Monday, May 12, 2014

የሀያኛውን ክፍለ ዘመን የኢትዮጵያ ፖለቲካ የቀየሩ አነስተኛ ሰነዶች- (በብዙዎች ጥያቄ የተደገመ)





አፈንዲ ሙተቂ

---
ይህንን አነስተኛ መጣጥፍ ከዚህ በፊት (በታህሳስ ወር 2006) ለጥፌው ነበር፡፡ ነገር ግን በርካታ ወዳጆቼ “ከፌስቡክ ግድግዳህ ላይ ልናገኘው አልቻልንም” ስላሉኝ እንደገና መድገሙ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ 

እነዚህ ሰነዶች በ20ኛው ክፍለ ዘመን የኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ አሳርፈዋል በማለት በዝርዝሩ ውስጥ የያዝኳቸው እኔ ነኝ፡፡ ዝርዝሩ በሌሎች ምሁራንም ሆነ የጥናት ተቋማት እውቅና አልተሰጠውም፡፡ ማንም ሰው የክፍለ ዘመኑን የኢትዮጵያ የፖለቲካ አካሄድ ገምግሞ ከፍተኛ ተጽእኖ አሳድረዋል ያላቸውን ሰነዶች ሊጠቁም ይችላል፡፡ እኔም ይህንኑ ነው ያደረግኩት፡፡
---
ሰነዶቹ የሚከተሉት ናቸው፡፡

1. አዕምሮ ጋዜጣ- 1904
2. የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ህገ-መንግሥት- 1923
3. የኤርትራ ፌዴሬሽን ህገ-መንግሥት 1944
4. የተሻሻለው የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ህገ-መንግሥት- 1948
5. የጀብሃ ቻርተር- 1954
6. የሜጫና ቱለማ ማህበር መተዳደሪያ ደንብ-1955
7. የብሄር ጥያቄ በኢትዮጵያ (በዋለልኝ መኮንን የተጻፈ ጽሑፍ)-1961
8. “ንህናን ዓላማናን”(እኛና ዓላማችን)- ሻዕቢያ ከጀብሃ የተገነጠለበት አነስተኛ ጥራዝ-1964
9. ደርግ ስልጣን የያዘበት አዋጅ- መስከረም 2/1967
10. የገጠር መሬትን ለህዝብ ያደረገው አዋጅ- የካቲት 25/1967
11. ዲሞክራሲያ ጋዜጣ (የኢህአፓ መመስረት ይፋ የሆነበት የፓርቲው ህቡዕ ጋዜጣ)- ነሐሴ 27/1967
12. የተሓሕት/ህወሐት ማኒፌስቶ- የካቲት 1968
13. የብሄራዊ ዲሞክራሲያዊ አብዮት ፕሮግራም አዋጅ- ታህሳስ 1968
14. የህዝብ ድርጅት ጉዳይ /ቤት የተመሰረተበት አዋጅ- ሚያዚያ 1968
15. የኦነግ የፖለቲካ ፕሮግራም- ሰኔ 1968
16. ኢሰፓአኮ የተቋቋመበት አዋጅ-ሰኔ 1971
17. ኢሰፓ የተመሰረተበት አዋጅ- መስከረም 1977
18. የኢህዲሪ ህገ-መንግሥት-ጳጉሜ 1979
19. የኢትዮጵያ የሽግግር መንግሥት ቻርተር- ሀምሌ 1983
20. የፕሬስ አዋጅ- የካቲት 1984
21. የክልሎች ማቋቋሚያ አዋጅ- ጥቅምት 1985
22. ኢትዮጵያ ለኤርትራ ነጻነት እውቅና የሰጠችበት ደብዳቤ (በአቶ መለስ ዜናዊ የተጻፈ)-ሚያዚያ 1985
23. የኢፌዴሪ ህገ-መንግሥት- ህዳር 29/1987
24. የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ያበቃበት የአልጀርስ ስምምነት -ታህሣስ 1993
25. አብዮታዊ ዲሞክራሲና ቦናፓርቲስታዊ የመበስበስ አደጋዎች (በአቶ መለስ ዜናዊ የተጻፈ ጥራዝ)- ጥር 1993
26. የቅንጅት ማኒፌስቶ-1997

ከላይ የተዘረዘሩት ሰነዶች በኔ እይታ 100 ዓመት (1900-2000 በነበረው) የኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ አድርሰዋል፡፡ እያንዳንዱን ሰነድ ልብ ብላችሁ ካያችሁት የፖለቲካ ሚናው ከፍተኛ እንደነበረ በቀላሉ መረዳት ትችላላችሁ፡፡ ለምሳሌ አቶ መለስቦናፓርቲዝምበሚል ርዕስ የጻፉት ጽሑፍ 1993-95 የነበረውን የኢትዮጵያ ፖለቲካ በከፍተኛ ጡዘት ውስጥ የጨመረ ነው፡፡ እነ ስዬ አብርሃን ከማባረር ጀምሮ የክልሎችን አስተዳደራዊ መዋቅር እስከመቀየር እና የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርም ለመሳሰሉት ፐሮግራሞች ትግበራ ጥርጊያ ጎዳና ያመቻቸ ነው (የጸረ-ሙስና ኮሚሽንም የርሱ ውልድ ነው)፡፡ የህዝብ ድርጅት /ቤት ማቋቋሚያ አዋጅምቀበሌየሚለውን የአስተዳደር አከፋፈል ከማስተዋወቅ ጀምሮ በቀይ ሽብር ውስጥ ከፍተኛ ሚና የነበራቸውን የጥበቃ ጓዶች እስከ ማስታጠቅ ድረስ ላሉት ታላላቅ ክስተቶች መፈጠር እንደ እርሾ ሆኖ አገልግሏል፡፡

በናንተ በኩል በዚህ ዝርዝር ውስጥ መካተት አለባቸው የምትሏቸው ሰነዶች የትኞቹ ናቸው? በናንተ ሚዛን ፖለቲካዊ ሚናቸው ሀይለኛ የሆኑትን መጠቆምና በኔ ያቀረብኩትን ዝርዝር መተቸት ትችላላችሁ (የኤርትራ ሰነዶች በዚህ ዝርዝር ውስጥ የተካተቱት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ ተጽእኖ ስለነበራቸው ነው)፡፡
ሰላም
-----------------------
አፈንዲ ሙተቂ
ግንቦት 4/2006

