Friday, December 12, 2014

ኢትዮጵያዊው “ጌታቸው ካሳ” እና ሱዳናዊው “ሳላሕ ኢብን ባዲያ”




አፈንዲ ሙተቂ
----
የአንጋፋው አርቲስት የጌታቸው ካሳ እውነተኛ ስም “ጌታቸው እሸቴ” ነበረ፡፡ ይህ አርቲስት በኪነ-ጥበቡ ተማርኮ መዘፋፈን ሲጀምር አባቱ ድምጹን በሬድዮ ይሰሙታል፡፡ አባት “ልጅህ አዝማሪ ነው” መባላቸው ክብራቸውን የሚቀንስ ሆኖ ስለተሰማቸው ልጃቸውን ያስጠሩትና እንዲህ አሉት፡፡ “ከዛሬ በኋላ ከዘፈንክ ግንባርህን በጥይት እበሳዋለሁ”፡፡
 
Salah ibn Badiya, One of the legendary Sudanese pop stars.

 ልጅ ጌታቸው ግን በአባቱ ማስፈራሪያ አላረፈረም፡፡ ከውስጡ የሚንቀለቀለው የጥበብ ዛር አላስቀምጥ ስላለው ከአባቱ እየተደበቀ ወደ ዘመኑ ክለቦችና ልዩ ልዩ መድረኮች ጎራ እያለ መዝፈኑን ቀጠለ፡፡ በዚህን ጊዜም በአንጋፋው ጋዜጠኛ ጌታቸው ደስታ ዐይን ውስጥ ገባ፡፡ ጌታቸው ደስታም ወጣቱን ድምጻዊ በሬድዮ እንዲዘፍን ጋበዘው፡፡ ነገር ግን የዘፋኙ አባት ልጃቸው በሬድዮ እንደዘፈነ ቢሰሙ በልጁ ላይ አደጋ ሊያደርሱ እንደሚችሉ ገመተ፡፡ ስለዚህ ወጣቱን ለመደበቅ እንዲቻል ስሙን “ጌታቸው ካሳ” በማለት ቀየረው፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ተወዳጁ አርቲስት ላለፉት አርባ አምስት ዓመታት ጌታቸው ካሳ ተብሎ እየተጠራ ነው፡፡
*****
አንጋፋው ሱዳናዊ ድምጻዊ “ሳላሕ ኢብን ባዲያ”ም ከኛው ጌታቸው ካሳ ጋር የሚመሳሰልበት ታሪክ አለው፡፡ የሳላሕ እውነተኛ ስሙ ሳላሕ ሼኽ ሙሐመድ ነበረ፡፡ በወጣትነቱ የዘፈናቸው ዘፈኖች በኦምዱርማን ሬድዮ ሲተላለፉ አባቱ እሳት ጎርሰው እሳት ለብሰው መጡለት፡፡ “አንተ አዝማሪ! ልታዋርደኝ ነው የምትፈልገው?… ከዛሬ ጀምሮ በኔ ስም የምትጠራ ከሆነ እረግምሃለሁ! ውርድ ከራሴ!” በማለት አስጠነቀቁት፡፡

  ሳላሕ የአባቱን ማስጠንቀቂያ ተቀበለ፡፡ ነገር ግን የአባቱን ስም ትቶ በሐሰት ስም መጠራቱን ነፍሲያው አልቀበል አለች፡፡ አሕመድ፣ ሰይድ፣ ኢብራሂም፣ ሱፍያን በመሳሰሉት የዐረብኛ ስሞች መጠራቱ አላመችህ አለው፡፡ ማን ተብሎ ይጠራ እንግዲህ?….  አንድ ቦታ ቁጭ ብሎ ሲያሰላስል እንዲህ የሚል ሐሳብ መጣለት፡፡

  “ሳላሕ አንተ የተወለድከው በገጠር ነው አይደል?… ለምን የገጠር ልጅ ነኝ ብለህ አትጠራም?… እግረ መንገድህንም የገጠር ሰው ታላቅ ተአምር መስራት እንደሚችል ታሳይበታለህ”

ሳላሕ በድንገት ውልብ ያለበትን ሓሳብ በተግባር ላይ ሊያውለው ተነሳ፡፡ የመጀመሪያ አልበሙን ሲያሳትምም “ሳላሕ ኢብን ባዲያ” (ሳላሕ የገጠር ልጅ) የሚል ስም ተጠቀመ፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ለሃምሳ ዓመታት በዚህ ስም እየተጠራ ነው፡፡
*****
ሳላሕ ኢብን ባዲያ ሱዳን ካበቀለቻቸው አንጋፋ አርቲስቶች አንዱ ነው፡፡ የሱዳንን ሙዚቃ በፍቅር የሚያዳምጡ አድናቂዎቹ በተለይም እንደ ብራቅ በሚወጣው ድምጹ በጣም ይገረማሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት እድሜው ወደ ሰባዎቹ አጋማሽ ቢሆንም በአዘፋፈን ዘይቤው ላይ ምንም ድካም አይታይበትም፡፡
ከሳላሕ ኢብን ባዲያ ዘፋኖች መካከል የሀገራችን ሙዚቃ አፍቃሪያን በደንብ የሚያዉቁት “ሻዕረ ዘሐብ” የሚለውን ዜማ ይመስለኛል፡፡ በነገዋ ዕለተ ቅዳሜ ከሳላሕ ቢን ባዲያ ጋር በሓሳብ ወደ ኦምዱርማን ትበሩ ዘንድ ይህንኑ ጨዋታ ጋብዘናችኋል፡፡
(ሳላሕ “ሻዕረ ዘሐብ”ን ሲዘፍን ለማየት ይህንን የዩቲዩብ ሊንክ ይክፈቱ)
-----
አፈንዲ ሙተቂ
ታሕሳስ 4/2007
ሀረር-ምሥራቅ ኢትዮጵያ
---
The writer, Afendi Muteki, is a researcher and author of the ethnography and history with special focus on the peoples of East Ethiopia. You may follow him on his blog and his facebook page by clicking the following links



