ከአፈንዲ ሙተቂ
------------
የአንደኛ ደረጃ ተማሪ ሳለሁ ያጋጠሙኝ አስተማሪዎች ቀልድ የለባቸውም፡፡ ተረት
ካልሆነ በስተቀር ቀልድ እየነገሩ ወይንም እየኮመኩ ተማሪዎችን ማሳቅ አያውቁበትም፡፡ በተቃራኒው ብዙዎቹ ተማሪው በሚፈጥራቸው ቀልዶችና
በያንዳንዱ ተማሪ ባህሪና ገጠመኝ ከልባቸው ይስቁ ነበር፡፡ ሆኖም እነዚያ አስተማሪዎቻችን ከፍተኛ የፈጠራ ችሎታ እንደነበራቸው አይካድም፡፡
አንድ ሁለቱን ግን በጣም እጠላቸው ነበር፡፡ ለምሳሌ ዘነበ ከበደ የሚባለው የአራተኛ ክፍል ስፖርት አስተማሪያችን “ዛሬውኑ በአየር
ላይ ተገልበጡ” የሚል ዓይነት ሰው ስለነበረ በጣም ነበር የምንጠላው (በግልበጣው ከሚደርስብን መላላጥና መፈንከት በላይ የርሱ ግርፊያ
ነበር የሚያስፈራን)፡፡
እጅግ የማይረሱ ቀልደኛ አስተማሪዎች የገጠሙኝ በሀይስኩል ነው፡፡ በቀለ ካሳ፣
ተስፋዬ ራሺያ፣ ዳንኤል አሰፋ፣ መሐመድ አብደላ ወዘተ… በፍጹም አይረሱኝም፡፡ እስቲ ከቲቸር ዳንኤልና ከጋሽ ተስፋዬ ቀልዶች ጥቂቱን
ላጋራችሁ፡፡
------
ጋሽ ተስፋዬ በአስረኛና አስራ አንደኛ ክፍል የኬሚስትሪ አስተማሪዬ ነበር፡፡
በቅጽል ስሙ “ተስፋዬ ራሺያ” እያልን ነበር የምንጠራው፡፡ ጋሽ ተስፋዬ ስለኬሚስትሪ ጠለቅ ያለ እውቀት አለው፡፡ ግን ውጪ አውጥቶ
በመናገር በኩል ችግር አለበት፡፡ ታዲያ ጋሽ ተስፋዬ ክፍል ከገባ አስር ደቂቃ ያህል በቀልድ ነው የሚያሳልፈው፡፡
አንድ ቀን ጋሽ ተስፋዬ ወደ ክፍል ለመግባት በሶምሶማ “ላፍ ላፍ” እያለ ወደኛ
መጣ፡፡ መሬቱ ግን በሀይለኛ ዝናብ በስብሶ ስለነበር እንኳንስ በሶምሶማ፣ በቀስታም ለመሄድ አዳጋች ነበር፡፡ ጋሽ ተስፋዬ እንደፈራነው
ወደኛ ክፍል ሳይደርስ አዳልጦት ወደቀ፡፡ በአቅራቢያው የነበሩ ተማሪዎችም ሮጥ ብለው ደጋግፈው አነሱት፡፡
ጋሽ ተስፋዬ
አንዴ መሬቱን አንዴ በጭቃ የተበላሸ ልብሱን እያየ እንዲህ አለ፡፡
“ጎበዝ
እዚህ አካባቢ ግራቪቲ የለም እንዴ?”
