Wednesday, November 26, 2014

“ጥጋብ አይቻልም”



ጸሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ
-----
እነሆ በድጋሚ ወደ ተረት ዓለም ልወስዳችሁ ነው፡፡ ድሮ የሰማሁት አንድ ተረት ከሰው ልጅ ደካማ ባህሪያት መካከል የሚቆጠረውን “ጥጋብ”ን በተዋበ መንገድ እንዴት እንደሚሄሰው እዩት፡፡
-----
በአንዲት መንደር የሚኖር አንድ ደሃ ሰው የሚበላውን እያጣ ይቸገር ነበር፡፡ ሰውዬው ብዙ ዘመን በችግር ካሳለፈ በኋላ “በተወለድኩበት ምድር በረሃብ ከምሞት ወደ ሌላ ሀገር ልሂድና ሲሳዬን ልፈልግ” በማለት ተሰደደ፡፡ ብዙ ከሄደ በኋላ ድካም ሲጀምረው ከአንድ ዛፍ ስር አረፍ አለ፡፡ ልክ እንደተቀመጠም ከዛፉ ላይ የነበረችው አንዲት በቀቀን “ጥጋብ አይቻልም” እያለች መዘመር ጀመረች፡፡ ሰውዬውም ወደላይ እያንጋጠጠ “እንዲህ ስትይ አታፍሪም እንዴ?! ረሃብ ነው የማይቻለው እንጂ ጥጋብማ በደንብ ነው የሚቻለው” በማለት አጸፋውን መለሰላት፡፡

  ሰውዬው የሚበቃውን ያህል ካረፈ በኋላ ጉዞውን ቀጠለ፡፡ ብዙ ከተጓዘ በኋላም ወደ አንዲት ትንሽ ከተማ ገባ፡፡ እዚያም ልመናውን ጀመረ፡፡ ብዙ ቤቶችን አዳረሰ፡፡ የከተማዋ ሰዎችም ያላቸውን ሰጡት፡፡ ሰውዬው ምሽቱን ከአንድ በረንዳ ስር አሳለፈ፡፡ በማግስቱም ልመናውን በመቀጠል ከአንድ ሰፊ ግቢ ደረሰ፡፡ እዚያም “ስለ አላህ! ያላችሁን ስጡኝ! ተዘከሩኝ” በማለት ልመናውን ተያያዘው፡፡ የቤቱ ባለቤት የግቢውን በር ከፈተችና ለማኙን አየችው፡፡ ሰውዬው ከመጎሳቆሉ በስተቀር መልከ መልካም ነው፡፡ አንድም የአካል ጉዳት የለበትም፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ሰው መለመኑ ስላስገረማት “አንተ ሰው! እንደዚህ ጤነኛ ሆነህ ነው እንዴ የምትለምነው?” አለችው፡፡ “ምን ላድርግ እመቤቴ ተቸግሬ ነው እኮ!” በማለት መለሰላት፡፡
“ለምን ሰርተህ አትበላም?”
“ስራ የለኝም፤ ትናንት ነው ከሌላ ሀገር የመጣሁት”
“እና ልትለምን ነው የመጣኸው?”
“አዎና እመቤቴ! ስራ የለኝም እኮ”
“ስራ ቢሰጥህ ትሰራለህ?”
“አዎን እሰራለሁ”

ሴትዮዋ የሀብታም ሰው ሚስት ነበረች፡፡ ባሏ በድንገት ሲሞትባት ከባሏ በወረሰችው ገንዘብ እየነገደችና እያስነገደች ትኖር ነበር፡፡ በመሆኑም ለማኙን ሰውዬ ከሌሎች ተቀጣሪዎቿ ጋር እንዲሰራ ፈቀደችና ወደ ግቢዋ አስገባችው፡፡ ከዚያም የለበሰውን ቡትቶ እንዲያወልቅ በመንገር አዲስ ልብስ እንዲሰጠው አደረገች፡፡ የሚኖርበትም ቤት ተሰጠው፡፡ ቀለብም ተቆረጠለት፡፡ ሰውዬወም በሴትዮዋ ለጋስነት እየተገረመና ምስጋና እያቀረበ የተመደበለትን የሱቅ አሻሻጭነት ስራ መስራት ጀመረ፡፡

 ሰውዬው ከስራው ጋር በጥቂት ጊዜ ውስጥ ተለማመደ፡፡ በስራው ውስጥ ከሁሉም ሰራተኞች በላጭ ሆኖ ተገኘ፡፡ በታማኝነቱም የተመሰገነ ሆነ፡፡ ሴትዮዋ በሰውዬው ባተሌነትና በታማኝነቱ ልቧ ተነካ፡፡ እያደርም በፍቅሩ ተነደፈች፡፡ ብዙ አውጥታ ካወረደች በኋላም ልታገባው ወሰነች፡፡ እናም ለሰውዬው ይህንኑ ነገረችው፡፡