“ቺርስ”- ለኢትዮጵያና ኤርትራ ህዝቦች ወዳጅነት




(አፈንዲ ሙተቂ)
------
አሁንም ግን እደግመዋለሁ!! እኔ ህልመኛ ነኝ! ይህ የኔ ህልም በፈጣሪም ሆነ በሰው ልጆች ዘንድ “ብሩክ” ተብሎ የሚወደስ ነው፡፡ ስለህዝቦች ፍቅር፣ ህብረት፣ አንድነትና እኩልነት ማለም የዘወትር ተግባሬ ነው፡፡ መቼም ቢሆን ይህንን ከማድረግ ወደ ኋላ አልልም፡፡ እንኳንስ በደንብ የማውቃቸውን የኤርትራና የኢትዮጵያ ህዝቦችን ይቅርና አምስቱ የምስራቅ አፍሪቃ ሀገራት (ሱዳን፣ ኢትዮጵያ፣ ሶማሊያ፣ ጅቡቲና ኤርትራ) በኮሎኒያሊስቶች የተሰመሩ ድንበሮችን በጣጥሰው በአንድ ግዛት ስር እንዲጠቃለሉ በጽኑ አልማለሁ፡፡ ምን ይሄ ብቻ! ትልቋ እማማ አፍሪቃም አንድ ሀገር እንድትሆን በብርቱ ነው የማልመው፡፡
*****
ኤርትራና ኢትዮጵያ ሰው ሰራሽ ችግሮች በቆሰቆሷቸው አቧራዎች መነሾነት ሁለት ሀገር ሆነዋል፡፡ ፍቺያችን በደም የታጀበ መሆኑ በጣም ያሳዝነናል፡፡ ያስለቅሰናል፡፡ ይህ ማለት ግን “አንድ ላይ የመሆናችን ጉዳይ ለዘልዓለሙ አብቅቶለታል” ማለት አይደለም፡፡ ሰው ሰራሽ ድንበር በኛ መካከል ቢሰመርም ባህል፣ ታሪክ፣ ቋንቋና ጂኦግራፊ በአንድ ላይ ያስተሳስረናል፡፡ የህዝቦቻችን የጋራ ታሪካዊ ውቅር መቼም ቢሆን አይፋቅም፡፡ 

  እኛና ኤርትራዊያን በጣም ነው የምንመሳሰለው፡፡ እንዲህ የሚመሳሰሉ ህዝቦች የማታ ማታ ተመልሰው አንድ የሚሆኑበትን ሁኔታ የዓለም ታሪክ አሳይቶናል፡፡ ሁለቱ ጀርመኖች ከአርባ አምስት ዓመታት በኋላ ተዋህደዋል፡፡ ሁለቱ የመኖችም ከሰላሣ ዓመታት በኋላ ሲዋሃዱ አይተናል፡፡ ታዲያ ይህንን እያየን የምን ተስፋ መቁረጥ ነው?

   እኛና ኤርትራዊያን ከመመሳሰልም አልፎ በጣም ነው የምንቀራረበው፡፡ በጣም እንዋደዳለን፡፡ ይህንን በቀላሉ ለመረዳት ኤርትራዊያንና ኢትዮጵያዊያን በዲያስፖራው ክፍለ-ዓለም የሚኖሩበትን ሁኔታ ማስተዋል ይበቃል፡፡ ወደየትኛውም የዓለም ሀገር ሄደን ብናይ ከማንም በላይ ለኤርትራዊያን የሚቀርቡት ኢትዮጵያዊያን ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ ለኢትዮጵያዊያንም ከማንም በላይ የሚቀርቡት ኤርትራዊያን ናቸው፡፡ አምና (በህዳር ወር 2005) የሳዑዲ ዐረቢያ የጸጥታ ሀይሎች በኢትዮጵያዊያን ላይ የወሰዱትን በደልና ግፍ የተቀላቀላበትን ከሀገር የማባረር እርምጃ ከኢትዮጵያዊያን ጎን ቆመው ሲያወግዙ የነበሩት ኤርትራዊያን ብቻ ነበሩ፡፡ ኢትዮጵያዊያን ባካሄዷቸው ሰልፎች ላይ ከኤርትራዊያን በስተቀር የሌላ ሀገር ዜጋ አልተሳፈተም፡፡
  
