Tuesday, December 30, 2014

ኢድሪስ ገላውዴዎስ- አንጋፋው “ጀብሃ”





ጸሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ


-----

  “ሻዕቢያ” የሚለው ስም ሲነሳ የዑስማን ሳልህ ሳቤ ስምም አብሮ ይነሳል፡፡ በእርግጥም “ሻዕቢያ” የሚለውን ስያሜ በስራ ላይ ከማዋል ጀምሮ ድርጅቱን በሁለት እግሩ እንዲቆም ያደረገው ዑሥማን ሳልህ ሳቤ በመሆኑ እርሱን እንደ ሻዕቢያ መስራች መመልከቱ አግባብ ነው፡፡ የ“ጀብሃ” ስም ሲጠቀስ ደግሞ ብዙዎች የሚያስታውሱት ሓሚድ ኢድሪስ አዋቴን ነው፡፡ ይህ ግን ስህተት ነው፡፡ ሃሚድ ኢድሪስ አዋቴ በታሪክ የሚታወሰው ጀብሃ የትጥቅ ትግል በጀመረበት ጊዜ የመጀመሪያውን ጥይት የተኮሰ ሰው በመሆኑ ነው፡፡ “ጀብሃት ታሕሪረል ኤርትሪያ” (በአጭሩ “ጀብሃ”) ወይንም በትግርኛ ስሙ “ተጋድሎ ሓርነት ኤርትራ” (ተ.ሓ.ኤ) የሚባለው የኤርትራ አንጋፋ የፖለቲካ ድርጅት የተመሰረተው “አዋቴ” ትግሉን በባርካ በረሃ ከመጀመሩ ከአንድ ዓመት አስቀድሞ ነው፡፡

 

የጀብሃ መስራቾች በአብዛኛው በካይሮ የሚማሩ ተማሪዎች ሲሆኑ የቀድሞው የኤርትራ ፓርላማ አባላት የነበሩ ጥቂት ግለሰቦችና ነጋዴዎችም ተቀላቅለቸዋል፡፡ ከመስራቾቹ መካከል ሙሐመድ ሳሊህ ሁመድ፣ ሙሐመድ አደም ኢድሪስ፤ ሰዒድ ሁሴን፣ ጣሓ ሙሐመድ ኑር፣ ወዘተ…ይጠቀሳሉ፡፡ ይሁንና እነዚህን ሰዎች አሰባስቦ የድርጅቱን መሰረት በመጣል ከፍተኛ ሚና የተጫወተው ሰው ኢድሪስ ገላውዴዎስ ይባላል፡፡

 

ኢድሪስ ዑሥማን ገላውዴዎስ በ1934 በከረን ከተማ አቅራቢያ በነበረችው “በይት ጀክ” በተባለች አነስተኛ ከተማ ነው የተወለደው፡፡ ኢድሪስ የቤኒአምር (ትግረ) ብሄረሰብ አባል ነው፡፡  አባቱ ሀብታም ነጋዴ የነበሩ ከመሆናቸው በተጨማሪ በምዕራባዊው ኤርትራ ሰፊ እርሻ ነበራቸው፡፡ በመሆኑም ኢድሪስ መደበኛ ትምህርቱን የጀመረው በ1942 የአባቱ እርሻ በሚገኝባትና በኢትዮጵያና ኤርትራ ድንበር ላይ ባለችው የአሊጊደር ከተማ ነው፡፡ በ1947 የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን ካጠናቀቀ በኋላ ለሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ወደ ከሰላ (ሱዳን) ተላከ፡፡ የፖለቲካ ተሳትፎውንም የጀመረው በከሰላ ከተማ በነበረበት ወቅት ነው፡፡

 

  እንደሚታወቀው በዚያ ዘመን ኤርትራ በእንግሊዞች አስተዳደር ስር ነበረች፡፡ በዘመኑ ኤርትራ ነጻ መውጣት አለባት የሚሉና ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር ትቀላቀል የሚሉ ሁለት ጎራዎች ነበሩ፡፡ የመጀመሪያውን ጎራ የሚያንቀሳቅሰው “ራቢጣ አል-ኢስላሚያ” የሚባል ፓርቲ ሲሆን ሁለተኛውን ጎራ የሚመራው ደግሞ “ማሕበር ሀገር ፍቕሪ” የሚባለው ቡድን ነው፡፡ የኢድሪስ አባት የራቢጣ አባል የነበሩ እንደመሆናቸው “ኤርትራ ነጻ ትሁን” በማለት ከራቢጣ መስራች ከሼኽ ሱልጣን ኢብራሂም ጋር ብዙ ተንቀሳቅሰዋል፡፡ ኢድሪስም በአባቱ ላይ ባየው የትግል መንፈስ በጣም ተማረከ፡፡ መሆኑም “የራቢጣ” የወጣቶች ክንፍ አባል ሆነ፡፡

