Monday, April 1, 2013

የገለምሶው “አቦ ደርጂ” ጨዋታዎች


    ጸሓፊ፡- አፈንዲ ሙተቂ
 
በተወለድኩባት ከተማ ስማቸው ገኖ ከሚወራላቸው ጥቂት ሰዎች መካከል አንዱ ናቸው። እኝህ ሰው የናጠጠ ቱጃር ወይንም የመሬት ከበርቴ አልነበሩም። “የሼኽ እገሌ ቤተሰብ አባል” ወይም “የሸሪፍ እገሌ ዝሪያ” የሚባሉ አይነትም አይደሉም። ይሁንና የከተማችን ተወላጆች ከመሬት ከበርቴም ሆነ ከናጠጠ ቱጃር በላይ ያስታዉሷቸዋል። በተለይ ከእርሳቸው ጋር በጉርብትናና በአጥቢያ (ሰፈር) የምናዛመድ ሰዎች ዘወትር አንዘነጋቸውም።
      ደርጂ ሙሳ ይባላሉ። ተወላጅነታቸው በጭሮ (ዐሰበ ተፈሪ) ቢሆንም ከጣሊያን ዘመን ጀምሮ ህይወታቸው እስክታልፍ ድረስ በገለምሶ ከተማ ነው የኖሩት። በቀልደኝነታቸውና በጨዋታ አዋቂነታቸው የከተማው ሰው በሙሉ ይወዳቸዋል። መከራ በገጠማቸው ጊዜ ከጥቃት ለማምለጥ የሚፈጥሯቸው ብልሀቶችም የብዙዎችን አድናቆት አስገኝተውላቸዋል። በዚህም የተነሳ የከተማችን ነዋሪዎች “አቦ ደርጂ” እያሉ ነው የሚጠሯቸው። (“አቦ” በኦሮምኛ “አባት” እንደማለት ነው። ታዲያ ይህኛው “አቦ” ሲነበብ ጠበቅ ይላል። ላልቶ ከተነበበ ትርጉሙ ይለወጥና “አንተ” እንደማለት ይሆናል)። የ“አቦ ደርጂ” ጨዋታ አዋቂነትና አባ-መላነት ከከተማችንም አልፎ በአጎራባች ከተሞች ጭምር በመናኘቱ በህይወት እያሉ ተረት እስከመሆን ደርሰዋል (ልክ እንደ ጋሼ ስብሃት ማለት ነው)። እነሆ እኔም ከአቦ ደርጂ ጨዋታዎች መካከል ለበረካ ያህል አንዳንዶቹን አጫውታችኋለሁ።
*****  *****  *****
   አንድ ጊዜ ጓድ ሊቀመንበር መንግስቱ ኃይለማርያም በገለምሶ አቅራቢያ ያለችውን “ዴፎ” የተሰኘች አነስተኛ ከተማ ለመጎብኘት እንደሚመጡ ይነገራል። የገለምሶ ህዝብም “ቆራጡ መሪያችን በከተማችን ሲያልፉ ሰላምታ እንድትሰጧቸው” የሚል አስገዳጅ ጥሪ ተላልፎለታል። በጥሪው መሰረትም “አቦ ደርጂ” ለጓድ ሊቀመንበር አብዮታዊ ሰላምታ ለመስጠት ከአካባቢው ሰዎች ጋር በሱቃቸው ፊት ለፊት በሚያልፈው መንገድ ዳር ይቆማሉ። ሆኖም “መንጌ” በተባለው ጊዜ አልደርስ አሉ። ለረጅም ሰዓት መንገድ ዳር መቆሙ ያሰለቻቸው አቦ ደርጂ “ለአንድ ሰው ብለው ስራ ያስፈቱናል፤ ይህንን ሁሉ ህዝብ መንገድ ዳር ለረጅም ሰዓት ማስቆም አግባብ ነው? ስራ ፈት ካድሬ ሁሉ!” እያሉ ማጉተምተም ጀመሩ። ለካስ አንድ ነጭ ለባሽ (ሲቪል ለባሽ የደህንነት ሰው) ከአጠገባቸው ቆሞ ይሰማቸው ኖሯል? ወዲያውኑ ፖሊሶችን ጠርቶ “እርምጃ ይወሰድባቸው” ከሚል ትዕዛዝ ጋር ወደ አውራጃው ፖሊስ ጣቢያ አስወሰዳቸው።