   የሜዲትራኒያን ባህርን በህገ-ወጥ ጀልባዎች በማቆራረጥ ወደ አውሮጳ ሲከንፉ ባህሩ የሚበላቸው ኢትዮጵያዊያንና ኤርትራዊያን ምንዱባንስ እንዴት ይረሳሉ?… ስለነርሱ በምንሰማው መጥፎ ዜና ሁለታችንም አንድ ላይ “እህ!” እያልንና በቁጭት እየተቃጠልን አይደለም እንዴ?… መርዶአቸው በአንድ ላይ እየደረሰን በአንድ ላይ ለቅሶ እየተቀመጥን አይደለም እንዴ?…

በደጉም ቢሆን መመሳሰላችንና መፈቃቀራችን ብዙ የተጻፈለት፣ ብዙ የተነገረለት ነው፡፡ ዛሬም ድረስ ያንን ሳቂታ የቤኒ አምር ወጣት የኛ ልጅ በመሆኑ ነው የምናውቀው፡፡ ዛሬም ድረስ ከኤርትራዊ ጎረቤቶቻችን ጋር ፋሲካና አረፋን በአንድነት እንታደማለን፡፡
*****
  እኛ ኤርትራን የምንፈልጋት ለወደቦቿ ስንል አይደለም፡፡ እኛ ኤርትራን የምንፈልገው ሁለመናዋ ከኛ ጋር ስለሚመሳሰልና አንድ ዓይነት ስለሆንን ነው፡፡ እኛ ኤርትራን የምንፈልገው ከነህዝቧ ነው፡፡ የኤርትራ ህዝብ የኛ ህዝብ ነው፡፡ እኛ ራሳችን የኤርትራ ህዝብ ነን፡፡ ኤርትራም ኢትዮጵያ ናት፤ ኢትዮጵያም ኤርትራ ናት፡፡ ኤርትራ ወደብ ባይኖራት እንኳ ይህ አቋማችን አይቀየርም፡፡ ታሪኳ፣ ባህሏ እና ቋንቋዋ እናንተ ከምታውቁት ተቀይሯል እስካልተባለ ድረስ ስለርሷ ማለማችንን አንተውም፡፡
 
  ህልማችን ጽኑ ነው፡፡ ወደፊት የትግበራ ምዕራፎቹን እያሰፋ የሚሄድ ነው እንጂ በእንጭጩ ተቀጭቶ የሚቀር አይደለም፡፡ ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማሪያም በአፋቤት ሽንፈት ሲያጋጥማቸው በተስፋ መቁረጥ ስሜት “ቤንዚን አይቆፈርበት፤ አልማዝ አይወጣበት፣ ሰው የለበት! Nothing`” እንዳሉት እኛም ተስፋ ቆርጠን ኤርትራንና ህዝቧን የምናጥላላበት ሁኔታ በፍጹም አይከሰትም፡፡ ቢኢዝኒላህ!! ኢንሻ አላህ!!

   እኛ ስለትልቋ ኤርትራ ማለምን ትተን “አሰብ የኢትዮጵያ ወደብ ናት” ከሚሉት የወደብ ጥማተኞች ጎንም አንሰለፍም፡፡ ፍላጎታችን “የኢኮኖሚ እድገት” በሚባለው የማቴሪያሊስቶች ዝባዝንኬ የሚመራ ባለመሆኑ ለጥቅም ብለን ህልማችንን በመንደር ደረጃ አናሳንሰውም፡፡ ቢኢዝኒላህ!!
   
    የእነዚህን የወደብ ጥማተኞች ቅስም ለመስበር በሚል የፖለቲካ ስሌት ተነሳስተን “የአሰብ ወደብ እጣ ፈንታ የግመሎች ውሃ መጠጫ ኩሬ ከመሆን አያልፍም” የሚል ታሪካዊ ተወቃሽነትን የሚያስከትል ቃልም አይወጣንም፡፡ ቢኢዝኒላህ!!
 
  እኛ ኤርትራዊያንን እንደኛው አድርገን ነው የምናያቸው እንጂ አንዳንድ ብስጩዎች በሚተነፍሷው ወሬዎች ተናደን “የቅኝ-ተገዥነት ስሜት ሰለባዎች ናችሁ” በማለት አንፈርጃቸውም፡፡ በምንም መልኩ ቢሆን ኤርትራዊ ወገናችንን የሚያሳቅቅና የሚያበሳጭ ክፉ ንግግር አንናገርም፤ ክፋታችንንና የውስጥ ጥላቻችንን የሚያሳብቅ ጽሑፍም አንጽፍም፡፡ በውስጣችን ስለኤርትራ መውደም እያሰብን በምላሳችን ብቻ “አንድ ህዝቦች ነን” እያልን የምንሰብክ መናፍቃንም አይደለንም፡፡ እኛ ኤርትራንና ህዝቧን የምንወደው ከልባችን ነው፡፡ ስለነርሱ የምናልመው ህልማችንም ከልባችን ከተወረወረ የፍቅር ፍላጻ የፈነጠቀ ነው፡፡
*****
ህልማችን የቅርብ ሳይሆን የሩቅ ነው! እጅግ በጣም ሩቅ!! ይሁንና ርቀቱን ፈርተን ማለማችንን አንተውም፡፡ ዘወትር ስለውቢቷ ኤርትራና ህዝቧ ማለማችንን እንቀጥላለን!! ከሩቁና መልከ-መልካሙ ህልማችን ጋር ወደፊት!!
----
አፈንዲ ሙተቂ
ጳጉሜ 4/2006
----
Afendi Muteki, is a researcher and author of the ethnography and history of the peoples of East Ethiopia. You may follow him on his facebook page. Just click this link


