Friday, December 19, 2014

አምር ኢብን ኣስ እና “ፉስጣጥ” (ክፍል ሁለት)




ጸሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ
-----

የጥንት ግብጻዊያን አንድ ልማድ ነበራቸው፡፡ በየዓመቱ ቆንጆ ልጃገረድ ይመርጡና ለአባይ ወንዝ (ኒል/ናይል) ይሰውለት ነበረ፡፡ እነዚያ ግብጻዊያን ናይል በየዓመቱ መስዋዕቱን ካላገኘ ውሃውን ይቋጥርብናል የሚል እምነት ነበራቸው፡፡ አምር ኢብን ኣስ ሀገሪቱን በያዘ በጥቂት ወራት ውስጥም ግብጻዊያኑ ለወንዙ መስዋእቱን ለማቅረብ እንደሚፈልጉ ነገሩት፡፡ አምር ጉዳዩን ለብቻው ለመወሰን ባለመቻሉ ለኸሊፋው ዑመር ቢን ኸጣብ ደብዳቤ በመጻፍ አንድ ነገር እንዲያደርጉ ጠየቃቸው፡፡ ዑመርም “እንዲህ ዓይነት ኢሰብአዊ የሆነ ድርጊት መከወን በጭራሽ አይፈቀድም” በማለት ውሳኔያቸውን አሳወቁት፡፡ አምርም ለግብጻዊያኑ ይህንኑ ነገራቸው፡፡ በመሆኑም ለናይል ወንዝ ልጃገረድ የመሰዋቱ ድርጊት ተከለከለ፡፡

ታዲያ በዚያ ዓመት የናይል ወንዝ ፍሰት በጣም ቀነሰ፡፡ ግብጻዊያኑም በተፈጠረው ሁኔታ ተጨነቁ፡፡ ወደ አምር በመሄድም “ወንዙ ፍሰቱን የቀነሰው የዓመቱን መስዋእት ስላላገኘ ነው፤ ስለዚህ ልጅቷን እንድንሰዋለት ይፈቀድልን”  በማለት ወጠሩት፡፡ አምርም የተፈጠረውን ሁኔታ ለኸሊፋ ዑመር በደብዳቤ አሳወቃቸው፡፡ ይሁንና ኸሊፋው አቋማቸውን የሚቀይሩ አልሆኑም፡፡ ስለዚህ የሚከተለውን መልዕክት በደብዳቤ አስጻፉ፡፡

  “ይድረስ የአላህ ፍጥረት ለሆነው የናይል ወንዝ! በአላህ ፈቃድ የምትፈስ ከሆነ እንደ ድሮው እንድትፈስልን አላህን እንለምናለን፤ በራስህ ፈቃድ የምትፈስ ከሆነ ግን ውሃህን መያዝ ትችላለህ፤ እኛም አንፈልግህም፡፡”

ዑመር ደብዳቤውን ለአምር በመላክ በወንዙ ውስጥ እንዲጨምረው አዘዙት፡፡ አምርም ግብጻዊያኑን ሰብስቦ መልዕክቱን አነበበላቸውና ኸሊፋው ያዘዙትን ፈጸመ፡፡ ከትንሽ ወራት በኋላም ናይል በሙሉ አቅሙ መፍሰስ ጀመረ፡፡ ግብጻዊያኑም ወንዙ በራሱ ሃይል እንደማይፈስ በማረጋገጥ ከፈርዖኖች ዘመን ጀምሮ ሲፈጽሙት የነበረውን አጉል ድርጊት አስወገዱ፡፡
       *****
በዚያ ዘመን የግብጽ ዋና ከተማ እስክንድርያ ነበረች፡፡ እስክንድርያ በባህር ላይ የተቆረቆረች መሆኗ ይታወቃል፡፡ በመሆኑም ሮማዊያን በባህር በመምጣት ከተማዋን በድንገተኛ ጥቃት ሊያጠፏት እንደሚችሉ የተገነዘበው አምር ቢን ኣስ በውስጠኛው የሀገሪቱ ክፍል አዲስ መዲና ለመቆርቆር ወሰነ፡፡ ለዚህ የተመረጠው ደግሞ ከእስክንድርያ በ200 ኪ.ሜ. የሚርቅ ቦታ ነው፡፡ አምርም አዲሷን ከተማ በ641 መሰረተ፡፡ መስጊድ፣ ለቢሮ የሚያስፈልጉ ቤቶች፣ መኖሪያ ቤቶች፣ የወታደሮች ካምፕ ወዘተ በከተማዋ ውስጥ ተሰሩ፡፡ ለከተማዋም “ፉስጣጥ” የሚል ስም ተሰጠ፡፡

ፉስጣጥ በናይል ወንዝ ምስራቃዊ ዳርቻ ላይ በነበረችው በሮማዊያኑ የ“ባቢሎን” ከተማዋ ጎን ነው የተሰመረተችው፡፡ ይህች ከተማ ለሶስት መቶ ዓመታት የግብጽ ዋና ከተማ በመሆን አገልግላለች፡፡ በነዚያ ዓመታት በሙስሊሞች የኺላፋ ግዛት ግንባር ቀደም ከሆኑ የትምህርትና የንግድ ማዕከላት አንዷ ነበረች፡፡ የእስልምና ስነ-መለኮት ህግ (ፊቅህ) ሊቅና የሻፊዒያ መዝሐብ መስራች የነበሩት ታላቁ ምሁር ሙሐመድ ኢብን ኢድሪስ አሽ-ሻፊዒ በመጨረሻ የህይወት ዘመናቸው የኖሩትና የሞቱት በዚህች ከተማ ነው፡፡ ታዋቂው የታሪክ ምሁር ዓሊ ኢብን ሁሴይን አል-መስዑዲም አብዛኛውን ህይወቱን ያሳለፈውና ሞቶ የተቀበረው በፉስጣጥ ነው፡፡
       *****
በ910 ገደማ በምድረ-ግብጽ የተመሰረተው የፋጢሚይ ስርወ መንግሥት (Fatimid Dynasty) መሪዎች ፉስጣጥን አልወደዷትም፡፡ “ከተማዋ ቅርጽ ቢስ ስለሆነች ውብ ፕላን ያላት ዋና ከተማ ሊኖረን ይገባል” በማለት በ967 ከፉስጣጥ በስተሰሜን 30 ኪሎሜትር ያህል በሚርቅ ቦታ ላይ አዲስ ዋና ከተማ መሰረቱ፡፡ ለአዲሷ ከተማም “አል-ቃሂራ (Cairo) የሚል ስም ሰጡ፡፡ ፉስጣጥም ዝናዋንና እውቅናዋን በአዲሷ ከተማ ተቀማች፡፡

ያም ቢሆን ግን ፉስጣጥ የንግድ ማዕከል በመሆን መስራቷን ቀጥላለች፡፡ ለዚህም የረዷት በከተማዋ ተስፋፍተው የነበሩት የመስተዋት፣የልብስና የሸክላ ስራ ኢንዱስትሪዎች ናቸው፡፡ በ1168 የመስቀል ጦረኞች (Crusaders) ግብጽን ሲወሩ የከተማዋን ህልውና የሚፈታተን አደጋ ተደቀነ፡፡ ከተማዋ እንደሌሎች የመካከለኛ ዘመን ከተሞች የመከላከያ ግንብ አልነበራትም፡፡ ስለዚህ የግብጽ መሪዎች ከተማዋ በጦረኞቹ እጅ ከምትወድቅ ብትቃጠል ይሻላል በማለት ነዋሪቿን ወደ ካይሮ ካዘዋወሩ በኋላ የአምር ቢን ኣስ መስጊድ ካለበት ክፍል በስተቀር የተቀረውን የከተማዋን ክፍል አቃጠሉት፡፡