 

ኢድሪስ በ1951 ትምህርቱን በከፍተኛ በማዕረግ በማጠናቀቁ ከካይሮ ዩኒቨርሲቲ የስኮላርሺፕ እድል አገኘ፡፡ ወደ ዩኒቨርሲቲው ገብቶም የህግ ትምህርት ማጥናት ጀመረ፡፡ ከዓመት በኋላም የኤርትራ ተማሪዎች ማህበር ሲመሰረት የማህበሩ ሊቀመንበር ሆኖ ተመረጠ፡፡ ኢድሪስ በዚህ ማህበር ኤርትራዊያን ስደተኞችን ለማሰባሰብ በሰፊው ተጠቅሞበታል፡፡

   *****

ኢድሪስና ጓዶቹ በስደት ላይ ሆነው የሀገር ቤቱን ሁኔታ በቅርበት ይከታተሉት ነበር፡፡ በተለይም የተባበሩት መንግሥታት ለኤርትራ የሰጠው የፌዴሬሽን መብት እየተሸረሸረ ነው በማለት ተቃውሞአቸውን ያሰሙ ነበር፡፡ በ1957 የኤርትራ ሰንደቅ ዓላማ ታገደ፡፡ ከዓመት በኋላም ትግርኛና ዐረብኛ የስራ ቋንቋ መሆናቸው አብቅቶ በአማርኛ ሲተኩ ደግሞ “ሐረካ” (Eritrean Liberation Movement) የተባለው ድርጅት በሚስጢር ተመሰረተ፡፡ ”

 

  የሐረካ ዓላማ ፌዴሬሽኑ በተቀመጠለት ደንብ መሰረት እንዲሰራ መጠየቅና ለዚህም እስከ መጨረሻው መታገል ነበረ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ይህ ድርጅት የትጥቅ ትግልን እንደ አማራጭ አልወሰደም፡፡ “ሐረካ” በካይሮ የነበሩትን ተማሪዎች በአባልነት ለማሳተፍ ሲሞክር ግን ተቃውሞ ገጠመው፡፡ እነ ኢድሪስ ገላውዴዎስ የሐረካ ዓላማና የትግል ስልት አዋጪ መስሎ ስላልታያቸው ድርጅቱን እንደ ከንቱ ማህበር ነበር ያዩት፡፡

   *****

 በ1960 ነው፡፡ ኤርትራዊያን በፌዴሬሽኑ አሰራር ሙሉ በሙሉ ተስፋ ቆርጠዋል፡፡ በርካቶቹም በአጼ ኃይለ ሥላሤ መንግሥት የተሾሙት ቢትወደድ አስፋሓ ወልደሚካኤል ለባርነት ሊዳርገን ነው እያሉ መነጋገር ጀምረዋል፡፡ ከዓመት በፊት የኤርትራ ሰራተኞችና ተማሪዎች ሰላማዊ ሰልፍ ባደረጉበት ወቅት የጸጥታ ሃይሎች በወሰዱት እርምጃ ሳቢያ በሀገር ቤት ተቃውሞ ማድረጉም ብዙ እንደማያራምድ አምነዋል፡፡ በዚህም የተነሳ በርካቶች የመንግሥትና የፓርላማ ስልጣናቸውን በመተው ወደ ውጪ መሰደድ ጀመሩ፡፡ እነዚህ ስደተኞች ካይሮ ከሚገኙት ተማሪዎች ጋር ከተቀላቀሉ በኋላ ስለ ድርጅት ምሥረታ መነጋገር ጀመሩ፡፡ ውይይቱም ፍሬያማ ሆኖ በመውጣቱ በጁላይ ወር 1960 ከነጻነት በስተቀር የፌዴሬሽንን ፎርሙላ የማይቀበል አዲስ ድርጅት ተመሰረተ፡፡ ይህም ድርጅት “ጀብሃት ታሕሪረል ኤሪቲሪያ” ወይንም “ተጋድሎ ሓርነት ኤርትራ” (ተ.ሓ.ኤ) ተብሎ ተሰየመ፡፡

