Monday, September 26, 2022

 

ፉቱሕ አል-ሐበሻ

-----

ጸሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ

------

የአዳል ሱልጣኔትን ታሪክ ለማጥናት የሚፈልግ ተመራማሪ የኢብን ፈድሉላህ አል-ዑመሪ፣ የአቡ አብዱራሕማን ኢብን ኻልዱን፣ የተቂኡዲን አል-መቅሪዚ እና የሸምሱዲን አል-ሳኻዊ ጽሑፎችን ማንበብ ይጠበቅበታል፡፡ በአስራ ስድስተኛው ክፍለ ዘመን የነበረውን የሱልጣኔቱን ታሪክ ለማወቅ ካሻን ግን እነዚህ ምሁራን የደረሷቸው ጽሑፎች አይጠቅሙንም፤ ምክንያቱም ጸሐፍቱ ከተጠቀሰው ዘመን አስቀድሞ ሞተው ተቀብረዋልና! የሰለሞናዊ አፄዎች ዜና መዋዕሎችም የዘመኑን ኩነት ጥርት ባለ ሁኔታ አያስረዱንም። በዜና መዋዕሎቹ ውስጥ የተጻፉት ታሪኮች በጣም ቁንጽል ናቸውና!

ይሁንና እያንዳንዱ ዘመን የየራሱን ጸሐፊ ይዞ ይመጣል። ታሪክ መዝጋቢዎች በየዘመኑ ይነሳሉ። በመሆኑም ከአስራ ስድስተኛው ክፍለ ዘመን መግቢያ ወዲህ የነበረውን የትንቅንቁን አካሄድ የሚዘግብ ታላቅ ድርሰት ከሌላ አቅጣጫ በመጣ ጸሐፊ ተበርክቶልናል። ይህም ድርሰት ፉቱሑል ሐበሻ ይባላል።

ፉቱሑል ሐበሻ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ልዩ ስፍራ ከሚሰጣቸው ጥቂት የታሪክ ሰነዶች አንዱ ነው፡፡ ይህ መጽሐፍ በተለይም በአስራ ስድስተኛው ክፍለ ዘመን የመጀመሪያ አጋማሽ በአፍሪቃ ቀንድ አካባቢ የነበረውን የህዝቦች አሰፋፈር፣ የቋንቋና የማህበረሰቦች ስብጥር፣ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ፣ ባህልና የአኗኗር ዘይቤ፣ የተፈጥሮ ክስተቶች፣ ዓለም አቀፍ ግንኙነቶች፣ የቴክኖሎጂ ደረጃ ወዘተ... አብጠርጥሮ ያስረዳል፡፡ ታዋቂው ኢትዮጵያዊ የታሪክ ፕሮፌሰር መርዕድ ወልደ-አረጋይ ስለዚህ መጽሐፍ ምስክርነታቸውን ሲሰጡ እንዲህ ብለዋል፡፡

“Futuh Al Habasha is indispensable for the identification of many of the provinces where for centuries lowland pastoralists and nomads clashed with highland agriculturalists”

(Merid Wolde-Aregay: 1972: 18)

ፉቱሑል ሐበሻን በእንግሊዝኛ የተረጎሙት ፖል ስቴንሃውስ እና ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት ደግሞ ደራሲው መጽሐፉን የጻፈበትን መንገድ (methodology) ካብራሩ በኋላ እንዲህ የሚል ምስክርነት ሰጥተዋል፡፡

"The author of “Futuh” thus able to present a largely balanced report of the minutes of events, as well as detailed and historically invaluable descriptions of the country through which the army of Imam Ahmed was passed"

(P. Stenhouse and R. Pankhurst: 2003: pp-xxii)

-----

የፉቱሕ አል-ሐበሻ ደራሲ ሺሃቡዲን አሕመድ ኢብን ዐብዱልቃዲር ወይም በማዕረግ ስሙ ዐረብ ፈቂህ ይባላል። የዚህ ሰው ትውልድ በደቡብ ዐረቢያ የሚገኘው የጂዛን ሀገረ-ግዛት ነው። ይህ ጸሐፊ ወደፊት የምናወሳው ኢማም አሕመድ ኢብራሂም አል-ጛዚ ያደረጋቸውን ዘመቻዎች እግር በእግር እየተከተለ ይተርካል፡፡

ደራሲው በአጻጻፉ ኢብን ጀሪር አል-ጠበሪ እና ጀላሉዲን አስ-ሱዩጢ፣ ወይንም በዚህ መጽሐፍ ደጋግሜ ከጠቀስኳቸው አል-ዑመሪ እና አል-መቅሪዚን ከመሳሰሉት ዝነኛ የዐረብ ታሪከኞች (historians) ጋር እንደማይስተካከል በግልጽ መረዳት ይቻላል፡፡ በተጨማሪም ደራሲው ከዚህ መጽሐፍ ውጪ ሌላ ድርሰት መጻፉ በግልጽ አይታወቅም፡፡ ሆኖም ይህ ብቸኛ ድርሰቱ የሀገራችንን ታሪክ ለመገንዘብ ያለው ጠቀሜታ በሌሎች የዐረብ ደራሲያን ከተጻፉት ድርሰቶች ሁሉ ይበልጣል፡፡