   ይሁንና ሰውዬው በሴትዮዋ አባባል አኮረፈ፡፡ “እኔ ከትቢያ ላይ የተነሳሁ አንድ ድሃ ሰው ነበርኩ፤ እንዴት ካንቺ ጋር በጋብቻ መተሳሰር እችላለሁ?” አላት፡፡ ሴትዮዋ ምክንያቱን ነገረችው፡፡ ከብዙ ክርክር በኋላ ሰውዬው ሊያገባት ወሰነ፡፡ በመሆኑም ድል ያለ ድግስ ተደግሶ ያ የጥንት ለማኝ የቤቱ አባወራ ለመሆን በቃ፡፡

ሰውዬው አባወራ ከሆነ በኋላም ኃላፊነቱን በትጋት መወጣቱን ቀጠለ፡፡ ሴትዮዋም ይበልጥ እያፈቀረችው ሄደች፡፡ “ይሄ ሰውዬ ለምንጊዜውም የሚከዳኝ አይመስለኝም፤ ስለዚህ የስራውን ኃላፊነት በሙሉ ለርሱ ልስጠው፤ ትንሽ ቆይቼ ደግሞ ድርጅቱን በርሱ ስም አዛውራለሁ” በማለት ወሰነች፡፡ ከዚያም ሰውዬውን ጠራችና እንዲህ አለችው፡፡

“እስከዛሬ ድረስ እንደ ሰራተኛም እንደ ባልም ሆነህ ጥሩ ጊዜ ከኔ ጋር አሳልፈሃል፤ ባሳየኸኝ ታማኝትና በሰጠኸኝ ፍቅር ሙሉ ደስተኛ ነኝ፡፡ ስለዚህ ከዛሬ ጀምሮ የድርጅቱ ሃላፊም ሆነ ተቆጣጣሪ አንተ ነህ፤ ካንተ በላይ ማንም የለም፤ እኔ ራሴ በአንተ ስር ነኝ” አለችው፡፡ይህንን ካለችው በኋላ የድርጅቱን አስፈላጊ ሰነዶች አስረከበችው፡፡ በቤቷ የሚገኙ የካዝና ቁልፎችንም ስታስረክበው እንዲህ አለችው፡፡

  “እኝሁልህ የካዝናዎቻችን መቆለፊያዎች! ከዛሬ ጀምሮ ባንተ ኃላፊነት ስር ሆነዋል፤ ወርቁም ሆነ አልማዙ በብዛት አለልህ፤ ነገር ግን የአንዱን ካዝና ቁልፍ አልሰጥህም፤ በዚያ ውስጥ ምን እንዳለ እንድትጠይቀኝም አልፈቅድልህም፤ እርሱን የጠየቅከኝ እለት መቆራረጣችንን እወቅ”፡፡ ሰውዬውም ስለጉዳዩ ምንም ነገር ላይጠይቃት ቃሉን ሰጣት፡፡ በመሃላ ጭምር አረጋገጠላት፡፡

    ባልና ሚስቱ እንዲህ ከተግባቡ በኋላ ኑሮአቸው ደራ፡፡ ትዳራቸው ይበልጥ ተሟሟቀ፡፡ ድርጅታቸው በትርፍ ላይ ትርፍ መዛቁን ቀጠለ፡፡ ሰውዬውም ምንም ተቆጣጣሪ ሳይኖረው ገንዘቡን እንዳሻው ያወጣ ጀመር፡፡ እያደር ግን የሰውዬው ልብ መቀየር ጀመረች፡፡ በአንድ ካዝና እና በውስጠ ሚስጥሩ ላይ ጥያቄ እንዳያቀርብ የተጣለበትን እግድ ሲያስታውስ ገና የሀብት ጣሪያ ላይ ያልደረሰ ሆኖ ተሰማው፡፡ ያንን ካዝና ከፍቶ አለማየቱም ያንገበግበው ጀመር፡፡ ሴትዮዋ አንዱን ካዝና ነጥላ በማስቀመጧም “እወድሃለሁ የምትለው ከልቧ አይደለም” በማለት ወቀሳት፡፡ በመሆኑም ካዝናውን ከፍቶ ለማየት ተመኘ፡፡ ወደሴትዮዋ ሄዶም ጥያቄውን አቀረበ፡፡
   
  ሴትዮዋ በጥያቄው ተደናገጠች፡፡ ተገረመችም፡፡ ቃሌን ያከብራል ብላ የገመተችው ሰው ቃል አባይ ሆኖ በመገኘቱ ተናደደችበት፡፡ ነገር ግን ከሰውዬው ፍቅር ስለያዛት የመጨረሻ እድል ልትሰጠውና ከመንገዱ ልትመልሰው ወሰነች፡፡ እንዲህም አለችው፡፡
   “አረ አንተ ሰው የፈጠረህን ፍራ! ስለዚህ ካዝና ጉዳይ አንድም ጥያቄ ላትጠይቀኝ ቃል ኪዳን ሰጥተህኛል እኮ፤ እባክህ ይህንን ጥያቄህን ተውና በሰላም አብረን እንኑር”
“አንቺ ራስሽ እወድሃለሁ የምትይው ከልብሽ አይደለም፤ ያንን ካዝና ከፍተሸ ከውስጡ ያለውን ነገር ካላሳየሽኝ አትወጂኝም ማለት ነው”
“አረ አንተ ሰው መሀላ አታፍርስ! እረፍልኝ ብዬሃለሁ”
“የካዝናውን ቁልፍ እንድትሰጭኝ እፈልጋለሁ”