Thursday, December 11, 2014

የኢሠፓ ምስረታ በዓል እና ሀገር አቀፉ ረሃብ (መስከረም 2/ 1977)



ጸሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ
-----


ዕለቱ መስከረም 2/1977 ነበር፡፡ በዚያች ዕለት ደርግ ከአጼ ኃይለሥላሤ መንግሥት ስልጣን የተረከበበት 10ኛው የአብዮት በዓል ይከበር ነበር፡፡ ያ በዓል ከቀደሙት በዓላት ለየት የሚልበት አንድ ነገር ታይቶበታል፡፡ ይህም የስመገናናው የኢትዮጵያ ሠራተኞች ፓርቲ (ኢሠፓ) ምስረታ በይፋ መታወጅ ነው፡፡ ይህንን ድርብ ደስታ ለማድመቅ ተብሎ የተዘጋጀው ክብረ በዓል በሀገራችን ታሪክ በድጋሚ አልታየም፡፡ ለዚህ በዓል ማክበሪያ በትንሹ አንድ መቶ ሚሊዮን ብር ወጪ ሆኗል (ያ ገንዘብ በአሁኑ ስሌት ሁለት ቢሊዮን ብር ሊሆን ይችላል)፡፡


በዚያን ጊዜ ነው በአስራ ዘጠኝ ሚሊዮን ብር የተሰራው ታላቁ የኢሠፓ የጉባኤ አዳራሽ ተመርቆ የተከፈተው፡፡ ከጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ፊት ለፊት ያለው የ“ትግላችን” ሀውልትም በዚህ በዓል ወቅት ነው የተመረቀው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ለበዓሉ የታጨችው አዲስ አበባ በደማቅ መብራቶችና በልዩ ልዩ መፈክሮች ተጥለቅልቃ ነበር፡፡ እንግዶች በሚንቀሳቀሱባቸው ዋና ዋና ጎዳናዎች ላይ ያሉ አሮጌ ቤቶች በግንብ አጥርና በትላልቅ የጨርቅ ሽፋኖች እንዲከለሉ ተደርገዋል፡፡ የክፍለ ሀገር ዋና ከተሞችና የአውራጃ ከተሞችም በመፈክሮችና በማጭድና መዶሻ ምስሎች አሸብርቀዋል፡፡ በዋና ዋና መንገዶች ላይ ያሉ የንግድ ድርጅቶችና የመንግሥት መስሪያ ቤቶች በሶስት ቀለማት (አረንጓዴ፤ ቢጫ፤ ቀይ) የተዘጋጁ አምፖሎችን እንዲያበሩ ታዘዋል፡፡ በየቀበሌው የተቋቋሙ የኪነት ቡድኖችም ኢሠፓን የሚያወድሱ መዝሙሮችን አፍልቀዋል፡፡ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የነጭና ጥቁር ስርጭቱን ትቶ ወደ ሙሉ የቀለም ስርጭት የተሸጋገረው በዚያች ታሪካዊ ዕለት ነው፡፡


በዚያ ታላቅ ክብረ በዓል ላይ የምስራቅ ጀርመን ኮሚኒስት ፓርቲ ዋና ፀሐፊና የሀገሪቱ መሪ የነበሩትን ጓድ ኤሪኽ ሆኔከርንና የየመን ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ (ደቡብ የመን) መሪ ጓድ ዓሊ ናስር አል-ሐሰንን ጨምሮ በርካታ የሶሻሊስት ሀገራት ልዑካን ተገኝተዋል፡፡ ከአፍሪቃም የዛምቢያው ኬኔት ካውንዳ፤ የዚምባብዌው ሮበርት ሙጋቤና የሞዛምቢኩ ጓድ ሳሞራ ማሼል የበዓሉ ታዳሚ ነበሩ፡፡ ዋናው የበዓሉ አከባበር ስነ-ስርዓት በኢሠፓ ጉባኤ አዳራሽና በአብዮት አደባባይ የተካሄደ ሲሆን በተለይም በአብዮት አደባባይ የተካሄደው ልዩ ትርዒትና ወታደራዊ ሰልፍ በሀገሪቱ ታሪክ ተወዳዳሪ አልተገኘለትም፡፡
*****
“ኢሠፓ” የሚባለው ዝነኛ ፓርቲ የተመሰረተው ለአምስት ዓመታት የዘለቀ መጠነ ሰፊ ዝግጅት ከተደረገ በኋላ ነው፡፡ ለፓርቲው ምስረታ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን እንዲያቀላጥፍና ህዝቡን በሶሻሊስታዊ ስርዓት እንዲያደራጅ በሚል “የኢትዮጵያ ሰርቶ አደሮች ፓርቲ አደራጅ ኮሚሽን” (ኢሠፓአኮ) የተባለ ከፍተኛ የአስፈጻሚ አካል በመስከረም 1972 ተመስርቶ ነበር፡፡ ይህንን ኮሚሽን ማቋቋሙ ያስፈለገው “የሰርቶ አደሩን ፓርቲ ለመመስረት የሚቻለው ህዝቡን በማንቃትና በማደራጀት በአንድ ማዕከል ዙሪያ ካሰባሰቡ በኋላ ነው ” በሚለው የኮሚኒስቶች ርዕዮተ-ዓለማዊ መርህ መሰረት ነው፡፡ የዚህ ኮሚሽን ተጠሪ በመሆን በየክፍለ ሀገሩ የተመደቡ ወኪሎች የየአካባቢው የበላይ ውሳኔ ሰጪዎች ነበሩ፡፡ የኮሚሽኑን ዓላማ የሚገልጸው “የኢሠፓአኮ ተልዕኮ ይሳካል” የተሰኘ መፈክር በመላው ኢትዮጵያ ተደጋግሞ ይሰማ ነበር፡፡

