አፈንዲ ሙተቂ
-----------
-----------
“ሀረር ጌይ” የተሰኘው መጽሐፌ ለመታሰቢያነት
ከተሰጣቸው ስብዕናዎች አንዱ ኢድሪስ ሻህ መሆኑን ከዚህ ቀደም አውግቼአችኋለሁ፡፡ ኢድሪስ ሻህ በኔ ህይወት ውስጥ ያለውንም ቦታ
በመጽሐፉ ውስጥ ገልጫለሁ፡፡ በአማርኛ “ተረበኛው ነስሩዲን” ተብሎ የተተረጎመው መጽሐፍ ደራሲም እርሱ እንደሆነም ተናግሬአለሁ፡፡
በዚህም ግድግዳ ላይ የኢድሪስን የህይወት ታሪክ በአጭሩ ጽፌላችሁ ነበር፡፡ ስለዚህ በዛሬው ፅሁፍ በነዚህ ጉዳዮች ላይ ምንም የምላችሁ
ነገር የለም፡፡ ከዚያ ይልቅ ከኢድሪስ መጻሕፍት ያገኘኋቸውን ምርጥ ጨዋታዎች አጋራችኋለሁ (የመጀመሪያዎቹን ሁለት ወጎች ከዚህ በፊት
ጽፌአቸው የነበረ ቢሆንም ላላነበቡት ብደግማቸው ጥሩ ይመስለኛል)፡፡
== ሶስቱ ልጆችና ዓሊ ኢብን አቡ-ጧሊብ ===
ሶስት ልጆች የነበሩት አንድ የዐረቢያ ሰው ነበር።
ይህ ሰው በህይወቱ መጨረሻ አካባቢ ልጆቹን ጠርቶ እንዲህ አላቸው።
“ልጆቼ ሆይ! በዚህ ምድር ላይ ስኖር የተገነዘብኩት
ትልቁ ነገር የዕውቀት አስፈላጊነት ነው። ያለ ዕውቀት የሚሄድ ሰው በጭለማ እንደሚጓዝ በቅሎ ይደናበራል። ንግግሩም ሆነ ስራው አያምርለትም።
ስለዚህ አዋቂና ታዋቂ እንድትሆኑልኝ እሻለሁ። ነገር ግን መምህራችሁን በጥንቃቄ መምረጥ አለባችሁ። ለዚህም ይረዳችሁ ዘንድ እነኝህን
17 ግመሎች ትቼላችኋለሁ። ታዲያ ግመሎቹን የምትከፋፈሉት በሚከተለው ቀመር መሰረት ይሁን።
• የመጀመሪያው ልጄ የግመሎቹን 1/2ኛ ይውሰድ።
• ሁለተኛው ልጄ 1/3ኛ ያህሉን ይውሰድ።
• ሶስተኛው ልጄ 1/9ኛ ያህሉን ይውሰድ።
አባታቸው ይህንን ከተናዘዘ በኋላ አረፈ። ልጆቹም
ግመሎቻቸውን እየነዱ በእርሱ የተነገራቸውን ዓይነት መምህር መፈለግ ጀመሩ። በየከተማው ወዳሉ አዋቂዎች እየቀረቡ አባታቸው በሰጣቸው
ስሌት መሰረት ግመሎቻቸውን እንዲያካፍሉአቸው ጠየቁ። ነገር ግን አንድም ሰው ስሌቱን መፍታት አልቻለም። ሌሎች በርካታ አዋቂዎችንም
አማከሩ። ግን ሒሳቡን አውቃለሁ የሚል ሰው ጠፋ።
በመጨረሻም አንደኛው ልጅ “ለምን ጥያቄውን ኸሊፋ
ዓሊ ቢን አቡ ጣሊብ ዘንድ አናቀርበውም? ከቻሉ ለራሳቸው ይፈቱታል። ካልቻሉም አንድ መላ ይመቱልናል” የሚል ሀሳብ አቀረበ። የቀሩት