Sunday, May 11, 2014

የኢድሪስ ሻህ በረከቶች




አፈንዲ ሙተቂ
-----------

“ሀረር ጌይ” የተሰኘው መጽሐፌ ለመታሰቢያነት ከተሰጣቸው ስብዕናዎች አንዱ ኢድሪስ ሻህ መሆኑን ከዚህ ቀደም አውግቼአችኋለሁ፡፡ ኢድሪስ ሻህ በኔ ህይወት ውስጥ ያለውንም ቦታ በመጽሐፉ ውስጥ ገልጫለሁ፡፡ በአማርኛ “ተረበኛው ነስሩዲን” ተብሎ የተተረጎመው መጽሐፍ ደራሲም እርሱ እንደሆነም ተናግሬአለሁ፡፡ በዚህም ግድግዳ ላይ የኢድሪስን የህይወት ታሪክ በአጭሩ ጽፌላችሁ ነበር፡፡ ስለዚህ በዛሬው ፅሁፍ በነዚህ ጉዳዮች ላይ ምንም የምላችሁ ነገር የለም፡፡ ከዚያ ይልቅ ከኢድሪስ መጻሕፍት ያገኘኋቸውን ምርጥ ጨዋታዎች አጋራችኋለሁ (የመጀመሪያዎቹን ሁለት ወጎች ከዚህ በፊት ጽፌአቸው የነበረ ቢሆንም ላላነበቡት ብደግማቸው ጥሩ ይመስለኛል)፡፡

== ሶስቱ ልጆችና ዓሊ ኢብን አቡ-ጧሊብ ===

ሶስት ልጆች የነበሩት አንድ የዐረቢያ ሰው ነበር። ይህ ሰው በህይወቱ መጨረሻ አካባቢ ልጆቹን ጠርቶ እንዲህ አላቸው።

“ልጆቼ ሆይ! በዚህ ምድር ላይ ስኖር የተገነዘብኩት ትልቁ ነገር የዕውቀት አስፈላጊነት ነው። ያለ ዕውቀት የሚሄድ ሰው በጭለማ እንደሚጓዝ በቅሎ ይደናበራል። ንግግሩም ሆነ ስራው አያምርለትም። ስለዚህ አዋቂና ታዋቂ እንድትሆኑልኝ እሻለሁ። ነገር ግን መምህራችሁን በጥንቃቄ መምረጥ አለባችሁ። ለዚህም ይረዳችሁ ዘንድ እነኝህን 17 ግመሎች ትቼላችኋለሁ። ታዲያ ግመሎቹን የምትከፋፈሉት በሚከተለው ቀመር መሰረት ይሁን።
           የመጀመሪያው ልጄ የግመሎቹን 1/2ኛ ይውሰድ።
           ሁለተኛው ልጄ 1/3ኛ ያህሉን ይውሰድ።
           ሶስተኛው ልጄ 1/9ኛ ያህሉን ይውሰድ።

አባታቸው ይህንን ከተናዘዘ በኋላ አረፈ። ልጆቹም ግመሎቻቸውን እየነዱ በእርሱ የተነገራቸውን ዓይነት መምህር መፈለግ ጀመሩ። በየከተማው ወዳሉ አዋቂዎች እየቀረቡ አባታቸው በሰጣቸው ስሌት መሰረት ግመሎቻቸውን እንዲያካፍሉአቸው ጠየቁ። ነገር ግን አንድም ሰው ስሌቱን መፍታት አልቻለም። ሌሎች በርካታ አዋቂዎችንም አማከሩ። ግን ሒሳቡን አውቃለሁ የሚል ሰው ጠፋ።

በመጨረሻም አንደኛው ልጅ “ለምን ጥያቄውን ኸሊፋ ዓሊ ቢን አቡ ጣሊብ ዘንድ አናቀርበውም? ከቻሉ ለራሳቸው ይፈቱታል። ካልቻሉም አንድ መላ ይመቱልናል” የሚል ሀሳብ አቀረበ። የቀሩት ሁለቱ ልጆች በነገሩ ተስማሙ። በዚሁ መሰረት ሶስቱም ልጆች ወደ ኸሊፋ ዓሊ አቢ ጣሊብ (ረ.ዐ.) ዘንድ ሄዱና ጥያቄውን አቀረቡ። ኸሊፋው ትንሽ ካሰበ በኋላ እንዲህ የሚል ምላሽ ሰጣቸው።

“አስራ ሰባቱን ግመሎች በአባታችሁ ቀመር መሰረት ባከፋፍላችሁ ውጤቱ በክፍልፋይ (fraction) የሚገለጽ ይሆናል። እንደዚያ ከሆነ ግመሎቹን መቆራረጥ ሊኖርብኝ ነው ማለት ነው። ስለዚህ እንዲያ እንዳይሆን የራሴን አንድ ግመል ልጨምርበትና የግመሎቹ ብዛት 18 ይሁን። ይህ ከሆነ ዘንዳ የአባታችሁ ቀመር የሚቀጥለውን ውጤት ያስገኛል።
           ታላቁ ልጅ ከጠቅላላው 1/2ኛ ያግኝ በተባለው መሰረት ዘጠኝ ግመሎች ይደርሱታል።
           ሁለተኛው ልጅ 1/3ኛ ያግኝ በተባለው መሰረት ስድስት ግመሎች ይደርሱታል።
           ሶስተኛው ልጅ 1/9ኛ ያግኝ በተባለው መሰረት ሁለት ግመሎች ይደርሱታል።
           ሶስታችሁ ያገኛችኋቸውን ግመሎች በአንድ ላይ ስንደምር (9+6+2) ውጤቱ አስራ ሰባት ይሆናል።
           ከአስራ ስምንቱ አንድ ግመል ብቻ ይቀራል አይደል? እርሱ ደግሞ የራሴ በመሆኑ ወደኔ ይመለሳል።”
ብልሁ ዓሊ ቢን አቢ ጣሊብ ሒሳቡን በዚህ አስገራሚ መንገድ ፈታው። ልጆቹም “አባታችን የጠቆመን መምህር ይህ ነው” በማለት እስከ መጨረሻው ድረስ ተማሪዎቹ ሆነው ዘለቁ።

===መርከበኛውና መምህሩ===

   አንድ የሰዋስው መምህር ራቅ ወዳለ ስፍራ ለመሄድ ጀልባ ይከራያል። ለመርከበኛው ሒሳቡን ከከፈለ በኋላም መርከበኛው ጀልባይቱን አስነስቶ ጉዞ ይጀመራል። ጥቂት ጊዜ እንደ ተጓዙ መምህሩ ወሬ ለመጀመር ያህል “ሰዋስው ተምረሃል?” በማለት ይጠይቃል። መርከበኛውም “አይ አልተማርኩም” በማለት ይመልሳል። በዚህን ጊዜም መምህሩ “አይ ጉድ! ሰዋስው ሳትማር ምን ልትረባ ነው ታዲያ? ወንድሜ ግማሽ ህይወትህን አጥተሃል” ይላል። መርከበኛው ይህንን ሲሰማ በጣም ይበሽቃል። ቢሆንም ስሜቱን ተቆጣጥሮ ጀልባዋን መንዳቱን ይቀጥላል።

