Thursday, May 8, 2014

“ዳሪዮስ ሞዲ” እና ትዝታዎቹ



ጥንቅር፡ አፈንዲ ሙተቂ
-----
በቅድሚያ እድሜአቸው ከሃያ ዓመት በታች ለሆነ ወዳጆቻችን አጭር ማስተዋወቂያ እነሆ ብለናል፡፡
   
  “ዳሪዮስ ሞዲ” በኢትዮጵያ ታሪክ ከታዩ ባለግርማ ሞገስ የሬድዮ ጋዜጠኞች አንዱ ነው፡፡ ይህ ጋዜጠኛ በተለይ የሚታወሰው
ሀ/. ግንቦት 13/1983 ፕሬዚዳንት መንግሥቱ ኃይለ-ማሪያም ሀገር ጥለው መሄዳቸውን በገለጸበት ዜና
ለ/. ግንቦት 20/1983 ኢህአዴግ አዲስ አበባን ከተቆጣጠረ በኋላ ድምጹን ያሰማ የመጀመሪያው ጋዜጠኛ በመሆኑ እና በሌሎችም የሬድዮ ጣቢያው ታሪካዊ ኩነቶች ነው (ከርሱ በፊት አንድ ታጋይ “የዘመናት የህዝብ ብሶት የወለደው ጀግናው የኢህአዴግ ሰራዊት የአዲስ አበባን ሬድዮ ጣቢያ ለሰፊው ህዝብ ጥቅም ተቆጣጥሯል” እያለ ሲናገር ነበር)፡፡ በተጨማሪም በዘመነ ደርግ እና በኢህአዴግ ዘመን የመጀመሪያው ዓመት ከመንግሥት የሚተላለፉ መግለጫዎችንና አዋጆችን የሚያሰማው በአብዛኛው እርሱ ነበር፡፡

   ዳሪዮስ ሞዲ አሁን ድምጹ ጠፍቷል፡፡ ሆኖም በትዝታዎቹና በግል ህይወቱ ዙሪያ ከተለያዩ መጽሔቶች ጋር ቃለ-ምልልስ አድርጓል፡፡ እኔም ትዝታዎቹን እንደሚከተለው አጠናቅሬአለሁ፡፡
===== ዳሪዮስና የ“ቡሽቲ” ወሬ===
ዳሪዮስ አራት ኪሎ አንድ ካፍቴሪያ ውስጥ የገጠመውን እንዲህ ያጫውተናል፡፡
 
  “ቡና ቤቱ ውስጥ ቡና እየጠጣሁ ነው፡፡ ሁለት ሰዎች ከኔ ፈንጠር ብለው ተቀምጠዋል፡፡ ከአንደኛው ጋር በዓይን እንተዋወቃለን፡፡ አንደኛውን ግን አላውቀውም፡፡ ከኔ ጋር የማይተዋወቀው ሰዉዬ “የሬድዮውን ድምጽ ከፍ አድርጉት” አለ፡፡ ተደረገለት፡፡ በአጋጣሚ እኔ የሰራሁት ፕሮግራም እየተላለፈ ነበር፡፡ እርሱም በአውስትራሊያ የተካሄደውን የጽንስ ማሳደግ ፕሮግራም የሚመለከት ነበር፡፡ ይኸውም አንድን ወንድ ሆዱን ቀደው ጽንስ ይከቱበታል፡፡ ከዚያም ሆዱን ይሰፉታል፡፡ ጽንሱ እያደገ ሄደ፡፡ የሰውየውም ባህሪይ ጽንሱ ባደገ ቁጥር የሴት ባህሪይ እየመሰለ ይሄዳል፡፡ ይህንን ነበር ያቀረብኩት፡፡

