኑም ለማኙን ሰውዬ ከሌሎች ተቀጣሪዎቿ ጋር እንዲሰራ ፈቀደችና ወደ ግቢዋ አስገባችው፡፡ ከዚያም የለበሰውን ቡትቶ እንዲያወልቅ በመንገር አዲስ ልብስ እንዲሰጠው አደረገች፡፡ የሚኖርበትም ቤት ተሰጠው፡፡ ቀለብም ተቆረጠለት፡፡ ሰውዬወም በሴትዮዋ ለጋስነት እየተገረመና ምስጋና እያቀረበ የተመደበለትን የሱቅ አሻሻጭነት ስራ መስራት ጀመረ፡፡

 ሰውዬው ከስራው ጋር በጥቂት ጊዜ ውስጥ ተለማመደ፡፡ በስራው ውስጥ ከሁሉም ሰራተኞች በላጭ ሆኖ ተገኘ፡፡ በታማኝነቱም የተመሰገነ ሆነ፡፡ ሴትዮዋ በሰውዬው ባተሌነትና በታማኝነቱ ልቧ ተነካ፡፡ እያደርም በፍቅሩ ተነደፈች፡፡ ብዙ አውጥታ ካወረደች በኋላም ልታገባው ወሰነች፡፡ እናም ለሰውዬው ይህንኑ ነገረችው፡፡

   ይሁንና ሰውዬው በሴትዮዋ አባባል አኮረፈ፡፡ “እኔ ከትቢያ ላይ የተነሳሁ አንድ ድሃ ሰው ነበርኩ፤ እንዴት ካንቺ ጋር በጋብቻ መተሳሰር እችላለሁ?” አላት፡፡ ሴትዮዋ ምክንያቱን ነገረችው፡፡ ከብዙ ክርክር በኋላ ሰውዬው ሊያገባት ወሰነ፡፡ በመሆኑም ድል ያለ ድግስ ተደግሶ ያ የጥንት ለማኝ የቤቱ አባወራ ለመሆን በቃ፡፡

ሰውዬው አባወራ ከሆነ በኋላም ኃላፊነቱን በትጋት መወጣቱን ቀጠለ፡፡ ሴትዮዋም ይበልጥ እያፈቀረችው ሄደች፡፡ “ይሄ ሰውዬ ለምንጊዜውም የሚከዳኝ አይመስለኝም፤ ስለዚህ የስራውን ኃላፊነት በሙሉ ለርሱ ልስጠው፤ ትንሽ ቆይቼ ደግሞ ድርጅቱን በርሱ ስም አዛውራለሁ” በማለት ወሰነች፡፡ ከዚያም ሰውዬውን ጠራችና እንዲህ አለችው፡፡

“እስከዛሬ ድረስ እንደ ሰራተኛም እንደ ባልም ሆነህ ጥሩ ጊዜ ከኔ ጋር አሳልፈሃል፤ ባሳየኸኝ ታማኝትና በሰጠኸኝ ፍቅር ሙሉ ደስተኛ ነኝ፡፡ ስለዚህ ከዛሬ ጀምሮ የድርጅቱ ሃላፊም ሆነ ተቆጣጣሪ አንተ ነህ፤ ካንተ በላይ ማንም የለም፤ እኔ ራሴ በአንተ ስር ነኝ” አለችው፡፡ይህንን ካለችው በኋላ የድርጅቱን አስፈላጊ ሰነዶች አስረከበችው፡፡ በቤቷ የሚገኙ የካዝና ቁልፎችንም ስታስረክበው እንዲህ አለችው፡፡

  “እኝሁልህ የካዝናዎቻችን መቆለፊያዎች! ከዛሬ ጀምሮ ባንተ ኃላፊነት ስር ሆነዋል፤ ወርቁም ሆነ አልማዙ በብዛት አለልህ፤ ነገር ግን የአንዱን ካዝና ቁልፍ አልሰጥህም፤ በዚያ ውስጥ ምን እንዳለ እንድትጠይቀኝም አልፈቅድልህም፤ እርሱን የጠየቅከኝ እለት መቆራረጣችንን እወቅ”፡፡ ሰውዬውም ስለጉዳዩ ምንም ነገር ላይጠይቃት ቃሉን ሰጣት፡፡ በመሃላ ጭምር አረጋገጠላት፡፡