በየትኛውም ወገን ሆኖ (በአድናቆትም ሆነ በማጥላላት) በዚያ ዘመን የተካሄደውን ጦርነት የሚጽፍ ሰው እንደ ቀዳሚ ማጣቀሻ የሚጠቀምበት መጽሐፍ ፉቱሑል ሐበሻ ነው። ለምሳሌ አቶ ተክለ ጻድቅ መኩሪያ የግራኝ አሕመድ ወረራ የተሰኘውን ታዋቂ መጽሐፋቸውን ሲጽፉ ቀዳሚ የመረጃ ምንጭ አድርገው የተጠቀሙት ፉቱሑል ሐበሻ ነው፡፡ ዶክተር ላጵሶ ድሌቦም የሱልጣኔቱን ታሪክ ሲጽፉ ዋነኛ ማጠቀሻቸው “ፉቱሕ አል-ሐበሻ” ነበር፡፡ የዛሬ አስራ አምስት ዓመት ገደማ ስለኢማም አሕመድ ኢብራሂም የጻፉት አቶ ተሾመ ብርሃኑ ከማልም የመጀመሪያ ደረጃ ማጣቀሻ ያደረጉት ፉቱሑል ሐበሻ ነው። እኔም ስለአዳል ሱልጣኔት ታሪክ ስጽፍ ከሌሎች ማጣቀሻዎች ሁሉ ያስቀደምኩት "ፉቱሑል ሐበሻ" ነው። ስለኢማም አሕመድ እና የአዳል ሱልጣኔት ታሪክ የጻፉ ፈረንጆችም እንዲሁ የመጀመሪያ ዋቢ የሚያደርጉት እርሱን ነው።

-----

ፉቱሑል ሐበሻ በሁሉም ዘንድ ተመራጭ ያደረገው ምን መሰላችሁ? ጸሐፊው ያየውን ነገር አይደብቅም። ቤት ሲቃጠል እገሌ ነው ያቃጠለው ብሎ ይጽፋል፡፡ ንብረት ሲዘረፍም እገሌ ነው የወሰደው በማለት ያስቀምጣል። በሌላ ጎኑ ደግሞ ለአዳሉ መሪ ያለውን ፍቅርና አድናቆትም አይሸሽግም፡፡ ጀግንነቱን በግጥም ያወድሳል። በዚህ ረገድ መጽሐፉን ወደ ፈረንሳይኛ የተረጎመው እውቁ ምሁር ኔሬ ባሴ ስለደራሲው ሲናገር እንዲህ ብሏል፡፡

የዚህ መፅሐፍ ባለቤት አብዛኛውን ጦርነት የተመለከተ በመሆኑ የተለየ ሆኖ ተገኘ፡፡ ድርጊቶችን በመተረክ ረገድ እጅግ ጠንቃቃ ነበር፡፡ ክርስቲያን ጸሐፍትም እርሱ ካሰፈራቸው ታሪኮች ጋር ተመሳሳይ ትረካዎችን አስፍረዋል

(ፉቱሕ አል-ሐበሽ፣ ቅጽ-1 ገጽ 10)

ደራሲው መጽሐፉን የጻፈበት ዘመን በውል አይታወቅም፡፡ ይሁንና መጽሐፉ ኢማም አሕመድ ኢብራሂም ከሞተ ከጥቂት ከዓመታት በኋላ እንደተጻፈ ከሚከተለው አንቀጽ መረዳት ይቻላል፡፡

ፈርሽሐም ዲን ከድል በኋላ የሊጋያ ገዥ የነበረና ከኢማሙ መሞት በኋላ በአፄው ዘንድ ሆኖ በሙስሊምነቱ የጸና፣ ከአሚር ኑር ኢብን ወዚር ሙጃሂድ ጋራ በመሆን ወደ ሙስሊሞች ሀገር ሀረር በመሄድ በዚያው የሞተ ነው

(ፉቱሕ አል-ሐበሽ፣ ቅጽ-1 ገጽ 64)

በዚህ አንቀጽ ውስጥ የተጠቀሰው አሚር ኑር ሙጃሂድ ኢማሙ ከሞተ ከአስር ዓመታት በኋላ ስልጣን የያዘ የአዳል መሪ ነው፡፡ 1559 አፄ ገላውዴዎስን በመግጠም ካሸነፈው በኋላ ገድሎታል፡፡ ፈርሸሐም ዲን ከኢማም አሕመድ ታዋቂ የጦር መሪዎች አንዱ ሲሆን ኢማሙ ሲገደል በአፄው ተማርኮ በቤተ መንግሥቱ ይኖር ነበር፡፡ አሚር ኑር 1559 አፄ ገላውዲዎስን ከገደለ በኋላ ግን ከርሱ ጋር ሆኖ ወደ ሀረር ተመልሷል፡፡ በዚህም መሠረት መጽሐፉ የተጻፈው 1560ዎቹ እስከ 1580ዎቹ ባለው ዘመን ነው ቢባል ያስኬዳል፡፡