    ከጥቂት ዓመታት በኋላ ግን ፉስጣጥ በእዉቁ የጦር ጀግና በሰላሃዲን አዩቢ ትዕዛዝ መሰረት እንደገና አንሰራርታለች፡፡ ሆኖም ሰላሃዲን ከተማዋ ለብቻዋ እንድትጓዝ አልፈለገም፡፡ በክፉም ሆነ በደጉ ከዋና ከተማዋ ጋር መሄድ አለባት በማለት ከካይሮ ከተማ ጋር እንድትዋሃድ መሰረቱን ጣለ፡፡ በመሆኑም ጥንት ለብቻዋ የከተመችው ፉስጣጥ እያደር በአዲሷ የካይሮ ከተማ ተዋጠች፡፡

  “ፉስጣጥ” በአሁኑ ጊዜ “መስር አል-አጢቃ” የሚባለው የካይሮ ከተማ ጥንታዊ ክፍል አካል ናት፡፡ የጥንቱ የአምር ቢን ኣስ መስጊድ ወደ ካይሮ ሊገባ የቻለውም ከተማዋ በካይሮ በመጠቅለሏ ነው፡፡
-----
አፈንዲ ሙተቂ
ህዳር 4/2007

Thursday, December 18, 2014

አምር ኢብን ኣስ እና “ፉስጣጥ” (ክፍል አንድ)




ጸሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ
-----
በፎቶው ላይ የምትመለከቱት ለአፍሪቃ አህጉር የመጀመሪያ የሆነውን መስጊድ ነው፡፡ ይህ መስጊድ የተሰራው በ641 ሲሆን የሚገኘውም በግብፅ መዲና ካይሮ ውስጥ ነው፡፡ መስጊዱ የሚጠራው በመስራቹ በ“አምር ኢብን ኣስ” ስም ነው፡፡ ይሁንና አምር እና ጓዶቹ መስጊዱን የሰሩት በአል-ፉስጣጥ እንጂ በካይሮ አልነበረም፡፡ ታዲያ መስጊዱን ወደ ካይሮ ማን ነው ያስገባው?… እስቲ የዛሬ ወጋችንን በአምር ታሪክ እንጀምርና ስለፉስጣጥም ትንሽ እናውራ፡፡
       *****
አምር ኢብን ኣስ የዐረቢያ ምድር ካበቀለቻቸው ታላላቅ ፖለቲከኞችና የጦር መሪዎች አንዱ ነው፡፡ የተወለደው በመካ ከተማ ሲሆን ነቢዩ ሙሐመድን (ሰ.ዐ.ወ) ያፈራው የቁረይሽ ጎሳ አባል ነው፡፡ አምር የጉርስምና ዘመኑን እንደ ሌሎቹ የዐረቢያ ወጣቶች በግመል ግልቢያና በፈረስ ጉግስ አላሳለፈም፡፡ የርሱ ቀልብ ወደ ንግዱ ነበር ያተኮረችው፡፡ በመሆኑም  በዘመኑ በገበያ ውስጥ ተፈላጊ የሆኑ ሸቀጦችን ለማምጣት ወደ የመንና ሻም (ሶሪያ) በብዛት ይመላለስ ነበር፡፡ ሀብቱ እየተስፋፋ ሲሄድ ደግሞ እስከ ፋርስ (ፐርሺያ)፣ መስር (ግብፅ)፣ አቢሲኒያ (ሐበሻ/ኢትዮጵያ) እና ኦማን ድረስ እየሄደ ሸቀጦችን ያመጣ ጀመር፡፡ በነዚህ ሀገራትም በርካታ የንግድ ሸሪኮችን ለመፍጠር ቻለ፡፡ በሸሪኮቹ በኩልም ከየሀገራቱ ገዥዎች ጋር በመተዋወቅ ልዩ ልዩ ገጸ-በረከቶችን ይወስድላቸው ነበር፡፡

Mosque of Amr in Old Cairo in 19th Century


ይህ በእንዲህ እንዳለ ነቢዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) በ610 ገደማ እስልምናን ማስተማር ጀመሩ፡፡ የዐረብ ጎሳዎች የድንቁርና ህይወታቸውን ትተው እንደ ጥንቱ ቅድመ-አያቶቻቸው እንደ ነቢዩ ኢብራሂምና እንደ ዒስማዒል ፈጣሪን ብቻ እንዲገዙ ሰበኩ፡፡ ጥቂት ሰዎች እምነቱን ተቀበሉ፡፡ አብዛኞቹ ግን “የአባቶቻችንን መንገድ ልታስተወን ነው እንዴ…?” በማለት በነቢዩ ላይ በጠላትነት ተነሱባቸው፡፡ በነቢዩ ያመኑትንም ያሰቃዩ ጀመር፡፡ ነቢዩ በተከታዮቻቸው ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ሊከላከሉላቸው አልቻሉም፡፡ ስለዚህ ከተከታዮቻቸው መካከል የተወሰኑትን በሚስጢር ጠርተው ወደ ሐበሻ (ኢትዮጵያ) እንዲሰደዱ አዘዟቸው፡፡ በዚሁ መሰረት አንድ መቶ የሚሆኑ ሰዎች ወደ ሐበሻ ተሰደዱ፡፡

የቁረይሽ ባላባቶች የነብዩ ተከታዮች ወደ ሐበሻ መሰደዳቸውን ሲሰሙ “እዚያ ሄደው ሳይደራጁ በቶሎ ልናስመልሳቸው ይገባል” በማለት አንድ የልዑካን ቡድን ወደ አክሱም ሰደዱ፡፡ ቡድኑ ሁለት አባላት የነበሩት ሲሆን እነርሱም አምር ቢን ኣስ እና አብዱላህ ቢን ረቢዓ ናቸው፡፡ ያ ቡድን በሚችለው መንገድ ሁሉ ተደራድሮ የሐበሻውን ንጉሥ አርማህን (አስሓማ) በማሳመን የነቢዩን ተከታዮች ወደ መካ እንዲያስመልስ ታዟል፡፡ ነገር ግን ወደ ሐበሻው ንጉሥ ቀርቦ ድርድሩን እንዲፈጽም ስልጣን የተሰጠው ለአምር ቢን ኣስ ነው (አብዱላህ ቢን ረቢዓ “አምር” መልዕክቱን በትክክል ማድረሱን እንዲታዘብ ብቻ የተላከ ነው የሚመስለው)፡፡