  ኢሠፓ የተመሰረተው ለአምስት ቀናት በተካሄደ መስራች ጉባዔ ነው፡፡ በጉባኤው ማጠቃለያ ላይ በድርጅታዊ አሰራር የተዘጋጀ ምርጫ ተደረገ፡፡ ጓድ መንግሥቱ ኃይለማሪያም የፓርቲው ዋና ጸሐፊ ሆነው መመረጣቸውም ተነገረ፡፡ ከርሳቸው ጋርም መቶ ሰማኒያ ሶስት የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ተመረጡ፡፡
*****
የኢሠፓ አወቃቀርና አሠራር በሌሎች የሶሻሊስት ሀገራት ከታዩት ኮሚኒስት ፓርቲዎች ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ ፓርቲው የመንግሥት አስፈጻሚ አካላት የበላይ ነው፡፡ የፓርቲውና የአስፈጻሚ አካላቱ ግንኙነት የጎንዮሽ ሳይሆን ከላይ ወደታች የተዘረጋ መዋቅራዊ መልክ ነበረው፡፡ በመሆኑም ኢሠፓ በየትኛውም እርከን ላይ ላሉት አስፈጻሚ አካላት የበላይና አመራር ሰጪ ነው፡፡ ይህ አወቃቀር በሀገር አቀፍ፣ በክፍለ ሀገርና በአውራጃ ደረጃ የተዘረጋ ነው፡፡ በሀገር አቀፍ ደረጃ የነበሩት የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች አመራር የሚቀበሉት ከኢሠፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽ/ቤት ነው፡፡ በክፍለ ሀገርና በአውራጃ ደረጃ ያሉ መስሪያ ቤቶችም ከኢሠፓ ጽ/ቤት ነው አመራር የሚሰጣቸው፡፡ በመሆኑም የአውራጃና የክፍለ ሀገር የኢሠፓ ኮሚቴ አንደኛ ፀሐፊ ሆኖ የተመደበ ሰው በፕሮቶኮልም ሆነ በስልጣኑ ከሌሎች ተሿሚዎች ሁሉ ይበልጣል፡፡

 የኢሠፓ መዋቅር በኢ-መደበኛ ሁኔታ ሁሉንም የመንግሥት መስሪያ ቤቶች አዳርሷል፡፡ በያንዳንዱ የመንግሥት መስሪያ ቤት፣  በማምረቻና ማከፋፈያ ድርጅቶችና በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ “የኢሠፓ መሰረታዊ ድርጅት ጽ/ቤት” የሚባል መምሪያ ነበረ፡፡ የዚህ መሰረታዊ ድርጅት ዓላማ የኢሠፓን ርዕዮተ ዓለም ማስተማርና ከበላይ አካል የመጡ መመሪያዎች ተፈጻሚ መሆናቸውን መቆጣጠር ነው፡፡ ለፓርቲ አባልነት ብቁ የሆኑ ጓዶችን መልምሎ የአባልነት መታወቂያ የሚሰጠውም እርሱ ነው፡፡

ኢሠፓ በፕሮፓጋንዳው ዘርፍ ከፍተኛ እንቅስቃሴ ያደርግ ነበር፡፡ የፓርቲው ልሳን “ሠርቶ አደር” የሚባለው ሳምንታዊ ጋዜጣ ነው፡፡  መስከረም ደግሞ የፓርቲው የርዕዮተ ዓለም መጽሔት ነው፡፡ የፓርቲው አባላት በሁለቱ ህትመቶች በወጡ ጽሑፎች ላይ የመወያየት ግዴታ አለባቸው፡፡

 ኢሠፓ የደርግ መንግሥት ከስልጣን እስከተወገደበት ጊዜ ድረስ ቆይቷል፡፡ በስልጣን ላይ በነበረባቸው ሰባት ዓመታት በጠቅላላው ከ100, 000 ያላነሱ አባላትን አፍርቷል፡፡ አባላቱ ከሲቪልም ሆነ ከጦር ሀይሉ ክፍል የተመለመሉ ናቸው፡፡ እያንዳንዱ የፓርቲ አባል በስራ ቀናት ከካኪ የተሰፋ ሱሪና ኮት የመልበስ ግዴታ አለበት (ይህ መመሪያ የወጣው “የሀገር ውስጥ ምርቶችን ማበረታታት አለብን” በሚል መነሻ ነው፤ ካኪው በቃሊቲ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ ነው የሚመረተው)፡፡ 