በስፍራው
የነበርነው በሙሉ ሳቃችንን ለቀቅነው፡፡
(“ግራቪቲ”
የስበት ኃይል መሆኑን ላስታውሳችሁ እሻለሁ! እንዲህ ሳደርግ ታዲያ አሁን ስሙ ተቀይሮ ከሆነ ብዬ ነው እንጂ ነገሩን ትረሱታላችሁ
በማለት እንዳልሆነ እወቁልኝ)፡፡
------
ጋሽ ተስፋዬ ኬሚስትሪን ሲያስተምር ስለያንዳንዱ ኬሚስት ህይወት አስደናቂ ወሬዎችን
ያወጋናል፡፡ እኛም በተመስጦ እናዳምጠዋለን፡፡ አንዳንድ ጊዜ ግን ተአማኒ ያልሆኑ ወሬዎችንም ይቀላቅላል፡፡ ለምሳሌ አንድ ጊዜ
“የአሲድ ጣዕም ምን ዐይነት ነው?” የሚለውን ሲያስረዳን እንዲህ ብሎን ነበር፡፡
“የአሲድን
ጣዕም እኮ ያገኙት ሁለት ባልና ሚስት ናቸው፡፡ ደግሞም የህይወት ዋጋ ከፍለውበታል፡፡ ይህ እንዴት የሆነ ይመስላችኋል? ባል ሚስቱን
ይጠራና “እኔ አሲድን ቀምሼ ጣዕሙ ምን ዓይነት እንደሆነ እጽፋለሁ፣ አሲዱ በድንገት ከገደለኝ ግን አንቺ እኔ የጀመርኩትን ትጨርሽዋለሽ”
አላት፡፡ ሚስትም “እሺ” አለችው፡፡
በዚህ ስምምነት መሰረት ባል አሲዱን ጠጣ፡፡ ወዲያኑ ተንዘፍዝፎ ወደቀ፡፡ ከመሞቱ
በፊት ግን “S” የተሰኘውን የእንግሊዝኛ ፊደል ጻፈ፡፡ ሚስትም ከርሱ ተከትላ አሲዱን ጨለጠችውና ወዲያኑ ተንዘፍዝፋ ወደቀች፡፡
እርሷም ከመሞቷ በፊት ግን ባሏ በጻፈው አንድ ፊደል ላይ “O”ን ጨመረችበትና “SO” አደረገችው፡፡ ዓለምም አሲድ “sour”
(ጎምዛዛ) መሆኑን በዚህ መንገድ አወቀ፡፡ ያኔ ሚስት ባሏን ተከትላ ባትሞት ኖሮ አሲድ “sour” (ጎምዛዛ) ወይስ “salt”
(ጨዋማ) የሚለው ክርክር ይቀጥል ነበር”፡፡
------
ዳንኤል አሰፋ የአስራ አንደኛ ክፍል የሒሳብ አስተማሪያችን ነበር፡፡ ጎብዝናው
ይገርማል! እኛ ተማሪዎቹ የዳንኤልን ችሎታ የጂኦሜትሪ ሳይንስን ከጀመረው “ኢኩሊድ” የሚባል የግሪክ ፈላስፋ ጋር እናወዳድረው ነበር፡፡
በህይወቴ እንደርሱ እየመሰጠኝ የተማርኩባቸው አስተማሪዎች ቢኖሩ ሰለሞን የሚባል የአስራ አንደኛ ክፍል እንግሊዝኛ መምህሬ፣ የሶፎሞር
እንግሊሽ አስተማሪዬ የነበረው ወልዱ ሚካኤል (በኋላ ዶ/ር ሆኗል) እና ለአንድ ዓመት ተኩል ያህል History of
Economic Thought እና Development Economics የሚባሉ ኮርሶችን ያስተማረኝ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ብቻ ናቸው
(እዚህ ዘንድ ፖለቲካ እየሰራን እንዳልሆነ ልብ በሉ፡፡ ነገሩን በፖለቲካ ዐይን የምታዩ ካላችሁ ዶ/ር ወልዱ የመንግሥት ደጋፊ፣
ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ የመንግሥት ተቃዋሚ መሆናቸውን እወቁልኝ)፡፡ በነገራችን ላይ ሁለቱ የዩኒቨርሲቲ አስተማሪዎቼ በውጤት ጊዜም ለተማሪው
ልፋት ተገቢውን ዋጋ ይሰጡ እንደነበር ማስታወስ እፈልጋለሁ፡፡
ወደ ቲቸር ዳንኤል
ቀልዶች እንመለስ፡፡ በሳምንቱ ቀናት ሁሉ ሒሳብ እንማር ነበር፡፡ ማክሰኞ ደግሞ ለሁለት ክፍለ ጊዜያት (ደብል ፔሬድ) ነበር የምንማረው፡፡
ቲቸር ዳንኤል በአንዱ ፔሬድ ሲያስተምር ከቆየ በኋላ ሁለተኛውን ፔሬድ እስኪጀምር ድረስ በመሀሉ የአምስት ደቂቃ እረፍት ይሰጠናል፡፡
ታዲያ እርሱ አምስት ደቂቃ ሲለን አንዳንዶቻችን ለስምንት ደቂቃ፣ አንዳንዶቻችንም እስከ አስር ደቂቃ እንቆይ ነበር፡፡ ቲቸር ዳንኤል
ይህንን ጉራማይሌ ሁኔታ ለትንሽ ጊዜ በትዕግስት አሳለፈው፡፡ አንድ ቀን ግን ትዕግስቱ አለቀበትና እንዲህ አለን፡፡
“ፕላኔቶች
ከጸሐይ በሚርቁበት ልክ በየፕላኔቱ ላይ የሚደረገው የጊዜ አሰፋፈርም ይለያያል፡፡ ሜርኩሪ ላይ ሁለት ደቂቃ ማለት መሬት ላይ አምስት
ደቂቃ ማለት ሊሆን ይችላል፡፡ ጁፒተር ላይ ስምንት ደቂቃ፣ ሳተርን ላይ ሀያ ደቂቃ ወዘተ… እና የጁፒተር ሰዎች ከዛሬ በኋላ አደብ
ግዙልኝ፡፡ እምቢ ካላችሁ ወደ ጁፒተር ሂዱልኝ”
--------
ይህኛው ደግሞ በሌላ ክላስ (11ኛ C) የተፈጠረ ተብሎ ነው የተነገረኝ፡፡
ቲቸር ዳንኤል ሲያስተምር አንዱ ተማሪ ከወዲያ ወዲህ ውርውር ይላል፡፡ ዳንኤል
በትዕግስት አሳለፈው፡፡ ተማሪው ግን በፍጹም አላርፍ አለ፡፡ ይሄኔ
ቲቸር ዳንኤል ተናደደና እንዲህ አለ፡፡
“አንተ
ልጅ አርፈህ አንድ ቦታ ቁጭ በልልኝ፡፡ እምቢ ካልክ ግን ይህንን ትሪያንግል የመሰለ ፊትህን ፔንታጎን አስመስልልሀለሁ”፡፡
(በሂሳብ መሳደብ እንዲህ ነው!)