ሴትዮዋ ተናደደች፤ ነገር ግን ሰውዬውን ስለምትወደው በሽማግሌ ልታመስክረው ሞከረች፡፡ ሽማግሌዎችም “መሃላህን አትብላ! የፈጣሪ ቁጣ ይወርድብሃል፤ እንደ ድሮው በሰላም ብትኖሩ ይሻላል” አሉት፡፡ ሰውዬው ግን “ካዝናው ካልተከፈተ ሞቼ እገኛለሁ” በማለት ሙግቱን አፋፍሞ ቀጠለ፡፡ ሴትዮዋም በነገሩ ተስፋ ቆረጠች፡፡ ሰውዬው ወደ ኋላ የማይመለስ መሆኑን ካረጋገጠች በኋላ የከተማዋ ሽማግሌዎችና ታዋቂ ሰዎች እንዲሰበሰቡ አደረገች፡፡ ከዚያም ካዝናውን ከፈተችውና ከውስጡ ያለውን እቃ አወጣች፡፡ በሀይለ ቃልና በቁጭት በሰውዬው ፊት ላይ ወረወረችው፡፡
----------
ከካዝናው ውስጥ የተገኘው እቃ ሰውዬው ከሀገሩ የመጣበት ቡትቶ ልብስ እንጂ እንቁ ወይንም ሌላ የከበረ ጌጣጌጥ አልነበረም፡፡ ሴትዮዋ ለክፉ ቀን መጠባበቂያ እንዲሆናት ነው ከካዝና ውስጥ የቆለፈችበት፡፡ እውነተኛው ቀን ሲደርስ ልብሱን እዚያ ማስቀመጧ ትክክል እንደሆነ ተረዳች፡፡ ልብሱን በሰውዬው ፊት ላይ ከወረወረችለት በኋላም እንዲህ አለችው፡፡
“አንተ ውለታ ቢስ! ቶሎ ብለህ የኔን ልብስ አውልቅ! አንተ ያመጣኸውን ልብስ ልበስና ከዚህ ቤት ጥርግ ብለህ ጥፋልኝ”

ሰውዬው በድንጋጤ ክው ብሎ ቀረ፡፡ ከትቢያ ተነስቶ በተከበረበት ከተማ መዋረዱ ከፍተኛ እፍረት ውስጥ ጣለው፡፡ በመሆኑም ከከተማዋ በደረቅ ሌሊት ጠፋ፡፡ ወደ ሀገሩ ሊመለስም ጉዞውን ተያያዘው፡፡ ረጅም ርቀት ከተጓዘ በኋላ በቀቀኗን ካገኘበት ቦታ አረፈ፡፡

  ታዲያ በቀቀኗ “ጥጋብ አይቻልም” እያለች የድሮውን መዝሙር መዘመሯን እንደቀጠለች ነው፡፡ ሰውዬውም “እውነትሽን ነው! ጥጋብን ከእግር እስከ ራሱ አይቼው የማልችለው ዐይነት ሲሆንብኝ ወደ ድሮው የድህነት ህይወቴ እየተመለስኩ ነው” አላትና የመዝሙሩን ሐቀኛነት አረጋገጠላት፡፡
-----------
አይጣል ነው መቼስ! በርግጥም ጥጋብ አይቻልም፡፡ በእውነታው ዓለም የተከሰቱ በርካታ ታሪኮችን ከዚህ ጋር ማነጻጻር ይቻላል፡፡ ሀብትን ስናገኝ  አዕምሮአችን ከርሱ ጋር ካላደገ የሰራነው ሁሉ ወደ ዜሮ ሊመልስብን ይችላል፡፡ ለሁሉም ግን ፈጣሪያችን ከእንዲህ ዓይነቱ ክፉ እጣ ይሰውረን!
አሚን!
------
መጋቢት 19/ 2006
አፈንዲ ሙተቂ

(ተረቱን ያጫወቱኝ የገለምሶ ትልቁ መስጊድ ኢማም የሆኑት ሼኽ ሙኽታር አሊይ ናቸው፤ ዘመኑም እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር 1988 ነበር፤ ሼኽ ሙኽታር በአሁኑ ጊዜ የ85 ዓመት አዛውንት ናቸው፤ አላህ ጤናውንና ብርታቱን ይጨምርላቸው)፡፡

No comments:

Post a Comment