     

   “ጀብሃ” ሲመሰረት የድርጅቱ ሊቀመንበር ሆኖ የተመረጠው የቀድሞ የፓርላማ አባል የነበረው ኢድሪስ ሙሐመድ አደም ነው፡፡ ሆኖም ኢድሪስ ሙሐመድ በምርጫው ሊያሸንፍ የቻለው ለረጅም ጊዜ የድርጅቱን መሰረት ሲጥል የቆየው ኢድሪስ ገላውዴዎስ ባደረገው ቅስቀሳ ሌሎቹ የድርጅቱ መስራቾች እምነታቸውን ስለጣሉበት ነው፡፡ ኢድሪስ ገላውዴዎስ ደግሞ በመስራች ጉባኤው የድርጅሩ ዋና ጸሐፊ ሆኖ ተመርጧል፡፡ የድርጅቱ ላዕላይ ምክር ቤት (Supreme Council) አባላት ኢድሪስ ሙሐመድ አደም፤ ኢድሪስ ገላውዴዎስ፣ ሙሐመድ ሳሊሕ አሕመድ፣ ዑሥማን ኢድሪስ ኪያር፣ ሙሐመድ ሰዒድ ኪያር፣ ሲሆኑ ከአንድ ዓመት በኋላም ዑሥማን ሳልህ ሳቤ ተቀላቅሎአቸዋል፡፡

  

 “ጀብሃ” ከተቋቋመ በኋላ በምዕራብ ኤርትራ በረሃ በተበታተነ ሁኔታ ከሚታገሉት እነ ሃሚድ ኢድሪስ አዋቴን ከመሳሰሉ ፋኖዎች ጋር ተገናኘ፡፡ ለአዋቴም የግንባሩን ወታደራዊ ክፍል እንዲመሩ ውክልና ሰጣቸው፡፡ በመስከረም 1/1961 በሃሚድ አዋቴ አዝማችነት በጀብሃ ስም የትጥቅ ትግሉ ተጀመረ፡፡ ሃሚድ ኢድሪስ አዋቴ ከአንድ ዓመት በኋላ ሲገደሉ ደግሞ የወታደራዊውን ክንፍ የመምራቱ ስልጣን ለኢድሪስ ገላውዴዎስ ተሰጠ፡፡ በዚህም የተነሳ የኢድሪስ ገላውዴዎስ መቀመጫ ከካይሮ ከተማ ወደ ሱዳኗ ከሰላ ከተማ ተቀየረ፡፡

 

ኢድሪስ ገላውዴዎስ ከሰላ ከደረሰ በኋላ በሱዳን ውስጥ የሚገኙ ኤርትራዊያን ስደተኞችን እያሰባሰበ ወታደራዊ ስልጠና እንዲያገኙ አድርጓል፡፡ በኋላ ላይ ደግሞ ለድርጅቱ ድጋፍ ለማግኘት ወደ ልዩ ልዩ ሀገራት ተጉዟል፡፡ በዚህም ውጤት አግኝቶበታል፡፡ ለምሳሌ በ1967 ወደ ቻይና ተጉዞ እነ ማኦ ዜዱንግን በማሳመን ለጀብሃ የመሳሪያና የስልጠና ድጋፍ አስገኝቷል (በዚያን ጊዜ ወደ ቻይና ሄደው ስልጠና ካገኙት መካከል አንዱ የአሁኑ የኤርትራ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ናቸው)፡፡ ወደ ኩባ በመሄድም የጀብሃ ተዋጊዎች የፓራ-ኮማንዶ ስልጠና እና የመሳሪያ ድጋፍ እንዲያገኙ አድርጓል፡፡ ከሶሪያና ከኢራቅም ብዙ እርዳታ አስገኝቷል፡፡ የእስያ-አፍሪቃ የወዳጅነት ኮንፈረንስ በተካሄደበት ጊዜም ድርጅቱን በመወከል ተሳትፏል፡፡