    ባልና ሚስቱ እንዲህ ከተግባቡ በኋላ ኑሮአቸው ደራ፡፡ ትዳራቸው ይበልጥ ተሟሟቀ፡፡ ድርጅታቸው በትርፍ ላይ ትርፍ መዛቁን ቀጠለ፡፡ ሰውዬውም ምንም ተቆጣጣሪ ሳይኖረው ገንዘቡን እንዳሻው ያወጣ ጀመር፡፡ እያደር ግን የሰውዬው ልብ መቀየር ጀመረች፡፡ በአንድ ካዝና እና በውስጠ ሚስጥሩ ላይ ጥያቄ እንዳያቀርብ የተጣለበትን እግድ ሲያስታውስ ገና የሀብት ጣሪያ ላይ ያልደረሰ ሆኖ ተሰማው፡፡ ያንን ካዝና ከፍቶ አለማየቱም ያንገበግበው ጀመር፡፡ ሴትዮዋ አንዱን ካዝና ነጥላ በማስቀመጧም “እወድሃለሁ የምትለው ከልቧ አይደለም” በማለት ወቀሳት፡፡ በመሆኑም ካዝናውን ከፍቶ ለማየት ተመኘ፡፡ ወደሴትዮዋ ሄዶም ጥያቄውን አቀረበ፡፡
   
  ሴትዮዋ በጥያቄው ተደናገጠች፡፡ ተገረመችም፡፡ ቃሌን ያከብራል ብላ የገመተችው ሰው ቃል አባይ ሆኖ በመገኘቱ ተናደደችበት፡፡ ነገር ግን ከሰውዬው ፍቅር ስለያዛት የመጨረሻ እድል ልትሰጠውና ከመንገዱ ልትመልሰው ወሰነች፡፡ እንዲህም አለችው፡፡
   “አረ አንተ ሰው የፈጠረህን ፍራ! ስለዚህ ካዝና ጉዳይ አንድም ጥያቄ ላትጠይቀኝ ቃል ኪዳን ሰጥተህኛል እኮ፤ እባክህ ይህንን ጥያቄህን ተውና በሰላም አብረን እንኑር”
“አንቺ ራስሽ እወድሃለሁ የምትይው ከልብሽ አይደለም፤ ያንን ካዝና ከፍተሸ ከውስጡ ያለውን ነገር ካላሳየሽኝ አትወጂኝም ማለት ነው”
“አረ አንተ ሰው መሀላ አታፍርስ! እረፍልኝ ብዬሃለሁ”
“የካዝናውን ቁልፍ እንድትሰጭኝ እፈልጋለሁ”

ሴትዮዋ ተናደደች፤ ነገር ግን ሰውዬውን ስለምትወደው በሽማግሌ ልታመስክረው ሞከረች፡፡ ሽማግሌዎችም “መሃላህን አትብላ! የፈጣሪ ቁጣ ይወርድብሃል፤ እንደ ድሮው በሰላም ብትኖሩ ይሻላል” አሉት፡፡ ሰውዬው ግን “ካዝናው ካልተከፈተ ሞቼ እገኛለሁ” በማለት ሙግቱን አፋፍሞ ቀጠለ፡፡ ሴትዮዋም በነገሩ ተስፋ ቆረጠች፡፡ ሰውዬው ወደ ኋላ የማይመለስ መሆኑን ካረጋገጠች በኋላ የከተማዋ ሽማግሌዎችና ታዋቂ ሰዎች እንዲሰበሰቡ አደረገች፡፡ ከዚያም ካዝናውን ከፈተችውና ከውስጡ ያለውን እቃ አወጣች፡፡ በሀይለ ቃልና በቁጭት በሰውዬው ፊት ላይ ወረወረችው፡፡
----------
ከካዝናው ውስጥ የተገኘው እቃ ሰውዬው ከሀገሩ የመጣበት ቡትቶ ልብስ እንጂ እንቁ ወይንም ሌላ የከበረ ጌጣጌጥ አልነበረም፡፡ ሴትዮዋ ለክፉ ቀን መጠባበቂያ እንዲሆናት ነው ከካዝና ውስጥ የቆለፈችበት፡፡ እውነተኛው ቀን ሲደርስ ልብሱን እዚያ ማስቀመጧ ትክክል እንደሆነ ተረዳች፡፡ ልብሱን በሰውዬው ፊት ላይ ከወረወረችለት በኋላም እንዲህ አለችው፡፡
“አንተ ውለታ ቢስ! ቶሎ ብለህ የኔን ልብስ አውልቅ! አንተ ያመጣኸውን ልብስ ልበስና ከዚህ ቤት ጥርግ ብለህ ጥፋልኝ”