አምር በንግድ ሰበብ ወደ ኢትዮጵያ በተመላለሰባቸው ዓመታት ከሐበሻው ንጉሥ ጋር ለመተዋወቅ ችሏል፡፡ ሆኖም አምር ለድርድሩ የተመረጠው በዚህ ብቻ ሳይሆን በዘመኑ ከነበሩት የመካ መኳንንት መካከል ተናግሮ በማሳመን ብቃቱ የተዋጣለት ሆኖ በመገኘቱም ጭምር ነው፡፡
       *****
አምር ከንጉሡ ዘንድ ቀርቦ ባደረገው ድርድር ያሰበው አልተሳካለትም፡፡ ንጉሡ ስደተኞቹን ለማንም አሳልፎ እንደማይሰጥ እቅጩን ነግሮታል፡፡ ይሁንና አምር በዚህ ተበሳጭቶ ወደ አክሱም መምጣቱን አላቆመም፡፡ ከድርድሩ በኋላም ቢሆን ለሁለት ጊዜያት ወደ ሐበሻ መጥቷል፡፡ ታዲያ ለመጨረሻ ጊዜ ከንጉሡ ጋር በተገናኘበት ጊዜ ንጉሡ እንዲህ ሲል መከረው፡፡

  “አምር ሆይ! አንተን የመሰለ ሰው የነቢዩ ሙሐመድን ትምህርት አልቀበልም ሲል ይገርመኛል፡፡ እናንተ ዐረቦች ከማንኛውም ህዝብ ወደ ኋላ ቀርታችኋል፤ ሙሐመድ ያመጣው ዐረቢያን ከጭለማ የሚያወጣውን አዲስ ብስራት ነው፡፡ በእርሱ ያመነ ሰው በፈጣሪ ዘንድ ከሚያገኘው ምንዳ በተጨማሪ ይህችን ዓለም ይገዛል፡፡”

ንጉሥ አርማህ አምርን እንዲህ ብሎ በሚመክርበት ጊዜ ለራሱም የነቢዩን እምነት ተቀብሏል፡፡ ይሁንና መላው የሐበሻ ህዝብ አዲሱን እምነት እንዲቀበል አዋጅ አልነገረም (አንዳንድ ጸሐፊያን “ንጉሥ አርማህ በነቢዩ ማመኑን በሚስጢር ይዞት ነበር” ይላሉ)፡፡
       *****
አምር ከሐበሻው ንጉሥ ከተለየ በኋላ በቀጥታ ወደ መካ ነው ያመራው፡፡ እዚያም ታዋቂው ጀግና ኻሊድ ቢን ወሊድ (ረ.ዐ) ወደ መዲና ለመሰደድ ሲዘጋጅ አገኘውና ከርሱ ጋር መሄድ እንደሚፈልግ ነገረው፡፡ ኻሊድም ሀሳቡን በደስታ ተቀበለው፡፡ ሁለቱ ሰዎች መዲና በደረሱ ጊዜ ነብዩ ሁለቱንም ሸሃዳ አስያዟቸው፡፡ ይሁንና ነቢዩ እነዚህን የዐረቢያ ጎምቱዎች አላሳረፏቸውም፡፡ ኻሊድን በሰሜን በኩል በነቢዩ መንግሥት ላይ አደጋ የጋረጡትን ሮማዊያንን ለመዋጋት በሚዘምተው የዘይድ ቢን ሓሪሳ ቡድን ውስጥ ቀላቀሉት፡፡ አምር ቢን ኣስ ደግሞ ወደ ኡማንና ባህሬን ሄዶ የዲፕሎማሲ ስራ እንዲሰራ አደረጉት፡፡ አምር ወደ ኡማን (ኦማን) የተጓዘው እነ አቡበከር፣ ዑመር እና አቡ ኡበይዳን (ረ.ዐ) የመሳሰሉ ታላላቅ ሰዎች የተካተቱበትን ቡድን በመምራት ነው፡፡ ነቢዩ አምር የቡድኑ መሪ እንዲሆን ያደረጉት የዲፕሎማሲ ችሎታውን በሚገባ ያውቁት ስለነበረ ነው፡፡ አምርም የዲፕሎማሲ ስራውን በደንብ ከመፈጸሙም በላይ የኦማን ሰዎች ወደ እስልምና እንዲገቡ ለማድረግ ችሏል፡፡
       *****
አምር ከነቢዩ ህልፈት በኋላም በአቡበከርና በዑመር ኺላፋዊ መንግሥት ውስጥም አገልግሏል፡፡ በጦር ግንባርም ሆነ በዲፕሎማሲ ስራ አንቱታን ያጎናጸፉትን ተግባራት ፈጽሟል፡፡ ከአምር ጋር የሁልጊዜ ተጠቃሽ ሆኖ የዘለቀው ግን ሮማዊያንን ከግብጽ በማባረር ወደ ኸሊፋዎቹ ግዛት የቀላቀለበት ዘመቻው ነው፡፡

አምር የግብጽን ዘመቻ (the conquest of Egypt) ያመነጨው በራሱ ነው ይባላል፡፡ በመሆኑም ኸሊፋ ዑመር ቢን ኸጣብ ሐሳቡን ተቃውመውት ነበር፡፡ የዑመር ተቃውሞ ዘመቻውን በመጥላት ሳይሆን “በተለያዩ ግንባሮች የተበተኑትን ወታደሮቻችንን በቶሎ አሰባስበን በዘመቻው እንዲሳተፉ ለማድረግ አንችልም” ከሚል የመነጨ ነው፡፡ ይሁንና አምር በወቅቱ በነበሩት ወታደሮች ብቻ ዘመቻውን በመጀመር ተጨማሪ ጦርን መጠባበቁን ነው የመረጠው፡፡
 
  አምር በ639 ዓ.ል በአራት ሺህ ወታደሮች የሲናይ በረሃን አቋረጠ፡፡ ሮማዊያንን በድንገተኛ ጥቃት በማራወጥ “ቢልቢስ” እና “ባቢሎን” በሚባሉት ስፍራዎች አሸነፋቸው (ይህቺ የግብጿ “ባቢሎን” የኢራቋ “ባቢሎን” አምሳያ እንድትሆን በሮማዊያን የተፈጠረች ናት)፡፡ ከጥቂት ወራት በኋላ ደግሞ በጥንቷ የኦኑ ከተማ (በፈረንጆች አጠራር Heliopolis) አጠገብ አሸነፋቸው፡፡ ከአንድ አመት በኋላ 12,000 ወታደሮች ከሶሪያ ሲመጡለትም አምር የዘመኑ የአፍሪቃ ታላቅ ከተማ የነበረችውን እስክንድርያን (አሌክሳንደሪያ) ለመያዝ ዘመተ፡፡ ሮማዊያን በከተማዋ ከሰማኒያ ሺህ የሚበልጥ ጦር የነበራቸው ቢሆንም ከነርሱ በአምስት እጥፍ በሚያንሰው የአምር ቢን ኣስ ጦር ድል ተመቱ፡፡ ግብጽም ሙሉ በሙሉ የሙስሊሞቹ ኺላፋ አካል ሆነች፡፡

ታዲያ አምር ግብፅን በአንድ ዓመት ውስጥ ለመያዝ የበቃው በጦር ሃይሉ ጥንካሬ ብቻ አልነበረም፡፡ በወቅቱ የግብጽ ክርስቲያኖች ከፍተኛ እርዳታ ስላደረጉለት ጭምር ነው ታላቁን ድል ለማጣጣም የበቃው፡፡ ክርስትያኖቹ አምርን የደገፉበት ምክንያት አለ፡፡

