ጸሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ
-----
አንጋፋውን
ሱዳናዊ ድምጻዊ ዐብዱልከሪም አል-ካብሊን ከዚህ ቀደም ተዋውቀነው ነበር፡፡ ታዲያ የዚህን ጎምቱ ሰው ድምጽ ዛሬ ከአንድ ጓደኛዬ
“አይፓድ” ውስጥ ሰማሁትና በሃሳብ ወደ ልጅነቴ ወሰደኝ፡፡ እናም ከርሱ ጋር “ሸዛ ዛሂር” እያልኩ ሳንጎራጎር “ስለዚህ ዘፈን ለምን
አንድ ነገር አልጽፍም?” የሚል ሃሳብ መጣብኝ፡፡ እነሆ ጻፍኩላችሁ!!
አል-ካብሊ
ከሌሎች ሱዳናዊያን ድምጻዊያን ከሚለይባቸው ባህሪዎች አንዱ አብዛኛውን ጊዜ ሙዚቃዎቹን በራሱ የሚጽፋቸው መሆኑ ነው፡፡ ሁለተኛው
ደግሞ በሙዚቃዎቹ ውስጥ ከሱዳን የዐረብኛ ዘይቤ ይልቅ ብዙ ጊዜ የጥንቱን “ዐረቢያ አልፉስሓ” (Classical Arabic)
የሚጠቀም መሆኑ ነው፡፡ ሦሥተኛው ደግሞ ግጥሞቹን በሚጽፈበት ጊዜ ጥንታዊ የሆኑትን “ቀሲዳ”፣ “ቡርዳ” እና “ሙዓለቃት”
የሚባሉት የዐረብኛ የስነ-ግጥም ዘይቤዎችን የሚጠቀም መሆኑ ነው፡፡
ከአል-ካብሊ
ዘፈኖች መካከል በጣም የሚደነቀው “ሸዛ ዛሂር” ይባላል፡፡ “ሸዛ ዛሂር” የሚደነቀው በጥንቱ ዐረቢያ ፉስሓ የተገጠመ በመሆኑ
ብቻ ሳይሆን ዜማውም በጣም ማራኪ በመሆኑ ነው፡፡ የዘፈኑ አዝማች በኢራኖቹ “ሩባኢያት” ስልት የተጻፈ ሲሆን ተከታዮቹ ግጥሞች
ግን በዐረብኛው “ሙዓለቃት” ስልት ነው የተጻፉት፡፡
*****
“ሸዛ
ዛሂር” በጣም የተደነቀው ግን በግጥሞቹ ውበት ሳይሆን በመልእክቱ እና ደራሲው ግጥሙን ሲጽፍ በተከተለው ለየት ያለ ተምሳሌታዊ
(allegorical) ዘይቤ ነው፡፡ ግጥሙ ሲጀምር “ሸዛ ዛሂር” ይላል፡፡ “አበባው ፈነዳ… መዓዛው ምድሩን ሞላ” እንደማለት
ነው፡፡ ታዲያ በዘፈኑ ውስጥ በአበባ የሚያስመስለው ሰው ሴት ሳትሆን ወንድ ነው፡፡ ወንድን አበባ እያሉ ማሞገስ አለ እንዴ?…
በሌላ ቦታ አይታወቅም፡፡ አል-ካብሊ ግን አደረገው፡፡
አል-ካብሊ
የወደደውን ወንድ ሲያሞግስ “ወአንዙሩ ላ አራ በድረን አንተ ለይለተል በድሩ” ይለዋል፡፡ “ወደ ሰማይ ሳንጋጥጥ ሙሉውን ጨረቃ