ሰውዬው በድንጋጤ ክው ብሎ ቀረ፡፡ ከትቢያ ተነስቶ በተከበረበት ከተማ መዋረዱ ከፍተኛ እፍረት ውስጥ ጣለው፡፡ በመሆኑም ከከተማዋ በደረቅ ሌሊት ጠፋ፡፡ ወደ ሀገሩ ሊመለስም ጉዞውን ተያያዘው፡፡ ረጅም ርቀት ከተጓዘ በኋላ በቀቀኗን ካገኘበት ቦታ አረፈ፡፡

  ታዲያ በቀቀኗ “ጥጋብ አይቻልም” እያለች የድሮውን መዝሙር መዘመሯን እንደቀጠለች ነው፡፡ ሰውዬውም “እውነትሽን ነው! ጥጋብን ከእግር እስከ ራሱ አይቼው የማልችለው ዐይነት ሲሆንብኝ ወደ ድሮው የድህነት ህይወቴ እየተመለስኩ ነው” አላትና የመዝሙሩን ሐቀኛነት አረጋገጠላት፡፡
-----------
አይጣል ነው መቼስ! በርግጥም ጥጋብ አይቻልም፡፡ በእውነታው ዓለም የተከሰቱ በርካታ ታሪኮችን ከዚህ ጋር ማነጻጻር ይቻላል፡፡ ሀብትን ስናገኝ  አዕምሮአችን ከርሱ ጋር ካላደገ የሰራነው ሁሉ ወደ ዜሮ ሊመልስብን ይችላል፡፡ ለሁሉም ግን ፈጣሪያችን ከእንዲህ ዓይነቱ ክፉ እጣ ይሰውረን!
አሚን!
------
መጋቢት 19/ 2006
አፈንዲ ሙተቂ

(ተረቱን ያጫወቱኝ የገለምሶ ትልቁ መስጊድ ኢማም የሆኑት ሼኽ ሙኽታር አሊይ ናቸው፤ ዘመኑም እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር 1988 ነበር፤ ሼኽ ሙኽታር በአሁኑ ጊዜ የ85 ዓመት አዛውንት ናቸው፤ አላህ ጤናውንና ብርታቱን ይጨምርላቸው)፡፡

Thursday, October 30, 2014

ሁለት የሀረር ተረቶች



 ጸሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ
-----
“ሀረር ጌይ” በተሰኘው መጽሐፌ ውስጥ “ሀረር የባግዳድ እህት ናት” የሚል የረጅም ጊዜ ልማድ እንዳለ አጫውአችኋለሁ፡፡ ይህም አመለካከት የመጣው ሁለቱ ከተሞች የሚመሳሰሉ በመሆናቸው ነው፡፡ ከተሞቹን ከሚያመሳስሏቸው የህይወት ዘርፎች መካከል አንዱ እምቅ የስነ-ቃል ሀብታቸው ነው፡፡ ከነዚህ የስነ-ቃል ሀብቶች ቀዳሚ ሆኖ የሚጠቀሰው ተረት ነው፡፡ የባግዳድ ተረቶችን በ“አንድ ሺህ አንድ ሌሊት” በኩል አንብበናቸዋል፡፡ የሀረር ተረቶች ግን በመጽሐፍ ያልተሰበሰቡ በመሆናቸው ከብዙኃኑ አንባቢ ዘንድ ሊደርሱ አልቻሉም፡፡ ስለዚህ እነርሱንም በመጽሐፍ የሚሰበስብ የብዕር ጀግና ያስፈልገናል፡፡

በዚህ ጽሑፍ ሁለት የሀረር ተረቶችን አጋራችኋለሁ፡፡ ሁለቱንም ተረቶች በልጅነቴ የማውቃቸው ቢሆንም በሀረር ከተማ ቆይታዬ በአዲስ መልክ ሰምቼአቸዋለሁ፡፡  