ሁለቱ ልጆች በነገሩ ተስማሙ። በዚሁ መሰረት ሶስቱም ልጆች ወደ ኸሊፋ ዓሊ አቢ ጣሊብ (ረ.ዐ.) ዘንድ ሄዱና ጥያቄውን አቀረቡ።
ኸሊፋው ትንሽ ካሰበ በኋላ እንዲህ የሚል ምላሽ ሰጣቸው።
“አስራ ሰባቱን ግመሎች በአባታችሁ ቀመር መሰረት
ባከፋፍላችሁ ውጤቱ በክፍልፋይ (fraction) የሚገለጽ ይሆናል። እንደዚያ ከሆነ ግመሎቹን መቆራረጥ ሊኖርብኝ ነው ማለት ነው።
ስለዚህ እንዲያ እንዳይሆን የራሴን አንድ ግመል ልጨምርበትና የግመሎቹ ብዛት 18 ይሁን። ይህ ከሆነ ዘንዳ የአባታችሁ ቀመር የሚቀጥለውን
ውጤት ያስገኛል።
• ታላቁ ልጅ ከጠቅላላው 1/2ኛ ያግኝ በተባለው መሰረት ዘጠኝ ግመሎች ይደርሱታል።
• ሁለተኛው ልጅ 1/3ኛ ያግኝ በተባለው መሰረት ስድስት ግመሎች ይደርሱታል።
• ሶስተኛው ልጅ 1/9ኛ ያግኝ በተባለው መሰረት ሁለት ግመሎች ይደርሱታል።
• ሶስታችሁ ያገኛችኋቸውን ግመሎች በአንድ ላይ ስንደምር (9+6+2) ውጤቱ አስራ ሰባት ይሆናል።
• ከአስራ ስምንቱ አንድ ግመል ብቻ ይቀራል አይደል? እርሱ ደግሞ የራሴ በመሆኑ ወደኔ ይመለሳል።”
ብልሁ ዓሊ ቢን አቢ ጣሊብ ሒሳቡን በዚህ አስገራሚ
መንገድ ፈታው። ልጆቹም “አባታችን የጠቆመን መምህር ይህ ነው” በማለት እስከ መጨረሻው ድረስ ተማሪዎቹ ሆነው ዘለቁ።
===መርከበኛውና መምህሩ===
አንድ የሰዋስው መምህር ራቅ ወዳለ ስፍራ ለመሄድ ጀልባ ይከራያል። ለመርከበኛው
ሒሳቡን ከከፈለ በኋላም መርከበኛው ጀልባይቱን አስነስቶ ጉዞ ይጀመራል። ጥቂት ጊዜ እንደ ተጓዙ መምህሩ ወሬ ለመጀመር ያህል “ሰዋስው
ተምረሃል?” በማለት ይጠይቃል። መርከበኛውም “አይ አልተማርኩም” በማለት ይመልሳል። በዚህን ጊዜም መምህሩ “አይ ጉድ! ሰዋስው
ሳትማር ምን ልትረባ ነው ታዲያ? ወንድሜ ግማሽ ህይወትህን አጥተሃል” ይላል። መርከበኛው ይህንን ሲሰማ በጣም ይበሽቃል። ቢሆንም
ስሜቱን ተቆጣጥሮ ጀልባዋን መንዳቱን ይቀጥላል።
ሁለቱ ሰዎች ከባህሩ መሀል ሲደርሱ ከየት መጣህ
የማይሉት ሀይለኛ ማዕበል ጀልባይቱን ከወዲያ ወዲህ ያላጋት ጀመር። መርከበኛው በሚችለው ሁሉ ጀልባዋን ከመስጠም ሊያድናት ሞከረ።