ሁለቱ ሰዎች ከባህሩ መሀል ሲደርሱ ከየት መጣህ የማይሉት ሀይለኛ ማዕበል ጀልባይቱን ከወዲያ ወዲህ ያላጋት ጀመር። መርከበኛው በሚችለው ሁሉ ጀልባዋን ከመስጠም ሊያድናት ሞከረ። ቢሆንም አልተሳካለትም። በዚህን ጊዜም ወደ መምህሩ ዞሮ “መምህር! ለመሆኑ ዋና ትችላለህ” በማለት ጠየቀው። መምህሩም እንደማይችል መለሰለት። ይሄኔ መርከበኛው “ አይ መምህር! ምንም ላደርግልህ አልችልም። ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ሙሉ ህይወትህን ልታጣ ነው” አለው። (የዚህ ወግ መልዕክት “ብድር በምድር ነውና ባለህ ነገር አትኩራራ” የሚል ነው)።

==የግመሉ ወግ==

ሶስት ባልንጀራሞች ወደ ሩቅ ሀገር ጉዞ ጀመሩ፡፡ የመንገዱን አጋማሽ ከሄዱ በኋላ የግመል ፋንዲያ ታያቸው፡፡ አንደኛው ሰውዬ “ይህንን ፋንዲያ የለቀቀው ግመል ጅራተ-ቆራጣ ነው” አለ፡፡ ሰዎቹ እንደገና ጉዞአቸውን ቀጠሉ፡፡ ጥቂት ከተጓዙ በኋላም ምሳ መብላት አሰኛቸውና ከአንድ ዛፍ ስር አረፉ፡፡ እዚያ ሳሉም የቡድኑ ሁለተኛ ሰው ወደላይ አንጋጦ ካየ በኋላ “ከዚህ ዛፍ የበላው ግመል አንድ ዐይና ነው” በማለት ተናገረ፡፡

 ሰዎቹ ምሳቸውን ካጠናቀቁ በኋላ እንደገና መጓዛቸውን ቀጠሉ፡፡ በመንገዳቸው ላይም ግመል የሄደበትን ፋና አዩ፡፡ በዚህን ጊዜም የቡድኑ ሶስተኛ ሰው “ይህንን ዳራ (ፋና) በአሸዋው ላይ ያሳረፈው ግመል ከባድ እቃ ተጭኖበታል” በማለት ተናገረ፡፡ ከጥቂት ቆይታ በኋላም “ግመሌ ጠፍቶብኛል” ከሚል ሰው ጋር ተገጣጠሙ፡፡
አንደኛው ሰውዬ: “ግመልህ ጅራተ-ቆራጣ ነው?”
ባለ ግመል፡ “አዎን”
ሁለተኛው ሰውዬ፡ “ግመልህ አንድ ዐይና ነው?”
ባለ ግመል፡ “አዎን”
ሶስተኛው ሰው፡ “ግመልህ ከባድ እቃ ተጭኖበታል?”
ባለ ግመል፡ “አዎን”
ሶስቱም በአንድነት፡ “ግመልህን አላየነውም፣ ሂድና ፈልገው ወንድም”
ባለ ግመል፡ “እንዴ ምልክቱን አንድ በአንድ እየነገራችሁኝ ሂድና ፈልገው ስትሉኝ አታፍሩም? ግመሌን ስርቃችሁታልና ቶሎ መልሱልኝ፡፡ አለበለዚያ ከዳኛ ላይ ከስሼ አስቀፈድዳችኋለሁ”
ሶስቱ ሰዎች፡ “በእውነት እኛ አላየነውም”
ሰውዬው በሰዎቹ አድራጎት ተናድዶ ከዳኛ ላይ ከሰሳቸው፡፡

ሶስቱ ሰዎች ከተከሰሱበት ችሎት ፊት ቀረቡ፡፡ ዳኛውም “እናንተ ግመሉን ለምን ሰረቃችሁት አላቸው?”
 ሶስቱ ሰዎች፡ “እኛ አልሰረቅነውም፡ ጭራሽ ግመሉን አላየነውም”
ዳኛው፡ “ታዲያ ሰውየው ግመሌን አይተውታል ነው የሚለው?”
ሶስቱ ሰዎች፡ “እኛ ስለግመሉ የተናገርነው በመንገድ ላይ ካየናቸው ምልክቶች ተነስተን ነው”
ዳኛው፤ “እስቲ ያያችኋቸውን ምልክቶች ንገሩን”

አንደኛው ሰውየ፡ “እኔ ግመሉ ጅራተ ቆራጣ ነው ያልኩት በመንገድ ላይ ካየሁት ፋንዲያ ተነስቼ ነው፡፡ በመንገድ ላይ ያየሁት ፋንዲያ በአንድ ቦታ ተከምሯል፡፡ ግመሉ ጅራት ቢኖረው ኖሮ በጅራቱ እየመታው ስለሚበታትነው በአንድ ቦታ አይከመርም ነበር፡፡ ስለዚህ ፋንዲያው በአንድ ቦታ የተከመረው ጅራት ስሌለው መሆን አለበት”

ሁለተኛው ሰውዬ፡ “እኔ “ግመሉ አንድ ዐይና ነው” ያልኩበት ምክንያት በግመሉ የተበላውን ዛፍ አይቼ ነው፡፡ ያየሁት ዛፍ በአንድ ጎኑ ብቻ ተበልቷል፡፡ የዛፉ ሌላኛው ክፍል ግን ምንም አልተነካም፡፡ ግመሉ ሁለት ዐይና ቢሆን ኖሮ ዛፉን በሁለቱም በኩል ይበላለት ነበር፡፡ አንድ ዐይና በመሆኑ ግን የዛፉን ሌላኛውን ክፍል ሳይነካው ሄዷል”

ሶስተኛው ሰውዬ፡ “እኔም ግመሉ ከባድ እቃ ተጭኖበታል ያልኩት የግመሉን ፋና አይቼ ነው፡፡ የግመሉ ፋና ወደ አሸዋው ውስጥ ሰርጉዶ ገብቷል፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት ግመሉ ከባድ እቃ የተጫነበት በመሆኑ ነው፡፡ ግመሉ ቀላል እቃ የተሸከመ ቢሆን ኖሮ የእግሩ ፋና ከአሸዋው ውስጥ ጠለቅ ብሎ አይገባም ነበር፡፡

   ዳኛው በሰዎቹ ብልህነትና አስተዋይነት ተገረመ፡፡ ከዚያም “በጣም አስገራሚ ሰዎች ናችሁ፡፡ እጅግ በጣም አስገራሚ ትምህርት ነው የሰጣችሁን፡፡ የማስተዋል ችሎታችሁ ያስደምማል፡፡ ስለዚህ እናንተ ከግመሉ ስርቆት ነጻ ናችሁ” በማለት አሰናበታቸው፡፡