    የአውራጃው ፖሊስ አዛዥም ከፊቱ የቆሙትን አቦ ደርጂ እያየ “እህስ ሽሜ! ቅድም ምን ስትል ነበር?” በማለት ይጠይቃቸዋል። ነገሩ ክፉ አደጋ ሊያስከትልባቸው እንደሚችል አስቀድሞ የተረዱት አቦ ደርጂም “አሃ! ጫቱን ነው?” አንተ ካልክ እሺ! አንተ እንደፈለግክ አደርጋለሁ!” በማለት በአፋቸው የሚያመነዥኩትን ጫት በፊታቸው ላይ ይለቀልቁት ገቡ። ነገሩ ያስደነገጠው የፖሊስ አዛዥ “አንተ ሰውዬ! ምን እያደረግክ ነው? ማን ነው በጫት ፊትህን አበላሸው ያለህ?” በማለት ደነፋ። አቦ ደርጂም ምንም ሳይሸበሩ “አንተ ካልክ አደርገዋለሁ! ምን ገዶኝ! ይኼው አደርገዋለሁ!” በማለት የታጠቁትን ሽርጥ ፈትተው ጣሉትና ከወገብ በታች ራቁታቸውን ቆሙ። ይሄኔ አዛዡ በጣም ተደናገረና በአቅራቢያው የነበረውን አንድ ፖሊስ ጠርቶ “አንተ ወታደር! ሽማግሌው እብድ ነው! ቶሎ ከዚህ አስወጣው” በማለት ትዕዛዝ ሰጠ። አቦ ደርጂም በዚያች በቅጽበት በፈጠሩት መላ ህይወታቸውን ከሞት አተረፏት።
*****  *****  *****
    በደርግ ውድቀት ማግስት አቦ ደርጂ አዲስ ሚስት አገቡ። ይህች ሚስት የደም ግባቷ በጣም የተወራላት ከመሆኗም በላይ በእድሜዋ በሀያዎቹ መጨረሻ ገደማ የምትገኝ ነበረች። እናም ሽማግሌው አቦ ደርጂ ወጣት ሚስት ማግባታቸው በመላው የገለምሶ መንደሮች መነጋገሪያ ሆኖ ነበር። በነገሩ የተገረሙት አንድ ጎልማሳም ወደ አቦ ደርጂ ዘንድ ይሄዱና “አንተ ለራስ ጥርስ የለህ፣ አርጅተሃል፣ ምን ልሁን ብለህ ነው በስተ እርጅና ሚስት የምታገባው?” በማለት ይጠይቁአቸዋል። አቦ ደርጂ በነገሩ እየሳቁ “ወይ ጉድ! እናንተ ጥርሰ በረዶዎች ሚስቶቻችሁን በጥርሶቻችሁ ነው የምትነካክሱት እንዴ?” በማለት ጥያቄውን በጥያቄ መለሱት።
*****  *****  *****
   በዚህች ወጣት ሚስታቸው ሳቢያ ነገር የበዛባቸው አባ ደርጂ ሌሎች ሰዎች ሚስቴን ሊያስኮበልሉብኝ ይችላሉ የሚል ፍራቻ አድሮባቸው ነበር ይባላል። ታዲያ ነጅብ ኢድሪስ የሚባለው የከተማችን ነጋዴ በዚያው ሰሞን የደረሰበትን አንድ ነገር እንደሚከተለው አጫውቶኝ ነበር።
   አቦ ደርጂ ለቅሶ (ታዚያ) ለመድረስ ራቅ ወዳለ ሰፈር ይሄዱና ይመሽባቸዋል። ወደቤታቸው ለመመለስ ቢፈልጉም የጨለማው ነገር የሽማግሌ አይናቸውን የማይመጥን ሆኖ ያገኙታል። ስለዚህ ለታዚያ (ለቅሶ) በተተከለው ድንኳን ውስጥ ያሉትን ሰዎች ወደ ቤታቸው እንዲያደርሷቸው ትብብር ይጠይቃሉ። በዚህ መሰረትም ከላይ የጠቀስኩት ነጅብ ኢድሪስ ፈቃደኛ ሆኖ እስከቤታቸው ድረስ ሊወስዳቸው ይነሳል።
