Wednesday, December 17, 2014

ኢራን፣ “ሩሚ” እና “መስነቪ”




ጸሓፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ
---
  ዛሬ በወግ ሽርሽር ብዙ ሀገር አቋርጠን “ፋርስ” ገብተናል፡፡ የዑመር ኻያም ሀገር! የፊርደውሲ ሀገር! የኒዛሚ ሀገር! የጃሚ ሀገር! የሓፊዝ ሀገር! በሩባኢያትና በገዛላት ዓለምን እያስፈነደቁ ለብዙ ክፍለ ዘመናት የዘለቁ የቅኔ ጠቢባን የተገኙባት ምድር!
  
   ዛሬ ፐርሺያ ነን! ዛሬ ኢራን ነን፡፡ ዛሬ ቴህራን ነን፡፡ ዛሬ ኒሻፑር ነን፡፡ ዛሬ ጠብሪዝ ነን፡፡ ዛሬ ሂልማንድ ነን፡፡ ዛሬ ኢስፋሓን ነን፡፡ ዛሬ ሺራዝ ነን! እዚያ ትልቅ የጥበብ ድግስ ተደግሶ ይጠብቀናል፡፡ እዚያ ከመድረሳችን በፊት ግን ለውዲቷ ኢራን ይህንን “ሩበእ” ብንቀኝላትስ?!  

አንቺ ሀገረ-ፋርስ የሀገር ጥበበኛ
ሁሉንም ያበቀልሽ አድርገሽ መልከኛ
የቅኔሽ መዓዛ ጠርቶኝ መጥቻለሁ
እጅሽን ዘርግተሸ መርሓባ በይኛ!

ሞክሬዋለሁ አይደል?. አዎን! “ሩበእ” (ሩባኢያት) ማለት እንዲህ ነው፡፡ ባለ አራት መስመር ቅኔ ሆኖ ሶስተኛው ስንኝ ከሌሎቹ አፈንግጦ ሲጻፍ በፋርሲ ቋንቋ “ሩበእ” ይባላል (ከዐረብኛው “ራቢዕ” የተገኘ ቃል ነው)፡፡ አንደኛ፣ ሁለተኛ እና አራተኛ መስመሮች በተመሳሳይ ፊደል ነው የሚያበቁት፡፡ ሶስተኛው ስንኝ ግን ከነርሱ ጋር አይገጣጠምም፡፡ “ሩበእ” ነጠላ ስም ነው፡፡ ለብዙ ቁጥር “ሩባኢያት” ይሆናል፡፡ አንዳንዶች የግጥሙ ዘውግ ከዐረቢያ ነው የተወረሰው ቢሉም “ሩባኢያት” ኦሪጂናሌ የኢራን የግጥም ዘይቤ መሆኑ በምሁራን ተረጋግጧል፡፡

ኢራናዊያን በሩባኢያት በጣም ይኮሩበታል፡፡ እንደ ብሄራዊ ቅርሳቸው ያዩታል፡፡ በተለይ The Zenith of Persian Literature በሚባለው ዘመን (ከ950 እስከ 1400 ድረስ) የተጻፉ ሩባኢያቶችን ከልብ ያፈቅሩአቸዋል፡፡ እኛም እንደ ዕድል ሆኖ በተስፋዬ ገሠሠ በኩል የዑመር ኻያም ሩባኢያትን በአማርኛ ለማንበብ በቅተናል፡፡ ዳሩ ግን እኛ ካጣጣምናቸው ሩባኢያት በላይ በኢራናዊያን የሚወደዱት የነ ሩሚ፣ ሳዲ፣ ጃሚ እና ሓፊዝ “ሩባኢያ”ት ናቸው፡፡ (ኢራናዊያን ከዑመር ኻያም በጣም የሚያደንቁለት የሒሳብ ሊቅነቱን ነው እንጂ ገጣሚነቱን አይደለም)፡፡
*****
ኢራን ነፍስ የሆነች ሀገር ናት! በጣም ውብ ባህልና የዳበረ ቋንቋ አላት፡፡ ታሪኳም ከቅድመ ክርስቶስ በፊት ከነበረው ዘመን ጀምሮ ነው የሚሰላው፡፡ በዚህ ረገድ ከመካከለኛው ምሥራቅ ሀገራት በእድሜ እርሷን የሚቀድሙት የርሷ ጎረቤት ሀገራት የሆኑት ሜሶጶጣሚያ (ኢራቅ) እና ሶሪያ ብቻ ናቸው፡፡ ዓለምን ያስደመሙ ታላላቅ ባለቅኔዎችን በማብቀል ግን ኢራን ከሁሉም ሀገራት ትበልጣለች፡፡