===“ሰዋስው ተማር”==
አንድ የሰዋስው ተማሪ ውሃ ለመቅዳት ወደ ጉድጓድ ሄደ፡፡ ሆኖም በጥንቃቄ ጉድለት የተነሳ ተንሸራተተና ከጉድጓዱ ውስጥ ተደፋ፡፡ እዚያም ሆኖ ዋይታውን ሲለቀው አንድ መንገደኛ ሰማውና ሊረዳው መጣ፡፡
“ምን ሆንክ?”
“እንደምታየው ከዚህ ጉድጓድ ውስጥ ልሰጥም ነው፤ ቶሎ ገመድ አምጥተህ ካላወጣኸኝ መሞቴ ነው”
“እሺ ገመድ ልፈልግና ልምጣ፤ እስከዚያው ግን የጉድጓዱን ዳር ይዘህ ለመንሳፈፍ ብትሞክር ይሻላል”

መንገደኛው ይህንን ተናግሮ ሊሄድ ሲል ተማሪው አላስችል አለው፡፡ እናም “አንድ ጊዜ ቆየኝ እስቲ” በማለት መንገደኛውን ከመንገድ ጠራውና እንዲህ አለው፡፡ “ቅድም የተናገርከው ዐረፍተ ነገር የሰዋስው ደንብን የጠበቀ አይደለም፤ ስለዚህ ላስተካክልልህ ብዬ ነው የጠራሁህ”፡፡
መንገደኛው ይህንን ሲሰማ በጣም ተናደደ፡፡ ከጉድጓድ ውስጥ ለሚንቦጫረቀው ተማሪም እንዲህ አለው፡፡ “እንደዚያ ከሆነ ሰዋስው ተምሬ እስክመጣ ድረስ እዚሁ ጉድጓድ ውስጥ ብትቆየኝ ይሻላል”

===ነስሩዲን እና የዶሮ እንቁላል===

የሰመርቀንድ ከተማ ገዥ በነስሩዲን ቀልድና ተረብ ይበሽቅ ነበር፡፡ እናም “ይህንን መናጢ ጉድ እሰራውና ልክ አገባዋለሁ” በማለት ዛተ፡፡ አንድ ቀን የከተማውን ባላባቶች ለምሳ ግብዣ ከጠራቸው በኋላ “ወደ ግብዣው ስትመጡ እያንዳንዳችሁ አንዳንድ እንቁላል ይዛችሁ ኑ” በማለት በሚስጢር ላከባቸው፡፡ ነስሩዲንም ለግብዣው ተጠራ፡፡ ይሁን እንጂ “እንቁላል አምጡ” የሚለው ትዕዛዝ ለርሱ እንዲደርሰው አልተደረገም፡፡

የግብዣው ቀን ሲደርስ ሁሉም ታዳሚ በቦታው ተገኘ፡፡ ነስሩዲንም በቦታው ደርሶ በተመደበለት ስፍራ ተሰየመ፡፡ የምሳ ግብዣው ተጀመረና ሁሉም እንደፍላጎቱ መብላትና መጠጣት ጀመረ፡፡ በመሀሉ ግን ገዥው “እያንዳንዳችሁ አንዳንዳንድ እንቁላል ውለዱ” በማለት ነስሩዲን ያልጠበቀውን ትዕዛዝ ሰጠ፡፡ በስፍራው የነበሩት መኳንንት አንዳንድ እንቁላል ከኪሳቸው እያወጡ ከጠረጴዛቸው ላይ አስቀመጡ፡፡ ነስሩዲን ይህንን ሲያይ በጣም ተደናገጠ፡፡ በመሆኑም ቶሎ ብሎ እንደ አውራ ዶሮ “አኩኩሉ” እያለ ደጋግሞ ጮኸ፡፡ ሀገረ-ገዥው ገርሞት “ምን እያደረግክ ነው?” በማለት ጠየቀው፡፡ “እነዚህን ዶሮዎች ያስወለድኩት አውራ ዶሮ እኔ መሆኔን እንድታውቁ ብዬ ነው የጮኽኩት” በማለት መለሰለት፡፡ ለነስሩዲን አንዳች ክብር ያልነበረው ሀገረ ገዥ በብልጠቱ ተገርሞ በሳቅ ፍርስ አለ፡፡ ከዚያን ጀምሮ ነስሩዲንን ለማክበር ተገደደ፡፡

====አባትና ልጅ===

ነገሮች ሁሉ እጥፍ እየሆኑ የሚታዩት አንድ ልጅ ከአባቱ ጋር ይኖር ነበረ፡፡ ልጁ አንድን ነገር “ሁለት” እያለ ነው የሚቆጥረው፡፡ ሁለት ነገሮችም አራት ሆነው ነው የሚታዩት፡፡ ሶስት ነገሮች ደግሞ ስድስት ይሆኑበታል፡፡ አባት በልጁ ጸባይ ተቸገረ፡፡ እናም አንድ ቀን ጠራውና “ልጄ! አንዱ ነገር ሁለት የሚሆንብህ ለምንድነው?” በማለት ጠየቀው፡፡
ልጁ ግን “ተሳስተሃል” አለው፡፡ “እንደዚያ ቢሆን ኖሮማ ጨረቃዎች መች ሁለት ብቻ ይሆኑ ነበረ፤ አራት ጨረቃዎች ይሆኑ አልነበር እንዴ?” በማለት አባትዬውን የባሰ ግራ አጋባው፡፡
(የዘመናችን የኢኮኖሚ እድገት አልገባን ያለው ዘጋቢዎቹ ልክ እንደዚህ ልጅ ነገሮችን በእጥፍ ስለሚቆጥሩ ይሆናል)
------------------
ቸር እንሰንብት!
አፈንዲ ሙተቂ
መጋቢት 18/2005

Thursday, May 8, 2014

“ዳሪዮስ ሞዲ” እና ትዝታዎቹ



ጥንቅር፡ አፈንዲ ሙተቂ
-----
በቅድሚያ እድሜአቸው ከሃያ ዓመት በታች ለሆነ ወዳጆቻችን አጭር ማስተዋወቂያ እነሆ ብለናል፡፡
   
  “ዳሪዮስ ሞዲ” በኢትዮጵያ ታሪክ ከታዩ ባለግርማ ሞገስ የሬድዮ ጋዜጠኞች አንዱ ነው፡፡ ይህ ጋዜጠኛ በተለይ የሚታወሰው
ሀ/. ግንቦት 13/1983 ፕሬዚዳንት መንግሥቱ ኃይለ-ማሪያም ሀገር ጥለው መሄዳቸውን በገለጸበት ዜና
ለ/. ግንቦት 20/1983 ኢህአዴግ አዲስ አበባን ከተቆጣጠረ በኋላ ድምጹን ያሰማ የመጀመሪያው ጋዜጠኛ በመሆኑ እና በሌሎችም የሬድዮ ጣቢያው ታሪካዊ ኩነቶች ነው (ከርሱ በፊት አንድ ታጋይ “የዘመናት የህዝብ ብሶት የወለደው ጀግናው የኢህአዴግ ሰራዊት የአዲስ አበባን ሬድዮ ጣቢያ ለሰፊው ህዝብ ጥቅም ተቆጣጥሯል” እያለ ሲናገር ነበር)፡፡ በተጨማሪም በዘመነ ደርግ እና በኢህአዴግ ዘመን የመጀመሪያው ዓመት ከመንግሥት የሚተላለፉ መግለጫዎችንና አዋጆችን የሚያሰማው በአብዛኛው እርሱ ነበር፡፡