   ሁለቱ ሰዎች መንገዳቸውን ጀመሩ። ነጅብ ባትሪውን ለአቦ ደርጂ ሰጥቶ ለራሱ ፊት ቀድሞ መጓዝ ጀመረ። እናም በአጭር ጊዜ ውስጥ ከቤታቸው አደረሳቸው። ነጅብ መንገዱን ሳይስት ከቤታቸው መድረሱ ያስገረማቸው አቦ ደርጂ ምስጋናቸውን ካቀረቡለት በኋላ “Ammoo Kharaa mana khiyyaa khana akkamitti akkati haffazde?” (“ግን ወደቤቴ የሚያደርሰውን መንገድ እንዴት ነው እንዲህ የሸመደድከው?”) በማለት ከልቡ አሳቁት።
    አቦ ደርጂ ወጣት ሚስት ከቤት ውስጥ እንዳላቸው የሚያውቀው ነጅብ “ኖራ ነጭ ነው” እንዲሉት አይጠብቅም። ለዚህም ነው በነገሩ ከአንጀቱ የሳቀው (እኔም ከአቦ ደርጂ ጨዋታዎች ሁሉ በጣም ያሳቀኝ ይህኛው ነው)።
******************
     በደርግ ጊዜ ሁሉም ጎልማሶች መሰረተ ትምህርት እንዲማሩ በሚያስገድደው ደንብ መሰረት አቦ ደርጂም ለትምህርት ገብተው ነበር። ግን የትምህርቱ አሰልቺነት በወቅቱ ከነበሩበት የኑሮ ሁኔታ ጋር ተዳምሮ አቦ ደርጂን ያነጫንጫቸው ገባ (በወቅቱ የመጀመሪያ ባለቤታቸውን በሞት የተነጠቁት አቦ ደርጂ ልጆቻቸውን እንደ እናትም እንደ አባትም ሆነው ያሳድጉ ነበር)። በዚህም የተነሳ አንድ ሰበብ ፈጥረው ከትምህርቱ ገበታ ለመጥፋት ወሰኑ። በዚህ ሁኔታ ላይ እያሉም ትምህርቱን የሚያስተምረው አስተማሪ አንድ ቀን የሂሳብ ጥያቄ ያቀርብላቸዋል።
“አቦ ደርጂ፣ አንድ ሲቀነስ አንድ ስንት ነው የሚሆነው?”
“እኔ ስለመቀነስ አላውቅም፤ መደመር ጠይቀኝ”
“እንዴት አያውቁም? ነጋዴ አይደሉም?”
“ነጋዴ ብሆንም ስለመቀነስ አላውቅም”
 
   ነገሩ ግራ የገባው አስተማሪ በምሳሌ ማስረዳት አማረውና “ለምሳሌ አቦ ደርጂ፤ አንድ ሙዝ አለኝ እንበል። እርሱን ብበላው ምን ያህል ይቀረኛል?” በማለት ይጠይቃል። አቦ ደርጂም “አይ አስተማሪው! ልጣጩ እንጂ ምኑ ነው የሚቀረው” የሚል ምላሽ ሰጡት። ይህንን የሰሙት በክፍሉ ውስጥ የነበሩት ጎልማሳ ተማሪዎች በሙሉ በሳቅ ያውካካሉ። አስተማሪው ግን በነገሩ ይናደድና ቂም ቢጤ ይቋጥራል።