   *****

ከዚህ ቀደም በጻፍኳቸው ጽሑፎች እንደገለጽኩት “ጀብሃ” የሚባለው ድርጅት በኤርትራዊያን ክርስቲያኖች ላይ ውገና ያካሄድ ነበር፡፡ የዚህም መነሻ “ለኃይለ ሥላሤ መንግሥት አሳልፈው የሸጡን ክርስቲያኖቹ ናቸው” የሚለው የተሳሳተ ፍረጃው ነው፡፡ እርግጥ የኃይለ ሥላሤ መንግሥት ኤርትራዊያን ሙስሊሞች ወደ ስልጣነ-መንግሥቱ እንዳይቀርቡ አድርጓል፡፡ በመንግሥት ስልጣንም ሆነ በፓርላማው ውስጥ የተሰገሰጉት በአብዛኛው ደገኛ ክርስቲያኖች ነበሩ፡፡ ይሁንና የእነዚህ ጥቂት ሰዎች ምግባር ሁሉንም የኤርትራ ህዝበ ክርስቲያን አይወክልም፡፡ ስለዚህ ጀብሃ ኤርትራዊያን ክርስቲያኖችን በጥርጣሬ ማየቱና በድርጅቱ ውስጥ የነበሩትንም እያሳደደ መምታቱ ትክክል አልነበረም፡፡ ድርጅቱንም ለውድቀት ያበቃውም ይህ የውገና አቋሙ ነው፡፡

 

  ይህ ወገንተኛ አቋም የሁሉም የጀብሃ አባላት አቋም አልነበረም፡፡ በመሆኑም በ1969 በወታደራዊ ግንባር የተሰለፉት አባላት ግንባሩ ራሱን እንዲፈትሽና እንዲያሻሽል የሚቀሰቅሰውን የአዶብሃ ኮንፈረንስ ጠሩ፡፡ በኮንፈረንሱ ማጠቃለያም ድርጅቱ ራሱን እስካላሻሻለ ድረስ ካይሮ የሚገኘው ላዕላይ ምክር ቤት የሚያወጣቸውን መመሪያዎች እንደማይቀበሉ አስታወቁ፡፡ የካይሮው ምክር ቤት ኮንፈረንሱን በህገ-ወጥነት ፈረጀው፡፡ ሆኖም በከሰላ የሚገኘው ኢድሪስ ገላውዴዎስ የተነሱትን ጥያቄዎች እንደሚቀበል አስታወቀ፡፡ በዚህም የተነሳ ኢድሪስ ገላውዴዎስ ከአመራሩ ጋር ተጋጨ፡፡ በድርጅቱ ውስጥ የነበረውንም ከፍተኛ ስልጣን አጣ፡፡ ይሁንና የወታደራዊ ኮሚቴ ሊቀመንበርነቱን አልተወውም፡፡

 

 ኢድሪስ ገላውዴዎስ የጀብሃን ወታደራዊ ክንፍ በሚመራበት ወቅት ነበር በዑሥማን ሳልህ ሳቤ እና በኢሳያስ አፍወርቂ የሚመሩት ቡድኖች ከድርጅቱ ተገንጥለው የወጡት፡፡ የጀብሃ አመራር እነዚህን ቡድኖች በወታደራዊ ጥቃት የማጥፋት ውሳኔ አሳለፈ፡፡ ኢድሪስ ገላውዴዎስ ግን ውሳኔው ኤርትራዊያንን የበለጠ ይከፋፍላል በማለት ተቃወመው፡፡ ወታደራዊ ዘመቻዎችንም እንደማያስፈጽም ለድርጅቱ መሪዎች ቁርጡን ነገራቸው፡፡ በዚህም የተነሳ የድርጅቱ መሪዎች ኢድሪስን ከወታደራዊ መሪነቱ አስነሱትና በውጪ ጉዳይ ላይ ሾሙት፡፡

 

ኢድሪስ ገላውዴዎስ ድርጅቱን በውጪ ጉዳይ ሃላፊነት በሚመራበት ወቅት ድርጅቱ በጣም እየተዳከመ ነበር፡፡ ቢሆንም ኢድሪስ በውጪው ዓለም የድርጅቱን ስም የሚያስጠሩ ስራዎችን ሰርቷል፡፡ ለምሳሌ እ.ኤ.አ. በ1978 ታላቋ ሶቭየት ህብረት ጀብሃ ከደርግ መንግሥት ጋር እንዲወያይ በፈጠረችው መድረክ ላይ ድርጅቱን ወክሎ ተገኝቷል፡፡

 

