Pages

Friday, August 30, 2013

==“የጂንኒ” ወግ==



ጸሓፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ
ክፍል አንድ
-------
በዚህች ጽሑፍ ከሰዎች ዓለም ወጥተን ወደ “ጂንኒ” ዓለም ልንገባ ነው፡፡ ሀይለኛ የፍርሃት ስሜት (phobia) የሚፈታተናችሁ በቀን እንጂ በጨለማ ባታነቡት ይመረጣል፡፡ በልጅነታችሁ “አንድ ሺህ አንድ ሌሊት” (The Arabian Nights) የሚባለውን ዝነኛ የተረት መጽሐፍ ያነበባችሁ ሰዎች ግን ስለ“ጅንኒ” በቂ ተመክሮ ያላችሁ በመሆኑ ምንም የሚያስፈራችሁ ነገር የለም፡፡ እንደኔ “ጂንኒ”ን ሳትተናኮሉ ከርሷ ጋር እየተያያችሁና አንዳንዴም እየተጋፋችሁ የመተላለፍ ልምድ ያላችሁ ሰዎችም በፈለጋችሁት ጊዜ ልታነቡት ትችላላችሁ፡፡
 -------
“ጂንኒ”ን አማርኛው “ጋኔን” በማለት የሚጠራት ይመስለኛል፡፡ የብዙ ቁጥር ስሟ ደግሞ “አጋንንት” ነው፡፡ ዐረብኛው “ጂንኒይ” ወይንም “ጂንን” ይላታል (አንዷ “ን” ለማጥበቅ ነው የገባችው- ስለዚህ ሁለቱንም እንደ አንድ ፊደል በማድረግ አንብቧቸው)፡፡ ኦሮምኛና የሀረሪ ቋንቋ ከዐረብኛ የወረሱትን ስም ቤተኛ በማድረግ “ጂንኒ” ይሏታል፡፡

  የጅንኒ ትውፊት መሰረቱ ዐረቢያ ነው፡፡ እዚያ ዘንድ በእስልምና በኩል ከመጣው የጂንኒ አስተምህሮ በተጨማሪ የዐረቦች መጠነ ሰፊ ልማድ ታክሎበት ራሱን  የቻለ ትልቅ ስነ-ቃል ሆኗል፡፡ በምስራቅ ኢትዮጵያ የሚነገረው የጅንኒ ወግም መሰረቱ ይኸው ነው፡፡ ሆኖም ቤተኛው አቅላችንና ኑሮአችን ትውፊቱን እያደለበው በጣም አዳብሮት ራሱን የቻለ ሀገርኛ ስነ-ቃል አድርጎታል፡፡  

    ይህ የጅንኒ ትውፊት በስፋት የሚታወቀው በኦሮሞ እና በሀረሪ ህዝቦች ዘንድ ነው፡፡ ይሁን እንጂ በምስራቅ ኢትዮጵያ የተወለደ ማንኛውም “ጅንኒ”ን በደንብ ያውቃታል፡፡ አማራም ሆነ ትግሬ፣ ጉራጌም ሆነ ወላይታ ልደቱ በሀረርጌ ክፍለ ሀገር ከሆነ የ“ጅንኒ”ን ማንነት በደንብ ይነግራችኋል፡፡

   በርግጥም በዚህ ጽሑፍ የማወጋችሁ በምስራቅ ኢትዮጵያ የማውቃትን “ጂንኒ” ነው፡፡ ስለዚህ በሌላ አካባቢ የሚታወቁ “ጂንኒ” ቀመስ ወሬዎችን አልቀላቅልበትም፡፡ በተጨማሪም በምስራቁ ትውፊት “ጅንኒ” እንደ ሴት “እርሷ” እየተባለች የምትጠራ በመሆኑ እኔም ይህንኑ ፈለግ እከተላለሁ፡፡