   በሌላ ጊዜ ደግሞ አስተማሪው አንድ ስነ-ግጥም በጥቁር ሰሌዳው ላይ ይጽፍና ተማሪዎቹን “በደብተራችሁ ገልብጣችሁ አሳዩኝ” በማለት ያዛቸዋል። አቦ ደርጂም በደብተራቸው ላይ ምንነቱ የማይገባ ነገር ሙጭርጭር አድርገው ይጽፉና ለማሳረም አስተማሪው ዘንድ ይወስዱታል። ታዲያ መምህሩ ነገሩን ሲያይ በአቦ ደርጂ አድራጎት እጅግ ተደንቆ “ይህ ደሞ ምንድነው?” በማለት ይጠይቃቸዋል። እርሳቸውም “ጽሁፍ ነው” በማለት በአጭሩ ይመልሳሉ። መምህሩም “የምን ጽሁፍ ነው? እንዴትስ ተደርጎ ነው የሚነበበው?” በማለት መልሶ ሲጠይቅ አቦ ደርጂም ዘና በማለት “አስተማሪው! ጽሁፉን ከቻልክ አንብበው፤ ካልቻልክ ለበላይ አካል አስተላልፈው፤ ራስህን ብዙም አታስጨንቀው” የሚል አብሻቂ መልስ ሰጡት። የአቦ ደርጂ ነገር ያልጣመው አስተማሪ “እርስዎ ትምህርት አይፈልጉም፤ስለሆነም ሁለተኛ እዚህ እንዳይመጡብኝ” በማለት አሰናበታቸው። በዚህም ብልሃት አቦ ደርጂ ከመሰረተ ትምህርቱ መድረክ ተለዩ።
     *****     *****   *****  
  አቦ ደርጂ ዘወትር የሚታወሱበት አንዱ ባህሪ ድፍረታቸው ነው። አንደበታቸው እንደ ብዙዎቻችን በይሉኝታ ገመድ የተሸበበ ስላልሆነ ያልጣማቸውን ነገር ፊት ለፊት ከመቃወም ወደ ኋላ አይሉም። ታዲያ እምቢ ባይነታቸው በደረቅ ቃላት የተደረተ አይደለም። እውነትን በሰፊው ይገልጻል። አንዳንዴ ደግሞ በአዝናኝነቱ የሁል ጊዜ ተጠቃሽ ሆኖ ይኖራል። ለዚህም ሁለት አብነቶችን ልስጣችሁ።
   ኢሕአዴግ ሀገሪቱን ከተቆጣጠረ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ነው። ስለ አዲሱ ስርዓት አካሄድና ስለዜጎች መብት በሚል በየቀበሌው ህዝባዊ ስብሰባ ይካሄድ ነበር። አቦ ደርጂ በታደሙበት አንድ ስብሰባ ደግሞ የመድረኩ መሪ አደም አብደላ (በቅጽል ስሙ “ጉመ ከፈል”) የሚባል የምዕራብ ሀረርጌ ዞን አስተዳዳሪ ነው። ታዲያ “ጉመ ከፈል” ስብሰባውን እየመራ ሳለ በአዳራሹ የመጀመሪያ ረድፍ ላይ ወደ ተቀመጡት አቦ ደርጂ እያየ እንዲህ አላቸው።
    “አባቴ፣ እርስዎ ትልቅ ሰው ነዎት፤ ቢያንስ ሶስት መንግስታትን አይተዋል። እስቲ የኃይለ ስላሴን፣ የደርግንና የአሁኑን መንግስት በማነጻጸር ሀሳብዎትን ይስጡኝ።”
አቦ ደርጂም “የእውነት መልስ ነው የምትፈልገው ወይስ ውሸት እንድናገር ነው የምትፈልገው?” አሉ።
    ጉመ-ከፈልም “እውነት ነው እንጂ ውሸት ምን ይሰራልኛል?” አላቸው።
አባ ደርጂም “ጥሩ! ኃይለስላሴ በድንቁርና ፈጀን። ከባላባት ልጆች በስተቀር የኛ ልጆች መማር አይችሉም ነበር። ደርግ ደግሞ “ቀይ ሽብር” እና “አብዮታዊ ዘመቻ” እያለ ልጆቻችንን ጨረሰብን። ስለአሁኑ መንግስት ግን ከወረደ በኋላ ብትጠይቀኝ ይሻላል” በማለት የዞኑን አስተዳዳሪና በአዳራሹ የነበረውን ህዝብ በሳቅ አፈረሱ።