  ሰውየው ይህንን ሲሰማ በመደነቅ “ከየት እንደሚያመጣው አይታወቅም፡፡ ትሰማዋለህ? ይሄ ቡሽቲ መሆን አለበት” አለ፡፡ ከርሱ ጋር የነበረው ሰውዬ (ከኔ ጋር በዐይን የሚተዋወቀው) ወሬውን እንዲያቆም ቢጠቅሰው አልሆነለትም፡፡ ጭራሽ ሰውዬው ወደኔ ዞሮ “አይመስልህም ወንድም?” አለኝ፡፡ እኔም “አዎ ልክ ነህ” አልኩት፡፡ “እንዴት ወንድ ልጅ ያረግዛል ብሎ ያወራል፡፡ አወቅሽ አወቅሽ ቢሏት መጽሐፍ አጠበች እንደሚባለው ነው፡፡ ሁለተኛ ይህንን ሰው አልሰማውም” አለና እንደገና ወደኔ ዞሮ “ይሄ ቡሽቲ አይደለም?” አለኝ፡፡ “ነው” አልኩት፡፡ በወቅቱ ከመቀበል በስተቀር ምንም መልስ የለኝም፡፡   
(አቢሲኒያ መጽሔት፡ ቅጽ 1፤ ቁጥር 2፤ የካቲት 1985)
=====ዳሪዮስ እና ግንቦት 13===
ግንቦት 13/1983፡፡ ከቀኑ 6፡00 ሰዓት፡፡ የኢትዮጵያ ድምጽ ብሔራዊ አገልግሎት (የአሁኑ የኢትዮጵያ ሬድዮ) ማንም ያልጠበቀውን ዜና አስተላለፈ፤ እንዲህ የሚል፡፡

   “ለረጅም ዓመታት በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ሲካሄድ የነበረው የርስ በርስ ጦርነት ያስከተለውን የኢትዮጵያዊያን ህይወት መጥፋትና ከኑሮ መፈናቀል ለማስቀረት በልዩ ልዩ መልክ ጥረት ሲደረግ ቆይቷል፡፡ ሆኖም ችግሩ አልተቃለለም፡፡ ይልቁንም ወደ ባሰ ደረጃ እየተሸጋገረ በመሄድ ላይ ይገኛል፡፡ ስለዚህ ደም መፋሰስ እንዲቆምና ሰላምም እንዲሰፍን በልዩ ልዩ ወገኖች የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ከስልጣን መውረዳቸው እንደሚበጅ የታመነበት ስለሆነ ይህንኑ በማመዛዘን ፕሬዚዳንት መንግሥቱ ኃይለማሪያም ከስልጣናቸው ወርደው ከኢትዮጵያ ውጪ ሄደዋል”

ዜናውን ያነበበው ድምጸ መረዋው ዳሪዮስ ሞዲ ነበር፡፡ ዳሪዮስ ከኢትኦጵ መጽሔት ጋር ባደረገው ቃለ-ምልልስ በጊዜው የነበረውን ሁኔታ እንደሚከተለው ገልጾታል፡፡

 ኢትኦጵ፡- ዳሪዮስ ያንን ዜና ስታነበው ፍርሃት አልተሰማህም?

 ዳሪዮስ፡ ለምን ትንሽ ሰፋ አድርጌ አልገልጽልህም? በወቅቱ የማስታወቂያ ሚኒስትር የነበሩት አቶ አብዱልሓፊዝ ዩሱፍ ጋዜጠኛ ጌታቸው ኃይለማሪያምን ወደ ቢሮአቸው ያስጠሩታል (ጌታቸው ያኔ የቅርብ አለቃዬ ነበረ)፡፡ ጌታቸው ከሚኒስትሩ ቢሮ ተመልሶ እንደመጣ “ቆይ ከዚህ እንዳትሄድ” አለኝ፡፡ “ለምን” ስለው “የሚነበብ ዜና አለ” አለኝ፡፡ “እኔ እኮ ተረኛ አይደለሁም” አልኩት፡፡ “አይ! አንተ ነህ የምታነበው አለኝ”፡፡ እና በዚያው አነበብኩት፡፡

 ኢትኦጵ፡ ዜናው ምን እንደሆነ አስቀድሞ አልተነገረህም?

