Thursday, December 18, 2014

አምር ኢብን ኣስ እና “ፉስጣጥ” (ክፍል አንድ)




ጸሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ
-----
በፎቶው ላይ የምትመለከቱት ለአፍሪቃ አህጉር የመጀመሪያ የሆነውን መስጊድ ነው፡፡ ይህ መስጊድ የተሰራው በ641 ሲሆን የሚገኘውም በግብፅ መዲና ካይሮ ውስጥ ነው፡፡ መስጊዱ የሚጠራው በመስራቹ በ“አምር ኢብን ኣስ” ስም ነው፡፡ ይሁንና አምር እና ጓዶቹ መስጊዱን የሰሩት በአል-ፉስጣጥ እንጂ በካይሮ አልነበረም፡፡ ታዲያ መስጊዱን ወደ ካይሮ ማን ነው ያስገባው?… እስቲ የዛሬ ወጋችንን በአምር ታሪክ እንጀምርና ስለፉስጣጥም ትንሽ እናውራ፡፡
       *****
አምር ኢብን ኣስ የዐረቢያ ምድር ካበቀለቻቸው ታላላቅ ፖለቲከኞችና የጦር መሪዎች አንዱ ነው፡፡ የተወለደው በመካ ከተማ ሲሆን ነቢዩ ሙሐመድን (ሰ.ዐ.ወ) ያፈራው የቁረይሽ ጎሳ አባል ነው፡፡ አምር የጉርስምና ዘመኑን እንደ ሌሎቹ የዐረቢያ ወጣቶች በግመል ግልቢያና በፈረስ ጉግስ አላሳለፈም፡፡ የርሱ ቀልብ ወደ ንግዱ ነበር ያተኮረችው፡፡ በመሆኑም  በዘመኑ በገበያ ውስጥ ተፈላጊ የሆኑ ሸቀጦችን ለማምጣት ወደ የመንና ሻም (ሶሪያ) በብዛት ይመላለስ ነበር፡፡ ሀብቱ እየተስፋፋ ሲሄድ ደግሞ እስከ ፋርስ (ፐርሺያ)፣ መስር (ግብፅ)፣ አቢሲኒያ (ሐበሻ/ኢትዮጵያ) እና ኦማን ድረስ እየሄደ ሸቀጦችን ያመጣ ጀመር፡፡ በነዚህ ሀገራትም በርካታ የንግድ ሸሪኮችን ለመፍጠር ቻለ፡፡ በሸሪኮቹ በኩልም ከየሀገራቱ ገዥዎች ጋር በመተዋወቅ ልዩ ልዩ ገጸ-በረከቶችን ይወስድላቸው ነበር፡፡

Mosque of Amr in Old Cairo in 19th Century


ይህ በእንዲህ እንዳለ ነቢዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) በ610 ገደማ እስልምናን ማስተማር ጀመሩ፡፡ የዐረብ ጎሳዎች የድንቁርና ህይወታቸውን ትተው እንደ ጥንቱ ቅድመ-አያቶቻቸው እንደ ነቢዩ ኢብራሂምና እንደ ዒስማዒል ፈጣሪን ብቻ እንዲገዙ ሰበኩ፡፡ ጥቂት ሰዎች እምነቱን ተቀበሉ፡፡ አብዛኞቹ ግን “የአባቶቻችንን መንገድ ልታስተወን ነው እንዴ…?” በማለት በነቢዩ ላይ በጠላትነት ተነሱባቸው፡፡ በነቢዩ ያመኑትንም ያሰቃዩ ጀመር፡፡ ነቢዩ በተከታዮቻቸው ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ሊከላከሉላቸው አልቻሉም፡፡ ስለዚህ ከተከታዮቻቸው መካከል የተወሰኑትን በሚስጢር ጠርተው ወደ ሐበሻ (ኢትዮጵያ) እንዲሰደዱ አዘዟቸው፡፡ በዚሁ መሰረት አንድ መቶ የሚሆኑ ሰዎች ወደ ሐበሻ ተሰደዱ፡፡