ለማለት አልቻልኩም፤ ምክንያቱም ያንተ ብርሃን ጨረቃውን አጨልሞታል” እንደማለት ነው፡፡ በተጨማሪ ደግሞ “አንተ ረሒቁን ለና”
እስከማለት ደርሷል (“አንተ የኛ Nectar ነህ” እንደማለት ነው፤ Nectar ወፎችና ንቦች የሚቀስሙት የአበባ ጣፋጬ ክፍል
ነው፤ በአማርኛ ምን ይባላል)፡፡
አል-ካብሊ
ከዚህም ርቆ ይሄድና የወደደውን ሰውዬ “ለደቱ አል-ኸምረ ዐን ሸፈቲ፤ ለዐለ ጀማለከል ኸምሩ” ይለዋል፡፡ “አንድም የመጠጥ
ብርጭቆ ወደ ከንፈሬ አላስጠጋሁም፤ ነገር ግን ውበትህ “ኸምር” ሆኖ አስክሮኛል” ማለቱ ነው፡፡ ለመሆኑ ሰውዬው ምን ነክቶት
ነው ወንድን እንዲህ የሚያሞግሰው (አንዳንዱ ሰው ምናልባት… Gay ሳይሆን አይቀርም ይል ይሆናል….ቂቂቂቂ)
የሰውዬውን
ማንነት ከኋላ ትመጡበታላችሁ፡፡ አሁን የዘፈኑን ግጥም ተመልከቱ፡፡
(አዝማች)
ሸዛ
ዛህሪን ወላ-ዛህሩ
ፈዐይነ
ዚሉ ወን-ነህሩ
ረቢዑ
ሪያዲና ወላህ
አሚን
አህ ፊከ አን-ነሽሩ
-----
ወሐዘ
ነሁሩ የብሱሙሊ ዐኒ-ድ-ዱንያ ወየፍተሩ
ወአንዙሩ
ላ አራ በድረን አአንተ ለይለተል በድሩ፡፡
-----
ወቢሂ
ሱክሩን ተመለከኒ ወዐጀቡን ከይፈ ቢሂ ሱክሩ
ረድቱ
አል-ከእሳ ዐን ሸፈቲ ለዐለ ጀማለከል ኸምሩ፡፡
----
ነዐም
አንተ ረሒቁን ለና ወአንተ ሲሕሩ ወልኢጥሩ
ወአንተ
ሲሕሩ ሙቅተዲረን ወገይረል ሀይ ወሀዋ ሲሕሩ፡፡
---
ኹዙ
ዱኒያ ቢዐጅማኢሀ ሐቢቡን ዋሒዱን ዙኽሩ
ኢዛ
ጃአት መጣሊኡሁ ፈኩሉ ሰማኡና በድሩ፡፡
---
ኹዙ
ዱኒያኩሙ ሃዚሂ ፈዱኒያዋቱና ኩስሩ፡፡
ኹዙ
ዱኒያኩሙ ሃዚሂ ፈዱኒያቱና ኩስሩ፡፡
*****
የአል-ካብሊ
ግጥም ቅኔያዊ ፍቺ በመጨረሻው ስንኝ ላይ ነው የሚገኘው፡፡ “ኹዙ ዱኒያኩሙ ሃዚሂ ፈዱኒያቱና ኩስሩ” ማለት “ዱኒያ ይህቺ ናትና
እዩዋት፤ መጨረሻ ላይ ተሰባሪ ናት” ማለት ነው፡፡ እውነትም ዱኒያ ተሰባሪ ናት፡፡ አል-ካብሊ ግን ሰውዬን አድንቆት ሲያበቃ
“ዱኒያ ተሰባሪ ናት ብሎ” ዘጋው፡፡ ከፊት የተናገረውን መቃረን ይሆናል አይደል…?