ቢሆንም አልተሳካለትም። በዚህን ጊዜም ወደ መምህሩ ዞሮ “መምህር! ለመሆኑ ዋና ትችላለህ” በማለት ጠየቀው። መምህሩም እንደማይችል
መለሰለት። ይሄኔ መርከበኛው “ አይ መምህር! ምንም ላደርግልህ አልችልም። ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ሙሉ ህይወትህን ልታጣ ነው”
አለው። (የዚህ ወግ መልዕክት “ብድር በምድር ነውና ባለህ ነገር አትኩራራ” የሚል ነው)።
==የግመሉ ወግ==
ሶስት ባልንጀራሞች ወደ ሩቅ ሀገር ጉዞ ጀመሩ፡፡ የመንገዱን አጋማሽ ከሄዱ
በኋላ የግመል ፋንዲያ ታያቸው፡፡ አንደኛው ሰውዬ “ይህንን ፋንዲያ የለቀቀው ግመል ጅራተ-ቆራጣ ነው” አለ፡፡ ሰዎቹ እንደገና ጉዞአቸውን
ቀጠሉ፡፡ ጥቂት ከተጓዙ በኋላም ምሳ መብላት አሰኛቸውና ከአንድ ዛፍ ስር አረፉ፡፡ እዚያ ሳሉም የቡድኑ ሁለተኛ ሰው ወደላይ አንጋጦ
ካየ በኋላ “ከዚህ ዛፍ የበላው ግመል አንድ ዐይና ነው” በማለት ተናገረ፡፡
ሰዎቹ ምሳቸውን
ካጠናቀቁ በኋላ እንደገና መጓዛቸውን ቀጠሉ፡፡ በመንገዳቸው ላይም ግመል የሄደበትን ፋና አዩ፡፡ በዚህን ጊዜም የቡድኑ ሶስተኛ ሰው
“ይህንን ዳራ (ፋና) በአሸዋው ላይ ያሳረፈው ግመል ከባድ እቃ ተጭኖበታል” በማለት ተናገረ፡፡ ከጥቂት ቆይታ በኋላም “ግመሌ ጠፍቶብኛል”
ከሚል ሰው ጋር ተገጣጠሙ፡፡
አንደኛው ሰውዬ: “ግመልህ ጅራተ-ቆራጣ ነው?”
ባለ ግመል፡ “አዎን”
ሁለተኛው ሰውዬ፡ “ግመልህ አንድ ዐይና ነው?”
ባለ ግመል፡ “አዎን”
ሶስተኛው ሰው፡ “ግመልህ ከባድ እቃ ተጭኖበታል?”
ባለ ግመል፡ “አዎን”
ሶስቱም በአንድነት፡ “ግመልህን አላየነውም፣ ሂድና ፈልገው ወንድም”
ባለ ግመል፡ “እንዴ ምልክቱን አንድ በአንድ እየነገራችሁኝ ሂድና ፈልገው ስትሉኝ
አታፍሩም? ግመሌን ስርቃችሁታልና ቶሎ መልሱልኝ፡፡ አለበለዚያ ከዳኛ ላይ ከስሼ አስቀፈድዳችኋለሁ”
ሶስቱ ሰዎች፡ “በእውነት እኛ አላየነውም”
ሰውዬው በሰዎቹ አድራጎት ተናድዶ ከዳኛ ላይ ከሰሳቸው፡፡
ሶስቱ ሰዎች ከተከሰሱበት ችሎት ፊት ቀረቡ፡፡ ዳኛውም “እናንተ ግመሉን ለምን
ሰረቃችሁት አላቸው?”
ሶስቱ ሰዎች፡
“እኛ አልሰረቅነውም፡ ጭራሽ ግመሉን አላየነውም”
ዳኛው፡ “ታዲያ ሰውየው ግመሌን አይተውታል ነው የሚለው?”