የሓኪም ጋራ መሰንጠቅ

በጥንት ዘመን ሀረር በድርቅ ተመታች፡፡ በድርቁ ሳቢያም ምንጮቿና ወንዞቿ ደረቁ፡፡ አንድ “ኤላ” (የውሃ ጉድጓድ) ግን በተአምራዊ መንገድ ከመጥፋት ተረፈ፡፡ ይሁንና መገኛው ያልታወቀ ትልቅ ዘንዶ ከጉድጓዱ አፋፍ ተቀምጦ “ኤላው የኔ ነው” በማለቱ ከኤላው ውሃ መቅዳት አስቸጋሪ ሆነ፡፡ የሀረር ህዝብ ከኤላው ውሃ መቅዳት ከፈለገ በየዓመቱ አንዲት ቆንጆ ወጣት መገበር እንዳለበት ዘንዶው በአዋጅ አስታወቀ፡፡ የመጠጥ ውሃ ማግኘት የቸገረው የሀረር ህዝብም አማራጭ ሲያጣ ለዘንዶው በመገበር ከኤላው ውሃ ለመቅዳት ተገደደ፡፡

ለዘንዶው የምትሰጠው ልጅ በእጣ ነው የምትወሰነው፡፡ እጣው የሚወጣበት ሁኔታ ግን ፍትሐዊ አልነበረም፡፡ የሀብታምና የባለስልጣናት ልጆች በስውር ዘዴ ከእጣው ውጪ እንዲሆኑ ይደረግና የድሃ ልጆች ብቻ እየተመረጡ ለዘንዶው ይሰጣሉ፡፡ ድሆቹ ይህንን በደል ቢያውቁትም ከሀብታሞቹ ጋር መፎካከር ስለማይችሉ ልጆቻቸውን ለዘንዶው እየገበሩ እምባቸውን መርጨት ግዴታ ሆነባቸው፡፡

ታዲያ በአንድ ዓመት ልጅ የመገበሩ እጣ የደረሰው ለአንዲት “ተቂይ” (አላህን የምትፈራ) ሴት ነው፡፡ ያቺ ሴት አንዲት ልጅ ብቻ ነበራት፡፡ ልጅቷንም ያገኘችው በስተእርጅና ሲሆን ባለቤቷ ከልጅቷ መወለድ በኋላ ሞቶባታል፡፡ በመሆኑም ሴትዮዋ አንድዬ ልጇን እንደ እናትና እንደ አባት ሆና ነው ያሳደገቻት፡፡  እንግዲህ እነዚያ እጣ አውጪዎች ሴትዮዋ በስተእርጅና ያገኛትንና በድህነት ያሳደጋችትን ያቺኑ ልጅ ለዘንዶው እንድትገብር ነው የፈረዱት፡፡

   ይሁንና ሴትዮዋ ልጇን ለዘንዶው አላስረክብም አለች፡፡ የሰፈሯ ሰዎች “እምቢ ካልሽ እኮ ዘንዶው አንቺንም ጨምሮ ይበላሻል” እያሉ ቢያስፈራሯትም ሴትዮዋ ወይ ፍንክች በማለት በቃሏ ጸናች፡፡ ሰዎቹም “በቃ! ውርድ ከራሳችን!! ዘንዶው ቢበላሽ ተጠያቂ አይደለንም” በማለት ብቻዋን ተዋት፡፡ ወደ ዘንዶው ሄደውም ስለሴትዮዋ እምቢተኝነት ነገሩት፡፡ ከዚያም በየቤታቸው ሆነው ተከታዩን ነገር መጠባበቅ ጀመሩ፡፡ ሴትዮዋም ልጇን ከምታስረክብበት ዕለት በፊት ባለው ምሽት የዘንዶውን ጭካኔና የእጣ አውጪዎቹን አሻጥር እያነሳች ፈጣሪዋን ስትለምን አደረች፡፡ በማግስቱም ከቤቷ ቁጭ ብላ ዘንዶው የሚያመጣውን መቅሰፍት መጠባበቅ ጀመረች፡፡