 ዳሪዮስ፡ በፍጹም! እንኳንስ እኔ ጌታቸው ራሱ ያወቀ አልመሰለኝም፡፡ ብቻ በቃ “የሚነበብ ዜና አለ” ነው የተባልኩት፡፡ ስድስት ሰዓት ሲደርስ ስቱዲዮ ገባሁ፡፡ ያኔ ወረቀቱን ሰጡኝ፡፡ “ለሀገርና ለህዝብ ደህንነት ሲባል ከሀገር እንዲወጣ ተደርጓል” ይላል፡፡

ኢትኦጵ፡-አልደነገጥክም?

ዳሪዮስ፡ በጭራሽ! እንዲያውም እውነት ለመናገር ትልቅ ደስታ ነው የተሰማኝ፡፡ ልክ አንብቤ እንደጨረስኩ “አሁን ወደምትፈልግበት መሄድ ትችላለህ ተባልኩ”፡፡
(ኢትኦጵ መጽሔት፡ ቅጽ 3- ቁጥር 36፤ ግንቦት 1994)

====የዳሪዮስ ልጆች====
ለልጆችዎ ያወጡት ስም ምን ይመስላል? ቆንጆ የተባለውን ስም ወይንም የህይወቴን ገጠመኝ ይገልጽልኛል የሚለውን ስም መርጠው እንሚሰጧቸው ይታመናል፡፡ ዳሪዮስም ቆንጆ ያላቸውን ስሞች ለልጆቹ ሰጥቷል፡፡ ሆኖም የርሱ ምርጫ እኛ ከምናውቀው ወጣ ያለ ነው፡፡ ከኢትኦጵ መጽሔት ጋር ያደረገው ቃለምልልስ ሲታተም ብዙዎች ናቸው የተገረሙት፡፡ እስቲ ከቃለ-ምልልሱ ትንሽ ጨልፈን አብረን እንገረም፡፡

 ኢትኦጵ፡- ዳሪዮስ ለልጆችህ የምትሰጠው ስም አስገራሚ ነው ይባላል፡፡ የሰሙ ሰዎች ለማመን ያቅታል ነው የሚሉት፡፡
 ዳሪዮስ፡ ለምን ያቅታቸዋል?
 ኢትኦጵ፡ አስገራሚ ስለሆነ ነዋ!
ዳሪዮስ፡ ምን የሚገርም ነገር አለውና?
 ኢትኦጵ፡ እስቲ ለምሳሌ ከልጆህ ስሞች መካከል አንዱን ጥቀስልኝ?
 ዳሪዮስ፡ ቼጉቬራ
ኢትኦጵ፡ እሺ ሌላስ?
ዳሪዮስ፡ ትግል ነው::
ኢትኦጵ፡ የምርህን ነው ዳሪዮስ?
ዳሪዮስ፡ አዎና! ትግል ነው ዳሪዮስ::
ኢትኦጵ፡ ከሴቶቹ መካከል ለምሳሌ?
ዳሪዮስ፡ አምጸሸ ተነሺ!
ኢትኦጵ፡ እየቀለድክብኝ ነው?
ዳሪዮስ፡ ቀልድ አልወድም! “አምጸሸ ተነሺ ዳሪዮስ” ብዬሃለሁ፡፡
ኢትኦጵ፡ እና አሁን ይሄ እውነት የልደት ስማቸው ነው? ትምህርት ቤትም በዚሁ ነው የሚጠሩት?
ዳሪዮስ፡ ስማቸው እኮ ነው!
(ኢትኦጵ መጽሔት፡ ቅጽ 3- ቁጥር 36፤ ግንቦት 1994)
====ዳሪዮስ እና ሚኒስትሩ=====
   ዳሪዮስ ሞዲ በአንድ ምክትል ሚኒስትር ተጎድቶ ነበር፡፡ በስራ ላይ እያለ ሰላም ነሱት፡፡ በኋላ ላይ እኚሁ ሚኒስትር በዝውውር ወደ ሌላ ቢሮ ሲዛወሩ ዳሪዮስ በአስገራሚ መንገድ ተበቀላቸው፡፡ እንዲህ ያወጋናል፡፡