በመጽሐፉ ውስጥ በስም የተጠቀሱትን በርካታ ከተሞችና አውራጃዎች በዘመናችን ከምናውቃቸው ስያሜዎች ጋር ማዛመዱ በጣም ያስቸግራል፡፡ ቢሆንም እንደ ሀረር፣ ዘይላ፣ ሸገራህ (ሸገር) ጉራጌ፣ አዋሽ፣ ወቢ (ዋቢ ሸበሌ) ባሊ (ባሌ) ሀዲያ፣ ኢፋት (ይፋት) ሻርካህ (ሺርካ) ዳሞት፣ ሐማሴን፣ ትግራይ፣ ሲረ (ሽረ)፣ አበርገለ፣ ሐይቅ፣ በጌምድር፣ አክሱም፣ ሳራዊ (ሰራዬ) ጎጃም፣ ዐምሐራ፣ ደምቢያ፣ ዳህላክ የመሳሰሉት ከነስማቸው ይገኛሉ፡፡

------

ፉቱሑል ሐበሻ በጣሊያንኛ፣ በፈረንሳይኛ፣ በሀረሪ፣ በአማርኛ፣ በእንግሊዝኛ እና በሶማሊኛ ቋንቋዎች ተተርጉሟል (እኔም በአፋን ኦሮሞ ልተረጉመው ሙከራ እያደረግኩ ነው)፡፡ ደራሲው በመጽሐፉ ማብቂያ ላይ ይህ የፉቱሑል ሐበሻ አንደኛ መጽሐፍ የተዘጋጀው የአላህ ባሪያ እና የምህረቱ ከጃይ ከሆነው ከጂዛን ተወላጅ (ጂዛኒ) ሺሃቡዲን አሕመድ ቢን ዐብዱልቃዲር ቢን ሳሊም ቢን ዑሥማን ነው የሚል ዐረፍተ ነገር አስፍሯል፡፡ በዚህም የተነሳ ብዙዎች መጽሐፉ ሁለተኛ ክፍል እንዳለው ያምናሉ፡፡

ዝነኛው ሀገር አሳሽ ሰር ሪቻርድ በርተንም የሀረሩ አሚር የፉቱሑል ሐበሻ አንደኛው ክፍል ብቻ እንደነበረውና ሁለተኛው ክፍል በአል-ሙኻ ወይም ሁዴይዳ (ሁለቱም የየመን ከተሞች ናቸው) ሊገኝ እንደሚችል ጽፎ ነበር። መጽሐፉን ወደ ፈረንሳይኛ የተረጎመው ሬኔ ባሴ ግን ደራሲው ሁለተኛውን ክፍል ሳይጽፈው እንደሞተ ነው የሚያምነው፡፡

ፉቱሑል ሐበሻ ደራሲ በአብዛኛው የሚተርከው በዐይኑ ያየውንና በራሱ ያነበበውን ቢሆንም ከርሱ በፊት የነበረውን የአዳል ሱልጣኔት ታሪክ ከሽማግሌዎችና ከታላላቅ ምሁራን ጠይቆ በመረዳት በመጽሐፉ ውስጥ አካትቷል። በአፄ ልብነ ድንግል በኩል ያለውን እውነታ ሲጽፍ ደግሞ ከአጼው ጦር የተያዙ ምርኮኞች፣ ከአጼ ልብነ ድንግል ወገን ኮልለው ወደ አዳል ቤተ መንግሥት የመጡ ሀገር አስተዳዳሪዎችና የጦር መኮንኖች፣ ኢማሙ በውጊያ በያዛቸው አካባቢ የሚኖሩ ህዝቦችንና ሌሎችንም እየጠየቀ ከእነርሱ የሰማቸውን መረጃዎች ጽፎልናል፡፡ ከነዚህ መረጃዎች መካከል አንዳንዶቹ በሌሎች ምንጮች ውስጥ በጭራሽ አይገኙም። በዚህም የተነሳ የመጽሐፉ አስፈላጊነት እጥፍ ድርብ ሆኖ እስከ ዘመናችን ድረስ ዘልቋል።

-------

(ምንጭ፡ አፈንዲ ሙተቂ፡ አዳል-ስመ ገናናው ሱልጣኔት እና የኢማም አሕመድ ኢብራሂም አል-ጋዚ ዘመቻዎች፡ 2009 ገጽ 186-189)

ፎቶ፡ እስከ አሁን ከተገኙት የፉቱሕ አል-ሐበሻ ጥንታዊ ቅጂዎች የአንዱ የፊት ሽፋን (በሳዑዲ ዐረቢያው ንጉሥ ሳዑድ ዩኒቨርሲቲ ሙዚየም ውስጥ የሚገኝ)

 

No comments:

Post a Comment