  ግብጻዊያን ክርስቲያኖች የሚያምኑበት የ“ተዋሕዶ” እምነት “ክርስቶስ የሁለት ባህሪ ባለቤት ነው” ከሚለው የሮማዊያን ክርስትና ይለያል፡፡ በዚህም ምክንያት ሮማዊያኑ የግብጽ ክርስቲያኖችን እንደ “መናፍቃን” ያዩዋቸው ነበር፡፡ ከቁስጥንጥንያ (የአሁኗ ኢስታንቡል) ተሹመው ግብጽን የሚገዙት እንደራሴዎችም የግብጽ ክርስትያኖች እምነታቸውን እንዲለውጡ ለማድረግ በልዩ ልዩ መንገዶች ይጨቁኗቸው ነበር፡፡ አንዳንዴም ፓትሪያኮቻቸውን እያሰሩ “እምነትህን ተው” እስከማለት ይደርሳሉ፡፡ አምር ቢን ኣስ ግብጽን ለመያዝ በሚዘምትበት ዘመን እንኳ የግብጽ ፓትሪያርክ የነበሩት “አቡነ ብንያም” (ቤንጃሚን) ከሀገር ተባረው ነበር፡፡ በመሆኑም ግብጻዊያኑ ከጭቆናው ለመገላገል ሲሉ አምር ቢን ኣስን በዘመቻው በእጅጉ ረድተዋል፡፡ (በነገራችን ላይ ከ5ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ጀምሮ ግብጽን ይገዟት የነበሩት ሮማዊያን መቀመጫውን በሮም ከተማ ያደረገው የታላቁ ኢምፓየር አካል አልነበሩም፡፡ የሮም ኢምፓየር በ395 “ምስራቅ” እና “ምዕራብ” ተብሎ ለሁለት ተከፍሏል፡፡ የሮማ ከተማ በ476 በጀርመን ጎሳዎች ስትወረር የምዕራቡ ኢምፓየር ህልውና አክትሟል፡፡ የምስራቁ ኢምፓየር ግን እስከ 1431 ድረስ ቆይቷል፡፡ ብዙዎች የምስራቁን ኢምፓየር የሚጠሩት “ቤዛንታይን” በሚል ስም ነው፡፡ ሆኖም ዐረቦችም ሆኑ የኢምፓየሩ ነዋሪዎች ግዛቱን “ሮም” እያሉ ስለሚጠሩት እኔም ይህንን ልማድ ተከትያለሁ)፡፡  

  አምር ግብጽን በሚያስተዳድርበት ጊዜ በክርስትያኖቹ ላይ ይደርስ የነበረውን ጭቆና ሙሉ በሙሉ አስወግዷል፡፡ በህዝቡ ላይ በየምክንያቱ ይጣሉ የነበሩትን ልዩ ልዩ የታክስ ዓይነቶች በማስቀረት ሁሉም ዜጎች ዓመታዊውን “ዑሽር” (አስራት) እና “ዘካት” ብቻ እንዲከፍሉ አድርጓል፡፡ በመንግሥቱ ቢሮክራሲ ውስጥም ክርስትያኖቹን አሳትፏል፡፡ የቤተ-ክርስቲያኖች ይዞታ የሆኑ መሬቶችና ንብረቶች እንዲከበሩም አድርጓል፡፡
       *****
 አምር ቢን ኣስ ግብጽን ማስተዳደር በጀመረ በዓመቱ ነው “አል-ፉስጣጥ” የተባለችውን ከተማ የቆረቆረው፡፡ ስለ“አል-ፉስጣጥ” ምስረታና ስለሌሎች ጉዳዮች በሚቀጥለው ክፍል እናወጋለን፡፡
---
አፈንዲ ሙተቂ
ህዳር 3/2007
ገለምሶ-ሀረርጌ

የህንድ ፊልም ትዝታ




አፈንዲ ሙተቂ
      -----
      የህንድ ፊልም ማየት የጀመርኩት በ1978 ይመስለኛል፡፡ በዘመኑ ቶማስ የሚባል የህንድ ክልስ ነበር፡፡ ይህ ሰው ፊልሞቹን ከድሬ ዳዋ ያስመጣና በሌሎች የሀረርጌ ከተሞች እያዞረ በፕሮጀክተር ያሳያል፡፡ በዘመኑ “የአሜሪካ ፊልም ውሸት ነው፤ የህንድ ፊልም እውነት ነው” የሚል አስተሳሰብ ስለነበረ የሰዎች ምርጫ በአብዛኛው የህንድ ፊልም ነበር፡፡ በመሆኑም ቶማስ ከሚያሳያቸው ፈልሞች መካከል ከመቶ ዘጠና የሚሆኑት የህንድ ፊልሞች ነበሩ፡፡ 

   በዚህም መሰረት ለመጀመሪያ ጊዜ ያየሁት የህንድ ፊልም “T.D” የሚል ርዕስ የነበረው ሲሆን አክተሩም “ጄተንድራ” ነው (በኋላ ላይ እንደተረዳሁት ያ ፊልም First Blood  ከሚባለው የራምቦ ፊልም የተቀዳ ነው)፡፡ ቶማስ ፊልሙን የሚያሳየው በሁለት ብርና በሶስት ብር ነው፡፡ በቶማስ ሲኒማ ስር ካየኋቸው ሌሎች የህንድ ፊልሞች መካከል Disco Dancer, Jimmy and His Elephant, Mard የተሰኙት ይታወሱኛል፡፡  

        በ1981 የአውራጃችን አኢወማ ቪዲዮ ሲያስመጣ ግን የቶማስ ሲኒማ “በጣም ውድ ነው” በሚል ተረሳ፡፡ ቶማስም ወደኛ መምጣቱን ተወ፡፡ በዚህም መሰረት Mister India, Ashanti, Kassam Paeda, Love Story, የመሳሰሉ ፊልሞችን በአኢወማ አየን፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ደግሞ “ፎቶ ማወርዲ” የሚባለው ፎቶ ቤት ሌላ ቪዲዮ ማሳያ ከፈተና ከአኢወማ ጋር ፉክክር ውስጥ ገቡ፡፡ ሁለቱም በርካታ ፊልሞችን አስኮመኮሙን፡፡ በፎቶ ማወርዲ ካየኋቸው ፊልሞች መካከል “Ter Kassam”, “Maa Kassam”, “Numberi Admi”, “Khoj”, “Marry Kassam”, “My Name is Lakan”, “Tarzan”, “Coolie”, የሚባሉትን ከነ ስሞቻቸው አስታውሳቸዋለሁ፡፡ የብዙዎቹን ስም ግን አላስታውስም፡፡
*****  *****  *****
        በህንድ ፊልሞች የምናውቃቸው አክተሮች በከተማችን በትክክለኛ ስማቸው አልነበረም የሚጠሩት፡፡ አንዳንዶቹ እኛ ባወጣንላቸው ስሞች ነው ይበልጥ የሚታወቁት፡፡ ለምሳሌ “ሚቱን ቻካርቦርቲ” የሚባለው አክተር “ጂሚ” በሚለው ስም ነው የሚታወቀው፡፡ “ዳርሜንድራም” በኛ አጠራር “ሻንካር” ነው የሚባለው፡፡ “ሪሽ ካፑር” ደግሞ “ኮጅ” እየተባለ ነው የሚጠራው፡፡ እውነተኛ ስሙ “ሰኒ” የሆነው አክተር ደግሞ በኛ አጠራር “ገባር” ነው የሚባለው፡፡ “አጄይ ኩማር”ም “ላቭ ስቶሪ” ተብሎ ነበር የሚጠራው፡፡ ከነዚህ ስሞች መካከል አንዳንዶቹ (እንደ “ጂሚ” እና “ሻንካር” ያሉት) አክተሩ ታዋቂ በሆነበት ፊልም ውስጥ ከሚጠራበት ስም ነው የተወሰዱት፡፡ እንደ “ኮጅ” እና “ላቭ ስቶሪ” የመሳሰሉት ደግሞ አክተሮቹ የተወኑባቸው ፊልሞች አርዕስት ናቸው፡፡    