   ዳሪዮስ ሞዲ አሁን ድምጹ ጠፍቷል፡፡ ሆኖም በትዝታዎቹና በግል ህይወቱ ዙሪያ ከተለያዩ መጽሔቶች ጋር ቃለ-ምልልስ አድርጓል፡፡ እኔም ትዝታዎቹን እንደሚከተለው አጠናቅሬአለሁ፡፡
===== ዳሪዮስና የ“ቡሽቲ” ወሬ===
ዳሪዮስ አራት ኪሎ አንድ ካፍቴሪያ ውስጥ የገጠመውን እንዲህ ያጫውተናል፡፡
 
  “ቡና ቤቱ ውስጥ ቡና እየጠጣሁ ነው፡፡ ሁለት ሰዎች ከኔ ፈንጠር ብለው ተቀምጠዋል፡፡ ከአንደኛው ጋር በዓይን እንተዋወቃለን፡፡ አንደኛውን ግን አላውቀውም፡፡ ከኔ ጋር የማይተዋወቀው ሰዉዬ “የሬድዮውን ድምጽ ከፍ አድርጉት” አለ፡፡ ተደረገለት፡፡ በአጋጣሚ እኔ የሰራሁት ፕሮግራም እየተላለፈ ነበር፡፡ እርሱም በአውስትራሊያ የተካሄደውን የጽንስ ማሳደግ ፕሮግራም የሚመለከት ነበር፡፡ ይኸውም አንድን ወንድ ሆዱን ቀደው ጽንስ ይከቱበታል፡፡ ከዚያም ሆዱን ይሰፉታል፡፡ ጽንሱ እያደገ ሄደ፡፡ የሰውየውም ባህሪይ ጽንሱ ባደገ ቁጥር የሴት ባህሪይ እየመሰለ ይሄዳል፡፡ ይህንን ነበር ያቀረብኩት፡፡

  ሰውየው ይህንን ሲሰማ በመደነቅ “ከየት እንደሚያመጣው አይታወቅም፡፡ ትሰማዋለህ? ይሄ ቡሽቲ መሆን አለበት” አለ፡፡ ከርሱ ጋር የነበረው ሰውዬ (ከኔ ጋር በዐይን የሚተዋወቀው) ወሬውን እንዲያቆም ቢጠቅሰው አልሆነለትም፡፡ ጭራሽ ሰውዬው ወደኔ ዞሮ “አይመስልህም ወንድም?” አለኝ፡፡ እኔም “አዎ ልክ ነህ” አልኩት፡፡ “እንዴት ወንድ ልጅ ያረግዛል ብሎ ያወራል፡፡ አወቅሽ አወቅሽ ቢሏት መጽሐፍ አጠበች እንደሚባለው ነው፡፡ ሁለተኛ ይህንን ሰው አልሰማውም” አለና እንደገና ወደኔ ዞሮ “ይሄ ቡሽቲ አይደለም?” አለኝ፡፡ “ነው” አልኩት፡፡ በወቅቱ ከመቀበል በስተቀር ምንም መልስ የለኝም፡፡   
(አቢሲኒያ መጽሔት፡ ቅጽ 1፤ ቁጥር 2፤ የካቲት 1985)
=====ዳሪዮስ እና ግንቦት 13===
ግንቦት 13/1983፡፡ ከቀኑ 6፡00 ሰዓት፡፡ የኢትዮጵያ ድምጽ ብሔራዊ አገልግሎት (የአሁኑ የኢትዮጵያ ሬድዮ) ማንም ያልጠበቀውን ዜና አስተላለፈ፤ እንዲህ የሚል፡፡

   “ለረጅም ዓመታት በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ሲካሄድ የነበረው የርስ በርስ ጦርነት ያስከተለውን የኢትዮጵያዊያን ህይወት መጥፋትና ከኑሮ መፈናቀል ለማስቀረት በልዩ ልዩ መልክ ጥረት ሲደረግ ቆይቷል፡፡ ሆኖም ችግሩ አልተቃለለም፡፡ ይልቁንም ወደ ባሰ ደረጃ እየተሸጋገረ በመሄድ ላይ ይገኛል፡፡ ስለዚህ ደም መፋሰስ እንዲቆምና ሰላምም እንዲሰፍን በልዩ ልዩ ወገኖች የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ከስልጣን መውረዳቸው እንደሚበጅ የታመነበት ስለሆነ ይህንኑ በማመዛዘን ፕሬዚዳንት መንግሥቱ ኃይለማሪያም ከስልጣናቸው ወርደው ከኢትዮጵያ ውጪ ሄደዋል”

ዜናውን ያነበበው ድምጸ መረዋው ዳሪዮስ ሞዲ ነበር፡፡ ዳሪዮስ ከኢትኦጵ መጽሔት ጋር ባደረገው ቃለ-ምልልስ በጊዜው የነበረውን ሁኔታ እንደሚከተለው ገልጾታል፡፡

 ኢትኦጵ፡- ዳሪዮስ ያንን ዜና ስታነበው ፍርሃት አልተሰማህም?

 ዳሪዮስ፡ ለምን ትንሽ ሰፋ አድርጌ አልገልጽልህም? በወቅቱ የማስታወቂያ ሚኒስትር የነበሩት አቶ አብዱልሓፊዝ ዩሱፍ ጋዜጠኛ ጌታቸው ኃይለማሪያምን ወደ ቢሮአቸው ያስጠሩታል (ጌታቸው ያኔ የቅርብ አለቃዬ ነበረ)፡፡ ጌታቸው ከሚኒስትሩ ቢሮ ተመልሶ እንደመጣ “ቆይ ከዚህ እንዳትሄድ” አለኝ፡፡ “ለምን” ስለው “የሚነበብ ዜና አለ” አለኝ፡፡ “እኔ እኮ ተረኛ አይደለሁም” አልኩት፡፡ “አይ! አንተ ነህ የምታነበው አለኝ”፡፡ እና በዚያው አነበብኩት፡፡

 ኢትኦጵ፡ ዜናው ምን እንደሆነ አስቀድሞ አልተነገረህም?