  የእስከ አሁኑ እንደ መግቢያ ይሁንልኝ፡፡ ከዚህ በኋላ ግን አካሄዴን እቀይራለሁ፡፡ ስለ “ጅንኒ” ሳወጋችሁ “እንዲህ ይባላል”፣ “እንዲህ ተብሎ ይነገራል” የሚሉ አነጋገሮች ከአሁን በኋላ አያስፈልጉኝም፡፡ ምክንያቱም የማወጋችሁ ስላነበብኩትና ስለሰማሁት ነገር ሳይሆን በህይወቴ ያለፍኩበትን ነገር ነውና፡፡ “እንዲህ ይባላል”፣ “እንዲህ ይነገራል” ካልኩማ ምኑን ስለ “ጂንኒ” ተጫወትነው? “ጅንኒ”  እንዲህ ናት” ስል ከርሜ አሁን ልገልበጥ እንዴ? ይህማ ደግ አይደለም፡፡ ስለዚህ ልክ እንደ ልጅነቴ ዘመን ነው የምጽፍላችሁ! ያሻው ሰው “እውነት ነው” ይበል፤ ያልፈለገውም እንደፍላጎቱ ይሁንለት፤ የፈለገው በሳይንስ ይፈትነው፡፡ ወጋችን ይመርልን እንጂ ለሌላ ሌላው እኛ ምን አገባን?
                   *****  *****  *****
በአማርኛ “ጋኔን” የሚባለው ነገር ምንጊዜም ቢሆን እርኩስ ነው፡፡ ደግሞም በሌሎች ላይ የሚያድር “መንፈስ” ነው እንጂ ከሌሎች ተለይቶ የሚኖር ፍጡር አይደለም፡፡ ጋኔንን የሚገፋው ሰይጣን ነው፡፡ በሰይጣን ጦር የተወጋ ሰው ነው የ“አጋንንት” መንፈስ የሚያድርበት፡፡

   “ጂንኒ” ግን ራሷን የቻለች ፍጥረት ናት፡፡ የራሷ አካልና ንቅናቄም አላት፡፡ እንደ ሰው ትበላለች፤ ትጠጣለችም፡፡ ግብርና ውሎዋም እርኩስ ብቻ አይደለም፡፡ በጎ ምግባር ያላቸውና በጎ የሚሰሩ “ጂንኒዎች” በብዛት አሉ፡፡ እርኩስ የሆኑና ክፋትን ብቻ በምድር ላይ የሚዘሩ ጂንኒዎችም ሞልተዋል፡፡

  “ጂንኒ” ማሰብ ከሚችሉ ሶስት ፍጥረቶችም መካከልም ናት (ቀሪዎቹ ሁለቱ መላእክትና የሰው ልጅ ናቸው)፡፡ የራሷ መንግሥትና ሀገርም አላት፡፡ የምትኖረው በምድር ላይ ብቻ ሳይሆን በባህርም ጭምር ነው፡፡ በተራራ፣ በጫካ፣ በዛፍ ስንጥቆች መሀል፣ በወንዝ፣ በኩሬ ወዘተ… መኖር ትችላለች፡፡

“ጅንኒ” እንደ ሰው በሁለት እግሯ ነው የምትራመደው፡፡ ነገር ግን የታችኛው ቅልጥሟ ከአህያ እግር ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ የእግሯ ኮቴም ቢሆን ከከብት እና ከአህያ ሽኮና ጋር ነው የሚመሳሰለው፡፡ ከዚህ ሌላ መላው የጂንኒ አካል ጸጉራም ነው፡፡ ከእግር እስከራሷ ድረስ በጸጉር ተሸፍናለች፡፡ ይህ ጸጉሯም ከቀበሮ ወይም ከውሻ ጸጉር ጋር ይመሳሰላል፡፡ መልኩ ግን እንደ አህያ ቆዳ ዳለቻ ነው፡፡ መላው አካሏም ዳለቻ መልክ ነው ያለው፡፡  

   ጅንኒ እንዲህ ሆና የምትታየው በተፈጥሮ አካሏ ነው፡፡ ነገር ግን በዚህ የተፈጥሮ ገላዋ ሁልጊዜ አትገኝም፡፡ አካልና ገላዋን እንደፈለገች መቀያየር ትችላለች፡፡ በአንድ ጊዜ ግዙፍ ሆና ከዛፍ ቁመት ጋር ልትስተካከል ይቻላታል፡፡ ብትፈልግ ላም፣ ካሻትም በሬ፣ ከፈቀደችም ድመት መሆን ትችላለች፡፡ ባህሪዋንም ቢሆን እንደፈለገች የመቀያየር ችሎታ አላት፡፡ አንድ ጊዜ “ደግ”፣ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ክፉ ትሆናለች፡፡

