Wednesday, December 10, 2014

ጥቂት ቆይታ- ከአል-በላቢል ጋር




ፀሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ
-----
ብዙዎቻችን በስርቅርቅ ድምጻቸው እናውቃቸዋለን፡፡ እጅግ በተዋጣለት የኦርኬስትራ ቅንብር በመታጀብ የተጫወቷቸው ጥዑም ዜማዎች  በአዕምሮአችን ላይ ተቀርጸዋል፡፡ እኔ ጸሐፊው ሙዚቃቸውን ለመጀመሪያ ጊዜ የሰማሁበትን አጋጣሚ አላስታውስም፡፡ ሆኖም የነርሱን ዘፈን በምሰማበት ጊዜ ሁሉ ሶስት ነገሮች ይታወሱኛል፡፡


   የመጀመሪያው ከተማችንን (ገለምሶን) ለሁለት ከፍሎ የሚያልፈውን አውራ ጎዳና ተከትለው ከተደረደሩት ሻይ ቤቶች ይንቆርቆር የነበረው የእንስቶቹ ዝማሬ ነው፡፡ በተለይም የሻይ ቤቶቹ ባለቤቶች በበርካታ የህብረተሰብ ክፍል እንደ ህብረ-ዜማ ይዘፈን የነበረውን “መሼና መሼና”ን እየደጋገሙ ማጫወታቸው የየዕለቱ ትዕይንት ሆኖ እንደቆየ አስታውሳለሁ፡፡ ሁለተኛው አይረሴ አጋጣሚ የተከሰተው በትምህርት ቤት ቆይታዬ ነው፡፡ በ1980 የአምስተኛ ክፍል ተማሪ እያለሁ ከለገዳዲ ሬድዮ ጣቢያ የሚተላለፈውን “የህብረተሰብ ትምህርት በሬድዮ” ለማዳመጥ በሄድንበት አንድ ጠዋት “ተማሪዎች፤ የኢትዮጵያ ጎረቤት የሆነችውን ሱዳንን ታውቋታላችሁ?” በሚል ርዕስ የተዘጋጀ ትምህርት ተሰጠን፡፡ የሬድዮ ትምህርቱን የሚያቀርበው ባለሙያ “ሱዳን፣ በአፍሪቃ ትልቅ ሀገር ናት፤ ስፋቷ ወደ አንድ ሚሊዮን ስኩዌር ማይልስ ይጠጋል፤ ዋና ከተማዋ ካርቱም ነው” እያለ በሚያስተምርበት ጊዜ በየአፍታው እንደመሸጋገሪያ አድርጎ የተጠቀመው እንስቶቹ “ለውነል መንጋ” እያሉ የሚያዜሙትን ተወዳጅ ዘፈን ነበር፡፡ ያንን ዘፈን ለመጀመሪያ ጊዜ የሰማሁት በዚያች ዕለት ነው፤ ከዚያ በኋላ ከጭንቅላቴ ላወጣው አልቻልኩም፡፡

  ሶስተኛው አጋጣሚ በ1984 በአንዲት የማክሰኞ ምሽት ነው የተከሰተው፡፡ በዕለተ ማክሰኞ ሲገበያይ የሚውለው የከተማችን ህዝብ የቀኑን ድካም ለማራገፍ ሲል ምሽት ላይ እራቱን ከበላ በኋላ ሆጃና ሻይ አፍልቶ ለበርጫ መሰየሙ የተለመደ ነገር ነው፡፡ እኔም በዚያች የማክሰኞ ምሽት አብዱልቃዲር ከተባለ ዘመዳችን ሱቅ ሄድኩና ከጥቂት ጓደኞቹ ጋር በርጫውን ሲያስኬድ አኘሁት፡፡ አብዱልቃዲር ለበርጫው ማሟሟቂያ የመረጠው የእንስቶቹን ተወዳጅ ካሴት ነው፡፡ በተለይም ደግሞ “ኡሸ ሰጊራ፣ ኪፋያ ዐለይና” የተሰኘውን ዘፈን ይደጋግመው ነበር፡፡ እኔም የአብዱልቃዲር ሁናቴ አስገርሞኝ ስለእንስቶቹ እንዲያጫውተኝ ጠየቅኩት፡፡ እርሱም የዘፋኞቹን ማንነትና የሙዚቃ ጉዞአቸውን እያዳነቀ ተረከልኝ፡፡ እንግዲህ በዚያች አጋጣሚ ነው ስማቸውን ለመያዝ የበቃሁት፡፡
*****
አዎን! የኢትዮጵያን ሙዚቃ አውቃለሁ የሚል ሰው ሶስቱን የሱዳን ድምጻዊያን በደንብ ነው የሚያውቃቸው፡፡ እነዚህ እንስቶች እህትማማቾች ናቸው፡፡ ትክክለኛ ስማቸውም “ሐያት”፣ “አመል” እና “ሃዲያ” ነው፡፡ በዓለም ዙሪያ በደንብ የሚታወቁት ግን “አል-በላቢል” በተሰኘው የቡድን ስማቸው ነው (በዐረብኛ “አል-ባቢል” ሲባል “ዘማሪ ወፎች” እንደማለት ነው)፡፡ በምስራቅ አፍሪቃ የሙዚቃ ታሪክ የነርሱን ያህል የሚታወቅ የሴት ድምጻዊያን ቡድን የለም፡፡