        ከዚህ ሌላ አክተሩ በፊልሙ ውስጥ ሲያንጸባርቀው የነበረውን ድርጊት በመመልከት የተሰጡ ስሞችም አሉ፡፡ ለምሳሌ “አኒል ካፑር” የሚባለው አክተር በአንድ ፊልም ውስጥ ያለ ማቋረጥ “ማስቲካ” ያኝክ ስለነበረ “ማስቲካ” ተብሎ ተሰይሟል፡፡ “ቆሮንዴ” ደግሞ “Sholay” በተሰኘው የአሚታብ ባችቻን ፊልም ውስጥ በአፍ የሚታኘክ ትምባሆ ስለሚጠቀም ነው እንዲህ ተብሎ የተጠራው (“ቆሮንዴ” በአፍ የሚታኘክ የትምባሆ ዐይነት ነው)፡፡ እንደ ከማል ሐሰን፣ ነስሩዲን፣ አሚታብ ባችቻን፣ ሻሽ ካፑር፣ ጄክ ሸሪፍ፣ ጎቪንዳ፣ ሳንጃይ የመሳሰሉትን ግን በትክክለኛ ስማቸው ነው የምንጠራቸው፡፡

     ታዲያ በጣም ያስገረመኝ ይህ በኛ ከተማ የምንጠቀምበት የስም አጠራር ዘይቤ ድሬ ዳዋና ሀረርን ጨምሮ በሌሎች ከተሞችም በስፋት የሚታወቅ መሆኑ ነው፡፡ በዚህ ዙሪያ ያደረግኩት ጥናት እንደሚያመለክተው ከስሞቹ መካከል አንዳንዶቹን እኛ መፍጠራችን ትክክል ቢሆንም ሌሎቹ ስሞች ከድሬ ዳዋ ልጆች የተኮረጁ ናቸው፡፡

      በድሮው ዘመን “አክተር” የምንለው በፊልሙ ውስጥ መልካም ስብዕና የሚያሳየውን ብቻ ነው፡፡ እኩይ ባህሪ ተላብሶ የሚተውነው በኛ ቋንቋ “ሙጅሪም” ነው የሚባለው፡፡ በአንደኛ ደረጃ ከሚነሱ ሙጅሪሞች መካከል “አሻንቲ”፣ “ሻክቲ”፣ “ጃሉ”፣ “ሼራ”፣ “ቆሮንዴ”፣ “ፋሩቅ” የመሳሰሉት ይጠቀሳሉ (ፋሩቅ Disco Dancer በተሰኘው ዝነኛ የጂሚ ፊልም ውስጥ የተወነው ወፍራም ሙጅሪም ነው፤ አስታወሳችሁት አይደል?)፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ከሚመደቡ ሙጅሪሞች መካከል ደግሞ “ሳምሶን መላጣ” እና “መለኪያ” የተባሉት ይጠቀሳሉ:: እነዚህኛዎቹ ሙጅሪሞች በአብዛኛው በታላላቆቹ ሙጅሪሞች እየታዘዙ ጥፋት የሚፈጽሙ ናቸው፡፡ ከማል ሐሰንም ሲያሻው ከነዚህ ጋር ይደመርና ሙጅሪም ይሆናል፡፡

      በህንድ ፊልም ውስጥ ዘወትር የሚታይ ሶስተኛ አክተር አለ፡፡ ይህ ሰው በፊልሙ ውስጥ የሚሰጠው ሚና እንደ ቤተሰብ አጫዋች ሆኖ ሰዎችን ማሳቅ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ አስቂኝ ገጸ-ባህሪ በያኔው አጠራር “ማህሙዴ” ይባላል፡፡ እጅግ ዝነኛ ከሆኑ ማህሙዴዎች መካከል “ሻክቲ” ተጠቃሽ ነው (“ሻክቲ” ሲፈልግ “ሙጅሪም”፤ ሲያሻው ደግሞ ማሕሙዴ ይሆናል)፡፡
*****  *****  *****
        የህንድ ፊልም ልዩ ገጽታው በርካታ ዘውጎችን አንድ ላይ የሚደበላልቅ መሆኑ ነው፡፡ የአክሽን ፊልም ውስጥ ኮሜዲ አለ፣ አስማት አለ፣ ሮማንስ አለ፤ ዳንስ አለ፤ በአንዱ ፊልም ውስጥ ሁሉም ነገር ይገኛል፡፡ ደግሞም አክተሮቹ ሲደንሱ ድምጻቸው አንድ ዓይነት መሆኑ በጣም ያደናግራል፡፡ የሴትም ሆነ የወንድ ድምጽ ለመለየት ያስቸግራል፡፡

      ከዚህ በተጨማሪ የህንድ ፊልም ውስጥ የሚታየው ግነት ከፍተኛ ነው፡፡ ለምሳሌ Mard በተሰኘው ፊልም ውስጥ አሚታብ ለመብረር የሚያኮበኩበውን ሂሊኮፕተር በገመድ ጠልፎ እንዳይበር ያደረገበት ትዕይንት ዘወትር አይረሳኝም፡፡ በልጅነታችን ያንን ትዕይንት እንደ ጉድ ነበር ያጨበጨብንለት፤ አሁን ቢሆን ግን “አንተ ውሸታም! ሞኝህን ፈልግ ” ብዬ ቪዲዮውን የምዘጋው ይመስለኛል፡፡

      የህንድ ፊልም ሲነሳ ዘወትር የሚታወሱኝ ሁለት ልጆች አሉ፡፡ አንደኛው ታገል ዲሪብሳ ይባላል፡፡ ሌላኛውን ልጅ ግን ስላላስፈቀድኩት ስሙን አልነግራችሁም፡፡ ታገል ምን አደረገ መሰላችሁ?.