 ዳሪዮስ፡ በፍጹም! እንኳንስ እኔ ጌታቸው ራሱ ያወቀ አልመሰለኝም፡፡ ብቻ በቃ “የሚነበብ ዜና አለ” ነው የተባልኩት፡፡ ስድስት ሰዓት ሲደርስ ስቱዲዮ ገባሁ፡፡ ያኔ ወረቀቱን ሰጡኝ፡፡ “ለሀገርና ለህዝብ ደህንነት ሲባል ከሀገር እንዲወጣ ተደርጓል” ይላል፡፡

ኢትኦጵ፡-አልደነገጥክም?

ዳሪዮስ፡ በጭራሽ! እንዲያውም እውነት ለመናገር ትልቅ ደስታ ነው የተሰማኝ፡፡ ልክ አንብቤ እንደጨረስኩ “አሁን ወደምትፈልግበት መሄድ ትችላለህ ተባልኩ”፡፡
(ኢትኦጵ መጽሔት፡ ቅጽ 3- ቁጥር 36፤ ግንቦት 1994)

====የዳሪዮስ ልጆች====
ለልጆችዎ ያወጡት ስም ምን ይመስላል? ቆንጆ የተባለውን ስም ወይንም የህይወቴን ገጠመኝ ይገልጽልኛል የሚለውን ስም መርጠው እንሚሰጧቸው ይታመናል፡፡ ዳሪዮስም ቆንጆ ያላቸውን ስሞች ለልጆቹ ሰጥቷል፡፡ ሆኖም የርሱ ምርጫ እኛ ከምናውቀው ወጣ ያለ ነው፡፡ ከኢትኦጵ መጽሔት ጋር ያደረገው ቃለምልልስ ሲታተም ብዙዎች ናቸው የተገረሙት፡፡ እስቲ ከቃለ-ምልልሱ ትንሽ ጨልፈን አብረን እንገረም፡፡

 ኢትኦጵ፡- ዳሪዮስ ለልጆችህ የምትሰጠው ስም አስገራሚ ነው ይባላል፡፡ የሰሙ ሰዎች ለማመን ያቅታል ነው የሚሉት፡፡
 ዳሪዮስ፡ ለምን ያቅታቸዋል?
 ኢትኦጵ፡ አስገራሚ ስለሆነ ነዋ!
ዳሪዮስ፡ ምን የሚገርም ነገር አለውና?
 ኢትኦጵ፡ እስቲ ለምሳሌ ከልጆህ ስሞች መካከል አንዱን ጥቀስልኝ?
 ዳሪዮስ፡ ቼጉቬራ
ኢትኦጵ፡ እሺ ሌላስ?
ዳሪዮስ፡ ትግል ነው::
ኢትኦጵ፡ የምርህን ነው ዳሪዮስ?
ዳሪዮስ፡ አዎና! ትግል ነው ዳሪዮስ::
ኢትኦጵ፡ ከሴቶቹ መካከል ለምሳሌ?
ዳሪዮስ፡ አምጸሸ ተነሺ!
ኢትኦጵ፡ እየቀለድክብኝ ነው?
ዳሪዮስ፡ ቀልድ አልወድም! “አምጸሸ ተነሺ ዳሪዮስ” ብዬሃለሁ፡፡
ኢትኦጵ፡ እና አሁን ይሄ እውነት የልደት ስማቸው ነው? ትምህርት ቤትም በዚሁ ነው የሚጠሩት?
ዳሪዮስ፡ ስማቸው እኮ ነው!
(ኢትኦጵ መጽሔት፡ ቅጽ 3- ቁጥር 36፤ ግንቦት 1994)
====ዳሪዮስ እና ሚኒስትሩ=====
   ዳሪዮስ ሞዲ በአንድ ምክትል ሚኒስትር ተጎድቶ ነበር፡፡ በስራ ላይ እያለ ሰላም ነሱት፡፡ በኋላ ላይ እኚሁ ሚኒስትር በዝውውር ወደ ሌላ ቢሮ ሲዛወሩ ዳሪዮስ በአስገራሚ መንገድ ተበቀላቸው፡፡ እንዲህ ያወጋናል፡፡

 ኢትኦጵ፡ ለምክትል ሚኒስትሩ መሸኛ ከሰራተኛው ገንዘብ ሲዋጣ አስር ሳንቲም ብለህ ሊስቱ ላይ ሞልተሃል ይባላል፡፡
 ዳሪዮስ፡ አይ ተሳስተሃል… አምስት ሳንቲም ነው ያልኩት፡፡ ግን እኮ ታዲያ ለበቀል አይደለም፡፡ እንዲያውም ከኔ በላይ የተጎዱ ብዙ ሰዎች ነበሩ፡፡ እነዚያ ሰዎች ከአቅማቸው በላይ አዋጥተዋል፡፡ ይህንን ሳይ ተናደድኩና አምስት ሳንቲም ብዬ ሞላሁ፡፡ “ቦቅቧቆች..ምን ያስፈራችኋል?” ለማለት ያህል ነው ያንን ያደረግኩት፡፡
ኢትኦጵ፡ ሚኒስትሩ ተናደው ቢሮህ ድረስ መጥተው ሳንቲሟን አፍንጫህ ላይ ወርውረው ሄዱ የተባለውስ?
ዳሪዮስ፡ ውሸት ነው፡፡ ምክንያቱም እኔ ሳንቲሟን ገቢ አላደረግኩም፡፡ አምስት ሳንቲም ብዬ ከስሩ ሌላ ነገር ጻፍኩበት፡፡
 ኢትኦጵ፡ ምን ብለህ?
ዳሪዮስ፡ ከደመወዜ ላይ የሚቆረጥ!!
(ኢትኦጵ መጽሔት፡ ቅጽ 3- ቁጥር 36፤ ግንቦት 1994)

==ዳሪዮስ እና ዓለም ነህ ዋሴ==
ዳሪዮስ በርካታ አድናቂዎችን አፍርቷል፡፡ ብዙዎች በርሱ ድምጽ ተማርከው የጋዜጠኝነቱን ዓለም ተቀላቅለዋል፡፡ ከነርሱም አንዱ ዓለም ነህ ዋሴ ነው፡፡ ዓለም ነህ ስለ ዳሪዮስ ሞዲ አስተያየቱን ሲሰጥ እንዲህ ብሎ ነበር፡፡