     *****     *****   *****  
    ዝናብ በጠፋበት በአንድ ወቅት ደግሞ ህዝቡ በመስጊድ ውስጥ ከሰላት (ስግደት) በኋላ ፈጣሪውን ይለማምናል። የመስጊዱ ኢማም ከተቀመጡበት ተነስተው ህዝቡ ቀንም ሆነ ማታ ፈጣሪውን መማጸኑን እንዳይተው አሳሰቡ። በመስጊዱ የነበረውም መላው ህዝብ ይሁንታውን ገለጸ። አቦ ደርጂ ግን “የምን ዝናብ ነው የምታወሩት? አይሆንም! እስቲ ይዝነብ!” በማለት ተቃውሞአቸውን አሰሙ። በዚህም የተነሳ በመስጊዱ የነበረው ህዝብ ተደናገጠ።
     ኢማሙ ግን “ቆዩ! ረጋ በሉ!” ካሉ በኋላ አቦ ደርጂ እንደዚያ ያሉበትን ምክንያት እንዲያስረዱ ጠየቁአቸው። እርሳቸውም “አምና የነፈሰው ሀይለኛ ነፋስ የቤቴን ጣሪያ ነቃቅሎት እንዳልነበረ አድርጎታል። ዘንድሮ ዝናቡ ከደገመኝ ደግሞ እኔና ልጆቼ የምንደርስበት ቦታ አጣን ማለት ነው። ስለዚህም ነው አይዝነብ ያልኩት” በማለት ተናገሩ።
ይህንን የሰሙት የመስጊዱ ኢማም ወደ ህዝቡ በመዞር “አያችሁ ሰዎች! ፈጣሪ የሚቀጣን እኮ ሀጢአታችን ስለበዛ ነው። እንደ አቦ ደርጂ ያሉ ሽማግሌዎችን ስለማናስታውስ ዝናቡም ይጠፋብናል። አሁን በአስቸኳይ ለአቦ ደርጂ ጣሪያ ጉዳይ መፍትሔ መፈለግ አለብን” አሉ። ወዲያው በመስጊዱ የነበረው አንድ ነጋዴ “የአቦ ደርጂን ጣሪያ እኔ ራሴ ነገውኑ አሰራዋለሁ” በማለት ሀላፊነት ወሰደ። ቃሉንም በሚቀጥለው ቀን ተግባራዊ አደረገ።
    እንግዲህ የአቦ ደርጂ ድፍረት እንዲህ ነው። በመስጊድም ውስጥ ቢሆን የተሰማቸውን ከመናገር ወደ ኋላ አይሉም። ሌላ ሰው ቢሆን ኖሮ ይሉኝታ ይዞት በዝምታው ይጸናል። ነገር ግን ይሉኝታ በሁሉም ቦታ አይሰራም። በተለይ መጠለያን በመሰለ መሰረታዊ ነገር ላይ አደጋ የሚጋርጥ ሁኔታ ሲፈጠር በዝምታ ማለፍ አግባብነት የለውም።
     *****     *****   *****  
   አንድ ጊዜ አቦ ደርጂ ታመሙ። በአካባቢው የነበርን ሰዎች ተሰባስበን ወደ ሀኪም ቤት ወሰድናቸው። ተረኛ ሀኪሙም ከመረመራቸው በኋላ መርፌ አዘዘላቸው። መርፌውን የሚወጋቸው ነርስም መጣ። መድኃኒቱንም ከሲሪንጅ ውስጥ ጨምሮ በታፋቸው ላይ ሰካ። መርፌው ግን በጣም ስላሳመማቸው አቦ ደርጂ በሀይለኛ ሁኔታ ተቆጡ፤ ነርሱንም እንዲህ አሉት፣ “አንተ! በኔ ላይ እየተለማመድክ ነው እንዴ?”