 ሴትዮዋ ልጇን የምታስረክበው ከጧቱ በሶስት ሰዓት ገደማ የነበረ ቢሆንም ዘንዶው በሰዓቱ ግብሩን አላገኘም፡፡ በዚህም የተናደደው ዘንዶ ሴትዮዋን ከነልጅቷ ሊውጣት እጅግ በሚያስፈራ ግርማ ወደ ቤቷ መጓዝ ጀመረ፡፡ የሰፈሩ ሰዎችም “ሊበላት ነው፤ ሴትዮዋ አለቀላት!” እያሉ በአድናቆትና በተመስጦ ትርዒቱን ይመለከቱ ገቡ፡፡

ዘንዶው አቧራውን እያቦነነ ከሴትዮዋ ቤት አጠገብ ደረሰ፡፡ ሴትዮዋንም ሊውጣት መንደርደር ጀመረ፡፡ ፍላጎቱን ከመፈጸሙ በፊት ግን ፈጣሪ ውጥኑን አከሸፈበት!! እጅግ ግዙፍ የሆነ ንስር (አሞራ) ከሀረር በስተሰሜን አቅጣጫ በመምጣት ዘንዶውን ከመሬት ላይ “ላጥ” አድርጎ አነሳው፡፡ ንስሩ ዘንዶውን ወደ ሰማይ በማውጣት ላይ ሳለም የዘንዶው ጭራ ሀረርን በደቡብ በኩል የከበበውን የሀኪም ጋራን በሁለት ቦታ ከፈለው፡፡
 
  ያ ከይሲ ዘንዶ ፈጣሪዋን የምትፈራው ሴትዮ ባደረገችው ጸሎት ተወገደ፡፡ በሀረር ከተማ ላይ የተጣለው ልጅን የመገበር ግዴታም ለዘልዓለሙ ተነሳ!! ይሁንና ያኔ በዘንዶው ጭራ የተከፈሉት ሁለቱ የሐኪም ጋራ ኮረብቶች በአንድ ላይ ሳይመለሱ እስከዚህ ዘመን ድረስ ዘለቁ፡፡

አሚር ሆይ! አንተ “ኸይሩ”ን ብቻ አስብ፤ “ለሸሩ” ባለቤት አለውና!!
------
በጥንት ዘመን አንድ ቅን ሰውዬ በሀረር ከተማ ይኖር ነበር፡፡ ይህ ሰው ሁለት ልጆች ነበሩት፡፡ የመጀመሪያው ልጁ ርህሩህና የዋህ የነበረ ሲሆን ሁለተኛው ልጁ ግን ተንኮል እየፈጠረ ሰዎችን ማሞኘትና መሳቅ ይወድ ነበረ፡፡ አባትዬው ትንሹን ልጅ ቢመክረው አልሰማ እያለ አስቸገረው፡፡ ስለዚህ በትንሹ ልጅ ተስፋ የቆረጠው አባት ዘወትር ትልቁን ልጅ እየጠራው “ልጄ ሆይ! አንተ ደጉን ብቻ አስብ፡፡ ለተንኮል ባለቤት አለውና” የሚል ምክር ይሰጠው ነበር፡፡ አባት በዚህም ሳያበቃ ለትልቁ ልጅ “ዓሊ ኸይሮ” (ቅን አሳቢው ዓሊ) የሚል ቅጽል አወጣለት፡፡ ትንሽየውን ግን “ዓሊ ሸርሮ” (ተንኮለኛው ዓሊ) በማለት ሰየመው፡፡
 
   ከጊዜ በኋላ አባት የአዱኛውን ዓለም ተሰናበተ፡፡ በዚህም የተነሳ ልጆቹ ተቸገሩ፡፡ ኑሮ በጣም ከበዳቸው፡፡ በመሆኑም ወደ ሀረሩ አሚር ሄደው በችግር መቆራመዳቸውን ነገሩት፡፡ አሚሩ በአጋጣሚ የቤተ መንግሥት ከብቶችን የሚጠብቅ ሰው ይፈልግ ነበርና ወንድማማቾቹ ለእረኝነት እንዲቀጠሩ ጠየቃቸው፡፡ ወንድማማቾቹ ለስራው የሚሰጣቸውን ምንዳ ሲጠይቁት ከሚበሉት ምግብና ከሚለብሱት ልብስ በተጨማሪ በዓመቱ መጨረሻ ላይ አንዲት ጊደር እንደሚያገኙ አሳወቃቸው፡፡ ወንድማማቾቹም ከአሚሩ የቀረበላቸውን ጥያቄ በደስታ ተቀበሉትና ስራቸውን ጀመሩ፡፡