“አል-በላቢል” በሰሜን ሱዳን በዋዲ-ሃልፋ ከተማ ነው የተወለዱት ነው፡፡ የአፍ-መፍቻ ቋንቋቸው “ኑቢያ” ነው፡፡ ሙዚቃን በዋዲ ሃልፋ ቢጀምሩትም ከእውቅና ማማ ላይ የወጡት ግን በካርቱም ከተማ ነው፡፡ በተለይም እንስቶቹ እ.ኤ.አ ከ1974-እስከ 1982 በነበረው ዘመን በሱዳን ሙዚቃ ላይ ነግሰው ነበር፡፡ በዚያ ዘመን ያወጧቸው “መሼና”፣ “ሙትዓሉ ዐለይና”፣ “ሸባብ አንኒል”፣ “ዑሸ ሰጊራ”፤ “ለውነል መንጋ”፣ “ሒልዊን ሐለዋ”፣ “ጣኢረል ጀንና” የመሳሰሉት ዘፈኖቻቸው ዘመን ተሻግረው እስከ ዛሬም ድረስ ይደመጣሉ፡፡

  የአል-በላቢል አዕዋፋት ዝና በምድረ-ሱዳን ብቻ አልታቀበም፡፡ ከካይሮ እስከ ሞምባሳ፣ ከበርበራ እስከ ባማኮ (ማሊ) ባሉት የአፍሪቃ ከተሞች የሚኖሩ የሙዚቃ አፍቃሪዎች በስራቸው ተማርከውላቸዋል፡፡ በኢትዮጵያ፣ በግብጽ፣ በሶማሊያ፣ በጅቡቲ፣ በቻድ፣ በኬንያ፣ በናይጄሪያ፣ በአልጄሪያ፣ በማሊና በሌሎችም የአፍሪቃ ሀገራት ሙዚቃዎቻቸውን አቅርበዋል፡፡ በመካከለኛው ምስራቅ፣ በአውሮጳና በአሜሪካም ተዟዙረዋል፡፡
*****
ሆኖም ሶስቱ እንስት ከ1986 በኋላ የሙዚቃ ስራቸውን በአንድ ላይ ለመቀጠል አልቻሉም፡፡ ትልቋ “ሐያት” እና ሁለተኛዋ ሃዲያ በጋብቻ ምክንያት ሱዳንን በመልቀቃቸው ብዙዎች ያደነቁላቸው የቡድን ስራቸው በመንገድ ላይ ቀረ (ሐያት በአሜሪካ፣ ሐዲያ ደግሞ በባህሬን ይኖሩ ነበር)፡፡ ሆኖም የሱዳን ህዝብ እንዲሁ አልተዋቸውም፡፡ እንስቶቹ በአንድ ላይ ተሰባስበው ስራቸውን እንዲሰሩ በልዩ ልዩ መንገድ ጫና ሲያደርግባቸው ነበር፡፡ እነርሱም ለህዝቡ ውዴታ በመሸነፋቸው በድጋሚ በመሰባሰብ የሙዚቃ ስራቸውን ማቅረብ ጀምረዋል፡፡

    ታዲያ አል-በላቢል በድጋሚ የቡድን ስራቸውን በጀመሩበት የአውሮጳዊያኑ 1998 አጋማሽ ላይ የለቀቁት “ኩልለ-ኑጁም” የተሰኘው አልበም በዓለም ዙሪያ በእልፍ አዕላፍ ቅጂዎች ነው የተሸጠው፡፡ የሱዳን የሙዚቃ ኤክስፐርቶች በዚያ አልበም የተካተቱትን ስራዎች ከሀገሪቱ የምንጊዜም ተወዳጅ ዜማዎች መካከል ደምረዋል፡፡ በተለይም የአልበሙ መጠሪያ የሆነው “ኩልላ-ኑጁም” የተባለው ዜማ ከሱዳን አልፎ በውጪው ዓለም (በጀርመን) ለሽልማት አብቅቶአቸዋል፡፡ የአውሮጳ ህብረት በበኩሉ ታህሳስ 11/ 2013 ባዘጋጀው ልዩ ዝግጅት እህትማማቾቹ ለሱዳን ሙዚቃ እድገት ላደረጉት አስተዋጽኦ ዓለም አቀፍ ሽልማት ሸልሞአቸዋል፡፡ እንስቶቹ የምታዩትን ፎቶግራፍ የተነሱት ሽልማቱን በተቀበሉበት ወቅት ነው፡፡
*****
አል-በላቢልን በሌላ ቀን እንዘይራቸዋለን፡፡ ለዛሬ ግን በኛ ሀገር በስፋት የሚታወቀውን “መሼና”ን እንገባበዝና እናብቃ፡፡
 መሼና መሼና መሼና
ቢጠሪቀል ሑብቢ መሼና
አዕዛቡ ያ ናር አልጊና
መሼና መሼና መሼና…
(እህትማማቾቹ መሼናን ሲዘፍኑ ለማየት የሚከተለውን ሊንክ ይክፈቱ)፡፡
-----
አፈንዲ ሙተቂ
ጥቅምት 4/2007
ገለምሶ-ምስራቅ ኢትዮጵያ
----
The writer, Afendi Muteki, is a researcher and author of the ethnography and history of the peoples of East Ethiopia.  You may like his facebook page and stay in touch with his articles and analysis: Just click the following link to go to his page.

No comments:

Post a Comment