  “ጂንኒ” በጥበብም ሆነ በችሎታዋ ከሰዎች ትበልጣለች፡፡ ሰዎች ያላቸው እውቀት ቢደመር የርሷን ዕውቀት ሩቡን እንኳ አይሆንም፡፡ ለምሳሌ የከበሩ ማዕድናት የሚገኙባቸውን ቦታዎች በቀላሉ ማወቅ ስለሚቻላት ማዕድናቱን እንዳሻት እያወጣች ትጠቀምበታለች፡፡ ነገር ግን በአንዳንድ ባህሪዎቿ ከእንስሳ እንኳ አትሻልም፡፡ ለምሳሌ ከንጹህ ቦታ ይልቅ ቆሻሻ ቦታዎችን ትመርጣለች፡፡ ከየቤቱ የሚጣለውን ቆሻሻ እንደ ምግብ የመብላት መጥፎ አመልም አላት፡፡ ደምና ፈርስ ከሚደፋበት ቦታ ትመላለሳለች፡፡ በነዚህ ቦታዎች ያየችውን እርጥበትና ፍሳሽ አትምርም፡፡ ከመሬቱ ላይ እየላሰች ትጨርሰዋለች፡፡

  “ጂንኒ” አመድንም እንደ ምግብ ትበላለች፡፡ ከዳቦ ቤቶች (ዳቦ በባትራ የሚያግሩትን የድሮ ዳቦ ቤቶች ማለቴ ነው) የሚወጣው አመድ የነፍስ ምግቧ ነው፡፡ ከዚህ ሻል የሚሉት ጅንኒዎች ግን “ቅቤ” መጠጣትን ያዘወትራሉ፡፡ በጣም የሚጀነኑትና የሚኩራሩት ጂንኒዎች ደግሞ ልክ እንደ “ቡዳ” ሰዎችን ይበላሉ፡፡ በተለይ ቆንጆ ሴቶች፣ ወንዳወንድ ቁመና ያላቸው ወንዶች እና ህጻናትን አይምሩም፡፡
                *****  *****  *****
 “ጅንኒ” ሀይለኛ ናት፡፡ በእጇ የነካችውን ነገር ወደ አፈር መቀየር ትችላለች፡፡ ከዐይኗ በምታፈልቀው ጨረር የወጋችው ዛፍም ሆነ እንስሳ ድርቅ ብሎ ይቀራል፡፡ ነፋስን እያሽከረከረች ከፍተኛ አደጋ መፍጠር ትችላለች፡፡ በርሷ የሚፈጠሩት አደጋዎችና  በርሷ እየተወጉ ሚጠወልጉ ፍጥረታት ከብዛቷ ጋር ሲነጻጻሩ ግን በጣም አነስተኛ ናቸው፡፡ በተለይ ጂንኒ በዚህ ዩኒቨርስ ውስጥ ስትኖር ሆን ብላ ሰዎችን የምትተናኮለው አልፎ አልፎ ነው፡፡ በአንድ መንደርና በአንድ ከተማ እንኳ ከሰዎች ጋር እየኖረች ከነርሱ ጋር ብዙም አትጋጭም፡፡ ደግሞም አልፎ አልፎ (rarely) ካልሆነ በቀር አብዛኛውን ጊዜ ለሰዎች በግልጽ ስለማትታይ ግጭቱ የሚፈጠርበት እድል በጣም የመነመነ ነው፡፡

   ነገር ግን “ጂንኒ” በጣም በሚርባት ጊዜ ለሰዎች በግልጽ ልትታይ ትችላለች፡፡ በዚያን ጊዜ በመንገዷ ላይ የምታገኘውን ሰው ያለ ርህራሄ በመርዛማ ፍላጻዋ ወግታ “ፓራላይዝ” ልታደርገው ትችላለች፡፡ አንዳንዴ ደግሞ ሰውየውን ወግታ ደም ከአፍና ከአፍንጫው ታስወጣዋለች፡፡

 እንደ “ቡዳ” ሰዎችን የሚበሉት “ጂንኒዎች” ደግሞ ይህንንም አያደርጉም፡፡ በወጉት ሰው ላይ ለዘላለም ተለጥፈው አሳሩን ያሳዩታል፡፡ ከላይ እንዳወሳሁትም የነዚህኛዎቹ ጂንኒዎች ዋነኛ ዒላማ ቆንጆ ሴቶች (በተለይ ረጃጅም ጸጉር ያላቸውና ዐይናቸው እንደ ኮከብ የሚያበራ)፣ ቆንጆ ወንዶችና ህጻናት ናቸው፡፡ ጂንነዋ እነርሱ ውስጥ ከገባች በኋላ መንፈሷን በሰውነታቸው ውስጥ ትተውና ሰዎቹ የሚበሉትን ትጋራለች፡፡ ደማቸውንም ትመጣለች፡፡ በዚህም የተነሳ ጅንኒ የወጋችው “ቆንጆ” ሰው በሀይለኛ የደም ማነስ በሽታና በልብ ህመም ይሰቃያል፡፡ “ያሲን” እና “ተባረክ” ካልተቀራበትና “ወዳጃ” ተቀምጦ በዱዓ አላህን ካልለመነለት በስተቀር ጂንነዋ ከሰውዬው ውስጥ አትወጣም፡፡