ወንድማማቾቹ በመቶዎች የሚቆጠሩትን የአሚሩን ከብቶች “አው-ሓኪም”፣ “አቦከር” እና “ሸድዳ ዋ መድዳ” ወደሚባሉት ተራሮች እያሰማሩ በትጋት ማገዱን ተያያዙት፡፡ ስራቸውን በደህና ሁኔታ እያከናወኑ ዓመቱን አገባደዱት፡፡ የዓመቱ መጨረሻ እየተቃረበ ሲመጣ ግን የ“አሊ ሸርሮ” ልብ በግለኝነት መመታት ጀመረች፡፡ ለምንዳ የምትሰጣቸውን ጊደር ጉዳይ ሲያስብ አዕምሮው በስስት ተወጠረ፡፡ በመሆኑም “ወንድሜን ገድዬው ጊደሪቱን የግሌ ማድረግ አለብኝ” በማለት ወሰነ፡፡ እቅዱንም በአው ሓኪም ተራራ ላይ ለመፈጸም ቆረጠ፡፡

ወንድማማቾቹ ከብቶቹን ወደ “ሓኪም” ተራራ በወሰዱበት በአንደኛው ቀን “አሊ ሸርሮ” ለወንድሙ “አንተ ከዚህ ሆነህ ከብቶቹን ጠብቅ፤ እኔ ተራራው ላይ ወጥቼ ለምለም ሳር እንዳለ ልይና ልመስ” አለው፡፡ “አሊ ኸይሮ”ም በቀረበለት ሃሳብ ተስማምቶ ከብቶቹን ለብቻው መጠበቅ ጀመረ፡፡ “አሊ ሸርሮ” ከተራራው ላይ እንደ ወጣ ትልቅ ድንጋይ አንቀሳቅሶ ወንድሙ ወዳለበት አቅጣጫ ቁልቁል ለቀቀው፡፡ ድንጋዩ ከተራራው ላይ እየተንከባለለ ወረደ፡፡ ከ“አሊ ኸይሮ” አጠገብ ሲደርስ ግን ወደ ወርቅነት ተቀየረ፡፡ “አሊ ኸይሮ” በዚህ ተአምር ተገረመ፡፡ “ወደ ወርቅነት የተቀየረው ድንጋይ እኔና ወንድሜ ሀብታም እንድንሆን ዘንድ ከአላህ የተሰጠን ነው” በማለት በደስታ ፈጣሪውን አመሰገነ፡፡ የተፈጠረውንም ተአምር ለወንድሙ ለመንገር በጉጉት ይጠባበቅ ጀመር፡፡
 
 “አሊ ሸርሮ” በበኩሉ “አሊ ኸይሮ በድንጋይ በመገደሉ “ጊደሪቱ የኔ ብቸኛ ሀብት ትሆናለች” እያለ በደስታ ከተራራው ወረደ፡፡ ወንድሙ ወደነበረበት ቦታ ሲደርስ ግን ያልጠበቀውን ነገር አየ፡፡ “ይህ ወርቅ ከየት ነው የመጣው?” በማለትም ወንድሙን ጠየቀው፡፡ አሊ ኸይሮም “አንድ ትልቅ ድንጋይ ከተራራው ላይ እየተንከባለለ መጥቶ እኔ ጋ ሲደርስ ይህንን ወርቅ ሆነ” በማለት መለሰለት፡፡ “አሊ ሸርሮም “ድንጋዩ የተንከባለለው ከስሩ የነበረውን ለምለም ሳር ለማየት ብዬ ስላንቀሳቀስኩት ነው፤ እዚህ ደርሶ ወደ ወርቅ ከተቀየረ እኔም የራሴ ወርቅ ሊኖረኝ ይገባል፡፡ ስለዚህ አንተም በተራህ ወደ ተራራው ውጣና ሌላ ድንጋይ አንከባልልኝ” አለው፡፡