 ኢትኦጵ፡ ለምክትል ሚኒስትሩ መሸኛ ከሰራተኛው ገንዘብ ሲዋጣ አስር ሳንቲም ብለህ ሊስቱ ላይ ሞልተሃል ይባላል፡፡
 ዳሪዮስ፡ አይ ተሳስተሃል… አምስት ሳንቲም ነው ያልኩት፡፡ ግን እኮ ታዲያ ለበቀል አይደለም፡፡ እንዲያውም ከኔ በላይ የተጎዱ ብዙ ሰዎች ነበሩ፡፡ እነዚያ ሰዎች ከአቅማቸው በላይ አዋጥተዋል፡፡ ይህንን ሳይ ተናደድኩና አምስት ሳንቲም ብዬ ሞላሁ፡፡ “ቦቅቧቆች..ምን ያስፈራችኋል?” ለማለት ያህል ነው ያንን ያደረግኩት፡፡
ኢትኦጵ፡ ሚኒስትሩ ተናደው ቢሮህ ድረስ መጥተው ሳንቲሟን አፍንጫህ ላይ ወርውረው ሄዱ የተባለውስ?
ዳሪዮስ፡ ውሸት ነው፡፡ ምክንያቱም እኔ ሳንቲሟን ገቢ አላደረግኩም፡፡ አምስት ሳንቲም ብዬ ከስሩ ሌላ ነገር ጻፍኩበት፡፡
 ኢትኦጵ፡ ምን ብለህ?
ዳሪዮስ፡ ከደመወዜ ላይ የሚቆረጥ!!
(ኢትኦጵ መጽሔት፡ ቅጽ 3- ቁጥር 36፤ ግንቦት 1994)

==ዳሪዮስ እና ዓለም ነህ ዋሴ==
ዳሪዮስ በርካታ አድናቂዎችን አፍርቷል፡፡ ብዙዎች በርሱ ድምጽ ተማርከው የጋዜጠኝነቱን ዓለም ተቀላቅለዋል፡፡ ከነርሱም አንዱ ዓለም ነህ ዋሴ ነው፡፡ ዓለም ነህ ስለ ዳሪዮስ ሞዲ አስተያየቱን ሲሰጥ እንዲህ ብሎ ነበር፡፡

  “ዳሪዮስ ሞዲ ድምጹ ቀጭን ነው፡፡ ግን ሚስጢራዊ ነው፡፡ ማንኛውንም ሞገድ አሳብሮ መሄድ የሚችል ነው፡፡
    ዳሪዮስ ልክ እንደ ድምጹ ሚስጢራዊ ነው፡፡ ድብቅ ነው፡፡ ማህበራዊ ህይወት ውስጥ ያልክ እንደሆነ ዳሪዮስ የለበትም፡፡ ሽሽግ ነው፡፡
ዳሪዮስ አዋቂ ነው፡፡ በጣም ብዙ ነገሮችን ያውቃል፡፡ የራሱ ጨዋታና ቀልዶች አሉት፡፡ በተረፈ በአለባበሱም ሆነ በማህበራዊ ህይወቱ ይሄን ያህል የሚታወስ አይደለም፡፡ ዳሪዮስን የምታስታውሰው ለምሳሌ ዜና ተረኛ ከሆነ ከአንዲት አሮጌ ታይፕራይተር ፊት ለፊት ተቀምጦ እሳቷ ፊልተሩ ጋር የደረሰች ሲጋራ ከንፈሩ ላይ ለጉሞ የውጪ ዜናዎችን ሲተረጉምና ሲተይብ ነው፡፡
 ዳሪዮስ ከፍተኛ የትርጉም ችሎታ አለው፡፡ ቃላትን መፈብረክም ይችልበታል፡፡ ዛሬም ድረስ በሬድዮ የምንሰማቸው ሙያዊ ቃላት በርካቶቹ የዳሪዮስ ፍብረካ ውጤቶች ናቸው፡፡
(ኢትኦጵ መጽሔት፡ ቅጽ 1- ቁጥር 12፤ ግንቦት 1992)