     የጄተንድራን ፊልም እያየን ነበር፡፡ በፊልሙ መሀል ላይ ሻክቲ የተባለው ሙጅሪም የጄተንድራን እህት በመኪና ካሯሯጣት በኋላ ይገድላታል፡፡ ትዕይንቱ በጣም ያሳዝናል፡፡ በተለይ ልጅቷ በደም አበላ ተነክራ ላያት ሰው ልብ ትሰብራለች፡፡ ይሁን እንጂ ብዙዎቻችን ፊልም መሆኑን አልሳትንም፡፡ ታገል ግን ከመመሰጡ ብዛት የእውነት ትዕይንት መሰለው፡፡ እናም ጮክ ብሎ “ህግ የለም እንዴ?” አለ፡፡ በቪዲዮ ቤቱ የነበረው ሰው ሁሉ በሳቅ ፍርስ አለ፡፡

      የሁለተኛው ሰው ማስታወሻዬ ግን ከዚህ ይብሳል፡፡ በጊዜው ከነበሩት የሀብታም ልጆች ነን ባዮች መካከል አንዳንዶቹ የለየላቸው ጅላጅሎች ነበሩ፡፡ አሪፍ መኪና ሲያዩ “የዘመዳችን ናት” ማለት ይቀናቸዋል፡፡ “ነዋይ ደበበ ቤታችን ሊመጣ ነው” የሚሉም ነበሩ፡፡ እኛም ለነዚህ ጅሎች ነገር እያሟሟቅን ብራቸውን እናጫርሳቸው ነበር፡፡ ከነዚያ ልጆች አንዱ “አሚታብ ዘመዳችን ነው” እያለ ያወራልን ነበር፡፡ እኛም እያወቅን እንሞኝለታን:: አብዛኛውን ጊዜ የፊልም መግቢያ ዋጋውን የሚከፍልልን እርሱ ስለሆነ ለርሱ መሞኘታችን የግድ ነበር፡፡

      ታዲያ በብዙ ፊልሞች ውስጥ ሲሞት የማይታየው “ጀግናው” አሚታብ ባችቻን ሲያቀብጠው Sholay በተሰኘው ፊልም መጨረሻ ላይ ሞተ፡፡ ነገሩ በጭራሽ ያልተገመተ በመሆኑ ብዙዎች ተገረሙ፡፡ “ጉድ ነው! አሚታብም ይሞታል እንዴ?”… ተባባልን፡፡ እኛ እንዲህ ያልነው “አሚታብ ወክሎት የሚጫወተው ገጸ-ባህሪ ዘወትር አይሞትም” ከሚል መነሻ ነበር፡፡ ያ የኛ ስፖንሰር የሆነው ልጅ ግን እየየውን አቀለጠው፡፡ “ዘመዴ ሞቶ የት አባቴ ነው የምገባው?” እያለ አነባ፡፡ ፊልም ለመመልከት የሄደው ሰው ግራ ተጋባ፡፡ ለምን እንደሚያለቅስ ብንነግራቸው ሁላችንንም እንደ ጅል ይቆጥሩናል ብለን ፈራን፡፡ ስለዚህ ቶሎ ብለን ልጁን ደጋግፈን ወደ ውጪ ካወጣነው በኋላ እያባበልነው ከቤታቸው ወሰድነው፡፡

   ይህ ትዕይንት በአሁኑ ዘመን ይከሰታል ተብሎ የማይታሰብ ነው መቼስ! ከዛሬ ሀያ አመት በፊት ግን ተመሳሳይ ድርጊቶችን ማየት የተለመደ ነው፡፡
-----
      የህንድ ፊልም ለመጨረሻ ጊዜ ያየሁት በ1995 ይመስለኛል፡፡ በወቅቱ ያየሁት Kabi Ghushi Kabi Gham የሚል የሻህሩኽ ኻን እና አሚታብ ፊልምን ነው፡፡ ያየሁበት ስፍራ አዲስ አበባ በመሆኑ ግን እኛ ስናደርግ እንደነበረው “ማህሙዴ፣ ሙጅሪም፣ ወዘተ…” እያለ ስለ ፊልሙ የሚተርክ ሰው አላጋጠመኝም፡፡ ከዚያ ወዲህ እኔና የህንድ ፊልም አንተዋወቅም፡፡ ለመሆኑ አሁን ምን ደረጃ ላይ ደርሷል?… እስቲ ስለ ህንድ ፊልም ያላችሁን ትዝታችሁ አካፍሉን፡፡
ሰላም!
የካቲት 17/2006
ሸገር

Wednesday, December 17, 2014

ኢራን፣ “ሩሚ” እና “መስነቪ”




ጸሓፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ
---
  ዛሬ በወግ ሽርሽር ብዙ ሀገር አቋርጠን “ፋርስ” ገብተናል፡፡ የዑመር ኻያም ሀገር! የፊርደውሲ ሀገር! የኒዛሚ ሀገር! የጃሚ ሀገር! የሓፊዝ ሀገር! በሩባኢያትና በገዛላት ዓለምን እያስፈነደቁ ለብዙ ክፍለ ዘመናት የዘለቁ የቅኔ ጠቢባን የተገኙባት ምድር!
  
   ዛሬ ፐርሺያ ነን! ዛሬ ኢራን ነን፡፡ ዛሬ ቴህራን ነን፡፡ ዛሬ ኒሻፑር ነን፡፡ ዛሬ ጠብሪዝ ነን፡፡ ዛሬ ሂልማንድ ነን፡፡ ዛሬ ኢስፋሓን ነን፡፡ ዛሬ ሺራዝ ነን! እዚያ ትልቅ የጥበብ ድግስ ተደግሶ ይጠብቀናል፡፡ እዚያ ከመድረሳችን በፊት ግን ለውዲቷ ኢራን ይህንን “ሩበእ” ብንቀኝላትስ?!  

አንቺ ሀገረ-ፋርስ የሀገር ጥበበኛ
ሁሉንም ያበቀልሽ አድርገሽ መልከኛ
የቅኔሽ መዓዛ ጠርቶኝ መጥቻለሁ
እጅሽን ዘርግተሸ መርሓባ በይኛ!

ሞክሬዋለሁ አይደል?. አዎን! “ሩበእ” (ሩባኢያት) ማለት እንዲህ ነው፡፡ ባለ አራት መስመር ቅኔ ሆኖ ሶስተኛው ስንኝ ከሌሎቹ አፈንግጦ ሲጻፍ በፋርሲ ቋንቋ “ሩበእ” ይባላል (ከዐረብኛው “ራቢዕ” የተገኘ ቃል ነው)፡፡ አንደኛ፣ ሁለተኛ እና አራተኛ መስመሮች በተመሳሳይ ፊደል ነው የሚያበቁት፡፡ ሶስተኛው ስንኝ ግን ከነርሱ ጋር አይገጣጠምም፡፡ “ሩበእ” ነጠላ ስም ነው፡፡ ለብዙ ቁጥር “ሩባኢያት” ይሆናል፡፡ አንዳንዶች የግጥሙ ዘውግ ከዐረቢያ ነው የተወረሰው ቢሉም “ሩባኢያት” ኦሪጂናሌ የኢራን የግጥም ዘይቤ መሆኑ በምሁራን ተረጋግጧል፡፡