ኢራን ከጥንትም ጀምሮ ትክክለኛ ስሟ “ኢራን” ነው፡፡ የርሷ ተወላጆች ሀገራቸውን በዚሁ ስም ነው የሚጠሯት፡፡ ነገር ግን አብዛኛው የዓለም ህዝብ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ “ፋርስ” ወይንም “ፐርሺያ” ይላት ነበር፡፡ ኢራናዊያኑ “ይህ ስም አንዱን ክፍለ ሀገር እንጂ ሀገሪቱን በሙሉ ስለማይወክል ሀገራችንን ፐርሺያ እንዳትሏት” የሚል ዘመቻ ከፍተው ተሳክቶላቸዋል፡፡ ዛሬ ይኸው ኢራን ትባላለች፡፡ ይሁንና ቋንቋው “ፋርሲ” ነው የሚባለው፡፡ በዚህ ላይ ኢራዊያኑ ተቃውሞ የላቸውም፡፡ እንግዲህ በዚህ የፋርሲ ቋንቋ ነበር እነዚያ ውድ ባለቅኔዎች ዓለምን በጥበብ ሲያጠምቁ የነበሩት፡፡
*****
   የጥንቷ ኢራን እንዲህ እንደ አሁኑ አልነበረችም፡፡ ዛሬ አፍጋኒስታን፣ ቱርክሜኒስታን እና አዘርባይጃን የሚባሉ ሀገራት ለብዙ ክፍለ ዘመናት የርሷ ግዛቶች ነበሩ፡፡ የዛሬው እንግዳችንም በአሁኗ አፍጋኒስታን፣ በበልኽ አውራጃ፣ “ሩማ” በምትባል ከተማ ነው የተወለደው፡፡ እውነተኛ ስሙ ጀላሉዲን ሙሐመድ ወለድ ነው፡፡ ብዙዎች እርሱን የሚጠሩት ግን በትውልድ ከተማው ስም “ሩሚ” በማለት ነው፡፡

የሩሚ አባት የታወቁ ሼኽ እና ቃዲ ነበሩ፡፡ ሩሚም መደበኛ ትምህርቱን እዚያው በአባቱ ስር መማር ጀመረ፡፡ ነገር ግን በአስራ አንድ ዓመቱ መጥፎ እጣ ገጠመው፡፡ በዘመኑ መካከለኛው እስያን ደም በደም አድርገው የነበሩት የሞንጎል ወራሪዎች ወደ “በልኽ” እየተቃረቡ መሆናቸው ተሰማ፡፡ ስለዚህ የሩሚ አባት ቤተሰቡን ይዞ በምዕራብ አቅጣጫ ተሰደደ፡፡ “ኒሻፑር” ከምትባለው ጥንታዊት የኢራን ከተማ ሲደርሱም ከዘመኑ ዝነኛ ገጣሚ ፈሪዱዲን አጣር ጋር ተገናኙ፡፡ አጣር በሩሚ ነገሮችን የማስተዋል ችሎታ ተደንቆ “ይህ ልጅ ለወደፊቱ ትልቅ ባለቅኔ የመሆን ተስፋ አለው” የሚል ትንቢት ተናገረ ይባላል፡፡

ከሞንጎል የሸሸው የሼኽ ሙሐመድ ባሀኡዲን ወለድ (የሩሚ አባት) ቤተሰብ በመጨረሻ “ኮኒያ” ከምትባለው የቱርክ ከተማ ደረሰ፡፡ ሼኽ ባሃኡዲን እዚያ ካለው መድረሳ ማስተማር ጀመሩ፡፡ እርሳቸው ከሞቱ በኋላ ደግሞ የማስተማሩ ተግባር አንጋፋ ልጃቸው ለሆነው ለሩሚ ተላለፈ፡፡ ይሁንና ልጁ በማስተማሩ ላይ ሊያተኩር አልቻለም፡፡ ተፈጥሮንና ኑሮን እያየ ይህንን ግልብጥብጥ ዓለም የፈጠረውን ፈጣሪ አፈቀረ፡፡ ለርሱ የሙገሳ ቃላትን በግጥም መደርደር ጀመረ፡፡ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ግን አንድ ያልተጠበቀ እንግዳ ወደ ሩሚ መንደር ብቅ አለ፡፡