ከላይ እንደገለጽኩት የኢሠፓ ዋና ፀሐፊ ጓድ መንግሥቱ ኃይለ ማሪያም ነበሩ፡፡ ፓርቲው ምክትል ዋና ፀሐፊ በይፋ ባይሰይምም የጓድ መንግሥቱ ተከታይ ሆነው ሲሰሩ የነበሩት ጓድ ፍቅረ ሥላሤ ወግደረስ ናቸው፡፡ የርዕዮተ-ዓለም መምሪያ ሃላፊው ጓድ ሽመልስ ማዘንጊያ ሲሆኑ ጓድ ብርሃኑ ባይህ የውጭ ግንኙነት መምሪያ ሃላፊ ነበሩ፡፡ ጓድ ሸዋንዳኝ በለጠ የኢኮኖሚ ልማት መምሪያ ሃላፊ፤ ጓድ ተካ ቱሉ የኦዲትና ቁጥጥር ኮሚሽን ሃላፊ፣ ጓድ ደበላ ዲንሳ የማህበራዊ ጉዳዮች መምሪያ ሃላፊ፣ ጓድ ሜጀር ጄኔራል ገብረየስ ወልደሃና የወታደራዊ ጉዳዮች መምሪያ ሃላፊ ነበሩ፡፡ ከሁሉም በላይ ስልጣናቸው ገንኖ የነበረው  ግን የድርጅት መምሪያ ሃላፊው ጓድ ለገሠ አስፋው ናቸው፡፡
  *****
ኢሠፓ የምስረታ ጉባኤውን በሚያካሄድበት ወቅት (ጳጉሜ1-ጳጉሜ 5/1976) ሀገሪቱ በከፍተኛ ድርቅ ተጠቅታ ነበር፡፡ ከአምስት ሚሊዮን የማያንሱ ዜጎች በትግራይ፣ በወሎ፣ በጎንደር፣ በኤርትራ፣ በሀረርጌና በባሌ ክፍላተ ሀገር በቸነፈር ተጠብሰው በሞት አፋፍ ላይ ነበሩ፡፡ አንዳንድ የሀገር ተቆርቋሪዎች መንግሥት የፓርቲ ምስረታ ጉባኤውን ለሌላ ጊዜ እንዲያስተላልፍና የ10ኛ አብዮት በዓልን እንዲያስቀር ቢወተውቱም ሰሚ አላገኙም፡፡ የወቅቱ መንግሥት የድርቁ መኖር ከታወቀ በአብዮት በዓል አከባበሩ ላይ ጥላውን ያጠላል በማለት የምዕራብ ሀገራት የዜና አውታሮች ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገቡ ከልክሎአቸው ነበር፡፡ ይሁንና አንዳንድ ሚዲያዎች የዜና ዘጋቢዎቻቸውንና የቪዲዮ ሪፖርተሮቻቸውን በድብቅ ወደ ሀገር ውስጥ በማስረግ የዓለም ህዝብ አስከፊውን ድርቅ እንዲያየው አድርገዋል፡፡ በነዚያ ሪፖርተሮች የተቀረጹ ምስሎችን የተመለከቱ የዓለም ህዝቦች ለድርቅ የተጋለጠውን ኢትዮጵያዊ ረሀብተኛ ለመታደግ በተንቀሳቅሰዋል (በሰር ቦብ ጊልዶፍ አስተባባሪነት የተሰባሰቡ የዓለማችን እውቅ አርቲስቶች Live Aid የተባለውን የሙዚቃ ዝግጅት ያቀረቡት ያኔ ነው፡፡ አርቲስቶቹ በዝግጅቱ ላይ በጋራ ያዜሙት We are the world የተሰኘው ዜማ ከምንጊዜም ምርጥ ዜማዎች መካከል አንዱ ሆኖ ተመዝግቧል)፡፡

   የደርግ መንግሥት በህጋዊ መንገድ ፈቅዶላቸው የመጡ ጥቂት የሶሻሊስት ሀገራት ዘጋቢዎች ደግሞ “ድርቅ በመቶ ሺህ የሚቆጠር ህዝብ እየቀጠፈ ለዚህ በዓል ከፍተኛ በጀት መመደብ አግባብ ነውን?” የሚል ጥያቄ በይፋ በማቅረብ የሀገሪቱን ከፍተኛ ባለስልጣናት አጨናንቀዋል፡፡ በመሆኑም የአብዮት በዓሉ ሲፈጸም መንግሥት በድርቅ የተጎዳውን ህዝብ ለመታደግ መንቀሳቀሱ ግድ ሆኖበታል፡፡ ሆኖም የመንግሥት እርምጃ በጣም የዘገየ በመሆኑ አምስት መቶ ሺህ የሚሆኑ ኢትዮጵያዊያን በዚያ አስከፊ ድርቅ አልቀዋል፡፡
-----
አፈንዲ ሙተቂ
መስከረም 2/2007