የቁረይሽ ባላባቶች የነብዩ ተከታዮች ወደ ሐበሻ መሰደዳቸውን ሲሰሙ “እዚያ ሄደው ሳይደራጁ በቶሎ ልናስመልሳቸው ይገባል” በማለት አንድ የልዑካን ቡድን ወደ አክሱም ሰደዱ፡፡ ቡድኑ ሁለት አባላት የነበሩት ሲሆን እነርሱም አምር ቢን ኣስ እና አብዱላህ ቢን ረቢዓ ናቸው፡፡ ያ ቡድን በሚችለው መንገድ ሁሉ ተደራድሮ የሐበሻውን ንጉሥ አርማህን (አስሓማ) በማሳመን የነቢዩን ተከታዮች ወደ መካ እንዲያስመልስ ታዟል፡፡ ነገር ግን ወደ ሐበሻው ንጉሥ ቀርቦ ድርድሩን እንዲፈጽም ስልጣን የተሰጠው ለአምር ቢን ኣስ ነው (አብዱላህ ቢን ረቢዓ “አምር” መልዕክቱን በትክክል ማድረሱን እንዲታዘብ ብቻ የተላከ ነው የሚመስለው)፡፡

አምር በንግድ ሰበብ ወደ ኢትዮጵያ በተመላለሰባቸው ዓመታት ከሐበሻው ንጉሥ ጋር ለመተዋወቅ ችሏል፡፡ ሆኖም አምር ለድርድሩ የተመረጠው በዚህ ብቻ ሳይሆን በዘመኑ ከነበሩት የመካ መኳንንት መካከል ተናግሮ በማሳመን ብቃቱ የተዋጣለት ሆኖ በመገኘቱም ጭምር ነው፡፡
       *****
አምር ከንጉሡ ዘንድ ቀርቦ ባደረገው ድርድር ያሰበው አልተሳካለትም፡፡ ንጉሡ ስደተኞቹን ለማንም አሳልፎ እንደማይሰጥ እቅጩን ነግሮታል፡፡ ይሁንና አምር በዚህ ተበሳጭቶ ወደ አክሱም መምጣቱን አላቆመም፡፡ ከድርድሩ በኋላም ቢሆን ለሁለት ጊዜያት ወደ ሐበሻ መጥቷል፡፡ ታዲያ ለመጨረሻ ጊዜ ከንጉሡ ጋር በተገናኘበት ጊዜ ንጉሡ እንዲህ ሲል መከረው፡፡

  “አምር ሆይ! አንተን የመሰለ ሰው የነቢዩ ሙሐመድን ትምህርት አልቀበልም ሲል ይገርመኛል፡፡ እናንተ ዐረቦች ከማንኛውም ህዝብ ወደ ኋላ ቀርታችኋል፤ ሙሐመድ ያመጣው ዐረቢያን ከጭለማ የሚያወጣውን አዲስ ብስራት ነው፡፡ በእርሱ ያመነ ሰው በፈጣሪ ዘንድ ከሚያገኘው ምንዳ በተጨማሪ ይህችን ዓለም ይገዛል፡፡”

