Monday, December 29, 2014

አለቃ ገብረሃና ማን ናቸው?



(አፈንዲ ሙተቂ)
----
     ጎንደር ካፈራቻቸው ሰዎች መካከል አብዛኛው ኢትዮጵያዊ የሚያውቀው እኝህ ሰው ይመስሉኛል፡፡ እኔ ጸሐፊው ስለርሳቸው የሰማሁት የቋራው መይሳው ካሳን ከማወቄ በፊት እንደሆነ አስታውሳለሁ፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ በአለቃ ገብረሃና ስም የሚነገሩ ቀልዶችን የነገረን ደግሞ ማን መሰላችሁ….? ከዚህ በፊት ያስተዋወቅኳችሁ የሁለተኛ ክፍል አለቃችን የነበረው አያሌው አብነት  ነው፡፡ ሆኖም እርሱ ያኔ የነገረንን እዚህ መጻፍ አይመችም፡፡ ስለዚህ የአያሌውን ቀልዶች ትተን ስለአለቃ ገብረሃና ከመዛግብት ያገኛቸውን ወጎች እንጨዋወታለን፡፡ ከዚያ በፊት ግን “ዐረፈ ዐይኔ ሐጎስ” “አለቃ ገብረሃ እና አስቂኝ ቀልዶቻቸው” በሚል ርዕስ ካሳተሙት መጽሐፍ ያገኘነውን የአለቃ ገብረሃናን ታሪክ አጠር አድርገን እናወሳለን፡፡
  
አለቃ ገብረሃና በሙሉ ስማቸው “ገብረሃና ደስታ ተገኝ” ይባላሉ፡፡ የተወለዱት በ1814 በጎንደር ክፍለ ሀገር በደብ ታቦር አውራጃ ፎገራ ወረዳ (አሁን ደቡብ ጎንደር ዞን ፎገራ ወረዳ) ውስጥ ነው፡፡ በተወለዱበት አካባቢ የቤተ ክህነት ትምህርት ተምረው በሃያ ስድስት ዓመታቸው የሊቀ-ካህናት ማዕረግ አግኝተዋል፡፡ በዚህ ሹመት ለሰባት ዓመታት ካገለገሉ በኋላ በፍትሐ ነገሥት አዋቂነታቸው ተመርጠው ጎንደር ውስጥ በዳኝነት ተሾሙ፡፡

  አለቃ በካህንነትም ሆነ በዳኝነት ሲያገለግሉ እንደ ሌሎች የዘመኑ መኳንንት ቁጥብ አልነበሩም፡፡ ከተራው ህዝብም ሆነ ከመንግሥት ባለስልጣናት ጋር ይቃለዱ ነበር፡፡ ይህ ቀልደኝነታቸው እየገነነ ሄዶ በትንሹ ራስ ዓሊ ዘንድ ተሰማላቸው፡፡ በመሆኑም ወደ ቤተ መንግሥት ተጠርተው የራስ ዓሊ አጫዋች በመሆን ተሰየሙ፡፡ እንግዲህ ከዚህን ጊዜ ጀምሮ ነው አለቃ ገብረሃና የመኳንንቱና የመሳፍንቱ አጫዋች በመሆን ህይወታቸውን የገፉት፡፡
 
   አለቃ ገብረሃና በአጼ ዮሐንስም ሆነ በአጼ ምኒልክ ዘንድ ክብርና ሞገሥ አግኝተው እንደ ታላቅ ሰው ይታዩ ነበር፡፡ በአጼ ቴዎድሮስ ዘመን ግን ከፍተኛ ችግር ደርሶባቸው ነበር፡፡ ቴዎድሮስ አለቃን ያገኟቸው በቤተ መንግሥቱን ከራስ ዓሊ በተረከቡ ጊዜ ነው፡፡ ቴዎድሮስ አለቃን በዝና ቢያውቋቸውም ቀልድና ባልቱን አልወደዱላቸውም፡፡ ቴዎድሮስ ቀልዱን እንዲያቆሙና በዳኝነቱ እንዲቀጥሉ ቢገስጿቸውም አለቃ በጄ የሚሉ አልሆኑም፡፡ በመሆኑም አለቃን ከዳኝነታቸው ሽረው ትግራይ ውስጥ የሚገኘው የጨለቆት ሥላሤ ገዳም አስተዳዳሪ አድርገው ሾሟቸው፡፡ 
  