ነገሩ
ወዲህ ነው፡፡ አል-ካብሊ እንዲህ ያደነቀው ሰው ጓደኛው ነበረ፡፡ ይህ ጓደኛው ገጣሚ ሲሆን በጣም ውብ የሆኑ ግጥሞችን በመጻፍ
ይታወቃል፡፡ አንድ ቀን ግን ሳይጠበቅ “ጭጭ” አለ፡፡ ምንም ሳይታመም ነፍሲያው ወጣች፡፡ አል-ካብሊ በዚህ ድንገተኛ አደጋ
ተደናገጠ፡፡ ልቡ ተሰበረች፡፡
ጓደኛው
ከተቀበረ ከጥቂት ቀናት በኋላ በሐዘኑ የተጎዳው አል-ካብሊ በምሽት ከቤቱ ወጥቶ ሰማይ ሰማዩን ማየት ጀመረ፡፡ ሰማዩን እያየ
ሟች ጓደኛውን ሲያስታውስ ይህ ግጥም መጣለት፡፡ ወዲያውኑ “ሸዛ ዛሂር”ን ጻፈውና መጫወት ጀመረ፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ደግሞ
በአንድ አልበም ውስጥ አካተተው፡፡ ግጥሙ በሱዳኖች ዘንድ ሲሰማ ዐጂብ ተባለ፡፡ የሙዚቃ ገምጋሚዎች በበኩላቸው የአል-ካብሊ
የምንጊዜም ምርጥ ዘፈን በማለት ሰየሙት፡፡
*****
አል-ካብሊ
“ሸዛ ዛህር”ን ከጻፈው በኋላ እንደ መግቢያ የሚጠቀምበት አጭር እንጉርጉሮም አክሎለታል፡፡ ዘፈኑ ለገጣሚው ጓደኛው የተጻፈ
መሆኑን በግልጽ የሚያሳውቀው በዚህ እንጉርጉሮ ውስጥ ነው፡፡ ይህ እንጉርጉሮ በተለምዶ “ማለሁ” እየተባለ የሚጠራው ነው
(አል-ካብሊ እንጉርጉሮውን “ማለሁ” በማለት ነው የሚጀምረው፤ ዐረብኛ እንዲህ ሲባል “ለምን ሲል ነው?” የሚል ዘይቤአዊ ፍቺ
አለው)፡፡ ታዲያ አል-ካብሊ ብዙ ጊዜ ዘፈኑን ከእንጉርጉሮው በመለየት ነው የሚጫወተው፡፡ አንዳንዴ ግን ሁለቱንም በአንድ ላይ
ይዘፍናቸዋል፡፡ ሁለቱ ግጥሞች ሲዘፈኑ የተለያየ የድምጽ ውጣ-ውረድን ስለሚጠይቁ ማንም ዘፋኝ ነኝ ባይ በአንድ ላይ ሊዘፍናቸው
ይቸገራል፡፡ እኔ ባለኝ ልምድ ግን አንድ ሰው ሁለቱንም በአንድነት ዘፍኖአቸው ተሳክቶለት አይቼአለሁ፡፡
አዎን!
ዓሊ ቢራ ነው፡፡ ዓሊ በ1998 የእንቁጣጣሽ በዓልን በማስመልከት በሸራተን አዲስ በተዘጋጀው የሙዚቃ ኮንሰርት ላይ
እንጉርጉሮውንና ሸዛ ዛህርን አንድ ላይ ዘፍኖአቸዋል፡፡ የዓሊ ቢራ አዘፋፈን ውብ መሆኑን ለማየት በዩ-ቲዩብ ላይ የተጫነውን
ቪዲዮ ይመልከቱ፡፡
(ቪዲዮውን
ለማለት የሚከተለውን ሊንክ ክፈቱ)፡፡
በነገራችን
ላይ ዓሊ ቢራ “ሸዛ ዛህር”ን ብቻ ሳይሆን ሌሎች የሱዳን ዘፈኖችንም ሲጫወት በጣም ይሳካለታል፡፡ የዚህ ስኬት አንደኛው
ምክንያቱ ደግሞ ዓሊ ግጥሞቹ የተጻፉበትን “ዐረቢያ አል-ፍስሓ”ን በትክክል መናገር የሚችል መሆኑ ነው፡፡ (ዐረቢያ አል-ፉስሓ
ሃያ ስምንቱን የዐረብኛ ድምጾች በትክክል ማውጣትን ይጠይቃል)፡፡
*****
አፈንዲ ሙተቂ
ህዳር 18/2007
--
No comments:
Post a Comment