 ከጥቂት ዓመታት በኋላ ጀብሃ ፍርስርሱ ወጣ፡፡ በኤርትራ ምድር የቀረው ትርፍራፊ ጦሩ በሻዕቢያ ተደመሰሰ፡፡ ድርጅቱም በስም ያለ በተግባር ግን የሌለ ሆኖ ቀረ፡፡ ይህንን የተመለከተው ኢድሪስ ገላውዴዎስ በድርጅቱ መሪዎች ላይ ከፍተኛ ሂስ ጽፎ አቀረበ፡፡ ድርጅቱ ሁሉንም ኤርትራዊያን በእኩል ሁኔታ አለማየቱና ዲሞክራሲያዊ አሰራር የሌለው መሆኑ ለሞት እንዳበቃው አሰመረበት፡፡ በመሆኑም ከጀብሃ አመራር ራሱን አገለለ፡፡

 

   በ1991 ሻዕቢያ ኤርትራን ሙሉ በሙሉ ሲቆጣጠር ኢድሪስ ገላውዴዎስ ለአዲሱ መንግሥት እውቅና እንደሚሰጥ አስታወቀ፡፡ እነ ኢሳያስ አፈወርቂም ወደ ሀገር መጥቶ በስራ እንዲረዳቸው ጥሪ አቀረቡለት፡፡ ኢድሪስም ግብዣውን ተቀብሎ ወደ ሀገር ውስጥ ገባ፡፡ ከ1991-1993 በነበሩት ዓመታትም ከዶ/ር በረከት ሃብተ ሥላሴ ጋር የሪፈረንደም ኮሚሽን ሃላፊ ሆኖ ሰራ፡፡ በተከታዮቹ ዓመታት ደግሞ የህገ-መንግሥት አርቃቂ ኮሚሽን አባል ሆኖ በመስራት ላይ እያለ እ.ኤ.አ በ1998 አረፈ፡፡ የቀብር ስርዓቱም በብሄራዊ ደረጃ ተፈጸመለት፡፡

   *****

   የጀብሃ አባላት ለኢድሪስ ገላውዴዎስ ሁለት ዓይነት እይታዎች ነው ያላቸው፡፡ ኢድሪስ ድርጅቱን ለመመስረትና የወታደራዊ ክንፉን መሰረት ለመጣል ያደረገውን አስተዋጽኦ በበጎ ዐይኑ ይመለከቱታል፡፡ ከዚያ በኋላ ግን አድርባይ ሆኖ ድርጅቱን ከድቷል በማለት ይኮንኑታል፡፡ የሻዕቢያ አባላትና ደጋፊዎች ግን ኢድሪስ ገላውዴዎስን በበረሃ ውስጥ የተገኘ ተክል አድርገው ነው የሚያዩት፡፡ “ጀብሃ ከውጥኑ ጀምሮ በርሱ ቢመራ ኖሮ ኤርትራዊያን እርስ በራሳቸው አይጋደሉም ነበር” በማለትም ያምናሉ፡፡ ሐቁ የትኛው እንደሆነ ታሪክ ነው የሚፈርደው፡፡ ከብዙ በጥቂቱ ግን ኢድሪስ ገላውዴዎስ ማለት ከላይ የተገለጸው ሰው ነው፡፡

-----

አፈንዲ ሙተቂ

ታሕሳስ 22/2007

ሀረር-ምሥራቅ ኢትዮጵያ

Afendi Muteki is a researcher and author of the ethnography and history with special focus on the peoples of East Ethiopia. You may follow him on his blog and his facebook page by clicking the following links

Facebook  https://www.facebook.com/afendimutekiharar

 

Blog:  https://afendimutekiharar.blogspot.com

 

 

ምንጮች

1.      www.awate.co,

2.     www.asmerino.com

3.     Tekste Negash: Ethiopia and Eritrea: The Federal Experience, 1997

Monday, December 29, 2014

አለቃ ገብረሃና ማን ናቸው?