የደብሩ ቆይታ የቤተ መንግሥት ኑሮ ለለመዱት አለቃ ገብረሃና የሚመች አልሆነም፡፡ በዚያ ላይ አጼ ቴዎድሮስ ቤተ ክህነትን ርስት አልባ ለማድረግ መሞከራቸው ከሀገሬው ህዝብ ጋር አጣላቸው፡፡ በመሆኑም ካህናቱ ቴዎድሮስን ለመገልበጥ ማሴር ጀመሩ፡፡ አለቃ ገብረሃናም ዱለታውን ተቀላቀሉ፡፡ ይህም ወሬ ለአጼ ቴዎድሮስ ደረሳቸው፡፡ አጼውም አለቃ ገብረሃና ታስረው እንዲቀርቡ አዘዙ፡፡ ሆኖም አለቃ ገብረሃና ሸሽተው ጎጃም ውስጥ ከሚገኘው ዘጌ ገዳም ተደበቁ፡፡

   ከሁለት ዓመት በኋላ አጼ ቴዎድሮስ በመቅደላው ጦርነት ራሳቸውን ገደሉ፡፡ አለቃ ገብረሃናም ከተደበቁበት ወጥተው ወደ ጎንደር ተመለሱ፡፡ በ1864 አጼ ዮሐንስ አራተኛ ሲነግሡ በጎንደር ከተማ የነበራቸውን የቀድሞ ሹመታቸውን አጸደቁላቸው፡፡ በምኒልክ ጊዜ ደግሞ ወደ አዲስ አበባ መጥተው በእንጦጦ ራጉኤል ቤተ ክርስቲያን የአቋቋም እና የመርገድ አስተማሪ ሆኑ፡፡ ከጥቂት ቆይታ በኋላም የቤተ ክርስቲያኑ አስተዳዳሪ ሆኑ፡፡

  አለቃ ገብረሃና በአዲስ አበባ ኑሮአቸው ከአጼ ምኒልክ ጋር ተዋድደው ይኖሩ ነበር፡፡ ነገር ግን እቴጌ ጣይቱ ቀልዳቸውንና ተረባቸውን አልወደዱላቸውም፡፡ በዚህም የተነሳ ሁለት ጊዜ ተጣልተው ወደ ደብረ ታቦር ሄደዋል፡፡ በሶስተኛው ዙር ግን ከአጼ ምኒልክም ጋራ ተቀያይመው ኖሮ እስከ መጨረሻው ተሰነባብተው ወደ ትውልድ ቄየአቸው ከሄዱ በኋላ እዚያው ኖረው በሰማኒያ አራት ዓመታቸው አርፈዋል፡፡

  አለቃ ገብረሃና መልከ መልካም ቢሆኑም አጭር ሰው ነበሩ፡፡ በዚህ ቁመታቸውም ከሌሎች ጋራ ብዙ ጊዜ ተቋስለዋል፡፡ አንዳንዶች ደግሞ በእግራቸው መንሻፈፍ ሊቀልዱ ሲሞክሩ አለቃ ያልጠበቋቸውን መልሶች እየሰጧቸው “ኩም” ያደርጓቸው ነበር፡፡