ኢራናዊያን በሩባኢያት በጣም ይኮሩበታል፡፡ እንደ ብሄራዊ ቅርሳቸው ያዩታል፡፡ በተለይ The Zenith of Persian Literature በሚባለው ዘመን (ከ950 እስከ 1400 ድረስ) የተጻፉ ሩባኢያቶችን ከልብ ያፈቅሩአቸዋል፡፡ እኛም እንደ ዕድል ሆኖ በተስፋዬ ገሠሠ በኩል የዑመር ኻያም ሩባኢያትን በአማርኛ ለማንበብ በቅተናል፡፡ ዳሩ ግን እኛ ካጣጣምናቸው ሩባኢያት በላይ በኢራናዊያን የሚወደዱት የነ ሩሚ፣ ሳዲ፣ ጃሚ እና ሓፊዝ “ሩባኢያ”ት ናቸው፡፡ (ኢራናዊያን ከዑመር ኻያም በጣም የሚያደንቁለት የሒሳብ ሊቅነቱን ነው እንጂ ገጣሚነቱን አይደለም)፡፡
*****
ኢራን ነፍስ የሆነች ሀገር ናት! በጣም ውብ ባህልና የዳበረ ቋንቋ አላት፡፡ ታሪኳም ከቅድመ ክርስቶስ በፊት ከነበረው ዘመን ጀምሮ ነው የሚሰላው፡፡ በዚህ ረገድ ከመካከለኛው ምሥራቅ ሀገራት በእድሜ እርሷን የሚቀድሙት የርሷ ጎረቤት ሀገራት የሆኑት ሜሶጶጣሚያ (ኢራቅ) እና ሶሪያ ብቻ ናቸው፡፡ ዓለምን ያስደመሙ ታላላቅ ባለቅኔዎችን በማብቀል ግን ኢራን ከሁሉም ሀገራት ትበልጣለች፡፡

ኢራን ከጥንትም ጀምሮ ትክክለኛ ስሟ “ኢራን” ነው፡፡ የርሷ ተወላጆች ሀገራቸውን በዚሁ ስም ነው የሚጠሯት፡፡ ነገር ግን አብዛኛው የዓለም ህዝብ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ “ፋርስ” ወይንም “ፐርሺያ” ይላት ነበር፡፡ ኢራናዊያኑ “ይህ ስም አንዱን ክፍለ ሀገር እንጂ ሀገሪቱን በሙሉ ስለማይወክል ሀገራችንን ፐርሺያ እንዳትሏት” የሚል ዘመቻ ከፍተው ተሳክቶላቸዋል፡፡ ዛሬ ይኸው ኢራን ትባላለች፡፡ ይሁንና ቋንቋው “ፋርሲ” ነው የሚባለው፡፡ በዚህ ላይ ኢራዊያኑ ተቃውሞ የላቸውም፡፡ እንግዲህ በዚህ የፋርሲ ቋንቋ ነበር እነዚያ ውድ ባለቅኔዎች ዓለምን በጥበብ ሲያጠምቁ የነበሩት፡፡
*****
   የጥንቷ ኢራን እንዲህ እንደ አሁኑ አልነበረችም፡፡ ዛሬ አፍጋኒስታን፣ ቱርክሜኒስታን እና አዘርባይጃን የሚባሉ ሀገራት ለብዙ ክፍለ ዘመናት የርሷ ግዛቶች ነበሩ፡፡ የዛሬው እንግዳችንም በአሁኗ አፍጋኒስታን፣ በበልኽ አውራጃ፣ “ሩማ” በምትባል ከተማ ነው የተወለደው፡፡ እውነተኛ ስሙ ጀላሉዲን ሙሐመድ ወለድ ነው፡፡ ብዙዎች እርሱን የሚጠሩት ግን በትውልድ ከተማው ስም “ሩሚ” በማለት ነው፡፡

የሩሚ አባት የታወቁ ሼኽ እና ቃዲ ነበሩ፡፡ ሩሚም መደበኛ ትምህርቱን እዚያው በአባቱ ስር መማር ጀመረ፡፡ ነገር ግን በአስራ አንድ ዓመቱ መጥፎ እጣ ገጠመው፡፡ በዘመኑ መካከለኛው እስያን ደም በደም አድርገው የነበሩት የሞንጎል ወራሪዎች ወደ “በልኽ” እየተቃረቡ መሆናቸው ተሰማ፡፡ ስለዚህ የሩሚ አባት ቤተሰቡን ይዞ በምዕራብ አቅጣጫ ተሰደደ፡፡ “ኒሻፑር” ከምትባለው ጥንታዊት የኢራን ከተማ ሲደርሱም ከዘመኑ ዝነኛ ገጣሚ ፈሪዱዲን አጣር ጋር ተገናኙ፡፡ አጣር በሩሚ ነገሮችን የማስተዋል ችሎታ ተደንቆ “ይህ ልጅ ለወደፊቱ ትልቅ ባለቅኔ የመሆን ተስፋ አለው” የሚል ትንቢት ተናገረ ይባላል፡፡

ከሞንጎል የሸሸው የሼኽ ሙሐመድ ባሀኡዲን ወለድ (የሩሚ አባት) ቤተሰብ በመጨረሻ “ኮኒያ” ከምትባለው የቱርክ ከተማ ደረሰ፡፡ ሼኽ ባሃኡዲን እዚያ ካለው መድረሳ ማስተማር ጀመሩ፡፡ እርሳቸው ከሞቱ በኋላ ደግሞ የማስተማሩ ተግባር አንጋፋ ልጃቸው ለሆነው ለሩሚ ተላለፈ፡፡ ይሁንና ልጁ በማስተማሩ ላይ ሊያተኩር አልቻለም፡፡ ተፈጥሮንና ኑሮን እያየ ይህንን ግልብጥብጥ ዓለም የፈጠረውን ፈጣሪ አፈቀረ፡፡ ለርሱ የሙገሳ ቃላትን በግጥም መደርደር ጀመረ፡፡ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ግን አንድ ያልተጠበቀ እንግዳ ወደ ሩሚ መንደር ብቅ አለ፡፡