(አፈንዲ ሙተቂ)
----
     ጎንደር ካፈራቻቸው ሰዎች መካከል አብዛኛው ኢትዮጵያዊ የሚያውቀው እኝህ ሰው ይመስሉኛል፡፡ እኔ ጸሐፊው ስለርሳቸው የሰማሁት የቋራው መይሳው ካሳን ከማወቄ በፊት እንደሆነ አስታውሳለሁ፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ በአለቃ ገብረሃና ስም የሚነገሩ ቀልዶችን የነገረን ደግሞ ማን መሰላችሁ….? ከዚህ በፊት ያስተዋወቅኳችሁ የሁለተኛ ክፍል አለቃችን የነበረው አያሌው አብነት  ነው፡፡ ሆኖም እርሱ ያኔ የነገረንን እዚህ መጻፍ አይመችም፡፡ ስለዚህ የአያሌውን ቀልዶች ትተን ስለአለቃ ገብረሃና ከመዛግብት ያገኛቸውን ወጎች እንጨዋወታለን፡፡ ከዚያ በፊት ግን “ዐረፈ ዐይኔ ሐጎስ” “አለቃ ገብረሃ እና አስቂኝ ቀልዶቻቸው” በሚል ርዕስ ካሳተሙት መጽሐፍ ያገኘነውን የአለቃ ገብረሃናን ታሪክ አጠር አድርገን እናወሳለን፡፡
  
አለቃ ገብረሃና በሙሉ ስማቸው “ገብረሃና ደስታ ተገኝ” ይባላሉ፡፡ የተወለዱት በ1814 በጎንደር ክፍለ ሀገር በደብ ታቦር አውራጃ ፎገራ ወረዳ (አሁን ደቡብ ጎንደር ዞን ፎገራ ወረዳ) ውስጥ ነው፡፡ በተወለዱበት አካባቢ የቤተ ክህነት ትምህርት ተምረው በሃያ ስድስት ዓመታቸው የሊቀ-ካህናት ማዕረግ አግኝተዋል፡፡ በዚህ ሹመት ለሰባት ዓመታት ካገለገሉ በኋላ በፍትሐ ነገሥት አዋቂነታቸው ተመርጠው ጎንደር ውስጥ በዳኝነት ተሾሙ፡፡

  አለቃ በካህንነትም ሆነ በዳኝነት ሲያገለግሉ እንደ ሌሎች የዘመኑ መኳንንት ቁጥብ አልነበሩም፡፡ ከተራው ህዝብም ሆነ ከመንግሥት ባለስልጣናት ጋር ይቃለዱ ነበር፡፡ ይህ ቀልደኝነታቸው እየገነነ ሄዶ በትንሹ ራስ ዓሊ ዘንድ ተሰማላቸው፡፡ በመሆኑም ወደ ቤተ መንግሥት ተጠርተው የራስ ዓሊ አጫዋች በመሆን ተሰየሙ፡፡ እንግዲህ ከዚህን ጊዜ ጀምሮ ነው አለቃ ገብረሃና የመኳንንቱና የመሳፍንቱ አጫዋች በመሆን ህይወታቸውን የገፉት፡፡
 
   አለቃ ገብረሃና በአጼ ዮሐንስም ሆነ በአጼ ምኒልክ ዘንድ ክብርና ሞገሥ አግኝተው እንደ ታላቅ ሰው ይታዩ ነበር፡፡ በአጼ ቴዎድሮስ ዘመን ግን ከፍተኛ ችግር ደርሶባቸው ነበር፡፡ ቴዎድሮስ አለቃን ያገኟቸው በቤተ መንግሥቱን ከራስ ዓሊ በተረከቡ ጊዜ ነው፡፡ ቴዎድሮስ አለቃን በዝና ቢያውቋቸውም ቀልድና ባልቱን አልወደዱላቸውም፡፡ ቴዎድሮስ ቀልዱን እንዲያቆሙና በዳኝነቱ እንዲቀጥሉ ቢገስጿቸውም አለቃ በጄ የሚሉ አልሆኑም፡፡ በመሆኑም አለቃን ከዳኝነታቸው ሽረው ትግራይ ውስጥ የሚገኘው የጨለቆት ሥላሤ ገዳም አስተዳዳሪ አድርገው ሾሟቸው፡፡ 
  
የደብሩ ቆይታ የቤተ መንግሥት ኑሮ ለለመዱት አለቃ ገብረሃና የሚመች አልሆነም፡፡ በዚያ ላይ አጼ ቴዎድሮስ ቤተ ክህነትን ርስት አልባ ለማድረግ መሞከራቸው ከሀገሬው ህዝብ ጋር አጣላቸው፡፡ በመሆኑም ካህናቱ ቴዎድሮስን ለመገልበጥ ማሴር ጀመሩ፡፡ አለቃ ገብረሃናም ዱለታውን ተቀላቀሉ፡፡ ይህም ወሬ ለአጼ ቴዎድሮስ ደረሳቸው፡፡ አጼውም አለቃ ገብረሃና ታስረው እንዲቀርቡ አዘዙ፡፡ ሆኖም አለቃ ገብረሃና ሸሽተው ጎጃም ውስጥ ከሚገኘው ዘጌ ገዳም ተደበቁ፡፡