   አለቃ ወይዘሮ ማዘንጊያ ከተባሉት ባለቤታቸው ተክሌ የተባለ ልጅ ወልደው ነበር፡፡ ይህ ልጃቸው በትምህርት ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሶ የደብረ ታቦር እየሱስ ጉባኤ ቤተ ክርስቲያን ካህን እስከ መሆን ደርሷል፡፡ ሆኖም ጠላቶቹ ተመቀኝተውት መድኃኒት በጥበጠው በማጠጣት ገድለውታል፡፡
   *****
    በአለቃ ገብረሃና ስም የሚነገሩ ብዙ ጨዋታዎችና ቀልዶች አሉ፡፡ አንዳንዶቹ በርሳቸው የተነገሩ መሆናቸው የተጻፈ ቢሆንም አንዳንዶቹ በጊዜ ሂደት የተፈጠሩ ናቸው፡፡ ለበረካ ያህል በርሳቸው ስም የሚነገሩ ጥቂት ጨዋታዎችን እንቋደስ፡፡

   አንድ ጊዜ አለቃ ለግብዣ ተጠሩ፡፡ በግብዣው የቀረበው ጎመን ሆዳቸውን ቆዝሮአቸው ኖሮ ወደ እሳት ዳር ተጠጉና ሆዳቸውን ማሻሸት ጀመሩ፡፡ ጋባዣቸው ነገሩ ገርሞት “ምነው አለቃ! ሆድዎትን ምን ሆነው ነው” ሲላቸው “ረ ምንም አይደለም! ጎመኑን እያበሰልኩት ነው” በማለት መለሱላቸው፡፡

  በሌላ ጊዜ ደግሞ አለቃ የታመመ ሰው ሊጠይቁ ይሄዳሉ፡፡ የቤቱ ባለቤት ጠላ ትሰጣቸውና ታቀርብላቸዋል፡፡ አለቃ ጠላውን ፉት እያሉት ሳሉ ሴትዮዋ አመለጣት፡፡ አለቃ ጠላቸውን አገባደው ሲጨርሱ ሴትዮዋ ወደርሳቸው መጣችና “ልድገምዎት እንዴ አለቃ” በማለት ጠየቃቸው፡፡ አለቃም “አዎ! ግን እንደ ቅድሙ ጠረር አታድርጊው” አሏት፡፡

    አለቃ ስንቃቸውን በአገልግል ይዘው ከጥቂት ነጋዴዎች ጋር የዐባይ በረሃን በማቋረጥ ላይ ሳሉ ሽፍቶች በአካባቢው እንዳሉ ይሰማሉ፡፡ ነጋዴዎቹም ለገንዘባቸው አለቃም ለነፍሳቸው ተጨነቁ፡፡ “ምን እናድርግ” እያሉ በመመካከር ላይ ሳሉ አለቃ አንድ ዘዴ ትዝ ይላቸውና ነጋዴዎቹ ገንዘባቸውን እንዲሰጧቸው ይጠይቁአቸዋል፡፡ ነጋዴዎቹም የተጠየቁትን አደረጉ፡፡ አለቃም ገንዘቡን ከአገልግላቸው ውስጥ ከተቱት፡፡

    ጥቂት እንደተጓዙ ሽፍቶቹ ከጫካ ውስጥ ወጥተው “ያላችሁን ቁጭ አድርጉ” ይሏቸዋል፡፡ ነጋዴዎቹ ምንም የለንም ይላሉ፡፡ ሽፍቶቹ ወደ አለቃ ዞረው “በአገልግሉ ውስጥ ያለው ምንድነው” ብለው ጠየቋቸው፡፡ ብልሃተኛው አለቃ “ወላሂ! ወላሂ! ክሽን ያለች የዶሮ ወጥ ናት! ከፈለጋችሁ እዚሁ እንብላ” ብለው መለሱ፡፡ ሽፍቶቹም “በስመ አብ! እኛ የእስላም ስጋ አንበላም” እያሉ በማማተብ ለቀቋቸው፡፡
------
አፈንዲ ሙተቂ)
ታሕሳስ 2007

No comments:

Post a Comment