ሙላህ ሸምሱዲን ይባላል፡፡ የጠብሪዝ ተወላጅ ነው፡፡ ኢራናዊያን “ሸምስ-ኢ-ጠብሪዚ” ይሉታል፡፡ ሩሚ በሸምሱ-ጠበሪዝ ላይ ባየው መንፈሳዊ ልቅና ተመሰጠ፡፡ እንደ መምህሩም ቆጠረው፡፡ ቤተሰቡንና ስራውን ሁሉ ትቶ ከርሱ ጥበብን መቅሰም ጀመረ፡፡ አንድ ቀን ግን ሸምስ ጠብሪዝ እዚህ ነኝ ሳይል ጠፋ፡፡ በዚህም የተነሳ ሩሚ የመምህሩን ፍቅር ተራበ፡፡ ፍቅሩ እያቃጠለው “መደድ” (የፍቅር የመጨረሻ ደረጃ) ውስጥ አስገባው፡፡  ከዚያማ ማን ይቻለው! ከመምህሩ የተማረውን በራሱ ቋንቋ ጻፈው፡፡ 30,000 “ገዛል” እና ቁጥራቸው በርካታ የሆኑ “ሩባኢያት”ን ከተበ፡፡ እነዚህም ግጥሞች “ዲዋን-ኢ-ሸምሹ-ጠብሪዝ” በተሰኘ መጽሐፍ በአንድ ላይ ተሰበሰቡ (“ገዛል” የሚባለው ግጥም “ዜማ” ጭምር እንዳለው ልብ በሉ)፡፡
*****
የሩሚ የጥበብ ፍቅር አላበቃም፡፡ በሸምስ ጠበሪዝ መጥፋት የተከፋችው ነፍስ ሌላ መምህር ፍለጋ አላቆመችም፡፡ ታዲያ ሩሚ ብዙም አልተጓዘም እዚያው “ኮኒያ” ከተማ ውስጥ ተማሪው የነበረ ልጅ መምህሩ ሆኖ ተገኘ፡፡
 ሑሳሙዲን ይባላል፡፡፡ ሑሳሙዲን ከሩሚ ግጥሞች ሌላ የነ ፈሪዱዲን አጣርን፣ የነ ሰነኢንና የሌሎች ታላላቅ የፋርስ ባለቅኔዎችን ስራ አጥንቷል፡፡ እናም አንድ ቀን ሩሚን እንዲህ አለው፡፡ “መምህር! የርስዎ ግጥሞች ጉድለት ይታይባቸዋል፤ የራስዎትን ስሜት ብቻ እየተከተሉ ስለሚጽፉ በሌላው ውስጥ ጠልቆ የመግባት ሀይል ያጥራቸዋል፤ ለምን እንደ አጣርና እንደ ሰነኢ አይጽፉም” አለው፡፡
 ሩሚም “እስቲ እንዴት አድርጌ ልጻፍ?” በማለት ጠየቀው፡፡
 ሑሳሙዲንም “ከልዩ ልዩ ምንጮች የተገኙ እውነተኛ ታሪኮችን፣ ተረቶችን፣ ምሳሌዎችን፣ ተምሳሌቶችን፣ ወዘተ… እያሰናሰሉ ቢቀላቅሉባቸውና የግጥሞቹ አካላት ቢያደርጓቸው የምን ጊዜም ተወዳጅ ይሆናሉ” ብሎ መለሰለት፡፡
 የሑሳሙዲን ምክር በሩሚ ልብ ውስጥ ጠልቆ ገባ፡፡ ከዚያም ቅኔ ሲመጣለት መቀኘት ጀመረ፡፡ ሑሳሙዲንም ከሩሚ አንደበት የሚወጣውን መጻፉን ተያያዘው፡፡ ሁለቱ ሰዎች እንዲህ እያደረጉ ዛሬ ዓለም በሙሉ የሚደመምበትን “መስነቪ”ን አስገኙ (የመጽሐፉ ትክክለኛ ስም “መሥነዊ” ነበር፤ ይህም “መሥን” ከተሰኘው የዐረብኛ ግስ የተገኘ ነው፡፡ ነገር ግን የ“ሠ” እና የ“ወ” ድምጾች በፋርሲ ቋንቋ ውስጥ ስለሌሉ ኢራናዊያን “መስነቪ” እያሉ ይጠሩታል፤ የዓለም ህዝብም የነርሱን ፈለግ በመከተል “መስነቪ” ይለዋል)፡፡
*****
ሩሚ “መስነቪ”ን የደረሰው ከዛሬ 800 ዓመት በፊት ነው፡፡ ይሁንና ዛሬም ድረስ የህዝብ ፍቅር ሳይነፈገው እንደተወደደ አለ፡፡ በዘመናችን “ሩሚ”ን እጅግ ተነባቢ ከሆኑ አስር ምርጥ ገጣሚዎች ተርታ ያሰለፈውም “መስነቪ” ነው፡፡ ይህ ዝነኛ የግጥም ድርሳን ለዓለም ስነ-ጽሑፍ መዳበር ያደረገውን አስተዋጽኦ በመመዘን የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት የሳይንስና የባህል ድርጅት የአውሮፓዊያኑ 2007 በዓለም አቀፍ ደረጃ የሩሚ ዓመት ተብሎ እንዲጠራ ወስኗል፡፡ በዚያው ዓመት ሩሚ የተወለደበት ስምንት መቶኛ ዓመት ተከብሯል፡፡