   ከሁለት ዓመት በኋላ አጼ ቴዎድሮስ በመቅደላው ጦርነት ራሳቸውን ገደሉ፡፡ አለቃ ገብረሃናም ከተደበቁበት ወጥተው ወደ ጎንደር ተመለሱ፡፡ በ1864 አጼ ዮሐንስ አራተኛ ሲነግሡ በጎንደር ከተማ የነበራቸውን የቀድሞ ሹመታቸውን አጸደቁላቸው፡፡ በምኒልክ ጊዜ ደግሞ ወደ አዲስ አበባ መጥተው በእንጦጦ ራጉኤል ቤተ ክርስቲያን የአቋቋም እና የመርገድ አስተማሪ ሆኑ፡፡ ከጥቂት ቆይታ በኋላም የቤተ ክርስቲያኑ አስተዳዳሪ ሆኑ፡፡

  አለቃ ገብረሃና በአዲስ አበባ ኑሮአቸው ከአጼ ምኒልክ ጋር ተዋድደው ይኖሩ ነበር፡፡ ነገር ግን እቴጌ ጣይቱ ቀልዳቸውንና ተረባቸውን አልወደዱላቸውም፡፡ በዚህም የተነሳ ሁለት ጊዜ ተጣልተው ወደ ደብረ ታቦር ሄደዋል፡፡ በሶስተኛው ዙር ግን ከአጼ ምኒልክም ጋራ ተቀያይመው ኖሮ እስከ መጨረሻው ተሰነባብተው ወደ ትውልድ ቄየአቸው ከሄዱ በኋላ እዚያው ኖረው በሰማኒያ አራት ዓመታቸው አርፈዋል፡፡

  አለቃ ገብረሃና መልከ መልካም ቢሆኑም አጭር ሰው ነበሩ፡፡ በዚህ ቁመታቸውም ከሌሎች ጋራ ብዙ ጊዜ ተቋስለዋል፡፡ አንዳንዶች ደግሞ በእግራቸው መንሻፈፍ ሊቀልዱ ሲሞክሩ አለቃ ያልጠበቋቸውን መልሶች እየሰጧቸው “ኩም” ያደርጓቸው ነበር፡፡

   አለቃ ወይዘሮ ማዘንጊያ ከተባሉት ባለቤታቸው ተክሌ የተባለ ልጅ ወልደው ነበር፡፡ ይህ ልጃቸው በትምህርት ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሶ የደብረ ታቦር እየሱስ ጉባኤ ቤተ ክርስቲያን ካህን እስከ መሆን ደርሷል፡፡ ሆኖም ጠላቶቹ ተመቀኝተውት መድኃኒት በጥበጠው በማጠጣት ገድለውታል፡፡
   *****
    በአለቃ ገብረሃና ስም የሚነገሩ ብዙ ጨዋታዎችና ቀልዶች አሉ፡፡ አንዳንዶቹ በርሳቸው የተነገሩ መሆናቸው የተጻፈ ቢሆንም አንዳንዶቹ በጊዜ ሂደት የተፈጠሩ ናቸው፡፡ ለበረካ ያህል በርሳቸው ስም የሚነገሩ ጥቂት ጨዋታዎችን እንቋደስ፡፡

   አንድ ጊዜ አለቃ ለግብዣ ተጠሩ፡፡ በግብዣው የቀረበው ጎመን ሆዳቸውን ቆዝሮአቸው ኖሮ ወደ እሳት ዳር ተጠጉና ሆዳቸውን ማሻሸት ጀመሩ፡፡ ጋባዣቸው ነገሩ ገርሞት “ምነው አለቃ! ሆድዎትን ምን ሆነው ነው” ሲላቸው “ረ ምንም አይደለም! ጎመኑን እያበሰልኩት ነው” በማለት መለሱላቸው፡፡

  በሌላ ጊዜ ደግሞ አለቃ የታመመ ሰው ሊጠይቁ ይሄዳሉ፡፡ የቤቱ ባለቤት ጠላ ትሰጣቸውና ታቀርብላቸዋል፡፡ አለቃ ጠላውን ፉት እያሉት ሳሉ ሴትዮዋ አመለጣት፡፡ አለቃ ጠላቸውን አገባደው ሲጨርሱ ሴትዮዋ ወደርሳቸው መጣችና “ልድገምዎት እንዴ አለቃ” በማለት ጠየቃቸው፡፡ አለቃም “አዎ! ግን እንደ ቅድሙ ጠረር አታድርጊው” አሏት፡፡