በርግጥም ዳሪዮስ በማህበራዊ ህይወቱ ደካማ እንደሆነ አረጋግጧል፡፡ ይህንንም በአንደበቱ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፡፡
  “እኔ ፎርማል ነገር አልወድም፡፡ ለምሳሌ ሰርግ ተጠርቼ አልሄድም፡፡ ደስ ካለኝ ደግሞ ባትጠራኝ እንኳ በሰርግህ ላይ ልገኝ እችላለሁ፡፡”
(ኢትኦጵ መጽሔት፡ ቅጽ 3- ቁጥር 36፤ ግንቦት 1994)

       *****  *****  *****
   ዳሪዮስ ሞዲ በ1940 አዲስ አበባ ከተማ ራስ መኮንን ድልድይ አካባቢ ተወለደ፡፡ አባቱ የ“ፓርሲ” (የጥንታዊቷ ኢራን ደም ያላቸው  ህንዳዊያን) ተወላጅ ሲሆኑ ለልጃቸው ዳሪዮስ የሚለውን ስም የሰጡት “ዳሪዮስ” የሚባለውን ዝነኛ የፋርስ ንጉሠ ነገሥት ለማስታወስ ነው፡፡ በዜግነታቸው እንግሊዛዊ የነበሩት እኝህ ሰው ( የዳሪዮስ አባት) የቤተ መንግሥት ፎቶ አንሺ ነበሩ፡፡ በኋላ ላይም በሀገራችን የመጀመሪያውን ፎቶ ቤት አራት ኪሎ በሚገኘው የአርመን ቤተክርስቲያን አካባቢ ከፍተዋል፡፡ ዳሪዮስ ለአባቱ ብቸኛ ልጅ ነው፡፡ በስተርጅና የተገኘ ልጅ በመሆኑ አባቱ በጣም አቀማጥለው ነው ያሳደጉት፡፡ ኢትዮጵያዊት የነበረችው እናቱ ግን ከዳሪዮስ በኋላ ሶስት ልጆችን ወልዳለች፡፡
 
  ዳሪዮስ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ካጠናቀቀ በኋላ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገባ፡፡ ይሁን እንጂ ትምህርቱን ሳያጠናቅቅ ዩኒቨርሲቲውን ለመሰናበት ተገደደ፡፡ ለዚህም ያበቃው የተማሪዎች ማህበር ፕሬዚዳንትና የርሱ የቅርብ ጓደኛ የነበረው የጥላሁን ግዛው መገደል ነው፡፡
   ዳሪዮስ በ1964 በቀድሞው ብስራተ ወንጌል ሬድዮ ጣቢያ ተቀጠረ፡፡ አብዮቱ ሲመጣ ደግሞ ወደ ኢትዮጵያ ሬድዮ በመዛወር እስከ 1985 ድረስ አገለገለ፡፡ ከ1985 አጋማሽ በኋላ በኃላፊነት ወደ ኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ተወሰደ፡፡ በዚያ መስሪያ ቤት እስከ 1999 ካገለገለ በኋላ በጡረታ ከስራው ተሰናብቷል፡፡
 መልካም የጡረታና የእረፍት ዘመን ለዳሪዮስ ሞዲ!!
       *****  *****  *****
አፈንዲ ሙተቂ
ጥቅምት 22/2006

No comments:

Post a Comment