Wednesday, December 10, 2014

ጥቂት ቆይታ- ከአል-በላቢል ጋር




ፀሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ
-----
ብዙዎቻችን በስርቅርቅ ድምጻቸው እናውቃቸዋለን፡፡ እጅግ በተዋጣለት የኦርኬስትራ ቅንብር በመታጀብ የተጫወቷቸው ጥዑም ዜማዎች  በአዕምሮአችን ላይ ተቀርጸዋል፡፡ እኔ ጸሐፊው ሙዚቃቸውን ለመጀመሪያ ጊዜ የሰማሁበትን አጋጣሚ አላስታውስም፡፡ ሆኖም የነርሱን ዘፈን በምሰማበት ጊዜ ሁሉ ሶስት ነገሮች ይታወሱኛል፡፡


   የመጀመሪያው ከተማችንን (ገለምሶን) ለሁለት ከፍሎ የሚያልፈውን አውራ ጎዳና ተከትለው ከተደረደሩት ሻይ ቤቶች ይንቆርቆር የነበረው የእንስቶቹ ዝማሬ ነው፡፡ በተለይም የሻይ ቤቶቹ ባለቤቶች በበርካታ የህብረተሰብ ክፍል እንደ ህብረ-ዜማ ይዘፈን የነበረውን “መሼና መሼና”ን እየደጋገሙ ማጫወታቸው የየዕለቱ ትዕይንት ሆኖ እንደቆየ አስታውሳለሁ፡፡ ሁለተኛው አይረሴ አጋጣሚ የተከሰተው በትምህርት ቤት ቆይታዬ ነው፡፡ በ1980 የአምስተኛ ክፍል ተማሪ እያለሁ ከለገዳዲ ሬድዮ ጣቢያ የሚተላለፈውን “የህብረተሰብ ትምህርት በሬድዮ” ለማዳመጥ በሄድንበት አንድ ጠዋት “ተማሪዎች፤ የኢትዮጵያ ጎረቤት የሆነችውን ሱዳንን ታውቋታላችሁ?” በሚል ርዕስ የተዘጋጀ ትምህርት ተሰጠን፡፡ የሬድዮ ትምህርቱን የሚያቀርበው ባለሙያ “ሱዳን፣ በአፍሪቃ ትልቅ ሀገር ናት፤ ስፋቷ ወደ አንድ ሚሊዮን ስኩዌር ማይልስ ይጠጋል፤ ዋና ከተማዋ ካርቱም ነው” እያለ በሚያስተምርበት ጊዜ በየአፍታው እንደመሸጋገሪያ አድርጎ የተጠቀመው እንስቶቹ “ለውነል መንጋ” እያሉ የሚያዜሙትን ተወዳጅ ዘፈን ነበር፡፡ ያንን ዘፈን ለመጀመሪያ ጊዜ የሰማሁት በዚያች ዕለት ነው፤ ከዚያ በኋላ ከጭንቅላቴ ላወጣው አልቻልኩም፡፡

  ሶስተኛው አጋጣሚ በ1984 በአንዲት የማክሰኞ ምሽት ነው የተከሰተው፡፡ በዕለተ ማክሰኞ ሲገበያይ የሚውለው የከተማችን ህዝብ የቀኑን ድካም ለማራገፍ ሲል ምሽት ላይ እራቱን ከበላ በኋላ ሆጃና ሻይ አፍልቶ ለበርጫ መሰየሙ የተለመደ ነገር ነው፡፡ እኔም በዚያች የማክሰኞ ምሽት አብዱልቃዲር ከተባለ ዘመዳችን ሱቅ ሄድኩና ከጥቂት ጓደኞቹ ጋር በርጫውን ሲያስኬድ አኘሁት፡፡ አብዱልቃዲር ለበርጫው ማሟሟቂያ የመረጠው የእንስቶቹን ተወዳጅ ካሴት ነው፡፡ በተለይም ደግሞ “ኡሸ ሰጊራ፣ ኪፋያ ዐለይና” የተሰኘውን ዘፈን ይደጋግመው ነበር፡፡ እኔም የአብዱልቃዲር ሁናቴ አስገርሞኝ ስለእንስቶቹ እንዲያጫውተኝ ጠየቅኩት፡፡ እርሱም የዘፋኞቹን ማንነትና የሙዚቃ ጉዞአቸውን እያዳነቀ ተረከልኝ፡፡ እንግዲህ በዚያች አጋጣሚ ነው ስማቸውን ለመያዝ የበቃሁት፡፡
*****
አዎን! የኢትዮጵያን ሙዚቃ አውቃለሁ የሚል ሰው ሶስቱን የሱዳን ድምጻዊያን በደንብ ነው የሚያውቃቸው፡፡ እነዚህ እንስቶች እህትማማቾች ናቸው፡፡ ትክክለኛ ስማቸውም “ሐያት”፣ “አመል” እና “ሃዲያ” ነው፡፡ በዓለም ዙሪያ በደንብ የሚታወቁት ግን “አል-በላቢል” በተሰኘው የቡድን ስማቸው ነው (በዐረብኛ “አል-ባቢል” ሲባል “ዘማሪ ወፎች” እንደማለት ነው)፡፡ በምስራቅ አፍሪቃ የሙዚቃ ታሪክ የነርሱን ያህል የሚታወቅ የሴት ድምጻዊያን ቡድን የለም፡፡