ሙላህ ሸምሱዲን ይባላል፡፡ የጠብሪዝ ተወላጅ ነው፡፡ ኢራናዊያን “ሸምስ-ኢ-ጠብሪዚ” ይሉታል፡፡ ሩሚ በሸምሱ-ጠበሪዝ ላይ ባየው መንፈሳዊ ልቅና ተመሰጠ፡፡ እንደ መምህሩም ቆጠረው፡፡ ቤተሰቡንና ስራውን ሁሉ ትቶ ከርሱ ጥበብን መቅሰም ጀመረ፡፡ አንድ ቀን ግን ሸምስ ጠብሪዝ እዚህ ነኝ ሳይል ጠፋ፡፡ በዚህም የተነሳ ሩሚ የመምህሩን ፍቅር ተራበ፡፡ ፍቅሩ እያቃጠለው “መደድ” (የፍቅር የመጨረሻ ደረጃ) ውስጥ አስገባው፡፡  ከዚያማ ማን ይቻለው! ከመምህሩ የተማረውን በራሱ ቋንቋ ጻፈው፡፡ 30,000 “ገዛል” እና ቁጥራቸው በርካታ የሆኑ “ሩባኢያት”ን ከተበ፡፡ እነዚህም ግጥሞች “ዲዋን-ኢ-ሸምሹ-ጠብሪዝ” በተሰኘ መጽሐፍ በአንድ ላይ ተሰበሰቡ (“ገዛል” የሚባለው ግጥም “ዜማ” ጭምር እንዳለው ልብ በሉ)፡፡
*****
የሩሚ የጥበብ ፍቅር አላበቃም፡፡ በሸምስ ጠበሪዝ መጥፋት የተከፋችው ነፍስ ሌላ መምህር ፍለጋ አላቆመችም፡፡ ታዲያ ሩሚ ብዙም አልተጓዘም እዚያው “ኮኒያ” ከተማ ውስጥ ተማሪው የነበረ ልጅ መምህሩ ሆኖ ተገኘ፡፡
 ሑሳሙዲን ይባላል፡፡፡ ሑሳሙዲን ከሩሚ ግጥሞች ሌላ የነ ፈሪዱዲን አጣርን፣ የነ ሰነኢንና የሌሎች ታላላቅ የፋርስ ባለቅኔዎችን ስራ አጥንቷል፡፡ እናም አንድ ቀን ሩሚን እንዲህ አለው፡፡ “መምህር! የርስዎ ግጥሞች ጉድለት ይታይባቸዋል፤ የራስዎትን ስሜት ብቻ እየተከተሉ ስለሚጽፉ በሌላው ውስጥ ጠልቆ የመግባት ሀይል ያጥራቸዋል፤ ለምን እንደ አጣርና እንደ ሰነኢ አይጽፉም” አለው፡፡
 ሩሚም “እስቲ እንዴት አድርጌ ልጻፍ?” በማለት ጠየቀው፡፡
 ሑሳሙዲንም “ከልዩ ልዩ ምንጮች የተገኙ እውነተኛ ታሪኮችን፣ ተረቶችን፣ ምሳሌዎችን፣ ተምሳሌቶችን፣ ወዘተ… እያሰናሰሉ ቢቀላቅሉባቸውና የግጥሞቹ አካላት ቢያደርጓቸው የምን ጊዜም ተወዳጅ ይሆናሉ” ብሎ መለሰለት፡፡
 የሑሳሙዲን ምክር በሩሚ ልብ ውስጥ ጠልቆ ገባ፡፡ ከዚያም ቅኔ ሲመጣለት መቀኘት ጀመረ፡፡ ሑሳሙዲንም ከሩሚ አንደበት የሚወጣውን መጻፉን ተያያዘው፡፡ ሁለቱ ሰዎች እንዲህ እያደረጉ ዛሬ ዓለም በሙሉ የሚደመምበትን “መስነቪ”ን አስገኙ (የመጽሐፉ ትክክለኛ ስም “መሥነዊ” ነበር፤ ይህም “መሥን” ከተሰኘው የዐረብኛ ግስ የተገኘ ነው፡፡ ነገር ግን የ“ሠ” እና የ“ወ” ድምጾች በፋርሲ ቋንቋ ውስጥ ስለሌሉ ኢራናዊያን “መስነቪ” እያሉ ይጠሩታል፤ የዓለም ህዝብም የነርሱን ፈለግ በመከተል “መስነቪ” ይለዋል)፡፡
*****
ሩሚ “መስነቪ”ን የደረሰው ከዛሬ 800 ዓመት በፊት ነው፡፡ ይሁንና ዛሬም ድረስ የህዝብ ፍቅር ሳይነፈገው እንደተወደደ አለ፡፡ በዘመናችን “ሩሚ”ን እጅግ ተነባቢ ከሆኑ አስር ምርጥ ገጣሚዎች ተርታ ያሰለፈውም “መስነቪ” ነው፡፡ ይህ ዝነኛ የግጥም ድርሳን ለዓለም ስነ-ጽሑፍ መዳበር ያደረገውን አስተዋጽኦ በመመዘን የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት የሳይንስና የባህል ድርጅት የአውሮፓዊያኑ 2007 በዓለም አቀፍ ደረጃ የሩሚ ዓመት ተብሎ እንዲጠራ ወስኗል፡፡ በዚያው ዓመት ሩሚ የተወለደበት ስምንት መቶኛ ዓመት ተከብሯል፡፡

የመስነቪ ይዘት ሰፊ ነው፡፡ የሰውን ልጅ አዕምሮ ያመራምራል፡፡ በዚህ ትንሽ መጣጥፍ ስለርሱ ብዙ ማውራት አይቻልም፡፡ ዳሩ ግን ከመስነቪ የተቀዳ አንድ ውብ ታሪክ ላካፍላችሁ እችላለሁ፡፡ ሩሚ ታሪኩን በግጥም ነው የጻፈው፡፡ ነገር ግን ተርጓሚው በስድ-ንባብ መልሶ ጽፎታል፡፡ እኔም በስድ ንባብ የተጻፈውን ታሪክ ነው የምጋብዛችሁ፡፡

===አራቱ ሰዎችና መንገደኛው===

  አራት ሰዎች ነበሩ፡፡ እነዚያም ሰዎች ግሪክ፣ ፋርሲ (ኢራናዊ)፣ ዐረብ እና ቱርክ ነበሩ፡፡ የሚፈልጉትን ነገር ይገዙበትም ዘንድ የተወሰነ ገንዘብ ተሰጣቸው፡፡ ግሪኩ “እኔ ስታፊል አምሮኛል፤ ስታፊል ግዙልንና እንብላው” አለ፡፡
ፋርሲው “የምን ስታፊል? ኡዙም ግዙልን እንጂ ሰዎች” አለ፡፡
ዐረቡ “አረ ወደዚያ! ኢነብ ነው የምንገዛው፤ ኢነብ መግዛት አለብን” በማለት ተናገረ፡፡
ቱርኩ “እንዴ! አንጉር ነው መግዛት ያለብን፤ አንጉር እንጂ ሌላ ነገር አትግዙብን” አለ፡፡

    አራቱ ሰዎች ተከራከሩ፡፡ ተነታረኩ፡፡ በጭራሽ ሊግባቡ አልቻሉም፡፡ እንዲህ እየተወዛገቡ ሳለም አንድ መንገደኛ መጣ፡፡ “ምንድነው የሚያጨቃጭቃችሁ?” በማለት ጠየቃቸው፡፡ ጉዳዩን ነገሩት፡፡ ሰውየውም “በዚህ ፍራንክ የሁላችሁንም ፍላጎት ማሟላት ይቻላል” አላቸው፡፡ ሰዎቹም “እንዴት?” በማለት ጠየቁት፡፡ ሰውዬም ገንዘቡን እንዲሰጡት ጠየቃቸው፡፡ እነርሱም እንደተባለው አደረጉ፡፡
መንገደኛው ሰውዬ በአካባቢው ከነበረ የፍራፍሬ መሸጫ ገብቶ አንዱን የፍራፍሬ ዓይነት ገዝቶ ሲወጣ አራቱ ሰዎች ተያዩ፡፡ በዚያው በሳቅ ፈረሱ፡፡ ለካስ አራቱም የአንዱን ፈራፍሬ ስም በየቋንቋቸው እየጠሩት ነበር? አራቱም “ወይን እፈልጋለሁ” እያሉ ነበር የሚከራከሩት::
*****
የታሪኩን “ማዕና” (መልዕክት) አገኛችሁት አይደል? ለኛም እንደ መንገደኛው ሰውዬ ያለ አስታራቂ ይላክልን፡፡ አንድ ውጥንና ግብ ያላቸው ሰዎች ዕድሜ ልካቸውን በአተገባበር ላይ ሲጣሉ ማየትን የመሰለ አሰቃቂ ህመም የለም፡፡ ሁሉም እይታውን ቢያስተካክል መግባባት ይቻላል፡፡ ሩሚ ይህንን ነው የመከረን፡፡
ብራቮ ጀላሉዲን ሩሚ! ብራቮ መሥነቪ!
*****
የካቲት 24/2006
*****
Afendi Muteki is a researcher and author of the ethnography and history with special focus on the peoples of East Ethiopia. You may follow him on his blog and his facebook page by clicking the following links