  “ዳሪዮስ ሞዲ ድምጹ ቀጭን ነው፡፡ ግን ሚስጢራዊ ነው፡፡ ማንኛውንም ሞገድ አሳብሮ መሄድ የሚችል ነው፡፡
    ዳሪዮስ ልክ እንደ ድምጹ ሚስጢራዊ ነው፡፡ ድብቅ ነው፡፡ ማህበራዊ ህይወት ውስጥ ያልክ እንደሆነ ዳሪዮስ የለበትም፡፡ ሽሽግ ነው፡፡
ዳሪዮስ አዋቂ ነው፡፡ በጣም ብዙ ነገሮችን ያውቃል፡፡ የራሱ ጨዋታና ቀልዶች አሉት፡፡ በተረፈ በአለባበሱም ሆነ በማህበራዊ ህይወቱ ይሄን ያህል የሚታወስ አይደለም፡፡ ዳሪዮስን የምታስታውሰው ለምሳሌ ዜና ተረኛ ከሆነ ከአንዲት አሮጌ ታይፕራይተር ፊት ለፊት ተቀምጦ እሳቷ ፊልተሩ ጋር የደረሰች ሲጋራ ከንፈሩ ላይ ለጉሞ የውጪ ዜናዎችን ሲተረጉምና ሲተይብ ነው፡፡
 ዳሪዮስ ከፍተኛ የትርጉም ችሎታ አለው፡፡ ቃላትን መፈብረክም ይችልበታል፡፡ ዛሬም ድረስ በሬድዮ የምንሰማቸው ሙያዊ ቃላት በርካቶቹ የዳሪዮስ ፍብረካ ውጤቶች ናቸው፡፡
(ኢትኦጵ መጽሔት፡ ቅጽ 1- ቁጥር 12፤ ግንቦት 1992)

በርግጥም ዳሪዮስ በማህበራዊ ህይወቱ ደካማ እንደሆነ አረጋግጧል፡፡ ይህንንም በአንደበቱ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፡፡
  “እኔ ፎርማል ነገር አልወድም፡፡ ለምሳሌ ሰርግ ተጠርቼ አልሄድም፡፡ ደስ ካለኝ ደግሞ ባትጠራኝ እንኳ በሰርግህ ላይ ልገኝ እችላለሁ፡፡”
(ኢትኦጵ መጽሔት፡ ቅጽ 3- ቁጥር 36፤ ግንቦት 1994)

       *****  *****  *****
   ዳሪዮስ ሞዲ በ1940 አዲስ አበባ ከተማ ራስ መኮንን ድልድይ አካባቢ ተወለደ፡፡ አባቱ የ“ፓርሲ” (የጥንታዊቷ ኢራን ደም ያላቸው  ህንዳዊያን) ተወላጅ ሲሆኑ ለልጃቸው ዳሪዮስ የሚለውን ስም የሰጡት “ዳሪዮስ” የሚባለውን ዝነኛ የፋርስ ንጉሠ ነገሥት ለማስታወስ ነው፡፡ በዜግነታቸው እንግሊዛዊ የነበሩት እኝህ ሰው ( የዳሪዮስ አባት) የቤተ መንግሥት ፎቶ አንሺ ነበሩ፡፡ በኋላ ላይም በሀገራችን የመጀመሪያውን ፎቶ ቤት አራት ኪሎ በሚገኘው የአርመን ቤተክርስቲያን አካባቢ ከፍተዋል፡፡ ዳሪዮስ ለአባቱ ብቸኛ ልጅ ነው፡፡ በስተርጅና የተገኘ ልጅ በመሆኑ አባቱ በጣም አቀማጥለው ነው ያሳደጉት፡፡ ኢትዮጵያዊት የነበረችው እናቱ ግን ከዳሪዮስ በኋላ ሶስት ልጆችን ወልዳለች፡፡
 
  ዳሪዮስ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ካጠናቀቀ በኋላ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገባ፡፡ ይሁን እንጂ ትምህርቱን ሳያጠናቅቅ ዩኒቨርሲቲውን ለመሰናበት ተገደደ፡፡ ለዚህም ያበቃው የተማሪዎች ማህበር ፕሬዚዳንትና የርሱ የቅርብ ጓደኛ የነበረው የጥላሁን ግዛው መገደል ነው፡፡
   ዳሪዮስ በ1964 በቀድሞው ብስራተ ወንጌል ሬድዮ ጣቢያ ተቀጠረ፡፡ አብዮቱ ሲመጣ ደግሞ ወደ ኢትዮጵያ ሬድዮ በመዛወር እስከ 1985 ድረስ አገለገለ፡፡ ከ1985 አጋማሽ በኋላ በኃላፊነት ወደ ኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ተወሰደ፡፡ በዚያ መስሪያ ቤት እስከ 1999 ካገለገለ በኋላ በጡረታ ከስራው ተሰናብቷል፡፡
 መልካም የጡረታና የእረፍት ዘመን ለዳሪዮስ ሞዲ!!
       *****  *****  *****
አፈንዲ ሙተቂ
ጥቅምት 22/2006

Sunday, April 6, 2014

የማይረሱ አባባሎች (ቆየት ካሉ ምንጮች የተገኙ)