ሶስቱ ሰዎች፡ “እኛ ስለግመሉ የተናገርነው በመንገድ ላይ ካየናቸው ምልክቶች
ተነስተን ነው”
ዳኛው፤ “እስቲ ያያችኋቸውን ምልክቶች ንገሩን”
አንደኛው ሰውየ፡ “እኔ ግመሉ ጅራተ ቆራጣ ነው ያልኩት በመንገድ ላይ ካየሁት
ፋንዲያ ተነስቼ ነው፡፡ በመንገድ ላይ ያየሁት ፋንዲያ በአንድ ቦታ ተከምሯል፡፡ ግመሉ ጅራት ቢኖረው ኖሮ በጅራቱ እየመታው ስለሚበታትነው
በአንድ ቦታ አይከመርም ነበር፡፡ ስለዚህ ፋንዲያው በአንድ ቦታ የተከመረው ጅራት ስሌለው መሆን አለበት”
ሁለተኛው ሰውዬ፡ “እኔ “ግመሉ አንድ ዐይና ነው” ያልኩበት ምክንያት በግመሉ
የተበላውን ዛፍ አይቼ ነው፡፡ ያየሁት ዛፍ በአንድ ጎኑ ብቻ ተበልቷል፡፡ የዛፉ ሌላኛው ክፍል ግን ምንም አልተነካም፡፡ ግመሉ ሁለት
ዐይና ቢሆን ኖሮ ዛፉን በሁለቱም በኩል ይበላለት ነበር፡፡ አንድ ዐይና በመሆኑ ግን የዛፉን ሌላኛውን ክፍል ሳይነካው ሄዷል”
ሶስተኛው ሰውዬ፡ “እኔም ግመሉ ከባድ እቃ ተጭኖበታል ያልኩት የግመሉን ፋና
አይቼ ነው፡፡ የግመሉ ፋና ወደ አሸዋው ውስጥ ሰርጉዶ ገብቷል፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት ግመሉ ከባድ እቃ የተጫነበት በመሆኑ
ነው፡፡ ግመሉ ቀላል እቃ የተሸከመ ቢሆን ኖሮ የእግሩ ፋና ከአሸዋው ውስጥ ጠለቅ ብሎ አይገባም ነበር፡፡
ዳኛው በሰዎቹ
ብልህነትና አስተዋይነት ተገረመ፡፡ ከዚያም “በጣም አስገራሚ ሰዎች ናችሁ፡፡ እጅግ በጣም አስገራሚ ትምህርት ነው የሰጣችሁን፡፡
የማስተዋል ችሎታችሁ ያስደምማል፡፡ ስለዚህ እናንተ ከግመሉ ስርቆት ነጻ ናችሁ” በማለት አሰናበታቸው፡፡
===“ሰዋስው ተማር”==
አንድ የሰዋስው ተማሪ ውሃ ለመቅዳት ወደ ጉድጓድ ሄደ፡፡ ሆኖም በጥንቃቄ ጉድለት
የተነሳ ተንሸራተተና ከጉድጓዱ ውስጥ ተደፋ፡፡ እዚያም ሆኖ ዋይታውን ሲለቀው አንድ መንገደኛ ሰማውና ሊረዳው መጣ፡፡
“ምን ሆንክ?”
“እንደምታየው ከዚህ ጉድጓድ ውስጥ ልሰጥም ነው፤ ቶሎ ገመድ አምጥተህ ካላወጣኸኝ
መሞቴ ነው”
“እሺ ገመድ ልፈልግና ልምጣ፤ እስከዚያው ግን የጉድጓዱን ዳር ይዘህ ለመንሳፈፍ
ብትሞክር ይሻላል”
መንገደኛው ይህንን ተናግሮ ሊሄድ ሲል ተማሪው አላስችል አለው፡፡ እናም “አንድ
ጊዜ ቆየኝ እስቲ” በማለት መንገደኛውን ከመንገድ ጠራውና እንዲህ አለው፡፡ “ቅድም የተናገርከው ዐረፍተ ነገር የሰዋስው ደንብን
የጠበቀ አይደለም፤ ስለዚህ ላስተካክልልህ ብዬ ነው የጠራሁህ”፡፡