  በሌላም በኩል አራት ዓይነት ሰው በጅንኒ ሊጠቃ ይችላል፡፡ አንደኛው “ጅንኒዎች” ለምግብ ፍለጋ በሚያዘወትሩት ቦታ ላይ የሚመላለስ ክልፍልፍ ሰው ነው፡፡ ጂንኒዎች እንዲህ አይነቱ ሰው ለነገር ፍለጋ የመጣባቸው ስለሚመስላቸው ዋጋውን ይሰጡታል፡፡ ቆሻሻ የሚደፋ ሰውን ግን በጭራሽ አይነኩትም፡፡ ሁለተኛው ጅንኒዎች እንደ የእዝ ማዕከል (command post) በሚገለገሉበትና እንደ ግምጃ ቤት (treasury) በሚጠቀሙበት ቦታ ላይ መመላለስ የሚያበዛ ሰው ነው፡፡ ጂንኒዎች ይህንን ሰው ሰላይ ነው ብለው ስለሚጠረጥሩት (ወይንም “በኛ እውቀት መክበር የሚፈልግ ነው” ብለው ስለሚያስቡ) በቀስታና በጨረር ይወጉታል፡፡ ከዚህ ሌላ በነዚህ ስፍራዎች ላይ ጅንኒዎች የማይፈልጉትን ነገር የሚያደርግ ሰውም የጥቃቱ ሰለባ ሊሆን ይችላል፡፡ ሰውየው በስፍራዎቹና በአቅራቢያቸው እሳት ማቀጣጠል ወይንም ጩኸት ማብዛት የለበትም፡፡ በስፍራዎቹ ላይ አዘውትሮ መመላለስ የሚያበዛ ሰውም ከጥቃት አይድንም፡፡ እነዚህ ስፍራዎች በጣም ጸጥ ብሎ የሚፈስና ጥልቀት ያለው ወራጅ ወንዝ (በኦሮምኛ ቱጂ ይባላል)፤ ረግረግ፣ ጥልቀት ያለው የውሃ ጉድጓድ፣ ወና የሆነ ትልቅ አዳራሽ፣ ግዙፍ የዋርካ ዛፍ፣ ግዙፍ ቋጥኝ ፣ ሰፊ እና ጥልቅ ገደል… የመሳሰሉት ናቸው፡፡
     በሶስተኛ ደረጃ ለጂንኒ ጥቃት የሚጋለጠው ጅኒንዎች ለስምሪት በሚወጡባቸው ጊዜያት ምላሱንና እንቅስቃሴዎቹን ለአደብ ያላስገዛ ሰው ነው፡፡ ጅንኒዎች በብዛት የሚሰማሩት ጧት፣ ቀን በጠራራ ጸሐይ (ጸሐይዋ የሰው አናት ልትበሳ በምትደርስበት ጊዜ)፣ እና በጸሐይ መግቢያ ወቅት (“ሚስቲጃብ” ወይም “መግሪብ”) ነው፡፡ በነዚህ ጊዜያት በቢሊዮኖች የሚቆጠር የጂንኒ ሰራዊት ሰለሚሰማራ በምድር ላይ የጅንኒ ቁጥር ከሰዎች በብዙ እጥፍ ይበልጣል፡፡ ስለዚህ ሰዎች በነዚህ ጊዜያት እንቅስቃሴ ማብዛት የለባቸውም፡፡ መሳደብና መራገምም ይለባቸውም-ጅንኒ እርሷ የተሰደበች መስሏት ተሳዳቢዉን ሰውዬ በጥፊ አጠናግራ ፊቱን ለዘልዓለሙ ወደ አንድ ጎን ልታጣምመው ትችላለችና፡፡ በአራተኛ ደረጃ ለጂንኒ ጥቃት የሚጋለጠው በውድቀት ሌሊት መሄድ የሚያበዛ ሰው ነው፡፡ በተለይ ሌሊት በተራራማና ጸጥተኛ በሆነ ሜዳማ ስፍራ የተገኘ ሰው የጂንኒ ጦርና ፍላፃ  ይወረወርበታል፡፡