“አል-በላቢል” በሰሜን ሱዳን በዋዲ-ሃልፋ ከተማ ነው የተወለዱት ነው፡፡ የአፍ-መፍቻ ቋንቋቸው “ኑቢያ” ነው፡፡ ሙዚቃን በዋዲ ሃልፋ ቢጀምሩትም ከእውቅና ማማ ላይ የወጡት ግን በካርቱም ከተማ ነው፡፡ በተለይም እንስቶቹ እ.ኤ.አ ከ1974-እስከ 1982 በነበረው ዘመን በሱዳን ሙዚቃ ላይ ነግሰው ነበር፡፡ በዚያ ዘመን ያወጧቸው “መሼና”፣ “ሙትዓሉ ዐለይና”፣ “ሸባብ አንኒል”፣ “ዑሸ ሰጊራ”፤ “ለውነል መንጋ”፣ “ሒልዊን ሐለዋ”፣ “ጣኢረል ጀንና” የመሳሰሉት ዘፈኖቻቸው ዘመን ተሻግረው እስከ ዛሬም ድረስ ይደመጣሉ፡፡

  የአል-በላቢል አዕዋፋት ዝና በምድረ-ሱዳን ብቻ አልታቀበም፡፡ ከካይሮ እስከ ሞምባሳ፣ ከበርበራ እስከ ባማኮ (ማሊ) ባሉት የአፍሪቃ ከተሞች የሚኖሩ የሙዚቃ አፍቃሪዎች በስራቸው ተማርከውላቸዋል፡፡ በኢትዮጵያ፣ በግብጽ፣ በሶማሊያ፣ በጅቡቲ፣ በቻድ፣ በኬንያ፣ በናይጄሪያ፣ በአልጄሪያ፣ በማሊና በሌሎችም የአፍሪቃ ሀገራት ሙዚቃዎቻቸውን አቅርበዋል፡፡ በመካከለኛው ምስራቅ፣ በአውሮጳና በአሜሪካም ተዟዙረዋል፡፡
*****
ሆኖም ሶስቱ እንስት ከ1986 በኋላ የሙዚቃ ስራቸውን በአንድ ላይ ለመቀጠል አልቻሉም፡፡ ትልቋ “ሐያት” እና ሁለተኛዋ ሃዲያ በጋብቻ ምክንያት ሱዳንን በመልቀቃቸው ብዙዎች ያደነቁላቸው የቡድን ስራቸው በመንገድ ላይ ቀረ (ሐያት በአሜሪካ፣ ሐዲያ ደግሞ በባህሬን ይኖሩ ነበር)፡፡ ሆኖም የሱዳን ህዝብ እንዲሁ አልተዋቸውም፡፡ እንስቶቹ በአንድ ላይ ተሰባስበው ስራቸውን እንዲሰሩ በልዩ ልዩ መንገድ ጫና ሲያደርግባቸው ነበር፡፡ እነርሱም ለህዝቡ ውዴታ በመሸነፋቸው በድጋሚ በመሰባሰብ የሙዚቃ ስራቸውን ማቅረብ ጀምረዋል፡፡

    ታዲያ አል-በላቢል በድጋሚ የቡድን ስራቸውን በጀመሩበት የአውሮጳዊያኑ 1998 አጋማሽ ላይ የለቀቁት “ኩልለ-ኑጁም” የተሰኘው አልበም በዓለም ዙሪያ በእልፍ አዕላፍ ቅጂዎች ነው የተሸጠው፡፡ የሱዳን የሙዚቃ ኤክስፐርቶች በዚያ አልበም የተካተቱትን ስራዎች ከሀገሪቱ የምንጊዜም ተወዳጅ ዜማዎች መካከል ደምረዋል፡፡ በተለይም የአልበሙ መጠሪያ የሆነው “ኩልላ-ኑጁም” የተባለው ዜማ ከሱዳን አልፎ በውጪው ዓለም (በጀርመን) ለሽልማት አብቅቶአቸዋል፡፡ የአውሮጳ ህብረት በበኩሉ ታህሳስ 11/ 2013 ባዘጋጀው ልዩ ዝግጅት እህትማማቾቹ ለሱዳን ሙዚቃ እድገት ላደረጉት አስተዋጽኦ ዓለም አቀፍ ሽልማት ሸልሞአቸዋል፡፡ እንስቶቹ የምታዩትን ፎቶግራፍ የተነሱት ሽልማቱን በተቀበሉበት ወቅት ነው፡፡
*****
አል-በላቢልን በሌላ ቀን እንዘይራቸዋለን፡፡ ለዛሬ ግን በኛ ሀገር በስፋት የሚታወቀውን “መሼና”ን እንገባበዝና እናብቃ፡፡
 መሼና መሼና መሼና
ቢጠሪቀል ሑብቢ መሼና
አዕዛቡ ያ ናር አልጊና
መሼና መሼና መሼና…
(እህትማማቾቹ መሼናን ሲዘፍኑ ለማየት የሚከተለውን ሊንክ ይክፈቱ)፡፡
-----
አፈንዲ ሙተቂ
ጥቅምት 4/2007
ገለምሶ-ምስራቅ ኢትዮጵያ
----
The writer, Afendi Muteki, is a researcher and author of the ethnography and history of the peoples of East Ethiopia.  You may like his facebook page and stay in touch with his articles and analysis: Just click the following link to go to his page.