መንገደኛው ይህንን ሲሰማ በጣም ተናደደ፡፡ ከጉድጓድ ውስጥ ለሚንቦጫረቀው ተማሪም
እንዲህ አለው፡፡ “እንደዚያ ከሆነ ሰዋስው ተምሬ እስክመጣ ድረስ እዚሁ ጉድጓድ ውስጥ ብትቆየኝ ይሻላል”
===ነስሩዲን እና የዶሮ እንቁላል===
የሰመርቀንድ ከተማ ገዥ በነስሩዲን ቀልድና ተረብ ይበሽቅ ነበር፡፡ እናም
“ይህንን መናጢ ጉድ እሰራውና ልክ አገባዋለሁ” በማለት ዛተ፡፡ አንድ ቀን የከተማውን ባላባቶች ለምሳ ግብዣ ከጠራቸው በኋላ “ወደ
ግብዣው ስትመጡ እያንዳንዳችሁ አንዳንድ እንቁላል ይዛችሁ ኑ” በማለት በሚስጢር ላከባቸው፡፡ ነስሩዲንም ለግብዣው ተጠራ፡፡ ይሁን
እንጂ “እንቁላል አምጡ” የሚለው ትዕዛዝ ለርሱ እንዲደርሰው አልተደረገም፡፡
የግብዣው ቀን ሲደርስ ሁሉም ታዳሚ በቦታው ተገኘ፡፡ ነስሩዲንም በቦታው ደርሶ
በተመደበለት ስፍራ ተሰየመ፡፡ የምሳ ግብዣው ተጀመረና ሁሉም እንደፍላጎቱ መብላትና መጠጣት ጀመረ፡፡ በመሀሉ ግን ገዥው “እያንዳንዳችሁ
አንዳንዳንድ እንቁላል ውለዱ” በማለት ነስሩዲን ያልጠበቀውን ትዕዛዝ ሰጠ፡፡ በስፍራው የነበሩት መኳንንት አንዳንድ እንቁላል ከኪሳቸው
እያወጡ ከጠረጴዛቸው ላይ አስቀመጡ፡፡ ነስሩዲን ይህንን ሲያይ በጣም ተደናገጠ፡፡ በመሆኑም ቶሎ ብሎ እንደ አውራ ዶሮ “አኩኩሉ”
እያለ ደጋግሞ ጮኸ፡፡ ሀገረ-ገዥው ገርሞት “ምን እያደረግክ ነው?” በማለት ጠየቀው፡፡ “እነዚህን ዶሮዎች ያስወለድኩት አውራ ዶሮ
እኔ መሆኔን እንድታውቁ ብዬ ነው የጮኽኩት” በማለት መለሰለት፡፡ ለነስሩዲን አንዳች ክብር ያልነበረው ሀገረ ገዥ በብልጠቱ ተገርሞ
በሳቅ ፍርስ አለ፡፡ ከዚያን ጀምሮ ነስሩዲንን ለማክበር ተገደደ፡፡
====አባትና ልጅ===
ነገሮች ሁሉ እጥፍ እየሆኑ የሚታዩት አንድ ልጅ ከአባቱ ጋር ይኖር ነበረ፡፡
ልጁ አንድን ነገር “ሁለት” እያለ ነው የሚቆጥረው፡፡ ሁለት ነገሮችም አራት ሆነው ነው የሚታዩት፡፡ ሶስት ነገሮች ደግሞ ስድስት
ይሆኑበታል፡፡ አባት በልጁ ጸባይ ተቸገረ፡፡ እናም አንድ ቀን ጠራውና “ልጄ! አንዱ ነገር ሁለት የሚሆንብህ ለምንድነው?” በማለት
ጠየቀው፡፡
ልጁ ግን “ተሳስተሃል” አለው፡፡ “እንደዚያ ቢሆን ኖሮማ ጨረቃዎች መች ሁለት
ብቻ ይሆኑ ነበረ፤ አራት ጨረቃዎች ይሆኑ አልነበር እንዴ?” በማለት አባትዬውን የባሰ ግራ አጋባው፡፡
(የዘመናችን የኢኮኖሚ እድገት አልገባን ያለው ዘጋቢዎቹ ልክ እንደዚህ ልጅ
ነገሮችን በእጥፍ ስለሚቆጥሩ ይሆናል)
------------------
ቸር እንሰንብት!
አፈንዲ ሙተቂ
መጋቢት 18/2005