    አለቃ ስንቃቸውን በአገልግል ይዘው ከጥቂት ነጋዴዎች ጋር የዐባይ በረሃን በማቋረጥ ላይ ሳሉ ሽፍቶች በአካባቢው እንዳሉ ይሰማሉ፡፡ ነጋዴዎቹም ለገንዘባቸው አለቃም ለነፍሳቸው ተጨነቁ፡፡ “ምን እናድርግ” እያሉ በመመካከር ላይ ሳሉ አለቃ አንድ ዘዴ ትዝ ይላቸውና ነጋዴዎቹ ገንዘባቸውን እንዲሰጧቸው ይጠይቁአቸዋል፡፡ ነጋዴዎቹም የተጠየቁትን አደረጉ፡፡ አለቃም ገንዘቡን ከአገልግላቸው ውስጥ ከተቱት፡፡

    ጥቂት እንደተጓዙ ሽፍቶቹ ከጫካ ውስጥ ወጥተው “ያላችሁን ቁጭ አድርጉ” ይሏቸዋል፡፡ ነጋዴዎቹ ምንም የለንም ይላሉ፡፡ ሽፍቶቹ ወደ አለቃ ዞረው “በአገልግሉ ውስጥ ያለው ምንድነው” ብለው ጠየቋቸው፡፡ ብልሃተኛው አለቃ “ወላሂ! ወላሂ! ክሽን ያለች የዶሮ ወጥ ናት! ከፈለጋችሁ እዚሁ እንብላ” ብለው መለሱ፡፡ ሽፍቶቹም “በስመ አብ! እኛ የእስላም ስጋ አንበላም” እያሉ በማማተብ ለቀቋቸው፡፡
------
አፈንዲ ሙተቂ)
ታሕሳስ 2007

ሰለዋት ከልዩ ልዩ አካባቢዎች





(አፈንዲ ሙተቂ)


-----አንድ--ኡምዱርማን (ሱዳን)---

አሕመድ ያ ሐቢቢ ሰላም ዐለይከ
ያ ሚስኪ ወጢቢ ሰላም ዐለይከ
ሰላም ዐለይከ ዘይነል አንቢያእ
ሰላም ዐለይከ አትቀል አትቂያእ
ሰላም ዐለይከ አስፈል አስፊያእ
ሰላም ዐለይከ ሚን ረብቢ ሰማእ
ሰላም ዐለይከ ዳኢማን ቢላ ኢንቲሃእ

------ሁለት--ገለምሶ---
1.      ሙሐመድ ሰላሙን ዐለይኩም
ሰይዲ ሰላም ዐለይኩም
ሰለዋቱላህ ዐለይኩም

2.     አላሁመ ሰሊ ዐላ ሰይዲና ሙሐመዲን ወዐላ ኩልሊ ነቢዪን
ወሰልሊ ዐላ አቢበክሪን ወዐላ ኩልሊ ወሊዪን
ወሰልሊ ዐላ ጂብሪለን ወዐላ ኩሊ መለክ

----ሶስት-- ጅማ---

አላህ አላህ ላኢላሀ ኢልለላህ
 ሙሐመዱን ረሱሉላሂ ሐቢቡ ዒንደላህ
ዐለይሂ ሰላቱ ወሰላሙ ሚነልላህ

----አራት-- ጅቡቲ----

ሰላዋቱልላህ ዐለይከ ያ ሙሐመድ
ሰላሙልላህ ዐለይከ ያ ሙሐመድ
ሰላሙልላሂ ያ ኑረል ቁሉቢ
ያ ኑረል ቁሉቢ

----አምስት-- ሐረሪ-----

ሰሊ ያ ረብቢ ዐላ ሙሐመዲን
ሰሊም ያ ረብቢ ዐላ ሙሐመዲን
ባሪክ ያ ረብቢ ዐላ ሙሐመዲን
ኩሉ የውሚን ወለያሊን አልፈ መር

----ስድስት-- ወሎ----- 

ሰላቱ ወተስሊሙ ወ አዝካ ተሒቲን
ዐለል ሙስጠፈል ሃዲ ጣሃ ያ ሙሐመዲን
--------------------------------------------