ንጉሥ አርማህ አምርን እንዲህ ብሎ በሚመክርበት ጊዜ ለራሱም የነቢዩን እምነት ተቀብሏል፡፡ ይሁንና መላው የሐበሻ ህዝብ አዲሱን እምነት እንዲቀበል አዋጅ አልነገረም (አንዳንድ ጸሐፊያን “ንጉሥ አርማህ በነቢዩ ማመኑን በሚስጢር ይዞት ነበር” ይላሉ)፡፡
       *****
አምር ከሐበሻው ንጉሥ ከተለየ በኋላ በቀጥታ ወደ መካ ነው ያመራው፡፡ እዚያም ታዋቂው ጀግና ኻሊድ ቢን ወሊድ (ረ.ዐ) ወደ መዲና ለመሰደድ ሲዘጋጅ አገኘውና ከርሱ ጋር መሄድ እንደሚፈልግ ነገረው፡፡ ኻሊድም ሀሳቡን በደስታ ተቀበለው፡፡ ሁለቱ ሰዎች መዲና በደረሱ ጊዜ ነብዩ ሁለቱንም ሸሃዳ አስያዟቸው፡፡ ይሁንና ነቢዩ እነዚህን የዐረቢያ ጎምቱዎች አላሳረፏቸውም፡፡ ኻሊድን በሰሜን በኩል በነቢዩ መንግሥት ላይ አደጋ የጋረጡትን ሮማዊያንን ለመዋጋት በሚዘምተው የዘይድ ቢን ሓሪሳ ቡድን ውስጥ ቀላቀሉት፡፡ አምር ቢን ኣስ ደግሞ ወደ ኡማንና ባህሬን ሄዶ የዲፕሎማሲ ስራ እንዲሰራ አደረጉት፡፡ አምር ወደ ኡማን (ኦማን) የተጓዘው እነ አቡበከር፣ ዑመር እና አቡ ኡበይዳን (ረ.ዐ) የመሳሰሉ ታላላቅ ሰዎች የተካተቱበትን ቡድን በመምራት ነው፡፡ ነቢዩ አምር የቡድኑ መሪ እንዲሆን ያደረጉት የዲፕሎማሲ ችሎታውን በሚገባ ያውቁት ስለነበረ ነው፡፡ አምርም የዲፕሎማሲ ስራውን በደንብ ከመፈጸሙም በላይ የኦማን ሰዎች ወደ እስልምና እንዲገቡ ለማድረግ ችሏል፡፡
       *****
አምር ከነቢዩ ህልፈት በኋላም በአቡበከርና በዑመር ኺላፋዊ መንግሥት ውስጥም አገልግሏል፡፡ በጦር ግንባርም ሆነ በዲፕሎማሲ ስራ አንቱታን ያጎናጸፉትን ተግባራት ፈጽሟል፡፡ ከአምር ጋር የሁልጊዜ ተጠቃሽ ሆኖ የዘለቀው ግን ሮማዊያንን ከግብጽ በማባረር ወደ ኸሊፋዎቹ ግዛት የቀላቀለበት ዘመቻው ነው፡፡

አምር የግብጽን ዘመቻ (the conquest of Egypt) ያመነጨው በራሱ ነው ይባላል፡፡ በመሆኑም ኸሊፋ ዑመር ቢን ኸጣብ ሐሳቡን ተቃውመውት ነበር፡፡ የዑመር ተቃውሞ ዘመቻውን በመጥላት ሳይሆን “በተለያዩ ግንባሮች የተበተኑትን ወታደሮቻችንን በቶሎ አሰባስበን በዘመቻው እንዲሳተፉ ለማድረግ አንችልም” ከሚል የመነጨ ነው፡፡ ይሁንና አምር በወቅቱ በነበሩት ወታደሮች ብቻ ዘመቻውን በመጀመር ተጨማሪ ጦርን መጠባበቁን ነው የመረጠው፡፡
 
  አምር በ639 ዓ.ል በአራት ሺህ ወታደሮች የሲናይ በረሃን አቋረጠ፡፡ ሮማዊያንን በድንገተኛ ጥቃት በማራወጥ “ቢልቢስ” እና “ባቢሎን” በሚባሉት ስፍራዎች አሸነፋቸው (ይህቺ የግብጿ “ባቢሎን” የኢራቋ “ባቢሎን” አምሳያ እንድትሆን በሮማዊያን የተፈጠረች ናት)፡፡ ከጥቂት ወራት በኋላ ደግሞ በጥንቷ የኦኑ ከተማ (በፈረንጆች አጠራር Heliopolis) አጠገብ አሸነፋቸው፡፡ ከአንድ አመት በኋላ 12,000 ወታደሮች ከሶሪያ ሲመጡለትም አምር የዘመኑ የአፍሪቃ ታላቅ ከተማ የነበረችውን እስክንድርያን (አሌክሳንደሪያ) ለመያዝ ዘመተ፡፡ ሮማዊያን በከተማዋ ከሰማኒያ ሺህ የሚበልጥ ጦር የነበራቸው ቢሆንም ከነርሱ በአምስት እጥፍ በሚያንሰው የአምር ቢን ኣስ ጦር ድል ተመቱ፡፡ ግብጽም ሙሉ በሙሉ የሙስሊሞቹ ኺላፋ አካል ሆነች፡፡