ከአሁን አሁን አንድ ነገር ይናገሩ ይሆናል ብለን የምንጠብቀው ሰዎችም ሀኪም ቤቱን በሳቅ ሞላነው።
     *****     *****   *****  
     የአቦ ደርጂ ልጅ ካገባ አንድ ሶስት ወር ሆኖታል። በዚያው ሰሞን የተወሰንን ሰዎች ከርሳቸው ጋር በመንገድ ላይ ተገናኘን። አንዱ ጓደኛችንም ወሬ ለመጀመር ያህል “አቦ ደርጂ! ልጅዎት እኮ አገባ!” አላቸው። እርሳቸውም ቀድመው የሰሙት ነገር በመሆኑ ቀዝቀዝ ያለ መልስ ሰጡት።  ሌላው ጓዳችን ደግሞ “ኧረ! እኔ እንዲያውም ወለደ ሲሉ ነው የሰማሁት” አላቸው። ይሄኔ አቦ ደርጂ “Mucaan khiyya baatii sadii kheessatti yoo dhale intalti inni fuudhe “Bukkurii” jechuudha gaa!” (“ልጄ በሶስት ወሩ የሚወልድ ከሆነ “ቡኩሪ” ነው ያገባው ማለት ነዋ!” በማለት ማንም ያልጠበቀውን ንግግር ተናገሩ። አቤት የዚያኔ የሳቅነው ሳቅ! እስካሁን ድረስ አይረሳኝም።
   (ማስታወሻ፡- ቡኩሪ የሀረርጌ ገበሬዎች በበልግ ወቅት የሚዘሩት የበቆሎ ዝርያ ነው። ይህ የበቆሎ ዓይነት ከሶስት ወራት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ለምግብነት ይደርሳል። አቦ ደርጂም “ልጄ ያገባት ሚስት በሶስት ወራት ውስጥ ከወለደች ልክ እንደ ቡኩሪ በአጭር ጊዜ የምታፈራ ዘር መሆን አለባት” ማለታቸው ነው።)
     *****     *****   *****  
    የሀብታም ቤተሰብ ተብለው ከሚጠቀሱት አንዱ ነው። የዚህ ቤተሰብ ሰዎች ልጃቸውን ለመዳር ያስቡና በአካባቢው በሚታወቀው ባህል መሰረት “ጂማ” (የሽምግልና ጫት”) ለማስገባት ይወስናሉ። አቦ ደርጂንም ለሽምግልና ወደ ልጅቷ ቤት በሚላከው ቡድን ውስጥ ለማካተት በማሰብ ያማክሯቸዋል። አቦ ደርጂ ግን በነገሩ ከት ብለው በመሳቅ “እኛ ዘወትር ጫታችንን እየቃምን ነው፤ አልሐምዱሊላህ! ፈጣሪ ለበርጫ የሚሆነን ያህል ነፍጎን አያውቅም። ባይሆን እኛን ድኩማኑን መጥራት ያለባችሁ ሰንጋ ተጥሎ ጥብስና ክትፎው በሚደረደርበት ቀን ነው፤ አደራ ያኔ እንዳትረሱኝ!” አሏቸው። እውነትና ብስለት የሞላበት ንግግር ! በድህነት የሚኖሩትን ወገኖች ”ሀጃ” (ጉዳይ) ሲይዛቸው ብቻ ለሚያስታውሱት የሀብታም ከንቱዎች የሚገባ መልስ ነው። 
   በአንድ ወቅት እንዲህ ዓይነቱ ነገር በከተማችን ውስጥ በስፋት ይታይ ነበር። ሀብታም የሚባል ሰው ድሃውን የሚያስታውሰው ጉዳይ ሲይዘው ብቻ ነው። በሀብታም ሰርግ ላይ የሚታደሙትም ሀብት ያላቸው ወገኖች ብቻ ናቸው። አባ ደርጂም በጊዜው የተቃወሙት እንዲህ አይነቱን ኢ-ሞራላዊ ድርጊት ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የድሮው ብልሹ ስርዓት እየቀረ ነው። ወደፊት የበለጠ መሻሻል ይታያል ብለን ተስፋ እናደርጋለን።
     *****     *****   *****  
   የገለምሶው አቦ ደርጂ ጨዋታዎች ብዙ ናቸው። እኔ ያልሰማኋቸው በርካታ ወጎች እንዳሉም አምናለሁ። ለወደፊቱ ሁሉንም በማሰባሰብ ለአንባቢያን ለማቅረብ እሞክራለሁ። ለአሁኑ ግን በዚሁ ይብቃኝ። ፈጣሪ የአቦ ደርጂን ነፍስ በጀንነት ያኑራት!
  ሰላም!
አፈንዲ ሙተቂ
መጋቢት 11/2005 ዓ.ል.
ሀረር

No comments:

Post a Comment