“አሊ ኸይሮ”ም ከወንድሙ የሰማውን ሳይጠራጠር ወደ ተራራው ወጥቶ ትልቅ ድንጋይ አነሳና “አሊ ሸርሮ” ወደነበረበት አቅጣጫ አንከባለለው፡፡ ይሁንና ድንጋዩ ወደ ወርቅነት ሳይቀየር “አሊ ሸርሮ”ን ጭፍልቅ አድርጎ ገደለው፡፡ “አሊ ኸይሮ” ከተራራው ወርዶ ወንድሙ ወደነበረበት ስፍራ ሲሄድ ወንድሙ ሞቶ አገኘው፡፡ በዚህም በጣም ደነገጠ፡፡ ወደ ሀረሩ አሚር ሄዶም የተከሰተውን ሁሉ አንድ በአንድ ነገረው፡፡ ሆኖም አሚሩ ሊያምነው አልቻለም፡፡ “ወንድምህን ራስህ ነህ የገደልከው” በማለትም ከሰሰው፡፡ በመሆኑም “ነፍስ ያጠፋ ሰው ይገደል” በሚለው የሀረር ከተማ ጥንታዊ ህግ መሰረት በድንጋይ ተጨፍልቆ እንዲሞት ተፈረደበት፡፡
 
“አሊ ኸይሮ”ም ፍርዱ ሊፈጸምበት ወደ “ሐኪም” ተራራ ግርጌ ተወሰደ፡፡ ከተራራው ላይ ትልቅ ድንጋይ ተንዶ ቁልቁል ተወረወረበት፡፡ ይሁንና ድንጋዩ “አሊ ኸይሮ” አጠገብ ሲደርስ እንደገና ወርቅ ሆኖ ቁጭ አለ፡፡ የቅጣቱን አፈጻጻም ለማየት በስፍራው ተሰብስቦ የነበረው የሀረር ህዝብም በተፈጠረው ነገር በጣም ተገረመ፡፡ “ይህ ተአምር ልጁ ወንድሙን እንዳልገደለ በሐቅ ይመሰክራል” በማለትም ደመደመ፡፡ የሀረሩ አሚር በበኩሉ “የዓሊ ኸይሮ”ን ተአምር ሲያይ “በህይወቴ ስፈልገው የነበረውን ሐቀኛ ሰው ዛሬ አገኘሁት” የሚል ቃል ተናገረ፡፡ “አሊ ኸይሮ”ንም የዙፋኑ ወራሽ በማድረግ ሾመው፡፡
-----
ወደ ሀረር ከተማ ከመጣችሁ “Amiroo! Kheyruma yaadi, Sharriin abbuma eeydii” የሚል አባባል ትሰማላችሁ፡፡ “አሚር ሆይ! አንተ ኸይሩን ብቻ አስብ፤ ለሸርሩ ባለቤት አለውና” እንደማለት ነው፡፡ ከአባባሉ ጀርባ ብዙ ታሪኮች ይነገራሉ፡፡ ከነዚያ ታሪኮች መካከል አንዱ ከላይ የቀረበው ተረት ነው፡፡

 በተረቱ እንደተገለጸው ተንኮለኛ ሰው በለስ የቀናው መስሎት ብዙ የሸር ትብታቦችን ሊተበትብ ይችላል፡፡ ይሁንና እንደዚህ ዓይነቱ ሰው አጓጉል ሆኖ ነው የሚቀረው፡፡ የማታ ማታ ራሱ በሸረበው የተንኮል ድር መታሰሩ የማይቀር ነው፡፡ ስለዚህ በህይወት እያለ ደግ ደጉን ብቻ አስብ!! ለተንኮሉ ባለቤት አለውና!!
በድጋሚ Amiroo kheyruma yaadi, Sharriin abuma eeydi ብለናል፡፡
----
አፈንዲ ሙተቂ
ጥቅምት 20/2007
-----
The writer, Afendi Muteki, is a researcher and author of the ethnography and history of the peoples of East Ethiopia.  You may like his facebook page and stay in touch with his articles and analysis: Just click the following link to go to his page.


አፈንዲ ሙተቂ
ጥቅምት 8/2007
ሀረር-ምስራቅ ኢትዮጵያ