ጥንቅር፡ አፈንዲ ሙተቂ
-----
 “ኢዴሐቅን ከለንደኑ ኮንፈረንስ ለማስቀረት የተናገሩት ምክንያት “ኢዴሐቅ ጦር የለውም” የሚል ነበር፤ ኢዴሐቅን ከሽግግር መንግሥቱ ምስረታ ኮንፍረንስ ሲያስቀሩ እንደምክንያት የተናገሩት ደግሞ “ኢዴሐቅ በጊዜያዊ መንግሥቱ ላይ ጦርነት አውጇል” የሚል ነው፡፡”
 አቶ መርሻ ዮሴፍ የኢዴሐቅ ሊቀመንበር እና የኢህአፓ ከፍተኛ የአመራር አባል (ኢትዮጵያን ሪቪው መጽሔት፣ እ.ኤ.አ. ጥቅምት 1992)
*****
“በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ግጭት የለም፡፡ ግጭት አለ ከተባለ በትምክህተኞች ጭንቅላት ውስጥ ነው”
አቶ መለስ ዜናዊ፣ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር እፎይታ መጽሔት “በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ግጭት ተፈጥሯል ይባላል” ብሎ በጠየቃቸው ጊዜ የተናገሩት (እፎይታ መጽሔት፤ ጥር 1990)
*****
“በእኛ ሀገር እውቀት ከስልጣን ይመነጫል”
 ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም፣ (የብራና ማህደር፣ ሚያዚያ 1985)
*****
“የኢትዮጵያን ባንዲራ እንኳንስ እኛ ግመሎቻችን ያውቋታል”
ሱልጣን ዓሊ ሚራህ፤ የአፋር ህዝብ መንፈሳዊ አባት (አፍሪካ ቀንድ መጽሔት፣ የካቲት 1985)
*****
“ከባድመ ወጣን ማለት ጸሀይ ጠፋች ማለት ነው፡፡ ጸሀይ ለዘላለሙ ጠለቀች ማለት ነው”
የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ (የኤርትራ ሬድዮ፣ ህዳር 1991)
*****
“የዘመናት የህዝብ ብሶት የወለደው ጀግናው የኢህአዴግ ሰራዊት ደርግ ሲጠቀምበት የነበረውን የአዲስ አበባን ሬድዮ ጣቢያ ለሰፊው ህዝብ ጥቅም ተቆጣጥሮታል”
በቅጽል ስሙ ላውንቸር በሚል የሚታወቀው የኢህአዴግ ታጋይ (የኢትዮጵያ ሬድዮ፣ ግንቦት 20/1983) 
*****
“የኢህአዴግን ልብ እንኳን ሰው እግዚአብሔርም አያውቀውም፤ ሳይንስም አልደረሰበትም”
ዶ/ር መረራ ጉዲና (ጦቢያ መጽሔት፤ ህዳር 1992)
*****
“ኢትዮጵያዊ ለመሆን መደራደር እንፈልጋለን”
አቶ ሌንጮ ለታ ፣ በወቅቱ የኦነግ ም/ሊቀመንበር (ሳሌም መጽሔት፣ ነሐሴ 1984)
*****
“የግንቦት ሀያው ድል የመጨረሻዋን ጥይት በአዲስ አበባ ላይ የተኮሱት የኢህአዴግ ታጋዮች ብቻ ሳይሆን የመጀመሪያዋን ጥይት በአሲምባ የተኮሱት የኢህአፓ ታጋዮች ጭምር ነው”
 አቶ ያሬድ ጥበቡ ፤ የኢህዴን መስራችና ሊቀመንበር የነበሩ (መስታወት መጽሔት ጥቅምት 1985)
*****
“ስዬ፣ ክንፈ እና መለስ በየተራው ወደኔ እየመጡ “እመን፤ አለበለዚያ ልጆችህን ፊትህ እንገድላቸዋለን” እያሉ ህሊናዬን ሲያስጨንቁት ምን ላድርግ?… ለልጆቼ ደህንነት ስል ያልሰራሁትን ሰራሁ ብዬ ከማመን በስተቀር ምንም ምርጫ አልነበረኝም”
     አቶ ታምራት ላይኔ፣ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር በተከሰሱበት የሙስና ወንጀል ፍርድ ቤት ቀርበው ከተናገሩት (ጎህ መጽሔት ሚያዚያ 1993)፣
*****
“የሆነ ነፋስ ነው የሰጣችሁ እንጂ ሰርታችሁ ያመጣችሁት ውጤት አይደለም፡፡ ህዝቡን አሳስታችሁ ነው ይህቺን ታክል ያገኛችሁት፡፡ ቢሆንም አሁንም ያሸነፍነው እኛ ነን”
  አቶ በረከት ስምኦን፣ በወቅቱ የማስታወቂያ ሚኒስትርና የኢህአዴግ ፕሮፓጋንዳ ኮሚቴ ኃላፊ የነበሩ፣ ተቃዋሚዎች በምርጫ-97 ያገኙትን ውጤት በማስመልከት ከተናገሩት (በበርካታ ፕሬሶች ላይ ታትሞ ነበር፣ ግንቦት 1997)
*****
“ኢህዴን (ብአዴን) የሕወሐት የአማርኛ ዲፓርትመንት ነው”
አቶ አብርሃም ያየህ (የብራና ማህደር፣ ሚያዚያ 1985)
*****
“እኛ ታሪክ ይቅርና ጦርነት መስራት እንችላለን”
በሽግግሩ ዘመን የመከላከያ ሚኒስትር የነበሩት አቶ ስዬ አብርሃ (አባባሉ በብዙ ጋዜጦችና መጽሔቶች ላይ ቢታይም አቶ ስዬ እንዲህ ያሉበትን አጋጣሚ በትክክል ለማወቅ አልቻልኩም)
*****
“የኦሮሞ ህዝብ ግንድ ነው፡፡ ቅርንጫፍ እንጂ ግንድ አይገነጠልም”
  አቶ ቡልቻ ደመቅሳ (ኢትኦጵ መጽሔት፤ መጋቢት 1996)
*****
“ያለምንም ማጋነን ለኢትዮጵያ ህዝብ ብዙ ነገር አድርገንለታል፡፡ የመሬት አዋጁን ያወጅነው እኛ ነን፡፡ ለሙስሊሙ ህዝብ የሃይማኖት በዓሉን በብሔራዊ በዓል ደረጃ አውጀንለታል፡፡ ለክርስቲያኑም ጥበቃ አድርገናል”
  የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ሻምበል ፍቅረ ሥላሴ ወግደረስ (ሳሌም መጽሔት፣ ጥር 1985)
*****
  “ኢትዮጵያ በታሪኳ ጦርነት አሸንፋ አታውቅም”
  አቶ ዳዊት ዮሐንስ ፣ የቀድሞ አፈ-ጉባኤ (ምኒልክ መጽሔት ፤  ታህሳስ 1992)
*****
 “ከእንግዲህ እግርህ ቢቆረጥስ ምንድነው? ማራቶን አትሮጥበት፡፡ አንተ በጊዜህ ለሀገርህ ሁሉንም አድርገሃል፡፡ ከአሁን በኋላ እግር  ብዙም ላያስፈልግህ ይችላል፡፡ ስለዚህ አንገትህን አትድፋ፡፡ ኮራ ነቃ በል”
ኮ/ል መንግሥቱ ኃይለ ማሪያም ጥላሁን ገሰሰ እግሩን ከተቆረጠ በኋላ ስልክ ደውለው ሲያነጋግሩት (ኢትኦጵ ጋዜጣ፤ የካቲት 1997)
*****
“ይህ ያለቀለት ጨዋታ ነው፡፡ በቃ! አንድ መንግስት አዲስ አበባ ታቆማለህ፡፡ አንድ መንግሥት በአስመራ ታቆማለህ፡፡ ይህንን አምነን መቀበል አለብን፡፡ የኛ ሰው ትልቁ ችግር እውነት አምኖ ለመቀበል አለመቻል እና የሚያምንበትን በግልጽ አለመናገር ነው፡፡ እኛ ግን የኤርትራ ጥያቄ በዚሁ መልኩ እንደሚፈታ ግልጽ ሆነን እንናገራለን”
አቶ ተፈራ ዋልዋ በዋሽንግተን ዲሲ ለተሰበሰቡ ኢትዮጵያዊያን (አባባሉ የተሰማው ኢህአዴግ ስልጣን ከመያዙ በፊት በአሜሪካ ድምጽ ሬድዮ በ1982 ባሰራጨው አንድ ዝግጅት ነው፡፡ እኔ እዚህ የጻፍኩት ግን ከኢትኦጵ መጽሔት የመስከረም 1997 እትም ወስጄው ነው)
*****