   አንዳንድ ተንኮለኛ ጅንኒዎች ግን ሰዎችን ለማጥቃት ምንም ምክንያት አይፈልጉም፡፡ ሰዎች ባልጠበቁት ስፍራና አጋጣሚ ሁሉ እነዚህ ተንኮለኛ ጂንኒዎች መርዛማ ቀስታቸውንና ጨረራቸውን ሊወረውሩ ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ አንዲት ጅንኒ እናንተ ሳታዩዋት “እገሌ” ብላ ልትጠራችሁ ትችላለች፡፡ በተለይ ሰው በሌለበት ምድረ በዳ፣ በተራራ ላይ፣ በደንና በማሳ ውስጥ ወዘተ ተንኮለኛ ጅንኒዎች ስንቱን ሚስኪን ሰው እየጠሩ ጉድ አድርገውታል፡፡ ከእንደዚህ ዓይነት ጅንኒ ራሱን መጠበቅ የሚፈልግ ሰው የተጣሪውን ማንነት ሳያጣራ “አቤት” ማለት የለበትም፡፡ “አቤት” ካለ ግን እድሉ ያውጣው! እርሱን የጠራው ፍጡር የሰው ልጅ ከሆነ በርግጥም ቀኑ አልደረሰም ማለት ነው፡፡ “ጅንኒ” የጠራችው እንደሆነ ግን ሰውየው ከዓለም ላይ መሰናበቱን ይወቅ! ቢበዛ ሶስት ቀን ብቻ በህይወት ቢቆይ ነው፡፡

   እንዲህ አይነት ነገር የገጠመው ሰው በ“ጅንኒ” መጠራቱንና በሰው ልጅ መጠራቱን እንዴት መለየት እንደሚችል አውቃችኋል? ቀላል ነው፡፡ የጥሪው ድምጽ ወደ መጣበት አቅጣጫ ዞር ብሎ ማየትን ብቻ ነው የሚጠይቀው፡፡ በዚያ አቅጣጫ ሰው ከሌለ “ጅንኒ” ናት ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ሰውየው ከቻለ “ያሲን” እና “ተባረክ” እየቀራ፣ ካልቻለም “አዑዚ ቢላሂ ሚነ-ሼይጣኒ ረጅም” ብሎ ከአካባቢው በቀስታ መልቀቅ አለበት፡፡ በሌላ  በኩል ሰውየው የሰማው የወንድ ድምጽ ሆኖ ሳለ ወደ ድምጹ አቅጣጫ ሲዞር ሴት ካጋጠመው፣ ወይንም የህጻን ድምጽ ሰምቶ ሽማግሌ ከታየው በርግጥም እርሱን የጠራችው “ጅንኒ” ናት ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ይህ ሰው ህይወቱን ማትረፍ ከፈለገ በቶሎ “አዑዙ ቢላሂ” ይበልና ከአካባቢው ላፍ ብሎ ያምልጥ፡፡ እምቢ ካለ ቁርጡን ይወቅ! እኛ የለንበትም፡፡
                *****  *****  *****
የጅንኒ ወጋችን ተጀመረ እንጂ አላለቀም፡፡ የጂንኒ የሌብነት ጉዞ፣ የጅብና የጂንኒ ጦርነት፣ የጂንኒ እና የምስጥ ውል፣ የቀለበቷ ሚስጢር፣ የጂንኒ ሸጎዬ ጨዋታ፣ የአስማእና የኢፍሪት ወግ.፣ የልዩ ልዩ ሰዎች የጂንኒ ገጠመኝ ወዘተ… ገና ይቀሩናል፡፡ በሚቀጥለው ሌሊት እንመለስባቸዋለን፡፡

  በነገራችን ላይ የምስራቅ ኢትዮጵያ ልጆች “ወዘተ” ለማለት ሲፈልጉ እንዴት እንደሚሉ በደንብ ታውቁታላችሁ አይደል? “ጅንኒ ጃንካ”፣ “ጂንኒ ቁልቋል”፣ “ጂንኒ ጀቡቲ”፤ “ጂንኒ ጡጡሩቅ”… ከተሰኙት ሐረጎች አንዱን መምረጥ ነው፡፡ እኛ “ወዘተ”ን የተማርናት በትምህርት ቤት ነው፡፡
   “ጅንኒ” ለዛሬ እንዲህ ናት፡፡ በሉ አሁን “አዑዙ ቢላሂ” በሉ፡፡
---
አፈንዲ ሙተቂ
ነሐሴ 25/2005

No comments:

Post a Comment