--------
በአስራ ሁለተኛ ክፍል የፊዚክስ አስተማሪ ቢቸግረን ቲቸር ዳንኤል “የኔ ማይነር
ፊዚክስ ነው፤ አይዞአችሁ! እኔ ራሴ አስተምራችኋለሁ” ብሎ ገባልን፡፡ እናም አንድ ቀን ሲያስተምረን “a metal rod
which is uniformly distributed” የሚል ነገር ተናገረ፡፡ “ውፍረቱ በሁሉም በኩል እኩል የሆነ ብረት” ለማለት
ፈልጎ ነው፡፡ ግን አንድ ተማሪ ተደናገረና “ቲቸር ምን ማለት ነው?” በማለት ጠየቀው፡፡ ቲቸር ዳንኤል በአማርኛ ተርጉሞ ነገረው፡፡
ተማሪው ግን አልገባህ አለው፡፡ ይህ ተማሪ አስተማሪዎችን በጥያቄ የመወጠር አመል እንዳለው ሁሉም ሰው ያውቃል፡፡ በመሆኑም ቲቸር
ዳንኤል ከተማሪው ጋር በቀጥታ መዳረቁን ተወና ነገሩን እንዲህ አብራራለት፡፡
“ለምሳሌ
ከቀበሌና ከሻይ ቤት የሚገዛውን ዳቦ ተመልከት፣ ውፍረቱ በሁሉም በኩል እኩል አይደለም፡፡ አንድ እናት እርሱን ገዝታ ለሶስት ልጆች
አከፋፍላለሁ ብትል የዳቦውን የመሀለኛውን ክፍል ካገኘው ልጅ በስተቀር ሌሎቹ እንደሚያለቅሱ አትጠራጠር፡፡ ሴትዮዋ “ሽልጦ ዳቦ”
ከጉልት ብትገዛላቸው ግን በሁሉም በኩል እኩል በመሆኑ ሁሉም ልጆች ያለ አንዳች ቅሬታ ነው የሚቀበሉት”፡፡
ቲቸር ዳንኤል
ሽልጦን ምሳሌ በማድረግ ከተማሪው ጭቅጭቅ ተገላገለ፡፡
----------
ቲቸር ዳንኤል የአዲስ አበባ ልጅ ነው፡፡ በቅርብ ዓመታት እንደሰማሁት የመምህርነት
ሙያውን ትቶ ከዘመዶቹ ጋር በአዲስ አበባ ቢዝነስ እየሰራ ነው፡፡ ጋሽ ተስፋዬ (ራሺያ) ግን እዚያው የኛ ከተማ ቤት ሰርቶ፣ ልጆች
ወልዶ እየኖረ ነው፡፡
አስተማሪዎቻችን ባለውለታችን ናቸው፡፡ በተለይ የአንደኛ ደረጃ እና የሁለተኛ
ደረጃ አስተማሪዎቻችን ውለታ መቼም ቢሆንም አይረሳም፡፡ በማትረባ ደመወዝ የማይረባ ኑሮ እየኖሩ ስንቶቻችንን ለቁምነገር አብቅተዋል፡፡
በሰለጠነው ዓለም ከሁሉም ተቀጣሪ በላይ ከፍተኛ ክፍያ የሚያገኙት እነርሱ ናቸው አሉ፡፡ በሀገራችን ግን ሁሉም ነገር የተገላቢጦሽ
ነው፡፡ እስቲ ይሁና! “መቼስ ማልጎዸኒ” አለ የሀገሬ ሰው!!
አፈንዲ ሙተቂ
ነሐሴ 27/2005
No comments:
Post a Comment