ታዲያ አምር ግብፅን በአንድ ዓመት ውስጥ ለመያዝ የበቃው በጦር ሃይሉ ጥንካሬ ብቻ አልነበረም፡፡ በወቅቱ የግብጽ ክርስቲያኖች ከፍተኛ እርዳታ ስላደረጉለት ጭምር ነው ታላቁን ድል ለማጣጣም የበቃው፡፡ ክርስትያኖቹ አምርን የደገፉበት ምክንያት አለ፡፡

  ግብጻዊያን ክርስቲያኖች የሚያምኑበት የ“ተዋሕዶ” እምነት “ክርስቶስ የሁለት ባህሪ ባለቤት ነው” ከሚለው የሮማዊያን ክርስትና ይለያል፡፡ በዚህም ምክንያት ሮማዊያኑ የግብጽ ክርስቲያኖችን እንደ “መናፍቃን” ያዩዋቸው ነበር፡፡ ከቁስጥንጥንያ (የአሁኗ ኢስታንቡል) ተሹመው ግብጽን የሚገዙት እንደራሴዎችም የግብጽ ክርስትያኖች እምነታቸውን እንዲለውጡ ለማድረግ በልዩ ልዩ መንገዶች ይጨቁኗቸው ነበር፡፡ አንዳንዴም ፓትሪያኮቻቸውን እያሰሩ “እምነትህን ተው” እስከማለት ይደርሳሉ፡፡ አምር ቢን ኣስ ግብጽን ለመያዝ በሚዘምትበት ዘመን እንኳ የግብጽ ፓትሪያርክ የነበሩት “አቡነ ብንያም” (ቤንጃሚን) ከሀገር ተባረው ነበር፡፡ በመሆኑም ግብጻዊያኑ ከጭቆናው ለመገላገል ሲሉ አምር ቢን ኣስን በዘመቻው በእጅጉ ረድተዋል፡፡ (በነገራችን ላይ ከ5ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ጀምሮ ግብጽን ይገዟት የነበሩት ሮማዊያን መቀመጫውን በሮም ከተማ ያደረገው የታላቁ ኢምፓየር አካል አልነበሩም፡፡ የሮም ኢምፓየር በ395 “ምስራቅ” እና “ምዕራብ” ተብሎ ለሁለት ተከፍሏል፡፡ የሮማ ከተማ በ476 በጀርመን ጎሳዎች ስትወረር የምዕራቡ ኢምፓየር ህልውና አክትሟል፡፡ የምስራቁ ኢምፓየር ግን እስከ 1431 ድረስ ቆይቷል፡፡ ብዙዎች የምስራቁን ኢምፓየር የሚጠሩት “ቤዛንታይን” በሚል ስም ነው፡፡ ሆኖም ዐረቦችም ሆኑ የኢምፓየሩ ነዋሪዎች ግዛቱን “ሮም” እያሉ ስለሚጠሩት እኔም ይህንን ልማድ ተከትያለሁ)፡፡  

  አምር ግብጽን በሚያስተዳድርበት ጊዜ በክርስትያኖቹ ላይ ይደርስ የነበረውን ጭቆና ሙሉ በሙሉ አስወግዷል፡፡ በህዝቡ ላይ በየምክንያቱ ይጣሉ የነበሩትን ልዩ ልዩ የታክስ ዓይነቶች በማስቀረት ሁሉም ዜጎች ዓመታዊውን “ዑሽር” (አስራት) እና “ዘካት” ብቻ እንዲከፍሉ አድርጓል፡፡ በመንግሥቱ ቢሮክራሲ ውስጥም ክርስትያኖቹን አሳትፏል፡፡ የቤተ-ክርስቲያኖች ይዞታ የሆኑ መሬቶችና ንብረቶች እንዲከበሩም አድርጓል፡፡
       *****
 አምር ቢን ኣስ ግብጽን ማስተዳደር በጀመረ በዓመቱ ነው “አል-ፉስጣጥ” የተባለችውን ከተማ የቆረቆረው፡፡ ስለ“አል-ፉስጣጥ” ምስረታና ስለሌሎች ጉዳዮች በሚቀጥለው ክፍል እናወጋለን፡፡
---
አፈንዲ ሙተቂ
ህዳር 3/2007
ገለምሶ-ሀረርጌ

No comments:

Post a Comment