የመስነቪ ይዘት ሰፊ ነው፡፡ የሰውን ልጅ አዕምሮ ያመራምራል፡፡ በዚህ ትንሽ መጣጥፍ ስለርሱ ብዙ ማውራት አይቻልም፡፡ ዳሩ ግን ከመስነቪ የተቀዳ አንድ ውብ ታሪክ ላካፍላችሁ እችላለሁ፡፡ ሩሚ ታሪኩን በግጥም ነው የጻፈው፡፡ ነገር ግን ተርጓሚው በስድ-ንባብ መልሶ ጽፎታል፡፡ እኔም በስድ ንባብ የተጻፈውን ታሪክ ነው የምጋብዛችሁ፡፡

===አራቱ ሰዎችና መንገደኛው===

  አራት ሰዎች ነበሩ፡፡ እነዚያም ሰዎች ግሪክ፣ ፋርሲ (ኢራናዊ)፣ ዐረብ እና ቱርክ ነበሩ፡፡ የሚፈልጉትን ነገር ይገዙበትም ዘንድ የተወሰነ ገንዘብ ተሰጣቸው፡፡ ግሪኩ “እኔ ስታፊል አምሮኛል፤ ስታፊል ግዙልንና እንብላው” አለ፡፡
ፋርሲው “የምን ስታፊል? ኡዙም ግዙልን እንጂ ሰዎች” አለ፡፡
ዐረቡ “አረ ወደዚያ! ኢነብ ነው የምንገዛው፤ ኢነብ መግዛት አለብን” በማለት ተናገረ፡፡
ቱርኩ “እንዴ! አንጉር ነው መግዛት ያለብን፤ አንጉር እንጂ ሌላ ነገር አትግዙብን” አለ፡፡

    አራቱ ሰዎች ተከራከሩ፡፡ ተነታረኩ፡፡ በጭራሽ ሊግባቡ አልቻሉም፡፡ እንዲህ እየተወዛገቡ ሳለም አንድ መንገደኛ መጣ፡፡ “ምንድነው የሚያጨቃጭቃችሁ?” በማለት ጠየቃቸው፡፡ ጉዳዩን ነገሩት፡፡ ሰውየውም “በዚህ ፍራንክ የሁላችሁንም ፍላጎት ማሟላት ይቻላል” አላቸው፡፡ ሰዎቹም “እንዴት?” በማለት ጠየቁት፡፡ ሰውዬም ገንዘቡን እንዲሰጡት ጠየቃቸው፡፡ እነርሱም እንደተባለው አደረጉ፡፡
መንገደኛው ሰውዬ በአካባቢው ከነበረ የፍራፍሬ መሸጫ ገብቶ አንዱን የፍራፍሬ ዓይነት ገዝቶ ሲወጣ አራቱ ሰዎች ተያዩ፡፡ በዚያው በሳቅ ፈረሱ፡፡ ለካስ አራቱም የአንዱን ፈራፍሬ ስም በየቋንቋቸው እየጠሩት ነበር? አራቱም “ወይን እፈልጋለሁ” እያሉ ነበር የሚከራከሩት::
*****
የታሪኩን “ማዕና” (መልዕክት) አገኛችሁት አይደል? ለኛም እንደ መንገደኛው ሰውዬ ያለ አስታራቂ ይላክልን፡፡ አንድ ውጥንና ግብ ያላቸው ሰዎች ዕድሜ ልካቸውን በአተገባበር ላይ ሲጣሉ ማየትን የመሰለ አሰቃቂ ህመም የለም፡፡ ሁሉም እይታውን ቢያስተካክል መግባባት ይቻላል፡፡ ሩሚ ይህንን ነው የመከረን፡፡
ብራቮ ጀላሉዲን ሩሚ! ብራቮ መሥነቪ!
*****
የካቲት 24/2006
*****
Afendi Muteki is a researcher and author of the ethnography and history with special focus on the peoples of East Ethiopia. You may follow him on his blog and his facebook page by clicking the following links


1 comment:

  1. ሁሉም እይታውን በያስተካከል ስለ አንድ ነገር ማሰባችን ይታወቀን ነበር

    ReplyDelete